November 22, 2024
16 mins read

የእንጦስን፣ የዮሐንስ አፈወርቅንና የቴዎፍሎስን ፍለግ ትተው የጣኦትን መንገድ የተከሉት መነኮሳት!

በላይነህ አባተ ([email protected])

453333

የቤተክርስትያን ታሪክ እንደሚያስተምረው በክርስትና ዓለም ምነናን ወይም የባህታዊ ኑሮን በሶስተኛው ክፍለ-ዘመን የጀመረው እንጦስ የተባለ መነኩሴ ነበር፡፡ እንጦስ ከሐብታም ቤተሰብ የወጣና ራሱም በውርስ ሐብታም የነበረ ሰው ነበር፡፡ ዳሩ ግን እንጦስ የዚህችን ዓለም ከንቱነት ተገንዝቦ የማቴዎስ ወንጌል ፲፱፡፳፩ ላይ ““ፍጹም ልትሆን ብትወድስ ሂድና ያለህን ሁሉ ሺጠህ ለድሆች ስጥ ሰማያዊ ሐብትም ታገኛለህ፤ መጥተህም ተከተለኝ”  ባለው መሰረት  ክርስትያን ወላጆቹ ያወረሱትን ሐብት ጥርግ አርጎ ለድሀ መጽውቶና አካላዊ ስሜቱን ከሰውነቱ አስወግዶ ገዳም በመግባት የብትሁትናን ዓለም ጀመረው፡፡ [1] የድሮዎች የኢትዮጵያ መነኮሳት ይከተሉት የነበረው ይኸንን የእንጦስን የምንኩስናና የምነና ሥርዓት ነበር፡፡ የእኔን አያት ጨምሮ የኢትዮጵያዊ ሴት አያቶች የመጨረሻውን ዘመናቸውን የሚጨርሱት ሐብታቸውን ለድሃ አካፍለው፣ አካላቸውንና ስሜታቸውን በፆምና በጸሎት አድቅቀው ተገዳማት ውስጥ በአቃቢነት በማገልገል ነበር፡፡

የእጦስን ፈለግ በመከተል ከክርስቶስ ልደት ሶስት መቶ አምሳ ዓመታት በኋ የመነኮሰው ዮሐንስ አፈወርቅ (በክሪኮች አጣራር Yannis Chrysostoma) ያደረገው ይኸንኑ ነበር፡፡ ዮሐንስ አፈወርቅ እንደ እንጦስ ይኽንን ዓለም ንቆ ሐብትን ለድሃ መጽውቶ ከመመነንም ባሻገር በሃይማኖት ትምህርት ጥልቅ እውቀት አካብቶና ተመራምሮ ምንኩስናን ሕዝብን ከጣኦት አምልኮና ከአረመኔአዊ ሥርዓት የሚያላቅቅ የሰማእትነት ሥራ አሸጋገረው፡፡ ወታደር አባቱ በልጅነቱ የሞተበት ዮሐንስ አፈወርቅ  አእምሮው ብሩህ የነበረና ተምሮም እንደ ቅዱስ ጳውሎስ ሁሉ የሕግ ባለሙያ የነበረ ሰው ነበር፡፡ ዮሐንስ አፈወርቅ ከሶቅራጥስ፣ ከፕሌቶና አርስቶትል ጀምሮ በእርሱ ዘመን እስክነበሩት ድረስ የነበረውን የፍልስፍናና የመንፈስ ልእልና እውቀት እኝክ አርጎ በልቶና ጥልቅ በሆነ የክርስትና ሃይማኖት ፍልስፍና ባህር ዋኝቶ ወጥቶ ሕዝብን የሚያስተምርና ክርስትናን የሚያስፋፋ ሊቅ ነበር፡፡ አፈወርቅ ወይም Chrysostoma የሚለው ስም የተሰጠውም ሲወለድ ሳይሆን ከአንደበቱ እንደ ወርቅ እየፈለቀ በሚወጣው የእውቀትና የመንፈስ ልእልና ትምህርቱ ነበር፡፡ በግሪክ Chryso ማለት ወርቅ ሲሆን stoma ደሞ አፍ ነው፡፡ [2]

በጊዜው የኮንስታቲኖፕል ግዛት ፓትርያርክ የነበረው የዮሐንስ አፈወርቅ ገድል ክርስትናና ሥነ-ምግባርን በማስተማር ላይ ብቻ አልነበረም፡፡ ዮሐንስ አፈወርቅ የወርቅ ነፀብራቅ በሆነው አንደበቱ ገዥዎች ሕዝባቸውን ሲያሰቃዩና ውስልትና ዓለም ውስጥ ሲገቡ አጥብቆ ይገስጥ ነበር፡፡ ባርነትን በመቃወም ባርያዎች ነፃ እንዲወጡ ይታገል ነበር፡፡ ገዥዎች መጠን የለሽ ድግስ እየደገሱ ከመጨፈር ይልቅ ሆስፒታልና ሌሎችም የሕዝብ አገግሎቶች እንዲገነቡ ይሰብክ ነበር፡፡ እንደዚህ ዓይነቱን በውስልትናና በጭካኔ ላይ ያነጣጠረ ስብከቱን ያልወደዱት የኮንስታንቲኖፕል ገዥዎች ከፓትሪያሪክነት አውርደው በግዞት እንዲኖር አደረጉት፡፡ ዳሩ ግን በግዞት መቀመጥ በጀመረ በጥቂት ቀናት ውስጥ በግዛታቸው የመሬት መንቀጥቀት ስለደረስ ገዥዎች ከሰማይ የወረደ ቁጣ ነው በሚል ተርበተበቱና ለመነው እንደገና በፓትሪያሪክ ቦታው አስቀመጡት፡፡ ዮሐንስ አፈወርቅ አሁንም አረመኔ ገዥዎችን መታገል ስለቀጠለና ለስልጣናቸው ስላሰጋ እንደገና ወደግዞት ከተውት የምድር ቅድስና ኑሮውን እዚያው ፈጠመ፡፡ [2]

የክርስትናን፣ የምንኩስናና የእነ ዮሐንስ አፈ ወርቅን ረቂቅ ምስጢር በሚገባ ያጠኑትና የየሚያውቁት ሊቁ አቡነ ቴዎፍሎስም የዮሐንስ አፈወርቅን ፈለግ ተከትለው የቅድስና ኑሮ ኖረው እንዳለፉ ስራቸው ይመሰክራል፡፡ ከብሩህ አእምሮ ጋር በ1910 ዓ.ም የተወለዱት አቡነ ቴዎፍሎስ ከፊደልና አቡጊዳ የትምህርት ወለል እስከ መጨረሻው የሃማኖት ትምህርት ጣራ ያለውን የእውቀት መድብል ሁሉ እንደ ጤፍ አበጥረው፣ ፈጭተው፣ አቡከተውና ጋግረው የበሉ ሊቅ እንደነበሩ  በክርስቶስና በሶቅራጥስ ላይ እንደ ደረሰው የውሸት ክስ ደርተው ባስገደሏቸው ቀናተኛ ሸረኞች ሳይቀር ይታወቃል፡፡ አቡነ ቴዎፍሎስ ድፍን አዲስ ኪዳንን ተርጉመዋል፡፡ ከውጪ አገር እንግሊዘኛ፣ ጣላኒያንኛ፣ ፈረንሳይኛና አረብኛን  ጨምሮ በጠቅላላ  ዘጠኝ ቋንቋዎች ይናገሩ እንደነበር በቅርብ የሚያውቋቸው ሰዎች መስክረዋል፡፡ በዚህ የቋንቋ ችሎታቸውም የእነ ዮሐንስ አፈ ወርቅን ወርቃማ ሃይማኖታዊና የፍልስፍና ስራዎች ፈትሸዋል፡፡ እንደ ወረቅ በሚፈልቀው አንደበታቸው እየሰበኩም በተለይ ጳጳስ ሆነው ባገለገሉበት ሃረርጌ ክርስትናን አስፋፍተዋል፡፡ በ1975 ዓ.ም አቡነ ቴዎፍሎስ የዓለም አቀፍ ቤተክርስትያኖች ጉባኤ መሪ ሆነው እንዲያገለግሉ ቢመረጡም ዮሐንስ አፈወረቅን በግዞት እንዳስቀመጡት የኮንስታንቲኖፕል ገዥዎች ሁሉ ወጠጤ የኢትዮጵያ የወታደራዊ ገዥዎች ስላሰሯቸው አገልግሎቱን ሳያበረክቱ አልፈዋል፡፡ [3]

እንደ ዮሐንስ አፈወርቅ ሁሉ አቡነ ቴዎፍሎስ  ሕዝብ የሚበድሉ ገዥዎችን አስጠንቅቀዋል፡፡ ኮሚኒዝም ያሳበደው ወታደራዊ አገዛዝ ሕዝብ ያለ ፍርድ ሲፈጅ አቡነ ቴዎፍሎስ በቃል ብቻ ሳይሆን የቤተ-ክርስትያን ልሳን በነበረችው አዲስ ሕይወት መጽሔት ተቃውሟቸውን ገልጠዋል፡፡ በዚህ ያልተደሰተውና በወጠጤዎች የተሞላው ወታደራዊ አገዛዝ እኒያን የመሰሉ አባት ወህኒ ቤት ከቶ ያለምንም ርህራሄ ደብድቦና አንቆ ገድሏቸዋል፡፡ [3]ተዚች ከንቱ ዓለም ከተገላገሉ በኋላ አባ እንጦስና ዮሐንስ አፈወርቅ ገድላቸውን ተዘክሮ የቅድስና እውቅና ተሰጥቷቸዋል፡፡ “መላክ በአገሩ አይከበር ሆነና” እኛ ግን አቡነ ቴዎፍሎስን እንኳን የቅድስና ማእረግ እንዲሰጣቸው ልንታገልላቸው የእርሳቸውን ቆብ ደፍተውና በእርሳቸው መንበር ተቀምጠው ቤተክርስትያኗን እየናዱና እሳት እንደነካው ላስቲክ እያጨማደዷት ያሉትን ፓትርያሪክና ጳጳሳት በሚያሳፍር መልኩ “ብጹእ ቅዱስ” ብለን እየጠራን መኖሩን ቀጥለናል፡፡ እነዚህ ፓትርያሪክና ጳጳሳት የዮሐንስ አፈወርቅንና የአቡነ ቴዎፍሎስ ፍለግ ሳይሆን የጣኦትን መንገድ እየተከተሉ መሆኑም አልታዬን ብሏል፡፡

የጣኦት አምልኮ ሲነሳ ለብዞቻችን በዛፍ፣ በድንጋይ፣ በወንዝ ወይም በተራራ ማምለክ ብቻ ሊመስለን ይችላል፡፡ በጣኦት ማምለክን በ12ኛው ክፍለ-ዘመን የኖረው ቶማስ አኩይናስ  የተባለ አቻ ያልነበረው የክርስትና ፍልፍስና ሊቅ ሱማ ቲዮሎጂካ በተባለው ግዙፍ ጽሑፉ እንዲህ ሲል ይገልጣል፡-“ ገንዘብ፣ ስልጣን፣ ዝናና የሚያስፈነጥዝ ድሎት የሰይጣን ምሳሪያ ጣኦቶች ናቸው” ይላል፡፡ ሰይጣን እንኳን ሰውን ክርስቶስን ሳይቀር ተራራ ላይ አውጥቶ በከተማና በገንዘብ እንደፈተነው ይታወቃል፡፡ ፓትርያሪኩን ጨምሮ አብዛኞቹ የዚህ ዘመን የኢትዮጵያ ጳጳሳት ለገንዘብ፣ ለስልጣን፣ ለዝናና ለድሎት ሲሉ ለግፍ ፈጣሚ ገዥዎች ስለሚያደገድጉና ስለሚሰግዱ፣ በአስራትና በስለት ገንዘብ አሞላቀው የሚያኖሯቸው ምዕመናን በባሩድና በድሮን ሲያልቁ ራሳቸውን እንደሰጎን ራስ ቀብረው ስለሚኖሩ ከእንጦስ፣ ከዮሐንስ አፈወርቅና አቡነ ቴዎፍሎስ በተቃራኒ የክርስቶስን መንገድ ሳይሆን የጣኦቶችን ፈለግ ተከትለዋል ማለት ይቻላል፡፡ የዘመኑ የኢትዮጵያ ፓትርያሪክና ጳጳሳት እንደ ዮሐንስ አፈወርቅና አቡነ ቴዎፍሎስ ነፈስ ገዳይ ጭራቅ ገዥዎችን ገስፀውና ገዝተው የቅድስና ህይወትን ኖረው ማለፍን ትተው የሕዝብ ደም ተሚጠጡና ሥጋ ተሚዘነችሩ አረመኔዎች ጀርባ ተሰልፈው በምድር ብእር ለዘላለም ሲወጋቸው እንዲኖር በሰማይ ቤትም ከመንግስተ ሰማያት እርቀው መኖርን መርጠዋል፡፡

የዘመኑ ፓትርያሪክና ጳጳሳት “መነኮሰ ሞተ!” የሚለውን መለኮታዊ አባባል በእውቀት አልባ ጭንቅላታቸው “መንኩሰ ናጣጠ!” ብለው ተርጉመውታል፡፡ አብዛኞቹ እንኳን እንደ ዮሐንስ አፈወርቅና አቡነ ቴዎፍሎስ በሃይማኖታዊ ፍልስፍና፣ ቅኔና መጽሕፍተ -ትርጓሜ ሊዘልቁ የአብነት ትምህርት ቤት ደጃፍም እረግጠው ሰላማያውቁና ለእንጀራ ሲሉ ስለመነኮሱ  መከተል የሚገባቸው ሶስት መጻሕፍተ መነኮሳት መጻሕፍት እንዳሉም አላውቅ ብለዋል፡፡ በዚህም ምክንያት “ተገንዘብና ተምቾት” እራቁ የሚለውን ትተው ከደመወዝ ጨምሩ ጭቅጭቅ ዘለው የ”ነፍስ ልጆች” የሚላቸውን ሞኞች ፎቅ እንዲሰሩላቸው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እየጠየቁ እንደ ጥገት ያልቧቸዋል፡፡ “ሰውነት እንደ ኮርማ ተሚያሳብጥ ምግብና መጠጥ እራቁ” የሚለውን ሕግ ጥሰው በፍታትና በተዝካር ስም ምሳና ራታቸው ክትፎና ቁርጥ ተቢራና ውስኪ ጋር እንደሆነ አብዛኛው ምእመን ያውቃል፡፡ “ተገንዘብ ሽሹ” የሚለውን የመጻሕፍተ መነኮሳት ድንጋጌ ቦጭቀውም የቤተ ክርስትያን ንብረት እንደሚሰርቁ፤ የመቃብር ቤት ሳይቀር በአስር ሺዎች ብር እየሸጡ ተሚያመልኳቸው ገዥዎች ጋር ሲከፋፈሉ እንደሚውሉ ይታወቃል፡፡ ይኸን የመሰለው እኩይ ፈልስጣ ሥራቸው አብዛኛው የዘመኑ ፓትርያሪክ፣ ጳጳሳትና ሌሎችም  ገዳሙን ለምእመናን ለቀው ከተማ የሚንፈላሰሱ መነኮሳት የእንጦስን፣ የዮሐንስ አፈወርቅንና የቴዎፍሎስን ፈለግ ሳይሆን የገንዘብን፣ የስልጣንን፤ የዝናንና ድሎትን ጣኦቶች መከተላቸውን ያሳያል፡፡

ይቆየን!

 

ዋቢ፡-

  1. 1. The fabric of the soul is strengthened when the pleasures of the body are weakened.”, Antony of EgyptAntony of Egypt | Christian History Institute

 

  1.  John Chrysostom, John Chrysostom: Did You Know? | Christian History Magazine

 

  1. . Tewoflos, Dictionary of African Chrisitan Biography, Tewoflos (B) – Dictionary of African Christian Biography

 

ህዳር ሁለት ሺ አስራ ሰባት ዓ..

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

ጥር 2 ቀን 2017 ዓ/ም   January 10, 2025  በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡ ቤተ ሰብ፡ ወዳጅ ዘመዶቻችሁን ያጣችሁ: ልጆቻችሁን የቀበራችሁ፡ አካልችሁን ያጣችሁ፡ የተሰነዘረውን ብትር በመከላከል ላይ ያላችሁ፡ያለፈቃዳችሁ በመንግሥት ተጽእኖ ወደመግደልና

በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛ ተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡

January 10, 2025
Go toTop