ህወሃት ከራያ መውጣት አለባት፣ ለትግራይ ህዝብ ሰላም እንጂ ዳግም ጦርነት አያስፈልገውም

የደቡባ አፍሪካ ስምምነት ሲፈረም ሰላም ያመጣል፣ የትግራይ ህዝብ ከከበባ ይወጣል፣ በትግራይ ልማት፣ ኢንቨስትመንት፣ ንግድ የመሳሰሉ ኢኮኖሚክ እንቅስቃሴዎች ይጠናከራሉ፣ የስራ እድሎች ይፈጠራሉ፣ በጦርነት በጣም የተጎዳ ማህበረሰብ ስለሆነ ህዝቡን የማቋቋም ስራ ይሰራል፣ ተፈናቃዮች ወደ ቅያቸው ይመለሳሉ፣ የጥይት ድምጽ መስማት ይቆማል ወዘተ የሚል ትልቅ ተስፋ ነበር፡፡

የደቡብ አፍሪካው ስምምነት ከተፈረመ አንድ አመት ተኩል ሆነው፡፡ ህዝቡ እንኳን ከስምምነቱ አገኛለሁ ብሎ የጠበቀው ሊሆን እንደውም ወደ አራተኛ ዙር ጦርነት ውስጥ እንዲገባ እየተደረገ ነው፡፡ በዚያ ያሉ መሪዎች፣ እነ አቶ ጌታቸው ረዳ፣ በአብይ አህመድ ወጥመድ ውስጥ በመግባት፣ ለብልጽግናዎች በመታዘዝ ፣ የትግራይ ማህበረሰብ ከአማራው ማህበረሰብ ጋር የበለጠ ደም እንዲቃባ ለማድረግ እየሰሩ ነው፡፡ ምን አይነት መርገምት ነው ወገኖች ???? ባለፈው ጦርነት ምክንያት ያለቁትን በመቶ ሺሆች ትተናቸው፣ በህይወት ካሉ 10 ወጣቶች ሶስቱ አካለ ስንኩል ናቸው ብሎ አንድ ሰው ነግሮኝ ነበር፡፡ ከዚህ ሁሉ ስቃይ በኋላ፣ ሌላ ጦርነት ?????

በጣም የማምንበት ጉዳይ አለ፡፡ የትግራይ ማህበረሰብ መሰረታዊ ችግር የሚፈታው በስሜኑ የአገራችን ክፍል ሰላም ሲኖር ብቻ ነው፡፡ ያ ደግሞ ሊሆን የሚችለው ከአጎራባች ማህበረሰባት ጋር እጅና ጓንት ሲኮን ነው፡፡ ትግራይ በስሜን ከኤርትራ፣ በምእራብና ደቡብ ምእራብ ከጎንደር፣ በደቡብ ከወሎ ጋር ተዋስነው ባለበት፣ ከአማራውና ከኤርትራ ወገኖች ጋር ሰላም ካልተመሰረተ፣ መነጋገር፣ መግባባት ከሌለ፣ ያሉ አወዛጋቢ ጉዳዮች ሁሉንም አሸናፊ ባደረገ መልኩ መፍታት ካልተቻለ እንዴት ነው የትግራይ ህዝብ ሰላም የሚያገኘው ????

ወደ ትግራይ የሚያስወጡና የሚያስገቡ አስራ አራት መንገዶች አሉ፡፡

ከኤርትራ በባድመ፣ በራማ/አድዋ/ በጾሮናና በዛላምባሳ በኩል በአራት መስመር፣

ተጨማሪ ያንብቡ:  የግብፅና ኢትዮጵያ መጪው ዘመን ምን ሊመስል ይችል ይሆን?

ከአማራ ክልል ጎንደር በአዲ ጎሹ፣ በቆራቲት፣ በማይጠምሪ በኩል በሶስት መስመር፣ ከአማራ ክልል በዋገመራ ዞን በሰቆጣ/አቢአዲ፣ ሰቆጣ/ሳምሪና በሰቆታ/ዛታ/ኮረም በኩል በሶስት መስመር፣

ከአምራ ክልል ከሰሜን ወሎ ፣ ሙጃ/ኮረም፣ በቆቦ/አላማጣ/ማይጨውና በቆቦ/አላማጣ/መኾኔ በኩል፣ በሶስት መስመር፣

ከአፋር ክልል በአፋር ዞን ሁለት በመቀሌ/አባላ በኩል በአንድ መስመር፣

በትግራይ ካሉ 14 መንገዶች በአስራ ሶስቱ እንቅስቃሴ ከሌለ፣ ንግድ፣ ኢንቨስትመንት ፣ ልማት እንዴት ሊኖር ይችላል ? ሌሎች ወደ ትግራይ፣ ትግራይ ያሉ ወደ ሌሎች አካባቢዎች በነጻነት መንቀሳቀስ ካልቻሉ፣ አካባቢው የጦርነት ቀጠና ከሆነ እንዴት ለትግራይ ወጣት ተስፋ መስጠት ይቻላል ?????

በህወሃት ውስጥ የሀሳብ ልዩነትና መከፋፈል እንዳለ ይሰማል፡፡ በአንድ በኩል እንደ ጌታችው ረዳ ያሉ አሉ፣ የነ አብይ አህመድ ታዛዦችና ጫማ ጠራጊዎች የሆኑ፡፡ በሌላ በኩል እነ ማንጆሪኖ አሉ፣ “አብይ አህመድ እንኳን አገር ወረዳ መምራት የማይችል፣ ለትግራይ ህዝብ መከራ ዋነኛ ምክንያት የሆነ ነው” ብለው የሚያምኑና ከብልጽግና ጋር በነ ጌታቸው ረዳ እየተደረገ ያለውን መሽኮርሞም የሚቃወሙ፡፡ “በአንድ በኩል ከአማራ ማህበረሰብ ጋር መነጋገር መወያየት እርቅ መመስረት ያስፈልጋል፣ የትግራይና የአማራ ህዝብ አንድ ነው” የሚሉ አሉ፣ በሌላ በኩል አሁንም በዘር ፖለቲካ የሰከሩ፣ አሁን ጥጋቸው ያልተነፈሰላቸው፣ የትግሬ መሬት እያሉ የሚያናፉ እብዶችም አሉ፡፡

እነዚህ ህወሃት ውስጥ ያሉ እብዶች፣ በአብይ አህመድ ወጥመድ ውስጥ ገብተው፣ ለህዝብ የሚጠቅመውን ሳይሆን ፣ ለአማራ ካላቸው ጥላቻ የተነሳ፣ ለአብይ የሚጠቅመውን ስራ እየሰሩ ነው፡፡ እነ ጌታቸው ረዳ፡፡ ራያን በጉልበት ተቆጣጥረዋል፡፡ በጉልበት ራያን ተቆጣጥረው እስከመቼ ይዘልቃሉ? የሚታይ ይሆናል፡፡

አሁንም እላለሁ፣ በአስቸኳይ የህወሃት ኃይሎች ከራያ መውጣት አለባቸው፡፡ ለትንሽ ነገር ብለው፣ ትልቁን ነገር አያበላሹ፡፡ ዘላቂ ሰላም በቀጠናው እንዳይኖር እንቅፋት አይሁኑ፡፡ የሰላምን፣ የውይይት፣ የመነጋገር በር አይዝጉ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  አገርን የማያጸና ህገ መንግስት - ገብረ አማኑኤል

አብይ አህመድና አራት ኪሎ የኦሮሙማ ኃይሎች አያዋጧቸውም፡፡ አሜሪካኖች እነ ማይክ ሃመር አያዋጧቸውም፡፡ ባለፈው ጦርነት አሜሪካኖች ከነርሱ ጋር ነበሩ፡፡ ሜዲያዎቻቸው ከነርሱ ጋር ነበሩ፡፡ የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው መክር ቤት ከነርሱ ጋር ነበር፡፡ የአዉሮፓ ህብረት ከነርሱ ጋር ነበሩ፡፡ ግን አሁን ካሉበት ሁኔታ አላዳኗቸውም፡፡ የአፍሪካ ህብረት አያዋጣቸውም፡፡

የሚያዋጧቸው ለዘመናት አብሯቸው የኖረ፣ ከነርሱ ጋር የተዛመደ፣ የተዋለደ፣ የአማራው ማህበረሰብ ነው፡፡ ለትንሽ እገር ብለው ከወንድማቸው ጋር አይቃቃሩ፡፡ ከዚህ በፊት የሆነው ይበቃል፡፡ ከዚህ በኋላ በፍቅር፣ በይቅር መባባል፣ በመያያዝ አብሮ ማዳግ እንጂ በጦርነት መፈላለግ መቆም አለበት፡፡

አዎን ጀብደኝነታቸውና እብደታቸውን አቁመው፣ በአስቸኲአይ ከራያ ይውጡ፡፡ ራያን ጨምሮ እነ ወልቃይትን በተመለከተ፣ ሌሎች ማናቸውንም ጉዳዮች እንደ ወንድማማቾች ቁጭ ተብሎ መነጋገር ይቻላል፡፡ ሁሉንማ አሸናፊ ያደረገ መፍትሄዎች አሉ፡፡

(ይህን ስል አንዳንድ የትግራይ ወገኖች ሙገት የሚፈጥሩ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ እኔን ለመሞኢገት አትሞክሩ፡፡ ከራሳችሁ ጋር ተሟገቱ፡፡ ራሳችሁን ጠይቁ፡፡ ከስሜት በጸዳ መልኩ፡፡ የትርጋይ ህዝብ ያለበትን ሁኔታ በማብሰ፣ ያለፈው ጥፋት በማሰብ፣ ረጋ ብላችሁ አስተማማኝ ሰላም የሚመጣው። ለህዝብ የሚበጀው ምንድን ነው ብላችሁ ጥይቁ፡፡ ከራሳችሁ ተሟገቱ፣ ለራሳችሁ ጥያቄ ራሳችሁ ማልሽ ስጡ፡፡ እርግጠኛ ነን በኔ ሃሳብ ትስማማላችሁ)

ግርማ ካሳ

1 Comment

  1. ወንድሜ ግርማ ሃሳብህ ማለፊያ ሆኖ እያለ አካፋን አካፋ ነው አለማለትህ ሃሳብህን ሸፋፋ ያረገዋል። የትግራይ ህዝብ ቀዳሚ ጠላት ወያኔ ነው። ከበረሃ እስከ ከተማ የትግራይን ህዝብ የሚያበራየው ወያኔ ሃርነት ትግራይ ነው። ይህ ድርጅት ካልከሰመ በምንም አይነት መልኩ ሰላም ትግራይም ሆነ በቀረው የሃገሪቱ ክፍል አይኖርም። የደቡብ አፍሪቃው ስምምነት ወያኔ የእኔ ናቸው ስለሚላቸው ስፍራዎች ጭራሽ አይጠቅስም። ስለ ወያኔ ትጥቅ መፍታት እንጂ! ወያኔ አታላይና አጭበርባሪ ድርጅት ለመሆኑ ያለፈ ተግባሩ አሁን ካለው ጋር ተደምሮ ቁልጭ አድርጎ ይመሰክራል። የብልጽግናው መንግስት ወያኔን አምኖ ከእነርሱ ጋር ያደረገውም ሆነ የሚያደርገው ስምምነት ውሃ አይቋጥርም። ለትምህርት ቤት ማሰሪያ የጠ/ሚ አብይ ባለቤት የላከችው ከ 200 ሚሊዪን በላይ ብር ወያኔ ወይ ት/ቤት አልሰራበት ወይ ብሩን አልመለሰ ዋጥ አርጎ አስቀርቶታል። ይህና ሌላ ከፌደራል መንግስቱ ለትግራይ የተላኩ እርዳታዎችና ገንዘብ የት ገባ?
    ባጭሩ ወያኔ ከትግራይ ህዝብ ጀርባ ላይ ካልወረደ ከመከራ የተረፉትን የትግራይ ልጆች ከማስጨረስ ወደኋላ አይልም። ይህን ሙት ድርጅት እስከ አሁን የሚደግፉ የትግራይ ልጆች እውነትን መረዳት ያልፈለጉና ከወያኔ ፍርፋሪ ችሮታ የሚያገኙ ብቻ ናቸው። ጦርነት የኋላ ቀርነት ምልክት ነው። ወያኔ ጊዜ የሻረው ድርጅት ነው። አሁን ምዕራብና ምስራቅ ትግራይ በሚላቸው አካባቢ ውጊያ መክፈቱ የብልጽግናው መንግስት ላይ ምራቁን እንደተፋበት ያሳያል። ይህ 4ኛ ዙር ጦርነት የተከፈተው ሁሉም ወያኔዎች ተስማምተው እንጂ አንድ የፓለቲካ ክንፍ አፈንግጦ የከፈተው ግጭት አይደለም። በወያኔ ዓለም አፈንግጦ መኖር አይቻልምና! ዓለምንና የሌላውንም እይታ ለማደናቆርና ለማምታታት ግን ወያኔ ለሁለት አልፎ ተርፎም ለሶስት እንደተከፈለ አርገው ወሬ ይነዛሉ። አሁን ማን ይሙት ጌታቸው ረዳ የሚታመን ሰው ነው? የኋላ ታሪኩ ይህን ሰው እንድናምነው የሚያደርግ ተግባር አለው? በጭራሽ። ግን የብልጽግናውን መንግስት በሾኬ ጠለፋ ለመጣል ወያኔ ለአሜሪካኖች ግጭቱ አሻፈረኝ በሚሉ ወታደሮችና አመራር የተጀመረ ጦርነት አድርገው ያወራሉ፤ ያስወራሉ። ለገባው ገና ነገርየው እኮ ሳይጀመር የአሜሪካ መንግስት ግጭት ሊጀመር ነው በማለት አሟርቶ ነበር። ጉዳዪን የሚፈጽሙት ከአሜሪካ መንግስት ጋር እየተማከሩ ነው። ሰርቀው ያካፍሏቸው የነበሩ የአሜሪካ አመራሮች ዛሬም እንደ ወያኔ አይናቸው ፈዞና ደንግዞ ስልጣን ላይ ናቸው።
    ባጭሩ የትግራይ መሬት የአማራ መሬት የአፋር የሚባል ጉድ የለም። ምድሩ ሁሉ የሁሉ ሃበሻ ነው። ግን ወያኔ የዘር መርዙን ከሻቢያ ተቀብሎ በምድሪቱ ከዘራው ወዲህ ሰው ሁሉ ባለሃገር ሆኖ በራፉ ላይ ቆሞ የክልሉን ባንዲራ እያውለበለበ ዓለሙ ሁሉ ይህ ነው፤ ከእኔ ውጭ ሌላ ሰው በክልሌ አይኑር በማለት ሲገድሉና ሲያሳድድ ሲዘርፉና ሲያማቱ ይኸው እንሆ አይናችን እያየ ነው። ብሄርተኞች ጨለምተኞች ናቸው። የሚያዪት ከራሳቸው የቀጥር ጥላ አያልፍም። ኦነግ፤ ፋኖ፤ ሌላውም ታጣቂ ቡድን ሁሉ የሰውን ልጆች መከራ ለማባዛት ካልሆነ በስተቀር ሰላምና ብልጽግናን ለህዝባችን አያመጡም። ዝም ብሎ መንዘላዘል ነው። በዚህ ላይ የጊዜው አለቆቻችን የዘር ስካር ለተመለከተ ወቸው ጉድ ሰው ሳይጠጣ እንዲህ በነገርና በጥላቻ ብቻ ይሰክራል በማለት ይገረማል። ሰዎች በኖሩበት ቀያቸው አርሰው የሚተዳደሩበት መሬታቸውን መንጠቅ፤ ቤታቸውን ማፍረስ፤ ክልልህ አይደለም ውጣ ማለት በስመ አማራ የፋኖ አባልና ደጋፊ ነህ እያሉ ማሰርና ማሰቃየት የዛሬ መቶ ዓመት ሚኒሊክ ጨቁኖናልና በሚል የድንጋይ ዘመን አስተሳሰብ ግፍና መከራን እያዘነቡ ይገኛሉ። ግን ለዚህም ማብቂያ አለው። አይተናል። ኑረንበታል። ታሪክ ራሱን ይገለብጣል። ገራፊው ይገረፋል፤ አሳሪው ይታሰራል፤ ገዳዪ ይገደላል። ለዚህ ነው የሃበሻው ፓለቲካ የመጠላለፍና የመገዳደል ፓለቲካ ነው የምንለው። ጊዜ የሰጠው ድባ ድንጋይ ሲሰብር ድንጋዪም ጊዜ ኑሮት እልፉን ድባ ይፈረካክሰዋል። የዓለም ታሪክ የሚያሳየን ይህኑ ሃቅ ነው።
    አሁን ወንድሜ ግርማ የትግራይ የመወጣጫ በሮችና የሌሎችን የመግቢያ መንገዶች እያመላከተ ለትግራይ ህዝብ ማሰቡ መልካም ነው። የትግራይ ህዝብ ምርጫ ቢኖረው ወያኔን አንድ ቀን እንዲኖር አይፈቅድለትም። ግን ልክ እንደ ሰሜን ኮሪያው ህዝብ የታፈነ ህዝብ ነው። ይህን ለመረዳት መቀሌ ብቻ ሳይሆን ራሱ ዲያስፓራው ጭምር በርቀት በወያኔ ቁጥጥር ስር በመሆኑ አንዳንድ የነቁ የትግራይ ልጆችን ማሳደድና መሳደብ፤ ከሥራ ስፍራቸው ድረስ በመሄድ ችግር መፍጠርን ሙሉ ተግባራቸው ያደረጉ ብዙዎች ናቸው። ባጭሩ ትግራዋይ ሆነህ ከጅምላ አስተሳሰብ ውጭ ማሰብ ከጀመርክ እንድትኖር አይፈቀድልህም። ወያኔ የትግራይን መከራና ሃበሳን የሚያላክከው በአማራው፤ በፌደራል መንግስቱና በኤርትራ ላይ ነው። ራሱን ግን አንድም ቀን የእኔ የቀምበር አገዛዝ ነው ይህን ህዝብ ለቀቅ ላርገውና እስቲ በራሱ አስቦና ሰርቶ ይኑር ያለበት ጊዜ የለም። ይፈራል። የፈሪ ደግሞ በትሩ ረጅም ነው። መኖሩን ይቀናቀናሉ የሚላቸውን ሁሉ ያስራል፤ ይቀብራል። ጊዜውም የበራል።
    አሁን ራሱን ለማትረፍ የሚንደፋደፈው የብልጽግናው መንግስት ከወያኔ ጋር አብሮ ለመስራት የሚያደርገው ሙከራ አይሰምርም። ወያኔ ጊንጥ ነው። ብልጽግናም እባብ። ሁለቱ በአንድ ስፍራ አብረው መኖር አይችሉም። ብልጽግና ለይቶለት የሰሜን እዝን ከቦታው በማድረግ ወያኔን እስከ ወዲያኛው እስካልሸው ድረስ ምድሪቱ ሰላም አትሆንም። በመለማመጥና በአሜሪካ ዛቻ በትግራይም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች ሰላምን ማስፈን አይቻልም። አሜሪካኖች በአንድ አፍ ሁለት ምላስ የሆኑ ሽንኮች ናቸው። ልብ ላለው ለፍልስጤማዊያን የሚፈሰው እንባና ንዋይ፤ ለእስራኤል የሚሰጠው የጦር ትጥቅና ጥቅማጥቅም በመከራ ለሚጠበሰው የሱዳን ህዝብ ደርሶታል? የጥቁሩ ዓለም መቼ እንደሚነቃ ሊገባኝ አይችልም። አሁን ማን ይሙት ሱዳን ውስጥ ካለው ሰቆቃ የባሰ ፍልስጤማዊያን ላይ ይደርሳል? አይመስለኝም። ግን ሰውን በቆዳው በሚመዝን በዚህ ሸንካላ አለም ውስጥ እርስ በእርሳችን እየተገዳደልን ነጭን አስታራቂ ስናደርግ አይገርምም። ስናሳዝን! በቃኝ።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share