September 3, 2024
35 mins read

ፋኖነት/አርበኝነት ከየት ወደ የት?

September 3,  2024

ጠገናው ጎሹ

ፋኖ (Patriot/hero/heroine) እና ተቃራኒው የሆነው ባንዳ (traitor/betrayer/the sell out to the enemy) የተሰኙ የማንነት/የምንነት መገለጫ ቅፅል ቃላት አመጣጥ ከውጭ ወረራ በተለይም ከፋሽስት ጣሊያን ወረራ ጋር የተያያዙ መሆናቸውን ከማስታወስ ያለፈ ብዙ ማለት አያስፈልገኝም።

እነዚህ ተቃራኒ ቃላት (ፅንሰ ሃሳቦች) አገርን ከውጭ ወራሪ ሃይል ከመከላከል ጋር ተያይዞ ከቆየው የማንነት መገለጫነታቸው አልፈው  ለአገር ውስጥ የፖለቲካ ትግል ጎራዎች ማንነትና ምንነት መገለጫዎች ሆነው ያገለገሉት በ1960 /70ዎቹ የሶሻሊስት አብዮት (የመደብ ትግል)  ወቅት እንደ ነበር ማስታወስ  የፖለቲካ ታሪካችን አካል የሆነውን የዚያን ትውልድ ፖለቲካዊ ምንነትና እንዴትነት ከነበረበት አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር በአግባቡ ተረድተን  ትምህርት ሰጭነት (ገንቢነት) ባለው ይዘትና አቀራረብ መተንተንና ማሄስ ለዘመናት ከመጣንበት ያንን ትውልድ በደምሳሳው የመራገም/የማውገዝ ክፉ ልማድ  ለመላቀቅ ያግዘናልና ከምር ብንወስደው መልካም ነው።

በአገራችን የዘመናዊ ፖለቲካ ታሪክ ማሳያ  የሆነው የፓርቲ ፖለቲካ ( party politics) በሁለቱ ተፃራሪ የዓለም ርዕዮተ ዓለም ጎራዎች መካከል በሚደረግ እጅግ አስቀያሚ ፉክክር (ፍልሚያ) ወቅት የተወለደ (የተፈጠረ) በመሆኑ ሂደቱም ሆነ ፍፃሜው በእጅጉ አስከፊ ሆኖ አልፏል።

ሥልጣኑን በጠመንጃ (በጭካኝ ሰይፍ) ተቆጣጥሮ በስመ “የኢትዮጵያ ትቅደም” ሶሻሊስታዊነት ለ17 ዓመታት ከቆየው ወታደራዊ አገዛዝ ጋር ሲተናነቅ የመውደቁን እውነታ ከምር በሆነ ትምህርት ሰጭነቱ ተረድቶ ፋኖነትን/አርበኝነትን የራሱን ዘመን በሚመጥን የትግል  ሜዳ ላይ በማደራጀትና በማሠማራት  ዴሞክራሲያዊ ለውጥን እውን ለማድረግ የተቀበነባበረ ጥረት ከማድረግ ይልቅ ያንን ትውልድ ተጠያቂ እያደረገና እየረገመ ከሦስት አሥርተ ዓመታት በላይ የእኩያን የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኞች ሰለባ ሆኖ የኖረው ይህ ትውልድ ያባከነውን ከትናንት በስቲያውንና ትናንቱን  በዛሬ ቆራጥና ቀልጣፋ ተጋድሎ  በማካካስ የነገና የተነገ ወዲያ እጣ ፈንታውን የተሳካ ለማድረግ የራሱን ታሪክ መሥራት ይኖርበታል።

በነገራችን ላይ የዘመን ጠገቡና በእጅጉ አስከፊ እየሆነ የቀጠለው ፖለቲካ ወለድ መከራና ውርደት ሰለባ የሆነው ፖለቲካዊ  ማንነታችንና እንዴትነታችን ብቻ ሳይሆን ሃይማኖታዊ (መንፈሳዊ) ማንነታችንና እንዴትነታችንም ጨምር ነው። በዚህ ረገድ” ነአምን በአብ ፣ ነአምን በወልድ፣ ፣ ወነአምን በመንፈስ ቅዱስ “ የሚለውን እጅግ ግዙፍ ጥልቅ የእምነት ቃል ” ነአምን በአብይ፣ ነአምን በኦህዴድ ፣ ወነአምን በብልፅግና” የሚል አይነት መወድስ  አብይ አህመድ በአዳራሽ ውስጥ ሰብስቦ እንደ ተማሪዎቹ ካናገራቸው የሃይማኖት አመራር አባላት መታዘባችን የወረድንበትን የውድቀትና የውርደት ቁልቁለት እየመረረንም ቢሆን ቁልጭ አድርጎ አሳይቶናል ።

አገርን ከውጭ ወራሪና ተስፋፊ ሃይል ተከላክሎና አስከብሮ ለትውልድ ባስተላለፈው በዚያ  የአርበኝነት/የፋኖነት ዘመን መስቀሉን በአንገታቸውና ዳዊቱን በጉያቸው ሸጉጠው“አብ፣ ወልድ፣ ወመንፈስ ቅዱስ ብለን የምናምንህ አንተው ተከተለን” ብለው የዘመቱና የተሰው የሃይማኖታዊ እምነት አገልጋይ ወገኖች በነበሩባት አገር የዚህ ዘመን ባለ ትልልቅ ማዕረግ የሃይማኖት አመራር አባላት ከውጭ ጠላት በከፋ ሁኔታ የገዛ ራሳቸውን ህዝብ የእልቂት፣ የመከራና የውድቀት ሰለባ ላደረጉና በማድረግ ላይ ለሚገኙ እኩያን ገዥዎች  የአምላክነትን ሙገሳ  በገፀ በረከትነት ሲያቀርቡ መታዘብ ቅንና ሚዛናዊ  ህሊናን በእጅጉ ይረብሻል።

ለሩብ ምዕተ ዓመት በህወሃት ጠርናፊነት በተመራው ኢህአዴግ ውስጥ በፍፁም ታዛዥነት ሲያገለግል የነበረው አብይ አህመድ መከረኛው የአገሬ ህዝብ በህወሃት ላይ የነበረውን የመረረ ጥላቻ  ተጠቅሞ በ2010 የጠርናፊነቱን መንበር ሥልጣን በተረኝነት ተቆጣጠረ። ብዙም ሳይቆይ አገርን ምድረ ሲኦል ያደረገውንና እያደረገ የቀጠለውን “የተሃድሶው” ጠቅላይ ሚኒስትር  “ለአገራችንና ለቤተ ክርስቲያናችን ስትል እረፍትና እንቅልፍ ማጣትህ በእጅጉ ያሳስበናል ፣ የልማት ግስጋሴህ ተአምር ነው ፣ ወዘተ ” የሚል እጅግ አሳፋሪና ጨካኝ ውዳሴ የሚያዥጎደጎዱ የሃይማኖት መሪዎችን (ጳጳሳት ተብየዎችን) እየመረረንም ቢሆን ሰማንና አየን።

እናም ይህ ትውልድ ተሳስቦና ተፋቅሮ ከሙሉ ሰብአዊ ክብሩ  ጋር የሚኖርባትን አገር ከምር እየፈለገ ከሆነ  አያሌ ዓመታት ያስቆጠረውንና ከስድስት ዓመታት ወዲህ ደግሞ ለማመን በሚያስቸግር ሁኔታ ይበልጥ እየከፋና እየከረፋ በመሄድ ላይ ያለውን የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኞች ሥርዓት አስወግዶ በእጅጉ አስከፊና አሳፋሪ ከሆነው  ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ሞራላዊ፣ ሥነ ልቦናዊ ፣ ሥነ ምግባራዊ ፣ ባህላዊና መንፈሳዊ ውድቀት  ራሱን ነፃ ለማውጣት የሚያስችል አስተማማኝ አቋምና ቁመና ላይ ለመድረስ በርካታና ውስብስብ ፈታኝ ሁኔታዎችን መጋፈጥ ይኖርበታል።

ከፈታኝ ሁኔታዎች አንዱ እጅግ መሪር የፖለቲካ ታሪካችን አካል የሆነውን የዚያን ትውልድ አነሳስና አወዳደቅ እና የገዛ ራሱን ዘመን ጠገብና ለመግለፅ የሚከብድ ሁለንተናዊ ውድቀት በመሪር ትምህርት ሰጭነቱ ተረድቶና ተቀብሎ ፋኖነትን/አርበኝነትን ለዚህ ለራሱ ዘመን ለሚመጥን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን መሆን የመታገያና የማታገያ ሃይል  በማድረግ የዚህ ክፍለ ዘመን ድንቅ ታሪክ  ሠሪነቱን ማስመስከር ነው ።

ይህ ትውልድ በአካልና በስም የራሱ ወገኖች ሆነው በድርጊት ግን ከውጭ ጠላት እጅግ በባሰ ሁኔታ የመከራና የውርደት ቀንበር ያሸከሙትን  ሴረኛ፣ ሸፍጠኛና  ጨካኝ የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ሥርዓት ፈጣሪዎችንና ጠርናፊዎችን ታግሎ በማሸነፍ የህዝብ ሉዓላዊትነት (ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት) የሚረጋገጥባት ኢትዮጵያን እውን የማድረግ ታሪካዊ ሃላፊነት መወጣት ሲኖርበት ባለጌና ጨካኝ ገዥዎችን እያማረረና እየተማፀነ በገዛ አገሩ ከሰብአዊ ፍጡርነት በታች ሆኖ የኖረበት እና እየኖረ ያለበት እጅግ አስቀያሚና አሳፋሪ እውነታ ከምር ካልፀፀተውና ፈፅሞ ለማይበገር የነፃነትና የፍትህ ትግል ካላነሳሳው የትክክለኛ ሰብአዊ ፍጡር ምንነቱና እንዴትነቱ ጥያቄ ላይ ቢወድቅ ፈፅሞ የሚገርም አይሆንም።

በእጅጉ የሚያሳዝነውና የሚያሳፍረው የፖለቲካ እኛነታችን ደግሞ ከሩብ ምዕተ ዓመት በኋላም (ከ2010 —)  ሥልጣነ መንበሩን በተረኝነት የተቆጣጠሩት የህወሃት/ኢህአዴግ አንጃዎች ያደጉበትንና የሰለጠኑበትን እኩይ የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ሥርዓት ከፈጣሪያቸውና ከአሳዳጊያቸው ህወሃት ላይ ነጥቀው የራሳቸውን አደገኛ  የፖለቲካ ቁማር  እጅግ አሰቃቂ በሆነ ደረጃ ለመፈፀምና ለማስፈፀም ይችሉ ዘንድ ፋኖነትን/አርበኝነትን ለእኩይ ዓላማቸው ባሰለጠኑት አንደበታቸው እያወደሱ በተግባር ግን የፖለቲካ ወለድ ወንጀላቸው ተባባሪ ሲያደርጉት ” አሁን የምንገኝበት ዘመን የፋኖነት/የአርበኝነት ተልእኮና ዓላማ (በደምና አጥንት የተገነባ የአገርና/የወገን አፍቃሪነት) ወንጀለኛ ሥርዓትን እንደ ሥርዓት አስወግዶ የነፃነት፣ የፍትህ ፣ የእኩልነት፣ የሰላምና የጋራ እድገት/ልማት እና አስተማማኝ ሉዓላዊነት ሥርዓት እውን ማድረግ እንጅ  የሥልጣን ሽኩቻ በፈጠረው ቆሻሻና አደገኛ የፖለቲካ ጨዋታችሁ ውስጥ ገብቶ ያልተቀደሰ መስዋእትነት መክፈል ማለት አይደለምና አደብ ግዙ” ብሎ ከምር የሚቆጣና የሚገዳደር የፖለቲካም ሆነ የሲቭል ሃይል ለመፍጠር አለመቻላችን ይኸውና እስከ አሁን ድረስ  ለማመን በሚከብድ ፖለቲካ ወለድ የመከራና የውርደት ቀንበር ሥር እንገኛለን ።

የዛሬ ፈተናችንን ፅዕኑና ዘላቂ በሆነ አቋምና ቁመና ለመወጣት እና የነገ መዳረሻችንን  ፅዕኑና ዘላቂ የሆነ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን እውን በማድረግ ላይ ያነጣጠረ ይሆን ዘንድ የትናንት ሁኔታችንን  ከዛሬ ሁኔታችን እና  በድርጊት ከሚገለፅ የተሻለ ነገና ከነገ ወዲያችን ጋር በአግባቡ እያገናዘብንና እየተገነዘብን ካላስኬድነው ወይ በትናንት ማንነታችንና ምንነታችን ተቸክለን እንቀራለን ወይም በዛሬው ማንነታችን/ምንነታችን ዙሪያ የሞላችና ጎደለች የፖለቲካ ጨዋታ ሰለባዎች ሆነን እንቀጥላለን ወይም ደግሞ የነገ ባዶ ምኞትና ተስፋ እስረኞች ሆነን እንቀራለን።

አንደኛ ዓመቱን ያስቆጠረው የአማራ ፋኖ  ትግል አነሳስ እጅግ አንገብጋቢውና አጣዳፊው ምክንያት (extremely burning and urgent cause) በዘመነ ኢህአዴግ ተዘጋጅቶ በሰፊው በተካሄድ የእኩይ ፖለቲካ ትርክት (evil -driven political narrative) የአማራ ማህበረሰብ በፖለቲካ ወለድ ወንጀል የህልውና አደጋ  ውስጥ የመውደቁ  ግዙፍና መሪር እውነታ የመሆኑ ጉዳይ ቅንና ሚዛናዊ ህሊና ላለው ሰው የሚያጠያይቅ አይመስለኝም።

በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሥርዓቱ ተጠቂ የሆነውና እየሆነ ያለው አብዛኛው ህዝብ ቢሆንም የአማራ ህዝብ እጅግ ለብዙ ዓመታት ሥርዓታዊ በሆነ አደገኛ የፈጠራ ትርክት ምክንያት ህልውናን የማጣት አደገ የተጋረጠበት መሆኑን አለመቀበል የመፍትሄ ሳይሆን የችግር አካል መሆን ነው። ከስድስት ዓመታት ወዲህ ደግሞ የሆነውንና እየሆነ ያለውን በጥሞና፣ በቅንነትና በሚዛናዊነት ለሚያስተውል አማራ እንደ ማህበረሰብ በገዛ አገሩ እንኳን ያለ ሥጋት ተዘዋውሮ ሊኖርና ሊሠራ  ቀርቶ  በእኩያን የጎሳ አጥንት ፖለቲካ ስሌት ቁማርተኞች ተከልሎ በተሰጠው ክልል ውስጥም ማመን በሚያስቸግር ግዙፍና መሪር  ፈተና ላይ የሚገኝ ማህበረሰብ ነው።

በእንዲህ አይነት ግዙፍና መሪር  ሁኔታ ውስጥ ነበር  ፋኖ ከሁሉም በፊት ህልውና ማረጋገጥን ዓላማ አድርጎ እና ከሌሎች ወገኖቹ ጋር በመመካከርና በመተባበር ለሁሉም ዜጎቿ የምትበጅ ዲሞክራሲያዊት አገርን እውን ማድረግን የዚህ ዘመን ወርቃማ ግብ አድርጎ በትግል ሜዳ ላይ ራሱን ይፋ ያደረገው።

በሥልጣነ መንበር ላይ በመፈራረቅ  መከረኛውን ህዝብ በጨካኝ ሰይፋቸው እያሸበሩና እየሰየፉ ፣ የድንቁርና ሰለባ እያደረጉ፣ በፍፁም የድህነት አለንጋ እያስገረፉ ፣ለበሽታ መናኸሪያነት አጋልጠው እየሰጡ  ፣ ግዴታን እንጅ መብትን እንዳያውቅና እንዳይጠይቅ  እያደረጉ  ፣ እግዚአብሔር ካላለው ነፃ አትወጣም የሚል እጅግ የተሳሳተና ጨካኝ ስብከት እያሰበኩ፣ በብልፅግና ወንጌል ነብይ/ነብይት ተብየዎቻቸው “እየሱስ ባርኮሃልና/ቀብቶሃልና ማንንም እንዳተሰማና እንዳትፈራ  የሚል እጅግ ጨካኝ ንግርት እያስነገሩ፣ እየገደሉና እያስገደሉ ፣ ሰላም ማሳጣታቸውን የሰላም በረከት እያስመሰሉ ፣ የግፍ እርምጃቸውን የአገር ደህንነት ዋስትና አድርገው እያወጁ ፣ በነፃና ትክክለኛ ምርጫ ስም እያጭበረበሩ፣ አገር ለዜጎቿ ምድረ ሲኦል በሆነችበት መሪር እውነታ ውስጥ ፈፅሞ ቅድሚያ ሊሰጣቸው ለማይገባቸው የግል ስም መጠሪያ ፕሮጀክት ተብየዎቻቸው እጅግ አስደንጋጭ የገንዘብ መጠን እያፈሰሱ ፣ ወዘተ ቀጥለዋል። አያሌ የመከራና የውርደት ዓመታትን ያስቆጠሩትንና አሁንም በባሰ ሁኔታ እያስቆጠሩት ያሉትን እነዚህን እኩያን ገዥ ቡድኖች  ለማስወገድ እና ተስፋ የሚደረገውን ህዝባዊ ሥርዓት እውን ለማድረግ አንድ ዓመቱን ያስቆጠረውን የፋኖ ሁለገብ  ተጋድሎ  አጠናክሮ ከመቀጠል ውጭ ሌላ የተሻለ አማራጭ ፈፅሞ  የለም ።እውነተኛ ነፃነት፣ ፍትህ፣ እኩልነት፣ ሰላምና የጋራ ልማት እውን የሚሆንበትን የፖለቲካ ሥርዓት ከምር የምንሻ ከሆነ መውጫ መንገዱ ይኸው ነው።።

ይህ ግቡን ይመታ ዘንድ ግን  እጅግ ጎጅ (ጋግርታም) ከሆነው የአገራችን የፖለቲካ ባህል የሚመነጩ ማለትም ከልክ የሚያልፍ የግል ፍላጎትን ፣ አፍራሽ ቡድናዊ ስሜትን፣ በመርህ ሳይሆን በስሜት መነዳትን፣ በግል ፍላጎት ደዌ ምክንያት ሰበብ እየፈጠሩ የነፃነት ትግልን  ከድቶ የገዥዎች መሣሪያ የመሆን ወራዳነትን፣ የአድርባይነት ደዌን ፣ አደገኛ የሥልጣን ሽሚያ ልክፍተኝነትን ፣ የቅጥረኝነት ካድሬነትን ፣  ስንጥቅን ከማጥበብ ይልቅ የማስፋት ጎጅ ባህሪን ፣ የአገርን (የወገንን) መከራና ውርደት በምን አገባኝነት የመመልከት እጅግ ጨካኝ ሰብዕናን፣ ወዘተ ጨርሶ ለማስወገድ ባይቻልም ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግርና ምሥረታ እንቅፋት በማይሆንበት ደረጃ በመቆጣጠር  በጋራ ጥረት (ተጋድሎ) የተሻለ ነገንና ከነገ ወዲያን እውን ማድረግን ግድ ይላል። ለዚህ ደግሞ ሁለተኛ ዓመቱን የያዘውን የፋኖን የህልውና፣ የነፃነት፣የፍትህ፣ የእኩልነት፣ የሰላምና የጋራ ልማት የሚረጋገጥበትን ሥርዓት እውን የማድረግን ተጋድሎ ከሌሎች ተመሳሳይ ዓላማና ግብ ካላቸው ወገኖች ትግል ጋር የማስተሳሰርና የማጠናከር ጉዳይ የነገ ሳይሆን የዛሬ ሥራ መሆን አለበት።

እርግጥ ነው እንኳንስ በእንደ እኛ አይነት ከእኩያን ገዥ ቡድኖች የግፍ ቀንበር ተላቆ የማያውቅ በመሆኑ በሁለንተናዊ  ቀውስና ውድቀት ክፉኛ በተመሰቃቀለና በመመሰቃቀል ላይ በሚገኝ አገር በአንፃራዊነት የተሻለ ሁኔታ ላይ በሚገኝ አገርም  ከውስጥና ከውጭ  የሚመነጩ እጅግ  ፈታኝ ሁኔታዎች ያጋጥማሉና በፋኖ ውስጥ የተፈጠረውም የማይጠበቅ አይደለም። ትክክል የማይሆነው እና በትግሉ ሂደትና ውጤት ላይ ጉዳት የሚያስከትለው ይህንን  አጠቃላይ እውነት (general truth) ከመነሻው ልንቆጣጠረው የምንችለውን ጎጅ የፖለቲካ ባህላችንና የገዛ ራሳችን ልክ የሌለው ደካማ አስተሳሰብና የተግባር ሽባነት/ልፍስፍስነት ለመሸፋፈን ስንጠቀምበት ነው።

በእውነት ስለ እውነት ከተነጋገርን በመንበረ ሥልጣን ላይ የሚፈራረቁ  እኩያን ገዥ ቡድኖች ዋነኛ ምክንያቶችና ተጠያቂዎች መሆናቸው እንደ ተጠበቀ ሆኖ ለዘመናት የመጣንበት ፖለቲካ ወለድ መከራና ውርደት ፍፃሜ የሚያገኝባት ዴሞክራሲያዊት አገር ባለቤቶች ሆነን ለመኖር ትልቅ ፈተና የሆነብንና እየሆነብን ያለው ትንንሽ ፣መለስተኛና ከፍተኛ ናቸው የምንላቸውን የውስጥ (ድርጅታዊ) ችግሮቻችን እንደየ ደረጃቸው እውነትን ፣ ቅንነትን፣ ሃላፊነትን፣ ግልፅነትን ፣ ተጠያቂነትንና ጥበብን (ትክክለኛው የፖለቲካ ትርጉም ማህበራዊ ሳይንስነት ብቻ ሳይሆን ጥበብም ነውና) በተላበሰ ይዘትና አቀራረብ በወቅቱ ሊፈቱ የሚችሉትን ለመፍታት እና ሌሎችን ደግሞ የሚፈታተነንን ግላዊና ቡድናዊ ፍላጎት አርቀን (ተቆጣጥረን) በሂደት ለመፍታት ፈቃደኝነቱ፣ ዝግጁነቱና ቁርጠኝነቱ ስለሚጎለን ነው።

አስተያየቴን በፋኖ ውስጣዊ ችግር ዙሪያ መነጋገሪያ በሆነው ጉዳይ ዙሪያ ያለኙን ጥያቄ አዘል ነጥቦች በማንሳት ላጠቃል ፦

ሀ)” መነሻችን አማራ መድረሻችን ኢትዮጵያ ! መነሻችን አማራ መድረሻችንም አማራ !” የሚሉ መፈክሮች (ሃይለ ቃሎች) እንደ ትልቅ የርዕዮተ ዓለም ልዩነት እንዴት የልዩነት ምክንያቶች ይሆናሉበቀላሉ ተነጋግሮና ተወያይቶ  የጋራ የሆነ መልእክት እንዲይዙ (እንዲያስተላልፉ) የሚያስችል ይዘትና ቅርፅ  ሰጥቶ እና አስፈላጊም ከሆነ የህዝብን አስተያየት አካቶ ማሳወቅ (ይፋ ማድረግ) እንዴት ችግር የሆናል

ለ) የመታገያ መሠረታዊ ምክንያቱ (root cause) እና ተልእኮው አንድ ሆኖ እያለ የስም ለውጥም ወይም ማስተካከያም ካስፈለገ ተመካክሮ ማስተካከል እየተቻለ በፋኖነት ከሚታወቀው አካል ተለይቶ የአማራ ህዝባዊ ሠራዊት/ድርጅት የሚል አካል በመፍጠር  በህዝብ ላይ አላስፈላጊ ስሜት ማሳደር ምን የሚሉት ፋኖንት/አርበኝነት/ጀግንነት ነው? አርበኝነት/ፋኖነት/ጀግንነት (በተለይም የዚህ ዘመን) አገርን በፖለቲካ ወለድ ወንጀል ምድረ ሲኦል በማድረግ ትርምሳችን ለሚፈልጉት የውጭ ሃይሎች ምቹ የሚያደርጉ እኩያን ገዥ ቡድኖችን በትጥቅ ትግል ሜዳ ላይ የማጥቃትና የማሸነፍ  ብቻ ሳይሆን የውጭም ሆነ የውስጥ ፖለቲካዊ ጉዳዮችንና ፈታኝ ሁኔታዎችን በጥበብ የመቅረብ፣ የመረዳት ፣ የማስተናገድ እና ለሚፈለገው የጋራ ዓላማና ግብ የማዋል ጥያቄ አይደለም እንዴ?

ሐ) ታዲያ በየክፍለ ሃገሩ የእገሌ እና የእገሌ ወይም ፋኖ እና ህዝባዊ ግንባር/ሠራዊት በሚል አስቀያሚ ስንጥቅ  ፈፅሞ ሊነጣጠል የማይገባውን የአማራውን እና የመላው ኢትዮጵያን ህዝብ እጣ ፈንታ በመወሰን ረገድ እጅግ ጉልህ ሚና በሚጫወተው የትግል ግስጋሴ ላይ አላስፈላጊ ተፅዕኖ የማሳደሩ ጉዳይ በአስቸኳይ መታረም የለበትም እንዴ?

መ) እስክንድርና ዘመነ ተወዳድረው እስክንድር አሸነፈ ተብሎ የተነገረለት ጉዳይ አወዛጋቢ የሆነው ከመጀመሪያውም ለምን? በምን? በማን? ለማን? እንዴት? የትና ወዴት? የሚሉ ጥያቄዎችን ከትግሉ ክብደትና ውስብስብነት አንፃር በሚያስተናግድ  ቅንና ግልፅ የፖለቲካ ወይይት አለመታገዙ ይመስላልና ይታሰብበት ማለት ነገር እንደ ማባባስ ይታይ ይሆን?

 

ሠ) ምርጫ የተባለው ጉዳይ እየተካሄደ ባለበት ወቅትም ይሁን ተመራጩ ታወቀ ከተባለ በኋላስ ቢሆን የትግል ጓዶችን ቅር የሚያሰኝ ነገር እንደ ነበረ ሲታወቅ የምርጫውን አዋጅ ከማወጅ (የእንኳን ደስ አለኝ/አለን መግለጫ) ከማስተጋባት ተቆጥቦ የግልን ወይም ቡድናዊ ስሜትን በመቆጣጠር ነገሩን በጥሞና መልሶ ማየትና መነጋገር አይገባም (አይሻልም) ነበር እንዴ? ሽሚያው ለምን አስፈለገ?

 

ረ) “ተመርጫለሁ” በሚለው እወጃ (መግለጫ) ላይ ቅሬታ የነበራቸው የፋኖ ታጋዮችስ ቢሆን የመግለጫ ምልልስ ለማድረግ ከመቸኮል ይልቅ  ቅሬታቸውንና አቋማቸውን ትግሉ ከተነሳበት ፣ ከደረሰበትና ሊደርስበት ከሚገባው ዓላማና ግብ አንፃር እንደዚያ አይነቱ አካሄድ አልመጥቀም ብቻ ሳይሆን አደገኛም እንደሆነ ግልፅነት፣ ቀጥተኛነትና ገንቢነት ባለው ይዘትና አቀራረብ ለማስረዳትና የጋራ ግንዛቤ ለመፍጠር ጥረት ቢያደርጉ አይሻልም ነበር እንዴ ?

ሰ) እንዲህ አይነት ከፖለቲካ ባህላችን ወደ ኋላ መቅረት ፣ እንደ ሰው አውቀንም ሆነ ሳናውቅ በምንሰራው ስህተት፣ በጣም ተለጣጭና አንዳንዴም አስቸጋሪ በሆኑ የሰው ልጅ ባህሪያት፣ ከማህበረሰባዊ መስተጋብር ምንነትና እንዴትነት፣ ወዘተ በአግባቡ ይያዙ ዘንድ የፖለቲካ ሥራው (ጠንካራ ድርጅታዊ ቅርፅና ይዘት ) ከትጥቅ ትግሉ ጋር እየተራመደ አለመሆኑን ያመላክታልና ቢታሰብበት መልካም ነው ማለት ነገር ማባባስ ወይም መለጠጥ ይሆን?

የሸፍጠኛና የጨካኝ ገዥ ቡድኖች ፖለቲካ ወለድ መከራና ውርደት አስተማማኝና ዘላቂ በሆነ ሁኔታ ፍፃሜ አግኝቶ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግር መግባት ካለብን የአማራ ፋኖ እና የሌሎች ነፃነትና ፍትህ ፈላጊ ወገኖች ተጋድሎ በማይታጠፍ የህዝብ አጋርነት እየታጀበ ለድል መብቃት አለበት። ያኔ ነው ይህ ትውልድ አገርን ከውጭ ጠላት ጠብቆ በማቆየት የሚታወቀውን ፋኖነት/አርበኝነት ዘመኑን ለሚመጥን የውስጥ ነፃነት (ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት) እውን  መሆን ያበቃ (ያስቻለ) ትውልድ የሚል የወርቃማ ታሪክ ባለቤት የሚሆነው።

 ለግማሽ ምዕተ ዓመት (1966-2016) በፍፁም የህይወት ጉስቁልና ብቻ ሳይሆን በደም የጨቀየው የፖለቲካ እኛነታችን እጅግ መሪርና ገንቢ ትምህርት ( ፀፀት) ሆኖን ከህዝብ፣ በህዝብ እና ለህዝብ የሆነውን የፋኖነት/የአርበኝነት ታላቅ እሴት ተጨባጭና ውጤታማ ወደ ሆነ  የትግል መሳሪያነት በመተርጎም መገመት ከሚያስቸግር መከራና ውርደት ጋር እንድንለማመድ ያደረገንን የጎሳ ደም/አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኞች ሥርዓት በማስወገድ እና በሽግግር ፍትህ አግባብ ወደ ዴሞክረሲያዊ ሥርዓት በመሽጋገር የውርቃማ ታሪክ ባለቤት ከመሆን የበለጠ ዓለማዊም ሆነ መንፈሳዊ ልእልና የሚኖር አይመስለኝም።

በአገር ፍቅርና ክብር፣ በነፃነትና ፍትህ ሃያልነት ፣ በብሔርና ብሔረሰቦች  እኩልነት፣ በእምነት ነፃነት፣ ድህነትን ታሪክ በማድረግ ፣ ትውልድን በመታደግ  ፣ ወዘተ ስም ርካሽና አደገኛ ፕሮፓጋንዳ እየተጋትንና እየደነቆርን  የቀጠልንበት የኦህዴዳዊያን/ኦነጋዊያን/ብልፅግናዊያን የጉልቻ ለውጥ ላስከፈለንና እያስከፈለን ላለው እጅግ ግዙፍና መሪር ዋጋ እኛው ራሳችን ሃላፊነት ያለብን መሆናችንን አምኖ በመቀበል እና ፈፅሞ ወደ ኋላ መመለስ የሌለበትን የፋኖ ተጋድሎ  ግቡን እንዲመታ ማድረግ  የዚህ ትውልድ ታሪካዊ ተልእኮ መሆን አለበት።

አዎ! ይህ ትውልድ (በተለይ ወጣቱ) እጅግ አደገኛ በሆነው በጎሳ ደምና አጥንት ስሌት ፖለቲካ ናላውን (አእምሮውን) እና ሰብአዊ ፍጡርነቱን ቀውስ ውስጥ ዘፍቀው ወርቃማ እድሜውን ያበላሹበትን (ያመሰቃቀሉበትን) ሴረኛ፣ ሸፍጠኛና ጨካኝ ገዥ ቡድኖች በቃ ብሎ ለራሱ ብቻ ሳይሆን ለቀጣይ ትውልድ የሚተላለፍ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን እውን ለማድረግ የሚደረገውን ተጋድሎ በባለቤትነት ስሜት እየተቀላቀለ ግቡን እንዲመታ ማድረግ የዛሬ እንጅ የነገ ሥራው መሆን የለበትም።

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

[ማስታወሻ ከፍል አንድ፣ በዘሐበሻ ድረ ገጽ ላይ ኦፍ ጃዋር አንድ ኢትዮጵያ ተብሎ በእንግልዝኛ ወጥቷል] https://zehabesha.com/of-jawar-and-ethiopia/ ባለፈው ሰሞን፣ ጃዋር መሐመድ ከደረጀ ኃይሌ ጋር  በነገራችን ላይ ክፍል ሁለት ባደረገው ቃለ ምልልስ ላይ ተመስርቼ ገንቢ አስተያየት ጽፌ በኢንግሊዝኛው ዘሐበሻ ድረ ገጽ ላይ አሳትሜ ነበር። አስተያየቴ በዚህ ቃለ ምልልስ ላይ

ስለ ጃዋርና ኢትዮጵያ (ክፍል ሁለት)

January 20, 2025 ጠገናው ጎሹ የአቤ ጎበኛው አልወለድም ለወገኖቹ መብት መከበር ሲል ባደረገው ጥረት ምክንያት እንደ ወንጀለኛ ተቆጥሮ ይሙት በቃ በፈረዱበት ጊዜ በምላሳቸው መልካም  አድርጎ ስለ መገኘት እያወሩ በድርጊት ግን ተቃራኔውን የሚያደርጉ ሁሉ

ወዮ ለመከረኛው የአገሬ ህዝብ እንጅ  ታየማ ታየ ነው

መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ “ ሰው የሰነፎችን ዜማ ከሚሰማ ይልቅ የጠቢባንን ተግሣጽ መስማት ይሻለዋል። ”   — መክብብ 7፥5 እስቲ ቆም ብለን በማሰብ  ራሳችንን እንፈትሽ ።  እንደ ሰው ፣ የምንጓዝበት መንገድ ትክክል ነውን ? ከቶስ ሰው መሆናችንን እናምናለንን ? እያንዳንዳችን ሰው መሆናችንን እስካላመንን ጊዜ ድረስ ጥላቻችን እየገዘፈ

 ለሀገር ክብርና ብልፅግና ብለን ፤ ቆም ብለን በማሰብ ፤ ህሊናችንን ከጥላቻ እናፅዳ

                                                         ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)                                                       ጥር 12፣ 2017(January 20, 2025) ጆ ባይደን ስልጣናቸውን ለማስረከብ ጥቂት ቀናት ሲቀራቸው በአሜሪካን ምድር በጣም አደገኛ የሆነ የኦሊጋርኪ መደብ እንደተፈጠረና፣ የአሜሪካንንም ዲሞክራሲ አደጋ ውስጥ ሊጥለው እንደሚችል ተናግረዋል።  ጆ ባይደን እንዳሉት በተለይም በሃይ ቴክ

አሜሪካ ወደ ኦሊጋርኪ አገዛዝ እያመራ ነው! ጆ ባይደን ስልጣን ለመልቀቅ ጥቂታ ቀናት ሲቀራቸው የተናዘዙት!!

ከነፃነት ዘገዬ የአራት ኪሎው ኦነግ ሸኔ ከቁጥር ጋር እንደተጣላ ዕድሜውን አገባደደ፡፡ ኦነግ/ኦህዲድ ዛሬም ሆነ ዱሮ፣ በቤተ መንግሥትም ይሁን በጫካ ቁጥር ላይ ያለው አቋም ምን ጊዜም ያስደንቀኛል፡፡ ደግሞም እየባሰባቸው እንጂ ሲቀንሱ አይታዩም፡፡ ጥቂት

80 ቢሊዮን ብር ስንት ብር ነው?

በላይነህ አባተ ([email protected]) መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ምዕራባውያን የኢትዮጵያን ልጆች እያታለሉና እየደለሉ ከእምነታቸው ለመንጠቅ ሲቃጡ በ1951 ዓ ም ባሳተሙት ‘መድሎተ አሚን ወይም የሃማኖት ሚዛን ጥልቅ መጽሐፍ ሽፋን ላይ ሕዝብ ልቡናውን፣ ዓይኑን፣ ጀሮውንና

ሰው ሆይ!

“በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ።”  መዝሙረ ዳዊት 39:1 ወንድሙ መኰንን፣ ኢንግላንድ 15 January 2025 መግቢያ የአገር መሪ፣ በስሜታዊነት እንዳመጣለት አይዘረግፍም። እያንዳንዷ ንግግሩ እየተሰነጠቀች ትታይበታለች። ንግግሩ ቁጥብ መሆን

ከተዘራ ያልታረመ አንደበት የጠቅላይ ሚኒስትር አነጋጋሪ ንግግሮች

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
Go toTop