March 9, 2024
22 mins read

እግዚኦታችን አልሰምር እያለን የተቸገርነው ለምንድን ነው? – ጠገናው ጎሹ

መቸም ሃይማኖታዊ እምነትን ያህል ለስሜት እጅግ ቅርብ (very sensitive) የሆነን ጉዳይ የሂሳዊ አስተያየት ርዕሰ ጉዳይ ማድረግ ለብዙ አማኝ ወገኖች የማይመች ብቻ ሳይሆን ሃጢአትን እንደ መጋበዝ ሆኖ ሊሰማቸው እንደሚችል በሚገባ እገነዘባለሁ። የርዕሰ ጉዳዬ ይዘት (ትርጉም) ለዘመን ጠገቡ እና ከስድስት ዓመታት ወዲህ ደግሞ እንኳን ለማመን ለመስማትም በሚከብድ ሁኔታ ለቀጠለው ፖለቲካ ወለድ ግዙፍና መሪር መከራና ውርደት ከዳረጉን ምክንያቶች አንዱ ይኸው ተግባር አልባ እግዚኦታችን ነውና ለሰማያዊውም ሆነ ለምድራዊው ህይወታችን ጤናማነት የሚበጀንን ሆነንና አድርገን እንገኝ ለማለት እንጅ እውነተኛው አምላክ ለበጎ ነገር የምናስበውንና የምናደርገውን ይባርክልን ዘንድ እግዚኦ ማለት  አያስፈልግም ማለት አለመሆኑ ግልፅ ይሁንልኝ።

እርግጥ ነው በገሃዱ ዓለም ለገጠመን እና እየገጠመን ላለው የመከራና የውርደት ዶፍ ዋነኛ ምክንያት (root cause) የሆነውን የእኩያን ገዥ ቡድኖች ፖለቲካ ሥርዓት በተደራጀና በተቀናጀ ሁኔታ መጋፈጥና እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን አምጠን ለመውለድ ሲሳነን የሰበብ ድሪቶ መደረቱ የሚቀናን በመሆኑ የሃይማኖታዊ እምነት ሃይለ ቃላትንም ከገሃዳዊው ግዙፍና መሪር እውነት እየሸሸን ለመደበቂያነት የመጠቀም (የማዋል) ክፉ አባዜ ከተጠናወተን አያሌ ዘመናት አስቆጥረናል።

በእጅጉ የሚሳዝነው ጉዳይ ደግሞ የሃይማኖት መሪዎችና ሊቃውንት በጎቻቸውን ከነጣቂ ተኩላ መጠበቅ እንደሚኖርባቸው እረኞች ሰብአዊ ማንነታችንና ምንነታችን በሚፈታተን ግዙፍና መሪር እውነታ ዙሪያ ከመዞር አልፈው የእኩይ ፖለቲካ ሥርዓት ዘዋሪዎችን (ጠርናፊዎችን) በግልፅና በቀጥታ ለመገሰፅ የሞራል ልዕልና ሲገዳቸው መታዘብ ነው ። ይህ ህሊናውን የማይረብሸው እውነተኛ ፍትህና ነፃነት ፈላጊ የአገሬ ሰው የሚኖር አይመስለኝም።

እናም እግዚኦታችን የሚፈለገውን ውጤት ያላስገኘልን የፈጣሪ ቁጣ ወይም ያለመታደል ሆኖብን ሳይሆን ሃይማኖታዊ እምነትን ከትክክለኛ እሴትነቱ (ትርጉሙ) እያወረድን የዘልማድ አይነት ድግግሞሽ ስላደረግነውና ይህ ደግሞ ፈጣሪ ከሌላው እንስሳ ሁሉ ለይቶ የረቂቅ አእምሮና የብቁ አካል ባለቤት አድርጎ የፈጠረበትን ዓላማ በአግባቡ ለመወጣት አለመቻላችን ነው የሚያሳየው።

“እግዚኦታችን ሠርቷል እንጅ ለምን አልሠራም?” በሚል ሊሞግቱና ሊያሳምኑ የሚፈልጉ ወገኖች ቁጥር ቀላል እንደማይሆን እረዳለሁ። ይህንን ጥያቄ ለመመለስ ከላይ የገለፅኩትን  በሌላ አገላለፅ እደግመዋለሁ። አዎ! ለዘመናት ከመጣንበትና አሁንም እጅግ አስከፊ በሆነ ሁኔታ ተዘፍቀን የምንገኝበትን እውነታ እና ከተግባር ጋር ያልተገናኘውን እግዚኦታችንን ትክክለኛና ገንቢ በሆነ ፀፀት (ቁጭት) ካላየነውና ከምር ካልመረመርነው በስተቀር መውጫ መንገድ የለንምና በየቤተ እምነቱ በምንሰግደው ስግደት፣ በየአደባባዩና  በየአዳራሹ በምናነበንበው እግዚኦታ፣ በምንዘምረው ዝማሬ፣ በምናሸበሽበው ሽብሸባ፣ በምንለብሳቸው ፀአዳ አልባሳት ፣ በምንቀኘው ቅኔ፣ በምናሿሿው ፀናፅል፣ በምንጎስመው ከበሮ፣ በምንፆመው ፆም፣ በምናዥጎደጉደው ፀሎተ ምህላ፣  ወዘተ ብቻ  ሰማያዊውንም  ሆነ ምድራዊውን ህይወት የተሳካ ማድረግ አይቻለንምና ቆም ብለን ራሳችንን  መጠየቅ ግድ ይለናል ። ከተግባር ውሎ ጋር የተቆራኘ ተማፅኖን/እግዚኦታን  ይበልጥ የመለማመድ ሃይማኖታዊ ማንነት በፈጣሪ አምሳል የተፈጠርንበትን ማንነትና ምንነት ሙሉ ያደርገዋልና።

 

ለሰማያዊውም ሆነ ለምድራዊው የህይወት ስኬታማነት የሚበጅ መፍትሄ መፍጠርና ማበጀት ካለብን የሚከተሉትን ጥያቄዎች ከምር መጋፈጥና መመለስ ይኖርብናል፦ 

·         ለመሆኑ ስንቶቻችን እንሆን በገሃዱም ሆነ በሃይማኖታዊው ዓለም ወይም በሁለቱም ተገቢና መልካም ነው ብለን የምናስበውና የምናደርገው ነገር እንደምናስበውና እንደምናደርገው መሆኑን ወይም አለመሆኑን በአግባቡ በመገምገም የመሆን ወይም ያለመሆኑ (የመሳካት ወይም ያለመሳካቱ) ምክንያት ምን እንደሆነና ማን እንደሆነ ለመረዳት ከምር የሆነ ጥረት የምናደርገው?

·         ስንቶቻችን ነን ያልተሳካው ነገረ ሥራችንን ያልተሳካበትን ምክንያት በትክክል ተረድተን የጎደለውን ለማስተካከል እና የተሳካውን ደግሞ ይበልጥ የተሳካ ለማድረግ ተገቢና ወቅታዊ ጥረት የምናደርገው?

·         ስንቶቻችን ነን ደጋግመን የወደቅንበትን መሠረታዊ ምክንያት በቅጡና በቅንነት አጢነን የራሳችንን ሃላፊነት ከመውሰድና ተገቢውን ከማድረግ ይልቅ ሁሉን ነገር የፈጣሪ ቁጣና ቅጣት እያደረግን (ድርጊት አልባ እግዚኦታ እያስተጋባን) ፈጣሪን ጨምረን የገዛ ራሳችን አስከፊ የውድቀት አካል በሚያደርግ አስቀያሚ አስተሳሰብ ውስጥ የምንቦጫረቅ?

·         ስንቶቹ የሃይማኖት መሪዎችና ሰባኪዎች ናቸው የፀሎትን (ለተደረገልን የማመስገንና መልካሙ ነገር እንዲደረግልን የመጠየቅን) ፣የፆምን (የሥጋ ፍላጎትን የመቆጣጠርና ለጤናማ ህሊና ተገዥ የማድረግን) ፣ የምህላን (እግዚኦ መሃረነ/አድነነ ብሎ የመማፀንን) ፣ የንስሃን (ከልብ ተፀፅቶ ከስህተት የመመለስን) ፣ ወዘተ ወርቃማ ሃይማኖታዊ እሴት ከተግባር አልባ መነባንብ ባለፈ በአርአያነት (ሠርቶ የማሠራት መሪነት) የሚነግሩን/የሚያስተምሩን/የሚያሳውቁን?

·         በአንድ በኩል እጆቻቸው በንፁሃን ደም ከጨቀዩ የቤተ መንግሥት ፖለቲከኞች ጋር እየተሻሹ እና በሌላ በኩል ግን ስለ ፆም፣ ስለ ፀሎት፣ ስለ ምህላ፣ ስለ ንስሃ፣ ስለ ፍቅር፣ ስለ ፍትህ እና ስለ ሰላም የሚሰብኩንን የሃይማኖት መሪዎችና ሰባኪዎች ተሳስታችኋልና ንስሃ ገብታችሁ በአርአያነት አደባባይ ላይ ተገኙ ብሎ እቅጩን መንገርና መነጋገር ለምንና እንዴት ተሳነንበእውን በዚህስ የሚቀየም እውነተኛ አምላክ አለ እንዴ?

·         ለመግለፅ የሚያስቸግር ፖለቲካ ወለድ የመከራና የውርደት ዶፍ እያወረዱ እግዚኦ ከሚያሰኙን ወንጀለኛ ፖለቲከኞች ጋር እየተሻሹ “እግዚኦ በሉ” ማለት ምን የሚሉት የሃይማኖት መሪነትና ሰባኪነት ነው?

·         የሩብ ምዕተ ዓመቱ ህወሃት መራሽ ፖለቲካ ወልዶ ያሳደገው የጎሳ አጥንት ስሌት አገዛዝና ከአስድስት ዓመታት ወዲህ ደግሞ በተረኛ ኦሮሙማዊያን/ብልፅግናዊያን ጠርናፊነት ተሰምቶና ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የመከራና የውርደት ዶፍ ማውረዱን በቀጠለበት በዚህ ወቅት የሃይማኖታዊ እምነት መሪነት ሃላፊነታቸውን ውድቀት አምነው በመቀበል ክፉ ገዥዎችን በአግባቡ ለመገሰፅ የሞራል ከፍታ የተሳናቸውን የሃይማኖት መሪዎች፣ ሊቃውንትና ሰባኪዎች በአግባቡ ተጠየቁ ማለት ለምንና እንዴት ሃጢአትና ድፍረት ይሆናል?

·         ሸፍጠኛና ጨካኝ ገዥዎችን በግልፅና በአግባቡ ለመገሰፅ በቃላት መረጣ የሚጨነቁ የሃይማኖት መሪዎች ክርስቶስ የህይወት መስዋእትነት ለመክፈል የሚያስችለውን መሪር ተግባር እያሰበና ለዚያም እየተዘጋጀ ስለ ፆመው ዓቢይ ፆም ባስተላለፉት መልእክታቸው መከረኛውንና የዋሁን አማኝ  “ባለመፆምህና እግዚኦ ባለማለት ነው መከራህ የበዛው” ሲሉት “ምነው ከምትነግሩን (ከምትሰብኩን) ሆናችሁና አድርጋችሁ ብታሳዩኝ (show me, do not just tell me)” ቢባሉ ድፍረት ይሆናል እንዴ?

 

·         የቤተ ክርስትያኗ የሃይማኖት “አባቶች” ወይም “አባላት”ነን ያሉ እጅግ ጨካኝ ወገኖች  የሃጢአት ማምረቻ፣ ማከፋፈያ ፣ ገዳይና አስገዳይ የሆነውን የቤተ መንግሥት ፖለቲካ ጠርናፊ (አብይ አህመድን) በቅኔ እያንቆለጳጰሱ እና በመስቀሉ እያማተቡ ሲያሞካሹት “የመከረኛ ንፁሃን ነፍሶች ይጮሃሉና ነውር ነው” ለማለት ያልደፈረ የሃይማኖት መሪ ስለ ምን አይነት ፆም፣ ፀሎት፣ ምህላና ፅድቅ እየነገረን እንደሆነ ለመረዳት አይከብድም እንዴ?

 

·          መከረኛው (ጦም አዳሪውና የገዥዎች ግፍ ሰለባ የሆነው) የአገሬ ህዝብ ከሌላው የዓለም ህዝብ በተለየ ሃጢአተኛ ይመስል ፖለቲካ ወለድ መከራና ውርደት ሰለባ የሆነው በሃጢአቱ ብዛት እንደሆነ መስበክ ምን የሚሉት የሃይማኖት መሪነትና ሊቅነት ነው?

 

·         የገዛ ራሳችንን እጅግ አስቀያሚ የውድቀት አዙሪት በነፃነት ጥረንና ግረን እንኖር ዘንድ በራሱ አምሳል በፈጠረን እውነተኛ አምላክ ማላከክ ምን የሚሉት የሃይማኖት አባትነትና ሰባኪነት ነው?

 

·         መከረኛውን ህዝብ ለጦርነት፣ ለርሃብና ለበሽታ የዳረጉት ሴረኛና ጨካኝ ገዥዎች መሆናቸው እየታወቀ ለይቶ መገሰፅ ሲገባ በደምሳሳው አካላት ወይም ወገኖች ወይም ሁሉም ተፋላሚዎች ፣ ወዘተ በሚል የሰለቸ መግለጫ ማሰራጨትን እንደ ታላቅ ሃይማኖታዊ መሪነት ተልእኮ መቁጠር እንኳንስ ሰማያዊ ምድራዊ ወንዝን እንዴት ሊያሻግር ይችላል?

 

“ፆም ስለሆነ የህልውና፣ የነፃነትና የፍትህ ተጋድሎ ማድረጉን አቁሙና የገዳዮችና የአስገዳዮች መጫወቻ ሁኑ” የሚል አይነት እጅግ የወረደና አዋራጅ ሰባኪነትን እንኳን ለመቀበል ለመስማት አይከብድም/አያምም እንዴ?  እንዲህ አይነቱን ሰንካላ ምክንያት ባርኮ የሚቀበል እውነተኛ ፈጣሪስ አለ እንዴ? በጨካኝ ገዥ ቡድኖች ጨካኝ ሰይፍ እንደ ጎርፍ የሚወርደውን የንፁሃን ደም ከመታደግ የበለጠ ምን አይነት የፅድቅ  አርበኝነት አለና ነው “ለፆም ስትል እጅህን አጣጥፈህ ተቀመጥና የሬሳ ክምርህን ‘በክብር’ ወደ አፈር ለመመለስ ተዘጋጅ፤ እናም ትፀድቃለህ” ማለት ምን የሚሉት ሃይማኖታዊ ሰብእና ነው?

የሰው ልጅ ከሌሎች እንስሳት ተለይቶ ከማሰቢያ ረቂቅ አእምሮና ከብቁ አካል ጋር ከተፈጠረባቸው ዓላማዎች (ምክንያቶች) አንዱ ትናንት የመጣበትን ፍኖተ ህይወት (የአስተሳሰብና  የተግባር ሂደት)  ቆም እያለ ከምር በመመርመር አወንታዊ ጎኖችን ይበልጥ በማጎልበት (በማጠናከር) እና አሉታዊ ጎኖችን ደግሞ ወደ አወንታዊነት በመለወጥ የተሻለ ነገንና  በእጅጉ የተሻለ ከነገ ወዲያን እውን ለማድረግ የሚጥር መሆኑን ለመረዳት የሊቅነት ወይም የሊቀ ሊቃውንትነት እውቀትን አይጠይቅም ።

ይህ መሠረታዊ እሳቤ ደግሞ ከዓለማዊው ብቻ ሳይሆን ከሃይማኖታዊ (ከመንፈሳዊ) እምነትና ተግባር ጋር በጥብቅ የተያያዘ (የተቆራኘ) ነው። ለምን? ቢባል የየራሳቸው የሆነና አንዱ የሌላውኛውን መሠረታዊ ተልእኮ፣ ዓላማና አሠራር መስመርን አልፎ አላሰፈላጊ ጣልቃ ገብነት ማድረግ የለበትም የሚለው መርህና ህግ እንደ ተጠበቀ ሆኖ ሁለቱም ከሰው ልጅ (ከማህበረሰብ) ሁለንተናዊ መስተጋብር ውጭ የሚታሰቡ አይደለምና ነው።

አዎ! ከሞት በኋላ ተስፋ የምናደርገው ህይወት የሚወሰነው በዚሁ ሁለገብ በሆነው ማህበረሰባዊ መስተጋብር ምንነት፣ለምንነት፣ እንዴትነት፣ እና ከየት ወደ የትነት እንጅ በአየር ላይ በሚንሳፈፍ አንዳች አይነት የማይጨበጥ መንፈስ ወይም ተአምር አይደለም። ይህንን ደግሞ አምላክ በክርስቶስ አማካኝነት ሥጋ ለብሶ በመወለድ፣ በማስተማር፣ በጥምቀት አማካኝነት ራሱን ገልጦ በማሳየት፣ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ በመሞት (ለእውነት፣ ለፍትህ ፣ ለፍቅርና ለሰላም ዋጋ በመክፈል) እና በመጨረሻም ሞትን አሸንፎ በመነሳት (የእውነትን፣ የፍትህን፣ የፍቅርንና የሰላምን አሸናፊነት በማረጋገጥ) አሳይቶናል።

በእውነት ስለ እውነት ከተነጋገርን አሁን ለምንገኝበት በእጅጉ ግዙፍና አስከፊ ለሆነ ሁለንተናዊ መከራና ውርደት የተዳረግነው ድንገተኛና ማስቀረት የማንችለው ፈተና ሆኖብን አይደለም። አለመታደል ወይም ከሌላው ህዝበ አዳምና ሔዋን በተለየ ሃጢአተኞች በመሆናችን ፈጣሪ በማያቋርጥ ቅጣት ሊቀጣን ስለ ፈለገም አይደለም።

አዎ እውነት ነው በማነኛውም የፖለቲካ ማህበረሰብ የእድገት ሂደት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ጉልህ ስህተቶች እኛንም ያጋጠሙን የመሆኑ እውነትነት እንደ ተጠበቀ ሆኖ የረጅም ጊዜ አኩሪ የአገርነትና የሃይማኖት ታሪክ ባለቤቶች መሆናችንን ለማስተባበልና ለማጣጣል የሚፈልጉት የውጭ ትምክህተኛ ሃይሎች ብቻ ሳይሆኑ በዋናነት በገዛ ውድቀታችን ምክንያት ወደ የጎሳና የመንደር ማህበረሰብነት ያወረዱን  ገዥ ቡድኖችና ግብረ በላዎቻቸው ናቸው።

ከዚህ ሁሉ የሚከፋው ግን የንፁሃን የምድራዊውም ሆነ የሰማያዊ ህይወት የተሳካ ይሆን ዘንድ (የሰማያዊ ህይወት የሚወሰነው በምድራዊ ሥራ በመሆኑ ሁለቱ የሚነጣጠሉ አለመሆናቸው ሳይረሳ) ተልእኮና ሃላፊነት የተጣለባቸው የሃይማኖት ተቋማት በደካማ መሪዎች ምክንያት የፖለቲካ ወለድ ወንጀል ሰለባ የመሆናቸው መሪር እውነት ነው።

ከዚህ በእጅጉ ከተመሰቃቀለና አስከፊ ከሆነ ፖለቲካ ወለድ አዙሪት መውጫው መንገድ አንድና አንድ ብቻ ነው። ህልውና ፣ ነፃነት፣ ፍትህ፣ እኩልነት፣ መተሳሰብ፣ ሰላም፣ እና የጋራ ሥልጣኔና እድገት ለሚረጋገጥባት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እውን መሆን እልህ አስጨራሽ ተጋድሎ በማካሄድ ላይ ለሚገኙ ወገኖች ሁለገብ ድጋፍ ከማድረግ ውጭ የሚኖረው አማራጭ የመቃብር ውስጥ እና የቁም ሙትትነት መቀበል ነው።

ምርጫችን የመጀመሪያው እንደሚሆን ያለኝን ተስፋ እየገለፅሁ አበቃሁ!

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ¹⁵ የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ ፥ ¹⁶ ተራራዎችንና   በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን ፤ ¹⁷ ታላቁ የቁጣው ቀን  መጥቶአልና ፥ ማንስ ሊቆም ይችላል ? አሉአቸው ። ራእይ 6 ፤  15_17 ይኽ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ። የኢየሱስን ልደት ሰናከብር የየሐንስ ራእይን ማንበብ ጠቃሚ ይመስለኛል ። ምክንያቱም በመጨረሻው ዘመን

ከኢየሱስ የፍርድ ቀን በፊት በህሊናችን ውስጥ ፍቅርን ለማንገስ እንጣር 

የምጣኔ ሀብታዊ ፍጥ፣ የፖለቲካ፣ የእውነትና የሰብአዊ መብት ታጋይ፣ የአመኑበትን ነገር ለመናገር እንደ ፖለቲከኛ በቃላት ሳያሽሞነሙኑ ቀጥታ የሚናገሩት የሀገሬ ኢትዮጵያ ታላቅ ሰው ነበሩ “ዘር ቆጠራውን ተዉት፤ የአባቶቻችሁን ሀገር ኢትዮጵያን አክብሩ!”  አቶ ቡልቻ ደመቅሳ

ሀገር ወዳዱ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ

January 6, 2025
ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። ) “ገብርዬ ነበረ

ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ?

January 3, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ዛሬ እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር ጥር 1ቀን 2025 ዓ/ም ነው ። አውሮፓውያኑ አዲስ ዓመትን “ሀ” ብለው ጀምረዋል ። አዲሱን ዓመት ሲጀምሩም ከልክ ባለፈ ፈንጠዚያ ነው ። ርቺቱ ፣ ምጉቡና መጠጡ

ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። )

Go toTop