March 9, 2024
3 mins read

በሬ ሆይ! – በላይነህ አባተ

Bere Hoyየዚች ዓለም ተንኮል ቁማሯ ተገባህ፣
ለቅዱሳን ሲኦል ለእርኩሳን ገነት ናት፡፡

ስለዚህ ተምድር እንዳይጠፋ ዘርህ፣
በጋማ ከብት መሐል ቅዱስ መሆን ይብቃህ፡፡

ዘርጥጦ ሊጥልህ ሊሰብር ወርችህን፣
ታመህ በረት ስትውል ሊግጥም ሜዳውን፣
ጉድጓዱን ሸፍኖ እያሳዬ ሙጃን፣
ስንቴ አንዘላዘለህ የጋማ ከብት አንተን?

በተስፋ እየሞሉ የማትደርስበትን እያሳዩ ሳሩን፣
ገደል ውስጥ ወርውረው ሊያጠፉት ዘርህን፣
መሸወድ ሰልችቶህ ሁልጊዜ ጅል መሆን፣
እንደ አንበሳ አግስተህ መች ትነሳ ይሆን!

አትንኩኝ ስላላልክ ቀንድህን ቀስረህ፣
ስላልተከላከልክ ሻኛህን ቦጅረህ፣
አለሌ አህያ እንኳን አለወግ ሰልሎህ፣
በተጋደምክበት ፋንድያ ጣለብህ፣
ያን ስትታገስም በእርግጫ አፈነዳህ፡፡

በሬ ሆይ!

አህዮች መጋዦች ተመስክ ጥፋ ያሉህ፣
ቅኔህንም ዘርፈው ተቆዳ ብራናህ፣
“በሬ ሳር ታሳዩት ገደል አይታየው” ብለው ሲስቁብህ፣
ሱርፍ ብሎብህ ምነው እንደ ኮርማ እምቡ አለማግሳትህ?

ቀንበር ጫንቃህ ጥለው ሂድ እረስ የሚሉህ፣
አቅምህ ደከም ሲልም አርደው የሚበሉህ፣
የቱ ተስፋ ታይቶህ ተበረት ታድራለህ፣
ጭልጥ በል እንጅ የዱር አውሬ ሆነህ!

በሬ ሆይ!

በእርሻ በጥበብህ ምርትን ስለቀመስክ፣
እንክርዳድ የሚቅም አህያ ቀንቶብህ፣
ተጅብ ሳይቀር መክሯል ተምድር ሊያጠፋህ፡፡

በሚለው ብሂሉ ተሞትኩ ሰርዶ አይብቀል፣
አንተን ተበላለት ታጠፋህ ተምድር፣
መቀመጫ ታፋን ለጅብ ይገብራል፡፡

በሬ ሆይ!

የዚህ ዓለም ነገር ተገባህ ምስጢሩ፣
እናት ደግ አትወድም እንኳን ሥም አይጠሩ፡፡

በዚህ እርጉም ምድር ሰይጣን በሚገዛት፣
ቅዱስ ፍጡር ሆኖ እንደ አንተ መገኘት፣
እንደ ጳውሎስ ጴጥሮስ ዘቅዝቆ ያሳርድ፡፡

ስለዚህ በሬ ሆይ ቅዱስ መሆን አቁም፣
ሸኮናህን ድፈን አውጣ የላይ ጥርስም፣
አንበሳ ነብር ሁን ይጥራህ ጫካው ዱሩም፣
አህያ መጋፋት መራገጥ እንዲያቆም፡፡

በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)
መጋቢት ሁለት ሺ አስራ አምስት ዓ.ም.
እንደገና መጋቢት ሁለት ሺ አስራ ስድስት ዓ.ም.

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop