መግለጫ ተብያችሁ የሚነግረን የትውልድ ገዳይ ሥርዓታችሁ ፍፃሜ መቃረቡን ነው!

April 28, 2024
ጠገናው ጎሹ

ባለፈው ሳምንት (እ.ኤ.አ በ4/24/24) በአብይ አህመድና በግብረ በላዎቹ ተፅፎና ተዘጋጅቶ በብሔራዊ መረጃና ደህንነት ተብየው ስም የተነበበውን በንፁሃን ደምና የቁም ሰቆቃ ላይ ማላገጫ የሆነውን ድርሰት (መግለጫ ተብየ) እልህ አስጨራሽ በሆነና በተደባለቀ ስሜት አደመጥኩት።

አዎ! ለሩብ ምዕተ ዓመት ከዘለቀው፣ ከስድስት ዓመታት ወዲህ ደግሞ የዚያው ሥርዓት ውላጆች በሆኑ ተረኞች  ፈፅሞ ለመግለፅ በሚያስቸግር ሁኔታ ከቀጠለው እና አገርን ምድረ ሲኦል እያደረገ ካለው  እጅግ ግዙፍና መሪር እውነታ ጋር ፈፅሞ የሚላተም መሆኑ ከበቂ በላይ  ግልፅ የሆነውን የማላገጫ ድርሰት (መግለጫ ተብ) አድምጦ ወይም አንብቦ ለመጨረስ  ትእግሥትን በእጅጉ ይፈታተናል

ድብልቅ ስሜትን የሚፈጥሩት ሁኔታዎች ደግሞ  ሀ) በአንድ በኩል በፋኖነት ጥላ ስር በመሰባሰብ  ፣መምከርና በመመካከር  ፣ በመሠረታዊና ወሳኝ የታሪክ ጥሪዎች ላይ በመስማማት ፣በፅዕኑ ቃል ኪዳን በመተሳሰር ራሳቸውን በማሰልጠንና በማዘጋጀት  በየትግል ምዕራፉ ከሚገኙ ጥንካሬዎችና ድክመቶች በመማርና በመማማር ፣ ነፃነት፣ ፍትህ ፣ እኩልነት፣ ሰላምና የጋራ እድገት እውን የሚሆንባት ኢትዮጵያን ለማየት ከሚፈልጉ ወገኖች ጋር  በመመካከርና በመተባበር  እያካሄዱት ያሉት እልህ አስጨራሽ ተጋድሎ የሚፈጥረው የተስፋና የደስታ ስሜት እና  ለ) በሌላ በኩል ግን በእኩያን ገዥ ቡድኖች  ርካሽ የፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ  መዘናጋት የሽንፈት መንገድ መሆኑን አውቆ  የእኩያን ገዥዎችን የጭካኔ ሰይፍ  ፈርቶ ከመከራና ከውርደት ጋር መኖር እንደ መኖር  የማይቆጠር መሆኑን ከምር ተገንዝቦ  መሠረታዊ የነፃነትና የፍትህ ሥርዓትን እውን ማድረግ የሚቻለው ከክስተቶች የትኩሳት መጠን ጋር በመሞቅና በመቀዝቀዝ ሳይሆን በፅዕኑና ዘላቂ የጋራ ተጋድሎ የመሆኑን መሪር ሃቅ ከዘመን ጠገቡ መከራና ውርደት ተሞክሮ ተምሮ  የሃይማኖታዊ እምነት መሠረታዊ ምንነት፣ ለምንነትና እንዴትነት ከረቂቅ የማሰቢያ አእምሮና ከብቁ የማከናወኛ አካል ጋር የተፈጠሩበትን ዓላማ ከፈጣሪ እገዛ ጋር ተግባራዊ አድርጎ የመገኘት እና መልካምና ስኬታማ የትውልድ ሰንሰለትን ለማስቀጠል የመቻል ግዙፍና ጥልቅ እሴትነት  እንጅ ድርጊት አልባ እግዚኦታ፣ ምህላ፣ ፆም፣ ፀሎት፣ ዝማሬ፣ ቅኔ መወድስ፣ ቅዳሴ፣ መነባንብ፣ ወዘተ ብቻ አለመሆኑን ተረድቶ  እና የሃዘንና የቁጣ ስሜቱ የእኔ ነው የሚለው ጎሳ/ነገድ ወይም የጎሳ/የነገድ አባል  ሲጠቃ ወይም የተጠቃ ሲመስለው ብቻ ሳይሆን ከአንድ አገር ልጅነትም አልፎ ማነኛውም ንፁህ ሰብአዊ ፍጡር ሲጠቃ ሌላው ቢቀር የተቃውሞ ድምፁን ለማሰማት ሞራላዊ ሰብእናው የሚያስገድደው መሆኑን አምኖና ተቀብሎ የተሻለ ነገንና በጣም የተሻለ ከነገ ወዲያን እውን ለማድረግ የሚችልና የሚያስችል ህዝባዊ ሃይል ለመፍጠር በሚያስችል አቅጣጫና ግሥጋሴ ላይ ነን ወይ? የሚለው ጥያቄ እጅግ ፈታኝ የመሆኑ እውነታ ነው ድብልቅ ስሜትን የሚፈጥረው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር በርዕዮት ጉዳይ ያልተጠየቀውን መለሰ

ዘመን ጠገብ የሆነውንና አሁንም  የዚያው ሥርዓት ውላጆችና ተረኞች በሆኑ ገዥ ቡድኖች ለመግለፅ በሚያስቸግር ሁኔታ የቀጠለውን ፖለቲካ ወለድ መከራና ውርደት በመስማት ወይም በማየት ሳይሆን በመኖር ወይም ሰለባ በመሆን ከበቂ በላይ የሚያውቀውን መከረኛ ህዝብ ግዙፍና መሪር የሆነውን እውነታ በአፍ ጢሙ የሚደፋ ድርሰት አዘጋጅተው “ሃቀኝነታችንና የበጎ ታሪክ ሠሪነታችንን አምነህ ካልተቀበልክና የነፃነትና የፍትህ ትግል የምትለውን ነገር  እርግፍ አድርገህ በመተው ይቅርታችን እየጠየቅህና እየተቀበልክ በመደመር የውርደት ፍርፋሪ ተጠቃሚ ሁን” ሲሉት መታዘብ የሚያሳድረውን የህሊና ፈተና በቃላት ለመግለፅ የሚቻል አይመስለኝም።

በአንፃራነት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትና ሥልጣኔ መሠረት የተጣለባቸው አገራት የመኖራቸው እውነታ እንደ ተጠበቀ ሆኖ ዓለማችን በቤተሰብ ወይም በቡድን ወይም በፖለቲካ ድርጅት ስም በመተሳሰርና ሥልጣነ መንግሥትን በመቆጣጠር  ልክ የሌለው ፍላጎታቸውንና ጥቅማቸውን የአገር (የህዝብ) ፍላጎት ፣ ልዑላዊነት እና እድገት  በሚያስመስሉ የሴራና የሸፍጥ  ህጎች፣  ድንጋጌዎች ፣መመሪያዎች፣ ትርክቶች፣ አዋጆች ፣ ድርስቶች ፣ መግለጫዎች/ማላገጫዎች ፣ ወዘተ እያጀቡ ህዝብ የመከራና የሰቆቃ ህይወት (ህይወት ከተባለ) ሰለባ ያደረጉና የሚያደርጉ ገዥ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች አውድ (መድረክ) የመሆኗን ግዙፍና መሪር እውነታ ማስተባበልና መሸሽ የሚቻል አይመስለኝም።

ለዚህ አይነት እጅግ አስቀያሚ የሸፍጥ፣ የሴራ፣ የብልግና፣ የእኩይ፣ ወዘተ የፖለቲካ አስተሳሰብና አካሄድ ማሳያነት (ምሳሌነት) ደግሞ  የእኛው ክፍለ ዓለም ከሆነው አህጉረ አፍሪካ የተሻለ የለም።

መጠኑና አይነቱ ከአገር አገር ሊለያይ ቢችልም አፍሪካዊያን ከባዕዳን የቅኝ ገዥዎች አገዛዝ ነፃ ወጣን በሚል የተሰማቸውን እፎይታ በቅጡ ለማጣጣም እንኳ ሳይችሉ በአገር ባለቤትነት ነፃነትና ልዑላዊነት ወርቃማ እሴት ስም እየማሉና እየተገዘቱ ሥልጣናቸውን ከተቻለ በማታለል እና ካልሆነ ደግሞ በሚታይና በማይታይ ጨካኝ ሰይፋቸው በሚያስጠብቁ ሴረኛ፣ ሸፍጠኛ፣ ጨቋኝ፣ ዘራፊ (በዝባዥ) እና ሙሰኛ  የገዛ ወገኖቻቸው የአገዛዝ ቀንበር ሥር በመውደቃቸው ምክንያት በአንፃራዊነት የዴሞክራሲያዊ ሥርዓተ ፖለቲካና የመልካም መስተዳድር ውጤቶች ተጠቃሚ የሆነው የዓለም ክፍል  የተመፅዋችነት ውርደት ለመላቀቅ አልተሳካላቸውም።

ብዙውን ጊዜ በአንፃራዊነት (ከክፈለ አህጉሩ ሁለንተናዊ ፈተናዎች አኳያ)  በዴሞክራሲና በተረጋጋ አገርነት የምንጠቅሳቸውን አገራት ከራሳችን እጅግ ዘመን ጠገብና አስከፊ ሆኖ ከቀጠለው የጎሳ ደምና አጥንት ስሌት ፖለቲካ ወለድ መከራና ውርደት አኳያ እያየናቸው ነው እንጅ  ከእውነተኛ የዴሞክራሲዊ ሥርዓት ( የሰብአዊ መብት፣ የነፃነት፣ የፍትህ፣ የእኩልነት፣ የዜጎች ህይወት ስኬት፣ ወዘተ) አንፃር ከምር ስንመረምረው የተባለውንና የሚባለውን ያህል የእውነት ሆነው አናገኛቸውም።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የአርባምንጭ ቅስቀሳ በከፊል

የእኛ ፖለቲካ ወለድ ቀውስና አወዳደቅ ግን እጅግ አስከፊና አንገት አስደፊ ነው። ለቅኝ ገዥዎች የአገዛዝ ቀንበር ካለመንበርከካችን አልፎ የቀንበሩ ሰለባ ለሆኑ ህዝቦች ሁሉ የነፃነት ትግላቸው አርአያና ድጋፍ ሰጭዎች  ከሆንበት ከረጅሙና ድንቅ ታሪካችን አንፃር ራሳችንን ስንገመግመው በአሁኑ ዘመን የወረድንበትና አሁንም ገና ማቆሚያ ያላገኘንለት የቀውስ፣ የውድቀትና የውርደት ቁልቁለት በእጅጉ አስከፊና አስፈሪ ነው።

እጅግ አስከፊና አደገኛ የሆነ ሁለንተናዊ አገራዊ የቀውስና የውድቀት ቁልቁለትና አዙሪት ሰለባዎች የሆነው ከዛሬ ሶስት አሥርተ ዓመታት በፊት  በወታደራዊው አምባገነን አገዛዝ ከመማረሩ የተነሳ “ከዚህ የተሻለ እንጅ የባሰ አይመጣም”  በሚል እጅግ አሳዛኝ የድንቁርና እና የተሸናፊነት ስሜት ተጠቂ የሆነውን ህዝብ ተጠቅመው በምትኩ እጅግ አደገኛ የሆነውን በጎሳና በቋንቋ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ላይ የተመሠረተውን የመለያየት፣ የጥላቻ፣ የመጠላለፍ፣ ያለመታመን፣ ያለመተማመን፣ በክልሌ አትድረሱብኝ ባይነት እና የመጠፋፋት የፖለቲካ ፕሮግራማቸውን  በእነርሱ መቃብር ላይ ካልሆነ በስተቀር በቀላሉ ትርጉም ያለው መሻሻል ወይም ለውጥ እንዳይደረግበት  አድርገው በህገ መንግሥት ደረጃ አዋጅ ያወጁ እለት ነበር።

የኸውና ከስድስት ዓመታት ወዲህ ደግሞ ያንኑ ህገ መንግሥት ተብየ የፈላጭነትና የቆራጭነት ሥልጣነ መንበራቸውን የማይጋፋ መናኛ ማሻሻያ ከማድረግ አልፎ ከመቃብር በላይ እያሉ ትርጉም ያለው ማሻሻያ ወይም ለውጥ ለማድረግ እንደማይፈቅዱ ቁርጡን የነገሩን ሸፍጠኛና ጨካኝ ተረኛ ገዥ ቡድኖች ናቸው  በፖለቲካዊና በሃይማኖታዊ ማንነት ምክንያት የመጠቃቱ እውነታ እንደተጠበቀ ሆኖ በተለይ ግን በጎሳ/በብሔረሰብ ማንነት ላይ ዒላማ ያደረገ ሰቆቃዊ ጭፍጨፋን ፣ መሳደድን፣ መፈናቀልን፣ ርሃብን ፣ እርዛትን፣ ጥማትን፣ በሽታን፣ አካለ ጎደሎነትን ፣ የሥነ ልቦና ቀውስን ፣ ወዘተ ተሰምቶና ታይቶ በማይታወቅ አኳኋን ያስኬዱትና እያስኬዱት ያሉት።

በእጅጉ አስከፊውና አስደንጋጩ ነገር ደግሞ የመከራውና የሰቆቃው ቀጥተኛ ሰለባ ከሆኑ መከረኛ  የኢትዮጵያ ህዝብ አልፎ ዓለም ሁሉ ያወቀውንና የሚያውቀውን የፖለቲካ ሥርዓት አሰቃቂ ወንጀል እንኳንስ አምነው በመቀበል አስፈላጊውን እርምት ሊያደርጉ የተለመደውንና አሰልችውን “የአፈፃፀም ስህተት ወይም ድክመት” ዲስኩር ተጠቅመው ይቅርታ የሚል ቃል ፈፅሞ ያልወጣቸውና የማየወጣቸው የመሆናቸው ጉዳይ ነው።

በዚህ በሰሞኑ የብሔራዊ ደህነትና መረጃ በሚሉት  (የንፁሃን ጥላ ወጊ በሆነና በንፁሃን ደምና ሰቆቃ በሚሳለቅ) ተቋማቸው አማካኝነት  አስረግጠው የነገሩንና ወዮላችሁ ያሉን ይህንኑ በወንጀል የበሰበሰውንና የከረፋውን የፖለቲካ ሰብእናቸውንና ማንነታቸውን ለማስቀጠል ካላቸው ከንቱ ቅዠት መሆኑን ለመረዳት አያስቸግርም።

ተጨማሪ ያንብቡ:  “ቤቲ አዋረደችን!” ከያሬድ አይቼህ

ለዚህም ነው፦

·         የሰላማዊና የዴሞክራሲያዊ የሥልጣን ሽግግር አኩሪ የፖለቲ ባህል ባለቤቶች እንደሆኑ ሊሰብኩን ሲሞክሩ ፣

 

·         ከ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በባሰና ለመግለፅ በሚያስቸግር ሁኔታ  አገርን ምድረ ሲኦል ያደረጉበትንና እያደረጉበት ያሉትን  ፖለቲካ ወለድ ወንጀል በፅዕናት የሚቃወሙትንና የሚታገሉትን ወገኖች በ18ኛው ክፍለ ዘመን አስተሳሰብ ላይ የተቸከሉ በሚል በህዝብ አሁናዊ መሪር ተሞክሮ ላይ ለመሳለቅ ሲሞክሩ፣

 

·         በሥልጣን ፍርፋሪ ተመፅዋችነትና በፍፁም አሽከርነት ተደማሪ ያደረጓቸውን ወራዳ ፖለቲከኞች እንደ እውነተኛ የብዝሃ ፓርቲ (multi-party) ሥርዓት ማሳያ አድርገው ሊያሳምኑን  ሲከጅላቸው፣

 

·         የወንጀላቸው ተባባሪ የሆኑትን ወይም ተልእኳቸውንና ሃላፊነታቸውን በቅጡ መወጣት አቅቷቸው የሚንደፋደፉትን ወይም የአድርባይነትና ልክ የሌለው ራስ ወዳድነት  ሰለባዎች የሆኑትን የሃይማኖት መሪዎችና ሽማግሌዎች “እየተደመራችሁ ለሽግግር ፍትህ አስተዋፅኦ አድርጉ” የሚል የሸፍጥ ጥሪ ሲያሰሙ፣

 

·         በምሁርነት፣ በሙያ እና በእድሜ ተሞክሮ አንቱ እንደተባሉ የተፈጥሮን ሞት መሞት ይገባቸው የነበሩና ነገር ግን ለፍርፋሪ ምፅዋተኝነትና አድርባይነት ራሳቸውን አሳልፈው ለመስጠት ፈቃደኛ በመሆን የቁም ሞት የሞቱትን ወገኖች (ግለሰቦች) መልምለው ለማታለያነት (ለፖለቲካ ወለድ ወንጀላቸው) ሽፋን ሰጭነት ለፈጠሩትና በእነርሱው ፍፁማዊ ቁጥጥር ሥር ለሚገኘው  የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን ተብየ በኮሚሽነርነት በመሾም የአገራዊ እርቅና ሰላም ሥራውን እያቀላጠፍነው ነውና የበረከቱ ተሳታፊ ሁኑ በሚል ማሰብና መረዳት  እንደማይችል እንስሳ ሲቆጥሩን መስማትና መታዘብ  በቃላት ገልፆ ለማስረዳት በእጅጉ ከባድ የሚሆነው።

እናም ከሦስት አስርተ ዓመታት በላይና በተለይም ከስድስት ዓመታት ወዲህ የዚያው ሥርዓት ውላጆች በሆኑ ተረኛ ቡድኖች  ለመግለፅ በሚያስቸግር ሁኔታ  የቀጠለው እና በንፁሃን ደምና የቁም ሰቆቃ የበሰበሰውና የከረፋው አገዛዝ አሁንም ግዙፉንና መሪሩን እውነት በአፍ ጢሙ የሚደፋ ድርሰት (መግለጫ) እያዘጋጀ በመከረኛው ህዝብ ላይ ሲሳለቅ ከመስማትና ከመታዘብ የበለጠ ለእውነተኛ የነፃነትና የፍትህ (ዴሞክራሲያዊ) ሥርዓት ለውጥ የሚያነሳሳ  ፈታኝ እውነታ የለምና ልብ ያለው ልብ ይበል!

ለመከራና ለውርደት (ለገዳይና አስገዳይ) ሥርዓት ከዚህ የበለጠ ጊዜ መስጠት ለነፃነትና ለፍትህ  ሥርዓት እውን መሆን የተዋደቁና የወደቁ  አርበኞችን/ፉኖዎችን/ ጀግኖችን በዋጋ የማይተመን መስዋእትነት ከንቱ ማድረግና ተመልሶ የውድቀት አዙሪት ሰለባ መሆን ነውና  እኩያን ገዥ ቡድኖችን የማላገጫ ድርሰታችሁ (የመግለጫ ጋጋታችሁ) የእኩይ ሥርዓታችሁን ግብአተ መሬት ከማሳየትና ከማፋጠን  የዘለለ ፋይዳ የለውም ብሎ በግልፅና በቀጥታ መንገር (ማሳወቅ) ተገቢ ነው።

 

1 Comment

  1. ታየ ደንዳአ ጥጋቡ ሰማይ ሊነካ ሲል አብይና ሽመልስ ለዚህም ደርሰሃል ለካ ብለው ከርቸሌ ልከውታል ቀሲስ ዶላርም እምነቱን በማራካሳቸው የእምነቱ አምላክ በዚህ ውርደት እንዲጠናቀቁ አደረጋቸው ከስርቆታቸው መልሳቸው ይበልጥ አዝናኝ ሆነ፡፡ ጓደኛቸው ህጻንም እስሩን አላላሁ ብለው ሸምቀቆውን ሳቡት፡፡ እንግዲህ የኢትዮጵያ አምላክ አረጋዊ በርሄን፤ግደይ ዘራጽዩንን፤ሽመልስ አብዲሳ፤ዲማ ነገዎ፤ሌንጮ ለታ፤ባቲ፤ ዳውድ ኢብሳን፤አቶ ዳንኤል ክብርትናና ሌሎችን ኢትዮጵያ ላይ በመትኮሳቸው ቢጎበኛቸው መልካም ነበር ይህ የእኛ ምኞት ነው አምላክ ደግሞ የሚሰራውን ያውቃል፡፡ አብይ ከታሰረ አሳሪ ይጠፋል ብዬ ነው ትግሬዎችንም ረስቼ አይደለም፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share