“የሰላም መንገድ አመቻቻለሁ”

/

March 31, 2024

ጠገናው ጎሹ

ይህንን እንደ ርዕሰ ጉዳይ የተጠቀምኩበትን አባባል የወሰድኩት ለእኩያን የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኞች በሽፋን ሰጭነት ያገለግል ዘንድ የተቋቋመውና ከተሰጠው የሥስት ዓመታት ተልእኮ አንድ ዓመት ብቻ የቀረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን (The Ethiopian National Dialogue Commission) ተብየው በዋና ኮሚሽነሩ (ሰብሳቢው) ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ በኩል ካስተላለፈውና በቢቢሲ የአማርኛው ክፍል ጠቅለል ተደርጎ በ03/28/24 በሪፖርት መልክ ከቀረበ ዜና ላይ ነው።

የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሰብሳቢው ፕ/ር መስፍን አርአያ
የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሰብሳቢው ፕ/ር መስፍን አርአያ

ይህ አይነት ከዘመን ጠገቡና በእጅጉ አስከፊ እየሆነ በመሄድ ላይ ካለው ግዙፍና መሪር እውነታ ጋር በቀጥታና በግልፅ የሚላተም “እባካችሁ እኛንም ሆነ የሾመንን መንግሥት እመኑን እና ከህልውና አደጋ ለመዳንናም ሆነ ነፃነት፣ ፍትህና እኩልነት የሚረጋገጥባት የጋራ ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የምትታገሉበትን መሣሪያ ሁሉ ቁጭ እያደረጋችሁ የምክክር በረከታችን ተሳታፊዎች ሁኑ” አይነት እጅግ ወራዳና ጨካኝ ዲስኩር አዲስና የሚያስገርም ባይሆንም በምሁርነትም ሆነ በእድሜና በሙያ ዓለም ተሞክሮ አንቱ እንባላለን ከሚሉ እንደ ፕሮፌሰሩ አይነት ወገኖች መምጣቱ ግን ቅንና ሚዛናዊ ህሊና ላለው የአገሬ ሰው የሚያሳድረውን የህሊና ቁስለት በቃላት ለመግለፅ የሚቻል አይመስለኝም።

ስለ እውነት በእውነት ከተነጋገርን አገርን አሁን ላለው ብቻ ሳይሆን ለነገው ትውልድም ምድረ ሲኦል ያደረገው፣ እያደረገ ያለው እና ከፀፀትና ከይቅርታ ጋር ፈፅሞ የማይተዋወቀው የጎሳ/የዘር አጥንት ስሌት ፖለቲካ ሥርዓት ተረኛ የበላይ ጠርናፊዎች በድንቁርና እና በመከራ ቀንበር ሥር ያለውን ህዝብ ስድስተኛ ዓመታዊ በዓላቸው (የወንጀል ተውኔታቸው) ተሳታፊ ይሆን ዘንድ በእጅጉ የበሰበሰና የከረፋ የፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ በሚያላዝኑበት በዚህ አስጨናቂ ወቅት በምሁርነትም ሆነ በተሞክሮ የአንቱታን ክብር  ልንቸራቸው ይገባቸው የነበሩ ወገኖች በምክክርና በሰላም ስም ራሳቸውን አዋርደው መከረኛው ህዝብ ከመከራና ከውርደት አዙሪት ሰብሮ እንዳይወጣ የሚያደርጉትን የህሊና ቢስነትና የምንደኝነት ባህሪና ተግባር አካፋን አካፋ በሚያሰኝ ደረጃ መንገርና መሞገት ቢያንስ የሞራል ግዴታ ሊሆንብን ይገባል።

አዎ! ሰብእናቸው በንፁሃን ደምና የቁም ሰቆቃ ፈፅሞ የበሰበሰውና የከረፋው ገዥ ቡድኖች ለሽፋን ሰጭ አሻንጉሊትነት ከፈጠሯቸውና ካሰማሯቸው አካላት መካከል አንዱ ይኸው የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ተብየው መሆኑን ለማስረዳት በስድስት ዓመቱ የእነ አብይ አህመድ አገዛዝ በየትኛውም የረጅም ዘመን የአገርነት ፖለቲካ ታሪካችን ተሰምቶና ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ  በመሬት ላይ ከሆነውና እየሆነ ከቀጠለው  ግዙፍና መሪር እውነታ በላይ የተለየ አስረጅ መፈለግ የጤናማና የሚዛናዊ ህሊና ባለቤትነት አይመስለኝም።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የአባይ ጉዳይ የዛፍ ላይ እንቅልፍ የሆነባት ግብጽ እና ለስልጣን ጸብ ጫሪው ህውሃት! ግርማ ሞገስ

የምክክር ኮሚሽን ተብየው (የእነ አብይ አህመድ የፖለቲካ ሴራና ሸፍጥ መጫወቻ ካርድ) ከተሳካለት በቀሪው አንድ ዓመት ካልሆነ ደግሞ በሚጨመርለት እድሜ ተጠቅሞ የእኩያን ገዥዎችን እድሜ የማራዘም (ከተሳካለት) እጅግ ትውልድ ገዳይና አስገዳይ ተልእኮውን ለመወጣት ጥረት  እንደሚያደርግ ዋናው ኮሚሽነር ነግረውናል።

ስድስት ዓመታት የሆነውንና አሁንም እጅግ አስከፊ በሆነ ደረጃ የቀጠለውን ፖለቲካ ወለድ የመከራና የውርደት ዶፍ ህግ የማስከበርና አገርን (ህዝብን) የመታደግ የተቀደሰ ዓላማና ተግባር እንደሆነ ሊያሳምኑን ሲሞክሩ ጨርሶ ሃፍረት በማይሰማቸው ገዥ ቡድኖች የተመለመሉ፣ የተሾሙና ምንዳዕ የሚሰፈርላቸው ኮሚሽነርሮች ተብየዎች በሚመሩት ኮሚሽን ተአማኒነት ያለውና ዘላቂ ሰላም የሚያረጋግጥ ምክክር መጠበቅ ወይ የለየለት ጨካኝ የብልፅግና ካድሬነት ወይም ድንቁርና ወይም ከመከራና ከውርደት ጋር የመለማመድ ክፉ ደዌ ወይም በእጅጉ ስር የሰደደውና አስከፊ የሆነው አድርባይነት ሰለባ የመሆን ወይም ከፈጣሪ እገዛ ጋር ለመብትና ለነፃነት ከመታገል ይልቅ እግዚኦ ማለትን እንደ የፅድቅ ዋስትና የመቁጠር ደካማነት ፣ወዘተ ካልሆነ በስተቀር ከቶ ሌላ ሊሆን አይችልም።

ዋና ኮሚሽነሩ (ፕሮፌሰሩ) ያነሷቸው ነጥቦች በርከት ያሉ ቢሆኑም ለዘማናት በመሬት ላይ ከሆነውና ከስድስት ዓመታት ወዲህ ደግሞ የበላይነት ጠርናፊነቱን የተቆጣጠሩት  የዚያው ሥርዓት ውላጆች (ኦህዴድ/ብልፅግናዎች) እንኳንስ ለማመን ለመስማትም በሚከብድ ሁኔታ እያስኬዱ ካሉት ፖለቲካ ወለድ መከራና ውርደት አንፃር ሲታዩ ተአማኔነት በእጅጉ የሚጎላቸውና አሳሳቾች ቢሆኑም ከምር ለመረዳት ለሚፈልግ ነፃነትና ፍትህ ፈላጊ ወገን  አስቸጋሪ ስለማይመስሉኝ ብዙ ለማለት የሚያስፈልገኝ ሆኖ አላገኘሁትም።

ፕሮፌሰሩ (ዋናው ኮሚሽነር) አገርን እጅግ ለመግለፅ በሚያስቸግር ሁኔታ ምድረ ሲኦል ያደረገውና እያደረገ ያለው የእነ አብይ አህመድ አገዛዝ ከተፈጥሮውና ከባህሪው ጋር ፈፅሞ ግንኙነት የሌላቸውን አካታችነት፣ ግልፅነት፣ ተአማኔነት፣ መቻቻል ፣መከባበር ፣ ምክንያታዊነት እና ገለልተኝነት የተሰኙ ወርቃማ ፅንሰ ሃሳቦች በኮሚሽን ተብየው ማቋቋሚያ አዋጅ እንዲካተቱ የማድረጉን የሸፍጥና የርካሽ ፖለቲካ ጨዋታ ከምር ወስደው ከእነዚህ መርሆዎች ንቅንቅ እንደማይሉ ለማሳመን ሲቸገሩ መታዘብ ባይገርምም በእጅጉ ያሳዝናል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  መዝቀጥ እንደ አብይ አህመድ - እውነቱ ቢሆን

ቀደምት ወላጆቹ ደምና አጥንት ከፍለው ከውጭ ሃይል ባርነት ነፃ ሆኖ እንዴኖርባት አድርገው ያስረከቡትን አገር ለእርሱ ዘመን የምትበጅ ዴሞክራሲያዊት አገር በማድረግ የራሱን ታሪክ ከመሥራት ይልቅ ከየግሉ፣ ከየጎሳው፣ ከየመንደሩና ከየቡድኑ እጅግ ጠባብና አደገኛ ፍላጎት ሰለባነት ሰብሮ መውጣት አቅቶት ከፉኛ ለተቸገረ ትውልድ እንዲህ አይነት “መስሎና አስመስሎ መኖርም ወይም አድር ባይነትም የኑሮ ዘዴ ነው” የሚል አይነት  መልእክት ማስተላለፍ ምን የሚሉት የምክክርና የሰላም ተልእኮ ነው?

የኋላ ቀርነታችን ማለትም ከዘመን ጋር አብረን ያለመራመዳችን ምክንያቶች በርካታ ሊሆኑ ቢችሉም በዚህ በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የገጠመንና እየገጠመን ያለው የምሁርነትና የመልካም ዜግነት ውድቀት ( crisis of intellectualism and good citizenship) ግን በእጅጉ አስከፊና አስፈሪ ነው።

ግዙፍና ጥልቅ የሆኑ እሴቶች መገለጫ የሆኑትን ፅንሰ ሃሳቦች በተለምዶ ከመጥቀስ ወይም ከማስተጋባት አልፈን ምንነታቸውንና ለምንነታቸውን ለመረዳት ካልሞከርን በስተቀር የእኩያን ገዥዎችን እና ለሽፋን ሰጭነት የፈጠሯቸውንና የፈቃዳቸው አስፈፃሚ ያደረጓቸውን እንደ የምክክር ኮሚሽን ተብየ አይነት  አካላትን ምንነትና ለምንነት የምንረዳበት አረዳድ ወይ በእጅጉ የተንሸዋረረ  ወይም ደግሞ ከግልብ ስሜት የማያልፍ ነው የሚሆነው።

ለነገሩ ሰላምን ሲያስፈልገው እያጋደመና ሲሻው ደግሞ ዘቅዝቆ የሚያርደው የሸፍጠኞችና የእኩያን አገዛዝ የሰላም ሚኒስቴር የሚል አካል አቋቁሞ እጅግ ውድ በሆነ የሰላም ምንነትና ለምንነት እና በመከረኛ ህዝብ ላይ የሚሳለቅ ገዥ ቡድን ከሚገዛት አገር ሌላ ምን ይጠበቃል?

በእነዚህ ገዥ ቡድኖች ከተመለመሉ፣ ከተሾሙና ምንዳዕ ከሚከፈላቸው ወገኖችስ (ኮሚሽነሮች ተብየዎችስ) እውነተኛ ምክክርና የምክክር ውጤት እንዴት መጠበቅ ይቻላል? በሌላ አገላለፅ በቆሻሻ ግባ እና ቆሻሻ ውጣ/ በጉልቻ መለዋወጥ ደዌ በበሰበሰና በከረፋ የጎሳ አጥንትና ደም ስሌት ፖለቲካ ሥርዓት ሥር የሚተነፍስና የሚንቀሳቀስ ኮሚሽን ተብየ እውነተኛ ሰላምን ማምጣት ከሚችል ምክክር ጋር ምን ዝምድና አለው?

ተጨማሪ ያንብቡ:  ለትግራይ ተወላጅ የወያኔ ደጋፊዎችና አንዳንድ ሌሎች ዓላማችሁ ምን ይሆን? - ሰርፀ ደስታ

ዘመን ጠገብ የሆነውንና ከስድስት ዓመታት ወዲህ ደግሞ እንኳንስ ለማመን ይሆናል (ይደረጋል) ብሎ ለማሰብም በሚከብድ ሁኔታ የሆነውንና እየሆነ ያለውን ፖለቲካ ወለድ ወንጀል ከምርና ከቁጭት ለሚያስተውል የአገሬ ሰው ምክክር፣ እርቅ ፣ መግባባት ፣ መስማማት ፣ ሰላም፣ መረጋጋት ፣ መተባበር፣ አንድነት፣ ሥልጣኔ፣ እድገት ፣ ወዘተ የተሰኙ እጅግ ግዙፍና ጥልቅ የእሴትነት ትርጉም ያላቸውን ፅንሰ ሃሳቦች ምን ያህል እንዳጎሳቆልናቸውና እያጎሳቆልናቸው እንደሆነ (how we terribly abused and abuse them) ለመረዳት የሚቸገር አይመስለኝም።

አዎ! በእውነት ስለ እውነት ከተነጋገርን ይህ የሆነውና እየሆነ ያለው ደግሞ በፊደል ቆጠራውም፣ በሙያና በሥራ ተሞክሮውም እና በእድሜ አንጋፋነቱም አንቱ መባል ሲገባቸው የትክክለኛ ሰብአዊነት መገለጫ የሆነውን የውስጠ ነፍሳቸውን (their inner soul) ምንነትና ለምንነት እጅግ ርካሽና ጊዜያዊ በሆነ ፍርፋሪ ለሚረካ ሥጋቸው አሳልፈው በሰጡና በሚሰጡ ወገኖች የመሆኑ ግዙፍና መሪር ሃቅ ባይገርምም በእጅጉ ያሳፍራል፤ ያስፈራልም ፤ ያሳዝናልም።

ፖለቲካ ወለድ የሆነው የህዝብ የመከራና የውርደት ሰንሰለት በማያዳግም ሁኔታ የሚሰበረው (የሚበጣጠሰው) እና እውነተኛ የሆነ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን የሚሆነው የተጋድሎ ምክንያታዊነትን፣ አገራዊ ራዕይን፣ ዓላማን እና ግብን ፣ አርበኝነትን፣ ዲሲፕሊንን ፣እንደ ተጨባጭ ሁኔታው ሊተገበር የሚችል ስልትንና ሊጨበጥ የሚችል ውጤታማነትን፣ ሰብአዊነትን፣ ለንፁሃን (ለሲቪሊያን) ደህንነት ብቻ ሳይሆን ለአገርና ለህዝብ ንብረት የመጠንቀቅን እና ብሎም መልካም የሆነች የጋራ አገርን እውን የማድረግን  እጅግ  ወርቃማ አስተሳሰቦችንና አካሄዶችን በሃላፊነት (በመሪነት) በሚሸከምና ታግሎ በሚያታግል ኀይል ብቻ ነው።

ለዚህ ነው የአማራ ፈኖን እና የተጋድሎ መነሻውንና መዳረሻውን የሚጋሩ እና በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል የሚኖሩና የየትኛውም ብሔር/ብሔረሰብ/ነገድ አባል የሆኑ ኢትዮጵያውያን የሚያደርጉት የህልውና፣ የነፃነት፣ የፍትህና የእኩልነት ንቅናቄና ተጋድሎ ለስኬት ይበቃ ዘንድ ሂሳዊና ገንቢ የሆነ ሁለንተናዊ ድጋፍ በእጅጉ አስፈላጊ የሚሆነው።

ያኔም ነው ኮሚቴ፣ ኮሚሽን፣ ቦርድ፣ ወዘተ የሚሰኙትን አካላት ከእኩይ የፖለቲካ ዓላማ ማስፈፀሚያነት ነፃ በማውጣት ለትክክለኛው የህዝብ (የአገር) አገልግሎት ብቻ እንዲመሠረቱና ተልእኳቸውን እንዲወጡ ለማድረግ የምንችለው።

1 Comment

  1. The purpose of this commission is to absolve Abiy Ahmed of his genocide, war crimes and treason and extend his rule Kagame-style.
    The commissioner can make better use of his expertise in treating the lunatic Abiy Ahmed in a mental asylum or sanatorium.

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share