ዳግማዊ ጉዱ ካሣ
ሁለተኛው ቤተ መንግሥት አዲስ አበባ ውስጥ ሊገነባ እንደሆነ እየሰማን ነው፡፡ በርግጥ ከሰማን ቆይተናል፡፡ ግን ወሬውም ሆነ የሥራው ጅማሮ ረገብ ብሎ ወደመረሳትም አዘንብሎ ነበር፡፡ ሰሞኑን በተሰራጩ የሶሻል ሚዲያ ዘገባዎች ግን ያ የአሜሪካውያንን የዋይት ሐውስ ቤተ መንግሥት የሚያስንቅ የሽመልስ አብዲሣ የኦሮምያው ቤተ መንግሥት በወንድሙ አቢይ አህመድ ቤተ መንግሥት ትይዩ ደምበል ሲቲ ሴንተር አካባቢ በልዩ ሁኔታ ሊገነባ እንደሆነ ተገልፆኣል፡፡
ሰባሪንና ተሰባሪን አንድዬ ይወቀውና “በሰበሩን ቦታ ሰበርናቸው” የሚለው የሽመልስ አብዲሣ የዘወትር ንግግር በገሃድ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ ሰባት ዓመቱን ደፍኖ ስምንተኛውን ይዟል፡፡ በነዚህ ዓመታት አማራ ከአዲስ አበባ እንዲወገድ የተደረገው ጥረት በእጅጉ የሠመረ ለመሆኑ የአዲስ አበባ የቀድሞ ሠፈሮችን ተዘዋውሮ መመልከት በቂ ነው፡፡ በዓለም ታይቶ በማይታወቅ ጭካኔ ያለአንዳች ማስጠንቀቂያም በሁለትና ሦስት ቀናት ማስጠንቀቂያም አንድን ሠፈር ሙሉ በሙሉ በማፍረስ ዜጎችን ለጅብ መዳረግ የኦነግ/ኦህዲድ የሠርክ መዝናኛ ከሆነ ቆዬ፡፡ አሁን ከተማዋ ኦና ሆናለች፡፡ በኮሪደር ሰበብ ያልጠፋ መንደር፣ ያልተፈናቀለ አማራ፣ ያልተሰደደና በረንዳ አዳሪ ያልሆነ ዜጋ የለም፡፡ በኢኮኖሚ ደህና የነበሩ ተቋቁመውት ሊሆን ይችላል እንጂ አብዛኛው ጨርቁን ጥሎ ከማበድና ወደሚቀርበው ዛፍ ሄዶ ራሱን ከማንጠልጠል ጀምሮ ብዙ ችግር ደርሶበታል፡፡ ይህን ሁሉ ጉድ እያሳለፈ የሚገኘው የአዲስ አበባ ነዋሪ አማራ ከዚህ አስከፊ ኦሮሙማዊ ግፍና በደል ራሱን ነፃ ለማውጣት ሲሞክር አይታይም፡፡ አማራንና ኢትዮጵያን ለመታደግ በሰሜን ምዕራብ በኩል የተጀመረው ትግልም ጠላት ባሸመቀበት ሤራና ተንኮል እንዲሁም ወቅቱን ባልጠበቀ የሥልጣን ሽሚያ እርስ በርሱ እየተባላ ባለበት መርገጡን ሳይመርጥ አልቀረም፤ “ራስ ሳይጠና ጉተና” ይሉት ነገር ገጥሞን ለአንዲት ወንበር ሲባል ገና ከጫካ የሚራወጥባት በዛና ተቸገርን፡፡ አንድ ሰው ወይም አንድ ተቋም የነፃነት ቀንዲል እንዲሆን ከፈለገ በመሠረቱ ከሦስት ነገሮች ራሱን ማጽዳት ይኖርበታል፡፡ እነሱም በቲቤታውያን መነኮሣት ዘንድ የመርኅ ያህል በአፅንዖት እንደሚሰበኩት ሥልጣን፣ ገንዘብና ወሲብ ናቸው፡፡ የእነዚህን ፍላጎቶች ያልተቆጣጠረ ሰው እንኳንስ ሌላውን ነፃ ሊያወጣ ራሱም የጨለማው ዓለም ባርያ ነው፤ በነዚህ ሰባት ዓመታት እንኳን ስንቱን አየን፡፡ እናም ከጠላት ጋር እየተሞዳሞደ በሚያገኘው ገንዘብ በከተሞች ውስጥ በወኪሎቹ ወይም በቤተሰቦቹ ስም ንግድ እያጧጧፈና ሕንጻ እየገነባ ለታይታ ያህል ግን በበረሃ ጥቁር ክላሽ አንግቶ የፋኖ መሪ በመምሰል በሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ ከሚያቅራራ አስመሳይ ይሁዲ ምንም አንጠብቅም፡፡ ከምንጠብቀው ግን የምንጠብቀውን እንጠብቃለን፤ እርሱም በቅርቡ እውን ይሆናል፡፡ አትጠራጠር፡፡
ወደተነሳሁበት ልመለስ፡፡ አንድ ከተማ የሁለት መንግሥታት ንብረት ሊሆን አይችልም፡፡ የአንድ መንግሥት መሪዎች የሁለት መንግሥታት መሪዎች ሊሆኑም አይችሉም፡፡ ይህ ዓይነቱ ትንግርታዊ የታሪክ አጋጣሚ የተከሰተው ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ነው፡፡ አዳነች አበቤና ሽመልስ አብዲሣ በተሰነቀረባቸው የአማራ ጥላቻና ቂም በቀል አንድ ይሁኑ እንጂ የሚመሯቸው መንግሥታት ለየቅል ናቸው፡፡ ይህን ባለማወቃቸውና የሚያሰቃያቸው አማራ ላይ ያላቸው ጥላቻ አንጎላቸውን ዜሮ ስላደረገባቸው አሁን የሚያደርጉትን አጥተዋል፤ የአቢይም ተልእኮ ኢትዮጵያን ማጥፋት በመሆኑ እነዚህን ወገኖች “ሃይ!” ይላቸዋል ተብሎ አይታሰብም፡፡ እንዲያውም ለምን ዘገያችሁ በሚል ሊቆጣቸውም ይችላል፡፡ እስካሁን ያልጠፋነው የያዘ ይዞን እንጂ እንደነአቢይ ቢሆን ኖሮ አንድም አማራና አንድም በኢትዮጵያዊነት የሚያምን ሰው በሕይወት ባልኖረ፡፡
በመሠረቱ ቤተ መንግሥት ለምን ይገነባሉ አልልም፡፡ እንመራዋለን የሚሉት ሕዝብ በርሀብ አለንጋ እየተገረፈ፣ እንመራዋለን የሚሉት ክልል በጦርነት እየወደመ፣ እንመራዋለን የሚሉት አካባቢ መሠረታዊ ልማቶችን አጥቶ አንድ ክሊኒክ ፍለጋ ሕዝቡ ብዙ ኪሎ ሜትሮችን በእግርና በጋማ ከብት እየተጓዘ፣ ሕዝባችን የሚሉት ወገን በኑሮ ውድነት እየተጠበሰ፣ ወዘተ. ይህን የሚነገርለትን የመሰለ ቤተ መንግሥት መገንባት ለራሣቸው ኅሊና ካልቀፈፋቸው እኔን እምብዝም ዕንቅልፍ አይነሣኝም፡፡ እርግጥ ነው – እነዚህ ደናቁርት በትምህርት የተበደሉ፣ በዕውቀት ዕጥረት የጠወለጉ፣ ከጥበብ ማዕድ እጅጉን የራቁ፣ በጥቅሉ ከሰውነት ተራ የወጡና ከእንስሳትም ያነሱ መሆናቸውን መረዳት አላቃተኝም፡፡ የገጠመን ማንም ያልገጠመው ነው፡፡
እኔን ያሳሰበኝ ይህን በ6.5 ሄክታር መሬት ላይ ሊገነቡ ነው የተባለውን ቤተ መንግሥት ለመገንባት የሚፈናቀለው ሕዝብና ቦታውን በማጽዳት ሂደት የሚወድመው የሀገርና የሕዝብ ሀብት ነው፡፡ እንደሰማሁት በ99 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ የሚገነባው ይህ ቤተ መንግሥት ከ30 በላይ ትላልቅ የንግድና የአገልግሎት መስጫ ሕንጻዎችን ያስፈርሳል፡፡ ይህ ብቻውን ከሀገሪቱ የገንዘብ አቅም አኳያ ሲታይ ትልቅ ወጪ ነው – ማፍረሻውና ለካሣ የሚሰጥ ገንዘብም ካለ፡፡ እነዚህ ጊዜ የሰጣቸው ጉዶች ማድረግ ስለቻሉ ብቻ የሚያደርጉት ይህ ዓይነቱ ጥፋት በየትም ዓለም የታዬ አይመስለኝም፡፡ በቀን አንዴ መቅመስ ህልሙ በሆነ ማኅበረሰብ ውስጥ እንዲህ ያለ መቀናጣትም ለምን ዓይነት ትዝብት እንደሚዳርገን መገመት አይከብድም፡፡ ቤተ መንግሥቱን ለመገንባት ሌላ ቦታም ጠፍቶ አይደለም፡፡ ግን እልህ ነው፡፡ ባልጠፋ ቦታ ዜጎችን እያስጨነቁና ያለበቂ ካሣ እያፈናቀሉ ማስለቀስ ከውስኪና ከጮማ ቀጥሎ የሚያስደስታቸው ስለመሆኑ በተግባር አረጋግጠውልናል፡፡ እልህ ጩቤ ያስውጣል መባሉ እንግዲህ ትክክል ነው፡፡ እነዚህ ጉዶች የሚውጡትን ጩቤ ደግሞ ዕድሜ የሰጠው ያየዋል፡፡ ሰነጣጥቆ የሚጥል ጩቤ እየመጣባቸው ነው፡፡
ኢትዮጵያ ትድናለች፡፡ መዳኗን የሚዘባበት አይኑር፤ ስህተት ነው፡፡ ስትድን ግን እንደምንጊዜውም ሁሉ ሁልአቀፍ የሆነ ብዙ ኪሣራ አለው፡፡ ለዚህ ደግሞ ከአፄው መንግሥት ጀምሮ ደርግንም ሕወሓትንም ዘወር ብለን ማጤን እንችላለን፡፡ ዕብዱ ማሙሽ አቢይ “ለሽህ ዓመታት ብትዋጉ አታሸንፉኝም” ማለቱን እንደቀልድ እንቁጠረውና፣ በተወሰኑ ድሎች ራሣቸውን በደስታ አስክረው አራት ኪሎን በቅርቡና በቀላሉ እንቆጣጠራለን ያሉትን ፋኖዎችም እንርሳቸውና የአንድ ክፋት መጨረሻ 99.9 በመቶው ኪሣራና ውድመት መሆኑን ቢያንስ ከታሪክ እንማር፡፡ የኢትዮጵያ ችግር ደግሞ በኃይል ሊፈታ እንደማይችል ሌላው ሁሉ ቀርቶ ያለፉት ሰባት ዓመታት ብቻ በቂ ናቸው፤ ብዙና ብዙ ተሞከረ ግን አበቅቴው ገና ሆነና በእስካሁኑ ሁኔታ የሚፈለገው ስኬት እውን አልሆነም፡፡ ለቅጣት የመጣ አቢይን መሰል ጭራቅ በምን ሊወገድ እንደሚችል በጊዜ ሂደት አሁንና ዛሬ ካልገባን ተታለናል፡፡ የኢትዮጵያ ችግር እጅግ ውስብስብ መሆኑን የምትረዳው ደግሞ እሥርንና ድብደባን ጨምሮ ስንትና ስንት መከራ የተቀበለ የነፃነት አርበኛ ቆራጥ ታጋይ የነበረ ሰው ባልገመትከውና ባልጠረጠርከው ሁኔታ ወደጠላትህ ጎራ ገብቶ ያንተን የባርነት ዘመንና የዕልቂት ዐዋጅ ከሚያራምዱ ሰዎች ጋር ማበሩን ስትገነዘብ ነው፤ ዕዝ ነዋ! ዕዝን ማምለጥ በፍጹም አይቻልም፤ ከላይ የታዘዘ ቅጣት መምጫ አቅጣጫም 360 ዲግሪ ነው – አይበልብህ እንጂ የቅርብ ጓደኛህን ጨምሮ ከሚስትህና ከልጅህም ሊሰነዘር ይችላል – በኛም ላይ እየደረሰ ያለው ይህ ክፉ ዕጣ ነው፤ ደግነቱ ይህም ያልፋል፡፡ ስለዚህ የችግራችን ምንጭ ምሥጢራዊና የአእምሮን ጤንነት እስከመፈታተን ከደረሰ መፍትሔውም የረቀቀና ከፈጣሪም ጋር ግንኙነት ያለው መሆኑ ግልጽ ነውና በርትቶ መጸለይ ይኖርብናል ማለት ነው፡፡ አቢይ አህመድ ለቅጣት መምጣቱንና የተሰጠውን የጥፋት ፓኬጅ በትክክል መተግበር ያለበት መሆኑን ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ እያደረሰብን ያለውን መቅሰፍታዊ ውርጅብኝ አያውቅም ማለት አይደለም – በደምብ ያውቃል፡፡ የተላከው ከማን እንደሆነም ከአንደበቱ ከማይነጥለው 666 ቁጥር መገንዘብ አይከብድም፤ የጫማውም ሶል ይህንኑ ይመሰክራል፡፡ ስለዚህ ከእርሱ ምንም ነገር መጠበቅ ወይም እርሱ ጋር ድርድርና ንግግር ለማድረግ መከጀል ከጅልነትም ባለፈ ወፈፌነት ነው፡፡ ከዚህ የአንድ ሰው መንግሥት ጋር ስለድርድር ሲወራ በተለይም አማሮች ሲያወሩ በጣም ይገርመኛል፤ “ድርድር” የሚለውን ቃል ራሱ ትርጉም ማሳጣት ነው፡፡ አቢይ የመጣበትን ተልእኮ ሳይሸራረፍ በአግባቡ መፈጸም ስላለበት እየዋሸም እየቀጠፈም፣ ያቺን የማትቀር የመጨረሻ ሰዓት መጠበቅ አለበት፡፡ ሰዓቱም አልቃለች፡፡ ፊሽካውን የያዘው መልኣክ ተሳንፎ እንጂ የዜጎች ዕንባና ደም ጽርሃ አርያም ደርሶ መልስ ሊሰጠን ተቃርበናል፡፡ ይሄ ግሳንግስ የከርሣሞች፣ የዘረኞችና የባንዳዎች ሥርዓት ሊወድቅ ዘምሟል፡፡
ሀገራችን በብዙ ነገር መበደሏን እናውቃለን፡፡ በፖለቲካው ብቻ ሣይሆን በሃይማኖቱም ረገድ ሁነኛ መሪዎች የሏትም፡፡ ሁሉም ማለት በሚቻል ደረጃ ከጠፋው የቤተ መንግሥት ኃይል ጋራ ተሞዳሟጅ ነው፡፡ ጭንቅላት ከአናት ወርዶ ሆድ ውስጥ ከተወሸቀና ኅሊና ለገንዘብ ከተሸጠ ምክንያታዊነትና ሃይማኖት ገደል ገቡ፡፡ በኛ ሀገር የሆነው ይሄው ነው፡፡ በሌላ በኩል ከአምባገነን መሪዎች መገለጫ አንዱና ትልቁ ትምህርትን ማጥፋት እንደመሆኑ በአሁኑ ወቅት ሀገራችንን የወረራት ማይምና በፌክ የትምህርት ማስረጃ የተሞላ ቢሮክራሲ ነው፡፡ እንደማይምነት አገር አጥፊ የለም፡፡ ማይም ሲበዛ አውቶቡስ ውስጥና ቡና ላይ እንኳን ተግባብተህ መለያየት አትችልም፡፡ የሰዎች ንግግር እንትን እንትን እያለህ መግባባት ይሣንህና በሰዎች የሃሣብ መቀጨጭ ምክንያት ተስፋ ትቆርጣለህ፡፡ በዚህ ሁኔታ ባለች ሀገር ውስጥ እውነትና ፍትኅ ይኖራሉ ተብሎ ደግሞ አይጠበቅም፡፡ የትም ግባ የትም በእጅህ እንጂ በእግርህ ሄደህ ጉዳይህ ዕልባት አያገኝም፡፡ በዚያ ላይ እውነተኛው የወር ገቢህ ከሦስት ቀን በዘለለ ስለማያኖርህ ሙስና ውስጥ የመዘፈቅ ዕድልህ የመኖርና ያለመኖር ያህል ነውና እያዘንክም ቢሆን ትገባበታለህ፡፡ ከዚህ አንጻር ሀገራችን በኪነ ጥበቡ አድራ ትውላለች እንጂ አለች ማለት አንችልም፡፡ የጨረባ ተዝካር በለው፡፡ ግን ይገርማል – ይመሻል ይነጋል፡፡ ይህ ተፈጥሯዊ ሥርዓት ብቻ አልተዛነፈም፡፡ ሌላው ከፍ ሲል እንዳልኩህ ተከድኖ ይብሰል፡፡
ይሄ ቤተ መንግሥት ግን ባዶ ቦታ ተፈልጎ እንዲሠራ ቢደረግ ካልተጠበቀ ወጪ ያድናልና እነዚህን ድፍን ቅሎች የምትቀርቧቸው ወገኖች ብትነግሯቸው መልካም ነው፡፡ ለመጪው መንግሥታችን አድካሚ ሸክም እንዳናቆዬው የምትችሉ ወገኖች የምትችሉትን ያህል ጥረት አድርጉ፡፡ እነሱ ስለታወሩ ዛሬን እንጂ ትናንትንም ሆነ ነገን የማየት ችሎታም ሆነ ትግስት የላቸውም፡፡ ከነሱ ጋር እንደሰው መቆጠሬ እጅጉን እያንገበገበኝ ሊያሳብደኝ ነውና ወገኖቼ እባካችሁን ለኔም ጸልዩልኝ ፡፡ ክርስቲያኖች መልካም የህማማት ሣምንትና መልካም የትንሣኤ በዓል ይሁንላችሁ፤ ይሁንልን፡፡ አምላክ በቶሎ ይጎብኘን፡፡
አሜን፡፡