January 10, 2025
47 mins read

በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡

ጥር 2 ቀን 2017 ዓ/ም  

January 10, 2025 

ababaበኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡ ቤተ ሰብ፡ ወዳጅ ዘመዶቻችሁን ያጣችሁ: ልጆቻችሁን የቀበራችሁ፡ አካልችሁን ያጣችሁ፡ የተሰነዘረውን ብትር በመከላከል ላይ ያላችሁ፡ያለፈቃዳችሁ በመንግሥት ተጽእኖ ወደመግደልና መገደል በመነዳት ላይ ያችሁ፡፡ ለእውነት ለተጎዳው ህዝብ አንደበት ሆናችሁ በመመስከር ላይ ያላችሁ፡፡ በማህበረሰብ አንቂነት የተሰማራችሁ አርቲስቶች ጸሐፊወችና ዩቱበሮች ይህች ጽሑፍ ትድረሳችሁ፡፡ 

ቀሲስ አስተርአየ ጽጌ  nigatuasteraye@gmail.com  በእርግማን የተዘጋውን የሰላም በር፦ በጾመ  ነብያት የሽምግልናውን በር መክፈቻ ቁልፍ  አድፍጠው ይዘው የተኙትን ፓትርያርክ  ተባብረን በመቀስቀስ እንዲከፍቱ  ካላደረግናቸው፡ በቅዳሴ ጊዜ ሰላም ለኩልክሙ  በማለት፡ በክርስቶስ ሰምራ ሽምግልና እና  በየግላችን በፈጠርናቸው ዩቶቦቻችን ጫጫታ  ወደ ሰላም አዳራሽ ፈጽሞ ልንገባ አንችልም፡፡ 

መግቢያ 

ወቅታዊው ጾማችን ጾመ ነብያት ነው፡፡ ልማዱን ተከትለን መጾሙ ለጤና ጠቃሚነት አለው፡፡ እጅግ የሚጠቅመው ግን በዚህ ወቅታዊው ጾማችን ስለ ሀገር ስለወገን እያሰብንና እየተጨነቅን ስንጾመው ብቻ ነው፡፡ በዚህ ወቅታዊ ጾም ከምናስታውሳቸው ነብያት አንዱ ነብዩ ኢሳይያ ስለህዝባቸው ትኩረት ሳይሰጡ ስለጾሙት ሰወች የተናገረውን እናስተውል፡፡ በኢሳይያስ አካባቢ የነበሩት ሰወች በራሳቸው ክብርና ጥቅም ላይ ብቻ ያተኮሩ ስሜታቸው ከህዝቡ ዋይታና ብሶት የራቀ ስለነበር “በሬ ጌታውን አህያ የጌታውን ጋጥ ሲያውቅ እስራኤል ግን አላወቁም ሕዝቤንም አልተቀበሉም ኃጢአተኛ ወገንና በደል የተሞላበት ሕዝብ የክፉወች ዘር ርኩሰትን የሚያደርጉ ልጆች ሆይ ወዮላችሁ” (ኢሳ 1፡3_4 ) በማለት እግዚአብሔር ከበሬና ከአህያ በታች ወደቃችሁ አላቸው፡፡ 

ሶስት ሽ ዘመን የተቆጠረለትን ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ጋራ አያይዘን የምንጾመው ወቅታዊ ጾም፡ አስተማሪወች የሆኑ ሁለት ቡድኖችን ያመለክተናል፡፡ አንዱ ቡድን ባስተሳሰባቸው ካህያና ከበሬ የባሱ በፖለቲካውና በቤተ ክርስቲያችን አመራር ላይ ተሰይመው ህዝብ በማሰር በመዝረፍ በማሳደድ ከሚኖሩበት ቦታ በማፈናቀልና በመግደል የተሰማሩ ያንደበተኞች ቡድን ነው፡፡ 

ሌላው ከደብዳቢወች ከገዳዮችና ካንደበተኞች ጋር በምንም ንክኪ ሳይነካኩና ሳይረክሱ ለተበደለውና ለተጨነቀው ህዝብ እያለቀሱ ከግፈኞች ከገዳዮች እና ከተቀጣሪ አንደበተኞች ጋር እየታገሉ ይጾሙ የነበሩት ነብያተጽድቅ (የጽድቅ ምስክሮች) እና ከነሱ ጋራ ጸንቶ የቆመው ሁሉ የተካተተበት ቡድን ነው፡፡ 

ነብያትን እንዲጾሙ ያደረጓቸው ምክንያቶች ዛሬ እኛ ያለበትን ተመሳሳይ አስከፊ ገጽታ መስታዋቶች ሆነው ያስዩናል፡፡ እኛም በነብያት ዘመን እንደነበሩት ሰወች በቡድኖች ተከፋፍለናል፡፡ አንዱ፦ኢትዮጵያን በዘር፡ በቋንቋና በክልል ከፋፍሎ፡ ሕዝቡን እርስ በርሱ እያደባደብ ነብረቱን የሚዘርፈው ቤቱን በማፍረስ የሚያፈናቅለው የተሰባሰበበት የብልጽግና ቡድን ሲሆን፦ ሌላው ቡድን ደግሞ ነቢዩ ኢሳይያስ “ለጥልና ለክርክር ትጾማላችሁ በግፍ ጡጫም ትማታላችሁ፡(ኢሳ 58፡ 4) እንዳለው ከጥልና ከከርክር ባላለፈ ንግግር የምንጋጭ የዘመኑ ሰባኪወች ቆሞሳትና ጳጳሳት የተሰባሰብንበት ነው፡፡ 

በዚህ ዘመን በቤተ መንግሥትም በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም ውስጥ የተሰገሰን ሰወች ለግል ጥቅማችን ንብረት በማፍራት ላይ ከማተኮር በቀር ለሕዝባችን የምናየው ራዕይ ሊኖረን ቀርቶ፡ ከፊታችን የወደቀውን ሰው ለማየት ዐይኖቻችን ታውረዋል፡፡ “ለመንግሥቱ ፍጻሜ የሌለው ድንቅ መካሪ ኃያል አምላክ የዘላለም አባት የሰላም አለቃ” ( ኢሳ 9) የተባለውን ዘላለማዊ መፍትኄ ሰጭውን አማኑኤልን ነብያት አሻግረው መመልከት የቻሉት፦ የህዝባቸውን ጭንቀትና ሥቃይ እየተመለከቱ ሕዝባቸው ከወደቀበት ስቃይ ተላቆ ፋታ የሚያገኝበትን ቅጽበት በመመኘት ይጾሙት ስለነበር ነው፡፡ 

ያንድ አባት የዮሴፍ ልጆች የኤፍሬም ነገድና የምናሴ ነገድ እርስ በርሳቸው ሲጋደሉ ኢሳይያስ አይቶ ኧረ አምላክ ፈጥነህ ድረስ “ምናሴ ኤሬምን በላው፡፡ ኤፍሬምም ምናሴን በላው! ” (ኢሳ 9፡21)  ወንድማማቾች እርስ በርስ ተባሉ እያለ በጾምና በልቅሶ የታጀበ ጩኸት ወደ አምላክ በማቅረቡ ድንግል ማርያም አማኑኤልን ታቅፋ አያት፡፡“ድንግል ትጸንሳለች ወንድ ልጆም ትወልዳለች ስሙን አማኑኤል ትለዋለች”(ኢሳይያስ 7፡14) ብሎ ተናገረ፡፡ 

አባቶቻችን ከጌታችን ከኢየሱስ ክስቶስ ልደት ጋራ አያይዘው በነብያት ሰይመው ያወረሱን ጾም ትኩረታችንን ከራሳችን ጥቅም አላቀን ያንዲት እናት ኢትዮጵያ ልጆች መገዳደል አይተን ኢሳይያስ እንዳደረገው ለአምላክና ለዐለም ዋይታችንን እንድናሰማ ነበር፡፡ በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ጉልላት መስለው በተቀደሰው ነዋየ ቅድሳት ተከብረውና ተሞግሰው የሚታዩት ቅዱስ ፓትርያርካችን በንደዚህ ያለ ጊዜ ለመላ ኢትዮጵያውያን አንደበት እንዲሆኑ ነበር፡፡ ይልቁንም የሚመሯት ቤተክርስቲያናቸው ያጠመቀቻቸው ልጆቻቸው ሁለቱ ወንድማማቾች ትግሬና አማራ  እርስ በርሳቸው ሲተላለቁ ኡ ኡ ኡ የገላጋይ ያለህ የሰው ያለህ! ብለው ለእግዚአብሔርም ለሰውም ባለመጮሀቸው፡ በኢሳስይያስ ዘመን ለነበሩት መሪወች እግዚአብሔር ባሱ ብሎ ለንጽጽር ከጠቀሳቸው እንስሳት እጅግ በጣም ስለባሱ ቅዱስ አባታችን ከፕትርክናቸው ወደቁ፡፡  የፕትርክናቸውን መውደቅ ለማሳየት የፓትርያርክነትን መለኪያወች ቢያንስ ሶስቱን ፓትርያርክ አብርሃምን ሙሴንና ኤሊን በመጥቀስ በቀላሉ ማሳየት ይቻላል፡፡ 

ፓትርያርክ አብርሃም  

በፓትርያርክነት መሰየም የሚገባው በሶስቱ ታላላቅ አብያተ እምነቶች ማለትም በይሁዲ በክርስትናና በሙስሊም ተቀባይነት አግኝቶ የተሰየመው ፓትርያርክ አብርሃም ያደረገውን ተግባር የሚያደርግ ሰው ነው፡፡ የፓትርያርክነትን ሐላፊነት ተሽክሞ በመጨረሻው ክብር ተራራ ጫፍ ላይ ቆሞ በግዚአብሔርም በሰውም ፊት የሚታይ ሰው፡ እንደ ፓትርያርክ አብርሃም ለሕዝቡ ራዕይ የሚያይ፤ ፓትርያርክ አብርሃም የሠራውን ሥራ ለመሥራት አቅም ያለው ሰው ሊሆን ይገባል፡፡ ፓትርያርክ አብርሃም የሠራውን እንመልከት፡፡ 

ፓትርያርክ አብርሃም በሱ ወገንና በወንድሙ ሎጥ ወገን መካከል በመሬት የተቀሰቀስውን ግጭት እንደሚፈጠር አስቀድሞ በራእዩ ተመለከተ:: ፓትርያርክ አብርሃም “በአንተ እና በኔ፡  በተከታዮቻችንም መካከል ግጭት አይፈጠር ፡፡ አገሩ ሰፊ ነው አንተ ቀኙን ብትወስድ እኔ  ግራውን እወስዳለሁ”፡፡ ብሎ ወንድሙን ሎጥን ተማጸነው፡፡ የአንድ ሰው ነፍስ ሳይጠፋ የሚፈጠረውን ግጭት ፓትርያርክ አብርሃም ገታው፡፡ ስግብግቡ ሎጥ የሚያስከትለውን አደጋ ሳያይ ልምላሜውን በማየት ለጥፋት ከተዘጋጀው ከሰዶም ጋራ የሚያዋስነውን ቦታ መረጠ፡፡ ለእሳትና ለጦርነት በተዘጋጀው ቦታ ላይ ወደቀ፡ (ዘፍ 13፡8_11)፡፡ ቢወድቅም ፓትርያርክ አብርሃም ሃዳጌ በቀል በመሆኑ የመረጠውን አገኘ ብሎ ሎጥን ከመታደገ ወደ ኋላ አላለም፡፡ (ዘፍ 14፡13_16)፡፡ ሎጥን ከማረኩት ኃያልን መንግሥታት ጋራ ተፋልሞ ድል በመንሳት ሎጥን ከነንብረቱ መለሰው፡፡ 

ፓትርያርክ አብርሃም ሊከሰት ያለውን ግጭት ማየቱን፤ መግታቱን፤ ሎጥን ከምርኮው መመለሱንና ለማያውቃቸው ለሰዶምና ለገሞራ ሰወች በመጨነቅ “በኃጢአታቸው ከሚጠፉ እኔ ስለነሱ አፈር አመድ ልሁን” (ዘፍ 18፡23_33) ብሎ ቤዛ ሆነላቸው፡፡ የአርሃምን ፕትርክና ቅዱስ ቄርሎስ “ወደለወ ለዘወረደ ይትመከር ወይትቃረኖ ለሰይጣን ዘሞዐነ ቀዳሚ ወተጻብአ በእንቲአነ ወገደፎ ታሕተ . . . (79:25)፡፡ ብሎ ለክርስቶስ ቤዛነት መግለጫ አድርጎ ተረጎመው፡፡ 

ቅዱስ ፓትርያርካችን የብርሃምን ምሳሌ በመከተል ወያኔወች መግሥት ገልብጠው በትረ ምንግሥት በጨበጡ ጊዜ በሎጣዊ ስግብግብ ባህርያቸው የቆየውን ድንበር እየጣሱ ለምለም ቦታወችን እየነጠቁ ሲወስዱ አይሆንም ተው! የቆየውን ድንበር ጥሳችሁ አዲስ ክልል ፈጥራችሁ የምታካሂዱት ወረራ በካባቢው የማይበርድ ጦርነት ትፈጥራላችሁ፡፡ እናንተ በምትፈጥሩት ጦርነት እንደ ገሞራ ሰወች ትቃጠላላችሁ ብለው መግታት በተገባቸው ነበር፡፡ ከዚያም ወዲህ ድንበር ጥሰው የገቡትን ወያኔወችን የአማራ ልጆች ክክልሉ ለማስወጣት ሲተላለቁ ቅዱስ ፓትርያርካችን ያለሕግ በጉልበት ድንበርንና ወሰን ጥሳችሁ የወሰዳችሁትን ክልል የኛ ክልል ነው ማለታችሁን አቁሙ፡፡ እንደ ቀድሟችሁ ተስማምታችሁ ኑሩ፡ “አገሩ ሰፊ ነው አንተ ቀኙን ብትወስድ እንተ ግራውን ውሰድ”  ብለው ፓትርያርክ አብርሃም ያደረገውን አባታዊ ተግባር አልፈጸሙም፡፡ 

ፓትርያርክ አብርሃም ሕገልቡና ከሚባለው ንጽሐጠባዩ በቀር ከሱ በፊት የሚመለከተው የሚማርበት ፓትርያርክ ሳይኖረው ይህን የመሰለ አስታራቂ ሽምግልና በማድረጉ ዓለም ክርስቶስ የሚድንበት ወንጌል ከኦሪት አስቀድሞ የተሰበከለት ጽድቅ የተቆጠረለት የብዙ ሕዝብ አባት ሆነ (ፓትርያርክ)“ገላ 3፡8” ብሎ ቅዱስ ጳውሎስ አብርሃምን አደነቀው፡፡ ቅዱስ ፓትርያርካችን ከፓትርያርክ አብርሃም እጅግ ተሽለው ፓትርያርክነታቸው ለመላው ኦርቶዶክሳውያን ይሆን ዘንድ  ለአብርሃም የተቆጠረለትን ጽድቅ “መፈጸም አለብን” ብሎ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ሲጠመቅ ያወጃትን ጽድቅ በሁሉም ፊት ያለ አድለዎ እኩል ማንጸባርቅ በተገባቸው ነበር፡፡ 

ከነብያት አንዱ ኤርምያስ እንደተናገረው፦ በፓትርያርክ አብርሃም የተከሰተች ይህች ጽድቅ ክርስቶስ ፍርዱን የሚያከናውንባት መጽደቂያችን ሚዛን ናት፡፡ በክርስትና እምነታችን ያጸደቀን ክርስቶስ ስለሆነ “እግዚአብሔር ጽድቃችን ተብሎ ይጠራል (ኤር 23፡6) ብሎ ኤርምያስ መሰከረ፡፡ ቅዱስ ፓትርያርካችን ወደ ፕትርክናው የገቡት ከፓትርያርክ አብርሃም እጅግ ልቀው ለጸደቅንበት ለክርስቶስ ጽድቅ ነጸብራቃችን እንዲሆኑ ነበር፡፡ ነገር ግን ያስመሳይነት የግብዝነት የፍርሀት የወላዋይነት ያድርባይነት የአድላዊነት ነጸብራቅ ምሳሌ በመሆናቸው ፓትርያርነታቸው እያስከሰሳቸውና እያስወቀሳቸው ነው፡፡ የበለጠ ወደ ሚያስወቀሳቸው ወደ ሙሴ ምስሌነት እንሻገር፡ ፡

የሙሴ ፓትርያርካዊ ምሳሌ  

ሙሴ ከፓትርያርክ አብርሃም ለየት ያሉ ቅዱስ ፓትርያርካችን አራግፈው የጣሏቸው ምሳሌወች ብዙ ናቸው ፡፡ ሙሴ “ስለሚነገረው ነገር ምስክር ለመሆን በቤቱ ሁሉ እንደ ሎሌ የታመነ እንደነበረ” ቅዱስ ፓትርያርካችንም በኢትዮጵያ በተለይም በኦርቶዶክሳውያን ልጆቻቸው ላይ የደረሰባቸውን መከራና ስቃይ ያለ አድለዎ ለዐለም የመመስከር ሐላፊነት ነበረባቸው፡፡ ቅዱስ አባታችን ብለን ለምንጠራቸው ልጆቻቸውም “የምንደፍርበትን የምንመካበትን ተስፋ እስከ መጨረሻ አጽንተን በመጠበቅ የክርስቶስ መገለጫ” እንድንሆን ምሳሌ ሊሆኑን ግዴታ ነበረባቸው፡፡ (ዕብ 3፡_6)፡፡ 

መንበረፕትርክናው በሚሰጣቸው ሥጋዊ ምቾትና ቅንጦት በሞት መላቀቅ ስለማይፈልጉ  “ልሸከመው አልቻልኩም፡፡ እባክህ ፈጽሞ ግደለኝ” (ዘኁ 11፡15) አላሉም እንደ ሙሴ፡፡ ክርስቶስን መሪአቸው ቢያደርጉት ኖሮ ክርስቶስ ሊሸከሙት የማይችሉትን ከባዱን ቀንበር ሰብሮ “ሸክም የከበደባችሁ ወደኔ ኑ ሸክሜ ቀላል ቀንበሬ ልዝብ ነው” ብሎ የሰጣቸው ሸክም ሳይሆን፡ የከባድ ችግር መክፈቻ ቁልፍ ነበር፡፡ 

የከበቧቸው ጥቅመኞች ካንጀታቸው ፈንቅሎ ያልወጣውን አስመሳይ እንባ አለቀሱ እያሉ፤ ካንጀቱ ፈንቅሎ ያልወጣውን ከባህር የተሸከመውን ውህ ከሰውነቱ ሲያንጠባጥብ በመታየቱ አለቀሰ የሚባለውን አዞ አድርገው ለከንቱ ውዳሴ ሲያቀርቧቸው መቃወም ይገባቸው ነበር፡፡  

ከቅዱስ ፓትርያርካችን የሚጠበቀው ፓትርያርክ አብርሃምና ሙሴ በዙሪአቸው ያሉት ሰወች የጫኑባቸውን ሸክም እንዴት አራግፈው ሐላፊነታቸውን እንደተወጡ መመልከት ነበር፡፡ ተስፋ እንደቆረጠች ባልቴት ቁጭ ብለው ከማልቀስ ይልቅ ዕብራዊው ክርስቲያን ጸሐፊ “እነዚህ ሁሉ ሉ ምስክሮች እንደ ደመና በዙሪአችን ካሉልን ሸክምን ሁሉ የሚከበንን ኃጢአት አስወግደን የእምነታችንን ራስና ፍጻሜውን ኢየሱስን ተምልክተን በፊታችን ያለውን ሩጫ በትግስት እንሩጥ”(ዕብ 12፡1) እንዳለው ልጆቻቸው እነ ዶክተር ደብረ ጽዮን ሰይጣን ያሸከማቸውን ቀንበር ሰብረው የሰሩትን ኃጢአት በንስሀ አስወግደው ወደ ጽድቅ እንዲሮጡ መሪና ምሳሌ ሊሆኑላቸው በተገባቸው ነበር፡፡ 

ቅዱስ ፓትርያርካችን በክርስቲያናዊው ፕትርክናቸው ከሙሴ መላቅ ያለባቸውን ግዴታ የሚያሳዩ በሙሴ መጻሕፍት የተመዘገቡ ሌሎች ብዙ ምሳሌወች ነበሩላቸው ፡፡ የሙሴ ሕግ የገደለ መገደል እንዳለበት ይደነግጋል፡፡ ይሁን እንጅ አንድ ሰው በስህተት የሌላ ሰው ነፍስ ቢያጠፋ በስህተት ላጠፋት ነፍስ የሞት ፍዳ መክፈል አይኖርበትም፡ ይሁን እንጅ የገደለው በስሕተትም ቢሆን የሞተው ሰው ክቡር ነውና ከንቱ እንዳይሆን ገዳዩ ከዋናው ካህን ሕይወት ጋራ በተያያዘ ስራት የሚከፈል ፍዳ አለ፡፡ ተበቃይ እንዳይገድለው ወደ መማጸኛ ቦታ ይሸሻል፡፡ በሸሸበት አቅራቢያው ያለው ዋና ካህን በህይወት እስካለ ድረስ ወደ ገደለበት ቦታ አይመለስም፡፡ ሕሊናው ሳይጸዳ ተመልሶ ከህዝብ ጋራ ቢቀላቀልና ተበቃዩ ቢገለው ገዳዩ ተጠያቂ አይሆንም፡፡ ይህም ማለት የገዳዩ ስነሕሊና በዋናው ካህን ትምህርት ከገዳይነት ህሊናዊ ሰንሰለት ተላቆ ፍጹም መጽዳት አለበት፡፡(ዘሑኁ 35፡ 24_25)፡፡ በዋናው ካህን ትምህት ሕሊናው ጸድቶ ከሕዝብ ጋራ ቢቀላቀል ከራሱ ሕሊናዊ ወቀሳ ተላቆ ሕዝባዊ ሕይወቱ የተስተካለ ይሆናል ማለት ነው፡፡ 

በአገራችን ተመሳሳይ ነገር የሚጠበቅባቸው ዋንው ካህን ቅዱስ ፓትርያርካችን ናቸው፡፡ ቅዱስ ፓትርያርካችን በስህተት ሳይሆን በከፍተኛ ትእቢትና ፉከራ ብዙ የገደሉትን ሰወች ወደልዕለሕሊና በማድረስ ከሞት ፍዳ ሊያድኗቸው ቀርቶ፡ ለፍርድ መቅረብ የሚገባቸው በሚሊዮን የሚቆጠሩትን ነፍሳት ያጠፉት እነዚሁ ነፍሰ ገዳዮች ከህዝብ ጋራ ሲቀላቀሉ ዝም አሉ፡፡ ራሳቸውም ተቀላቀሉ፡፡ 

ከመጽሐፉ ሳንወጣ ልናልፈው የማይገባ ቅዱስ ፓትርያርካችን የሚከሰሱበት ሙሴ ሌላ አስደናቂ ስርአት አውርሷል፡ገዳዩ ባልታወቀ ሰው ያልታወቀ ሰው ተገሎ የፈሰሰው ደም ተጠያቂ አልባ እንዳይሆን የተገደለው ሰው ሬሳ ለወደቀበት መሬት ቀራቢ የሆነው ዋናው ካህን የተጠያቂነቱን ሸክም ይሸከማል(ዘዳ 21፡1፡6)፡፡ በኢትዮጵያ ምድር በግፍ እየተገደለ ሞቶ ለተቀበረበትና ወድቆ ለተገኘበት ሬሳ ሁሉ በቀራቢነት የሚጥየቁት ዋና ካህናችን በመንበረ ፕትርክናው የተሰየሙት የአክሱም ሊቀ ጳጳስ ሆነው እጨጌ ሆነው በኢትዮጵያ ያሉት የተለያዩ አብያተ እምነቶች ድርጅትም የበላይ ጠባቂ ዋና ሆነው ከተቀመጡት ከቅዱስ ፓትርያርካችን ሌላ ማንም የለም፡፡ 

“በስንፍናችን የሰራነውን ኃጢአት አትቁጠርብን እርሷንም በናቱ ማሕጸን ሳለ ሞቶ ግማሽ አካሉ ከተበላ በኋል የተወልደ ጭንጋፍ መስላ እንድትቀር አታድርግ”(12፡12) ብሎ ሙሴ ለእህቱ እደተማጸነ፡ በኢትዮጵያ በተልይ በማራውና በትግራይ ምድር ባውሬ የተበላው ግማሽ አካሉን በጦርነት ያጣው ሞቶ የተገኘው በጦርነቱ ድምጽ በናቱ ማህጸን ሞቶ የተወልደው ሙሴ ተማኅጽኖ ካቀረበበት ኃጢአት እጅግ የከፋ ሲሆን ሙሴ ያስጨነቀውን ያህል ፓትርያርካችንን አላስጨነቃችውም፡፡ 

እስራኤላውያን ተሰገብግበው የሰበሰቡትን ድርቂት ጎርሰው በጥራሳቸው ሳለ ሳይውጡት የእግዚአግሄር ቁጣ በራሳቸው ላይ እንደነደደባቸው (ዘኁ 11፡31_35) ወያኔወችም ከኢትዮጵያ ሕዝብ እየዘረፉ የሰበሰቡትን ሁሉ ጎርሰው በጥርሳቸው ሳለ ሳይውጡ የነደደባቸው ራሳቸው የጫሩት የጦርነት እሳት ንጹሁን የትግራይንም ሕዝብ ሲያቃጥለው ዝም ማለታቸው ምንኛ ያልታደሉ ናቸው!  የሚያሰኝ ነው፡ 

ከይሁዲ ማለትም ከሙሴ እምነት ወደ ክርስትና የገባው ዕብራዊ የሕግ ሊቅ ከሙሴ ሕግና ስርአት ይልቅ ቅዱስ ፓትርያርካችን የተቀበሉት ሐላፊነት እጅግ የላቀና ሐላፊነታቸውን ባይወጡ የሚጠብቃቸው ቅጣት እጅግ ከባድና አስፈሪ እንደሆነ እንዲህ ሲል ገልጾታል፡፡ “የሚሴን ሕግ የናቀ ሰው ሁለት ወይም ሶሶት ምስክር ቢመሰክሩበት ያለ ርህራሄ ይሞታል፡፡ የእግዚአብሔርን ልጅ የረገጠ የተቀደሰውን የኪዳን ያክፍፋ እንዴት ይልቅ የሚብስ ቅጣት የሚገባው ይመስላችኋል? (ዕብ 10፡

25_29)፡፡ ቀጥለን የዋና ካህናችንን የቅዱስ ፓትርያርካችንን አባትነት በሌላው ዋና ካህን በኤሊ አባትነት እንመዝነው፡፡  

የቅዱስ ፓትርያርካችን ዋና አባትነት፡ በዋናነት ይታይ በነበረው በኤሊ አባትነት ሲመዘን፡፡  

ኤሊ ልጆቹ የፈጸሙትን በደል ሰምቶ “ስለ ክፉ ስራችሁ ከዚህ ሕዝብ ሁሉ ሰምቻለሁ፡፡ ለምን እንዲህ ያለ የከፋ ነገር ታደርጋላችሁ ልጆቼ ሆይ የእግዚአብሄርን ሕዝብ ኃጢአተኛ በማድረጋችሁ ስለእናንተ የደረሰኝ ወሬ መልካም አይደለምን የምታደርጉትን አቁሙ” በማለቱ ከቅዱስ ፓትርያርካችን ኤሊ በእጅጉ ይሻላል፡፡ ቅዱስ ፓትርያርካችን እንደ ሙሴ እንደ አብርሃም የማሸማገሉን ሐላፊነት በተግባር ላይ ሊያውሉት ቀርቶ ኢትዮጵያን በዘር ከፋፍለው ለ28 አመት ሲገሉና ሲያጋደሉ የኖሩትን እነ ዶክተር ደብረ ጽዮንና አሁንም በባሰ ጭካኔ በመግደል ላይ ያለውን የብልጽግና መሪወችን “ስለእናንተ የደረሰኝ ወሬ መልካም አይደለምን የምታደርጉትን አቁሙ”  አላሉም፡፡ 

ዋናው ካህን ኤሊ ብየ ነበር ለማለት ጥቂት ቃላት ወርውሮ ከመተኛት በቀር ፓትርያርካዊ ሽምግልናው የተሸከመውን ኃይል ሙሉ ባለመጠቀሙ “ለቤትህ ሽማግሌ እንዳይገኝ ክንድህን ያባትህንም ቤት ክንድ የምሰብርበት ዘመን ይመጣል፡፡ . . . በማደርሪያየ ጠላትህን ታያለህ በቤትህም ለዘላለም ሽማግሌ አይገኝም. . . . ልጅህም ቢገኝ ዐይንህን ያፈዘዋል ነፍስህንም ያሳዝናል፡፡ ከቤትህ የሚወለዱ ልጆች ሁሉ በጎልማሳነታቸው ይሞታሉ” የሚል ርግማን በቤተ ሰቡና በሕብረተ ሰቡ ላይ አስከተለ (1ኛ ሳሙ 2፡24_33)፡፡ ታዲያ የኤሊ ያንድ ጊዜ ስህተት ይህን ያህል መርገም ካስከተለ የቅዱስ ፓትርያርካችን ተደጋጋሚ ስህተት “እግዚአብሔር ያሳየዎ ክርስቶስ ያመልክተዎ” የሚባልበት ኢትዮጵያዊው ሽምግልና በክርስቶስ ሰምራ ሽምግልና ተዋርዶ ቢቀርብ ምን ያሰደንቃል?  

የክርስቶስ ሰምራ ሽምግልና 

እናታችን ክርስቶስ ሰምራ ዲያብሎስንና መድኃኒታችን ክርስቶስን ለማስታረቅ መሞከሯ በገርነቷና ርኅርሂትነቷ አናደንቃታለን፡፡ ይሁን እንጅ አስታርቂነቷ በኦርቶዶክሳዊው ነገረ መለኮት ሲለካ መግቢያ በር የሌውን ግንብ እንደ ማንኳኳት ፍጹም ሞኝነት ነው፡፡ ቅድስት ድንግል እመቤታችን አምኑኤልን ስትጸንስ ዲያብሎስ በተሸናፊነት ክርስቶስ ባሸናፊነት ጉዳዩ ዳግም የምይነሳ ሆኖ መዘጋቱን “በክንዱ ኃይል አድርጓል ትእቢተኞችን በልባቸው አሳብ በትኗል፡፡ ገዥወችን ከዙፋናቸው አውርዷቸዋል ትሑታንን ከፍ አድርጓል” ብላ ያወጀችውን አለማወቅ ነው፡፡ የክርስቶስ ሰምራ ሽምግልናዋ ከኪዳነ ምሕረት እመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ርሕራሄ በላይ እጅግ በራቀው ርህራኄዋ ላይ ስለተመሰረተ አስተምህሯችን መጠኑ ከባድ (overdose) ሆኖ እንደሚገድል መድኃኒት ተቀባይነት ያሳጣዋል፡፡

ቅንጅትንና አቶ መለሰን እንዲሁም እውስጥና እውጭ የነበሩትን ሲኖዶሶችን በየዋህነት ለማሸማገል የሞከሩት የወገኖቻችን ሽምግልና፡ አገር ሲጠበቅበት የኖረውን ሽምግልና ሰባራ ሚዛን ያደረገ እንደነበረ ልንዘነጋው አይገባም፡፡ አሳሪውን አሳዳጁንና ገዳዩን ከፍ በማድረግ ቅዱስ አድርጎ፡ የታሳሪወችን ስነሕሊና ዝቅ ያደረገ ነበር፡፡ ተለያይቶ የኖረውን ሲኖዶስ ያስታረቀው የጠቅላይ ምንስቴር ዓቢይ ሽምግልናም ከክርስቶስ ሰምራ ሽምግልና ብሶ ከቀኖናችን ጋራ የተጋጨ በመሆኑ አሁን በቤተ ክርስቲያን በመካሄድ ላይ ያለውን የባሰ አደጋ አስከተለ፡፡ ራሳቸው ጠቅላይ ምኒስቴሩ ያሸማገሉትን ሲኖዶስ በቤተ መንግሥት ጠርተው “ገዳዮችም ተገዳዮችም የናንተ ልጆች ናቸው”  በማለት ቅዱስ ፓትርያርኩን የነፍሰ ገዳዮች አባት በማድረግ ሲወነጅሏቸው የራሳቸውን ሽምግልና የምርገም ውጤት መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ታዲያ ሁሉም እንዲህ ከሆነ ምን መደረገ አለበት?  መውጫውስ ምንድነው? ብሎ ለሚጠይቀኝ በየግላችን መንጫጫታችንን አቁመን ከዚህ በታች ያቀረብኩትን ሐሳብ ማድረግ ነው እላለሁ፡፡ 

መፍትሄው 

በቅዱስ ፓትርያርካችን አካባቢ ያላችሁ፡ በሩቅም በቅርብም ያለን ሁላችን የግል ጫጫታችን እናቁም፡፡ እስካሁን በየቤተመቅዳሳችን ሆነነ “ሰላም ለኩልክሙ” የምንል ቀዳሾች፡ መዝሙሩ ወረቡ ስብከቱ ሁሉ ጫጫታ ነው፡፡ ሁላችንም በፈጠርነው ዩቱብ የየግል ቤተ ስብ በመፍጠር እርስ በርስ ከመደናቆር በቀር የህዝባችን መከራ ቅድመ እግዚአብሔር አልደረሰም፡፡  

ከዚህ ቀድም ወያኔዎች “ታራሚ” እያሉ ንጹሐን ኢትዮጵያውያንን ሲያስሩ ሲያሳድዱ፡ ቅዱስ ፓትርያርካችንም ወያኔን ከመውቀስና ከመገሰጽ ይልቅ ወያኔን ደግፈው በወያኔ የተበደለውን ሁሉ  “ታራሚ” በማለታቸው ከተበደለው ሕዝብ አልቆሙም ብለን ስንወቅሳቸው ነበር፡፡  

ዛሬ ደግሞ የብልጽግናው መንግሥት በድሮን እየታገዘ በከባድ መሳሪያ በህዝብ ላይ የሚያካሂደውን ጭፍጨፋ “ግጭት” የሚል ስያሜ ሰጥቶታል፡፡ መንግሥት “ግጭት” ያለው የሱ እጅ እንደሌለበትና ተወቃሹም ተከሳሹም ህዝቡን ለማድረግ ነው፡፡ በከባድ መሳሪያ ሕዝብ የሚጨፈጭፈው መንግሥት “ግጭት” የሚለውን አደናቋሪ ቃል ቅዱስ ፓትርያርካችን እየተቀበሉ ግጭት በማለታቸው የሕዝቡን ዋይታ እያፈኑት ነው፡፡  

ምንግሥት የሚፈጽመውን በደል “ግጭት” ቢለው “ታራሚም” ቢለው የመጀመሪያው ተጠያቂ ስለሚሆን ከተጠያቂነት ራሱን ለመከላከል ነው፡፡ ክቅዱስ ፓትርያርካችን ጀምሮ እላይ እንደገለጹኩት ሁላችንም የምናሰማው ቃል አፋኝ ጫጫታ ስለሆነ መሬት አፏን ከፍታ እንደዋጠጫቸው ዳታንና ቆሬ “እናንተ እጅግ አብዛችሁት በእግዚአብሔር ጉባኤ ላይ ለምን ትታበያላችሁ”(ዘኁ 17፡3)፡፡ የሚል አምላክዊ ጥያቄ እየተሰነዘረብን ነው፡፡ ኦርቶዶክስ ክርስቲያን ስለሆንኩ ክስተቶችን የማያቸው በማውቀው በነገረ መለኮቱ ነውና ሰሞኑን በአገራችን የሚካሄደው የመሬት መንቀጥቀት ከነዳታን ኃጢአት እጅግ የከፋው የራሳችን ኃጢአት ይመስለኛል፡፡ በየግላችን የምናሰማው ጫጭታ ሰሚ አደናቋሪና የህዝብ ድምጽ አፋኝ ስለሆነ በህዝብም በእግዚአብሔር ላይ አመጸኞች ሆነናል፡፡ “ሰማያት ስሙ ምድርም አድምጭ ልጆችን ወልድኩ፡፡ አሳደኩም እነርሱም ዐመጹብኝ”(ኢሳ 1፡2) በማለት እግዚአብሔር ለዳኝነቱ ሰማይንና ምድርን ምስክር እየጠራብን ነው፡፡ 

ድምጻችን የሚሰማባት የተራራ ጫፍ ከብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በቀር ሌላ ሰው የማይቆምበት መንበረ ፓትርያርኩ ነው፡፡ አቡነ ማትያስ በዚህ ቅዱስ ተራራ ጫፍ ላይ የቆሙት እንዲህ የመሰለ አስጨናቂ መከራ በህዝብ ላይ ሲደርስ የሁላችንንም ዋይታ አንድ ላይ አጠቃለው ለአግዚአብሔርም ለዓለምም እንዲያቀርቡልን ነው፡፡ አኀት አብያተ ክርስቲያናት ምስራቃውያን ኦርቶዶክሶችና በመስራችነቷ የመሰረተችው የዓለም አብያተ ክርስቲናት ድምጻችንን መስማት ያልቻሉት በቅዱስነታቸው ድምጻችን ተጠቃሎ ስላልደረሳቸው ነው፡፡ በአቡነ ቴዎፍሎስ ይመራ የነበረው ኮሚቴ የጀመረው ህዝባዊ ጩኸት ሊሰማ ሳይችል የቀረው ቅዱስ ፓትርያርካችን አፋቸውን ዘግተው በመተኛታቸው ነው፡፡ 

እኛም እርስ በርስ ከመደናቆርና ቅዱስ ፓትርያርኩን ድምጻቸውን አፍነው ተኙ እያልን ከመውቀስ በቀር ያደርነው ጥረት የለም፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን አስተምሕሮ ወቃሽና ከሳሽ ሌላውን ከሚወቅስበትና ከሚከስበት ጉዳይ ራሱ ነጻ ካልሆነ በተከሳሹ ላይ ከሚደርሰው ፍርድ ነጻ ሊሆን እንደማይችል ሐዋርያው ያዕቆብ “በጎ ለማድረግ አውቆ ለማይሠራው ኃጢአት ነው”(ያዕ 4፡17) ብሎ ነግሮናል፡፡ 

ቅዱስ ፓትርያርካችንን ሁላችንም ተኝተዋል እያልናቸው ነው፡፡ መተኛታቸውን ካወቅንና ከእንቅልፋቸው መንቃት አቅም እንዳጠራቸው ከተረዳን መቀስቀስና ማንቃት አለብን ማለት ነው፡፡ የተኛ ሰው በአካባቢው የተፈጠረውን ነገር አያውቅም፡፡ ሌላውን ከጥፋት ሊያድን ቀርቶ ራሱም ይጠፋል፡፡ ቅዱስ አባታችን መተኛታቸውን ያወቅን ሰወች፦ በዙሪቸው ከበው በከንቱ ውዳሴያቸው የሚያፈዟቸውን አሽቃባጮች መገሰጽና እሳቸውንም የመቀስቀስ ግዴታችን ነው፡፡ 

እስካሁን አልተቀሰቀሱም ማለት አይደለም፡፡ አሽቃባጮቻቸው ግብረ በላወች ጠልተው እንድንጠላ እስኪያደርጉን ድረስ በየግላችን ከቅስቅሳም በጠነከረ ጉትጎታ ጎትጉተናቸዋል፡፡ ከነቁ በኋል ተመልሰው እንዳይተኙ ማድረግ የሚቻለው የግል ጉትጎታችንን አቁመን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሳለ የደቂቀ አዳምን ዋይታ ለባሕርይ አባቱና ለደቂቀ አዳም ባሰማበት ድምጽ ተባብረን ብንጎተጉታቸው ይመስለኛል፡፡ 

ራሳቸው ባንደበታቸው ለሚያቆርቡት ሕዝብ ሲያሰሙት በኖሩትና አሁንም በሚያነቡት “ኢየሱስ እንዘ ሀሎ በመስቀሉ ገዐረ በሕማሙ፡፡ ወጸርሐ ኀበ አቡሁ፡፡ . . . . . . ወኀበ አዳም ገብሩ፡፡ ወለኩሎሙ ደቂቁ “(ሠለስት ምዕት ቁ 97_97) በሚለው በመጽሐፈ ቅዳሴያችን ተባብረን ብንጎተጉታቸው ተመልሰው የሚተኙ አይመስለኝም፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቀራንዮ አደባባይ በመስቀል ላይ ሆኖ ለባህርይ አባቱና ለደቂቀ አዳም ያሰማው ድምጽ የህዝቡን ሥጋዊና መንፈሳዊ ቁስል ነው፡፡ ቅዱስ አባታችን በሚቀድሱበት ጊዜ ሁሉ በመንበሩ ላይ ሆነው ከላይ የተጠቀሰውን የሚያሰሙት በመጎዳት ላይ ላሉት ለቆራቢወች ነው፡ ፡ ይህን የመሰለ እጅግ የከፋ መከራ በህዝህብ ላይ ሲደርስ የሁሉንም ድምጽ ጠቅልለው ከመንበሩ ውጭ በሩቅና በቀርብ ላለው ሁሉ ደቂቀ አዳም በመስቀል አደባባይ ማሰማት ግዴታ አለባቸው፡፡ 

አባቶቻችን በአዲስ አበባ መካከል መስቀል አደባባይ ብለው ለይተው የሰየሙልን ቦታ፡ ይህን የመሰለ ከባድና ዘግናኝ መከራ በህዝብ ላይ ሲደርስ ቅዱስ ፓትርያርካችን የህዝቡን ዋይታ በአንደበታቸው ለደቂቀ አዳም ሁሉ እንዲያደርስቡት ነው፡፡ ከራሳቸው እስከ እግር ጥፍራቸው ማንም በማይለብሰው ነዋየ ቅድሳት ተሸፍነውና ተሞግሰው በመንበሩ ላይ የተቀመጡት፡ በሰላም ጊዜ እግዚአብሔርን እየቀደሱ እንዲያስቀድሱበት ይህን የመሰለ መከራ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ሲገጥመው ልቅሶውን ዋይታውን እንዲያሰሙበት እንጅ፦ የተለየ ሰው ሆነው ሲወለዱ ከናታቸው ማኅጸን ይዘውት መጥተው ሲሞቱ ተገንዘበው ወደ መቃብር እንዲሸኙበት አልነበረም፡፡ 

የናቶች ልቅሶ ያዛውንቶች ዋይታ የወጣቱ እልቂት አሳስቧችሁ የምታዝኑ የምታለቅሱ የምታነቡ የምትጮኹ ሁሉ፦ በየቤተ መቅደሱ “ሰላም ለኩልክሙ” የምትሉ ቀዳሾች፡ በክርስቶስ ሰምራ ሽምግልናውን የጀምራችሁት አዛውንቶች፡ በተለያዩ የሙያ መስኮች ተሰልፋችሁ የህዝብ አንቂ የሆናችሁ፡ ሊቃውንት፡ ጸሐፊወች፡ አርቲስቶች፡ በፈጠርናቸው ዩቱቦች የየግል ቤተ ሰብ ፈጥረን የምንጮህ ሁላችን ፡ጫጫታችንን አቁመን ቅዱስ አባታችንን ከተኙበት ነቅተው የሁላችንን ድምጽ በመስቀል አደባባይ ለዓለም እንዲያስሙ ከተኙበት እንቀስቅሳቸው፡፡  

ሁላችንም በመተባበር እንዲነቁ ጎትጉተናቸው ካልሰሙ ሞተዋል ማለት ነው፡፡ እኛን የወከሉበትን ነዋየ ቅድሳት ከሞተው አካላቸው ለይተን እንደማነኛውም መናኝ መነኩሴ በሰሌን ገንዘን ልንቀብራቸው ይገባል፡፡ ካልሞቱ “የማያስተውሉ ውል የሚያፈርሱ ፍቅር የሌላቸው ምህረት ያጡ ናቸው፡፡ እነዚህን ለሚያደርጉት ሞት ይገባቸዋል የሚለውን የእግዚአብሔርን ሕግ እያወቁ እነዚህን ከሚያደርጉ ጋራ ይስማማሉ እንጅ አድራጊወች ብቻ አይደሉም”(ሮሜ 1፡31_32) የሚለውን ሐዋርያዊ ትውፊት ተከትለን በእግዚአብሔርና በዓለም አደባባይ ከሰን ልናቆማችን ቀኖናችን ይፈቅድልናል፡፡ 

እግዚአብሔር እንድንቀሰቅሳቸው እኛን ይርዳን፡፡ ተቀስቅሰው እንዲነቁ ቅዱስነታቸውንም ይርዳቸው! 

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ¹⁵ የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ ፥ ¹⁶ ተራራዎችንና   በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን ፤ ¹⁷ ታላቁ የቁጣው ቀን  መጥቶአልና ፥ ማንስ ሊቆም ይችላል ? አሉአቸው ። ራእይ 6 ፤  15_17 ይኽ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ። የኢየሱስን ልደት ሰናከብር የየሐንስ ራእይን ማንበብ ጠቃሚ ይመስለኛል ። ምክንያቱም በመጨረሻው ዘመን

ከኢየሱስ የፍርድ ቀን በፊት በህሊናችን ውስጥ ፍቅርን ለማንገስ እንጣር 

የምጣኔ ሀብታዊ ፍጥ፣ የፖለቲካ፣ የእውነትና የሰብአዊ መብት ታጋይ፣ የአመኑበትን ነገር ለመናገር እንደ ፖለቲከኛ በቃላት ሳያሽሞነሙኑ ቀጥታ የሚናገሩት የሀገሬ ኢትዮጵያ ታላቅ ሰው ነበሩ “ዘር ቆጠራውን ተዉት፤ የአባቶቻችሁን ሀገር ኢትዮጵያን አክብሩ!”  አቶ ቡልቻ ደመቅሳ

ሀገር ወዳዱ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ

January 6, 2025
ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። ) “ገብርዬ ነበረ

ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ?

January 3, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ዛሬ እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር ጥር 1ቀን 2025 ዓ/ም ነው ። አውሮፓውያኑ አዲስ ዓመትን “ሀ” ብለው ጀምረዋል ። አዲሱን ዓመት ሲጀምሩም ከልክ ባለፈ ፈንጠዚያ ነው ። ርቺቱ ፣ ምጉቡና መጠጡ

ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። )

Go toTop