እናትነት !

June 28, 2024

449094947 3807795739542251 3274854934486005595 n

ወንዶች ልጆች እናታቸውን በጣም ይወዳሉ ይባላል። ለናታቸው የሚሰጡትን ፍቅር ለማንም መስጠት አይችሉም ። በተለይ በልጅነታቸው ከናታቸው ጉያ አይወጡም ። የናታቸው ነገር አይሆንላቸውም ። እናቶችም ለወንድ ልጆቻቸው ያደላሉ ሲባል እንሰማለን ። እውነት ለመናገር ሲያደሉም ያየኋቸው እናቶች አሉ ።

ዛሬ በስልኬ የተከማቹ ፎቶዎችን ሳገላብጥ የግፍ እስረኛዋ መምህር መስከረም አበራ ከልጇ ጋር እንዲህ አምራ የተነሳችው ፎቶ አየሁት ። የልጁ እናቱ ጉያ ሽጉጥ ማለት ። የእናትየው ልጇን ግማሽ ደረቷ ላይ ልጥፍ አድርጎ ፀጉሩን ማሻሸቷን ሳይ መምህርዋ ከእስር ተፈትታ ልጇን ዳግም የምታቅፍበትን ቀን ማየት ናፈቀኝ ።

ልጆች በጣም የዋሆች ናቸው ። በህይወታቸው የሚገጥማቸው ምስቅልቅል በፍጹም አይገባቸውም። ወላጅም ቢሆን የሆነው እንዲህ ነው ብሎ ማስረዳት በጣም ከባድ ነው ። ወላጆች በረባ ባልረባ ወደ እስር ሲወረወሩ ልጆችም ከወላጆቻቸው ባልተናነሰ ሁኔታ እየተቀጡ መሆኑን መዘንጋት የለብንም ።

ወላጅ ለልጅ በጣም አስፈላጊ ነው ። አንድም ቀን ይሁን አንድ ሳምት ፣ ልጆቹ ባልተረዱት መልክ ወላጆቻቸውን ከጎናቸው ሲያጡ እየሆነ ያለውን ወይንም የሆነውን ለመቀበል በጣም ነው የሚከብዳቸው ።

መምህር መስከረም አበራ እንደቀልድ እንደታሰረች ይኸው እስከዛሬ አለች ። መስከረም ሁሉን ያደረገችው በአደባባይ ነው ። የተናገረችውንም ይሁን የፃፈችው ያመነችበትን ነገር ነው ። ሀሳብዋን በሀሳብ ሞግቶ መቀራረብ አንድ ነገር ሆኖ ሳለ እነሆ መንግስት ጥርስ አወጣና አሳዳጅ ሆኖ እንደ ኢህአዴግ የአይንህ ቀለም ካላማረኝ ማለትን ተያይዦታል ።

እናንተ የመንግስት ባለስልጣናት ሆይ ! ልጆቻችሁን ከስራ ስትመጡ ከአይናችሁ ብታጧቸው ምንድነው የሚሰማችሁ ?

እባካችሁ ይቺን እናት ፍቷት !

ፍትህ ለመምህር መከረም አበራ እና ቤተደቦችዋ

 

መንበረ ካሳዬ

 

1 Comment

  1. አንድ የጊዜው የዓይን ምስክር የሆነ ሰው እንዲህ ብሎ አጫወተኝ። ጊዜው ረጅም ነው ወቅቱ የደርግና የኢህአፓ ፍልሚያ በከተማና በገጠር የፈመበት ነበር ይላል። ድንገት በአፋኝ ጓዶች ሳናስበው በላንድሮቨር ታፍነን ወደ እስር ቤት ተወሰድን። ከዚያም ብዙ ሴቶችና ወንዶች ተጨማሪ እስረኞች ተያዙ። ከእነዚህ መካከል አንዷ ነፍሰ ጡር ነበረች። ከቀናት በህዋላ ለምርመራ ወስደው ሲገርፏት ምጧ መቶ ወንድ ልጅ በደህና ተገላገለች። ያቺ ሴት አሁንም በህይወት አለች። የተወለደው ልጅም አለ በማለት ያለፈበተን የግፍ ዘመን እንባ እየተናነቀው ሙትና ቋሚን አስታኮ በትዝታ አጫውቶኝ እኔንም አስለቀሰኝ።
    ሃበሻ ጨካኝ ነው። አረመኔ። መስከረም አበራ ምንም የሰራቸው ለእስር የሚያበቃ በደል የለባትም። ግን መናገርና መጻፍ በማይፈቀድበት ምድር ላይ ሁለቱም በደል ሆነው ይኸው የሃገሪቱን ልጆች ያኔም ሆነ አሁን እየበላና እያስበላ የዛሬውም መንግስት ያለፈውን የከረፋ ያረጀ እያለ ራሱ አፍንጫ የሚያሸንፍ የጠነባ ፓለቲካ ሲከተል አይናችን እያየ ነው። ሰው በሰራውም ሆነ ባልሰራው የሚርድባት ምድር ኢትዮጵያ ብቻ ናት። ካህን በጥፊ የሚመታባት ምድር ቀን የሰጣቸው የዘርና የቋንቋ ሰካራሞች የሚያራምድት እድፋም ፓለቲካ ሁሉንም ክፋት እየቀባ በወረፋ ሲጠላለፉ መኖር ነው። ሌላ ትርፍ የለውም!
    አሁን በብልጽግናው መንግስት ታግተው ሃበሳ የሚያዪት ወገኖች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መፈታት አለባቸው። እስቲ አስቡት ስብሃት ነጋን በቃሬዛ ተሸክሞ አዲስ አበባ ከነዘመዶቹ ያደረሰና አልፎ ተርፎም ወደ አሜሪካ እንዲሄድ የፈቀደ መንግስት ዛሬ ላይ በጎጃም፤ በሽዋ፤ በወሎና በጎንደር አርሶ አደሮችን በመግደልና በማፈናቀል ላይ ይገኛል። እርግጥ ነው ፋኖም ይተኩሳል፤ ኦነግ ይገላል ሌላው በዚህም በዚያም ስም ህዝብን ያሸብራል። ግን ረጋ ብሎ ላየው የሃበሻ ፓለቲካ የእብዶች ስብስብ እድር እንጂ ለህዝባችን በፊትም አሁንም ወደፊትም የሚጠቅም ነገር አያስገኝም። ልክ እንደ ሰንበቴ ማነህ ባለሳምንት ያስጠምድህ ባስራስምንት በማለት በወረፋ እየተሽከረከሩ ማውደምና መውደም ነው። ዘርፎና አግቶ መክበር ባህል ሆኗልና!
    በማሰር፤ በመግደል፤ በማፈን፤ በመሰወር ቢሆን ኑሮ ዛሬ ወያኔና ደርግ በስልጣን ላይ በሆኑ ነበር። ብሄርተኞች ብሄራዊ እሳቤ የላቸውም። ይህም በመሆኑ በደርግ ዘመን የደርግ ባለስልጣኖች ሆነው ስንቶች ናቸው ለሻቢያና ለወያኔ የውስጥ አርበኞች በመሆን በፈጠራ ክስ የኢትዮጵያን ምርጥ ልጆች ያስበሉት? የብሄር ሰካራሞች መስፈሪያቸው እኔ እንጂ እኛ ብለው አስበው አያውቁም። ለዚህም ነው ዛሬ ኢትዮጵያ በክልል ሂሳብ የአፓርታይድ ዘይቤ ውስጥ የገባችው። እንበለ ፍርድ በኢትዮጵያ ምድር በየሥርቻው ተጥለው የሚሰቃዪ ታሳሪዎች በአስቸኳይ መፈታት አለባቸው። የቀድሞው የወያኔ ሰው ስዬ አብርሃ ከረጅም ጊዜ እስራት በህዋላ ተለቆ ጋዜጠኛ አቶ ስዬ እስር ቤት እንዴት ነበር ሲለው ” እስር ቤቱ ሁሉ ኦሮምኛ ይናገራል” ነበር ያለው። ዛሬ ስዬም ወያኔም ብልጭ ድርግም እያሉ ነው ጊዜና እድሜ የሰው ደምና ክፋት ጊዜውን ቆጥሮ አሽቀንጥሯቸው። አሁን ደግሞ እስር ቤቱ ሁሉ ” አማርኛ ተናጋሪ” ነው። አይበቃም? ከአለፈው አንማርም? ይህች የሃበሻ ምድር ምሷ ምን ይሆን? ሁሌ የልጆቿን ደም መጋት? ተው በህዋላ ይሄ ልቅ የሆነ ጭካኔና ክፋት አዙሪቱ ሰፍቶ ምድሪቱን እንደ ሱዳን/የመን/ሶርያና ሌሎችም እንዳያደርጋት እንንቃ! እንበለ ፍርድ የታሰሩ እናቶች አባቶች ወንድሞችና እህቶች ሁሉ ይፈቱ! ምህረት በሃገሪቱ ላፍታም ቢሆን ደምቆ ይታይ!

Leave a Reply

Your email address will not be published.

191589
Previous Story

“ህልውናችንን አስጠብቀን ሀገራችንን እናድናለን” አርበኛና ጠበቃ አስረስ ማረ

new ethiopan amhara music off
Next Story

ሳሚ ጌቱ-ጃውሳው New Ethiopan Amhara music (official video)2024

Go toTop