ከሃይለገብርኤል አያሌው
የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ በጣም ይጠቅማል:: ጃዋር ከልጅነት እስከ እውቀት የቱጏዘበት መንገድ ይደንቃል:: ከአንድ በጣም የገጠር መንደር ትምህርቱን በችግር ምክንያት ያቋረጠና ወደ ግብርና የተሰማራ ወጣት ሁለተኛ ደረጃን ሲንጋፑር የኮሌጅ ትምህርቱን በዝነኛው ስታንፎርድ ዮንቨርሲቲ ያደረሰው እድል ባስተማሪው ጉትጎታና ድጋፍ መሆኑ ይደንቃል::
ጁሃር በኢትዮጵያ አይደለም በአፍሪካ ደረጃ እንኳ በጣም በቀላሉ የማይገኝ ጥሩ የትምህርት እድል ገና በለጋ እድሜው አግኝቷል:: እድሉን ተጠቅሞ እራሱን ለከፍተኛ ትምህርት ማብቃቱ ጉብዝናና ታታሪነቱን ያስያል:: በጎበዝ ተማሪነቱ ለወጣቱ ትውልድ ያለው አርዐያነት ጎልቶ መታየት እንዳለበት አምናለሁ:: ጃዋር ከጥሩ የትምህርት እድሉ ባሻገር በሲንጋፑርና ባካባቢው ባሉ በርካታ የእስያ ሃገራት የተመለከተው የሃገሮችና የመንግስት መዋቅሮች አሰራር እጅግ የሚደንቅ ነው:: የነዚህ ሃገራት የፖለቲካና የብሄር ቅራኔ የተፈታበትን መንገድ የተነተነበት መንገድ አጃይብ ነው:: በእርግጥ ይህ ልጅ ይህን ሁሉ አይቶ ያሳለፈው አወዛጋቢና ጽንፈኛ የተባለው ጁሃር ነው ያስብላል? የፖለቲካ አካሄዱና ግልብ ንግግሮቹ ምሁራዊ ሳይሆን ግብታዊ የጉርምስና ስሜት ይዞት ነው እንድል አድርጎኛል:: በብዙ ሃገሮች ተዘዋውሮ ያገኘው ልምድ በተለያዩ ታላላቅ ዩንቨርስቲዎች ያገኘው እውቀት ተጨማምሮ ለሃገር ኩራትና አሴት የመሆን እድል ሲኖረው አወዛጋቢና አይታመኔ ስብዕና መላበሱ ያሳዝናል::
ጃዋርን በመጽሃፉ የጠበኩት በእስር ቤት ያገኘው ጽሞና : በእድሜ መብሰሉ : መሬት ላይ ያየው : ጭፍጨፉና ማፈናቀል ; የፖለቲካ ሃይሎች ክሽፈት : የመንግስት የአመራር መቀንጨር የርዕዮተ ዓለም ክስረት : በግሉ የደረሰበት ወከባ : ተደማምሮ ከትምህርትና ከተሞክሮው አኳያ የሚመጥነውን የብስለት ደረጃ ላይ ሆኖ አላገኘሁትም:: ጁሃርን በርቀት ስታዘበው ከወዳጆቹ ( ከኦነግ መሪዎች) ጋር ጭምር ስገመግመው የወጣትነት ስሜቱን መቆጣጠር የማይችል ግልብና ጀብራሬ እንጂ እንደ አብይ አህመድ ጨካኝና እረመኔ እንደ ዳውድ ኢብሳ ግትርና ተቸካይ አይደለም ብዬ መገመቴን ከመጽሃፉ ተረድቻለሁ:: ነገር ግን ብልጣ ብልጥና ቀጣፊ ባህሪው ሊላቀቀው እንዳልቻለም ታዝቢያለሁ:: በመጽሃፉም ” ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ አበው” እንዲሉ ሲንጋፑር ላይ በ ሊ ኩዋን ይው ከፍታ ላይ ስንጠብቀው ጎሎልቻ ቆላ ዝቅታ ላይ በዳካ ጉያ ኦነግ ውስጥ እናገኘዋለን::
( ሊ ኩዋን ይው /የሲጋፑር መሪና የእድገቷ ሃሳብ አፍላቂ) ገጽ74
(ዳካ / የኦነግ ወታደራዊ ክንፍ መሪ) ገጽ 34
በመጽሃፉ ብዙ ጉዳዮች አንስቷል:: ብዙዎችም አስተያየትና ግምገማቸውን በተረዱት መጠንና ባላቸው መረጃ ተንተርሰው እይታቸውን አጋርተዋል:: እያጋሩም ነው:: ጃዋር በመጽሃፉ ብዙ የተዛቡ መረጃዎችን በውሸት የታጀቡ ተረኮችን በጀብደኝነትና በግነት የቀረቡ ሃሳቦችን አንስቷል:: በእኔ እይታ ባለኝ መረጃና በፖለቲካው ውስጥ እረጅም ግዜ እንደማሳለፌ የታዘብኳቸውን እና መታረም አለባቸው ብዬ የማምንባቸውን ሃሳቦች በርካቶች ቢሆኑም ለዛሬ አንዱን ዝንፈት አነሳለሁ::
የአርባጉጉ ጭፍጨፉ (ገጽ34)
ጃዋር አርባጉጉ የትውልድ አካባቢው በመሆኑ ከማንም የተሻለ መረጃና ማስረጃ ይቸግረዋል ብዬ አልገምትም:: አርባጉጉ ጃዋር በመጽሃፉ በቁንጽል እንዳቀረበው ቀላል ጦርነት አልነበረም:: ክርስቲያኗ የጃዋር እናት ከሰላሌ ሄደው የአሩሲ ሙስሊም ባል አግብተው እሱን እንደወለዱት ሁሉ የቤተሰብ ግንዳቸውን ከቡልጋ ከመንዝ በአጠቃላይ ከሸዋና ከሌሎች ቦታዋች ጭምር የሚቆጥሩ በርካታ አማራዎች ከአሩሲም ከባሌም ኦሮሞዎች ጋር ተጋብተው በፍቅርና በአብሮነት የኖሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን በአካባቢው ይኖራሉ:: በ1987 ቡልጋ ዘመድ ለመጠየቅ በሄድኩበት ወቅት በአርባጉጉ በነበረው ጭፍጨፉ ዘመዶቻቸው ሲያልቁ በተዐምር ተርፈው ቡልጋ ውስጥ በአራሽነት ተጠግተው ያገኘሗቸው ግለሰብ በመሪር እንባ የተሞላ ታሪካቸውን አጫውተውኛል:: በግዜው ስለአርባጉጉ ጭፍጨፉና ጦርነት የመዐሕድ አባል በመሆኔ ጥቅል ግንዛቤ ቢኖረኝም ተፈናቃዩ ግለሰብ በነገሩኝ በዚያ ልክ ጭካኔና ጥላቻ ይኖራል ብዬ አስቤ አላውቅም:: የጭካኔው ጥግና የመከራው አሰቃዊነት ከዛ ዘመን በሗላም በተለይ አብይ አህመድ ከመጣ ወዲህ ባየንና በሰማንው መጠንና አይነት ልክ በመሆኑ አልደግመውም::
ወንድማችን ጃዋር የእውነትን አስፈላጊነት የፍትሕና የሰብዐዊነት ውሃ ልክን ከመሃተመ ጋንዲ ማየቱን መስክሯል:: እሩቅ ምስራቅ ሃገሮችን ተዘዋውሮ በአይኑ ያየ ቅራኔ አፈታታቸውን ያጠና ምሁር ብዙ የተባለለትን እልፍ መዛግብትና ማስረጃ ያለውን የአደባባይ እውነት ሽምጥጥ አድርጎ በመካድ በግፍ ባለቁት ሰማዕታት ላይ ተሳልቋል:: ጃዋር የአርባጉጉ ጦርነት (ገጽ 34) በሚል ርዕስ ስር መራራውን ሃቅ ባላወቀ ማለፍም ሲችል የበለጠ ትምህርትና እውቀት ከቀሰመ ከአሜሪካ የአመታት ቆይታ በሗላ ተመልሶ የአርባጉጉን ጦርነት አጠናሁት በሚል የችግሩ መነሻ የሆኑት መጤ አማሮች መሆናቸውን በድፍረት አስነብቦናል::
መዐሕድ የ1984 የአርባጉጉ ጦርነት (ፍጅት) ሰለባዎችን በስም ከነጠፉው ሃብትና ንብረታቸው የቀንድ ከብቶቻቸው ጭምር በሚገባ ሰንዶ ለተለያዩ መንግስታዊና አለማቀፉዊ ድርጅቶች በግዜው ማቅረቡን አስታውሳለሁ:: በመዐሕድ ልሳን አንድነት ጋዜጣ ላይ ሰቆቃወ አማራ በሚል እራሱን የቻለ አምድ ኖሮት የእርባጉጉን ጨምሮ በመላው ሃገሪቷ ላይ የተካሄደውን በአማራና በኦርቶዶክስ ክርስቲኖች ላይ የተካሄደው ጭፍጨፉ ተዘግቦ ይገኛል:: የኢትዮጵያ ሰብዐዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) በቦታው በቀጥታ ተገኝቶ ያዘጋጀውን የጥናት እሪፖርት ማመሳከር ይቻላል:: በሰሜን አሜሪካ የነበረው ሞረሽ ወገኔ የተባለው ሲቪክ ድርጅት ባስጠናው የባለሙያ የመስክ ጥናት የአርባጉጉ ሰቆቃ ከነማስረጃው በዝርዝር አቅርቧል:: (ምጽዐተ ዐማራ ገጽ 345)
ጃዋር ይህን ተራራ የሚያክል እውነት በሶስት ገጽ አቃሎ ሊያልፈው አይችልም:: ይህ 30 አመት ያልሞላው የዚህ ነዋሪ ትውልድ በሰቆቃ የተቃኘ እውነት ነው:: የአርባጉጉ ሰቆቃ ተዋናዮች ኦነግ ኦህዴድ/ ሕወሃት በተናጥልና በሕብረት የፈጸሙት በጭካኔ የተሞላ የግፍ ቁማር ነው:: ለምን ይህን እውነት ለመካድ ፈለገ ኦነግን ለመከላከል እንዳይባል ኦህዴድ እና ሕወሃትም ከመጋረጃ በስተጀርባ የፈጸሙት የጋራ ጭፍጨፉ ነው:: ጆሃር በቀጥታ ሊያስጠይቀው የማይችለውን በእሱ የልጅነት ዘመን የተፈጸመን መከራ ያስካደው የትውልድ መንደሩን ስም ነጻ ለማውጣት ወይስ ለምን? በግሌ ሊገባኝ አልቻለም::
ጆሃር ምንም አወዛጋቢ ቢሆን ሃሳቡ የሚዋልል ሙልጭልጭነት ቢይኖረውም ለወደፊቱ ለሃገር የሚጠቅም ሆኖ ለመውጣት ተራራ ከሚያህል እውነት ጋር ሊታገል አይገባም:: ትምህርት ተሞክሮው እና ልምዱ በቂ ሆኖ ሳለ ውሸትና የተዛነፈ አስተሳሰብ ለሚወክለው ሕዝብም አይጠቅምም::
መለስ ዜናዊ ለመሪነት የሚያንስ አልነበረም:: የነቃና ቀልጣፉ የፖለቲካ ሰው ነበር:: ወደ ገነትም ወደ ገሃነብም የሚያደርሱ እድሎች ሁሉ እጁ ላይ ነበሩ:: ሆኖም ምርጫው ጠባብ ብሄርተኝነት ሆኖ የገሃነብን መንገድን በመምረጡ ሃገሪቷን ለመከራ እወክለዋለሁ የሚለውን የትግራይ ሕዝብ ለጥፉት እንደዳረገ ቆመን አይተናል::
የነገዋ ሃገር ተረካቢ መሆን የሚችሉ በታሪክ አጋጣሚ የመማር የመደመጥና የመታወቅን እድል ያገኙ እንደ ጁሃር ያሉ ወጣቶች ከትላንት ዛሬ ተሽሎ መቅረብ ሲችሉ በአሮጌ አቁማዳ አዲስ የወይን ጠጅ ሊጨምሩ ሲሞክሩ ያሳዝናል:: ያሳለፈንው አሁንም ያለንበት መጋደል እንዲቆም ሳይማር ያስተማረን ደሃ ወገናችን ቢያንስ በሰላም እንዲያድር ከእውነት የታረቀ የሰለጠነና ቅራኔን ፈቺ የፖለቲካ አቅጣጫን ልንይዝ ይገባል:: እውነትን ላልተገባ የፖልቲካ ትርፍ ማዋል ለትዝብት ይዳርጋል:: ማንም ይሳሳታል :: በፖለቲካ አለም መሳሳት ያለ የነበረና የሚኖር እውነታ ነው:: ይቅርታ መጠየቅ ይቻላል:: የተደረገን አልተደርገም ብሎ ከመሟገት ዝም ብሎ ማለፍም ሌላ እማራጭ ነው:: በሺዎች ያለቁበትን እና የተፈናቀሉበትን እውነት በምን እይነት የጥናት መስፈርት ነው መለወጥ የሚቻለው:: ይህን አይነት ነውር እንዳንነጋገር የሚያደርግ እንቅፉት በቀልን የሚያዋልድ እርኩስ ተግባር ነው::
ዋልታ እረገጥ የብሄር አሰላለፍ ለማርገብ መነጋገር በጨዋነት የተሞላ ሂስን የማስተናገድ በሃላችን ሊዳብር ይገባል:: ይህንን ለማድረግ በተጨበጡ እውነቶች እና በተረጋገጡ ታሪካዊ ሃቆች ላይ መግባባት ይጠበቅብናል:: በፖለቲካዊ እሳቤዎች ላይ የግድ መስማማት ባይኖርብንም መነጋግር ይገባል ብዬ አምናለሁ:: በግሌ በአማራ ፖለቲካ ውስጥ ላለፉት ሶስት አስዕርተ አመታት ብቆይም ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ሃይሎች ጋር ተቀራርቦ መነጋገርና አብሮ መስራት አስፈላጊ ነው ብዬ አምናለሁ:: በተለይ ከኦሮሞ ሃይሎች ጋር በቅርብ የመነጋገርና የመስራት እድል ካላቸው ጥቂቶች ውስጥ አንዱ ነኝ ማለት እችላለሁ:: በፖለቲካ ጉዞዬም ከዶር መራራ ጋር በሕብረት ውስጥ በጋራ ተሰልፈን ታግለናል:: ከአቶ ዳውድ ኦነግ ጋር ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ በተደረገ ውይይት ላይ ከባልደርቦቼ ጋር ለሰዐታት ተወያይተን በድፍረትም ትውልዱን ከታሪክ እስረኝነት እንዲያፉቱት በግዜው የነበሩትን አመራሮች ጠይቄያለሁ::በሗላም ከነአቶ ሌንጮ ለታ ከነዶር ዲማነገዎና ከኦዴግ አመራሮች ጋር አብሮ ከመስራት ባለፈ ቅርብ ግንኙነቶች ነበሩኝ:: ይህ የኔ አቋምና እምነት ብዙ ስድብና ውግዘትን በግል ቢያስከትልብኝም በእኔ እምነት የብሄር ፖለቲካውን የመሩትን ማለዘብ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ለመመለስ ፖለቲከኞቹን ከማግለል ማቅረብ ይገባል ብዬ ስለማምን ነው::
በመጨረሻም
ፖለቲካችን እጅግ በጣም ከሮ ሰላማዊ ምህዳሩ ጠቦበት ወታደራዊ ፍጥጫን አስከትሏል:: የኦነግ ወራሴው የሕወሃት ኢሃዴግ ማደጎው ብልጽግና በአብይ አህመድ ዘዋሪነት ወዴት እንደሚሄድ ጠፍቶት በብርሃን ፍጥነት ሃገሪቷና ሕዝቧን ይዞ ወደ መቀመቅ እየነጎደ ነው:: ያለፉት ዘመናት የፖለቲካ ኪሳራ ያስከተለውን ውድቀትና ወደፊት ሊያስከትል የሚችለውን እጅግ አስከፊ ቀውስ መገምገም ያልቻለ የተቃዋሚ የፖለቲካ ኤሊት ዛሬም ከሚሽከረከርብት የአሮጌ አጀንዳ ኦርቢት መላቀቅ አልቻለም:: በተለይም ጁሃርን ጨምሮ አብዛኛው የኦሮሞ የፖለቲካ ኤሊት ከብሄር ፖለቲካው ቀኖናው ሳይላቀቅ ጥገናዊ ለውጥ ላይ ትኩረት ማድረጉ ነገን በተስፉ እንዳናይ ያደርጋል:: ምንም ላነሳ የፈለኩት የአማራውን ሕዝብ የአርባጉጉ ጭፍጨፉ የታሪክ መዛነፍን ቢሆንም ጆሃር በመጽሃፉ ያስነበበን የኦሮሞና የአጎራባች ብሄሮች ግጭት ለግዜው የሃይል የበላይነቱ ስላለ ቢዳፈንም ነገ ላለማገርሸቱ እርግጠኛ መሆን አይቻልም:: አሁን ባለንበት ከቀጠለ ከዚህ የመውጫ መንገድ ካልተቀየሰ የአብይ አገዛዝ በእራሱ ግዜ ቢወድቅ ሃገር ከማቅናት ይልቅ የግጦሽ መሬት ጦርነት ላይ መጠመዳችን አይቀርም::
የብሄር ፖለቲካ ፍጹም ጨለምተኛ ያደርጋል::መንደርተኝነት ያሳብዳል:: የማመዛዘን አቅምን የሚያሳጥ እርኩስ ደዌ ነው:: የብሄር ፖለቲካ ክፉቱ ያቀነቀነውን ብቻ ሳይሆን የማይመለከተውን ሁሉ በብሄር ብያኔ የሚቀጥፍ መርገምት ነው:: ወለጋ ላይ ” ወላሂ ሁለተኛ አማራ አልሆንም” ብላ የተማጸነችው ብላቴና የዘመናችን የክፉት ጥግ ማሳያ ነች::
ሕውሃት ከወርድና ቁመቱ የማይስማማውን ማህበራዊ መሰረቱ ፈጽሞ ሊሸከም የማይችለውን የብሄር አደረጃጀትና የጥላቻ ፖለቲካ መመሪያው አድርጎ የመጣበት መንገድ ንዳይነሳ አድርጎ የታሪክ ገደል ውስጥ ሚሊዮን ንጹሃን ትግራውያን ይዞ ወድቋል:: በግዜያዊ የሃይል ብልጫ ወይም በፖለቲካ ማምታታት ወደ ስልጣን ሊወጣና የተወሰኑ አመታት ሊያራምድ ይችላል:: በግፍ በሃሰት ትርክትና በጥላቻ ፖለቲካ የሚነዳ ቡድን መጨረሻው አስከፊ ውድቀት ለመሆኑ ከሕወሃት በላይ ምስክር የለም::
ተረኛ ነን ባዮቹ የኦሮሞ ብሄረተኞች የስልጣንና የፖለቲካ ፍላጎታቸው ዋና የመዐዘን ድንጋይ ያደረጉት የተዛባ የተበድያለው ታሪክን ነው::m ተወረርን ተጨፈጨፍን ተነጥቀን ነበር ያንን እናስመልሳለን በሚል ቅስቅሳ ለመቶ ሺዎች እልቂት ለሃብትና ንብረት ውድመት ለሚሊይኖች መፈናቀል ምክንያት ሆነዋል:: ዛሬም ታሪክን ዋና አጀንዳቸው አድርገው ሃገሪቱን የጦርነት እወድማ አድርገዋታል::
ታሪክ በታሪክነቱ ሲነገር የተዛባው ትርክት በእውነት ሲጠራ የወራሪ ተወራሪ ማንነት በታሪክ ሚዛን መሰፈር ሲጀምር መረጃ ሲወጣና ፍትሃዊ መድረክ ሲፈጠር ያኔ ማፈር ይመጣል:: የተለመደው የተዛባ የበሬ ወለደ መጤ ወራሪ ተወራሪ የጥላቻና የሃሰት ትርክት እንደወረደ የሚቀርበው የታሪክ አተያይ ነጋችንን የሚያጨልም እንጂ የሚጠቅም አይሆንም:: ነገ ለሌሎች ኢትዮጵያውያን ሌላ የመታገያ አጀንዳ ሆኖ እንደሚወጣ እነጁሃር ሊይስቡበት ይገባል:: የታሪክ ክርክር በተለይ ለኦሮሞ ብሄርተኞች ፈጽሞ ፈጽሞ አያዋጣም::
ብልጽግና ኦነግ እና ሕወሃት ፖለቲካቸው ጨንግፏል:: መስመራቸው መርገም አካሄዳቸው ገደል ሆኗል:: የትላንት ስህተት ለዛሬ ትምህርት ሊሆን ሲችል ከዛ ጋር መጣበቅ በጣም ደካማነት ነው:: አዲሱ ትውልድ ከሻገተ የርዕዮተ ዓለም ውርስና ከመከነ የጠባብ ብሄርተኝነት እሳቤ ባሻገር ዘመኑን የሚዋጅ ፖለቲካዊ አስተሳሰቦችን የኢኮኖሚና ማህበራዊ ግንዛቤዎች ሊያስብ ይገባል:: እንደ ጁሃር ያለ ንቁ ወጣት ከተቆራኘው ኦነጋዊ መናፍስት ተላቆ ዘመኑን ሊመጥን የሚችል አዲስ ታሪክም ሊሰራ ይችላል ብዬ አምናለሁ::
ጀዋር በመጽሃፉ እንዳስነበበን : ከተማረበትና ከጎበኛቸው በአጭር ግዜ አስደናቂ እድገት ካስመዘገቡት የእስያ ነብር የተባሉት ሃገሮች የለውጥ ሚስጥር እንደተረዳሁት:: አዲሱ ትውልድ ሕዝቡን ከወደደ ሕልሙ ሃገርን ማዳንና ማበልጸግን ከሆነ : መርሆው እውነት ተራማጅ አመለካከት : ከመንደር ያለፈ ምልከታ : ከታሪክ እስረኝነት መላቀቅ : ቅንነት : ቀጥተኛነት እና የአቋም ጥራት የአሸናፊ ትውልድ የስኬት ስንቅ እንደሚሆን ከጃዋር መጽሃፍ ላይ ተምሬያለሁ::
እግዚያብሄር ማስተዋሉን ያድለን!!
የጀዋር መፅሀፍ ከልደቱ እሰካሁን ድረሰ ውሸትና ፕሮፐጋንዳ ነው ይላል። pic.twitter.com/S7p5EsizjR
— ጆሮ ጠቢ/informant (@kushNegus) January 10, 2025