January 11, 2025
82 mins read

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)

  ጥር 2 2017(January 10, 2025)

መግቢያ

ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ በፖለቲካ ስም የሚደረገው ትግል ነው ማንም እየተነሳ የሚጨፍረውና አገራችንና ህዝባችን አሁን ባሉበት አሳፋሪ ሁኔታ ውስጥ እንዲወድቁ የተደረገው። ለዚህ ዋናው ምክንያት ደግሞ ለአብዛኛዎቻችን ፖለቲካ የሚባለው ጽንሰ-ሃሳብ ዋናው ተግባሩ ምን እንደሆነ ባለመገንዘባችን ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን፣   ፖለቲካም እንደማንኛውም ነገር የራሱ የሆነ ሂደት ያለው ብቻ ሳይሆን፣ አንድ ሰው ፖለቲከኛ ልሁን ብሎ ከመነሳቱ በፊት ማለፍ ያለብትን የተወሳሰቡ ጉዞዎች ስለማያልፍ በደመ-ነፍስ በመነሳት በፖለቲካ ስም የሚያካሂደው ትግል የመጨረሻ መጨረሻ በቀላሉ መቋጫ የማያገኝ ህብረተሰብአዊ ምስቅልቅል ሁኔታዎችን ውስጥ ከቶናል። በፖለቲካ ስም የተደረገውና የሚደረገው ትግል በእኛ አገር ውስጥ በቀላሉ መቋጫ የማያገኝ ምስቅልቅል ሁኔታዎችን ቢፈጥርም፣ ይህ ዐይነቱ ችግር በአብዛኛዎቹም የአፍሪካና የተቀሩት የሶስተኛው ዓለም አገሮችም ውስጥ ይታያል። የኛን ለየት የሚያደርገው ግን በፖለቲካ ስም እየተነሱ የሚነግዱ ድርጅቶች መብዛታቸው ብቻ ሳይሆን፣ በተለይም ብሄረሰብን ተገን በማድረግ በፖለቲካ ስም የሚካሄደው ትግል በቀላሉ ልንፈታው የማንችለው ችግር ውስጥ ከቶናል። በተለይም ፖለቲካዊ ትግሉ በጭንቅላት ላይና በዕውቀት ላይ ያተኮረ መሆኑ ቀርቶ በጉልበት ወይም በጦርነት ላይ ያተኮረ በመሆኑ በቀላሉ መፍትሄ ሊያገኝ አልቻለም። ራሱ አጋጣሚዎችን ተጠቅሞም የሚወጣው ኃይል የፖለቲካን ትርጉም በሚገባ ከመረዳት ይልቅ በደመ-ነፍስ እየተመራ በኃይል ላይ ያመዘነ የሚካሂደው ትግል የአገራችንን የተወሳሰቡ ሁኔታዎች እያባባሰው ሊመጣ ችሏል። ይህም የሚያረጋግጠው ለአብዛኛዎቻችንም ሆነ በተለያዩ ጊዜያት ስልጣንን ለጨበጡና ለሚጨብጡም ኃይሎች ፖለቲካ የሚባለውን ትርጉሙን፣ ዋናው ተግባሩንና ዓላማውን ባለመረዳታቸው የተነሳ ነው።

በፖለቲካ ስም የሚደረገው ግብግብና የሚፈጠሩት ምስቅልቅል ሁኔታዎች ደግሞ ሰፊውን ህዝብ እያረሰ በሚመግበው ገበሬና በየፋብሪካዎች ውስጥ ተቀጥሮ በሚሰራውና በነጋዴውና በተቀሩት የራሳቸውን ህይወት መልክ ለማሲያዝ ወዲህና ወዲያ በሚሯሯጡ ሰዎች አይደለም። በአገራችንም ሆነ በተቀሩት የአፍሪካና ሌሎች የሶስተኛው ዓለም አገሮች በፖለቲካ ስም የሚሰራው ወንጀል ተማርን በሚሉና፣ አንዳንዶችም የዲግሪን ማዕረግነት በጨበጡ ነው። ይሁንና ግን እነዚህ ተማርን የሚሉንና ዲግሪም የጨበጡ ሰዎች በራሳቸው ህብረተሰብአዊ ሀብትን(National Wealth) የሚፈጥሩ ስላልሆነ መሆን ያለበት ዋናው ተግባራቸው አንድን አገር በስርዓትና ጥበባዊ በሆነ መንገድ በማስተዳደር አዳዲስ ቲክኖሎጂዎች እንዲፈጠሩ አመቺ ሁኔታውችን በመፍጠር የገበሬዎንና የሰራተኛውን ስራ ማቃለልና ምርታማነቱንም እንዲያሳድግ ማውጣትና ማውረድ ነበረባቸው፤ አለባቸውም። ይህንን ከማድረግ ይልቅ በስልጣን ላይ ያሉ ኃይሎችና ከስራቸው ያሉ ቴክኖክራቶች በራሳቸው ዓለም እየኖሩ እያንዳንዱ ገበሬና ሰራተኛ በምን ዐይነት ሁኔታ  ውስጥ እየሰራ እንደሚመግባቸው ስለማይገነዘቡ ምርታማነት አድጎ የገበሬውም ሆነ የሰራተኛው የኑሮ ሁኔታ እንዲሻሻል ከማድረግ ይልቅ በኑሮው እየማቀቀ እንዲኖር ያደርጉታል። በተለይም ደግሞ ስልጣንን የጨበጡና በቀጥታም ፖለሲ በማውጣት አገር እናስተዳድራለን የሚሉ ሰዎች ራሳቸውን በማስጨነቅ  የተሻለና ጥበባዊ ሁኔታ እንዲፈጠር ከማድረግ ይልቅ የአገራችን ሁኔታ የባሰውኑ እንዲመሰቃቀል አድርገውታል፤ እያደረጉትም ነው። ወደ ተጨባጩ ሁኔታም ስንመጣ ደግሞ ስልጣንን የጨበጠውና የግብረ-አበሮቹ ተግባራቸው ጦርነትን ማካሄድ ስለሆነ እንኳን ህብረተሰብአዊ ሀብትና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች የሚፈጠሩበትን ሁኔታዎች ከማመቻቸት ይልቅ እንዲያውም ይባስ ብለው ያለውን በማውደም የጠቅላላው ህዝብ ህይወት እንዲጨልም እያደረጉ ነው። 

ከዚህ አጠር መጠን ያለ መግቢያ ስንነሳ ለመሆኑ የመማርና የስልጣን መያዝ ትርጉሙ ምንድነው? ፖለቲካስ ሲባል ራሱን የቻለ ሙያ ወይስ አገርን ማፍረሺያና ማተረማመሲያ መሳሪያለምንስ ነው በአገራችን ምድር የፖለቲካ ትርጉም በተጣመመ መልክ ግንዛቤ ውስጥ የገባውና ወደ መነታረኪያነትና ወደ ግብግብነት የተለወጠውመጽሀፍ ቅዱሱ እንደሚያስተምረን በመጀመሪያ ቃል ነበር። በቃልም ወይንም በመናገርም ሰው መሆንና በአምላክም ምስል እንደተፈጠርክ ራስህን ትገልጻለህ፤ ታረጋግጣለህም።  ስለሆነም  ከእንስሳ የተለየ መሆንህን ታረጋግጣለህ። ይህም ማለት ጉልበትን ከመጠቀም ይልቅ ወይም ኃይል አለኝ ብሎ ከመመካትና ሌላውንና ደካማውን ከማስፈራራት ይልቅ በመነጋገር፣ በመከራከር፣ የተሻለ ወይም ሳይንሳዊ ሃሳብና መፍትሄ በማቅረብ ችግርን በጋራ መፍታት ይቻላል ነው የሚለን። ይህ ከመሆኑ ይልቅ  በአገራችንም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ፖለቲካ ሳይንስ መሆኑና ችግርን መፍቺያ መሳሪያ ከመሆን ይልቅ ወደ አመጽነት በመለውጥ በተለይም የአገራችንን ህዝብ ፍዳ ውስጥ ከቶታል። ራሱን በማግኘትና አርፎ በመቀመጥና በማሰብ ኑሮውን ለማሻሻል አዳዲስ ነገሮችን እንዳይፈጥር ታግዷል። ስለሆነም የፖለቲካን ትርጉምና ተግባሩንም መረዳት በጣም አስፈላጊ ነው።

ፖለቲካ እንደማንኛውም ትምህርት ሙያ ወይስ የመነታረኪያ መሳሪያ?

በአገራችንም ሆነ በተቀሩት የሶስተኛው ዓለም አገሮችም ሆነ፣ አሁን ደግሞ ሰለጠን፣ የተሻልንም ነን በሚሉ  የካፒታሊስት አገሮችም ውስጥ ፖለቲካ ልክ እንደሌሎች ነገሮች፣ ለምሳሌ የአናጢነትን ሙያ እንደተማረና፣ ሰርቶ በሚያቀርበው ጠረቤዛ፣ መቀመጫና መዝጊያ ሙያውን እንደሚያረግጠው ሰው ፖለቲካ በተጨባጭ የሚመዘንበት ነገር የለም። ሌሎችም ሙያዎች ለምሳሌ መካኒካል ኢንጂነሪንግ ወይም ፊዚክስና ኬሚስትሪ የተማሩ ሰዎች በተማሩት ትምህርት አዳዲስ ማሽኖችን በመፍጠር፣ ያለውን በማሻሻል፣ ፊዚክስ የተማረው ደግሞ መጽሀፍም በመጻፍና አዳዲስ መሳሪያዎችን በመፍጠር ብቃትነቱን ማረጋገጡ ብቻ ሳይሆን፣ የስራው ወይም የፈጠራው ውጤት ተጠቃሚ ከአገሩ ህዝብ አልፎ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን እንዲጠቀሙበት በማድረግ ሙያውን በተግባርና በውጤቱ ያረጋግጣል። ሌሎች እንደ አርኪቴክችር የመሳሰሉትንና ሌሎችንም በጣም ዝቅ ብለው የሚታዩ ሙያዎችንና የስራ ውጤቶችን ስንመለከት በተለያዩ ሙያዎች ተቀጥረው የሚሰሩ ሰዎች የመጨረሻ መጨረሻ በሚሰሩት ስራና በሚያቀርቡት ሙያ ብቻ ነው የሚለኩት። በስራቸውም ላይ ሊቆዩና የተሻለም ማዕረግ ሊያገኙ የሚችሉት በተከታታይ ሰርተው በሚያቀርቡት ውጤት ብቻ ነው። ደሞዛቸውንም የሚያገኙት በሚሰሩት ስራና በሚያቀርቡት ውጤት ብቻ ነው።

ከዚህ አጠር መጠን ያለ አቀርቅረብ ስንነሳ አንድን ፖለቲከኛ ነኝ የሚል ሰውና ስልጣንን በተቆጣጠረ ግለሰብም ሆነ በፓርቲ ደረጃ ተደራጅተው በዚህም በዚያም ብለው ስልጣንን በጨበጡ ሰዎች ፖለቲከኛ መሆናቸውን በምንድን ነው የምንለካው? ዝም ብለው ስልጣን ላይ ስለወጡ፣ በወታደርና በጸጥታ ኃይል ስለታጀቡና ህዝባቸውንም ስለሚያስፈራሩ፣ ሲያገረሽባቸው ደግሞ ጦርነት በመክፈት አገርን በሚያተረማምሱ፣ እንዲያም ሲል የሌላን ህዝቦች አገሮች በመውረርና ታሪካቸውንና ቅርሳቸውን በማፈራረስ ነው ፖለቲከኞች መሆናቸውን ለማረጋገጥ የምችንችለው ወይ? ወይስ ሌላ መለኪያ አላቸው? ለመሆኑ ፖለቲካ ምንድነው ነው? እንደ ማንኛውም ትምህርትና ስልጠና እንደሙያ የሚቆጠር ወይም የሚወሰድ ነገር? በፖለቲካ ዓለም ውስጥ ከገባሁበት ጊዜ ጀምሮ፣ በተለይም ባለፉት አስርና አስራዓምስት ዐመታት ራሴን እየመላለሱ የምጠይቀው ለምንድ ነው በፖለቲካ ስም ይህን ያህል ትርምስ የሚፈጠረውና፣ በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ህይወት ጭንቀት ውስጥ የሚከተው? ፖለቲካ ነን ብለው ስልጣን ላይ የሚወጡና የወጡ ሰዎች ለመሆኑ ስለ ሰው ልጅና ስለህሊናው(Psychology) የሚገባቸው ነገር አለ ወይ? አንድስ ሰው ወይም በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ እየፈራና እየተሸማቀቀ የመኖር ግዴታ አለበት ወይ? እግዚአብሄርም የሰውን ልጅ ሲፈጥር አንደኛውን አሰቃይ፣ ሌላው ደግሞ የሚሰቃይ፣ የሚታሰር፣ የሚደበደብና እንዲያም ሲል የሚገደል አድርጎ ፈጥሮታል ወይ

እንደሚታወቀው ያለንበት የሳይንስ ዘመን ነው። ሳይንስና ቴክኖሎጂም በሰው የማሰብ ኃይል ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ የተፈጠሩና ወደ ተግባር በመመንዘር አብዛኛዎቻችን እንድንጠቀምባቸው የተደረጉ ናቸው። በሌላ ወገን ደግሞ ያለፍንበትን ጊዜ ወደ ኋላ ዞር ብለን ስንመለከት(going back in time) ከየት ተነስተን እዚህ ደረጃ ላይ ለመድረስ ስንትና ስንት ውጣ ውረዶችን እንዳሳለፍን ለመገንዘብ ሙከራ ስናደርግ ብዙ ነገሮች ግልጽ ይሆኑልናል። ያለፍንበት ጊዜና ያሳለፍናቸውም ጊዜዎች ቀላል እንዳልነበሩ መገንዘቡ ይህን ያልህም ከባድ አይሆንም። በተለይም የመጣንበትንና በጣም ኋላ-ቀር የነበረውን ሁኔታ አሁን ካለንበትና በኮምፕዩተር እየጻፍን ሃሳብችንን በምንለዋወጥበት፣ መኪና እየነዳን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ መሄድ መቻላችንና፣ ከዛሬ ሰላሳና አርባ ዓመት ከነበረን የኑሩ ሁኔታ ጋር የዛሬውን አኗኗራችንን ስናነፃፅረው ዛሬ በልዩ ዓለም ውስጥ እንዳለን መገንዘቡ ከባድ አይሆንም። ስንቶቻችንም ወደ ኋላ ጉዞ በማድረግ የተወለድንበትን መንደር፣ ያደግንበትንና ብዙ ውጣ ውረዶችን አሳልፈን እዚህ ደረጃ ላይ የደረስንበትን ሁኔታ እንደምንቃኝ ማወቅ በጣም አስቸጋሪ ነው። ከራሴ ሁኔታ ብቻ ስነሳ ከአንድ ትንሽ መንደር ቢያንስ አምስት ሺህ ሰው ከማይበልጥበት መንደር ተወልጄና አድጌ እዚህ ደረጃ ላይ መድረሴንና፣ የዓለምን ፖለቲካ ብቻ ሳይሆን፣ የየህብረተሰብ ዕድገቶችን ዕድገትና፣ አንደኛው ለምን አደገ፣ ሌላውስ ለምን ለማደግ አልቻለም፣ ወይም የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት ለመሆን አልቻለም? ብዬ ራሴን  ስጠይቅና ከሞላ ጎደል መልስ ለማግኘት ሙከራ ሳደርግ በአስተሳሰቤ የተሻልኩ መስሎ ይታየኛል። ከሌሎችም ጋር ቁጭ ብዩ ስወያይና ስከራከር ይህ ሁኔታ በቀላሉ እንዳልተገኘ መገንዘቡ ብቻ ሳይሆን ይህ ዐይነቱ ውጤት የራሴ ጥረት ብቻም እንዳለሆነም እገነዘባለሁ። የአብዛኛዎቻችንም፣ በተለይም ተማርን የምንልና የፖለቲካ ዓለም ውስጥ ገብተን ተፍ ተፍ የምንልም ይህንን ዐይነቱን የውጣ ውረድ ጉዞ የተጓዝን ጥቂት የማንባል ነን። ይሁንና በተለይም ለፖለቲካ እንታገላለን ወይም ፖለቲከኛ ነን ስንልም ተልዕኮ እንዳለንና ይህም በተግባር መመንዘር እንዳለበት ስንቶቻችን እንደተገነዘብንና  እንደምንገነዘብም ማወቅ አስቸጋሪ ነው።

ወደ ዋናው መሰረተ-ሃሳብ ልምጣና ያም ተባለ ይህ አንድ ሰው ወይም በድርጅት የተደራጁ ሰዎች ፖለቲከኛ ነን ሲሉ ፖለቲካ ሙያቸው እንደሆነ መገንዘብ አለባቸው። ፖለቲከኛ ነኝ ማለቱም ብቻ አይበቃም። አንድ ሰው ወይም በቡድን የተደራጀ ሰው ፖለቲከኛ ነኝ ሲል በመጀመሪያ ደረጃ በአንድ አገር ውስጥ የሚኖርን ህዝብ ዕድል ወሳኝ ነው ማለት ነው። በፖለቲካ ስም የሚፈጽመው ወይም የሚሰራው ነገር በመጀመሪያ ደረጃ ራሱን ለመጥቀም ሳይሆን በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብን ነው። ከዚህ ሀቅ ስንነሳ በተለይም እንደኛ አገር ባለው ውስጥ በፖለቲካ ስም እዚያና እዚህ የሚሯሯጡና ፖለቲካ ነኝም የሚሉ የቱን ያህል የፖለቲካን ትርጉም ተረድተዋል? የፖለቲካ ትምህርት በየትምህርትቤቶች ውስጥ በትምህርት መልክ በሚሰጥበት ጊዜ  እንደማንኛውም ሙያ መማሪያና መሰልጠኛ ተብሎ ነው የሚሰጠው? አንድንም ነገር የሚያስጨብትና እንደማንኛውም ሙያ የሚቆጠርና በተግባርም የሚመነዘር ነው ወይ? ወይስ የፖለቲካ ዋናው ተልዕኮ ጥፋትና አንድን አገር ማተረማመስ? አንድን ህዝብ ዘለዓለማዊ ስቃይ ውስጥ በማስገባት ታሪክን እንዳይሰራ ማድረግእነዚህን የመሳሰሉትንና ሌሎችንም ጥያቄዎችን ስናነሳ ብቻ ነው መልስ ማግኘት የምንችለው።

በተለይም በዩኒቨርሲቲ ወስጥ ገብተው ፖለቲካን የሚመርጡ ተማሪዎች ፖለቲካን እንደሳይንስ ነው የሚማሩት። ትምህርቱም የፖለቲካ ሳይንስ ሲሆን፣ በመጀመሪያ ደረጃ መሰረቱም ፍልስፍና ነው። ፍልስፍና ደግሞ የተፈጥሮን ትርጉም በመረዳት፣ በተለይም የሰው ልጅ ከየት እንደመጣ፣ በዚህች ዓለም ላይ ለምን እንደሚኖርና ወዴትስ እንደሚያመራ ለመረዳት የሚያስችለንና አዋቂም እንድንሆን የሚያስተምረን ነው። ስለሆነም ፖለቲካ ሳይንስ ተብሎ በትምህርት መልክ በሚሰጥበት ጊዜ በጭንቅላት ምርምር አማካይነት የአንድን ህብረተሰብ የተወሳሰቡ ችግሮች መፍቺያ መሳሪያ ነው። ስለዚህም ነው ሳይንስ የሚባለው። ለምሳሌ አንድ ተማሪ ከተፈጥሮ ሳይንስ ጋር የተያያዘውን ወይም የተፈጥሮ ሳይንስ አካል የሆነውን ፊዚክስ በሚማርበት ጊዜ የመጨረሻ መጨረሻ የሚሰራው አንድ መሳሪያ የሰውን ልጅ ለመጉዳት ተብሎ ሳይሆን የሰውን ልጅ ለመጥቀም ወይም ኑሮውን ለማቃለል ነው። በሌላ ወገን ግን በተበላሸ ግንዛቤና የአገዛዝ አወቃቀር የተነሳ የሰውን ልጅ ኑሮ ለማቃለል የተፈጠረው ሳይንስ የሰውን ልጅና ተፈጥሮን ለማወደሚያ ሲውል እናያለን። ስለሆነም ሳይንስ፣ በተለይም ደግሞ የተወሰኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶች የመጨቆኛና ጦርነትን ማካሄጃ በመሆን በአጠቃላይ ሲታይ የሳይንስንና የቴክኖሎጂን ትርጉም እንዳንረዳ ተደርገናል። በተለይም ምሁራዊ እንቅስቃሴ እጅግ ደካማ በሆነበት እንደኛ ባለ አገር ውስጥ ከውጭ የሚመጣ የተወሰነ ቴክኖሎጂ የሰውን ልጅ ለመግደያ፣ ለማስፈራሪያና ለማሰቃያ ሲውል እናያለን። ይህ ዐይነቱ የተሳሳተ ግንዛቤና ስልጣንም ላይ የሚወጡ ሰዎች በገለብ ገለብ ያለ ትምህርት የተማሩ ስለሆነ ቴክኖሎጂን እንደማስፈራሪያ በመጠቀም ከሌላው የተሻሉ ወይም የበለጡ እንደሆኑ ለማረጋገጥ ይሞክራሉ።    

ለማንኛውም በመጀመሪያ ደረጃ መታወቅ ያለበት ጉዳይ እንደማንኛውም ሙያ ፖለቲካ ራሱ ተፈጥሮአዊ ስጦታን የሚጠይቅ ነው። ለምሳሌ አንድ ጭንቅላቱ ለፊዚክስ ወይም ለሂሳብ ያልተፈጠረ ሰው ፊዚክስ ወይም ሂሳብ ልማር ብሎ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በሚመዘግበት ጊዜ ከፍተኛ ችግር ውስጥ ይወድቃል። በመሰረቱ በተለይም እንደጀርመን የመሳሰሉ አገሮች ውስጥ አንድ ሰው በተለይም ከበድ ባሉ ትምህርቶች ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ገብቶ ለመማር የሚፈቀድለት የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ በነበረበት ጊዜና ያመጣውን ውጤት ታይቶ ነው ፊዚክስን፣ ሂሳብንና እንደህክምና የመሳሰሉትን ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ገብቶ መማር የሚፈቀድለት። ይሁንና አንዳንዱ ዕድል አጋጥሞት የመማር ዕድል ያጋጠመው የፊዚክስንና የሂሳብን ትምህርት ተፈጥሮአዊ ስጦታ እንዳለው ተማሪ በቀላሉ ለመቅሰም እንደማይችልና ችግር ውስጥ እንደሚወድቅ ግልጽ ነው። በሌላ ወገን፣  ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ገብቶ የፖለቲካ ሳይንስን ለመማር የሚፈልግ ልጅ  ይህን ያህልም ብዙ ውጣ ውረድን የሚጠይቅ ነገር ባይሆንም፣ በመሰረቱ አንድ ሰው የፖለቲካ ሳይንስን ለመማር ሲፈልግና ፖለቲከኛም ለመሆን እፈልጋለሁ ሲል በመጀመሪያ ደረጃ ተፈጥሮአዊ ስጦታ ያስፈልገዋል። ስጦታው ደግሞ የሰውን ልጅ ስነ-ልቦና ማንበብና የህብረተሰብ ችግሮችንም በመፍታት የሚገለጽ ነው። ይሁንና ግን የዓለምን የፖለቲካ ሁኔታ ስንመለከት በየአገሮች ውስጥ ስልጣን ላይ የሚወጡት አብዛኛዎቹ የፖለቲካ ሳይንስን ትምህርት ያልተማሩ ወይም ደግሞ በምሁራዊ እንቅስቃሴና ትምህርት ዓለም ውስጥ ከፖለቲካ ሳይንስ ውጭም ከሌሎች ነገሮች፣ ለምሳሌ አንትሮፖሎጂ፣ ሶስዮሎጂ፣ ሰለ ኢኮኖሚክስ ታሪክና ስለተለያዩ የኢኮኖሚክስ ፖሊሲዎች አመለካከቶችና፣ ለምንስ አንደኛው ከሌላው ይለያል? በማለት ተምረውና በተግባርም በመንደር ደረጃ አረጋግጠው የሚወጡ ሳይሆን በአንድ ኃይል ተለቅመው የሚወጡና የአንድን የተወሰነ የህብረተሰብና ክፍልና የዓለም አቀፍ ኮሙኒቱውን ጥቅም ለማስጠበቅ የሚቀመጡ ናቸው። ስለሆነም በቂና ጠለቅ ያለ ስለህብረተሰብ አወቃቀርና ለጠቅላላው ህዝብ የሚሆን ብሄራዊ ሀብት ለመፍጠር የማይችሉ ግለሰቦችና ቡድኖች ስልጣን ላይ በሚወጡበት ጊዜ አንድን ህብረተሰብ ማዘበራረቅ ይጀምራሉ። ሰላም ሊያመጣና ህዝባዊ መቻቻልን ሊያጎናጽፍ የሚችል የህብረተሰብ አወቃቀርን ከመፍጠር ይልቅ በተበላሽ ወይም ኢ-ሳይንሳዊና ኢ-ፍልስፍናዊ የሆነ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ በማድረግ በቀላሉ መፍትሄ የማይገኝለት ህብረተብአዊ ቅራኔን ይፈጥራሉ። በተጨማሪም የስነ-ልቦናና የባህል ቀውስ እንዲፈጠር በማድረግ የተወሰነው የህብረተሰብ ክፍል በስቃይ ዓለም ውስጥ እንዲኖር ያደርጋሉ። በአገራችን ምድር አማኑዔል በሚባለው ሆስፒታልና በሌሎችም የስነ-ልቦና ህክምና የሚሰጥባቸው ሀኪም ቤቶች ውስጥ ያለውን ሁኔታና የታካሚውንም ብዛት ስንመለከት ይህ ሁሉ ሊፈጠር የቻለውና የሚችለው ስለሰው ልጅና ስለህብረተሰብ አወቃቀር ምንም ዐይነት ግንዛቤ የሌላቸው ግለሰቦችና ቡድኖች ስልጣን ላይ በሚወጡበት ጊዜ ነው።  

በአገራችንም  ሆነ በተቀሩት የአፍሪካ አገሮች ያለው ትልቁ ችግር አብዛኛዎች ስልጣን ላይ የሚወጡ፣ ስልጣንም ላይ ሳይወጡ በደፈናው እኔ ፖለቲከኛ ነኝ የሚሉ ፖለቲካ ማለት ምን ማለት እንደሆነ የማይረዱና፣ ስልጣን ላይ በሚወጡበት ጊዜም  የብዙ ሚሊዮኖችን ህዝቦች በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ፣ በስነልቦና፣ በባህልና በልዩ ልዩ የአኗኗር ሁኔታዎች የሚገለጹ የተወሳሰቡ ችግሮችን ለመፍታት የማይችሉና፣ ሰው ማለትም ምን ማለት እንደሆነ የማይገነዘቡ ናቸው። በተወሳሰበ መልክ ማሰብ የማይችሉና ተጨባጭ ሁኔታዎችን በማንበብ ስርዓት ባለው መንገድና ኦርጋኒክ በሆነ መልክ የአንድን ህብረተሰብ ችግር ከታች ወደላይ ለመፍታት የሚችሉ አይደሉም። ስለሆነም በአብዛኛዎቹ የአፊካ አገሮችና አገራችንንም ጨምሮ  ፖለቲካ እንደ ችግር መፍቻ መሳሪያ መሆኑ ቀርቶ ስልጣንን ማጎልመሻና ሀብትን ማዘረፊያ መሳሪያ ለመሆን በቅቷል። ከዚህ በአፍጢሙ ከተደፋ አስተሳሰብ ስንነሳ ፖለቲካ ሳይንስ እንደመሆኑ መጠን አዳዲስ ችግሮችን በመፈልፈልና በመፍጠር የአንድን አገር ህዝብ መቆሚያና መቀመጫ የሚያስጣው ሳይሆን ችግሩን መፍቺያ መሆን አለበት። ፖለቲካ ፖለቲካ መሆኑንም መረዳት የሚቻለው ህዝባዊ ባህርይ ሲኖረውና፣ እያንዳንዱ የህብረተሰብ ክፍልም የመንቃት፣ የመማር፣ ራሱን የማወቅና የመደራጀት መብት ሲኖረውና በዚህም አማካይነት ሳፈራ ሳይቸር ራሱን መግለጽ ሲችል ብቻ ነው። በዚህ መልክ ፖለቲካ ሲዋቀርና ህዝባዊ ተሳትፎም እንዲኖረው ሲደረግ ማንም ግለሰብ የሚዘባርቅበትና ህዝብን የሚያወናብድበት ሁኔታ አይፈጠርም ማለት ነው። አንደኛው ሌላውን በጣፈጡ ቃላቶች በመሸወድ እንደፈለገ የሚወራጭበት ሁኔታ አይኖርም ማለት ነው። ፖለቲካ ከሳይንስ አንፃር መታየት ያለበትና ሎጂካው በሆነ መልክ በማሰብ የህብረተሰብን አወቃቀርና ችግሮችን በመረዳት  ችግር መፍቺያ መሳሪያ እንደመሆኑ መጠን የፖለቲካ መድረክ ለማንኛውም አወናባጅ ሰውና ድርጅት ክፍት መሆን የለበትም። 

ስለሆነም  አንድ ሰው ፖለቲከኛ ለመሆን ከመነሳቱ ወይም ከማሰቡ በፊት ብዙ ዓመታት ወስዶ የፖለቲካ ትርጉምን ለመረዳት ከልዩ ልዩ ዕውቀቶች ጋር መተዋወቅ አለበት። ምክንያቱም ፖለቲካ ከህብረተሰባዊ ዕድገትና ክንዋኔዎች ተነጥሎ የማይታይ ነገር ስለሆነና፣ ከብዙ ዕውቀቶች ጋር የተሳሰረ ስለሆነ፣ አንድ ሰው ፖለቲከኛ ለመሆን ከመፈለጉ በፊት በተለይም ከፍልስፍና ዕውቀት ጋር በሰፊውና በጥልቀት መተዋወቅና ማጥናትም አለበት። ይህ ግልጽ ሲሆንለት፣ እንደ ኢኮኖሚክስ የመሳሰሉትንና ሌሎችንም ዕውቀቶች በመረዳት፣ ፖለቲካ ስነ-ምግባርን፣ ሎጂካዊ አስተሳስብን የሚጠይቅና ጥበባዊም ነገር እንደሆነ መረዳት ይችላል። በዚህ ዐይነት ምሁራዊ ሂደት ውስጥ ያላለፈ ዝም ብሎ ፖለቲከኛ ነኝ ብሎ ስልጣን ላይ የመውጣት ዕድል የሚያጋጥመው ከሆነ መቶ በመቶ እንደዚህ ዐይነቱ ሰው አምባገነን በመሆን አገሩንና ህዝቡን ያተረማምሳል። ስለሆነም ፖለቲካ እንደተራ ሙያ ብቻ የሚታይ ሳይሆን ብዙ ነገሮችን በማካተት በአንድ አገር ውስጥ ታሪክን መስሪያና ለተከታታዩ ትውልድ ቋሚ ነገር ማስተላለፊያ የሆነ ልዩ ዐይነት ዕውቀት መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል

የፖለቲካ አስተሳሰብ ለምንና እንዴትስ ሊፈጠር ቻለ

ችግር ወይም ጭንቀት የመፍጠር እናት(Necessity is the Mother of Invention) ወይስ ፖለቲካን የሰው ልጅ በከፍተኛ ችግር ውስጥና በጦርነት ምስቅልቅሉ በወጣበት ዘመን በአምላከ ከላይ ወደ ምድር የተላኩ ሰዎች የፈጠሩት ነገር? የሰውን ልጅ ዕድገት አንትሮፖሎጂካሊ ስንመረምረውና የጊዜም ጉዞ ስናደርግ ከዝቅተኛ ደረጃ በመነሳት የተወሳሰቡ ነገሮችን እንደፈጠረ፣ ከተማዎችንና መንደሮችን እንደገነባም፣ የስራክፍፍልና ገበያን፣ እንዲያም ሲል የመገበያያ ገንዘብን እንደፈጠረ እንገነዘባለን። ከዚያም በላይ በአንድ የተወሰነ የዕድገት ታሪክ ላይ የተፈጥሮ ሳንይንስና ማቲማቲክስን በመፍጠር ልዩ ዐይነት ዕምርታን በማግኘት ለቴክኖሎጂ ማፍለቂያ መሳሪያዎች መሰረት እንድተጣለ ይታወቃል።

ወደ ፖለቲካ ስንመጣም የፖለቲካ አስተሳሰብ የተፈጠረው በግሪኩ የጥንት የስልጣኔ ዘመን ነው። በመጀመሪያው ወቅት በየጊዜው የሚከሰቱት የተፈጥሮ አደጋዎችና ጎሳን አሳቦ የሚካሄዱ የርስ በርስ ጦርነቶች በአምላኮች ፈቃድ በሚያስፈልጋቸው ጊዜ ወይም ደስ ሳይላቸው የሚከሰቱና በእነሱም የሚላኩ ነው ተብሎ ይታመን ነበር። ይሁንና ይህ አስተሳሰብ ውድቅ በመሆን  የኋላ ኋላ  በተነሱ ፈላስፋዎች የተደረሰበት ምርምር በተፈጥሮ ውስጥ የሚከሰቱ ልዩ ልዩ አደጋዎች የተፈጥሮ ህጎች ሲሆኑ፣ ተፈጥሮ በአጠቃላይ ሲታይ ተንቀሳቃሽ ስለሆነች በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ ከፍተኛ የውሃ ሙላት ይክሰታል፤ የመሬት መንቀጥቀጥም ይፈጠራል። ሌሎች የተፈጥሮ አደጋዎችም እንደዚሁ በመፈጠር የሰውን ልጅ አደጋ ውስጥ ይጡልታል። በአሁኑ ወቅት ደግሞ የአየር ለውጥ(Climate Change) የሚከሰቱቱ ተፈጥሮአዊ ቀውሶች፣ ለምሳሌ አየሩ ከሚያስፈልገው መጠን በላይ መሞቅ፣ በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ የውሃ ሙላት መከሰት፣ የመሬት መሸንራተት መታየትና. በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን አደጋ ውስጥ መክተት፣ እነዚህ ሁሉ  ባለፉት  ሶስትና ሁለት መቶ ዓመታት ከተፈጥሮ ህግ ጋር ሳይነፃፀር  በዕድገት ስም ተግባራዊ የሚሆነው ፖሊሲና በተለይም የኢንዱስትሪ ፖለቲካ የካፒታሊዝም በፍጥነት ማደግና፣ ካለአግባብ የብዙ መቶ ዓመታት ዕድሜ ያላቸውን ዛፎች መቁረጥና አንድን አካባቢ ወደ ምድረ-በዳነት መለወጥ ለተፈጥሮ አደጋ መከሰት ምክንያት እንደሆኑ የአየር ጠባይ ተመራማሪዎች ያስተምሩናል። በተለይም እንደኛ ባለው አገር ውስጥ ስለተፈጥሮና ስለአካባቢ ምንም ዐይነት ግንዛቤና፣ በተለያዩ ጊዜያት የሚከሰቱ የተፈጥሮ አደጋዎችን የሚከታተልና የሚያጠና ሳይንሳዊ ተቋም በሌለበት አገር ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የተፈጥሮ ሀብትን ከማውደሙ ባሻገር፣  ህዝባችንን ከፍተኛ የሆነ የማህበራዊና የስነ-ልቦና ቀውስ እንደከተተው መረዳቱ ከባድ አይሆንም። ያም ተባለ ይህ ይህ ሁሉ ነገር የሚፈጠረው በአምላክ ቁጣ ሳይሆን በተለይም ፖለቲከኛ ነን ባዮችና የተማሩ ሰዎችም ሎጂካዊ በሆነ መልክ ማሰብ ስለማይችሉና፣ ከዚህም የተነሳ ህብረተሰብአዊና ታሪካዊ ኃላፊነት እንዳለባቸው ስለማይረዱ ነው።

ወደ ጦርነት ጋ  ስንመጣም ጦርነት አምላኮች የሰውን ልጅ ለማናደድ ወይም ለመቅጣት የሚልኩት ውርጅብኝ ሳይሆን የሰው ልጁ የማሰብ ኃይሉ በጣም ደካማ ከሆነ ወይም ደግሞ የግራጫ-ሴሎቹ በደንብ ያልታያያዙ ከሆነና፣ በዚህም አማካይነት አርቆ-ማሰብ ካልቻለ አንድን ሁኔታ ከተለያዩ ሁኔታዎች አንፃር ስለማይመለከት ወይም ግንዛቤ ስለማያደርግ በስሜት ብቻ በመነዳት ወደ ጠብ ጫሪነት ያመራል። ከዚህ ሁኔታ ስንነሳ ከሶክራተስና ክፕሌቶ በፊት የቀደሙት እንደነ ሄራክሊተስ የሚባሉት የተፈጥሮ ፈላስፋዎች በንግርት(Mythyology) ላይ ሳይሆን በሰው ጭንቅላቱና በድርጊቱ ላይ ነው ማተኮር የጀመሩት። በጊዜው ይታይ የነበረው የስራ-ክፍፍል መዳበር፣ የንግድ ልውውጥና በዚህም አማካይነት የተፈጠረው የርስ በርስ ግኑኝነት ለተፈጥሮ ፈላስፎች ለመመራመር መነሻ በመሆን የሰው ልጅ በማሰብ ኃይሉ ራሱን እንደሚለውጥ ነው ልመገንዘብ የቻሉት። ስለሆነም በግሪክ ፈላስፋዎች ዕምነት፣ ትክክልኛ ዕውቀትና ሎጂካዊ በሆነ መልክ ማሰብ በጭንቅላት አማካይነት የሚፈጠሩ ናቸው። በሌላ ወገን ደግሞ ተፈጥሮንና የህብረተሰብን ህግ በትክክለኛ መንገድ ካለማንበብ የተነሳና፣ የተወሰነውን የህብረተሰብ ክፍል ለመጥቀምና፣ አብዛኛውም ህዝብ እንደከብት እየተነዳ እንዲኖር ለማድረግ የተፈጠሩና የሚፈጠሩ ዕውቀት የሚመስሉ ነገሮች አሉ። በተለይም ይህ በተወሰኑ ምሁራን ነን በሚሉ ኢኮኖሚክስን ከሌሎች የህብረተሰብ ግንባታ ዕውቀቶች ጋር ከማያያዝ ይልቅ ብቻውን እንደሚጓዝና፣ የሰውም ልጅ የመጨረሻ መጨረሻ ዓላማ በኢኮኖሚክስ  ብቻ የሚገለጽና፣ ይህም ጉዳይ በገበያ ኢኮኖሚ አማካይነት ብቻ የሚሟላ(Market Fundamentalism) ነው በማለትና አንድን ህብረተሰብ ወደ ተራ የመገበያያ መድረክ በመለወጥ የብዙ ቢሊዮንን ህዝብ መንፈስ ለማቃወስ ችለዋል። እነዚህም ኒዎ-ክላሲካል ወይም ኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚስቶች በመባል የሚታወቁና በዓለም አቀፍ ደረጃ እንደሰንሰለት በመተሳሰር በየአገሮች ውስጥ የጥሬ-ሀብትን በመዝረፍና በማዘረፍ፣ ማህበራዊና የኢኮሎጂ ቀውስ በመፍጠር የሰው ልጅ ከተፈጥሮ ጋር ያለውን ግኑኘነት በመበጠስና በተፈጥሮም ላይ ዘመቻ በማድረግ ሚዛናዊ የሆነ ኑሮ እንዳይኖር እያደረጉት ነው። ስለሆነም በዕውነተኛ ዕውቀትና በተሳሳተ ወይም ደግሞ በርዕዮተ-ዓለም በታጠረ ዕውቀት በሚመስል መሀከል ያለውን ትልቅ ልዩነት መገንዘብ በተለይም ለፖለቲካ ስልጣን የሚታገሉና ፖለቲካም ያገባኛል ለሚሉ ሰዎች ግልጽ መሆን ያለበት ጉዳይ ነው።

ከዚህ ሁኔታ ስንነሳ የመጀመሪያውን የፖለቲካ ፍልስፍና ያዳበሩት ሶክራተስና ፕሌቶ ያተኮሩትም በየጊዜው ጎሳን አስታከው የሚፈጠሩት የርስ በርስ ግብግቦች ወይም ጦርነቶች የሰው ልጅ አርቆ ማሰብ ያልቻለ እንደሆነ ብቻ ነው። የሰው ልጅም አርቆ ማሰብ የማይችለው ጭንቅላቱ በጥሩ ዕውቀት ከልጅነቱ ጀምሮ በደንብ ያልተኮተኮተና ያልዳበረ ከሆነ ብቻ ነው። ስለሆነም እንደ ስነምግባርና(Ethics) ግብረ-ገብነት፣ እንዲሁም ጥበብ የመሳሰሉት ነገሮችን በመፍጠር፣ የሰውንም ልጅ ከዝቅተኛ የአደረጃጀት ወደ ተሻለና ከፍ ወዳለ የአደረጃጀት ሁኔታ መሸጋገርን በመረዳት በፖለቲካ ዓለም ውስጥ ሊሳተፍ የሚችል የተመረጠና ጭንቅላቱም ከልጅነቱም ጀምሮ በጂኦሜትሪ፣ በቋንቋና በጥሩ አነጋገር፣ እንዲሁም በጂምናስቲክ መቀረጽ እንዳለበት በመረዳት ፖለቲካና ስነ-ምግባር ወይም ፖለቲካ የግዴታ በሞራል መደገፍ እንዳለበት በማስተማር የመጀመሪያውን የፖለቲካ ቲዎሪ ማዳበር ቻሉ። ስለሆነም በጊዜው የሰብአዊነት የትምህርት ዘዴ(Humanisitic School of Thought) የተስፋፋና ተከታታዩ ትውልድም በዚህ ዐይነቱ የትምህርት ዘዴ ጭንቅላቱ ከህፃነንቱ ጀምሮ ከተቀረፀና ከታነፀ ስራው ሁሉ ሰላማዊና ጥበባዊ ይሆናል የሚል ነው። ይሁንና ግን ይህ ዐይነቱ ቀናና ትክክለኛ አስተሳሰብ ቀስ በቀስ እየተስፋፋ ቢመጣም ይህንን ቀና አስተሳሰብ የሚፃረሩ ሶፊስቶችና ለስልጣን የሚስገበገቡ በመፈጠር የሰብአዊነትን የትምህርት ዘዴ ለመቅጨት ቻሉ። ይህ ሁኔታ የግዴታ የሰውን ልጅ፣ በተለይም ስልጣን ላይ የወጡትንና የሃይማኖት መሪዎችን ጭንቅላት በማጨለም ተግባራቸው ሁሉ ጦርነትና መስገብገብ፣ ፕሌቶ ስግብግብነትና ለስልጣን መቋመጥ(Power & Greed) የሚለው በማየል ፖለቲካ የመማሪያ፣ ጭንቅላትን የማዳበሪያና አገርን የመገንቢያና ሰላምን የሚያመጣ መሆኑ ቀርቶ ፖለቲካ ላይ የሚወጡ ሰዎች ዋናው ተግባራቸው ርስ በርስ መከሳከስ ሆነ። ሀብትንም በማግስበስበስ ራሳቸውን ማደለብ ሆነ። በዚህም የተነሳ የኋላ ኋላ ላይ የአቴን ኢምፓየር፣ ቀጥሎ ደግሞ የሮማውያን ኢምፓየር ሊፈረካከስ ቻለ። በስልጣን መባለግና በኃይል መመካት የመጨረሻ መጨረሻ አገርንና ማህበረሰብን እንደሚያፈራርስ በታሪክ ውስጥ በተደጋጋሚ ተረጋግጧል። ይህ ሁኔታ አሜሪካን ውስጥም እንደሚከሰትና የአሜሪካንም ኢምፓየር ወይም ኃያልነት እንደሚያፈራርስ ብዝ ጥናቶች ያረጋግጣሉ።

በአውሮፓ ምድር የጨለማው ዘመን እስከ አስራ ሰባተኛው ክፍለ-ዘመን ድረስ በመዝለቅ የኋላ ኋላ ላይ ለተነሱት የእንግሊዝና የጀርመን ፈላስፎች በግሪኩ የፖለቲካ ፍልስፍና ላይ በመመርኮዝ የፖለቲካል ቲዎሪዎቻቸውን ማዳበር ቻሉ። የአውሮፓ ህዝብና በኋላ ላይ ብቅ ያሉት ፈላስፎች ይህንን አዲስ የፖለቲካ ቲዎሪ ማዳበር በአውሮፓ ምድር ሬናሳንስና የፕሪቴስታንት ሃይማኖት የጥገና ለውጥ ካካሄዱ በኋላ ነው። ይህ ሁሉ የመንፈስ ተሃድሶ ተደርጎና፣ የዕደ-ጥበብ ስራና ንግድ ተስፋፍተው፣ የማዕከለኛው ክፍለ-ዘመን ከተማዎች በዕቅድና በአማረ መልክ ተገንብተው ስልጣን ላይ የሚወጡ ሰዎች ጭንቅላታቸው ሁልጊዜ በጦርነት የተያዘና የሚሰራውንና የሚፈጥረውንም ሰው ሁሉ ጦርነት ውስጥ እንዲገባ በማድረግ የዕድገትን ጉዞ መቅጨት ነበር። ይህንን በሚገባና በጥልቀት ያጠኑና፣ የጊዜውም ሁኔታ ስለደገፋቸውና አዳዲስ ሰላምን የሚፈለጉ ኃይሎች በመፈጠራቸው እንደ ጆን ሎክ የመሳሰሉ ምሁሮች አዲስ የፖለቲካን ቲዎሪ በማደበር ስልጣን ላይ የሚወጣ ግለሰብ ስልጣኑን ተጠቅሞ ህብረተሰብአዊ ጉዳት እንዳያደርስ የግዴታ የተወሰኑ የአሰራር መካኒዝሞች መፈጠር እንዳለባቸው ማስተማር ቻሉ። ስለሆነም የህግ የበላይነት የሚለውና፣ የአንድን ሰው ስልጣን የሚገድብ ሶስት የአደረጃጀት መሰረቶች ተጣሉ። ህግ አውጭ፣ ህግ አስፈጻሚና ስልጣንን የሚቆጣጠርና(Excutive) ቢሮክራሲው ጨምሮ የመንግስት አካል በመሆን፣ በተለይም የመንግስትን መኪና የሚቆጣጠረው ማንኛውንም ነገር ብቻውን ማድረግ እንደሌበትና፣ የሚያደርግም ከሆነ በህግ እንደሚጠየቅና እንደሚከሰስ ሰፋ ያለና ተቀባይነትን ያገኘ የፖለቲካ ቲዎሪ ሊስፋፋና ተቀባይነትም ሊያገኝ ቻለ። በሌላ ወገን ደግሞ በጀርመን ምድር የተፈጠሩት፣ እንደላይብኒዝ፣ ካንትና ሄግል የመሳሰሉት ፈላስፋዎች የህግ የበላይነት ብቻውን እንደማይበቃ በማስገንዘብ በጭንቅላት ላይ ከፍተኛ ስራ መሰራት እንዳለበት በማስገንዘብ፣ በተለይም ስልጣን ላይ የሚወጡ ግለሰቦች የግዴታ ሞራላዊ ብቃትና ስነ-ምግባር እንዲኖራቸው ያስፈልጋል የሚል ቲዎር አዳበሩ። አንድ ሰው ወይም ቡድን የሞራል ብቃት ሲኖረው ነው የህግን የበላይነት ሊገነዘብና ሊያከብር የሚችለው። 

ለማንኛውም በአውሮፓ ምድር ውስጥ የህግ-የበላይነት ይበልጥ ተግባራዊ መሆን የጀመረው በተለይም ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ ነው። ይሁንና ግን አሁንም ቢሆን የመንግስትን መኪና በራሳቸው ቁጥጥር ስር ለማድረግ የቻሉና፣ አዳዲስ ህጎችን ለሀብታሞች እንዲስማማ ተደርጎ በአብዛኛዎቹ የካፒታሊስት አገሮች ውስጥ በሽወዳ እንደሚፀድቅ የሚታወቅ ጉዳይ እንደሆነ የታወቀ ነው። እነዚህ በሀብት የናጠጡና ቴክኖሎጂዎችን የሚቆጥጠሩና ከሚሊተሪ-ኢነስትሪ ውስብስብ  ጋር የተሳሰሩ ኃይሎች የመንግስት መኪና በተዘዋዋሪ በመቆጣጠር ጥልቀት ያለውና የረቀቀ መንግስት ለመፍጠራ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጦርነትን ለማካሄድ ችለዋል። አሜሪካን አገር ኮንግረስ አካባቢና እዚህ ጀርመን ደግሞ ፓርሊያሜንት አካባቢና፣ የአውሮፓ አንድነት መቀመጫ አካባቢ ብረሰልስ ሀብታሞች ወይም የኢንዱስትሪ ባለቤቶች ቢሮ በመክፈትና ህግ አውጭዎችን በሙስና በማባለግ ህግ ለእነሱ በሚስማማ መንገድ እንዲወጣ በማድረግ በተዘዋዋሪ መንግስታትን ይቆጣጠራሉ። ይህ ግልጽ ናየሚታወቅ ጉዳይ ሲሆን እንደ ኮንስፒራሲ ቲዎሪ መወሰድ የለበትም።

በአጠቃላይ ሲታይ የካፒታሊዝም መዳበርና ምጥቀትን ማግኘት በተለያየ ዕውቀት ላይ የሚረባረቡና የሚጽፉ ሰዎች እንዲፈጠሩ ለማድረግ በመቻሉ አንድ አስተሳሰብ ብቻ የበላይነት ይዞ አምባገነናዊ ሁኔታ እንዳይፈጠር ለማድረግ ተችሏል። ስለሆነም አንድ ግለሰብ ወይም ጥቂት ሰዎች በራሳቸው ስሜት እየተነሱ አንድን ህዝብና አገር እንደፈለጋቸው የሚያተረማምሱበትና አገራቸውንም ወደ ጦር አውድማነት የሚለውጡበት ሁኔታ የለም። ይህ ማለት ግን አደገኛ ሁኔታ ሊፈጠር አይችልም ማለት አይደለም። በተለይም የራሳቸውን የበላይነት ላለማጣት የሚፈልጉ እንደ አሜሪካ የመሳሰሉ ኃያላን መንግስታት ሌሎችንም በማካተት ጦርነትን በየቦታው ስለሚቀሰቅሱ በተለይም እንደው አውሮፓ የመሰለ አህጉር መስቀልያ መንገድ ላይ ይገኛል። ያም ሆነ  ይህ ካፒታሊዝም ለልዩ ልዩ ዕውቀቶች መዳበር አመቺ ሁኔታዎችን በመፍጠር ሰፋ ያለና በዚያው መጠንም ጦርነትንና ማህበራዊ መዛባትን የማይፈልጉና አጥብቆም የሚከራከሩ በግልጽ ወጥተው ስልጣን ላይ ካሉት ሰዎች ጋር በመጋፈጥና በመከራከር ገደባቸውን ለማሲያዝ የሚችሉበት ሁኔታ ሊፈጠር ችሏል። በተለይም በአሁኑ በኢንተርኔትና በዩቱቭ ዘመን ደግሞ በጣም ግሩም ግሩም የፖለቲካ፣ የፍስልፍናና የሳይንስ ሰዎች በመነሳትና በጥልቀት በመጻፍ እስከተወሰነ ደረጃ ድረስ ፖለቲካን መቆጣጠር ችለዋል። አንዳንዶችም የትምህርት አሰጣጡ እንደገና መጠናትና የጥንቱ የሰብአዊነት የትምህርት አሰጣጥ ዘዴ በመስፋፋት አዳዲስ ትውልድ መፈጠር አለበት ብለው የሚከራከሩና የሚጽፉ አሉ። እኛም እነዚህን ከመሳሰሉና ጥልቅ ዕውቀት ካላቸው ምሁራን የምንማራቸው አያሌ ነገሮች አሉ። አንድን ህብረተሰብና የፖለቲካን አወቃቀር ሰፋ ባለና በሰለጠነ ምሁራዊ እንቅስቃሴ መቆጣጠር እንደሚቻል ከግሪክ ስልጣኔ አንስቶ እስካሁን ድረስ ያለውን የፖለቲካ ሁኔታ ለተከታተለ የሚገነዘብው ሀቅ ይህንን ነው። የፖለቲካ ቲዎሪና ፍልስፍና፣ የኢኮኖሚክስና የሶስዮሎጂ ዕውቀቶች፣ የተፈጥሮ ሳይንስና በጠቅላላው ለሰው ልጅ የሚጠቅሙና እንደማህበረሰብም እንዲኖር የሚረዱት ማንኛውም ዕውቀቶች የተፈጠሩትና ሊፈጠሩ የሚችሉት በፖለቲከኞች ሳይሆኑ ለሰው ልጅና ለህብረተሰብ ልዩ ዐይነት ተልዕኮ አለኝ ብለው በሚነሱ ግለሰቦች አማካይነት ብቻ ነው። ፖለቲከኛ ነን ባዮች ከመጀመሪያውኑ ጭንቅላታቸው በሌላ ነገር ስለሚወጠር የማሰብ ኃይላቸው ይወሰናል።  ምህራዊ እንቅስቃሴና ኃይል በጣም ደካማ ወደሆነበት ወደ እኛ የመሰለው አገር ስንመጣ ደግሞ ፖለቲካ ወደ ተራ ተንኮል በመለወጥ ለጦርነትና ለማህበራዊ ውዝግብ መንስዔ ለመሆን በቅቷል። ስለሆነም ቅድሚያ መስጠት ያለብንና መሆንም ያለብትም ሰፋና ጥልቅት ለሚኖረው ምሁራዊ እንቅስቃሴ እንጂ ፖለቲከኛ ነን ብለው ለሚያወናብዱና የህብረተሰንና የተፈጥሮን ህግ ለማይረዱ ሰዎች መሆን የለበትም። ለዚህ ደግሞ የግዴታ በጭንቅላት ላይ ማትኮርን አዲስና ማሰብ የሚችል ትውልድን መፍጠር ያስፈልጋል።

በአገራችን ያለው ዋናው የፖለቲካ ችግር ምክንያት!

የመጀመሪያዎችን ስድስት ገጾች በጥሞና ላነበበና በሚገባ ለተረዳ በዛሬው ወቅት በአገራችን ምድር በፖለቲካ ስም የሚሰራውን ትልቅ የታሪክ ወንጀል ለመረዳት አይከብደውም። አገርን ማፈራረስ፣ ህዝብን ማሰቃየትና እንዲያም ሲል መግደልና ከቀዬው ማፈናቀል በሌላ መልክ ከድሮው የፖለቲካ ሁኔታ የቀጠለና በህብረተሰብአችን ታሪክ ውስጥ የበሰለና የተደራጀ ኃይል ባለመኖሩ ምክንያት ነው። በፖለቲካ ስም የሚነግዱና በህዝባችንና በአገራችን ላይ ጦርነት አውጀው ሃምሳ ዓመት ያህል ህዝብን የሚያሰቃዩ ግለሰቦችና ቡድኖች ጭንቅላታቸው ያልበሰለና የሚሰሩትን ስለማያውቁ ነው። ሰው መሆናቸውን የማይረዱም ናቸው። እንደሰው ይንቀሳቀሳሉ፣ እንደ ሰው ግን ማሰብ የሚችሉ አይደሉም። 

ለዛሬው የአገራችን ፖለቲካ መንስዔው ዋናው መሰረት አብዮት የሚባለው ነገር በአገራችን ምድር ስለፈነዳ ሳይሆን የተጣለው፣ በጊዜው ያንን ሁኔታ በሚገባ ለማስተናገድ የሚችል ኃይል ባለመኖሩና፣ አንዳንድ የታሪክንና የህብረተሰብን ህግና ሂደታ ባለመረዳት ስልጣንን ለመያዝ በመስገብገባቸውና፣ ሳያውቁት ለውጭ ኃይሎች በአገራችን ምድር ገብተው እንዲፈተፍቱ አመቺ ሁኔታዎች በመፍጠራቸው ነው። በተለይም በግራና በሶሻሊዝም ስም ይነግዱ የነበሩ ኃይሎች የፖለቲካን ትርጉም በሚገባ ባለመረዳታቸው ለቀደመው፣ ለአሁኑና ለመጭውም ትውልድ ትልቅ የቤት ስራ ጥለውለት አልፈዋል።

በመጀመሪያ ደረጃ መታወቅ ያለበት ጉዳይ በአገራችን ምድር እንደዚያ ዐይነት የርስ በርስ ሽኩቻና መገዳደል ሊፈጠር የቻለው የግራ ወይም የሶሻሊስታዊ አስተሳሰብ በመግባቱ ሳይሆን 90% የሚሆነው በፖለቲካ ትግል ውስጥ የተሳተፈው ጭንቅላቱ በሚገባ ያልዳበረና፣ ከጥሩ ዕውቀትም ጋር ያልተዋወቀ ስለነበረ ነው። ራሱንም ሶሻሊስት ወይም ግራ ነኝ ብሎ ይጠራ የነበረው ከተወሰኑ መጽሀፎች በስተቀር በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ስለሶሻሊዝም አስተሳሰብ የተጻፉና፣ በተለይም የማርክስና የኤንግልስን ኦሪጂናል መጽሀፎች ያላነበበ ነው። ከዚህም በላይ ማርክስና ኤንግልስ በአጠቃላይ ሲታይ ስለካፒታሊዝምና ስለህብረተሰብ ዕድገት ትችታዊ ጽሁፎችን ሲጽፉ ራሳቸውን ከፍልስፍናና ከተፈጥሮ ሳይንስ ጽሁፎች ጋር በማስተዋወቅ፣ በማንበብና በመመራመር ነው። አቀራረባቸውም ቀኖናዊ ያልሆነና በጊዜው ካፒታሊዝም እንደዚያ ዐይነቱ የተወሳሰበ የቴክኖሎጂ ደረጃ ላይ ሊደርስ የቻለው የተወሳሰቡ ሂደቶችን ያለፈ መሆኑን በመረዳታቸውና፣ በህይወታቸውም ዘመን የኖሩበት ሁኔታ ስለሆነ ነው። ማርክስም ሆነ ኤንግልስ ስለሶሻሊዝምና ስለተግባራዊነቱ ሲጽፉ፣ ሶሻሊዝም በአንድ አገር ውስጥ ተግባራዊ ሊሆን የሚችለው ሁለት ቅድመ-ሁኔታዎች ከተሟሉ በኋላ ነው የሚል ዕምነት ነበራቸው። ይኸውም አንደኛው አንድ ህብረተሰብ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ማደግ አለበት፣ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ፣ የሰፊው ህዝብ ንቃተ-ህሊና ማደግና የሶሻሊዝምን አስተሳሰብ ለመቀበል ዝግጁ መሆን አለበት። ከነዚህ ቅድመ-ሁኔታዎች በመነሳት ሶሻሊዝም በአንድ ወደ ኋላ በቀረ አገር፣ ማለትም የማቴሪያል ሁኔታዎችና የንቃተ-ህሊና መዳበር ባልተሟላበት አገር ውስጥ ተግባራዊ ሊሆን እንደማይችል በግልጽ ማስቀመጥ የቻሉት። ለማንኛውም ግልጽ መሆን ያለበት ነገር በተለይም የሶሻሊዝም ስም ሲነሳ የሚያንገበግባቸው ማወቅ ያለባቸው ነገር የገበያ ኢኮኖሚ ወይም ካፒታሊዝም የሰው ልጅ የመጨረሻው የአኗኗር ስልት እንዳልሆነ ነው። የገበያ ኢኮኖሚ የመጨረሻው ነው ብሎ ማሰብ የሰው ልጅ የማሰብ ኃይሉ ውስን ነው እንደማለትና ከአንድ የአኗኗር ስልት ወደ ሌላ አይሸጋገርም ብሎ እንደማሰብ ነው። በሌላ ወገን ደግሞ በተወሰኑ ኃይሎች አርቆ አለማሰብ የተነሳ ሌላ ዓለም አቀፋዊ ጦርነት በመነሳትና ከፍተኛ ጉዳት ካደረሰ በኋላ፣ ጦርነት ቆሞ  ሁሉም ነገር እንደገና ሀ ብሎ የሚጀመርበት ሁኔታ አለ። ስለሆነም የታሪክ መጨረሻ ብሎ ነገር የለም።

ስለሆነም በአገራችን ምድር የተሰራው ትልቁ የፖለቲካ ስህተት ሶላሺዝምን እንደመመሪያ በመውሰድ የተነሳ ሳይሆን፣ ፖለቲካን ወደ ቡድናዊ ስሜትና አደረጃጀት በመለወጥና ከዚህም በመነሳት ስልጣን ላይ ለመውጣት ከመስገብገብ የተነሳ ነው። በተለይም በሶሻሊዝም አስተሳሰብ ውስጥና እነ ማርክስም ከጻፉት ሳይንሳዊ አስተሳሰብ ውጭ የሆነና ያልተለመደ የትግል ዘዴ፣ በመጀመሪያው ወቅት የህቡዕ ትግል የሚሉት ፈሊጥ፣ ኋላ ላይ ደግሞ በከተማ ውስጥም ሆነ በገጠር የጦር ትግል ማካሄድ፣ ወይም ጠላቴ የሚሏቸውን በመፈረጅና በመግደል በቀናና በሳይንሳዊ መልክ የተጻፈውን አስተሳሰብ በአፍጢሙ በመድፋት ወደ አጠቃላይ ጦርነት ስለተገባ ያ ዐይነት ዕልቂት ሊደርስ ቻለ። ፖለቲካ ግልጽና ወደ ውጭ ወጥቶ መወያያ፣ መከራከሪያ መሳሪያና ማስተማሪያ መሆኑ ቀርቶ የግለሰቦች ፍላጎት ማርኪያ ሆኖ በመተርጎሙ የግዴታ ተንኮል ማውጠንጠኛ ለመሆን በቃ። ይህ ሁኔታ በተለይም ስልጣንን የጨበጠውን ደርግ በመባል የሚጠራውን የሚሊታሪ ኃይል አስቆጣው፤ ነብርም አደረገው። ይህ ዐይነቱ ቡድናዊ ስሜትና ሶሻሊዝምን በተሳሳተ መልክ መተርጎም በአንድ ላይ ሆኖ ለአንድ ዓላማና ለአንድ አገር መታገል የሚገባውን ኃይል በታተነው። በሳንይንስ በተለይም በፊዚክስ ኃይል ደግሞ ወሳኝ ነው። በተለያዩ መልኮች የሚገለጸው ኃይል ሲዋሃድና ጥንካሬና ሲያገኝ ብቻ ነው ችግርን መፍታት የሚቻለው። አንድ ህብረተሰብና ተፈጠሮም ርስ በርሳቸው የተሳሰሩ እንደመሆናቸው መጠን፣ አንድ ቡድን ወይም የተለያዩ ቡድኖች ይህንን ካልተረዱ ወደ ተራ የተንኮል ስራ በመሰማራት በጋራና በመተባበር የሚሰራውን ስራ እንዳይሰራ ያደርጋሉ። ስለሆነም ፖለቲካ ህብረተሰብአዊ፣ ማህበራዊና ኃይልን መሰብሰቢያ መሳሪያ መሆኑን ስለማይረዱ ቡድናዊ ስሜትንና ግለሰብአዊ ፍላጎትን በማስቀደም የአንድን ህዝብ ህልም እንዳለ ያወድሙታል። ይህ ነው አብዮት በመባል በሚታወቀው ዘመን የተፈጸመው።

ከዚህ አጠር መጠን ያለ ሀተታ ስንነሳ፣ እስከዛሬም ድረስ ንትርክ ውስጥ የከተተንና፣ ካለመጸጻት አሁንም ቢሆን በድሮው ትዝታ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ያላቸውን የፖለቲካ ግንዛቤ ስመለከት የቱን ያህል ጭንቅላታቸው በጥሩ መንፈስ እንዳልተኮተኮተና አገርን ለመገንባትና ዘመናዊ ተቋማትን ለመገንባት እንደማይችሉ ነው። በተለይም አገራችንን በግራ ስም ሲያተራምሱና ወደ ርስ በርስ መገዳደልም እንዲያመራ ያደረጉ አንዳንድ ግለሰቦችና ድርጅቶች ለህብረተሰብ ዕድገትና ለመንፈስ መዳበር እጅግ አስፈላጊ ከሆነው ከግሪክ ፍልስፍናና፣ ከአስራስባተኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ ደግሞ በአውሮፓ ምድር ውስጥ ከዳበረው ዓለም አቀፋዊ ዕውቀት(Universal Knowledge) ጋር ያልተዋወቁ ስለሆኑ እንደዚያ የመሰለ ህብረተሰብአዊ ወንጀል ለመፈጸም በቁ። ስለሆነም ስለሰው ልጅና ስለህብረተሰብ ዕድገት ያላቸው ግንዛቤ አልቦ ነው ማለት ይቻላል። በመሆኑም ፖለቲካን እንደሳይንስ በመገንዘብና በህብረተስባችን ውስጥ ያሉ የተለያዩ ቅራኔዎችን በመረዳት ህዝባችንን በማደራጀት ችግሩን እንዳይፈታ ለማድረግ የበቁት ፖለቲካ ከሳይንስና ከፍልስፍና ጋር ያለውን የጠበቀ ግኑኘነት፣ ወይም በእነዚህ ዕውቀቶች ላይ የተመሰረተ መሆኑን ባለመረዳታቸው ነው።

ብሄረሰባችንን ከጭቆና እናወጣለን ብለው የብሄረሰብን አርማ ይዘው እንታገላለን ብለው የተነሱትም የተለያዩ ኃይሎች የህብረተሰብን ከታች ወደ ላይ የማደግ ተፈጥሮአዊ ህግ ባለመረዳታቸውና፣ የአንድን ህብረተሰብ የተወሳሰበ ሂደትና በየጊዜው የሚፈጠሩትን ችግሮች ወደ ብሄረሰብ ጭቆናና መበደል ስለለወጡት ብቻ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን በህብረተሰብ ሂደት ታሪክ ውስጥ አንድ ጎሳ ራሱን ችሎ ያደገበት ሁኔታ በፍጹም አልነበረም። የዓለምን የስልጣኔ ታሪክ ስንመለከት አንድ ማህበረሰብ ሊያድግና ሊያብብ የሚችለው ከተለያዩ አካባቢዎች አዳዲስ አስተሳቦችና ቴክኖሎጂዎች የመጡ እንደሆን ከሌላው ጋር ሲዋሃዱ ብቻ ነው። ተፈጥሮ ራሷ እንደዚህ ናት። ህብረተሰብም ሆነ ተፈጥሮ ዲያሌክቲካዊ በሆነ የቅራኔ ህግጋት የሚገዙና ከአድ ሁኔታ ወደ ተሻለ የሚሸጋገሩ ናቸው። ስለሆነም አንድ ራሱን እንደጎሳ የሚቆጥር ቡድን ይህንን ዐይነቱን መመሰቃቀልና መዋሃድ በፍጹም የማይገነዘብ ከሆነና ነጽሳ ወጣለው ብሎ ትግል ከጀመረ በቀላሉ ሊወጣ የማይችለው ማጥ ውስጥ ነው የሚገባው። በጎሳ ሽፋን ስምም የሚካሄደው ጦርነትና ግብግብ የታሪክን ሂደት ወደ ኋላ የሚጎትትና ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ ዕድገት እንቅፋት የሚሆን ነው። ስለዚህ ነው የኤርትራ ህዝብ ነፃ ካለ ከሰላሳ ዓመት በኋላ በጨለማ ዓለም ውስጥ የሚኖረውና የተወሰነው የህብረተሰብ ክፍል ደግሞ ችግርን ለማምለጥ ሲል የሚሰደደው።

ይህንን የመሰለ የህብረተሰብ ህግ ያልተረዱና ራሳቸውንም በተለይም ከአውሮፓው የካፒታሊዝም ዕድገት ጋር ማስተዋወቅ ያልቻሉ በብሄረሰብ ስም የተደራጁ. የኤርትራ ነፃ አውጭ ድርጅቶች፣ ህወሃትና የኦሮሞ ነፃ አውጭ ድርጅቶች በሙሉ በሃሳብ የቀጨጩና የህብረተሰብንም ህግ ያልተረዱ ናቸው። ከሶስትና ከሁለት መቶ ዓመት በፊት የነበሩበትን ሁኔታ የማያዉቁና እንወክለዋልን የሚሉት ብሄረሰብ በዚያን ወቅት በምን ዐይነት የአመራረት ስልት ይኖር እንደነበር የማይገነዘቡ ናቸው። ስለሆነም ነፃ መውጣት አለብን ብለው ትግል ሲጀምሩ ከተሳሳተ የፖለቲካ ግምት በመነሳት ነው። ምንም ዐይነት የምሁር መሰረትና የፖለቲካ ቲዎሪም አልነበራቸውም። በደመ-ነፍስ ነበር የሚመሩት ማለት ይቻላል። እስከዛሬም ድረስ ጭንቅላታቸውን ቆልፎ የያዘው ይህ ዐይነቱ አስተሳሰብና፣ በተለይም ደግሞ ኢትዮጵያንና አማራን እንደዋና ጠላት አድርጎ መውሰዳቸው በቀላሉ ሊወጡ የማችሉ ጉድጓድ ውስጥ ከቷቸዋል።  በሌላ ወገን ደግሞ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ከአማራ የፈለቁ ነገስታትና የአማራ ብሄረሰብ ውጤት ሳትሆን ሁሉም ብሄረሰቦች በተለያየ መልክ ተሳትፈውባታል። 

ያም ተባለ ይህ በአገራችን ምድር በፖለቲካ ስም የሚካሄደው ትግል ከሳይንሳዊ ዕውቀት ጋር ምንብም ዐይነት ግኑኝነት አልነበረውም፣ የለውምም። በፍልስፍናም የተደገፈ አይደለም። ስለሆነም የተወሳሰበውንና በልዩ ልዩ መልኮች የሚገለጸውን ችግር ሊፈታ የሚችል አይደለም። ከዘመናዊ አስተሳሰብም የራቀ ሰለሆነ አብዛኛው በፖለቲካ ዓለም ውስጥ የተሳተፈውና የሚንቀሳቀሰው የዓለምንም የፖለቲካ አወቃቀር የሚረዳ አይደለም። የዓለምን የፖለቲካ አወቀቃር፣ በተለይም ደግሞ ካፒታሊዝምና ኢምፔሬያሊዝም ምን እንደሆኑ የማይረዳና በእነዚህም ላይ ጥናትና ምርምር ለማድረግ ዝግጁ የማይሆን ግለሰብም ሆነ ድርጅት አገራችንን ለአጥፊና ለወራሪ ኃይሎች የሚጋብዝ ይሆናል። ህዝባችን ዝንተ-ዓለሙን እየተተራመሰ እንዲኖር የሚያደርግ ነው። በዚያውም ድህነት፣ ማህበረዊ ውጥንቅጥነት፣ ውንብድና፣ በልዩ ልዩ መልኮች የሚገለጹ ብልግናዎችና፣ ሌሎችም አገርን የሚያፈራረሱ የተፈጥሮንና የህብረተሰብን ህግ የሚፃረሩ ነገሮች  መድረክ በመሆን ጠቅላላው ህዝባችን የኑሮን ትርጉም እንዲያጣ ይደረጋል። ይህ ደግሞ ዘመናዊ ተቋማትን እንዳንገነባ፣ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት በመሆን ትልቅ አገርና ህብረተሰብ እንዳንገነባ ያግደናል።

ከዚህ ሁኔታ ስንነሳ በአሁኑ ወቅት በተለይም እትዮጵያንና አማራውን እንወክላለን ብለው እዚህና እዚያ ደፍ ደፍ የሚሉ፣ እንዲያም ሲል ኢምፔሪያሊስት ኃይሎችን የሚለማመጡ ኃይሎች ጠጋ ብሎ ለተመለከተ በአስተሳሰባቸው ወደ ኋላ የቀሩ ናቸው። የፖለቲካ ዘመናዊነትን በአገራችን ምድር ዕውን ሊያደርጉ የሚችሉ አይደሉም። የፖለቲካ ዘመናዊነት ወይም የሰለጠነ፣ በክርክር፣ በውይይትና በትንተናና ላይ ያልተመረኮዘ ፖለቲካ ደግሞ የግዴታ አንድን ህብረተሰብ የተሟላ ነፃነት ሊያጎናጽፈው አይችልም። አገሩንም እንደ አገር በጠንካራ መሰረት ላይ እንዳይገነባ ያደርገዋል። ስለሆነም ይህ ዐይነት ኋላ-ቀር ፖለቲካ መቅረት አለበት። በግልጽ፣ በጥናትና በውይይት፣ እንዲሁም በክርክር ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ትግል ብቻ ነው ለአገራችን መፍትሄ ሊሆን የሚችለው። በፖለቲካ ትግል ውስጥ የሚሳተፍና እሳተፋለሁ የሚልም መሰረታዊ በሆኑ፣ የፖለቲካ ዘመናዊነት፣ የፖለቲካል ኢኮኖሚክስ፣ የሶስዮሎጂ ጥያቄዎችንና ጥበባዊ የሆኑ የአገር ግንባታ መሰረተ-ሃሳቦችን እያነሳና እየጻፈ ራሱን ማስተዋወቅና ለምን ዓላማም እንደሚታገል ማስረዳት አለበት። ይህ ብቻ ሲሆን ማን ለምን ዓላማና ለምን ዐይነት ህብረተሰብ እንደሚታገል ይታወቃል። አስፈላጊ በሚሆንበትም ጊዜ የተሻለ አስተሳሰብ ማቅረብ ይቻላል። ባጭሩ ግልጽነት የሌለው የፖለቲካ ትግልና በቡድን በቡድን እየተደራጁ እዚህና እዚያ መሯሯጥ ለሌላ ዐይነት የውንብድና ፖለቲካ የሚጋብዝ ነው። ስለሆነም የጊዜው ጥያቄ የፖለቲካ ፕሮፌሺናሊዝምነትን የሚጠይቅ ነው። ይህ ጉዳይ ደግሞ በብዙ ሰዎች ትከሻ ላይ መውደቅ ያለበትና በአንድ የአስተሳሰብ ስልት ዙሪያ መሰብሰብን ይጠይቃል። የጊዜውም አንገብጋቢ ጥያቄ በጥልቀትና በጥራት መስራት ነው። መልካም ግንዛቤ!! 

 

[email protected]

www.fekadubekele.com

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

ጥር 2 ቀን 2017 ዓ/ም   January 10, 2025  በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡ ቤተ ሰብ፡ ወዳጅ ዘመዶቻችሁን ያጣችሁ: ልጆቻችሁን የቀበራችሁ፡ አካልችሁን ያጣችሁ፡ የተሰነዘረውን ብትር በመከላከል ላይ ያላችሁ፡ያለፈቃዳችሁ በመንግሥት ተጽእኖ ወደመግደልና

በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛ ተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡

January 10, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ¹⁵ የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ ፥ ¹⁶ ተራራዎችንና   በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን ፤ ¹⁷ ታላቁ የቁጣው ቀን  መጥቶአልና ፥ ማንስ ሊቆም ይችላል ? አሉአቸው ። ራእይ 6 ፤  15_17 ይኽ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ። የኢየሱስን ልደት ሰናከብር የየሐንስ ራእይን ማንበብ ጠቃሚ ይመስለኛል ። ምክንያቱም በመጨረሻው ዘመን

ከኢየሱስ የፍርድ ቀን በፊት በህሊናችን ውስጥ ፍቅርን ለማንገስ እንጣር 

የምጣኔ ሀብታዊ ፍጥ፣ የፖለቲካ፣ የእውነትና የሰብአዊ መብት ታጋይ፣ የአመኑበትን ነገር ለመናገር እንደ ፖለቲከኛ በቃላት ሳያሽሞነሙኑ ቀጥታ የሚናገሩት የሀገሬ ኢትዮጵያ ታላቅ ሰው ነበሩ “ዘር ቆጠራውን ተዉት፤ የአባቶቻችሁን ሀገር ኢትዮጵያን አክብሩ!”  አቶ ቡልቻ ደመቅሳ

ሀገር ወዳዱ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ

January 6, 2025
ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። ) “ገብርዬ ነበረ

ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ?

January 3, 2025
Go toTop