እስካሁን ሃብታም ያልሆንክባቸው 10 ምስጢሮች

ሀብታም መሆን ሁሉም ይፈልጋል፡፡ ግን የፍላጎታችንን ያህል ተሳክቶልን ሀብታም የሆንን አይደለንም፡፡ ዘ ስትሪት የተባለው በፋይናንስ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ጋዜጣ የተለያዩ ሰዎችን ሀሳብ እና ልምዶች አሰባስቦ የፋይናንስ ባለሞያዎችንና ሚሊየነሮችን ትንታኔ በተቀበለበት ወቅት ተለይተው የታወቁ ከሀብት መስመር የሚያርቁ የዕለት ተዕለት ልምዶችና አስተሳሰቦች ታትመው ወጥተው ነበር፡፡ ‹‹የምታገኘው የገንዘብ መጠን ሀበታም በመሆንህ ላይ ያለው አስተዋፅኦ ትንሽ ነው፡፡ ዋነኛው ጉዳይ ያገኘኸውን ገንዘብ የምትቀበልበትና የምታስተናግድበት መንገድ ነው ይላሉ›› ሀሳባቸውን የሰጡት ሚሊየነሮች፡፡ ይህን መነሻ አድርገው ትንታኔ የተሰጠባቸውን አስር ከሀብት ያራቁንና ሀብታም እንዳንሆን ያደረጉንን ምክንያቶች እንመለከታለን፡፡
1. ጎረቤቶች ስላንተ ስለሚያስቡት ትጨነቃለህ
ከጎረቤቶችህና ውድድር ውስጥ ከገባሃቸው ሰዎች የተሻለ የቁስ ባለቤት መሆንህን ለማሳየት በየጊዜው አዳዲስ ግን ዘለቄታ የሌላቸውን እቃዎች በመግዛት ለፍተህ የመጣኸውን ገንዘብ ታባክናለህ፡፡ በዚህም ብልፅግህናህን ከማፋጠን ይልቅ ሰዎችን ስታስደንቅ ዕድሜህን እና ሀብትህን ስታባክን ትኖራለህ፡፡
2. ትዕግስት የለህም
ለህይወትህና ኑሮህ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን መግዛት ሊያስፈልግ ይችላል፡፡ ነገር ግን ገንዘቡ በእጅህ ላይኖር ይችላል፡፡ ገንዘቡ እስኪመጣ ከመጠበቅ ይልቅ በወለድም ቢሆን ተበድረህ ትገዛለህ፡፡ የራስህ ገንዘብ ሲመጣ እዳውን ብቻ ሳይሆን በወለዱ ምክንያት ሌላውንም ሊጠራቀም የሚችል ገንዘብ ይዞብህ ይሄዳል፡፡
3. በአቋራጭና በፍጥነት ለመክበር ትፈልጋለህ
አብዛኞቹ የምናውቃቸው ሀብታሞችና ሚሊየነሮች ጥረው ግረው ሰርተው በረጅም ጊዜ ሀብታቸውን እንዳፈሩ የሚታወቅ ቢሆንም አንዳንዶቻችን በአንድ ሌሊት መበልፀግ እንፈልግና ያለንን ገንዘበ ሁሉ በፍጥነት ያበለፅገናል ባልነው ጉዳይ እናጠፋለን፡፡ አብዛኞቹ በአቋራጭ እና በፍጥነት መክበሪያ መንገዶች ደግሞ በአጭበርባሪዎች የተያዙ በመሆኑ ያለህን ጥሪት በዚህ ሂደት ስለምታጣ ሀብት ማፍራት እንዳማረህ ይቀራል፡፡
4. በማይገባህ ስራ ውስጥ ገንዘብህን ታፈሳለህ
ጓደኛህ አቶ እከሌ የሆነ ስራ ጀምሮ በፍጥነት ገንዘብ አፍሶበት ይሆናል፡፡ ግን የእርሱ ስራና መንገድ የአንተ ሊሆን ይችላል? የስነ ጥበብ ሰው ሆነህ ሳለ በአውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪ ገብቼ በአጭር ጊዜ እከብራለሁ ብለህ ከሆነ ይህ ጥርጣሬ ላይ ይጥላል፡፡ ይህን መሰል ከራሳችን ትምህርት፣ ችሎታ፣ ተሰጥኦና ብቃት ጋር ባልተያያዘ ስራ ውስጥ ገንዘብን ማፍሰስ ከሀብት የመድረሻ መንገዱን በእጅጉ ያርቅብናል፡፡
5. የምትወደውን ስራ አትሰራም
ሁሉም ሰው የሚያልመውን እና የሚደሰትበትን ስራ ብቻ እንዲሰራ መጠበቅ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ቢያንስ ውጥረት እና ጭንቀት ውስጥ ወደማይከትህ ስራ መሰማራት ይመከራል፡፡ ብዙ ገንዘብ አለው ብለህ የምትሰራው እና የማትፈልገው ስራ የማያስከትልብህን ድብርት እና ውጥረት ለማስታገስ ብርህን ስትረጭ እና ‹‹ስትዝናና›› ጥሪትህ ያልቃል፡፡ ገንዘብ ማጠራቀም ከዝርዝርህ መጨረሻ ይሆናል፡፡
6. የገንዘብ ነገር ላይ ፈሪ ነህ
ያለህን ገንዘብ በባንክ አካውንት ማስቀመጥ ለብክነት እንዳትጋለጥ ቢረዳህም ኪሳራን ፍራቻ ብሩን የማታንቀሳቅሰውና የማትሰራበት ከሆነ ካለህ ነገር መቼም ፈቀቅ አትልም፡፡ እንዲያውም የዋጋ ግሽበት በየወቅቱ በሚያምሳት በዚህች ዓለም ያስቀመጥከው ገንዘብ ዋጋው እየረከሰ የሚሄድበትም ዕድል ይኖራል፡፡
7. የማትጠቀምበትን ዕቃ ትገዛለህ
እስቲ እቤትህ ግባና ያሉህን እቃዎች ተመልከት፡፡ ወሳኝ ጥቅም ያላቸው እና በእርግጥ የምትፈልጋቸው ምን ያህል ዕቃዎች ናቸው? ላለፉት በርካታ ወራት ያልተጠቀምክባቸው ዕቃዎች ቁምሳጥንህ ውስጥ፣ መኝታ ቤትህ አለዚያም ኩሽና ውስጥ ምን ያህሉ አሉ? ተመልከታቸውና ልምድህን አስተካክል፡፡
8. ገንዘብህን አትከታተልም
ምን ያህል ገንዘብ እንደነበረህ፣ ምን ያህል እንዳጠፋህ ያለብህ ዕዳ ይኖር እንደሆነ እና መሰል የገንዘብ ጉዳዮች ቢያንስ በወር አንድ ጊዜ ቁጭ ብለህ ማስላትና መስራት ይኖርብሃል፡፡ በባንክ አካውንትህ ስላለው ወጪና ገቢህ ክትትል አድርገህ አስፈላጊውን ማስተካከያ ማድረግን ካልለመድህ የገንዘብ ጉዳይ ቸልተኝነትህ ብዙ ሊያስከፍልህ ይችላል፡፡
9. መጥፎ ልምዶች አሉህ
የገንዘብ ፀር የሆኑ ክፉ ልማዶች ከሚባሉት መካከል ሲጋራ፣ አልኮል፣ ጫት እና ቁማር ሱሰኛ ከሆንክ ገንዘብ የማስተዳደር እና ተጨማሪም የማፍራት አቅምህ በእጅጉ ይፈተናል፡፡ በእቅድ የመስራት፣ የመዝናናትና የመስራት ልምድህን በማዛባት የሚበልጠውን ጊዜህን ከዚሁ ጋር ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች እንድታጠፋ ትገደዳለህ፡፡
10. በህይወት ግብ የለህም
ወደ ፊት ማሳካት የምትፈልጋቸውና አንድ፣ ሁለት፣ ሶስት ብለህ የምትቆጥራቸው ግቦች ከሌለህ ሀብትና ብልፅግናን ማሰብ ይከብዳል፡፡ የምትቆምለት፣ የምትሰራለት ህልም እና ግብ የበለጠ ለስኬት ይገፋፋሃል፡፡ ይህ ደግሞ ገንዘብን ይዞ ይመጣል፡፡
ከላይ ከተጠቀሱት ወደሃብት የሚደረግ ጉዞን የሚገቱ መሰናክሎች መካከል አንድ፣ ሁለት፣ ሶስት አለዚያም ከዚያ በላይ የሆኑት በአንተ ህይወት ውስጥ የሚንፀባረቁ ጉዳዮች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እስቲ ቁጭ በል እና በጥሞና አሰላስላቸው፡፡ መወገድ የሚችሉትን በቶሎ አስወግድ፣ ጭንቅላትህንም ለእነዚህ እንቅፋቶች የነቃ እንዲሆን አድርገውና በህይወትህ እንዳይደገሙ ተከላከላቸው፣ መልካም ውጤት ቀና የሀብት ጉዞ፡፡ S

ተጨማሪ ያንብቡ:  በጀርመን የገባውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን በተመለከተ ያለው ቴከኒካዊና ተቋማዊ ልምድና አስተያየት - ክፍል 16 - ፀጋዬ ደግነህ (ዶ/ር)

ምንጭ፡ ዘ-ሐበሻ ጋዜጣ ቁጥር 46

3 Comments

  1. ዋዉ መረጃው በጣም ምርጥ ነው በዚሁ ቀጥሉበት
    እውነተኛ የዘሐበሻ የሆነ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሁሌም ሊያነበው የሚገባ ጠቃሚ መረጃ !!!

Comments are closed.

Share