ኢትዮጵያን እናድን !

ኤፍሬም ማዴቦ (emadebo@gmail.com )

በአለማችን ላይ ጠንካራ የፌዴራል ሥርዓት እንዳላት የሚነገርላት አሜሪካ፣ በ1776 ዓም ከእንግሊዝ ቅኝ አገዛዝ ነጻ ከወጣችበት ግዜ ጀምሮ በ1789 ዓም የመጀመሪያው በህዝብ የተመረጠ ፕሬዚደንት (ጆርጅ ዋሺንግተን) መሪዋ እስኪሆን ድረስ፣የመጀመሪያዎቹ 13ቱ ግዛቶች የተያያዙት በፌዴራል የመንግስት መዋቅር ሳይሆን በኮንፌዴሬሺን ነበር። ዛሬ በአለማችን በዕድሜ ተወዳዳሪ የሌለው (The Oldest Constition) በመባል የሚታወቀውና ከተጻፈበት ግዜ ጀምሮ አሁንም ድረስ የሚሰራው ህገ መንግስት፣ አሜሪካ ነጻ ሆና በቆየችባቸው በመጀመሪያዎቹ 13 አመታት አልነበረም። በእነዚህ 13 አመታት አሜሪካ ትተዳደር የነበረው “Articles of Confederation” በመባል በሚታወቀው ሰነድ ነበር። በዚህ ሰነድ መሠረት እያንዳንዱ ግዛት ማዕከላዊው መንግስት ጣልቃ የማይገባበት ልቅ የሆነ ከፍተኛ ሥልጣን የነበረው ሲሆን፣ ማዕከላዊው መንግስት ደሞ የወታደር ደሞዝ መክፈል እስኪያቅተው ድረስ ደሃና ደካማ መንግስት ነበር።

ከሚያስተዳድራቸው ግዛቶች (States) ያነሰ ሥልጣን የነበረውና ግብር የመሰብሰብ አቅም ያልነበረው ማዕከላዊው መንግስት፣ በእያንዳንዱ ግዛት ውስጥ የሚፈጠረውን ግጭትና በተለያዩ ግዛቶች መካከል የሚነሳውን የግዛት ይገባኛል ፍጥጫ ቁጭ ብሎ ከመመልከት ውጭ የማብረድም ሆነ የማቆም ሥልጣኑም ጡንቻውም አልበረውም። የእንደዚህ አይነት ደካማ ማዕከላዊ መንግስት መኖር ባለራዕዮቹን ጀምስ ማድሰንን እና ጆርጅ ዋሺንግተንን ሁሌም ዕረፍት ይነሳቸው ነበር። ሁለቱ ሰዎች በተለይ ማዲሰን፣ ጠንካራ ማዕከላዊ መንግስት ያለበት ፌዴራል ሥርዓት እንጂ፣ ኮንፌዴራሺን ለዚህ በጋራ ለፈጠርነው ትልቅ አገር ያለንን የወደፊት ራዕይ እውን አያደርግም ባይ ነበር። ማዲሰን ይህንን ሃሳቡን ለማስረጽ ከጓደኞቹ ከአሌክሳንደር ሃሚልተንና ከጆን ጄይ ጋር በመቀባበል ዛሬም ድረስ  እንደ መረጃ የሚያገለግለውን  “The Federalist Papaers” በመባል የሚታወቀውን ተከታታይ ጽሁፍ ጽፏል።

ሁለቱ ሰዎች (ጆርጅ ዋሽንግተንና ጀምስ ማዲሰን) ሃሳባቸውን እና ስጋታቸውን ለብዙ ስዎች በማጋራታችው፣በ1787 ዓም ፊላደልፊያ ላይ የተጠራው ኮንግሬስ የጆርጅ ዋሺንግተንና የጀምስ ማዲሰን ስጋት የሁላችንም ስጋት ነው ብሎ በማመኑ፣ዛሬ በስራ ላይ ያለውን የአሜሪካ ህገ መንግስት በማርቀቅ በፌዴራሊዝም የሚተዳደርና ጠንካራ ማዕከላዊ መንግስት ያለው “የተባበሩት የአሜሪካ ግዛቶች” የሚባል አዲስ ህብረት ፈጠረ። ዛሬ የብዙዎቻችን መጠጊያ የሆነችው የአለማችን ኃያሏና ኃብታሟ አገር አሜሪካ የዚህ ፈጠራ ውጤት ናት። አሜሪካ ኮንፌዴሬሺን ሆና ብትቀጥል ኖሮ፣ በተለያየ ግዜ ጥያቄ እያቀረቡ ከህብረቱ ጋር ተቀላቅለው ዛሬ በቁጥር 50 የደረሱ ግዛቶች ሊኖሩ ቀርቶ፣ የመጀመሪያዎቹ 13ቱ ግዛቶችም እንደ አገር አብረው መቀጠላቸው አጠራጣሪ ነበር።

ዛሬ ላወራችሁ የፈለኩት ስለአሜሪካ የአለማችን ኃብታምና ኃያል አገር መሆን አይደለም፣ይልቁንም ዛሬ እንድታውቁልኝ የምፈልገው፣ ኃብታምና ኃያል አገር መሆን በህልም የሚደረስበት ወይም በመፈክር ብዛት የሚመጣ ክስተት እንዳልሆነ ነው። ከእያንዳንዱ ኃብታምና ኃያል አገር ጀርባ፣ አርቀው የሚያስቡ፣ የዛሬውን ብቻ ሳይሆን የነገውን የሚመለከቱና ከራስ በላይ የሆኑ (Selfless) ባለራዕይ መሪዎች አሉ። አሜሪካ ጆርጅ ዋሺንግተን፣ ጀምስ ማዲሰን፣ ቶማስ ጃፈርሰንና ሌሎችም ዛሬ “The Founding Fathers” እየተባሉ የሚወደሱ ባለራዕይ መሪዎች ነበሯት። ጀርመን፣ ጣሊያን፣ፈረንሳይ፣ጃፓንና ሞንጎሊያ ደሞ ቢስማርክ፣ጋሊባርዲ፣ሻርልማኝ፣ ንጉሰ ነገስት ጂሙ እና ጂንጂስካን የሚባሉ አገሮቹን እንደ አገር ያቆሙ መሪዎች ነበሯቸው።

እንደ አውሮፓ ዘመን አቆጣጠር እስከ ጥር 18 1871 ዓም ድረስ ፔሩሲያ፣ ባቫሪያ፣ ሃኖቨር፣ ሳክሶኒ፣ ባደን፣ ሄሲ፣ውርቲምበርግ ወዘተ የሚባሉ በንጉስ የሚተዳደሩ ግዛቶች እንጂ ጀርመን የሚባለው ዛሬ በህዝብ ብዛቱ፣ በዕድገት ደረጃውና በኃብት የመጀመሪያ የሆነው የምዕራብ አውሮፓ አገር አልነበረም። የዛሬዋ ጀርመን የፔሩሲያው ጠ/ሚ ኦቶ ቢስማርክ በ1862 ከዴንማርክ፣ በ1866 ከኦስትሪያ በ1870 ደግሞ ከፈረንሳይ ጋር በተከታታይ ባደረጋቸው ጦርነቶች ያሰባሰባቸውና ያዋሃዳቸው ግዛቶች ዉጤት ናት። ኦቶ ቢስማርክ ከእነዚህ አገሮች ጋር ጦርነት የገጠመው ሰው የመግደል ጥማት ኖሮት ሳይሆን ዕድሜ ልኩን ይመኝ የነበረውን ትልቅ አገር (ጀርመን) የመፍጠር ፍላጎቱን ለማሳካት ነበር፣ ደግሞም ይህንን ፍላጎቱን በሚገባ አሳክቶ የዘመናችንን ትልቅ አገር ፈጥሯል። የዛሬዎቹ ጀርመኖች ሴት፣ ወንድ፣ወጣት፣ሽማግሌ ሳይሉ ጀርመን የሚባል ትልቅ አገር ፈጥሮ የሰጣቸው ሰው ሃውልት ስር በሰልፍ እየሄዱ ፎቶግራፍ ይነሳሉ እንጂ፣ አምስት ሚሊዮን ባቫሪያ ገደለ፣የሃኖቨር ሴቶችን ጡት ቆረጠ እያሉ አይንህ ይጥፋ ወይም ሃውልቱ ይፍረስ አይሉም።

የዘመናዊት ኢትዮጵያ አፈጣጠር ከዘመናዊቷ ጀርመን አፈጣጠር ጋር ተመሳሳይ ነው። ከዘመነ መሳፍንት በኋላ ዳግማዊ ሚኒልክ የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት ተብለው እስኪነግሱ ድረስ በነበረችው ኢትዮጵያ ዉስጥ የዛሬዎቹ የምዕራብ፣የምስራቅና የደቡብ ግዛቶች አልነበሩም። እነዚህን ግዛቶች ከተቀረው ኢትዮጵያ ጋር አዋህደው የዛሬዋን ትልቅ ኢትዮጵያ ፈጥረው የሰጡን ዳግማዊ ሚኒልክ ናቸው። አፄ ሚኒልክ ይህንን ለማድረግ ከጂማው አባጅፋር፣ ከወላይታው ጦና፣ከሐረር አሚሮችና ከአርሲ ኦሮሞዎች ጋር እልህ አስጨራሽ ጦርነት ተዋግተዋል። ልክ እንደ ጀርመኑ ቢስማርክ ዳግማዊ ሚኒልክም ትልቅ ኢትዮጵያን ለመፍጠር ሦስት ቁልፍ ጦርነቶች ተዋግተዋል። ዳግማዊ ምንሊክ በምዕራብ ከአባ ጅፋር፣በደቡብ ከንጉስ ጦና፣ በምስራቅ ከአርሲ ኦሮሞዎችና ከሐረር አሚሮች ጋር በሦስት አቅጣጫዎች ሄደው ጦርነት የገጠሙት ሰው የመግደል ሱስ ኖሯቸው አይደለም። አላማቸው ትልቅ ኢትዮጵያን መፍጠር ነበር፣ደግሞም ፈጥረው የዛሬዋን ትልቅ ኢትዮጵያ ሰጥተውናል። ከሳቸው በኋላ የመጣው ተከታታይ ትውልድ እሳቸው ሰርተው ያስረከቡትን ትልቅ አገር የበለጸገ የፍትህ፣ የነጻነት፣ የዲሞክራሲና የእኩልነት አገር ማድረግ ተስኖት እኚህን ትልቅ ሰው መራገም ጀመረ እንጂ፣ አፄ ሚኒልክ ኖረው የሞቱት ኢትዮጵያን ትልቅ አገር ለማድረግ ነው።

ከራሳችን በላይ የወደፊቷን ኢትዮጵያ ማሰብ ተስኖን፣ጎራ ለይቶ ከመገዳደል ውጭ ቁጭ ብለን መወያየት አቅቶን፣ ባጠቃላይ አንድን ሥርዓት ከማፍረስ ባሻገር ያፈረስነውን ሥርዓት በምን እንተካዋለን የሚለውን ጥያቄ ሥርዓቱን ከማፍረሳችን በፊት መመለስ ተስኖን ነው እንጂ፣ እኛ ኢትዮጵያዊያን ባለፉት ሃምሳ አመታት ኢትዮጵያን ዲሞክራሲያዊ አገር የማድረግና የአገረ-መንግስት ግንባታ ሂደታችንን አጠናቀን ሙሉ ኃይላችንን ለአገር ልማትና ዕድገት ማዋል የምንችልበት ሦስት ወርቃማ ዕድሎች አጋጥመውን ነበር። ታሪክ ቸር ሆኖ እነሆ ዛሬም አራተኛው ዕድል እጃችን ዉስጥ ነው።

አፄ ዘርዓ ያዕቆብ ንጉሰ ነገስት ተብለው ሲሾሙ ክርስቶፎር ኮሎምበስ ገና አልተወለደም ነበር፣ክርስትና የኢትዮጵያ መንግስት ሃይማኖት(State Religion) ሲሆን አፍሪካን ከክርስትና ጋር አስተዋወኩ ብላ የምትኩራራውን እንግሊዝን የአለም ካርታ አያውቃትም ነበር። አውሮፓ ውስጥ ድንቅ አብያተ ክርስትያናት በተገነቡበት ዘመን ኢትዮጵያ ውስጥም ዛሬ አለም የሚያደንቃቸው የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ተሰርተዋል። ታድያ ለምንድነው ከኛ በኋላ የመጡ አገሮች መፅዋች እኛ ተመፅዋች የሆነው? ለምንድነው መሠረት ሳይኖረን ግንባታ የሚያምረን? ለምንድነው እነዚህ መራራ እውነቶች በቁጭት አነሳስተውን ለፈጣን ዕድገት የመሠረት ድንጋይ የማናኖረው?

ኢትዮጵያ ውስጥ ደርግ እሱ እራሱ በውል የማያውቀውን ሶሻሊስት ሥርዓት ለመገንባት ለ17 አመታት ማድረግ የሚችለውን ሁሉ አድርጓል፣ ዛሬ ደርግም አቆመዋለሁ ብሎ የታገለለት ሶሻሊስት ሥርዓትም የሉም። ህወሓ/ኢህአዴግ በማንነት ላይ የተመሰረተ ፌዴራል ሥርዓት ፈጥሮና አብዮታዊ ዲሞክራሲ ብሎ 27 አመት ቆየ። ዛሬ ህወሓት/ኢህአዴግ በብልፅግና፣ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ደሞ ”መደመር” በሚሉት ምናቡ ያልተባ ፍልስፍና ተተክተዋል፣ ነገር ግን ህወሓት የተከለው የማንነት ፓለቲካና ከዚህ ፖለቲካ ጋር ቆርበው የተጋቡ የህወሓት ልጆች አሁንም ኢትዮጵያን እየመሩ ነው። ይህንን በ2010 ዓም አጋማሽ ላይ “ስንኖር ኢትዮጵያዊ” . . . “ስንሞት ኢትዮጵያ” እንሆናለን እያለ ሲመጣ በሆታ የተቀበልነውና በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶም ተሰምቶም የማይታወቅ ድጋፍ የሰጠነውን መንግስት ዛሬ እየታገልነው ነው። እኛ ኢትዮጵያዊያን ምን ዕዳ ጥሎብን ነው አንድን ሥርዓት ታግለን አስወግደን ወር ሳይሞላን አዲስ የመጣውን ሥርዓት መታገል የምንጀምረው? ለምንድነው በ1966፣ በ1983 እና በ2010 በቅርፅና ይዘት የሚለያዩ ሦስት ሥርዓቶችን ማስወገድ የቻለ ህዝብ አንዴም ታግሎ ካስወገደው ሥርዓት የተሻለ ሥርዓት መገንባት የተሳነው?

ባለፉት ሃምሳ አመታት የተቃውሞ ፖለቲካ ታሪካችን ውስጥ፣ በህወሓት የተመሩ ኃይሎች እንደጻፉት ህገ መንግስት ተቃውሞ የቀረበበትና የህዝብን ተቀባይነት ያጣ ምንም ነገር የለም። ታድያ ምነው 120 ሚሊዮን ህዝብ በሚኖርባት ኢትዮጵያ ውስጥ፣ ይህ ህገ መንግስት አብሮ አያኖረንም፣ ይህ ህገ መንግስት የወደፊቷን ትልቅና የበለጸገች ኢትዮጵያን አይፈጥርም፣ ይህ ህገ መንግስት እስካለ ድረስ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላምና መረጋጋት አይኖርም ብሎ በድፍረት የሚናገርና፣ ህዝብን አስተባብሮ ህገ መንግስቱ እንዲሻሻል የሚያደርግ ባለ ራዕይ መሪ ማየት አቃተን? ምነው ከጎጥ ይልቅ አገርን፣ ከዛሬው ይልቅ የወደፊቱን፣ ከግዜያዊ ጥቅም ይልቅ ዘለዓለማዊ ስምን፣ከራሱ ጥቅምና ዝና በላይ የኢትዮጵያን ዘላቂነትና ትልቅነት የሚያስቀድም መሪ መፍጠር ተሳነን? ለምንድነው የትልቅ አገር መሠረት አኑረን ተከታታይ ትውልድ እንደነ ጆርጅ ዋሺንግተን እና እንደነ ጀምስ ማዲሰን  “መስራች አባቶች” ብሎ የሚጠራንን ትልቅ ስም ትተን የትንሽ ጎጥ መሪ መሆን የሚያምረን?

ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የመንግስት መዋቅር ፌዴራልዝም ነው ተብሎ በህገ መንግስቱ ውስጥ ይጻፍ እንጂ፣ ኢትዮጵያ ዉስጥ ያለው ፌዴራል ሥርዓት “ፌዴራሊዝም” ኢትዮጵያን በመሳሰሉ ህብረ-ብሔር አገሮች ውስጥ ማድረግ የሚገባውን እንዲያደርግ ተደርጎ ዲዛይን ባለመደረጉ፣ በብሔር ብሔረሰቦች መካከል መኖር የሌለበት ግኑኝነት ተፈጥሮ ዛሬ በምስራቅ፣ በምዕራብ፣ በደቡብና በሰሜናዊው የአገራችን ክፍል በሚገኙ ክልሎች ወይም ብሔሮች መካከል እስከ ጦርነት ድረስ የዘለቀ የግዛት ይገባኛል ጥያቄ አለ። ህወሓት ሥልጣን ላይ በነበረባቸው 27 አመታት ዉስጥ እያንዳንዱ ክልል እራሱን በራሱ ያስተዳድራል ይባል እንጂ በማዕከልም በክልልም ሥልጣን ብቻውን ተቆጣጥሮ በፌዴራሊዝም ስም ኢትዮጵያን በአሃዳዊነት የመራው ህወሓት ነው። ህወሓት ከሥልጣን ከተወገደ በኋላ የተፈጠረው ማዕከላዊ መንግስት ደሞ ባለፉት 50 አመታት ከነበሩን ማዕከላዊ መንግስታት ጋር ሲነፃፀር እጅግ በጣም ደካማው መንግስት በመሆኑ፣የኢትዮጵያ ፌዴራል ሥርዓት ከመጠን በላይ ላልቶ፣ዛሬ ማዕከላዊውን መንግስት የሚገዳደሩ ብቻ ሳይሆን ከማዕከላዊው መንግስት ጋር ውጊያ ገጥሞ አገርን ያመሰ ክልል አለ። ይህ አልበቃ ብሎ ጭራሽ የአንዳንድ ክልል መሪዎችና የፖለቲካ ልህቃን አሜሪካና ሲዊዘርላንድን የመሳሰሉ ፌዴራል የመንግስት መዋቅር ያላቸው የዛሬዎቹ የአለማችን ኃብታም አገሮች ከምዕተ አመታት በፊት አይበጀንም ብለው ከላያቸው ላይ አራግፈው የጣሉትን ኮንፌዴሬሺን ይሻለናል ማለት ጀምረዋል።

ዛሬ በብዙዎቹ ክልሎች ውስጥ ማንነትን መሠረት ያደረጉ መንግስታዊ አሰራሮችና የዚህ አደገኛ አሰራር ዉጤት የሆኑ በማንነት ላይ የተመሰረቱ ግጭቶችና ግድያዎች አሉ። የኢትዮጵያ ህገ መንግስት መሬትና ማንነት እንዲጣበቁ ያደረገ ህገ መንግስት በመሆኑ፣ ባለፉት ሰላሳ አመታት ደቡብ ኢትዮጵያ፣ ቤንሻንጉልና ኦሮሚያ ውስጥ “መጤ” ነህና ወደ መጣህበት ሂድ በሚል ዘመቻ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ኢትዮጵያዊ ከቅድም አያቶቹ ጀምሮ ከኖረበት አካባቢ ተፈናቅሎ ቤትና መሬት አልባ ሆኗል። ጠሚ አቢይ አህመድ ወደ ሥልጣን በመጡባቸው የመጀመሪያዎቹ 18 ወራት ውስጥ ብቻ ኦሮሞና ሱማሌ፣ወላይታና ሲዳማ፣አፋርና ሱማሌ፣ጌዲኦና ጉጂ፣ ሞያሌ ውስጥ ደሞ በቦረናዎችና በገሪ ማህበረሰቦች መካከል ጦርነት ተቀስቅሶ የብዙ ሰላማዊ ዜጎች ህይወት ተቀጥፏል። ወለጋ፣ ሸዋ፣አርሲና ባሌ ውስጥ የአማራ ተወላጆችና የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች እንደ ዱር አውሬ እየታደኑ ታርደዋል።

ኦሮሚያ ዉስጥ ኦሮሞዎችና ከኦሮሞ ውጭ የሆኑ ዜጎች የመሬት ባለቤትነትንና ሰርቶ ኃብት ማፍራትን በተመለከተ እኩል መብት የላቸውም፣ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ህገ መንግስት የአራት ብሔሮችን ስም ይጠቅስና እነሱን የክልሉ ባለቤቶች ናቸው ብሎ የተቀሩትን “ሌሎች” በሚል አግላይ ቃል ይጠቅሳቸዋል። የትግራይ ክልል መዝሙር  “በጅቦች እንከበብ መሬት ይጥበበን”  . . .“የጠላቶቻችን ጥርስ ስጋችን ውስጥ ይቀርቀር” የሚሉ አብሮነትን የማይጋብዙ ስንኞች አሉበት። እነዚህ አብረው የማያኖሩን፣ እንደ አንድ አገር ህዝብ እንዳንተያይ የሚያደርጉንና ለጠንካራ አገራዊ አንድነት መፈጠር እንቅፋት የሆኑ የፌዴራሉና የክልል ህገ መንግስቶች በቀጥታና በተዘዋዋሪ መንገድ የፈጠሯቸው ግኑኝነቶች እስካልተበጠሱና አዲስ ማህበራዊ ኮንትራት እስካልተፈራረምን ድረስ፣ የኮሪዶር ልማት ብንል፣ የዳር አገር ልማት፣ፓርክ ብንሰራ፣አደባባይ ብንሰራ፣ ጫካ ፕሮጀክት ብንል ሜዳ ፕሮጀክት ብዙ ርቀት መጓዝ የምንችል አይመስለኝም። ጠንካራ መሠረት በሌለው ቤት ላይ ወደጎንም ወደ ላይም ብንጨምርበት ጭራሽ ያቺው ያለችን አንድ ቤት ተደርምሳ ቤት አልባ እንሆናለን እንጂ መሠረት የሌለውን ቤት ማተለቅ አንችልም።

አገራችን ኢትዮጵያ ዉስጥ ከአመታት በፊት ተጀምሮ ያልተጠናቀቀ የአገረ-መንግስት ግንባታ ሂደት አለ፣ የዛሬው ትውልድ ይህንን ሂደት ሁላችንንም በሚያስማማ መልኩ ከፍጻሜው የማድረስ ታሪካዊ ኃላፊነት አለበት። የብሔር ፓለቲከኞች “አሃዳዊያን” እያሉ በነጋ በጠባ የሚያብጠለጥሉት ማንን እንደሆነ በግልጽ ባይታወቅም፣ ዛሬ ፌዴራሊዝምን በተመለከተ ኢትዮጵያ ውስጥ በቀኝም በግራም በኩል ያለው ሃቅ ከፌዴራሊዝም ጋር የተጣላ የፖለቲካ ድርጅት አለመኖሩ ነው። እውነቱን እንናገር ከተባለ፣ ላለመስማማት የተማማሉት የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች የሚስማሙበት አንድ ጉዳይ ቢኖር፣ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ፌዴራል የመንግስት መዋቅር ነው ማለታቸው ነው. . . . . የሚለያዩት ምን አይነት የፌዴራል አወቃቀር ያስፈልገናል በሚለው ጥያቄ ላይ ነው።

ኢትዮጵያ ውስጥ መሠረቱን ብሔር ያደረገ የፓለቲካ ሥርዓትና የዜግነት ፓለቲካ አብረው ጎን ለጎን መኖር አይችሉም፣ ከሁለቱ አንዱን መምረጥ አለብን። አንዱን መረጥን ማለት ግን የሌላውን ደጋፊዎች እናቅፋለን ማለት ነው እንጂ፣እንዳለፈው ሃምሳ አመት ታሪካችን እናጠፋቸዋለን ወይም እንበቀላቸዋልን ማለት አይደለም። በሌላ በኩል ደሞ በርካታ  ቁጥር ያለው ኢትዮጵያዊ መሠረቱን ብሔር ካደረገው ፌዴራሊዝም መላቀቅ እየፈለገ ከማይስማማው፣ ሰላሳ አመት ሙሉ ዋጋ ካስከፈለውና አሁንም እያስከፈለው ካለ ሥርዓት ጋር በግድ አብረህ ኑር ሊባል አይገባም።

የብሔር ፖለቲካ በዜጎች መካከል “እኛ” እና “እናንተ” የሚል ግድግዳ የሚፈጥር አግላይ ፖለቲካ መሆኑን ዛሬ አፍሪካ ውስጥ ከኛ ከኢትዮጵያዊያን በላይ የሚረዳ ሌላ ህዝብ ያለ አይመስለኝም። የሁላችንንም ማንነት፣ ባህል፣ ቋንቋና ሃይማኖት የሚያከብርና እውቅና የሚሰጥ ጠንካራ አገራዊ አንድነት ያለውና፣ መሠረቱ ፍትህ፣ነጻነትና እኩልነት የሆነ ዲሞክራሲያዊ አገር መፍጠር ከፈለግን፣ አግላይ ከሆነው የማንነት ፖለቲካ መላቀቅ አማራጭ ሳይሆን ግዴታ ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ በሚከፍለው ግብር የሚተዳደሩትን የአገራችንን ዋና ዋና የሜዲያ አውታሮች 100% ተቆጣጥሮ የራሱ ፕሮፓጋንዳ መሳሪያ ያደረጋቸው የብልፅግና ካምፕ በነጋ በጠባ እንደሚሰብከው ሁሉንም ነገር በማንነት ቀመር እየቀመርን የመጨረሻውን ውጤት ኢትዮጵያዊነት ማድረግ አንችልም። ኢትዮጵያዊነት 80ውንም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች እኩል እንዲያቅፍ አድርገን ዲዛይን ማድረግ እንችላለን፣ደሞም ይህ ዲዛይን የማድረጉ ስራ እኛ እንስማማ እንጂ እጃችን ዉስጥ ያለ ስራ ነው። የብሔር ፖለቲካ ግን በተፈጥሮው አግላይ ፖለቲካ በመሆኑ ሺ ግዜ ዲዛይን ብናደርገው ሁላችንንም እኩል አያቅፍም። የብሔር ፖለቲካ ምን ያክል አግላይ ፖለቲካ እንደሆነ ህወሓቶች 27 አመት ሙሉ አሳይተውናል፣ ጉዟቸውን “ኢትዮጵያ’ ብለው የጀመሩት ብልፅግናዎች ደሞ አሁንም በግልፅ እያሳዩን ነው።

ህንድ እንደ ኢትዮጵያ ፌዴራል የመንግስት መዋቅርን የምትከተልና በሺዎች የሚቆጠሩ ብሔር ብሔረሰቦች የሚኖሩባት አገር ናት። የህንድ መስራች አባቶች የዛሬዋን ህንድ የፈጠሩት በህብረ-ማንነት ላይ ተመስርተው ነው (Composite Nationalism)። አንድን የህንድ ዜጋ ማንነት የሚገልጹት የብሔር፣ የቋንቋ፣ የሃይማኖት፣ የባህልና ፕሮፌሺናል ማንነቶች ሁሉም አንድ ላይ ሆነው  ነው  እንጂ፣ አንድ የህንድ ዜጋ በአንድ ነጠላ ማንነት ብቻ አይገለጽም። እኛም አገር አንድ የኦሮሞ ተወላጅ እንደየአግባቡ በኢትዮጵያዊነቱ፣በኦሮሞነቱ፣የእስልምና እምነት ተከታይ ከሆነ በሙስሊምነቱ፣ የማዕከል ፖለቲካ አራማጅ ከሆነ በማዕከላዊነቱ፣መሃንዲስ ከሆነ በመሃንዲስነቱ ተራ በተራ ሊገለጽ ይገባዋል እንጂ፣ ከእነዚህ ብዙ ማንነቶች ዉስጥ አንዱን ብቻ ነጥለን አውጥተን የሚገልጽህ ማንነት ይህ ብቻ ነው ማለት የፖለቲካ ሽባነት ነው።

ህንድ ውስጥ 28 ክልሎችና 8 “Union Territories” አሉ። እያንዳንዱ የህንድ ግዛት ሁለትና ከሁለት በላይ ብሔር ብሔረሰቦችን ያቀፈ ሲሆን፣ ህንድ ውስጥ እንደ ኢትዮጵያ አንድን ግዛት በብቸኝነት የኔ ነው የሚል ብሔር የለም። የህንድ ህገ መንግስት መግቢያ ከኛ ህገ መንግስት መግቢያ ፍጹም በተለየ መንገድ “እኛ የህንድ ህዝብ” ብሎ ነው የሚጀምረው። ይህ መሠረቱን ህዝብ ያደረገ ህገ መንግስት ነው ህንድ የአለማችን ትልቁ ዲሞክራሲ ተብላ እንደትጠራና የሰላምና የመረጋጋት አገር ያደረጋት። ህንድ ውስጥ በተለያዩ የቋንቋ፣የባህልና የሃይማኖት ስብስቦች መካከል ግጭት አይፈጠርም ማለት አይደለም፣ ግን ህንድ ዉስጥ ግጭቶች ተፈጥረው እንደ ኢትዮጵያ ህይወትና ንብረት ወደሚያወድም ጦርነት አያመሩም፣ ምክንያቱም የህንድ ዲሞከራሲ እንደዚህ አይነት ችግሮችን እንዳይጀመሩ ማድረግ፣ ማርገብ ወይም ማስወገድ በሚችልበት መንገድ ነው የተዋቀረው።

ወደራሳችን ክፍለ አህጉር ወደ አፍሪካ መጥተን ናይጄሪያን ስንመለከት ደሞ፣ ናይጄሪያ ነጻነቷን ካገኘችበት ከ1960 ዓም ጀምሮ ያተራመሳትንና ሁለት አመት ለፈጀ የርስ በርስ ጦርነት የዳረጋትን የብሔር ፖለቲካ በቃኝ ያለች አገር ናት፣ዛሬ ናይጄሪያ ዉስጥ መሠረቱን ብሔር ወይም ሃይማኖት ያደረገ የፖለቲካ ፓርቲ ማደራጀት በህግ የተከለከለ ነው። ናይጄሪያ ውስጥ 36 ክልሎች አሉ፣ልክ እንደ ህንድ ናይጄሪያ ዉስጥም እያንዳንዱ ክልል ሁለትና ከሁለት በላይ ብሔር ብሔረሰቦች አብረው ግዛታችን ነው ብለው ስለሚኖሩ፣ በዛሬዋ ናይጄሪያ ዉስጥ አንድን ግዛት ወይም ክልል አንድ ብሔር ብቻውን የኔ ነው ብሎ ሌሎችን ማግለል አይችልም። ናይጄሪያ ከ250 በላይ ብሔር ብሔረሰቦች የሚኖሩባት አገር ናት። የናይጄሪያ ህገ መንግስት እንደ ህንድ ህገ መንግስት “እኛ የናይጄሪያ ህዝብ” ብሎ ነው የሚጀምረው።

አገር ለመሆን በተመሳሳይ የጆግራፊ ክልል የሚኖርና ተመሳሳይ ታሪክ፣ባህልና ትርክት የሚጋራ ማህበረሰብ ያስፈልጋል። በዚህ ማህበረሰብ ውስጥ ዲሞክራሲ ለመገንባት “ህዝብ’ ተብሎ የሚጠራ የዲሞክራሲ መሠረት የሆነ ክስተት ያስፈልጋል፣ ለዚህ ነው የህንድ፣ የናይጄሪያና ሁሉም በሚባል መልኩ የአብዛኛው የአለም አገሮች ህገ መንግስቶች መግቢያ “እኛ” እና የዚህ ወይም የዚያ አገር “ህዝብ” በሚል መሠረታዊ ቃል የሚጀምረው። ናይጄሪያ ከእንግሊዝ ቅኝ አገዛዝ ነጻ ከወጣችበት ከ1960 ዓም ጀምሮ ለመጀመሪያዎቹ 30 አመታት በብሔር ፖለቲካ፣አይን ባወጣ ሙስና፣በተከታታይ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስትና ሁለት አመት ተኩል በቆየ የርስ በርስ ጦርነት የታመሰች አገር ናት። የናይጄሪያ አራተኛው ሪፑብሊክ አንፃራዊ ሰላምና መረጋጋት አግኝቶ መኖር የቻለው ናይጄሪያ የብሔር ፖለቲካን ለማርገብ ተከታታይ ህገ መንግስታዊ ዕርምጃዎች በመውሰዷ ነው።

የአገር ወይም የአንድ ፖለቲካ ማህበረሰብ መሠረቶች ግለሰቦች ናቸው እንጂ ብሔር ብሔረሰቦች አይደሉም፣ ሊሆኑም አይችሉም፣ ምክንያቱም ግለሰቦች ሳይኖሩ ብሔር ብሔረሰቦች የሚባል ጽንሰ ሃሳብ እራሱ ሊኖር አይችልም። ሰው የእግዚአብሔር ፍጡር ነው የሚለውን አስተምህሮ ለምናምን ሰዎች (እኔን ጨምሮ)፣ እግዚአብሔር አዳምና ሔዋን ተብለው የሚጠሩ ሁለት ግለሰቦችን ነው የፈጠረው እንጂ፣ ትግሬ፣ ኦሮሞ፣ አማራ፣ሱማሌ፣ሲዳማ ወዘተ የሚባሉ የወል ስብስቦችን አልፈጠረም። የሰው ልጅ የአዝጋሚ ለውጥ(Evolution) ሂደት ዉጤት ነው ብለው ለሚያምኑ ሰዎችም ቢሆን፣ በአዝጋሚ ለውጥ ሂደት ከሌላ ዛሬ በምድር ላይ ከሌለ የእንስሳ ዝሪያ ወደ ሰውነት የተለወጡት ግለሰቦች ናቸው እንጂ፣ብሔር ብሔረሰቦች አይደሉም። ስለዚህ ብሔር ብሔረሰቦችን ከግለሰቦች ማስቀደምና የግለሰቦች የወደፊት ዕድል በብሔር ብሔረሰቦች እንዲወሰን ማድረግ የማህበረሰብን ዕድገት ወደ ኋላ ከመጎተት ተነጥሎ አይታይም። ብሔር ብሔረሰቦች ግለሰቦች በረጂም ግዜ አብሮ የመኖር ሂደት የፈጠሯቸው ማህበራዊ ስሪቶች ናቸው።

ዲሞክራሲ  ጥንታዊያን  ግሪኮች  “ዴሞስ”  (The  People)  እና  “ክራቲያ”  (Power or Authority) የሚባሉ ሁለት ቃላቶቻቸውን አጣምረው የፈጠሩት ግዙፍ ፅንሰ ሃሳብ ነው። ይህ ማለት ደሞ ዴሞክራሲ የሚበለው ትልቅ ተቋም ገና ካፈጣጠሩ ጀምሮ “ህዝብ” ከሚባል ክስተት ጋር በቅርብ የተቆራኘ ነው ማለት ነው፣ህዝብ ማለት ደሞ የግለሰቦች ጥርቅም ማለት ነው። ጠቅለል ባለ መልኩ ዲሞክራሲ ማለት የፖለቲካ ሥልጣንን ለህዝብ የሚሰጥ ሥርዓት ማለት ቢሆንም፣ ከዲሞክራሲ መሰረታዊ መርሆዎች ውስጥ አንዱና ዋነኛው፣ አብዛኛው በዲሞክራሲ ስም አናሳውን እንዳሰኘው ውጣ ግባ ማለት እንዳይችል ወይም አናሳው በዲሞክራሲ ስም በአብዛኛው እንዳይጨፈለቅ ማድረግ ነው. . . . . በየትኛውም የፖለቲካ ማህበረሰብ ውስጥ የመጨረሻው ትንሹ አናሳ ደሞ ግለሰብ ነው (The smallest minority on earth is the Individual)-

የኢትዮጵያ ህገ መንግስት መሻሻል አለበት እያሉ ላለፉት 30 አመታት የጮሁ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ የመጀመሪያ ትኩረታቸው ህዝብን መሠረቱ ያላደረገው የህገ መንግስቱ መግቢያና፣ የአገርን ሉዓላዊነት ለህዝብ ሳይሆን ምንነታቸው በውል ተለይቶ ለማይታወቅ ለብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የሰጠው አንቀፅ ላይ ነው። እነዚህ ሁለት አንቀጾችና ሌሎችም የኢትዮጵያን እንደ አገር ቀጣይነት አደጋ ላይ የጣሉ አንቀጾች ሳይሻሻሉ፣ እራሱን ከውጭና ከውስጥ አደጋ መጠበቅ የሚችል አገር፣ጠንካራ አገራዊ አንድነትና የበለጸገ የኤኮኖሚ ሥርዓት መገንባት አንችልም። ለመሆኑ የብሔር፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች ትክክለኛ ትርጉም ወይም አንድነታቸውና ልዩነታቸው ምንድነው? ደሞስ ኢትዮጵያ ዉስጥ ብሔር ሆኖ ብሔረሰብና ህዝብ ያልሆነ፣ብሔረሰብ ሆኖ ብሔርና ህዝብ ያልሆነና፣ ህዝቦች ሆኖ ብሔርና ብሔረሰቦች ያልሆነ ማነው? በ1987 ዓም የጸደቀውና ዛሬም ድረስ በስራ ላይ ያለው የኢትዮጵያ ህገ መንግስት የአገርን ሉዓላዊነት የሰጠው ምንነታቸው፣አንድነታቸውና ልዩነታቸው በውል ተለይቶ ለማይታወቅና፣ ግለሰቦች በረጂም ዘመን አብሮ የመኖር ሂደት ውስጥ ለፈጠሯቸው ማህበራዊ ስሪቶች ነው (Socially Constructed)።

ዛሬ ያለንበት ዘመን የኢትዮጵያን እንደ አገር ቀጣይነት አረጋግጠን፣ኢትዮጵያን እንደ ብዝሃነቷ መሸከም የሚችሉ ዲሞክራሲያዊ ተቋሞች ገንብተን፣ የጠንካራ የኤኮኖሚ ማህበረሰብ ግንባታ ምዕራፍ የምንጀምርበት፣ ወይም ወደ ትናንሽ የጎጥ መንግስታት ተለውጠን እርስ በርስ የምንተላለቅበትና የሩቅና የቅርብ ጠላቶቻችን መጫወቻ መሆን የምንጀምርበት የታሪክ መታጠፊያ ላይ ነው። ምርጫችን የቱ ነው? ምርጫችን ሁለተኛው ከሆነ ሆዳችንን እየሞላን ያ ቀን እስኪደርስ መጠበቅ ነው እንጂ ሌላ ምንም ማድረግ አይጠበቅብንም። ምርጫችን የመጀመሪያው ከሆነ ግን ቅደም ተከተል አውጥተን መስራት ያለብን ብዙ ከበድ ያሉ ስራዎች አሉ። የመጀመሪያውን ምርጫችንን ከባድ የሚያደርገው አገራችን ባለፉት ሃምሳ አመታት የገባችበት የፖለቲካ ውጣ ውረድና ዛሬ የምትገኝበት እጅግ በጣም አሳሳቢ ሁኔታ ነው።

ዛሬ በአንድ በኩል፣የትግራይ ወራሪ ኃይሎች ሰሜን ኢትዮጵያን ለሁለት አመት የጦርነት ቀጣና ማድረጋቸው አልበቃ ብሏቸው እንደገና ወደ አማራ ክልል እየገቡ የተለያዩ አካባቢዎችን በኃይል እየያዙ ነው፣ በሌላ በኩል ደሞ እመራዋለሁ የሚለው ህዝብ አንዴ በህወሓት፣አንዴ በኦነግ ሸኜ አሁን ደሞ በጠሚ አቢይ ሠራዊት ቁም ስቅሉን ሲያይ አጁን አጣጥፎና አፉን ዘግቶ የተቀመጠው የአማራ ክልል መንግስት ትዕግስቴ እያለቀ ነው እያለ ነው። የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ኦሮሚያ ክልልን የሞት ቀጣና ስላደረጉት ዛሬ ከአዲስ አበባ በየትኛውም አቅጣጫ በመኪና መጓዝ በህይወት መወራረድ ሆኗል። በዚህ የተነሳ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአገር ውስጥ በረራ የሚያገኘው ገቢ በሁለትና ሦስት እጥፍ አድጓል። ሌላ ሁሉ ቀርቶ ከአዲስ አበባ 275 ኪሜ ርቀት ወደምትገኘው ሃዋሳ እንኳን በአውሮፕላን እንጂ በመኪና መጓዝ ቀርቷል። የጠሚ አቢይ ሠራዊት በአንድ ወቅት ከጉድ ካዳነው ከአማራ ክልል ጋር ትርጉም የለሽ ጦርነት ዉስጥ ከገባ አንድ አመት ሊሞላው ነው። በህዝብ ብዛት፣ በቆዳ ስፋትና በኤኮኖሚያዊ እንቅስቃሴያቸው የኢትዮጵያ 60% በላይ የሆኑት ኦሮሚያና አማራ ክልል ምርት ማምረቱን ትተው የጦርነት ቀጣና ሆነዋል።

በአቶ ሽመልስ አብዲሳና በወሮ አዳነች አቤቤ የሚመራው ቡድን አዲስ አበባን በኛ አምሳያ እንሰራታለን የሚለውን ዘመቻ ከጀመረ ሁለት አመት አልፎታል። ይህ ዘመቻ አዲስ አበባና አካባቢያዋን ሰዎች በማንነታቸው ቤታቸው የሚፈርስበት፣የሚፈናቀሉበት፣የሚታፈኑበት፣    የሚታሰሩበትና የሚገደሉበት ቦታ እንዲሆን አድርጓል። በ10 ሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ሠላም በመጥፋቱና ት/ቤታቸው የወታደር ካምፕ በመሆኑ ትምህርት መማር አቁመዋል፣ገበሬው ማረስ ቀርቶ በሬውን ጠምዶ ከመኖሪያ ቤቱ ፈቀቅ ማለትም አልቻለም። የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የሚበላ ጠፍቶ ተራብን እያሉ ነው፣የመሠረታዊ ፍጆታ ዕቃዎች እጥረትና የዋጋ መናር የኢትዮጵያ ህዝብ ከሦስቱ የቀን ምግቦች አንዱን እንዲመርጥ እያደረገው ነው (እሱም ከተገኘ ነው)። ትግራይ ውስጥ ህገ ወጥነትና ስነስርዓት አልባነት ነግሶ ለጋ ወጣቶች ታፍነው ገንዘብ እየተጠየቀባቸው፣ ገንዘቡ ካልተከፈለ እሬሳቸው በየስርቻው እየተለቀመ ነው። የመንግስት ባለሥልጣኖች ከአገርና ከህዝብ የሚዘርፉት መጠነ ሰፊ ገንዘብ አልበቃ ብሏቸው የግለሰቦችን ኃብትና ንብረት በማንአለብኝነት እየቀሙ ነው። ዱባይ ዉስጥ መኖሪያ ቤት ያልገዛ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ ባለሥልጣን “ፋራ” እየተባለ የዘበትበታል። ኢትዮጵያ ዝርፍያ ክብርና ብልጠት፣ አለመዝረፍ ደሞ የሞኝነት ምልክት የሆነባት የጉድ አገር ሆናለች። አገራችን ኢትዮጵያ ይህንን ሁሉ ሌሎች አገሮች ለአንድ ቀንም የማይችሉትን ድርብርብ ዕዳ ተሸክማ እንደ አገር የዘለቀችው በረጂም ግዜ ሂደት የተገነባ አብሮነት ያለባት አገርና፣ ከሺ አመታታ በላይ የዘለቀ ተከታታይ ሥርዓተ መንግስት ያላት አገር በመሆኗ ነው። እኛ ልጆቿ ቁጭ ብለን መክረንና መላ አግኝተን ከዚህ አደገኛ መንገድ ካልገላገልናት ግን በዚህ በተያያዘችው መንገድ ላይ ብዙ የምትቀጥል አይመስለኝም!

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ባለፉት ሃምሳ አመታት የገባበት ቅርቃርና ዛሬ አገራችን የምትገኝበት እጅግ በጣም አሳሳቢ ሁኔታ እኛ ልጆቿ ከዚህ ቀደም ካደረግነው ጥረት በተለየ መንገድ አስበን፣ተናበንና ቁጭ ብለን መክረን የተለያዩ ፓለቲካዊና ማህበራዊ ውሳኔዎችን የማንወስንና ውሳኔውን ተግባራዊ የማናደርግ ከሆነ፣ከጀግኖች አባቶቻችን የተረከብናትንና የጥቁር ህዝብ የነጻነት ተምሳሌት የሆነችውን አገር እንደገና በምናውቃት መልኩ ላናያት እንችላለን። ኢትዮጵያ ሁሉም ዜጎቿ እኩል አገሬ የሚሏት አገር እንጂ እያንዳንዱ በለስ የቀናው የብሔር ልህቅ ሥልጣን ላይ እየወጣ የሚዘርፋትና ከሱ ብሔር ውጭ የሆኑ የሌሎች ብሔር አባላትን የሚያስርባት፣ የሚገድልባትና ከፖለቲካዊና ኤኮኖሚያዊ ተሳትፎ የሚያገልበት አገር ሆና መቀጠል አትችልም።

ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ በየአቅጣጫው የሚካሄዱ የተለያዩ ህዝባዊ እንቅስቃሴዎች አሉ። አንዳንዶቹ በመሳሪያ የታጀቡ የህልውና እንቅስቃሴዎች ናቸው፣አንዳንዶቹ ከዚህ የባሰ ምን ሊመጣ ይችላል የሚሉ ነገር ግን መሪና አስተባባሪ የሌላቸው በየቤቱ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ናቸው፣አንዳንዶቹ ያዩትንና ያለፉበትን ቦታ ሁሉ የኛ ነው በሚሉ ተስፋፊዎች ልንዋጥ ነው የሚሉ ከፍራቻ የመነጩ እንቅስቃሴዎች ናቸው። እነዚህን እንቅስቃሴዎችና ሌሎችንም የሚያመሳስላቸው ጉዳይ ቢኖር ሁሉም ጠንካራ ፀረ ብልፅግና አቋም ያላቸው እንቅስቃሴዎች መሆናቸው ነው።

እነዚህ በተናጠል የሚካሄዱ ሦስት የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ዛሬ ሁሉንም ነገር እኔ ጀምሬ እኔው ካልጨረስኩ ከሚለውና ካልሰማችሁኝ እጨፈጭፋችኋለሁ ከሚለው የብልፅግና አገዛዝ ጋር ፊት ለፊት የሚጋፈጥና፣ የዚህን የዘር ፖለቲካ የመጨረሻ ዋሻ የሆነ ፀረ አንድነት ድርጀት ዕድሜ የሚያሳጥር ግንባር መፍጠር አለባቸው። በተለይ እነዚህ የተጀመሩና ገና በጅምር ላይ ያሉ እንቅስቃሴዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ከዚህ ቀደም ታይቶ የማይታወቅ የፖለቲካ ለውጥ በአጭር ግዜ ዉስጥ ማምጣት በሚችሉበት መንገድ መቀናጀትና መጣመር አለባቸው፣ ደግሞም አብዛኛውን ኢትዮጵያዊ ያቀፉ እንዲሆኑ ወይም አብዛኛው ኢትዮጵያዊ እነዚህ እንቅስቃሴዎች የኔ ናቸው ብሎ እንዲቀላቀል ሁላችንም የየራሳችንን አስተዋጽኦ ማድረግ አለብን።

ኢትዮጵያ ውስጥ በደርግ ዘመን የነበረው ሽግግር አብዛኛውን ኢትዮጵያዊ ያላሳተፈና በወታደራዊ መኮንኖች ብቻ የተመራ ሽግግር ነበር። ከደርግ ወደ ኢህአዴግ የተደረገው ሽግግርም ከዋና ዋናዎቹ የህወሓት ሰዎች ውጭ አብዛኛውን ኢትዮጵያዊ የፖለቲካና የሲቪክ ባለድርሻ ያገለለ ነበር።  በ2010 ዓም የተጀመረውና በጠሚ አቢይ አህመድ የተመራው ሦስተኛው ሽግግርም አቃፊና አካታች ነኝ ብሎ ቢጀምርም፣ በሂደት በግልፅ እንደታየው ግን ሽግግሩ በቃልም በተግባርም የአንድን ብሔር የበላይነት ያረጋገጠ ሽግግር ነው። አራተኛውና ምናልባትም በታሪካችን የመጨረሻው መሆን አለበት የምንለውና ፊት ለፊታችን ላይ የሚጠብቀን ሽግግር ግን፣ አካታችነቱ፣ አቃፊነቱና ህዝባዊነቱ ሽግግሩ ከተጀመረ በኋላ ሳይሆን ገና ሳይጀመር መረጋገጥ ይኖርበታል። አራተኛው ሽግግር ሁሉንም የኢትዮጵያ ባለድርሻ ማቀፍ ያለበት አራት ኪሎ ከገባ በኋላ ሳይሆን፣ አራት ኪሎ ለመግባት መሆን አለበት።

አገራችን ኢትዮጵያ ዛሬ ከምትገኝበት በሙስና የተጨማለቀና ትኩረቱ ክቡር የሆነው የሰው ህይወት ሳይሆን የከተማ ውበት የሆነ ነብሰ በላ ሥርዓት ተላቅቃ ዲሞክራሲያዊ ሽግግር ማድረግ አለባት። ይህ ዲሞክራሲያዊ ሽግግር በፍጥነት እንዲጀመርና፣ ከዚህ ቀደም ከነበሩት ሦስት የሽግግር ሂደቶች ፍጹም በተለየ መንገድ ተጀምሮ እንዲያልቅ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ ማድረግ አለበት። ይህ እንዲሆን የዚህ ጽሁፍ ጽሐፊ “ኑ አገራችንን እናድን”፣ “ኑ ኢትዮጵያን እናድን” እያለ ለፖለቲካ ፓርቲዎች፣ለሲቪክ ማህበራት፣ ለምሁሩ፣ለልህቃኑ፣ ለሴቶች፣ለወጣቶች፣ለከተማ ነዋሪው፣ለገበሬውና ለሠራተኛው ክፍል የአደራ ጥሪውን  ያስተላለፋል!!!

 

2 Comments

  1. ወንድም ኢፍሬም፦
    ጥሩ ትምሕርት እየሰጠኸን ነው። ልብ ያለው ልብ ይበል! የትም ቦታ ሆነን መመኪያችንና መኩሪያችን ኢትዮጵያ ናት ። ኢትዮጵያን በጋራ ጠብቀን፣ በዘር፣ በሃይማኖት፣ በመንደር ሳንከፋፈል አቆይተን ለተከታይ ትውልድ ማስተላለፍ ግዴታችን ነው። ለምሣሌ፣ አርሲን፣ ጎጃምን ወይም ትግራይን ነጻ የማውጣት ቅዠት እንኳን ለክብር ሊያበቃ፣ ለቡና ቤት ወሬም አይሆንም። ክብራችን ኢትዮጵያ ናት ። በጥንቃቄ ከወንበዴም፣ ከቅጠረኛም፣ ከባንዳም፣ ከነጋዴ ካድሬም እንጠብቃት !

    ራሳችን ባለፉት ዓመታተ ገዝግዘን ገዝግዘን አወረድናት እንጂ፣ ከ 50 ዓመት በፊትማ አውሮጳና አሜሪካ የሚሄድ ኢትዮጵያዊ ቪዛም አያስልገውም ነበር። ኢትዮጵያዊነትና ፓስፖርት በቂ ነበር። መሪዎቻችንም ዘመናዊ የፖለቲካ ቋንቋና ጥቅስ ባያዘወትሩም፣ ሕዝብንና እግዚአብሔርን ማክበሩን ያውቁበት ነበር። የጎደላቸው ዘመናው የፖለቲካ ሥርዓት ምሥረታው ሆኖ ሳለ፣ ለትምሕርት የተላኩ ጥሬ ወጣቶቹ ከያገሩ ወረሩንና ላይሳካላቸው አድናግረውን ለተከታታይ የአውሬ ሥርዓት አስረከቡን። የአውሬ ሥርዓቶችም፣ ሰው ማስተዳደር ስላልፈጠረባቸው፣ በከፍተኛ መስዋዕት የተሰባሰበ አገር አስገንጥለው ወደብ አልባም አደረጉን፣ ሰላምም አሳጡን። ልጅ ያቦካው ለእራት አይበቃም ይባል የለ !

  2. በእኔ እምነት የሚድን ሃገር ወይም ህዝብ የለም ባይ ነኝ። ላስረዳ። እውቁ ኢትዪጵያዊ አቶ አሰፋ ጫቦ አንድ ሥፍራ ላይ እንዲህ ብለው ነበር “የማይመጣን ነገር መጠበቅ የማይሰለቸው ህዝብ”። ይህ ህዝብ እኛ ነን። ታሪካችን ይህኑ የግርግርና የወረፋ መገዳደልን አመላካች ለመሆኑ ብዙም ሳንርቅ ያለፉትን 50 ዓመታት ብቻ መመልከት ይበቃል። ችግሩ ከሥር ከመሰረቱ ነው። ከልጅነት እስከ መቃብር የሚያንገላታ በሽታ! ሌላው እውቅ የአየር ሃይል አብራሪ ጄ/ለገሰ ተፈራ ወልደስላሴ ለሃገር አንድነት ተፋልመው በጠላት እጅ ወድቀው ከ11 ዓመት የመከራ የሶማሊያ እስራት በህዋላ ተለቀው ኖሩ ተብለው ካረፉ በህዋላ የመቃብር ቦታ እስከ መከልከል ተደርሷል። ስንቶቹ ናቸው ሳይኖሩ ወይም ሌላውን ሲያኖሩ የኖሩ? ስንቶች ናቸው ለእናት ሃገር ተብለው በየሜዳው ወድቀው የቀሩት? ስንቶች ናቸው ዛሬ የዚያ አስፈሪ ሰራዊት አባላት የነበሩ ተበትነው በልመናና ባለባሌ ቦታ የቀረ እድሜአቸውን የሚገፉት? የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ ይሉሃል ይሄ ነው!
    ሌላው ምሳሌ ደ/ዘይት የነበረውን “የጀግኖች አንባ” ወያኔ ሲንደው እነዚያ በየጦር ግንባሩ ደማቸው ፈሶ አካላቸው ጎድሎ ሲረድ የነበሩትን የበተነው በብሄሩ የሰከረው ወያኔ ዛሬ ላይ ያለፈውን ተግባሩን ልብ ብሎ ቢፈትሽ ምን ይሰማው ይሆን? መልሱ ምንም ነው። ሃገር ቆርሶ የሚሰጥ፤ ታሪክ የሚከልስ፤ ለዚያውም ከታሪካዊቱ አድዋ ምንጫቸው የሆኑ የፓለቲካ ቁማርተኞች ይኸው አሁንም ገና የሃገሪቱ ችግር ከመሆን አልተገቱም።
    ያ ትውልድም “ኢትዮጵያን እናድን” የዙፋኑን መንግስት ተጋፍቶ መሬት ለአራሹ መፈክርን አንግቦ ተፋለመ፤ ተጋዘ፤ ሞተ፤ ተሰደደ። ዛሬ ላይ ምሬት ለአራሹ ሳይሆን ለባለጸጋ ሆኖአል። ሰው የሚበላው ጠፍቶ ጾሙን የሚያድርበት ጊዜ እንደአሁኑ ያለ ጊዜ በጣሊያን ወረራም አልተከሰተም። የኢትዮጵያ ችግር ውስብስብና ጭራሽ መፈወስ የማይችል ደዌ ነው። በዚህ ላይ የክልልና የቋንቋን ፓለቲካ ስትደርብበት ጭራሽ ድቅድቅ ጨለማ ነው። ኢትዪጵያ ለምትባል ሃገር ብዙዎች ቃትተዋል። በዚህም በዚያም በጊዜው በነበሩ መንግስታት ደማቸው ፈሷል፤ ቤተሰቦቻቸው ተበትነዋል፤ የተረፉትም በዓለም ዙሪያ ተሰደው አሁን ተራ በተራ ወደማይቀረው ዓለም በመሰናበት ላይ ናቸው። አሁንም ለዚህች ሃገር እንቅልፍና ሰላም አጥተው ሌት ተቀን የሚያስቡ ለመኖራቸው ጥርጥር የለውም። ግን ፓለቲካችን ውሃ ወቀጣ የሚሆነው እኛ የሚለውን እኔ በሚለው ስለተተካ ነው። የእኔ ክልል፤ ያንተ መኖሪያ፤ የአማራ ህዝብ ነጻ አውጭ፤ የኦሮሞ፤ ወዘተ ማለት የድንጋይ ዘመን እሳቤ እንጂ በ 21ኛ ክፍለ ዘመን ከቁጥር የሚገባ አይደለም። ሃገር ማለት ማንም የምድሪቱ ሰው በህግና በደንቡ ከየትኛውም የሃገሪቱ ክፍል በነጻነት ተንቀሳቅሶ ሰርቶ የመኖር መብት ሲኖረው ነው። ሰው ማሳ እንደበሉ ከብቶች እያገቱ ገንዘብ የሚጠየቅባት፤ በጠራራ ጸሃይ ሰው ታፍኖ የሚሰወርባት፤ ሥራና ትምህርት በዘርና በቋንቋ በሚተመንባት ምድር ላይ እኩል ሆኖ እኩልነትን ማስፈን ሃገርን ማዳን አይቻልም።
    ታዲያ ነገር ሁሉ እንዲህ ጨለማ ከሆነ መፍትሄው ምንድን ነው ለሚሉ መፍትሄው ዝም ነው። ሰውን ሰው ሲበላው እያዪ እንደ እሳት ራት እየገቡ መማገድ ለራስም ቢሆን ለሃገር አይጠቅምም። በዚህም በዚያም የቃል ኪዳን ሃገር፤ እጆቿን ወደ ፈጣሪ ታነሳለች ገለ መሌ መባሉ ሁሉ በህዝቡ መካከል ሲፈተሽ የማይገኝ ጉዳይ ነው። ፓለቲካን መጠየፍ አማራጭ የማይገኝለት መድሃኒት ነው። የአንድ ዘፈን ስንኝ ትዝ አለኝ። ልዋስና ይብቃኝ።
    እንዲህም እንዲህም እንዲህም አረገኝ
    ያለ መተው በቀር መድሃኒት አይገኝ።
    ስንቶች ለሃገር ለወገን ልዕልና በጎ ነገርን ተመኝተው በግፈኞችና በነገረ ሰሪዎች እጅ አፈር ተመለሰባቸው? የዛሬውስ ካለፈው የወያኔ ዘመን የሚለየው የቱ ላይ ነው? የሽግግር መንግስት መባሉስ መቼ የበፊቱ ታሪካችን አሻግሮን ያውቃል። እውነተኛ ኢትዮጵያዊ ራስን ፈትሾ፤ ታሪክን መርምሮ፤ ለምን እንዴት ብሎ ቢጠይቅ መልሱ ከልጅነት እስከ ሽምግልና ችግር ያለበትን ሃገርና ህዝብ ተግባርና ቃል ለማግኘት ይችላል። ዶሮ እዚህ ቅዝምዝም ወዲያ አይነት። በቃኝ!

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Fano
Previous Story

ኣንድ የፋኖ ድርጅት ወይንስ ኣንድ የፋኖ መሪ? ኣንድ መሆን ለምን ኣቃታን ዘመነ ካሴ?

191421
Next Story

የሽግግር ፍኖተ ካርታ – በገለታው ዘለቀ

Go toTop