የወሰን ይገባኛል የሚነሳባቸውን አካባቢዎች (የራያ ፣ ጠለምት እና ወልቃይት) በተመለከተ የትግራይና የአማራ ክልል አመራሮች የፕሪቶሪያውን የሰላም ውል ተንተርሰው በደረሱት የመተግበሪያ ስምምነት መሰረት ታጣቂዎችን ማስወጣት ተፈናቃዮችን መመለስና አዲስ የአስተዳደር መዋቅር መዘርጋትን ጨምሮ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ለማድረግ መታቀዱን ዋዜማ ስለጉዳይ ከሚያውቁ መንግስታዊ ምንጮች ያገኘችው የሰነድ መረጃ ያመለክታል።
የወሰን ውዝግቡን ለመፍታት የተሰየመው ብሄራዊ ኮሚቴ በቅርቡ ባደረገው ምክክር በደረሰው ስምምነት መሰረት የፌደራል መንግስት መከላከያ ፀጥታውንና ሂደቱን የማስተባበር ኃላፊነት ይረከባል።
ተፈናቃዮችን ወደ ቀደመ መኖሪያቸው ያለቅድመ ሁኔታ መመለስ ቅድሚያ የሚሰጠው መሆኑን ያሰመረበት መርሀግብሩ የትግራይ ክልል የተፈናቃዮችን ቁጥርና ዝርዝር አሰናድቶ ለመከላከያ እንዲያቀርብ፣ ከተመላሾች መካከል በወንጀል የሚጠረጠሩ ወደ መኖሪያቸው መመለስ እንደማይከለከሉና የተጠረጠሩበት ወንጀል ካለ በተናጠል የሚታይ እንደሆነ ያትታል።
ማናቸውንም የወንጀል ድርጊት ክስ የፌደራል መንግስቱ በሂደት የሚመለከተው ይሆናል።
የቀደመ መኖሪያቸው በአወዛጋቢዎቹ አካባቢዎች የሆኑ የትግራይ ተወላጅ ታጣቂዎች እና ሚሊሻ እንደታጣቂ ሳይሆን እንደተፈናቃይ ወደ ቦታቸው መመለስ እንደሚችሉም ከስምምነት ተደርሷል።
የወሰን ይገባኛል ጥያቄ በሚነሳባቸው አካባቢዎች በአማራ ክልል የተመሰረቱ የአስተዳደር እና የፀጥታ መዋቅሮች ይፈርሳሉ።
ከሌሎች አካባቢዎች የመጡ የአማራ ክልል ታጣቂዎች ከአካባቢው የሚወጡ ሲሆን የአካባቢው ተወላጅ የሆኑት ደግሞ እንደታጣቂ ሳይሆን እንደ ነዋሪ መቆየት እንዲችሉ በብሄራዊ ኮሚቴው ስምምነት ተደርሷል።
ከጦርነቱ ተከትሎ የተፈጠሩ የአስተዳደር መዋቅሮች ሲፈርሱ የንብረትና የሰነድ መጥፋት እንዳይኖር መከላከያ ሰራዊት ጉዳዩን ተረክቦ አዲስ ለሚቋቋመው አስተዳደር እንዲያስረክብ ሀለፊነት ተሰጥቶታል።
በዕቅዱ መሰረት ተፈናቃዮች ወደ መኖሪያቸው ከተመለሱ በኃላ ሁሉን ያካተተ የቀበሌ አመራር ምርጫ ይደረጋል። የቀበሌ አመራሮች የወረዳ አመራሮቻቸውን ይመርጣሉ።
የአካባቢው አስተዳደር በምርጫ ከተሰየመ በኃላ የፌደራል መንግስት በጀት እንደሚመድብላቸው ስምምነቱ ያብራራል።
ይህ ከተፈፀመ በኋላ በአመቺ ጊዜና ነባራዊ ሁኔታው ተገምግሞ በአካባቢው ህዝበ ውሳኔ ለማካሄድ ታቅዷል።
የራያ እና ጠለምት አካባቢዎች ጉዳይን በቅድሚያ በመፍታት የወልቃይት ጉዳይ ይህንን ተከትሎ በተመሳሳይ እንዲፈታ ለማድረግ አስፈፃሚ ቡድን ተቋቁሞ ስራውን እንደሚያከናውን ብሄራዊ ኮሚቴው ከስምምነት ደርሷል።
ከሁለቱ ክልልሎች የተውጣጣ ግብረ ሀይል በአፈፃፀሙ ላይ በታዛቢነት የሚሳተፍ ሲሆን ጉድለቶችንና የማሻሻያ ሀሳቦችን በግብረመልስ የሚያቀርብ ይሆናል።
ይህ ስምምነት በተደረስ በቀናት ውስጥ በራያ፡ አላማጣ በኩል የትግራይ ኀይሎች ከአማራ ክልል ሚሊሻ ጋር የተጋጩ ሲሆን ሁለቱ ክልሎች እርስ በርስ እየተወነጃጀሉ ሰንብተዋል።
ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ምንጮች ለዋዜማ እንደነገሩት፣ ይህን ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ሲሆን በቀጣዮቹ ቀናት መፈፀም ይጀምራሉ።
[ዋዜማ]