ከምድር ግፍ እንጅ ፍትህ አጠብቂ!

June 25, 2024

Amhara cry

መላ ቤተሰብን ለሕዝብ ብትገብሪም፣
ዛሬ አንቺን የሚያስብ ብዙም አልተገኘም፡፡

ልብሽ እየደማ ሐዘንሽ መርቅዞ፣
አይንሽ እየቀላ የደም እንባ አጉርፎ፣
ስንቱ ይጨፍራል በደስታ ሰክሮ፣
በባሩድ በስደት ያለቀን ረስቶ፡፡

አባትሽን ገለው ለአውሬ ሜዳ ጥለው፣
ወንድምሽን ሰልበው ዘር መና አስቀርተው፣
አጎትሽን ጠልፈው ዳብዛውን አጥፍተው፣
አፍቅሪን ይሉሻል በደረቀ ዓይናቸው፡፡

አንቺም እንደኔው ሰውን ታዝበሻል፣
እንደ እምነት ፍቅርንም ካይምሮው አውጥቷል፣
ከልብ አንጀት ነቅሎ ከከንፈሩ አጣብቋል፡፡

ይሉኝታ ቢሶቹ እንደምታያቸው፣
ሮጠው ሳይጠግቡ በጨረገዷቸው፣
ለግላጋ ልጆችሽ ፍትህ በጠማቸው፣
ይቅርታ ይቅርታ ተባባሉባቸው፡፡

አንቺም ሆነ እኛ ወደ ላይ እናንጋጥ፣
እግዜር ፍርድ ውሳኔን ከሰማይ እንዲያወርድ፣
መነገጃ ሆኗል የይቅርታ መንገድ፡፡

እንደተረዳሽው ዛሬም ባደባባይ፣
ይቅርታ ጠያቂም ይቅርታ ተቀባይ፣
አንድም ነፍሰ-ገዳይ ወይም ይዞ አስገዳይ!

ሸምጋይና ወሳኝ አስታራቂም ብትይ፣
በተገፋ እሚፈርድ ኤፍሬም ይሳቅ መሳይ፡፡

ያያቶሽ ብሂል ሁሉን ጨርሶታል፣
አለባብሶ የሚያርስ ባረም ይመለሳል፣
ዋሽቶ የሚያስታርቅ ብጥብጥ ይዘራል፡፡

ለመሆኑ እታለም ይኸን ጠይቀሻል?
ሰማእትን ወክሎ ሰው ፍትህ ያስገኛል፣
እንዴት ይቅርታን ግን ሊቀበል ይችላል?

የተወጋው ልብሽ በምቱ አውግቶኛል፣
ያረረው አንጀትሽ በጪሱ ነግሮኛል፣
የቀላውም ዓይንሽ በእንባው አርድቶኛል፣
ለፍትህ ፀሎቱ እንቅልፍ ነስቶሻል፡፡

እባክሽ አታልቅሽ ባርባር አይበል ሆዴ!
እኔም የምኖር ነኝ ፍትህን ተርቤ፣
ላፅናናሽ አፅናኝኝ ቻይው እታለሜ!

በመርዶ ላይ መርዶ አይሁንብሽ እንጅ፣
ከምድር ግፍ እንጅ ፍትህ አጠብቂ!

ቀብረር ጅንን ብለሽ በክብር እንድትኖሪ፣
ወንድምሽ ክንድ ያሳይ አንቺም በለው በይ!

ባህር አሻጋሪዎች ዳግማዊ ሙሴ፣ ኢያሱና ሳምሶን መጡ
እያሉ ህልቁ መሳፍርት የሌላቸው ምሁራን በደለቁበት ዘመን የተደረሰ!

በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)
ሰኔ ሁለት ሺ አሥር ዓ.ም.

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Abiy 3
Previous Story

የፀረ ግፍ አገዛዝ ታጋድሎ እና መልካምና ፈታኝ ሁኔታዎች

Dr. Fekadu Bekele
Next Story

ኢትዮጵያን እናድን! እንዴት? ለእፍሬም ማዴቦ በዘሃበሻ ላይ ላቀረበው ጽሁፍ የተሰጠ ትችታዊ ማብራሪያ!!

Go toTop