January 12, 2025
48 mins read

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

abiy and his parlamaኤፍሬም ማዴቦ ([email protected])

ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን ያቀረቡለትን ሁሉ እንደሚበላ የቤት ውስጥ እንስሳ፣ የህግ አስፈጻሚው አካል ያቀረበለትን የህግ ረቂቅ ምንም ይሁን ምን እንዳለ የሚያፀድቅ የእንቅልፋሞች ፓርላማ ነው። ፓርላማው ከህወሓት/ኢህአዴግ ዘመን ጀምሮ የህግ አስፈጻሚው አካል የሚልክለትን የህግ ረቂቅ ምንም አይነት የረባ ማሻሻያ ሳያደርግበት እንዳለ በማጽደቅ ህግ ሆኖ እንዲወጣ አድርጓል። በህወሓት ዘመን በቅርቡ ከዚህ አለም በሞት የተለዩት እነ አቶ ቡልቻ ደመቅሳን የመሳሰሉ ጥቂት ሰዎች የህግ ረቂቁ ላይ ሃይለኛ ትችት ያቀርቡ ነበር፣ በአሁኑም ፓርላማ እነ ዶር ደሳለኝ ጫኔን የመሳሰሉ ለሂሊናቸው ያደሩ ሰዎች ትክክል አይደለም ብለው ባመኑባቸው ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ የተቃውም ድምጽ ያሰማሉ፣ ሆኖም ከ98% በላይ የፓርላማ መቀመጫ የተያዘው እስከ 2010 ድረስ በኢህዴግ፣ ከ2013 በኋላ ደሞ በብልፅግና ፓርቲ ስለሆነ፣ የህግ ረቂቅ ከአስፈጻሚው አካል ከመጣ ረቂቁን ከማጽደቅ ውጭ ሌላ አማራጭ ያለም አይመስላቸውም። ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት የፖለቲካ ፓርቲዎችና ፓርቲ ሲስተም ደካማ በመሆኑና፣ኢትዮጵያ ውስጥ ምርጫ የሚደረገው በገዢው ፓርቲ ሙሉ ቁጥጥር ስር ስለሆነ የኢትዮጵያ ፓርላማ ሁሌም የአንድ ፓርቲ መጨፈሪያ ቤት ነው። እኛ ነን ለምንድነው አንድ ቀን እንኳን ፓርላማው ከአስፈጻሚው አካል የሚላክለትን የህግ ረቂቅ አላጸድቅም የማይለው እያልን የምንጮኸው እንጂ፣ የኢትዮጵያ ፓርላማ በአዋጅ ሲዋቀር የህግ አስፈጻሚው አካል አገልጋይ እንዲሆን ተደርጎ ነው የተዋቀረው። ለመሆኑ ፓርላማዊ የመንግስት ቅርፅ ሲባል ምን ማለት ነው? ፓርላማዊ የመንግስት ቅርፅ መቼና የት ተጀመረ? ይህ የመንግስት ቅርፅ ከሌሎቹ የመንግስት ቅርጾች ለምሳሌ፣ ከፕሬዚደታዊ የመንግስት ቅርፅ በምን ይለያል?

ዛሬ በአለማችን ውስጥ ፓርላማዊ፣ፕሬዚደንታዊ፣ጠቅላይ ሚኒስትር-ፕሬዚደንት፣ፕሬዚደንት-ፓርላማና ንጉሳዊ አገዛዝ (Monarhcy) በመባል የሚታወቁ አምስት ዋና ዋና የመንግስት ቅርጾች አሉ፣ ከእነዚህ አምስት ዋና ዋና የመንግስት ቅርጾች ውስጥ ፓርላማዊ የመንግስት ቅርፅ ከንጉሳዊ ሥርዓት ቀጥሎ ረጂም ዕድሜ ያስቆጠረ የመንግስት ቅርፅ ነው። የተለያዩ የመንግስት ቅርጾችን ስንመለከት የህገ መንግሥት አርቃቂዎችና የተለያዩ ልህቃን አስበውና ለረጂም ጊዜ ተወያይተውበት  የነደፉት የመንግሥት ዓይነት ቢኖር የአሜሪካው ፕሬዚደንታዊ ዲሞክራሲ ብቻ ነው። የፓርላማ፣ የፕሬዚደንት -ፓርላማ እና የ ጠ/ ሚኒስትር -ፕሬዚደንት የመንግሥት ዓይነቶች ቀስ በቀስ በህደት እያደጉ የመጡ ናቸው እንጂ እንደ ፕሬዚደንታዊ ዲሞክራሲ የህገ መንግሥት አርቃቂዎች ቁጭ ብለው እየተወያዩ የነደፏቸው የመንግሥት ዓይነቶች አይደሉም።

ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ከዲሞክራሲ ጋር የተዋወቁ አገሮች ህገ መንግሥታቸውን ሲጽፉ “ምን ዓይነት የመንግሥት ቅርፅ” ያስፈልገናል የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ የሚያስችሉ ብዙ ሳይንሳዊ መረጃዎችና ምሳሌዎች ነበሯቸው። ለምሳሌ፣ የሶቭዬት ኅብረትን መፈራረስ ተከትሎ ወደ ዲሞክራሲ የመጡ የምሥራቅ አውሮፓ አገሮች ከብዙ አገሮች ልምድና ከአያሌ የፖለቲካ ሳይንስ ጠበብቶች የጥናትና ምርምር ሥራዎች ብዙ ጠቃሚ የሆኑ ልምዶችን አግኝተዋል።

የአሜሪካ መሥራች አባቶች ግን እንዲህ ዓይነቱ ዕድል አልነበራቸውም። የአሜሪካ ህገ መንግሥት ሲጻፍ በዓለም ላይ የነበረው የመንግሥት ዓይነት ንጉሣዊ አገዛዝ ነበር። አሜሪካ ውስጥ ንጉሣዊ አገዛዝ ባይኖርም አሜሪካ በንጉሣዊ አገዛዝ የምትተዳደር አገር ቅኝ ግዛት ነበረች። ንጉሣዊ አገዛዝን አምርረው ይቃወሙ የነበሩት የአሜሪካ መሥራች አባቶች ‹‹ንጉሥ›› በሌለበት ሥርዓት ውስጥ የህግ አስፈጻሚው አካል ምን መምሰል አለበት የሚለውን ጥያቄ መመለስ እጅግ በጣም አስቸግሯቸው ነበር።

የፓርላማ ዲሞክራሲ ልደትና ዕድገት ከፕሬዚደንታዊ ዲሞክራሲ ልደትና ዕድገት በጊዜ፣ በቦታ፣ በአጀማመርና በዕድገት ህደቱ እጅግ በጣም ይለያል። ፕሬዚደንታዊ ዲሞክራሲ የተጀመረው አሜሪካ ውስጥ በ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ማለቂያ ላይ ሲሆን “ፕሬዚደንታዊ ዲሞክራሲ” የረጂም ጊዜ ሃሳብ ልውውጥ፣ውይይትና የተጠና ህገ መንግስታዊ ቀረፃ ውጤት ነው። በአንጻሩ ፓርላማዊ ዲሞክራሲ በመካከለኛው ዘመን በተለያዩ የአውሮፓ አገሮች ውስጥ (እንግሊዝ፣ ኔዘርላንድ፣ ቤልጂግ፣ ፈረንሳይና በዛሬዋ ስፔን ውስጥ በምትገኘው ሊዮ በምትባለው ንጉሣዊ አስተዳደር) ውስጥ እንደተጀመረና በቅርፅና በይዘት እያደገ ዛሬ ያለውን መልክ ለመያዝ ከስምንት መቶ ዓመት በላይ ፈጅቶበታል።

ፓርላማ ዲሞክራሲያዊ በሆኑም ባልሆኑም አገሮች ውስጥ የሚገኝ እጅግ በጣም ረጂም ዕድሜ ያስቆጠረ ተቋም ነው። በአንድ አገር ውስጥ ፓርላማ ስላለ ብቻ አገሩ ዲሞክራሲያዊ ነው ወይም በዚያ አገር ውስጥ ያለው የመንግስት ቅርፅ ፓርላማዊ የመንግስት ቅርፅ ነው ማለት አይቻልም። ለምሳሌ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በፊውዳሉ፣ በወታደራዊው ዓምባገነንና በ2010 ዓም በተሰናበተው የህወሓት ዓምባገነን ሥርዓት ውስጥም ፓርላማ የሚባል ተቋም ነበር፣ዛሬም ኢትዮጵያ ውስጥ ፓርላማ አለ። የቀ.ኃ.ሥ. አስተዳደር ስለ ዲሞክራሲ የሚያውቀው ምንም ነገር አልነበረም። እንዲያውም ዲሞክራሲ የሚለውን ቃል ተጠቅሞም አያውቅም። ሆኖም በንጉሱ ዘመን የነበረው ፓርላማ በሰራቸው ሥራዎችም ሆነ አባላቱ በሚመረጡበት መንገድ ዛሬ ‹‹ዲሞክራሲያዊት›› እየተባለች በምትጠራው ኢትዮጵያ ውስጥ ካለው ፓርላማ የተሻለ ፓርላማ ነበር። ኢትዮጵያ ግን እስከ 1987 ዓ.ም. ድረስ ፓርላማዊ ሥርዓትን የምትከተል አገር አልነበረችም።

በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (UNESCO) ጥናታዊ ዘገባ መሠረት በ1188 ዓ.ም. በንጉሥ አልፎንሶ 9ኛ የተጠራው የአማካሪዎች ምክር ቤት ስብሰባ (The Cortes of León ) አውሮፓ ውስጥ የመጀመሪያው ፓርላማ ነው። የሊዮን አማካሪዎች ምክር ቤት የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ያካተተና የግል ኃብት ጥበቃን፣የመኖሪያ ቤት አለመደፈርንና የይግባኝ መብትን አስመልክቶ ከፍተኛ ግምት የተሰጣቸውንና በወቅቱ ዕፁብ ድንቅ የተባሉ ድንጋጌዎችን ማውጣት የቻለ ፓርላማ እንደነበረ የታሪክ ማስረጃዎች ያሳያሉ። ከዚህ በተጨማሪ የሊዮን አማካሪዎች ምክር ቤት ንጉሱ የምክር ቤቱን ፈቃድ ሳያገኝ ጦርነት ማወጅ እንዳይችል በማድረግ የንጉሡን ሥልጣን መገደብ የቻለ ፓርላማ ነበር።

የሊዮን አማካሪዎች ምክር ቤት ዛሬ ፓርላማ እያልን የምንጠራው ተቋም ቅርፅ ይኑረው እንጂ እንደ ዛሬዎቹ ፓርላማዎች የመንግሥት የበላይ አካል አልነበረም። ዛሬ በምናውቀው መልኩ የፓርላማ መንግሥት (Parliamentary Form of Government) የተጀመረው ኔዘርላንድና ቤልጂግ ውስጥ በ1580ዎቹ የ”ዳች አብዮት” እየተባለ በሚጠራው ወቅት እንደነበር አንዳንድ የታሪክ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ይህ ወቅት ኔዘርላንድና ቤልጂግ ውስጥ ህግ የማውጣትና ህግ የማስፈጸም ሥልጣን ቀስ በቀስ ከንጉሡ እጅ እየወጣ ወደ ህዝብ ተወካዮች እጅ የገባበት ወቅት ነበር። ዛሬ በብዙ አገሮች ውስጥ ለሚገኘው የፓርላማ ዲሞክራሲ መሠረት የሆነው የዘመናዊ የፓርላማ መንግሥት ጥንስስ የተጣለው እንግሊዝና ሲውዲን ውስጥ ከ1707 እስከ 1800 በነበሩት ዓመታት ውስጥ ነው።

በ1208 ዓ.ም. ፈረንሳይ ውስጥ ተወልዶ በ1265 ዓ.ም. እንግሊዝ ውስጥ የሞተው ሲሞን ደሞንትፎርት በህዝብ ውክልና ላይ የተመሠረተ መንግሥት አባት ነው እየተባለ ይነገርለታል። ሲሞን ደሞንትፎርት የሚዘከርባቸው ሁለት ዐቢይ ሥራዎች አሉ።አንደኛው በ1258 ዓ.ም. ፓርላማው የንጉሡን ሥልጣን እንዲገደብ ማድረጉ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በ1265 ዓ.ም. ተራ የከተማ ውስጥ ነዋሪ የሆኑ ዜጎች የፓርላማ አባል እንዲሆኑ ማድረጉ ነው። ይህ ከሆነ ከ450 ዓመታት በኋላ የእንግሊዝ ፓርላማ የሊብራል ዲሞክራሲ አስተሳሰቦችንና የዘመናዊ ፓርላማ አሠራር ዘዴዎችን በማቀፍ ለዛሬው “ዌስት ሚኒስቴር ሲስተም” እየተባለ ለሚጠራው ጠንካራ የመንግሥት ዓይነት መፈጠር የመሠረት ድንጋይ ማስቀመጥ ችሏል።

በንጉሣዊ ሥርዓት ትተዳደር በነበረችው እንግሊዝ ውስጥ ንጉሡ የካቢኔ አባላቱን መምረጥ ብቻ ሳይሆን የካቢኔው ሊ/መንበርም ነበር። እንግሊዝ ውስጥ የካቢኔ ሊ/መንበርነት ከንጉሱ እጅ ወጥቶ ሌላ ሰው እጅ የገባው በቀዳማዊ ጆርጅ ዘመነ መንግሥት ነው። ቀዳማዊ ጆርጅ እንግሊዝኛ ቋንቋ አጣርተው መናገር የማይችሉ ሰው ስለነበሩ የካቢኔ ስብሰባዎችን የመምራቱ ኃላፊነት ርዕሰ ሚኒስቴሩ ላይ የወደቀው በሳቸው ዘመነ መንግሥት ነበር። እንግሊዝ ውስጥ ፓርላማዊ ዲሞክራሲ እየጎለበተ ሲሄድና የፓርላማውን አባላት የሚመርጠው የኅብረተሰብ ክፍል ብዛትና ስፋት እያጨመረ ሲሄድ፣ ፓርላማውም በመንግሥት ምሥረታና አሠራር ላይ የሚጫወተው ሚና እየጨመረ መጣ። በመጨረሻም በ1832 ዓ.ም. የወጣው የፓርላማ ማሻሻያ ህግ የህግ አስፈጻሚውን አካል አባላትና የህግ አስፈጻሚውን አካል መሪ (ጠ/ሚኒስቴር) የመወሰን ሥልጣን ለፓርላማው ሰጠውና ዛሬ በመላው ዓለም የሚታወቀው የዌስት ሚኒስቴር ሞዴል የመንግሥት ዓይነት ወይም የፓርላማ ዲሞክራሲ ተመሰረተ። በዚህ የመንግሥት ሞዴል ውስጥ የህግ አስፈጻሚው አካል ለህግ አውጪው አካል ወይም ለፓርላማው ሙሉ ለሙሉ ተጠያቂ ሲሆን የረባ የመንግሥት ሥልጣን የሌላት ንግስትቱ (ንጉሥም ሊሆን ይችላል) ርዕሰ ብሔር ናት፣ ጠ/ ሚኒስትሩ ደግሞ ርዕሰ መስተዳድር ነው።

የፓርላማ ሥርዓት ሲባል የህግ አውጪው አካል በአካባቢ ደረጃ በቀጥታ በህዝብ የሚመረጥበት፣የፓርላማውን ግማሽ (50%+1) ያሸነፈ ፓርቲ ወይም የፓርቲዎች ጥምረት መንግስት የሚመሰርትበት፣ የመንግስት መሪ ጠሚ ወይም ቻንስለር የሆነበት የመንግስት አይነት ነው። የህግ አስፈጻሚውን አካል የሚመራው ጠሚሩ ሲሆን፣የካቢኔውን አባላት መርጦ ፓርላማው እንዲሾምለት የሚያቀርበውም ጠሚሩ ነው። በፓርላማ ሥርዓት ውስጥ አንድ ጠሚ የፓርላማውን አብዛኛ እምነት ካጣ ከሥልጣን ሊወገድ ይችላል።

አንድ የፖለቲካ ሥርዓት የፓርላማ ሥርዓት ነው እንዲባል ሦስት ዋና ዋና ሁኔታዎችን ማሟላት አለበት፡ አንደኛ- የህግ አስፈጻሚው አካል አገር ለማስተዳደር የሚያበቃውን ዲሞክራሲያዊ ህጋዊነት (Democratic Legtimacy) ከፓርላማው ማግኘት አለበት፣ ሁለተኛ- የህግ አስፈጻሚው አካል ተጠያቂነቱ ለፓርላማው ነው፣ ሶስተኛ- የህግ አውጪው አካል የህግ አስፈጻሚውን አካል በትኖ አዲስ ምርጫ እንዲጠራ ማድረግ ይችላል። በፓርላማ ሥርዓት ውስጥ ርዕሰ መስተዳደር ተብሎ አገር የሚመራው ጠ/ ሚኒስትሩ ቢሆንም በዚህ ሥርዓት ውስጥ በቀጥታ በህዝብ የተመረጠ ብቸኛ አካል ፓርላማው ብቻ ነው። ኢትዮጵያን ጨምሮ በብዙ የፓርላማ ሥርዓትን በሚከተሉ አገሮች ውስጥ ጠሚ የመስተዳድሩ መሪ ሲሆን፣ርዕሰ ብሔሩ በህዝብ የማይመረጥና ብዙም ሥልጣን የሌለው ፕሬዚደንት ነው።

ጠቅለል ባለ መልኩ ሲታይ የፓርላማ ሥርዓት የሚከተሉት ሦስት ባሕርያት አሉት፣ የህግ አስፈጻሚውና የህግ አውጪው አካላት የተጣበቁ ናቸው፣ የህግ አስፈጻሚው አካል ወይም መስተዳድሩን የሚመራው ሰው የሚወጣው ከፓርላማው ውስጥ ነው፣ በፓርላማ ሥርዓት ውስጥ መንግሥት (Government) የሚመሰርተው ከግማሽ በላይ የፓርላማ መቀመጫ ያሸነፈው ወይም ያሸነፉ ፓርቲዎች ጥምረት ነው። በፓርላማ ሥርዓት ውስጥ የዕምነት ማጣት ድምፅ በመስጠት ጠ/ሚኒስትሩን ማባረር ወይም ፓርላማው ተበትኖ አዲስ ምርጫ እንዲጠራ ማድረግ ይቻላል። የፓርላማ ሥርዓት እንግሊዝ፣ዳችና ጃፓንን በመሳሰሉ ‹‹ህገ መንግሥታዊ ›› የንጉሥ አስተዳደር ባለባቸው አገሮች ውስጥ እንዳለ ሁሉ እስራኤል፣ጀርመንና ጣሊያንን በመሳሰሉ የይስሙላ ፕሬዚደንት ባለባቸው ሪፑብሊኮች ውስጥም አለ።

በአንድ አገር ውስጥ ያለው የመንግስት ቅርፅ ምን ዓይነት እንደሆነ ማወቅ የሚቻለው በህግ አስፈጻሚውና በህግ አውጪው አካላት መካከል ያለውን ግንኙነት በመመልከት ነው። ለምሳሌ፣ የህግ አስፈፃሚውን አካል ህገ መንግሥታዊ በሆነ መንገድ ከሥልጣን ማባረር የማይቻል ከሆነ ይህ ሥርዓት ፕሬዚደንታዊ ሥርዓት ነው። የህግ አስፈጻሚውን አካል ማስወገድ የሚችለው ምክር ቤቱ ብቻ ሲሆን ሥርዓቱ የፓርላማ ሥርዓት ነው፣ የህግ አስፈፃሚውን አካል ምክር ቤቱም ፕሬዚደንቱም ማስወገድ የሚችሉ ከሆነ ሥርዓቱ ድብልቅ ሥርዓት (ድብልቅ የመንግሥት ዓይነት) ነው።

የፓርላማ ሥርዓትና ፕሬዚደንታዊ ሥርዓት በጣም የተለያዩ ናቸው፣ በፕሬዚደንታዊ ሥሮዓት ውስጥ ሁለት በቀጥታ በህዝብ የሚመረጡ አካላት አሉ (ፕሬዚደንቱና የምክር ቤት አባላት)፣ምክር ቤቱ ፕሬዚደንቱን ከሥልጣን ማባረር አይችልም፣ በፕሬዚደንታዊ ሥርዓት ውስጥ ያለው ፕሬዚደንት ከጠሚር የበለጠ ሥልጣን አለው። በፓርላማ ሥርዓት በቀጥታ በህዝብ የሚመረጡት የፓርላማው አባላት ናቸው፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደ ሌሎቹ የፓርላማው አባላት በአንድ የምርጫ ወረዳ ውስጥ ነው የሚመረጠው እንጂ  እንደ ፕሬዚደንት በአገር አቀፍ ደረጃ አይመረጥም።

የፓርላማ ሥርዓት ጠንካራ ጎኖች በተነሱ ቁጥር ሁሌም የሚጠቀሰውና፣ አንዳንድ የፖለካ ሳይንስ ምሁራን የፓርላማ ሥርዓት ከፕሬዚደንታዊ ሥርዓት የተሻለ ነው ከሚያሰኛቸው ምክንያቶች ውስጥ አንዱና ዋነኛው፣ በፓርላማ ሥርዓት ውስጥ የህግ አውጪውና የህግ አስፈጻሚው አካላት ፍጥጫ ውስጥ ሲገቡ፣ ፓርላማው የህግ አስፈጻሚውን አካል  ከሥልጣን ማባረር የሚችልበት ህገ መንግስታዊ መሳሪያ አለው። ይህ ህገ መንግሥታዊ መሳሪያ የ”እምነት ማጣት” ድምፅ (Vote of no Confidence) በመባል ይታወቃል። በፕሬዚደንታዊ ሥርዓት ውስጥ ግን ፕሬዚደንቱና ምክር ቤቱ ማለቂያ የሌለው ፍጥጫ ውስጥ ሲገቡ የህግ አስፈጻሚውና የህግ አውጪው አካላት ምንም ሥራ ሳይሰሩ እንደተፋጠጡ የአንደኛው የሥልጣን ዘመን ያልቃል እንጂ ፍጥጫው የሚፈታበት ህገ መንግሥታዊ መንገድ የለም።

የኢትዮጵያ ፓርላማ

ኢትዮጵያ ውስጥ ከቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ዘመን ጀምሮ ፓርላማ የሚባል ተቋም ነበረ፣ ይህ በንጉሠ ነገሥቱ ዘመን የነበረው ፓርላማ የመማክርት ምክር ቤትና(House of Deputies) የህገ መወሰኛ ምክር ቤት(Senate) የሚባሉ ሁለት ምክር ቤቶች ነበሩት። በቀኃሥ ዘመን ፓርላማ የሚባል ተቋም ይኑር እንጂ የኢትዮጵያ የመንግሥት ዓይነት ፓርላማዊ ቅርፅ ይዞ ኢትዮጵያ ፓርላማዊ የመንግሥት ቅርፅ ካላቸው አገሮች ተርታ የተሰለፈችው የሽግግሩ መንግሥት ፈረሶ የመጀመሪያው ምርጫ ከተካሄደ ከ1987 ዓ.ም. በኋላ ነው። ዛሬ በሥራ ላይ ያለው የኢትዮጵያ ፓርላማ በሚከተሉት ሦስት ምክንያቶች የተነሳ መዋቅራዊ በሆነ መልኩ (Structurally) የህግ አስፈጻሚው አካል ጉዳይ ፈጻሚ (Rubber Stump) ነው፣ አንደኛ- ፓርላማው በህግ ማውጣት ሂደት ላይ የሚሳተፉ ሁለት ምክር ቤቶች (Chambers) ያሉት ፓርላማ አይደለም፣ሁለተኛ- የህግ አስፈጻሚውን አካል የሚፈጥረው የህግ አውጪው አካል ስለሆነ፣ አንድ ምከር ቤት ብቻ ያለው ፓርላማ (Unicameral Legislature) እራሱ የፈጠረው አካል የሚልክለትን የህግ ረቂቅ ይደግፋል እንጂ አይቃወምም(በተለይ ትርጉም ያለው የፖለቲካ ተቃውሞ በሌለበት ኢትዮጵያን በመሰለ የአንድ ፓርቲ አገር)፣ሦስተኛ- የኢትዮጵያ ፓርላማ  ዳች፣ቤልጂግ፣ እንግሊዝ፣ጀርመን፣ጣሊያን፣እስራኤልና ካናዳን የመሳሰሉ የዳበረ የፓርላማ ልምድ ባላቸው አገሮች ውስጥ እንዳሉት ፓርላማዎች  የእምነት ማጣት ድምጽ የሚባል ህገ መንግስታዊ መሳሪያ የለውም። እንዲያውም የኢትዮጵያን ህገመንግስት አንቀጽ 60 ንዑስ አንቀጽ 1 ካየን፣ የእምነት ማጣት ድምጽ እንዲሰጥ ፓርላማውን የመጠየቅ ሥልጣን ያለው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ነው። በሌሎች አገሮች ውስጥ ባሉ ፓርላማዎች ውስጥ ይህ መብት የፓርላማው ነው(አንዳንድ አገሮች ውስጥ ሁለቱም ሊኖራቸው ይችላል)። የእምነት ማጣት ድምጽ የሚሰጠው ጠሚኒስትሩን ከሥልጣን ለማባረር ነው፣እጅግ በጣም በሚገርም ሁኔታ የኢትዮጵያ ህገመንግስት ይህንን ሥልጣን የሚሰጠው ለጠሚሩ ለራሱ ነው። ዛሬ በስራ ላይ ያለው የኢትዮጵያ ህገ መንግስት የተጻፈው በእንደዚህ አይነት የአንድን ፓርቲ ብቻ ሳይሆን የአንድን ግለሰብ ፍላጎት በሚያስጠብቁ አንቀጾች ታጭቆ ነው። ለዚህ ይመስለኛል ታዋቂው የህግ አስተማሪ ሙሉጌታ አረጋዊ  የኢትዮጵያ ፓርላማ የተሰራው በመለስ ዜናዊ ልክ ነው እያለ በተደጋጋሚ የሚናገረው።

ኢትዮጵያን በመሳሰሉ ፌዴራል የመንግሥት መዋቅር ባለባቸውና የተለያየ ቋንቋ፣ባህልና ሃይማኖት ያለው ህዝብ በተለያዩ ክልሎች ውስጥ ብቻ ሳይሆን በአንድ ክልል ውስጥም በሚኖርባቸው አገሮች ውስጥ የክልሎችን ጥቅምና ፍላጎት የሚያስጠብቅ አካል በህግ አውጪው አካል ውስጥ መኖሩ እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው። ለምሳሌ፣ አርሲ ውስጥ በገጠርም በከተማም ከፍተኛ ቁጥር ያለው አማራ ይኖራል፣ በቁጥር ከተወሰደ አማራው አርሲ ውስጥ ከኦሮሞ ቀጥሎ ሁለተኛው ትልቅ ማህበረሰብ ነው። ነገር ግን የኢትዮጵያ ፓርላማ ክልሎችን የሚወክል አካል ስሌለውና፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የምርጫ ሥርዓት አናሳ ክፍሎችን የሚያገል የምርጫ ሥርዓት ስለሆነ፣አርሲ ውስጥ ትልቅ ቁጥር ያለው የአማራ ማህበረሰብ ጨፌ ኦሮሚያ ውስጥም ሆነ በብሔራዊ ፓርላማ ውስጥ የኔ ነው የሚለው ተወካይ የለውም።

የኢትዮጵያ ፓርላማ አንድ ምክር ቤት ብቻ  ያለው (Unicameral Legislature) ፓርላማ ነው የሚል ክርክር በተነሳ ቁጥር የሥርዓቱ ደጋፊዎች ከሚያቀርቡት ተቃውሞ ዋናው የፌዴሬሺን ምክር ቤት ነው። በእርግጥ የኢትዮጵያ ፓርላማ የፌዴሬሺን ምክር ቤት የሚባል አካል አለው፣ ሆኖም በኢትዮጵያ ህገ መንግሥት መሠረት ይህ ምክር ቤት የፓርላማው አካል ይሆን እንጂ በህግ ማውጣት ሂደት ውስጥ አይሳተፍም፣ ደሞም የፌዴሬሺን ምክር ቤት የሚወክለው ብሔር ብሔረሰቦችን ነው እንጂ፣ በኢትዮጵያ ህገ መንግስት መሰረት ብሔር፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች በሚለው ስብስብ ውስጥ የማይጠቃለለውን ቁጥሩ ከ7 ሚሊዮን በላይ የሚገመተውን የአዲስ አበባ ህዝብ አይወክልም። የአዲስ አበባ ከተማ ህዝብ ብቁጥር ሲለካ ከ80ዎቹ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ውስጥ ከ78ቱ ይበልጣል። ሌላው የኢትዮጵያን ፓርላማ አንድ ምክር ቤት ብቻ ያለው ፓርላማ ነው የሚያሰኘው በህግ አውጪው አካል ውስጥ አንድ የህግ ረቀቅ ሲታይና ህግ ሆኖ ሲጸድቅ የህግ ረቂቁን ከተለያዩ የሀገሪቱ ጥቅሞችና ፍላጎቶች አኳያ አይቶ የሚያሻሻል ወይም ህግ ሆኖ መውጣት የለበትም ብሎ የሚያስቆም አካል ፓርላማው ውስጥ አለመኖሩ ነው።

ከላይ ከፍ ሲል ለመግለጽ እንደተሞከረው በፓርላማ ሥርዓት ውስጥ የህግ አስፈጻሚውና የህግ አውጪው አካላት የተጣበቁ ናቸው፣ የህግ አስፈጻሚው አካል ወይም መስተዳድሩን የሚመራው ሰው የሚወጣው ከፓርላማው ውስጥ ነው፣ በፓርላማ ሥርዓት ውስጥ መንግሥት የሚመሰርተው ከግማሽ በላይ የፓርላማ መቀመጫ ያሸነፈው ፓርቲ ወይም ያሸነፉ ፓርቲዎች ጥምረት ነው። የኢትዮጵያ ፓርላማ መዋቅራዊ በሆነ መልኩ የህግ አስፈጻሚው አካል ጉዳይ ፈጻሚ ነው የሚባለውም፣ በአንድ በኩል ፓርላማው አንድን የህግ ረቂቅ በተለያየ መልኩ የሚመለከቱ ሁለት አካላት የሌሉበት መሆኑ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ የኢትዮጵያ ፓርላማ የአንድ ፓርቲ ቤት በመሆኑ ነው። ባለፉት 30 አመታት 99% የሚሆነውን የኢትዮጵያ ፓርላማ መቀመጫ የተቆጣጠሩት ኢህአዴግና ብልፅግና ናቸው።  ህወሓት/ኢህአዴግ ኢትዮጵያን በመራባቸው 27 አመታትና ዛሬም ድረስ የኢትዮጵያ ፓርላማ የህግ አስፈጻሚው አካል የላከለትን የህግ ረቂቅ አላጽድቅም ብሎ የመለሰበት ግዜ ያለ አይመስለኝም።

በቀኃስ ዘመን የነበረው ፓርላማ ንጉሱና ጠሚሩ የሚልኩለትን የህግ ረቂቅ ውድቅ ያደረገባቸው ግዜዎች ነበሩ፣ ይህ በሚሆንበት ግዜ ንጉሱና ጠሚሩ አንገብጋቢ ናቸው ብለው ያመኑባቸውን የህግ ረቂቆች በልዩ ድንጋጌ ዓዋጅ እያወጁ ነጋሪት ጋዜጣ ላይ እንዲወጣ የሚያደርጉት ፓርላማው አመታዊ ሥራውን አጠናቅቆ ዕረፍት የሚወጣበትን ጊዜ እየጠበቁ ነበር። ለምሳሌ፣ በ1952 ዓ.ም. ፓርላማው ዕረፍት ላይ እያለ በልዩ ድንጋጌ የወጣው የህንፃ መሣርያዎች ግብር ዓዋጅ ፓርላማው የዕረፍት ጊዜውን ጨርሶ ሲሰበሰብ እጅግ በጣም እልህ አስጨራሽ ክርክር ከተደረገበት በኋላ ልዩ ድንጋጌው እንዲታገድ ተደርጓል። ልዩ ድንጋጌው መታገዱን ወይም መሻሩን የሚገልጽ ማስታወቂያ በነጋሪት ጋዜጣ ላይ ታትም እንዲወጣ ፓርላማው ለህግ አስፈጻሚው አካል መመሪያ ቢሰጥም፣ መመሪያው ለሚቀጥሉት አምስት ወራት ተግባራዊ ሳይሆን ቆይቷል። ይህ ያበሳጫቸው የፓርላማው አባላት ለንጉሠ ነገሥቱ ጠ/ ሚኒስትሩን ከሥልጣን የሚያወርድ የህግ ሂደት እንዲጀምሩ ጥያቄ ሲያቀርቡላቸው፣ ንጉሠ ነገሥቱ ልዩ ድንጋጌው ውድቅ መሆኑን የሚገልፅ ማስታወቂያ ወደኋላ ተመልሶ ይውጣ በተባለበት ወርና ቀን በነጋሪት ጋዜጣ ላይ ታትሞ እንዲወጣ አስቸኳይ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል። ይህ ፊውዳሊዝም ብለን የዛሬ 50 አመት ባስወገድነው ሥርዓት ውስጥ የነበረው ፓርላማ የህዝብን ጥቅም ለማስጠበቅ የነበረው ቁርጠኝነት በዛሬዋ ፌዴራል ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ውስጥ የለም።

ለወደፊቷ ኢትዮጵያ ይበጃል ተብሎ የሚታመነው የመንግሥት ቅርፅ ፓርላማዊ የመንግሥት ቅርፅ ከሆነ፣ አሁን ያለው ፓርላማ በሚቀጥለው መልኩ መሻሻል አለበት- አንደኛ- ፓርላማው በህግ ማውጣት ሂደት ውስጥ የሚሳተፉ ሁለት የተለያዩ ምክር ቤቶች ሊኖሩት ይገባል፣ ሁለተኛ- አንደኛው ምክር ቤት የሚመረጠው በክልል ደረጃ ሲሆን ውክልናው ለመረጠው ክልል ይሆናል፣ሁለተኛው ምክር ቤት ደሞ በአካባቢ ደረጃ የሚመረጥ ሲሆን፣ውክልናው ለመረጠው አካባቢ ይሆናል፣ሦስተኛ- የሁለቱ ምክር ቤቶች የፓርላማ አበላት የሚመረጡበት የምርጫ ሥርዓት የተለያየ መሆን አለበት፣አራተኛ-አንድ የህግ ረቂቅ ከመጽደቁ በፊት በእነዚህ ሁለት ምክር ቤቶች ተራ መታየት አለበት፣ደሞም የታችኛው ምክር ቤት ያጸደቀውን የህግ ረቂቅ የላይኛው ምክር ቤት አላጸድቅም ብሎ የህግ ረቂቁን መልሶ ወደታችኛው ምክር ቤት መላክ መቻል አለበት፣አምስተኛ- የፌዴሬሺን ምክር ቤት ከፓርላማው ውስጥ መውጣት አለበት።

የፓርላማውን ሁለት ምክር ቤት መቀመጫ የሚይዙት የህዝብ ተወካዮች በክልልና በአካባቢ ደረጃ መመረጣቸው፣ በአንድ በኩል የሁለቱን ምክር ቤቶች የውክልና አድማሳቸው የተለያየ ያደርገውና፣ሁለቱ ምክር ቤቶች አንድን የህግ ረቂቅ የሚመለከቱበት መነጽር ይለያያል፣ በሌላ በኩል ደሞ በሁለቱ ምክር ቤቶች ውስጥ አብላጫውን መቀመጫ የሚያሸንፉ ፓርቲዎች የተለያዩ ሊሆኑ ይችላል። ፓርላማዎች የላይኛውና የታችኛው ምክር ቤት የሚባል ሁለት ምክር ቤት ሲኖራቸው፣ የህግ አውጪው አካል የህግ አስፈጻሚው አካል ጉዳይ ፈጻሚ መሆኑ በከፍተኛ ደረጃ ይቀንሳል፣ በሌላ በኩል ደግሞ ህዝብ የሚኖረው የውክልና አድማስ ይሰፋና የተለያዩ ፍላጎቶች ሚዛናዊና ህገ መንግሥታዊ በሆነ መንገድ ውሳኔ ማግኘት የሚችሉበት መንገድ ይፈጠራል።

የፌዴሬሺን ምክር ቤት የሚባለው አካል ከፓርላማው መውጣት ብቻ ሳይሆን ስር ነቀል ለውጥ የሚያስፈልገው ወይም በሌላ አካል መተካት ያለበት አካል ነው።ፓርላማው ውስጥ እያንዳንዱ ክልል የራሱ ተወካይ እስካለው ድረስ ሌላ የብሔር ብሔረሰቦች ተወካይ የሚባል ተቋም የሚያስፈልግ አይመስለኝም። በኢትዮጵያ ህገ መንግሥት መሠረት የፌዴሬሺን ምክር ቤት የተለያዩ ስራዎች ቢኖሩትም የዚህ  አካል ትልቁ ሥራ ህገ መንግሥቱን መተርጎም ነው። ህገ መንግስት የመተርጎም ሥልጣንና ሃላፊነት ከሶስቱ የመንግስት አካላት የአንደኛው በተለይም የህግ ተርጓሚው (Judicai Boday) ነው እንጂ በህግ አውጪው ተቋም ውስጥ ያለ ሌላ አካል የሚሰራው ስራ መሆን የለበትም። ደሞም ህግ የመተርጎም ስራ ከፍተኛ ሙያዊ እውቀትና በስነምግባር የታነጹ ግለሰቦችን የሚፈልግ ስራ ስለሆነ፣ እዚህ ቦታ ላይ የሚቀመጡ ግለሰቦች በምርጫ ሳይሆን በህግ አስፈጻሚው አካል መሪ እየተመረጡ በህግ አውጪው አካል ብቃታቸውና ስነምግባራቸው እየተረጋገጠ ቢሾሙ የተሻለ ይሆናል የሚል እምነት አለኝ። በምርጫ የሚመጡም ከሆነ ለዚህ ቦታ በዕጩነት የሚቀርቡ ተወዳዳሪዎች ህግ ለመተርጎም የሚያስችል የትምህርት ዝግጅት፣ ልምድ፣ ብቃትና ችሎታ እንዳላቸው መረጋገጥ አለበት። ባለፉት 30 አመታት የፌዴሬሺን ምክር ቤት አባላት የነበሩትን ሰዎች ስናይ አብዛኛዎቹ ህገ መንግስቱን መተርጎም ቀርቶ፣የኢትዮጵያን ህገ መንግስት አንብበው ለሌላ ሰው ማስረዳት የሚችሉም አይደሉም . . . . ይታያችሁ እንግዲህ እንደነዚህ አይነት ሰዎች ህግ በሚተረጉሙበት አገር ውስጥ ነው የምንኖረው!

ፓርላማዊና ፕሬዚደንታዊ ዲሞክራሲ ከሚለያዩባቸው ነጥቦች ውስጥ አንዱና ዋነኛው በፓርላማ  ሥርዓት  ውስጥ  የህግ  አውጪው  አካል  የ”እምነት  የለኝም”  ድምፅ  በመስጠት የህግ አስፈጻሚውን አካል ከሥልጣን ማስወገድ መቻሉ ነው። ይህ ህግ መንግሥታዊ ህደት በፓርላማ ሥርዓት ውስጥ አንደኛው የመንግሥት አካል ሌላውን ህገ መንግስታዊ በሆነ መንገድ የሚቆጣጠርበት መሣርያ ነው። ፓርላማዊ ሥርዓት ከፕሬዚደንታዊ ሥርዓት ይሻላል ተብሎ ከሚነገርላቸው ጠንካራ ጎኖች ውስጥ አንዱና ትልቁ ይኸው የህግ አውጪው አካል የህግ አስፈጻሚውን አካል ከሥልጣን ማባረር መቻሉ ነው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ግን እንዲህ ዓይነት ህገ መንግሥታዊ መሣርያ የለውም፣ እንዳያውም በኢትዮጵያ ህገ መንግሥት መሠረት ጠ/ ሚኒስትሩ ነው ፓርላማውን በትኖ አዲስ ምርጫ እንዲጠራ የማድረግ ሥልጣን ያለው። ይህ የተገላቢጦሽ የሆነ አሠራር ኢትዮጵያ ውስጥ ተቋማዊ መሻሻሎች ሲደረጉ መሻሻል ካለባቸው አሰራሮች አንዱ መሆን አለበት።

ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ፓርላማዊ ሳይሆን ፕሬዚደንታዊ የመንግስት ቅርፅ ነው ከተባለም፣ ካለ ምንም የጥናትና ምርምር ስራ ዘለን ፕሬዚደንታዊ ሥርዓት ውስጥ መግባት አለብን ብዬ አላምንም። በህገ መንግስታዊ ምህንድስና ሂደት (Constitutional Design Process) ውስጥ አልፈው ዲሞክራሲያዊ ሽግግር ያደረጉትን የተለያዩ የአለማችን አገሮች ልምድ ስንመለከት፣እነዚህ አገሮች ዛሬ ያላቸውን የመንግስት ቅርፅ የመረጡት የተለያዩ አማራጮችን አይተውና፣እያንዳንዱን አማራጭ ከአገራቸው ባህል፣የዕድገት ደረጃ፣የዲሞክራሲና የፖለቲካ ልምድ ጋር እያወዳደሩ በሚገባ ካዩ በኋላ ነው የሚበጃቸውን የመንግስት ቅርፅ የመረጡት። በነገራችን ላይ ሁሉም የመንግስት ቅርጾች ደካማና ጠንካራ ጎን አላቸው፣ ይህ የሚነግረን የመንግስት ቅርፅ ስንመርጥ በጥናትና ምርምር ላይ ተመስርተን ካሉን የተለያዩ አማራጮች ውስጥ አንዱን የመንግስት ቅርፅ ከነደካማ ጎኑ መምረጥ  እንዳለብን ነው። ከዚህ ውጭ ዛሬ ፕሬዚደንታዊ የመንግስት ቅርፅ ነው የሚያስፈልገን ብለን በነጋታው አዋጅ ብንወጣ አገራችንን ወደ ባሰ ትርምስ ውስጥ እንወስዳታለን ከህመሟ አንፈውሳትም!!!

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

ጥር 2 ቀን 2017 ዓ/ም   January 10, 2025  በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡ ቤተ ሰብ፡ ወዳጅ ዘመዶቻችሁን ያጣችሁ: ልጆቻችሁን የቀበራችሁ፡ አካልችሁን ያጣችሁ፡ የተሰነዘረውን ብትር በመከላከል ላይ ያላችሁ፡ያለፈቃዳችሁ በመንግሥት ተጽእኖ ወደመግደልና

በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛ ተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡

January 10, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ¹⁵ የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ ፥ ¹⁶ ተራራዎችንና   በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን ፤ ¹⁷ ታላቁ የቁጣው ቀን  መጥቶአልና ፥ ማንስ ሊቆም ይችላል ? አሉአቸው ። ራእይ 6 ፤  15_17 ይኽ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ። የኢየሱስን ልደት ሰናከብር የየሐንስ ራእይን ማንበብ ጠቃሚ ይመስለኛል ። ምክንያቱም በመጨረሻው ዘመን

ከኢየሱስ የፍርድ ቀን በፊት በህሊናችን ውስጥ ፍቅርን ለማንገስ እንጣር 

የምጣኔ ሀብታዊ ፍጥ፣ የፖለቲካ፣ የእውነትና የሰብአዊ መብት ታጋይ፣ የአመኑበትን ነገር ለመናገር እንደ ፖለቲከኛ በቃላት ሳያሽሞነሙኑ ቀጥታ የሚናገሩት የሀገሬ ኢትዮጵያ ታላቅ ሰው ነበሩ “ዘር ቆጠራውን ተዉት፤ የአባቶቻችሁን ሀገር ኢትዮጵያን አክብሩ!”  አቶ ቡልቻ ደመቅሳ

ሀገር ወዳዱ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ

January 6, 2025
Go toTop