የኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴ እና የ1966ቱ ሕዝባዊ አብዮት ክፍል -፪-

በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን)

(ለሪፖርተር ጋዜጣ እንደጻፈው)

  1. የኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴ እ.ኤ.አ ከ 1916-1960

‹‹ፋኖ ተሰማራ፣

ፋኖ ተሰማራ፣

እንደ ሆቺሚኒ እንደ ቼጉቬራ፣

ትግሉን እንድትመራ …፤››

(የለውጥ አራማጅ ተማሪዎች ይዘመሩ ከነበሩ አብዮታዊ/ሕዝባዊ መዝሙሮች አንዱ)

የዩኔስኮው የአፍሪካ ተማሪዎችን እንቅስቃሴ የፖለቲካ፤ ታሪክ በሚያትተው የዳጎሰ ጥራዝ ውስጥ የኢትዮጵያን ተማሪዎችንና ምሁራንን እንቅስቃሴ በተመለከተ፤ ‹‹Class Struggle or Jockeying for Position? A Review of Ethiopian Student Movement from 1900 to 1975›› ጥናታቸውን ያቀረቡት የብፅአት ክፍለሥላሴ፤

እ.ኤ.አ. ከ1916 እስከ 1960 ያለውን ጊዜ በሚሸፍነው የኢትዮጵያን ተማሪዎችንና ምሁራንን የለውጥ እንቅስቃሴ ወደፊት እንዲራመድና እንዲያድግ ያደረገው የአልጋ ወራሽ በኋላም ቀዳማዊ ዐፄ ኃይለሥላሴ በሚል ወደ ንግሥናው መንበር የመጡት የተፈሪ መኮንን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ አንድምታ ያላቸው ርምጃዎቻቸው እንደሆነ ያስመሩበታል፡፡

ከእነዚህም ርምጃዎች መካከል ገና ንጉሠ ነገሥቱ አልጋ ወራሽ በነበሩበት ጊዜ ዘመናዊ ትምህርት ቤቶች እንዲስፋፉ በማድረግ የተጫወቱት ሚና የሚጠቀስ ነው፡፡ ትምህርት ቤቶች ከመክፈት ጀምሮ በየክፍለ ግዛቱ ለተለያዩ ጉዳዮች በሚጓዙበት ጊዜ ልጆችን ወደ መናገሻ ከተማቸው በማምጣት ዘመናዊ ትምህርት እንዲማሩ ያደረጉ ነበር፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ንጉሡ በርካታ ተማሪዎችን ወደ ውጭ አገር በተለይም ደግሞ ወደ ካይሮ፣ ፈረንሳይ፣ እንግሊዝና አሜሪካ በመላክ ዕውቀት ቀስመው እንዲመለሱ አድርገዋል፡፡

ኢትዮጵያ ካላት የረጅም/የሺሕ ዘመናት ታሪክ፣ ገናና ሥልጣኔና ባህል አንጻር በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተሰሚነትና ስፍራ እንዲኖራት በማድረግ ረገድ ኢትዮጵያን ‹የሊግ ኦፍ ኔሽን› አባል አገር እንድትሆን በማድረግ አገራችንን ወደ ዓለም አቀፉ የዲፕሎማሲ መድረክ አስገብተዋታል፡፡ በተጨማሪም ንጉሡ ነገሥቱ የዛን ጊዜዋ ኢትዮጵያ የዘመናዊነትና የዕድገት መሰላል ላይ መወጣጣት እንድትጀምር በማድረግ የተሳካና ውጤታማ ሊባል የሚችል መሻሻሎችን አድርገዋል፡፡

ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጋር መቀላቀል የጀመረችው ኢትዮጵያ ወጣት ልጆቿም ወደ ምዕራቡ ዓለምና አሜሪካ በመጓዝ ዘመናዊ ትምህርትን ብቻ ሳይሆን ያሉበትን አገር ዘመናዊ አኗኗር፣ የፖለቲካ ሂደት፣ ሥልጣኔና ዕድገት በአገራቸውም ዕውን እንዲሆን በብርቱ መመኘት ብቻ ሳይሆን ይበጃል በሚሉት መንገድ መሰባሰብና መደራጀት ጀምረው ነበር፡፡

ከዓለም ሁሉ ቀድማ የነቃችውና ከግሪክ፣ ከሮማ፣ ከፋርስና ከቻይና ጥንታዊ፣ ኃያልና ገናና ሥልጣኔዎች ጋር ስሟ በክብር ሲጠቀስ የነበረች አገራቸው የገባችበት የድኅነትና የጉስቁልና እንቅልፍ፣ የኋላ ቀርነት ድብታ እንቆቅልሽ የሆነባቸው የዛን ጊዜዋ ኢትዮጵያውያን የውጭ አገር ተማሪዎችና ምሁራን ማኅበር በማቋቋም ለእናት አገራቸው የበኩላቸውንና የሚችሉትን ያህል ድጋፍ ለማድረግ እንቅስቃሴ ማድረግ ጀመሩ፡፡

የብፅአት የዩኔስኮ የጥናት ጥራዝ እንደሚያትተው፤ እ.ኤ.አ በ1920ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ በፈረንሳይ አገር ባሉ ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ የሚማሩ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች በወቅቱ በቅዱስ ሲሪል ወታደራዊ ተቋም በሚማረው በአየለ ስብሐት አማካኝነት፣ ‹‹የኢትዮጵያ ተማሪዎች የመረዳጃ ማኅበረ በፈረንሳይ›› የሚል ማኅበር አቋቋሙ፡፡ ይህ ማኅበር የተቋቋመው በአብዛኛው የቆየውን የኢትዮጵያውያንን የመረዳዳትና የመተጋገዝ ባህል በባዕድ አገርም ጸንቶ እንዲቆይ በማለም ላይ ነበር፡፡

‹‹ይህ እምብዛም ፖለቲካዊ መሠረት ያልነበረው በፈረንሳይ የኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ማኅበር በወቅቱ በኢትዮጵያ ውስጥ ከነበሩት አካባቢ ዕድሮች ተርታ የሚመደብ፣ በይበልጥ ማኅበራዊ እንጂ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መሠረት ያልነበረው ነበር፤›› ሲሉ ነው ብፅአት በጥናታቸው የገለጹት፡፡ ስለሆነም ይላሉ እኚሁ ምሁር፤

ተጨማሪ ያንብቡ:  የጭለማ ዘመን ከኢትዮጵያ ማህጸን ደጋግሞ የመፍለቁ ሚስጢር ምን ይሆን?

‹‹ይህ ማኅበር አገሪቱ በፋሽሰት ኢጣሊያ በተወረረች ጊዜ ለፈረንሳይ መንግሥትም ሆነ ሕዝብ ስለ ግፍ ወረራው በሚገባ በመግለጽም ፈረንሳይና ፈረንሳውያን ከኢትዮጵያ ጎን እንድትቆም ማድረግ አለመቻላቸውን፤›› ይገልጻሉ፡፡ ለዚህ እንደ ምክንያትነት ሊጠቀስ የሚችለው ደግሞ በወቅቱ ለዚህ የተማሪዎቹ ኅብረት ፖለቲካዊ ምሪትና ኃይል የሚሰጠው የተደራጀ፣ የነቃ ግለሰብም ሆነ ድርጅት አለመኖሩ ነው ማለት ይቻላል፡፡

 

  1. ተማሪዎች እና የምሁራን እንቅስቃሴ በዘመነ ፋሽስት

ይሁን እንጂ በፋሽስት ወረራ ወቅት በማኅበር በተደራጀ መልኩም ባይሆን ስለ ኢትዮጵያ ነጻነት፣ አንድነት፣ ዘመናዊ ፖለቲካዊ አሥተዳደርና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት በግላቸው ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ያሰሙና በብርቱ ይታገሉ የነበሩ በውጭ አገር የሚማሩ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ምሁራን እንደነበሩ የታሪክ ድርሳናት ይጠቁማሉ፡፡

ከእነዚህም መካከል ስማቸው ጎልቶ የሚጠቀሱት የውጭ አገር ትምህርታቸውን ግብፅ አሌክሳንደሪያ በሚገኘው የፈረንሳይ ትምህርት ቤት አሐዱ ያሉትና ከፍተኛ የሕግ ትምህርታቸውን በአውሮፓዊቷ አገር በፈረንሳይ/ፓሪስ የተማሩት በሳሉ ኢትዮጵያዊው ዲፕሎማትና ምሁር አቶ አክሊሉ ሀብተ ወልድ ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ በፋሽስት ወረራ ስር በቆየችባቸው ጊዜያት ውስጥ ወጣቱ ምሁርና ዲፕሎማት አክሊሉ ሀብተ ወልድ በፈረንሳይ አገር ‹‹ኑቪል ዲ ኢትዮጵያ/የኢትጵያ ዜና›› በሚል በሚያሳትሙት ጋዜጣ የፋሽስቱን ኢሰብአዊ ግፍና ጭፍጨፋ ለፈረንሳይና ለመላው ዓለም በማሳወቅ ታላቅ የሆነ የዐርበኝነት ሥራ ፈጽመዋል፡፡

በተመሳሳይም በአገር ቤትም የሥነ ጥበብ ትምህርታቸውን በፈረንሳይ አገር የተከታተሉት ሰዓሊ አቶ አገኘሁ እንግዳ ከዕውቁ ገጣሚና ጸሐፊ ተውኔት ዮፍታሔ ንጉሤ ጋር በመሆን ስለ ኢትዮጵያ ነጻነት፣ አንድነትና ልዑላዊነት በጥበብ ሥራዎቻቸው አብዘተው የሰበኩና የተጋደሉ ዐርበኞች ነበሩ፡፡ እነዚህ ሁለት ኢትዮጵያውያን ምሁራንና ዐርበኞች በጠላት ፋሽስት ወረራ ጊዜም በዚሁ ፀረ-ፋሽስት እንቅስቃሴያቸው የተነሳ ለስደትና ለመከራ ተዳርገው ነበር፡፡

በአገሪቱ እያበበ የመጣውን የዘመናዊ ትምህርት ዕድገት፣ ሥልጣኔና የመሻሻል ርምጃዎች ያደናቀፈው 1928ቱ የፋሽስት ኢጣሊያ ወረራ፣ ተማሪዎች እስከ አራተኛ ክፍል ብቻ እንዲማሩ የሚያሰገድደው የፋሽስቱ ሕግ በአገሪቱ እየጎመራ የነበረውን የዘመናዊ ትምህርት ቡቃያ በአጭሩ እንዲቀጭና ወደኋላ እንዲመለስ አደረገው፡፡ በዘመኑ የተማሩ የነበሩት አንዳንድ ኢትዮጵያውያንም- ‹‹አንድም አገራችን ካለችበት የዘመናት የማሃይምነትና የኋላ ቀርነት ሲኦላዊ ቅርቃር ውስጥ ለመውጣት ከኢጣሊያኖቹ ጋር ተባብረን ብንሠራ ይሻላል፤›› በሚል ሰልፋቸውን ከፋሽስቱ ወራሪ ኃይል ጋር አድርገው ነበር፡፡

የተቀሩት ምሁራን ደግሞ፤ ‹‹በምዕራባውያን ዘመናዊነትና ሥልጣኔ ስም በነጻነታችንና በልዑላዊነታችን ላይ ፈጽሞ ድርድር አይኖርም፤›› በማለት ለነጻነት ትግሉ ክንዳቸውን በማንሳት ወደ ዐርበኞች ጎራ ተቀላቀሉ፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥም ታሪክ መዛግብትን ስንፈትሽ- የተደራጀ መልክ ያለው የተቃዋሚ ኃይል ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ያቆጠቆጠው በጣሊያን ወረራ ጊዜ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ እናም አገር ወዳድና ነጻነታቸውን አፍቃሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎችና ምሁራን ተሰባስበው የዐርበኞችን እንቅስቃሴ መሠረቱ፡፡ እነዚሁ ምሁራን ዐርበኞች ‹‹ዱር ቤቴ›› ብለው በዱር በገደል ለሚዋደቁት ኢትዮጵያውያን ዐርበኞች ከፍተኛ የሆነ ድጋፍና እገዛ አድርገዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብና ዐርበኞች በውስጥና በውጭ ለነጻነታቸው የጀመሩትን እንቅስቃሴና ተጋድሎ ሞራል በመስጠት ተጋግሎ እንዲቀጥል ለማድረግና የፋሽስቱን የሞሶሊንን ወረራና ኢ-ሰብአዊ የሆነ አሰቃቂ ግፍና ጭፍጨፋ ዓለም እንዲያውቀው በማሰብ በ1920ዎቹ በቱርክ መንግሥት የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ/እልቂት ምክንያት ተሰደው ወደ ኢትዮጵያ ከገቡት አርመናውያን መካከል አንዱ በነበሩት በአቶ ዮሐንስ ስማርጂባሽን አዘጋጅነት ይታተም የነበረው ‹‹የኢትዮጵያ ዓውደ ልሳን›› ጋዜጣ ይጠቀሳል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  [የሃረሩ እሳት ቃጠሎ ጉዳይ] - የእሳት ፖለቲካ በኢትዮጵያ (Fire Politics in Ethiopia) - ይሄይስ አእምሮ

በተጨማሪም በብላታ ኪ/ማርያም ይመራ የነበረው፤ ‹የኢትዮጵያ ወጣቶች ንቅናቄ› በአሜሪካ አገር በነበረው በዶ/ር መላኩ በያን፣ በሆለታ ገነት ጦር ትምህርት ቤት ኢትዮጵያውያን መኮንንኖች፣ ምሁራንና ተማሪዎች የተቋቋመው ‹የጥቁር አንበሳ› ድርጅትም የነጻነቱን እንቅስቃሴ ወደሌላ ምዕራፍ ያሻገሩ እንቅስቃሴዎች ነበሩ፡፡

እነዚህ የፖለቲካ ቡድኖች የኢትዮጵያ ሕዝብ የፋሽስት ኢጣሊያንን ወረራ አጥብቆ እንዲታገል ላደረጋቸው እንቅስቃሴዎችና ተጋድሎዎች በርካታ በአገር ውስጥና በውጭ አገር ያሉ ኢትጵያውያን ምሁራንን፣ ዐርበኞችንና ወታደሮችን ሊያነሳሱ ችለው ነበር፡፡

እነዚህ የተቃውሞ ትግሎች ካፈራቸው ተወዳጅና ስመ-ጥር ገጣሚዎች መካከልም የጥቁር አንበሳው ዮፍታሔ ንጉሤን ማነሳት ይቻላል፡፡ በተለይ በርካታ ኢትዮጵያውያን ምሁራንን፣ እንዲሁም አፍቃሪ ኢትዮጵያውያን የሆኑ ጥቂት የውጭ አገር ምሁራንን፣ የሆለታ ገነት ጦር ትምህርት ቤት ምሩቃንና ተማሪዎችን ያቀፈው ጥቁር አንበሳ ቡድን፣ ‹‹ከነጻነት በኋላ በሕዝቡ የተመረጠ መንግሥት ይቋቋም!›› የሚል ጥሪ እስከማሰማት ደርሰው እንደነበር የታሪክ ምሁሩ ባሕሩ ዘውዴ (ፕሮፌሰር) ጽፈዋል፡፡

በዚህ የፀረ-ፋሽስት ትግል የምሁራን እንቅስቃሴ አካል እንደሆነ በሚጠቀሰው በኤርትራውያኑ ወጣቶች አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስግዶም፣ (አብርሃ የተፈሪ መኮንን፣ ሞገስ አስግዶም ደግሞ የዳግማዊ ምኒልከ ትምህርት ቤት ፍሬዎች እንደነበሩ ልብ ይሏል) በኢጣሊያዊው ጄኔራል በግራዚያኒ ላይ ባደረጉት የግድያ ሙከራ ተሳቦ በርካታ ኢትዮጵያውያን  ምሁራን እንዲገደሉና እንዲጋዙ ተደረገ፡፡ በዚህ ሠላሳ ሺሕ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ባለቁበት ዘግናኝ ጭፍጨፋ አገሪቱን ምሁር አልባ አደረጋት፡፡

ከአምስት ዓመት የኢጣሊያን ወረራ በኋላ በኢትዮጵያውያን ዐርበኞች ታላቅ ጀግንነትና ተጋድሎ፣ በቀዳማዊ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ያላሰለሰ ዲፕሎማሲያዊ ጥረትና በእንግሊዛውያን ዕርዳታ ነጻነቷን የተጎናጸፈችው ኢትዮጵያ በአፍሪካና በዓለም መድረክ ዳግመኛ የነጻነት፣ የጀግንነትና የአይበገሬነት ጽናት ምልክት ሆና ብቅ አለች፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ‹ከአምስቱ ዓመት የኢጣሊያ ወረራ› በኋላ በዐርበኞቿ ተጋድሎ ዳግመኛ ነጻነቷን በእጇ ያስገባችው ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ቀንበርና በባርነት ስር ሲማቅቁ ለነበሩ የአፍሪካ፣ የላቲንና የእስያ አገሮች የነጻነት ተጋድሎ ምልክትና ተምሳሌት ሆና መጠቀስ ጀመረች፡፡

የቻይናው ዕውቁ ኮሚኒስት አብዮተኛና ‹‹የቻይና ሕዝባዊ ሪፐብሊክ አባት›› ተብሎ የሚጠራው ማኦ ዜዱንግ/ሴቱንግ፣ ኢትዮጵያውያን ለነጻነታቸው ያደረጉትን እልህ አስጨራሽ ፍልሚያና ተጋድሎ በተመለከተ ሲናገር፤

‹‹the Ethiopian resistance also became Mao Zedong points out, symbol of the struggle of the oppressed people of Asia.›› በማለት በጭቆና ስር ሆነው ለሚማቅቁ የእስያ ሕዝቦች የኢትጵያውያን የፀረ-ፋሽስት የነጻነት ተጋድሎ ልዩ ምልክትና መስሕብ መሆኑን መስክሯል፡፡

እንዲሁም በተመሳሳይም ፍሬይድ ሃሊዴይና ማክሲን የተባሉ ምዕራባውያን ምሁራኖች፤ ‹‹The Ethiopian Revolution›› በሚለው መጽሐፋቸው ውስጥ ተመሳሳይ የሆነ አሳባቸውን እንደሚከተለው በማለት አስፍረዋል፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ የረጅም ዘመናት ታሪክና አንጸባራቂ ሆነ የነጻነት ተጋድሎ እንቅስቃሴ በዓለም ሕዝቦች ነጻነት እንቅስቃሴና ንቅናቄ ላይ ከፍተኛ የሆነ መነቃቃትና መስህብነትን ፈጥሯል፡፡›› በዚህ የነጻነት መንፈስ ነበር በመላው አፍሪካ የተነሡ እንቅስቃሴዎችና የፀረ-ቅኝ ግዛት ንቅናቄዎች ለፍሬ በቅተው የአፍሪካ አገራት ነጻነታቸውን ለመቀዳጀት የበቁት፡፡

የአርነት ተጋድሎ ማዕበል ያጥለቀለቃት አኅጉረ አፍሪካ ከመቅጽበት ለአውሮፓውያን የቅኝ አገዛዝ ድንገተኛ መቅሰፍት ሆነች፡፡ አያሌ አፍሪካውያን አገራት ነጻነታቸውን በመቀዳጀታቸው በፌሽታና በፈንጠዝያ ተዋጡ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ግንጊልቻ (Gingilchaa)- የጠቅላዩ የፓርላማ ውሎ ትዝብት... በ-ሙሉዓለም ገ/መድኀን 

ከዚሁ አኅጉራዊ ሁካታና ጫጫታ ተገልላና የፖለቲካ እርካታ ደሴት መስላ የተቀመጠችው ኢትዮጵያ፣ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ከዚህ ለዘመናት ከተንሳፈፈችበት የረጋ ባሕር ላይ የሚያናውጧት አኅጉራዊና አዓለም አቀፋዊ የሆኑ ንቅናቄዎች፣ የለውጥ ክስተቶችና ማዕበሎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ይፈታተኗት ጀመረ፡፡ በሂደትም ቀስ በቀስ አገሪቱ ውስጥ ውስጡን እየጋለና እየናረ በመጣ የለውጥና የነውጥ እንቅስቃሴ መናጥ ጀመረች፡፡

ይህ የለውጥና የነውጥ እንቅስቃሴም በሦስት ሺሕ ዘመናት የነጻነት ታሪክ ስም ተኮፍሳ ባለችው ኢትዮጵያ ከዚሁ የዘመናት ታሪኳና ዝናዋ ጋር ፈጽሞ ሊገጥም በማይችል ድህነት፣ ኋላ ቀርነትና ሕዝቦቿም በማሃይምነት ጨለማ ውስጥ ሆነው የሚማቅቁባት ምድራዊ ሲኦል መሆኗን የሚገልጹ ተማሪዎች ድምፃቸውን በተደራጀ መልኩ ማሰማት ጀመሩ፡፡

ከዚሁ አገራችን ካለችበት ድህነት፣ ኋላ ቀርነትና በታሪኳ ከምትተርከው የሺሕ ዘመናት የነጻነት ታሪክ ትርክት ጋር ፈጽሞ በማይጣጣም መልኩ ያለችበትን የፖለቲካ ነጻነት ዕጦት፣ ፊውዳላዊ፣ አምባገነናዊና ኢ-ዲሞክራሲያዊ አገዛዝ በተመለከተ በ1954 ዓ.ም. ለፖለቲካዊና ወታደራዊ ሥልጠና ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የነበሩት ደቡብ አፍሪካዊው፤ የነጻነት ታጋይ ኔልሰን ሮሂላላ ማንዴላ፤ ‹‹Long Walk to Freedom›› በተባለው የራሳቸውንና የሕዝባቸውን የነጻነት ትግል ታሪክ በተረኩበት ዝነኛ መጽሐፋቸው፤

‹‹በባለ ሦስት ሺሕ ዘመን ታሪክ ባለቤት በሆነችው ኢትዮጵያ አስከፊ የሆነ ድህነትና ኋላ ቀርነት የተንሰራፋባት፣ ምንም ዓይነት የፖለቲካ ፓርቲ፣ ነጻ ፕሬስም ሆነ የዲሞክራሲ ጭላንጭል የማይታይባት፣ ሁሉም ነገሯ ንጉሠ ነገሥቱ የሆኑባት አገር ናት፡፡›› ሲሉ ነው የዛን ጊዜዋን ኢትዮጵያን በተመለከተ ትዝብታቸውን ያሰፈሩት፡፡

ይህ የአገሪቱ ያለችበት ጥልቅ የሆነ ድህነትና ፖለቲካዊ አፈና እረፍት የነሳቸው የከፍተኛ ተቋማት (የሁለተኛ ደረጃ፣ የኮሌጆችና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች)፣ ላብ አደሩ፣ አርሶ አደሩ፣ ምሁሩ፣ ሴቶች፣ ወታደሩና ሁሉም ኅብረተሰብ ክፍል የለውጥ የእንቅስቀሴያቸው አካልና ደጋፊ እንዲሆን ማነሳሳት ጀመሩ፡፡ የተማሪዎቹ እንቅስቃሴም ከዩኒቨርሲቲያቸው የውስጥ አሥተዳደር ጥያቄዎች በመውጣት እንደ ‹‹መሬት ላራሹ›› እና ‹‹ሕዝባዊ መንግስት በአስቸኳይ ይቋቋም›› የሚሉ መፈክሮችን ይዞ ወደ አደባባይ ብቅ አለ፡፡

ይቀጥላል . . .

(በቀጣይ ጽሑፌ ከ1950ዎቹ እስከ አብዮቱ ፍንዳታ ድረስ የነበረውን የኢትዮጵያን ተማሪዎችንና ምሁራንን እንቅስቃሴ ለማየት እሞክራለሁ)፡፡

(ይህ ጽሑፍ ማስታወሻነቱ፤ በቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን መስሪያ ቤት የማይዳሰሱ ቅርሶች /Intangible Heritage/ ከፍተኛ ኤክስፐርት፤ የኢትዮጵያና አፍሪካ ታሪክ ተመራማሪ፣ ተቆርቋሪ ለነበረው ለወዳጄ፤ ለነፍሰ ኄር አቶ ኃ/መለኮት አግዘው እና በቅርቡ በሞት ለተለየን፤ ‹ለታሪክ አዋቂውና ለታሪክ ነጋሪው› ለነፍሰ ኄር፣ ገነነ መኩሪያ/ሊብሮ ይሁንልኝ)፡፡

(ጸሐፊው ተረፈ ወርቁ (/) በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ክ፤ በደቡብና በምዕራብ አፍሪካ  ሀገረ ስብከት ዋና ጸሐፊ ሆነው  ያገለገሉ ሲሆኑ፤  በአሁን  ሰዓት  ደግሞ በጥናትና ምርምር ዘርፍ ከፍተኛ ተመራማሪ/ሪሰርቸር፤ የታሪክና የቅርስ አስተዳደር ባለሙያ ናቸው፤ እንዲሁም Universal Peace Federation/UPF የሰላም አምባሳደር ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ)፡፡ 

 

ልዩ ምሽት በአዲስ አበባ -1930ዎች

 

 

2 Comments

  1. ዲን ተረፈ ከዚህ በፊት እምነቴ ስለሚከለክለኝ እንደ እርሶ አይነት መንፈሳዊ ላይ ብእርን ማንሳት ያስቀስፋል ብዬ በማሰብ ትቼው ነበር፡፡ በወቅቱ የማርክስ ሶስቱ ክፍሎች ፖለቲካል እኮኖሚ፤የማርክስ ፍልስፍናና ሳይንሳዊ ሶሲሽያሊዝም ይሆን ኮሙኒዝም እምቢ ብሎ ቢያቅረንም ስንጋት ነበር ፡፡ በየውይይት ክበቡ እግዚአብሄር የለም አማኝ ከሆንክ አድሃሪ ነህ ተብሎ ስንቱ ከስራው ስንቱ ከአደባባይ ተገልሎ ዛሬ ሀገር ምስቅልቅሏ የሚወጣበትን መደላድል ይህ ፍልስፍና አዘጋጅቶልን ዛሬ እዚህ ደርሶናል፡፡ እንግዲህ ሁኔታው ይህ ሁኖ ሳለ እርሶ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተከታይ ነዎት ወይስ የማርክስ ሰው ነዎት? የክህነቱ ማእረግ አሁን አሁን ሌሎች እንደሚሉት ተጭኖቦት ነው ፈቅደው ነው? ግራ አያጋቡን እንጅ ጌታየ ስለዛ ዘመን ፈረንጆች ትራውማ የሚሉት ስላለብን ቀስቅሰው አያሰቅቁን ቢችሉ እንደ ጥንቱ በጥናት ክበብ ተወያዩበት ከዚህ በላይ ምን እንሁን? በእርግጥ አብይ መሃመድና ጌታቸው ረዳ ታደሰ ወረደ የሰላም ሰዎች ተባብለው ሲጨባበጡ አጨብጭበን የለ? አብይ እንዳለው ነገር ቶሎ እንረሳለን መሰል፡፡

  2. ተረፈ ወርቁ በከንቱ እየደማንና እየሞትን ያለፍንበትን ዘመን ታሪክ እየዳሰሱ ነው። አገራችን በሺ የሚቆጠር ዕድሜ እያላት ለምን ኋላ ቀር ሆነች በሚለው ቁም ነገር ላይ ግን አንድም ቃል የላቸውም። በዚች ታሪክ የትምሕርት መነሻ እንጂ መድረሻ አለመሆኑ በማይታወቅበት አገር፣ ይህ የዘመናት ትርምስ፣ መፈናቀል፣ ግድያና ውድመት ለዛሬው ኋላ ቀርነታችን አንዱ ግልጽ ምክንያት ነው ብንል፣ ከዚህ አስከፊ ሕይወት እንዴት እንደምንወጣ ተረፈም ሆነ ሌሎች ፍንጭ ሊሰጡን ይገባል። አለዚያ ከእንሥሣት ብዙም አንሻልም። ይህን ሁሉ ዋጋ ከፍለን ዛሬ ላይ ኢትዮጵያ ለምን በተሻለ ደረጃ ላይ የለችም ለሚለው ዲያቆኑ አስተያየት የላቸውም። ታሪክ መደገሙን ብቻ ነው የነገሩን። ዋናው ቁም ነገር ግን ከኋላ ቀርነታችን እንዴት እንደምንወጣና ከመፈናቀል፣ ከመዳማት፣ ከመገዳደልና ከውድመት ወጥተን በዚች ሰፊ ለም መሬት፣ አያሌ ወንዞች፣ በሚሊዮን የሚቆጠር ሥራ ፈት ወጣት፣ ሰፊ የማዕድን ሀብት ያላት አገር ለምን ዘመናዊ ዕድገት ራቃት የሚለውን ጥያቂ መመለስ እንጂ ስለ ውድመትና ኋላቀርነት ደጋግሞ ማተት ብቻውን ምንም አይፈይድም።

    ጃፓን ሶስት ጥሬ ዕቃዎች ብቻ ወደ ውጭ እየላከች በአፄ ቴዎድሮስ ዘመን አብዮት አካሂዳ በ30 ዓመት ውስጥ የሩቅ ምሥራቅ ኃያል አገር ስትሆን እኛ ግን አገሩንም ጠንቅቆ የማያውቅ ተማሪ በጠበጠና ለጅብ አስረከበን እንጂ ለዘላቂ ገንቢ ለውጥ አላበቃንም። ለጃፓን ፈጣን ዕድገት መሠረቱ የሆኑት አገር በምዕራባውያን መደፈሩ ያንገበገባቸው መሣፍንትና መኳንንት የለውጡ መሪዎች መሆናቸው ብቻ ሳይሆነ፣ ለውጡም በማንም የማትደፈር ዘመናዊ ጃፓንን መገንባት ብሔራዊ ግዴታቸው መሆኑን የተረዱና ራሳቸው በሀቅ እየሠሩ ፈጣን ዕድገት ለማምጣት ቆርጠው የተንሱ፣ አገር አቀፍ ተልዕኮ የነበራቸው ጀግኖች አገር ስለመሩ ነበር። በ30 ዓመት ውስጥ ሃያል አገር መሥርተው የሩቅ ምሥራቅ አገሮችን፣ ቻይናን ጭምር፣ አስገብረው ነበር። እኛ አገር ግን፣ ሕዝባቸውን የማያውቁ፣ አገራዊ ተልዕኮ የሌላቸው፣ በግል ወይም በቡድን ጥቅም የናወዙ ፣ እንደ ደርግ በጥላቻና በበበቀል፣እንደ ኢሕአዴግ በበቀልና በቡድን ጥቅም ላይ ያተኮረ አገዛዝ ስለመጣብን፣ አገራዊ አጀንዳ ቦታ ስላልነበረው ኋላ ቀርነት በተባባሰ ሁኔት ቀጠለ። ተረፈ ወርቁ ሊነግሩን የሚገባ እንዴት ከኋላቀርነት አዙሪት እንደምንወጣ ጭምር ካልሆነ፣ አሳፋሪ የውድቀት ታሪክ መደርደሩ ብቻውን አይጠቅመንም። በእኔ በኩል የምናሻሽለው አንዱ ለ83 ጎሣ 9 ጎሣ በፈላጭ ቆራጭነት የሚገዛበትንና በተለይ 74 ጎሣዎችን አገር የለሽ ያደረገውን ፀረ ዲሞክራሲ ሥርዓት ለውጦ ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ አገር እንድትሆን ማድረግ ነው። በሕገ መንግሥቱም ውስጥ ሕግ በማያከብሩና በማያስከብሩ ሹሞች ላይ ግልጽና ፈጣን ቅጣትና ከሥልጣንም ማባረር የሚያስችል ድንጋጌና ተቋም መገንባት ወሳኝ ነው። ሁለተኛው፣ የተለያየ የዩኒቬርሲቲ ወረቀት ሰብስበው በተመደቡበት ሥራ ውጤት በማያሳዩ፣ በጉቦኞች፣ ሌቦችና በአውደልዳዮች ላይ ከፍተኛ ቅጣት የሚደነግግ አንቀጽም አስፈላጊ ነው። የዛሬ የአገራችን አንዱ ዋና ችግር ከፍተኛ ወረቀት አለን እያሉ ተወጥረው ሥራ የማያውቁ፣ ከፈረንጅ የገለበጡትን እንኳ አሟልተው የማያቀርቡ፣ ለዓለቃ በማደግደግ ዕድገትና ሹመት የሚሰጣቸው፣ የማያሰሩና የማይሠሩ ጡረተኛ ባለዲግሪዎች በመብዛታቸውም ጭምር ነው። እነዚህንም ማስተካከል ይገባል። አለዚያ በባዶ ዲግሪ እየተመራን ከአንድ ደካማ ትውልድ ወደ ሌላው እየተሸጋገርን፣ ሁልጊዜ ግድብ የሚገድብልን፣ የባቡር ሀዲድ የሚዘረጋልን፣ ፋብሪካ የሚከፍትልን፣ ግብርናና የግብርና መሣሪያ የሚያዘምንልን፣ ረጅም ህንፃ የሚገነባልን ከውጭ እየቀጠርን፣ ዛሬም ከፍተኛ የትምሕርት ተቋም ከከፈትን ከ 70 ዓመትም በኋላ፣ የትምሕርት ሥርዓቱን በማስተካከልና ራሳችንን በመቻል ፈንታ፣ ባግባቡ ተደራጅተን መሥራት ሳይቸግር እንደ አፄ ምኒልክ ዘመን ፈረንጅ እየቀጠርን መኖሩ የፈረንጅ ሲሳይ ሆነን ኋላቀርነትን አንግሠን መኖር ይሆናል።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share