ሕወሃቶች የአማራውንና የሌላውን ኢትዮጵያዊ ሥነ ልቡና ቀርጥፈው የበሉ ናቸው። በአማራ ሕዝብ ላይ ፊት ለፊት ጦርነት ከፍተው ካደረሱበት ጥፋት ይልቅ በዚህ እውቀታቸው ተጠቅመው በሠሯቸው ሴራዎች የጎዱት ጉዳት ይከፋል። ሕወሃቶች በየትኛውም ተቃዋሚ አካል ውስጥ አንድ ጠንካራ መሪ ሲያጋጥማቸው በመጀመሪያ የሚያደርጉት መሪውን ከሕዝቡ የመነጠል ሥራን መሥራትን ነው። ያንን ተቃውሞ ፊት ለፊት ከመጋፈጣቸው በፊት መሪውን ከሕዝቡ ይነጥለዋል ያሉትን ድርጊት ሁሉ ይፈጽማሉ። ይህንን ለማድረግ ያለ የሌለ አቅማቸውን (ከገንዘብ እስከ ተንኮል) ይጠቀማሉ። ተንኮላቸው ደግሞ የሕዝቡን ድክመት በረቀቀ ስልት ለዓላማቸው ስኬት የሚጠቀም ነው። ሕዝቡን የተሳሳተ መረጃ በመስጠት፣ በማሸበር፣ አሉባልታ በመንዛት፣ መሪው ላይ ጫና አድርሶ ወይም አዘናግቶ በማሳሳት፣ ወዘተ ብዙ ብዙ ዘዴዎች አሏቸው።
በዚህ ተግባር የተሳካ ሥራ በመጀመሪያ በራሳቸው መሪዎች ላይ ሠርተው የመጡ ናቸው። እነ አረጋዊ በርሄ ላይ ማለት ነው። መሪዎቹ ላይ አደጋ ከማድረስ ይልቅ ይህኛውን ስልት ተመራጭ አድርገው በርትተው እና የተራቀቀ ተንኮል ዘርግተው ይንቀሳቀሳሉ። ያ ከሕዝብ የነጠሉትን ሰው አንዴ ከነጠሉት በኋላ እንኳንስ ሊያጠቁት ይቅርና ሊያቅፉት ሊስሙትም ሁሉ ይቻላሉ።
ልደቱ አያሌውን በቅንጅት ዘመን ምን እንዳደረጉት እናስታውሳለን።
አቢይ አህመድን ከአማራው ለመነጠል የሄዱበት ቀዳሚው እና እስከዛሬ ይፋ ያልወጣው መንገድ የደምቢዶሎው የተማሪዎች እገታ ነው። በአማራ ክልል በድፍኑ እስከታችኛው መንደር ድረስ ብአዴንን ተጠቅመው በቃ! የሚል ሰልፍ አስወጥተውበታል። በቡዳ ቤት ሰላቢ ገባ ሆኖ አቢይ ነገሩን በላያቸው ቀልብሶ እሳት ቢያዘንብባቸውም። በቃ! የሚለውን በኖሞር! አስጠልፎ ዱቄት ቢያደርጋችውም። ከአማራው ሕዝብ ግን በተሳካ ሁኔታ ነጥለውታል። ልብ በሉ በዘወርዋራ መንገድ ነው ያጠቁት። በኦነግ ውስጥ ያላቸውን መዋቅር ተጠቅመው ልጆቹን ካሳገቱ በኋላ በብአዴን ውስጥ ባላቸው መዋቅር ነው ዳር እስከዳር ሰላማዊ ሰልፍ ያስወጡበት። መቼም በአማራ ክልል ብአዴን ሳይሳተፍበት እስከታችኛው መንደር እንኳን ሰው ዝንብ ያልሞተበት የተሳካ ስላማዊ የተቃውሞ ሰልፍ አይወጣ እንደነበር እናስታውሳለን። የዛሬውን አያድርገውና (ወይስ ያድርገውና ነው የሚባለው?)።
ሕወሃቶች ከአቢይ ጋር ከገጠሙ በኋላ በዚሁ የአማራን ሥነ ልቡና ቀርጥፎ በበላው ዘወርዋራ ስልታቸው የእነሱ እጅ ፈጽሞ እንዳይጠርጠር አድርገው የፋኖ መሪዎች ላይ (በተለይ ዘመነ ካሴ እና እስክንድር ነጋ ላይ) ከተመሪው የመነጠል ሰፊ ዘመቻ አካሂደዋል። በአምሳ አመት የክፋት ጉዟቸው ተንኮላቸውን አራቅቀውት ሲጠቀሙብህ እንኳን እንዳይታወቅህ አድርገው ነው የሚጠቀሙብህ።
ሕወሃቶች ይህንን ተንኮላቸውን በኤርትራውያን እና በኦሮሞዎችም ላይ ሞክረውት ነበር። ያው እጃቸውን ሠውረውና የሚጠቀሙባቸው ሰዎች ጭምር የሌላ መጠቀሚያ መደረጋቸውም ሳይታወቃቸው ማለት ነው። መጠቀሚያ የተደረጉት ሰዎች ጭራሽ ሕወሃትን የሚቃወም አቋም ያላቸው ሁሉ ሊሆኑ ይችላሉ። ነገር ግን የኦሮሞ እና የኤርትራውያን ሥነ ልቡና ከአማራው ሥነ ልቡና ስለሚለይ ተንኮሉ በበቂ ሁኔታ አልሠራላቸውም። አቢይን ከኦሮሞ ለመነጠል ያደረጉትንም፣ ኢሳያስን ከኤርትራ ሕዝብ ለመነጠል የሄዱባቸውንም ርቀቶች እና ያገኙትን ደካማ ውጤት ልብ ይሏል።
ዛሬስ ወልቃይትን በጦርነት ማግኘት የማይሞከር መሆኑ ከገባቸው በኋላ ሕወሃቶች ጥርስ ወደ ነቀሉባት የመሪ መነጠል ተግባራቸው ተመልሰው ገብተው ይሆን? ብለን እንጠይቃለን። “መጀመሪያ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱን ከሕዝቡ እንነጥለው። ከዚያ በኋላ ወልቃይትን ብናጠቃ ውጤታማ እንሆናለን” ብለው አስበው ይሆን?
ይህን ያስባለኝ እጅግ የማደንቀው የቀድሞው የኢትዮ 360 ባልደረባና እውቁ ፖለቲከኛ ኤርምያስ ለገሰ በአንድ የትግሬ ሚድያ ቀርቦ ስለወልቃይት የሰጠው ትንተና ነው። አቢይ በሕወሃት እና ብልጽግና ጦርነት ዋዜማ ወልቃይትን ለሦስት አካላት ሸጦታል ይላል ጭብጡ። ለጎንደሬዎች፣ ለኤሚሬትስና፣ ለዱባይ። እውነት መሆኑም አያጠራጥርም። በነገራችን ጣልቃ ወልቃይትን ብዙ ባእዳን (እስራኤልና እንግሊዝን ጨምሮ) ለሰፈራ፣ ለቅኝ ግዛት ወይም ለእርሻ መሬት ሲመኝዋት ኖረዋል። ዱባይም ብትቋምጥ አይገርመኝም ለማለት ነው። በገጠርም በከተማ በኢትዮጵያ ያለውን ማፈናቀል መጠነ ሰፊ ባጀት መድባ በገንዘብ እያገዘች ተቃዋሚዎችን ለማደንም የደህንነት ድጋፍ እየሰጠች መሆኑ ያደባባይ ምሥጢር ነውና። ይህም አቢይ አህመድ ወደ ሥልጣን ከወጣበት ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ የተደረገና እየተጠናከረ የመጣ ነው። ወደ ጉዳያችን ስንመለስ ፖለቲከኛው ኤርምያስ ለገሠ ይቺን ነገር በዚች ወቅት ያውም በትግሬ ሚዲያ ያለ አንዳች የጋራ ፖለቲካዊ ስሌት እንደማያነሳት በማመን ይሄ ሕወሃቶች እጃቸውን ሠውረው በገዛ ተቃዋሚዎቻቸው እጅ ሳይቀር እየተጠቀሙ የሚነዙት ውዥንብር ኮሎኔል ደመቀን የመነጠል ስልት ይሆን ወይ? ብዬ ለመጠየቅ ተገድጃለሁ። ምክንያቱም ጥቃቱ ከተለያዩ አቅጣጫዎች በተሰበጣጠረ መልኩ ግን በአንድ ጊዜ እየተካሄደ ስለሆነ የኦክቶፐስ ዐይነት ብዙ እጆች ያሏትና የሌሎችንም እጆች ሳይታወቃቸውም ጭምር የምትጠቀመው ሕወሃት ስትወራጭ ታይቶኝ ነው። ሕወሃትን የምናውቃት ሁላችንም ነገሩን እስኪ እንመርምር። አራት ኪሎን ለመቆጣጠር በሁለት ዙር ከተጋችው ትጋት በላይ ነው ወልቃይትን ለመቆጣጠር አሁን እየተጋች ያለችውና።
ጠርጥር ከገንፎም አለ ስንጥር። ያልጠረጠረ ተመነጠረ እንደሚሉት ግራና ቀኝ ማየት ያስፈልጋል። ወልቃይት የኮሎኔል ደመቀ ብቻ ስላልሆነ ሁሉም አማራ፣ በይበልጥ ደግሞ ሁሉም ጎንደሬ የወልቃይትን ጉዳይ በንቃት እንዲከታተል በአንድ በኩል በሌላ በኩል ደግሞ ሁነኛና ጀግና ወንድም፣ ብልህ አስተዳዳሪ፣ ያለ አግባብ እንዳናጣ አድርገን በጥንቃቄና በአስተውሎት እንድንጓዝ እመክራለሁ። አልፎ ተርፎ የወልቃይት ጉዳይ የኢትዮጵያን፤ የኤርትራን እንዲሁም የቀረውንም ምሥራቅ አፍሪካ መጻኢ የሚወስን ጉዳይ በመሆኑ ሁሉም በአንክሮ ይከታተለው።
ሰሞነኛው የጨፍጫፊዎቹ የሕወሃትና የኦነግ እንቅስቃሴም ከብልጽግና ጋር የጋራ ሴራ ውስጥ መዘፈቃቸውን የሚያጋልጥ ነው። የሕወሃት ሁለት አመት ያለፈበት “ትጥቅ እየፈታሁ ነው” ማላገጫ እና የጨፍጫፊው ኦነግ “መንግሥት በታጣቂዎች የሚደረግ ጭፍጨፋን ያስቁምልኝ፡ ማላገጫ (መግለጫ) የደራ የሦስትዮሽ ቁማር በአማራው ላይ እየታሰበ መሆኑን ያመላክታል (አዎ ቅኔ አለው)። በተለይ የፋኖ ግስጋሴና ሀገር አቀፍ ድጋፉ እጅግ ሥጋት እንደሆነባቸው ይህንንም ለመቀልበስ የማይፈነቅሉት ድንጋይ እንደማይኖር ግልጽ ነው። ወልቃይት ደግም ለቁማርተኛው አቢይ አህመድ እንደ ጆከር የሚታሰብ ነው። ያለበትን አጣብቂኝ ባልረዳም በግሌ ደመቀ ሕወሃትን ወደ ወልቃይት አምጥቶ ወልቃይት ተመልሳ የአማራ ቄራ እንድትሆን ያደርጋል ብዬ አላምንም። (በቅንፍ ውስጥ በሕወሃት ዘመን ወልቃይት ኦህዴድ፣ ብአዴንና ሕወሃት ከባእዳን አካላት ጭምር በጋራ የሚያካሂዱት የኦሮሞ ቄራም የተቋቋመባት ሥፍራ ነበረች። ነገሩ ከሕዝብ ተሸፋፍኖ እንዲቀር ቢደረግም። )
እንደምንመኘው አማራ ላይ የሕልውና ስጋት ያልደቀነ ሕገ መንግሥት ቢኖረን እና አንቀጽ ሰላሳ ዘጠኝ የምትባለው የንብረት ዘርፎ ማሻገሪያ አንቀጽ ባትኖር፣ ሁሉም ባሻው ሄዶ መኖር ቢችል ምኞታችን ነው። እስከዚያው የሌላውን ርስት ይዞ ለመሮጥ የሚደረገውን መንደፋደፍም ሆነ ሰውን በገዛ አገሩ በትግሪኛ ሞጋሳ ለመሰልቀጥ የሚደረገውን ክፋት እንቃወማለን። በአጭሩ የሁላችንም ካደረግነው የሁላችንም እናድርገው፤ ካለበለዚያ እዚያው በጸበልህ!
የኦሮሞውና የኤርትራዊያን ስነ ልቦና ከአማራው የሚለየው የቱ ላይ ነው? ብታመላክተን የተሻለ ነበር። የእኔው እይታ ግን ሻቢያ የወያኔ የነፍስ አባት ስለሆነ ያቃመሳቸው ራሱ የቀመሰውን ተንኮል በመሆኑ እኔም ጉንድሽ አንተም ጉንድሽ እንደሚሉት ዘይቤ ካልሆነ በስተቀር ወያኔ ሻቢያን ሾኬ መጥለፍ አይችልም። ሻብያም አይሞክረውም። ኦሮሞውን ደግሞ የሚለየው በተሳከረ የፈጠራ ታሪክ ልክ እንደ ሻቢያ ሃገር እንሆናለን እያሉ መቃጀታቸው አንድ ያደርጋቸዋል። ግራም ነፈሰ ቀኝ የወያኔና የሻቢያ የዝንተ ዓለም ትግል ያተረፈው መከራና ስደት ለመሆኑ በየዓለማቱ የተሽጎጡትና በተስፋ በመከራ አምልጠው በመንገድ ላይ የሚመሰክሩት ስለሆነ ቋሚ ምስክር አያሻም። ይህን በዚሁ ዘለን ወደ አማራው ስንመለስ ደግሞ በመጣ በሄደው በተለይም በሻቢያ፤ በወያኔ እንዲሁም አይናቸው ደብዝዞ፤ ጉልበታቸው ዝሎ ዛሬ ላይ ቆመው ” የፌደራል መንግስቱ አዲስ አበባ ላይ መሬት የለውም” የሚሉትና ዋንኛው ጠላትህ አማራ ነው በሚሉ የእብድ ስብስቦች የተሞላው የኦሮሞ ፓለቲካ ነው። እነዚህን ሶስት ሃይሎች የሚያስተሳስራቸው ደግሞ ለአማራ ህዝብ ያላቸው በትርክት ላይ የተመሰረተ ጥላቻ ነው። ሙትን ሙት እየተካው የሃበሻው የመጠላለፍ ፓለቲካ በብሄርና በቋንቋ ይሰመር እንጂ ግቡ አንድ ነው። ይኸው ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ። እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል ነው። በትግራይ እልፍ ወጣት ሲያልቅ አንድም የትግራይ ባለስልጣን ልጅ የውጊያው ተሳታፊ አልሆነም። ይባስ ተብሎ በውጭ ሃገር ተቀምጠው በለው ያዘው ሲሉ እንደነበር መረጃው ብዙ ነው። እልፍ እያለቀሰ እነርሱ ሊስቁ!
ታዲያ ወደ ዋናው ቁም ነገር ስንመለስ ወያኔ በአማራ ህዝብ ላይ ባለው ጭፍን ጥላቻ የተነሳ ይህን ህዝብ እርስ በእርሱ ለማናከስም ሆነ ሰርጎ በመገባት ለማባላት የማይገለብጠው ድንጋይ አይኖርም። በፊትም አርጎታል። አሁንም አይተኛም። ግን ጀግናው ኮ/ሌ ደመቀ የወያኔን ሴራ ውስጥና ውጭውን ጠንቅቆ የሚያውቅ የቁርጥ ቀን ልጅ ለመሆኑ ሥራው ትላንትና ዛሬም ይመሰክራል። እርግጥ ነው ጥንቃቄ ማድረጉ መልካም ነው። ግን ብልጽግናም ሆነ ወያኔ ከአሁን በህዋላ ወያኔ በግድ ከቤጌምድርና ሰሜን ጠ/ግዛት ቆርሶ የእኔ ነው ያላቸው ቦታዎች ተመልሰው ትግርኛ ተናጋሪና ትግሬ ብቻ የሚኖርበት ማድረግ አይችልም። ልክ እንደ በፊቱ አብሮ ለመኖር ግን ትግሬውና አማራው ብቻ ሳይሆን በአራቱም አቅጣጫ ያለው የሃገሪቱ ሰው ሁሉ መኖር የማይነፈግበት ምድር መሆን ትችላለች። ሌላው ሁሉ የጥላቻና የወረራ ወሬ ራስን ለማሰንበት የሚደረግ የጨለምተኛ ብሄርተኞች ቀቢጠ ተስፋ ነው።
ባጭሩ የአለም ፓለቲካ እየተሽመደመደ ባለበት በዚህ አስጊና ሁሉም ሮኬት ወንጫፊና አስወንጫፊ፤ ድሮን ተጠቃሚ በሆነበት ጊዜ የዛሬ 50 ዓመት የተጠቀሙበትን የጦር ስልት ይዞ እንዘጥ እንዘጥ ማለቱ ማንበብና መጻፍ የማይችሉ ለፍቶ አዳሪዎችን ለማሰቃየት እንጂ ጦር ተገጥሞ አንድ አንድን የሚያሸንፍበት ዘዴ አይሆንም። መገዳደል ግን ይቻላል። እያደርግን ያለነውም ይህኑ ነው። ወንድምና እህቱን ገድሎ ፎካሪ ጀግና ተብሎ ተሸላሚ! ወያኔ ከበረሃ እስከ ከተማ ያለተንኮል መኖር ስለማይችል ያው ብልጽግናን መቅረቡ ለተንኮል እንጂ ለሰላም እንደማይሆን የታወቀ ነው። አሁን እንሆ ትጥቅ ተፈታ መባሉ ራሱ የውሸት ፓለቲካ ነው። ገንዘብ ተቀብሎ ራስን ዳግም ለማስታጠቅ የወዳደቀና የማይሰራ መሳሪያን ከቀበሩበት እያወጡ በማስረከብ ራሳቸውን አታለው ዓለም እንደሚያታልሉ ከወዲሁ መገመት ይቻላል። ራሱ በጌታቸውና በደብረጽዪን መካከል አለ የሚሉት ሽኩቻም ለማስመሰል እንጂ ጊንጥ ጊንጥን ሲነድፈው አይተን አናውቅም። የወያኔ መሪዎች ከላይ እስከ ታች ያሉት አመራሮችና ካድሬዎች እጃቸው በሰው ደም የጨቀየና በተንኮል ጥቢራቸው የዞረ ነው፡፡ ለበሽታቸው ከሞት ሌላ መድሃኒት የለውም። የሚያሳዝነው ግን ወያኔ ይህን ሰራ ያን ሰራ ይለን የነበረው ብልጽግናም እርምጃው ሁሉ ልክ እንደ ወያኔ ለእኔ ብቻና ግፈኛ መሆኑ የቱን ያህል ምድሪቱ ፈውስ አልባ እንደሆነች ያሳያል። ወቸው ጉድ አያድርስ ነው የሃበሻ ፓለቲካ! ለሁሉም ጠንቀቅ፤ ልቅም ብሎ መኖሩ ነገን ለማየት ይረዳል።