የቀድሞው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት እና የሪፐብሊካን ፕሬዝዳንታዊ እጩ ዶናልድ ትራምፕ ዛሬ፣ ሐምሌ 6 ቀን 2016 ዓ.ም. ፔንሰልቬኒያ፣ ባትለር ውስጥ በምርጫ ቅስቀሳ ላይ እያሉ በተተኮሰባቸው ጥይት ጭንቅላታቸው አካባቢ ጉዳት የደረሰባቸው ሲኾን፣ በአኹኑ ወቅት ግን ደኅና መኾናቸው ተገለጸ።
ከጥቃቱ በኋላ የዩናይትድ ስቴት ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን፣ ፖለቲካዊ ብጥብጥን አውግዘው ጠንከር ያለ መግለጫ አውጥተዋል።
በብዙኅን መገናኛ የግድያ ሙከራ በሚል የተዘገበውና እየተመረመረ ያለው የዛሬው ክስተት ፣ቀድሞውኑ የከበደውን የፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ውድድር የበለጠ ጠንካራ እና ውስብስብ ሊያደርገው ይችላል በሚል ተሰግቷል።
ዶናልድ ትራምፕ በማኅበራዊ ገጻቸው “ኤክስ” ላይ ባወጡት መግለጫ፣ የምርጫ ቅስቀሳውን እያካሄዱ በነበሩበት ባትለር ውስጥ የተኮሰባቸው ግለሰብ መገደሉን እና ሌላኛው ደግሞ መቁሰሉን አርጋግጠዋል።
“ሴክሬት ሰርቪስ” በመባል የሚታወቀው፣ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት የጥበቃ አገልግሎት በበኩሉ፣ የቆሰሉት ግለሰቦች ሁለት መኾናቸውን አስታውቋል።
የ”ሴክሬት ሰርቪሱን” የሕግ አስከባሪዎች ያመሰገኑት ትራምፕ፣ “ከሁሉም በላይ በሰልፉ ላይ ለተገደለው እና ከባድ ጉዳት ለደረሰበት ግለሰብ ቤተሰቦች መጽናናትን እመኛለኹ። እንዲህ ያለ ድርጊት ሀገራችን ውስጥ መፈጸሙ የማይታመን ነው። በአሁኑ ጊዜ ስለ ተገደለው ተኳሽ ምንም የሚታወቅ ነገር የለም።” ብለዋል።
” የቀኙ ጆሮዬ የላይኛውን አካባቢ የተተኮሰው ጥይት በስቶኛል።” ያሉት ትራምፕ “የተኩስ ድምጽ እንደሰማኹ ነበር መጥፎ ነገር እንደተፈጠረ ያወኩት። ወዲያውኑ ጥይት ቆዳዬን ሲያልፍ ተሰማኝ። ብዙ ደም ፊቴን ሲያለብሰኝ ምን እደተፈጠረ በትክክል ገባኝ። እግዚያብሔር አሜሪካንን ይባርክ” ብለዋል።
ትራምፕ ስለሚገኙበት ሁኔታም ኾነ ክስተቱ የግድያ ሙከራ በሚል እየተጣራ ስለመኾኑ ተጨማሪ መረጃ አልሰጡም።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት የጥበቃ አገልግሎት ወይም “ሴክሬት ሰርቪስ” ኤክስ በተሰኘው ማኅበራዊ ገጽ ላይ ባሰፈረው መግለጫ መግለጫ ፣ ጉዳዩ በምርመራ መኾኑን ከመግለጽ ውጪ “ግድያ” የሚለውን ቃል አልተጠቀመም።
“ደኅና እና በጥሩ ኹኔታ ላይ እንደሚገኝ በመስማቴ እፎታ ተሰምቶኛል” ሲሉ መግለጫ ያወጡት ባይደን፣ “ተጨማሪ መረጃን ለማግኘት እየተጠባበቅን ባለንበት በዚኽ ጊዜ፣ ለእርሱ ፣ለቤተሰቡ እና በሰልፉ ላይ ለነበሩት ኹሉ እየጸለይኩ ነው” ብለዋል።
“ሴክሬት ሰርቪስ” በመባል የሚታወቀው፣ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጥበቃ አገልግሎት፣ ወዲያውኑ በወሰደው የዶናልድ ትራምፕን ደኅንነት የመጠበቅ ርምጃ እርሳቸው እና ባለቤታቸው ጂል ባይደን መደሰታቸውንም በመግለጫቸው ላይ አስፍረዋል።
“አሜሪካ ውስጥ ለዚህ ዓይነት ጥቃት ምንም ቦታ የለንም። እንደ አንድ ሀገር ተባብረን ድርጊቱን ማውገዝ አለብን” ሲሉም አሳስበዋል።
ባይደን ከደቂቃዎች በኋላ በሰጡት መግለጫም፣ “ዛሬ ማታ እንደማነጋግረው ተስፋ አደርጋለኹ” ሲሉ ብለዋል። ድርጊቱ የግድያ ሙከራ እንደኾነ የተጠየቁት ባይደን፣ “አስተያየት አለኝ፣ ግን ደግሞ ምንም የተረጋገጠ ነገር የለኝም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
ከትራምፕ ጥቃት በኋላ መግለጫ ያወጡት የቀድሞው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በበኩላቸው “በዲሞክራሲያችን ውስጥ ለፖለቲካ ብጥብጥ የሚኾን ምንም ቦታ የለንም” ሲሉ ድርጊቱን ኮንነዋል።
አክለውም “ምን እንደተፈጠረ በትክክል ባናውቅም፣ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ትራምፕ ላይ የከፋ ጉዳት ባለመድረሱ ሁላችንም እፎይታ ተሰምቶናል። ይህንን ጊዜ በፖለቲካችን ውስጥ ለመከባበር እንጠቀምበት።” ሲሉ ከባለቤታቸው ሚሼል ኦባማ ጋራ በመኾን ትራምፕ በቶሎ እንዲያገግሙ መልካም ምኞታቸውን አስተላልፈዋል።
የትራምፕ ምርጫ ቅስቀሳ ባወጣው መግለጫ፣ የሪፐብሊካን ፕሬዚዳንታዊ እጩ ጥቃቱ ከደረሰባቸው በኋላ በአካባቢው በሚገኝ የህክምና ተቋም፣ አገልግሎት ማግኘታቸውን አስታውቋል።
Source –
ባይደን ከደቂቃዎች በኋላ በሰጡት መግለጫም፣ “ዛሬ ማታ እንደማነጋግረው ተስፋ አደርጋለኹ” ሲሉ ብለዋል። ድርጊቱ የግድያ ሙከራ እንደኾነ የተጠየቁት ባይደን፣ “አስተያየት አለኝ፣ ግን ደግሞ ምንም የተረጋገጠ ነገር የለኝም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
ከትራምፕ ጥቃት በኋላ መግለጫ ያወጡት የቀድሞው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በበኩላቸው “በዲሞክራሲያችን ውስጥ ለፖለቲካ ብጥብጥ የሚኾን ምንም ቦታ የለንም” ሲሉ ድርጊቱን ኮንነዋል።
አክለውም “ምን እንደተፈጠረ በትክክል ባናውቅም፣ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ትራምፕ ላይ የከፋ ጉዳት ባለመድረሱ ሁላችንም እፎይታ ተሰምቶናል። ይህንን ጊዜ በፖለቲካችን ውስጥ ለመከባበር እንጠቀምበት።” ሲሉ ከባለቤታቸው ሚሼል ኦባማ ጋራ በመኾን ትራምፕ በቶሎ እንዲያገግሙ መልካም ምኞታቸውን አስተላልፈዋል።
የትራምፕ ምርጫ ቅስቀሳ ባወጣው መግለጫ፣ የሪፐብሊካን ፕሬዚዳንታዊ እጩ ጥቃቱ ከደረሰባቸው በኋላ በአካባቢው በሚገኝ የህክምና ተቋም፣ አገልግሎት ማግኘታቸውን አስታውቋል
ቪኦኤ ዜና