May 12, 2024
ጠገናው ጎሹ
በሁለቱ የኢህአዴግ እኩያን አንጃዎች (በፈጣሪው ህወሃት እና የእርሱ ፍጡርና ፍፁም አሽከር በነበረው ኦህዴድ/ብልፅግና) መካከል በተፈጠረ የበላይነቱ (የጠርናፊነቱ) ሥልጣነ ዙፋን “የይገባኛልና የአይገባህም” ውዝግብ ምክንያት እጅግ አስከፊ የሆነ አገራዊ ጉዳት ካደረሱ በኋላ አንዱ ሌላውን አሽንፎ ሊቀጥል እንደማይችል ሲገነዘቡ እና የዓለም ማህበረሰብን ተፅዕኖ በቀላሉ ማለፍ እንደማይቻላቸው ሲረዱ በሦስተኛ ወገን አቀራራቢነትና ጫና ፈጣሪነት “የፕሪቶሪያና የናይሮቢ የሰላም ስምምነት” እየተባለ በሚጠራው የስምምነት ሰነድ ላይ ተፈራርመዋል።
በመሠረተ ሃሳብ ብቻ ሳይሆን ለአገር (ለህዝብ) ካላቸውና ሊኖራቸው ከሚችለው ጠቀሜታ አንፃር እንዲህ አይነት እጅግ አስከፊ የሆኑ ፖለቲካ ወለድ ጦርነቶች ሲሆን እንዳይጀመሩ የማድረግን ፣ ካልሆነም ቢያንስ ብዙ ውድመት ሳያስከትሉ እንዲቆሙ የማድረግን እና ይህ ካልሆነ ደግሞ ከመሪር ተሞክሮ በኋላም ቢሆን ትርጉም በሚሰጥ ፀፀት፣ ቁርጠኝነት፣ የህዝብ አሳታፊነት እና አስተማማኝ ዘላቂነት ባለው የድርድርና የስምምነት አግባብ የማስቆምን አስፈላጊነት የማይረዳና የማይፈልግ እውነተኛ ነፃነት፣ ፍትህ፣ እኩልነት፣ መከባበር፣ ሰላምና የጋራ እድገት ፈላጊ የአገሬ ሰው የሚኖር አይመስለኝም።
ገዥዎቻችንም ሲሆን ይህንን እውን ለማስደረግ የሚያስችል ፖለቲካዊና ሞራላዊ ተፈጥሮ፣ ባህሪና ተሞክሮ ያላቸው ቢሆኑ ኖሮ እና እኛም ዘመን ጠገቡንና አስከፊውን ፖለቲካ ወለድ የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማራቸውን አስወግደን መሠረታዊ የሥርዓት ለውጥ እውን ከማድረግ ይልቅ በባዶ የቃላት ዲስኩር በተቃኘውና በተለወሰው የሸፍጥ፣ የሴራና የጭካኔ ፕሮፓጋንዳቸው ተሽመድምደን ባንወድቅ ኖሮ ምንኛ በታደልን ነበር።ግን አልሆነም።
ለዚህም ነው ሁለቱ አንጃዎች (የአራት ኪሎውና የመቀሌው) አያሌ ሚሊዮኖችን ከገደሉና ካገዳደሉ፣ እጅግ አያሌ ሚሊዮኖችን መግለፅ ለሚያስቸግር የቁም ፍዳ (ሰቆቃ) ከዳረጉ እና በአጠቃላይ አገርን ምድረ ሲኦል ካደረጉ በኋላ ቢያንስ ለሆነው ሁሉ እናዝናለን የሚል መሠረታዊ የሰብአዊነት ድምፅ እንኳ ሳያሰሙ የፕሪቶሪያና የናይሮቢ ስምምነት ተፈራርመው በመተቃቀፍና የችርስ ብርጭቆ እያጋጩ ከደሙ ንፁህ እንደሆኑ አድርገው የተሳለቁብን።
የዚህ የሸፍጥና የሴራ ስምምነታቸው ሰለባ ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ የወልቃይትና የራያ ጉዳይ ነው። ጥያቄው ለምን? በማን? ለማን? እንዴት? ከየት ወደ የት? የሚል እንጅ የድርድርንና የስምምነትን መሠረታዊ ጠቀሜታ የመካድ ወይም የማጣጣል ጉዳይ አይደለም። እንኳንስ ከአጎራባች ትግራይ ከየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል በመሄድ ሠርቶና ተከባብሮ ይኖርባቸው የነበሩትንና ለረጅም ዘመናት በአማራ ሥር ሲስተዳደሩ የነበሩትን ወልቃይትንና ራያን በጉልበት ከተቆጣጠሩ በኋላ ወደ ህገ መንግሥትነት በተለወጠ ርካሽና አደገኛ የፖለቲካ ፕሮግራማቸው” ከዛሬ ጀምሮ ምእራብ ትግራይና ደቡብ ትግራይ ሆነዋልና ይህንን የማይቀበል ወይም የሚቃወም ወዮሎት” በሚል ንፁሃንን ለግፍ አሟሟትና ለቁም ሰቆቃ መዳረግ ፈፅሞ ይቅርታ የሌለው ትውልዳዊ ወንጀል መሆኑን ለመረዳት ብዙና ጥልቅ የሆነ ጥናትን አይጠይቅም። ይህ ደግሞ ከትግራይ የተገኙና እድሜ ጠገብ የሆኑ እውነተኛ ኢትዮጵያዊያንን ምስክርነትንም ይጨምራል።
እርግጥ ነው የሃሰት ትርክት እየፈበረኩ አማራንና የአማራ የሆነውን ሁሉ እጅግ አደገኛ በሆነ የሸውራራነት አመለካከት መርዝ እየበከሉ ያሳደጉትን የእነርሱ ዘመን ወጣት ትውልድ ወደ እውነተኛው የጋራ መግባባትና የእድገት ጉዞ መስመር ማምጣት ቀላል አይሆንም። በእኩያን የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ መሃንዲሶችና ጠርናፊዎች ሥርዓት ከርሰ መቃብር ላይ እውነተኛ ነፃነት፣ ፍትህ፣ እኩልነት፣ መተሳሰብ፣ ፍቅር፣ ሰላምና የጋራ እድገት የሚረጋገጥባት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን እውን ማድረግ ካለብን ይህ ትውልድ እኩያን ገዥ ቡድኖች ካስለከፉት የጎሰኝነት፣ የመንደርተኝነት ፣ የደምና የአጥንት ስሌት ፖለቲካ ማንነት ይላቀቅ ዘንድ እልህ አስጭራሽ ጥረትና ትግል የግድ ነው።
ማንም ነፃ አውጭ ነኝ ባይ ጊዜና ሁኔታውን እየተጠቀመ መሬትን ብቻ ሳይሆን መሠረታዊውን የማንነት መብት በጉልበት እየደፈጠጠ እና ሽፍትነቱንና ዘራፊነቱን በህጋዊ ሰነድ ስም ህጋዊ እያስመሰለ የሚኖርበት አገር የአናርኪስቶችና የአደገኛ ቀማርተኞች ምድር እንጅ ትክክለኛ የአገር ምንነትና እንዴትነት ትርጉም አይኖረውም። በተጠና የፖለቲካ ስትራቴጂ ጨቋኝ፣ ነፍጠኛና ትምክህተኛ የሚል እጅግ አስቀያሚና አደገኛ የፖለቲ ትርክት ዒላማቸው ያደረጉትን የአማራን ማህበረሰብ ከገዛ ርስቱና ቀየው ከማፈናቀልና ለከፋ ስቃይና መከራ ከመዳረግ አልፈው በመግደል/በመጨፍጨፍ የተቆጣጠሩትን መሬት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ወደ ቀድሞው የምእራብ ትግራይና የደቡብ ትግራይ ይዞታ (status qua ante) ካልተመለሰ በሚል ያዙንና ልቀቁን ሲሉ መታዘብ ባይገርምም ለዚህ አይነት ቅዠታቸው ግን ተገቢ ምላሽ የግድ ነው።
ከህገ መንግሥት ተብያቸው በፊት ጊዜና ሁኔታውን ተጠቅመው ሸፍጥን፧ ሴራንና ጉልበትን ባቀናጀ ሁኔታ ወደ ትግራይ የጠቀለሉት የአማራ መሬትና ማንነት አራት ኪሎ በገቡ በ4ኛው ዓመት አገዛዛቸው (1987 ዓም) በሴራና በሸፍጥ ወደ ህገ መንግሥትነት በለወጡት የፖለቲካ ፕሮግራማቸው የሚዳኝበት ወይም ትክክለኛ መፍትሄ የሚያገኝበት አንዳችም አሳማኝ ምክንያት ባለመኖሩ ነገሮች ቀድሞ ወደ ነበሩበት ይመለሱ( status qua ante) የሚለው ፈፅሞ ተቀባይነት አይኖረውም። በማንነቱ ምክንያት በገዛ ባድማው ላይ እንዳይኖር መደረግ ብቻ ሳይሆን የህወሃት/ኢህአዴግ የግፍ ግድያና የቁም ሰቆቃ ሰለባ በመሆን አያሌ ዓመታት ባስቆጠረው ማህበረሰብ ላይም መሳለቅ ነው የሚሆነው።
በረጅሙ የነፃ አውጭነትና በአራት ኪሎው አገዛዛቸው ወቅት በዚያ መከረኛ ማህበረሰብ (ወልቃይትና ራያ) እና በአጠቃላይ በአገር ላይ በፈፀሙት ፖለቲካ ወለድ ወንጀል የጨቀየው ህሊናቸውና ፖለቲካዊ ማንነታቸው በእንዲህ አይነት እጅግ አስከፊና አደገኛ ፖለቲካዊ ስላቅ እንዲቀጥል ሊፈቀድለት አይገባም።
በእውነት ስለ እውነት ከተነጋገርን ለተፈፀመው ዘመን ጠገብና በእጅጉ አስከፊና ሁለንተናዊ ለሆነ መከራና ውርደት ዋነኛው ምክንያት ሥርዓተ ፖለቲካው ነው። አግባብነት ባለው የሽግግር ፍትህ አማካኝነት ዲሞክራሲያዊ የሽግግር መንግሥት እውን ለማድረግ እስካልቻልን ድረስ የወልቃይትና የራያ ጉዳይ ትክክለኛ መፍትሄ ያገኛል ብሎ እንኳንስ ማመን ማሰብም ፈፅሞ አይቻልም ። “በህገ መንግሥቱ መሠረት” የሚባለውና እኛም ልማድ ሆኖብን እንደ በቀቀን መልሰን የምናስተጋባው የፖለቲካ መነባንብ በሥርዓቱ አስከፊ አዙሪት ውስጥ እየጓጎጥን ተአምር እንፈጥራለን የሚል አይነት እጅግ አሳፋሪና አስፈሪ የፖለቲካ አስተሳሰብ ነው። ከዚህ አይነት አስቀያሚ ወለፈንዲነት ካልተላቀቅን በስተቀር የምንፈታው ችግርና እውን የምናደርገው ፍኖተ ዴሞክራሲ አይኖርም። የወልቃይትና የወራያ ጉዳይም እንዲሁ። በዘመናት ፖለቲካ ወለድ ወንጀል ህሊናወቻቸውና እጆቻቸው የበሰበሱና የከረፉ እኩያን ገዥዎች በሚያስቀምጡት ቅድመ ሁኔታና በሚዘውሩት አውድ (መድረክ) ሥር ሆኖ እንኳንስ ውስብስብነት ያላቸውን ሌሎች ጉዳዮች እንደ ወልቃይትና ራያ የመሰሉ ግልፅና ግልፅ የመሬትና የማንነት ጥያቄዎችን በአግባቡ ለመመለስ ፍፅሞ አይቻለንም።
እናም በአማራ ፋኖዎችና በሌሎች ነፃነትና ፍትህ ወዳድ ወገኖች ተባባሪነት በመካሄድ ላይ ያለው በመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ለውጥ ለሁሉም ዜጎቿ የምትመች ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን እውን የማድረግ ተጋድሎ ዓላማውን፣ መርሁን፣ አቅጣጫውን፣ ዒላማውንና ግቡን ጠብቆ ለድል እንዲበቃ ገንቢነት ባለው ሂሳዊ ድጋፍ ማጎልበት የወቅቱ አንገብጋቢ ጉዳይ መሆን ያለበት። በሽተኛ ሥርዓት በጤነኛ ሥርዓት ሲተካ የወልቃይትና የራያ ጉዳይም በወንድማማቾችና እህትማማቾች ምክክርና ድርድር አስተማማኝና ዘላቂ መፍትሄ የሚያገኝ ይሆናል።