የአድዋ ድል፣ የህብረ-ብሄር ግንባታ ሂደትና ዘመናዊነት በፍልስፍናና በሳይንስ መነፅር ሲመረመሩ!

(በፀና መሰረት ላይ ያልተገነባው ህብረ-ብሄርና መዘዙ!)

ፈቃዱ በቀለ(/)

 መጋቢት 4 2024 ዓ.ም

እ.አ አ በ1896 ዓ.ም ጣሊያን ለመጀመሪያ ጊዜ አገራችንን ስትወር በጊዜው የነበረውን ደካማ አገር፣ የጠነከረ የመንግስት አወቃቀርና አመራር አለመኖር በመገንዘብ ነበር። እንደሚታወቀው በወቅቱ ኢትዮጵያ ከጣሊያን ጋር ስትወዳደር በቴክኖሎጂና በጦር ኃይል ወደ ኋላ የቀረች ነበረች። ህዝቡን የሚያስተሳስረውና በአንድነት የሚያስነሳው ልዩ ልዩ ተቋማት አልነበሩም። በተለይም በሰሜኑ ክፍል የሚገኘው ህዝብ አብዛኛው በግብርና የሚተዳደር ነበር። ከዚህም በላይ ሁኔታውን ከባድ የሚያደርገው አፄ ምኒልክ ስልጣንን ሲይዙ በተለይም በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በመሳፍንቶች መሀከል ይደረግ የነበረው ትግልና የኋላ ኋላ በአፄ ቴዎድሮስ ድል አድራጊነት ቢቋጭም ይህንን ያህልም የበረደ አልነበረም።  አብዛኛው መሳፍንት እዚያው በዚያው የሚያስብ እንጂ አገራዊና ብሄራዊ ስሜትን ያዳበረ አልነበረም። በሌላ አነጋገር፣ ሙሉ በሙሉ በማዕከላዊና በአንድ ንጉሰ ነገስት ጥላ ስር የመገዛት ፍላጎት አልነበረውም። በዚህና በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ ጣሊያን ኢትዮጵያን ለመውረርና ድል በመቀዳጀት  ሙሉ በሙሉ የመቆጣጠር ዕድል ነበራት።

እንደሚታወቀው ጣሊያን ከሌሎች የቅኝ አገዛዝ ኃይሎች ጋር፣ ማለትም ከስፔይን፣ ከፖርቱጋል፣ ከእንግሊዝና ከፈረንሳይ ጋር ስትወዳደር  ኋላ ብቅ ያለችና በአፍሪካ ውስጥም አንድንም አገር የቅኝ ግዛቷ ያደረገች  አገር አልነበረችም። ስለሆነም ልክ እንደሌሎች የምዕራብ አውሮፓ አገሮች የራሷ የሆነ የቅኝ ግዛት እንዲኖራት የምትመኝ ነበረች። ለዚህ ደግሞ በጊዜው በማንም የአውሮፓ ኃይል ቅኝ-ግዛት ያልሆነችው ኢትዮጵያ አመቺ ነበረች። አብዛኛዎቻችን እንደምናውቀው ቀደም ብሎም ሆነ በኋላ ላይ የአውሮፓ ኃያል መንግስታት በጀርመኑ ቻንስለር በኦቶ ቢስማርክ አማካይነት በ1884 ዓ.ም በርሊን ተጋብዘው ሲወያዩ ዋና ዓላማቸውም በጊዜው አልሰለጠነም የሚሉትን አህጉር እንዴት አድርገው እንደሚቀራመቱ ነበር።  በእነሱ ዕምነት የአፍሪካ ህዝብ ያልሰለጠነ፣ ንጉሳዊ ወይም ሌላ የሰለጠነ አገዛዝ የሌለው፣ ሃይማኖት ያልነበረውና፣ እዚህና እዚያ እንደ አውሬ እየዘለለና ፍራ-ፍሬ በመለቃቀምና በአደን የሚኖር ነበር። ስለሆነም በእነሱ ግምት ይህንን ያልሰለጠነ ህዝብ ማስልጠን ያስፈልጋል የሚል ነበር። ይሁንና በዚህ አሳበው ወደ አፍሪካ ቢመጡና ብዙ አገሮችንም በቁጥጥራቸው ስር ለማድረግ ቢችሉም፣ ድብቅና ዋናው ዓላማቸው የአፍሪካን ህዝብ ለማስልጠንና ለማስተማር፣ ከተማዎችንና መንደሮችን ለመገንባት፣ የባቡር ሃዲድ ለመዘርጋትና በስራ-ክፍፍል ላይ የተመሰረተ የዳበረ ኢኮኖሚና የሰለጠነ ተቋማት ለመገንባት ሳይሆን የእፍሪካን የጥሬ-ሀብት ለመቀራመትና ለመዝረፍ ነው።

ከ18ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በእንግሊዝ ምድር የተጀመረው የኢንዱስትሪ አብዮት በፈረንሳይና  ኋላ ደግሞ በጀርመን ምድር ተቀባይነትን በማግኘት በመሀከላቸው የጦፈ ውድድር ይደረግ ነበር። አብዛኛዎቹ የአውሮፓ አገሮች ኢንዱስትሪዎችን ቢተክሉምና ዘመናዊነት የሚባለውን ፖለቲካ ቢከተሉም ኢንዱስትሪዎቻቸውን ለማንቀሳቀስ የሚረዳ የጥሬ-ሀብት አልነበራቸውም። ስለሆነም የግዴታ የተለያዩ የጥሬ-ሀብቶችንና፣ በአውሮፓ ምድር ሊበቅሉ የማይችሉትን እንደ ቡና፣ ካካኦና ኦቾሎኒ፣ እንዲሁም ሌሎች የትሮፒካል ፍራፍሬዎችና የቅባት እህሎችን ለማግኘት የሚችሉት ከአፍሪካና ከሌሎች ኋላ-ቀር  አህጉርና አገሮች  ብቻ ነበር።  በመሆኑም ያላቸው አማራጭ አፍሪካን መቀራመትና በቁጥጥራቸው ስር በማድረግ ሀብቷን መዝረፍ ነው። የጣሊያንም አካሄድ ከዚህ የተለየ አልነበረም። ጣሊያን በደንብ የተደራጀ ኃይል የነበራትና ቀደም ብሎ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ግዛት መሬት በመከራየት የያዘችውን ቦታ በማስፋፋትና ራሷን በማጠንከር ኢትዮጵያን በቀላሉ ለመያዝና በቁጥጥሬ ስር ለማድረግ እችላለሁ የሚል ግምት ብቻ ሳይሆን የጸና ዕምነትም ነበራት።

የውጫሌው ውል ስምምነት ከፈረሰ በኋላ አፄ ምኒልክ ያላቸው ዕድል እንደምንም ብለው የጦር መሳሪያ ከዚህና ከዚያ በማግኘት፣ አልተባበራቸውም ያላቸውን የመሳፍንት ኃይል በማባበልና አገር ማስቀደም ያስፈልጋል በሚለው ጠቢባዊ አካሄዳቸው፣ ህዝባቸውም ከጎናቸው እንዲሰለፍና የተቻለውን እንዲያድረግ በማድረግ ራሳቸውና እትጌ ጣይቱ ጦሩን በመምራትና በመዝመት ቀስ በቀስ የጣሊያንን ጦር በመግጠም መግቢያና መውጫ ካሳጡት በኋላ ጣሊያን ባልጠበቀውና ባላሰበው ሁኔታ አፄ ምኒልክና አርበኞቻቸው የተደራጀውን ኃይልና የተሻለ አዘገጃጀት አለኝ የሚለውን የወራሪ ኃይል አንኮታክተው በመጣል ለመጀመሪያ ጊዜ የጥቁር ህዝብ በንጉሳዊ አመራሩ በመመራት በነጭ ወራሪ ኃይል ላይ ድልን ለመቀዳጀት ቻለ። በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥም አዲስ ምዕራፍ ተከፈተ። ይህ ዐይነቱ ድልና የህዝቡም መሰባሰብ አዲስ ለምትገነባው ኢትዮጵያ መሰረት ሊሆን ቻለ።

አፄ ምኒልክና የተቀሩት አርበኞቻቸው ድልን ከተቀዳጁ በኋላ፣ በተለይም የአገራቸውን ደካማ ጎን የተረዱት መሪ የግዴታ አገራቸውን ዘመናዊ ማድረግ ነበረባቸው። በሳቸውም ዕምነት ሆነ ከህብረ -ብሄር አገነባብ ታሪክ እንደምንማረው አንድ አገር በድጋሚ ለመወረር የማትችለው በጸና መሰረት ላይ ስትገነባ ብቻ ነው። ስለሆነም በአፄ ምኒልክ ተነሳሽነትና አርቆ አሳቢነት ህዝቡን የሚያስተሳስር የኢኮኖሚ መሰረት ለመጣል ቻሉ፡፡ የባቡር ሃዲድ መዘርጋት፣ ድልድዮችንና መንገዶችን መስራት፣ ትምህርትቤቶችንና ክሊኒኮችን መክፈት፣ የፖስታ ቤት መክፈት፣ የማዕከላዊ ባንክ በመክፈት በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት የሚኖረው የመገበያያ ገንዘብ ማተም… ወዘተ. እነዚህና ሌሎች ተግባራዊ የተደረጉት እርምጃዎች በሙሉ የዘመናዊነትና ህዝብን በአዲስ መንፈስ የማስተሳሰር መሰረቶች ናቸው። በእነዚህም አማካይነት ነው አንድ አገር እንደ አገር ሊገነባ የሚችለውና በህዝቡም ዘንድ የአገራዊነት ስሜት ሊዳብር የሚችለው። በዚህም የተነሳ ነው ቀስ በቀስ የኢትዮጵያዊነት ስሜት ሊዳብር የሚችለውና የቻለው።

በአብዛኛዎቻችን ዘንድ ይህንን ያህልም ግንዛቤ ያላገኘው አፄ ምኒልክና አርበኞቻቸው ህዝባቸውን ከጎናቸው አሰለፈው በወራሪው ጣሊያን ላይ ያንን የመሰለ ድል ቢቀዳጁም፣ ከድል በኋላ ተግባራዊ ካደረጓቸው የዘመናዊነት ፖሊሲዎች ባሻገር አንድን አገር ለመገንባት የሚያስችል የተማረ ኃይልና ተቋማት በጣም ወሳኝ ነው። በሰለጠነ ኃይልና በሰለጠኑ  ቁማት ብቻ ነው ለሰፊው ህዝብ ልዩ ግልጋሎቶችን መስጠት የሚቻለው። ህዝቡንም ለማስተማር፣ በተለያየ የሙያ ዘርፎች ለማስልጠንና በምድር ላይ ያለውን የጥሬ-ሀብትና የሰው ኃይል ለማንቀሳቀስ የሚቻለው፣ የሰለጠነ ኃይል ሲኖርና ዘመናዊነት ማለት ምን ማለት ነው? እንዴትስ ነው ቀስ በቀስ በስርዓት የሚተገበረው?  የሚለውን መሰረተ-ሃሳብ የተረዳ ኃይል ሲኖር ብቻ ነው። በዚህም መሰረትና ከተለያዩ አካባቢዎችና ምሁሮች የሚመጡትን ሃሳቦች በማሰባሰብ፣ በማውጣትና በማውረድ ነው ቀስ በቀስ የሰለጠነና በጠንካራ መሰረት ላይ ሊቆም የሚችል አገር መገንባት የሚቻለው:: በጊዜው የአፄ ምኒልክ ኢትዮጵያን ዘመናዊ የማድረግ ፍላጎት ግልጽ ቢሆንም ሰፋ ያለና የተገለጸለት ምሁራዊ ኃይል ስላልነበረ ኢትዮጵያን እንደ ተሟላ ህብረ-ብሄር ለመገንባትና ሁሉም ህዝብ ብሄራዊ ስሜቱን ለማዳበር የሚችልበት ሁኔታ አልነበረም ። የተገለጸለት ኃይልም ሲባል ከራሱ ጥቅም ባሻገር ማሰብ የሚችልና በከፍተኛ ደረጃ ብሄራዊ ስሜትን ያዳበረ ማለት ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን አንድ አገር በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ ተመስርቶ ሁለ-ገብ ኢኮኖሚ መገንባት ያስፈልጋል ብሎ የሚያስብና የመሪነትን ብቻ ሳይሆን ለታዳጊውና ለተከታታዩ ትውልድ ምሳሌ ሊሆን የሚችል ምሁራዊ ኃይል ካለ በእርግጥም የተገለጸለት ነው ሊባል ይችልካል። ከዚህ አኳያ ስንነሳ የታሪክ ግዴታ ሆኖና የኢትዮጵያ ህብረተሰብም ማለፈ የነበረበትን ልዩ ልዩ የዕድገት ደረጃዎች ለመጓዝ ባለመቻሉ በሰፊውና በጥልቀት የሚያስብ የተገለጸለት ምሁራዊ ኃይል ሊፈጠር አልቻለም።  ይህም ማለት አፄ ምኒልክ ስልጣንን ሲጨብጡና ከአደዋ ድል በኋላ የዘመናዊንትን ፖሊሲ ተግባራዊ ለማድረግ ሲነሱ ከዜሮ መነሳት ነበረባቸው። በተለያዩ ቦታዎች እንደ ዕደ-ጥበብ የመሳሰሉ ለኢንዱስትሪ ዕድገት መሰረት የሚሆኑና የገበያ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴና ተቋማትና በስነ-ስርዓትና ጥበባዊ በሆነ መልከ የተገነቡ ከተማዎችና መንደሮች  ስላልነበሩ ሰፊውን ህዝብ በተለይም በኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ለማስተሳሰር አይቻልም ነበር። አፄ ምኒልክም ዕድሜያቸው እየገፋ በመምጣቱና በመጨረሻም በመታመማቸው የተነሳ ህልማቸውንና ዓላማቸውን ሙሉ በሙሉ ለማገባደድ አልቻሉም። እንደሚታወቀው የህብረ-ብሄር ወይም የአንድ አገር ግንባታ በአንድ ንጉሰ-ነገስት ወይም በአንድ ትውልድ ብቻ የሚጠናቀቅ ሳይሆን፣ በተከታታይነት በተከታታዩ ትውልድ መተግበር ያለበት ጉዳይ ነው።

ያም ሆኖ አፄ ምኒልክ የጣሉት መሰረት የኋላ ኋላ ከ1940ዎቹ አጋማሽ ላይ ጀምሮ በአፄ ኃይለስላሴ ተግባራዊ በመሆን በተለይም ከ1950ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ በኢትዮጵያ ምድር ውስጥ አዲስ ዐይነት ለውጥ ሊመጣና ህዝቡንም ቀስ በቀስ ለማስተሳሰር ችሏል። የሙዚቃ አብዮት፣ የቲያትር ቤቶችና ሲኒማ ቤቶች መከፈት፣  የስነ ጽሁፍ መዳበር፣ ልዩ ልዩ ህንጻዎች መሰራት፣ የምግብ ቤቶችና ሆቴል ቤቶች መከፈት፣ የንግድ እንቅስቃሴ መዳበር፣ ማዕከለኛ ኢንዱስትሪዎች እዚህና እዚያ መከፈትና ስራ ለሚፈልገው የስራ ዕድል መስጠት፣ የዕደ-ጥበብ ስራዎች ማበብ፣ ትምህርት ቤቶችና በተለይም የዕደ-ጥበብ ሙያ ማስልጠኛ መቋቋም፣ ዩኒቨርሲቲና ኮሌጆች መከፈት፣ የመገናኛ መንገዶች መስፋፋት፣ አዲስና ዘመናዊ ቢሮክራሲ መቋቋም፣ አገሪቱን ከወራሪ ኃይል ለመከላከል የሚችል ወታደራዊ ኃይልና ማሰልጠኛ አካዳሚ መክፈት፣ ፖሊሶችን ማሰልጠን፣ እነዚህና ሌሎች ከ1950ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ መከናወን የጀመሩት የዘመናዊነት መሰረቶች በእርግጥም ህዝባችንን ለማስተሳሰርና መንፈሱንም ለማጠንከር ችለዋል። የአንበሳ ምልክት ያለበት የአረንጓዴ ቢጫና ቀይ ባንዲራ የአገራችን መለያ መሆን፣ እነዚህና ሌሎች ነገሮች በሙሉ ለጊዜው ውስጣዊ ጥንካሬ የሰጡን ነበሩ።

ይሁንና ግን ይህ ዐይነቱ አካሄድ የራሱ የሆነ ጉድለት እንዳለው የማይካድ ሃቅ ነው። ዕድገትና ዘመናዊነት የሚባሉት ነገሮች በእኩል ደረጃ በአገሪቱ ምድር የተካሄዱ አልነበሩም። የተተከሉትም ኢንዱስትሪዎች የማደግና የመስፋፋት ኃይል አልነበራቸውም። ለስልጣኔንና ለዕድገት የሚሆን የሳይንስና የቴክኖሎጂ ጉዳይ አትኩሮ አልተሰጠውም።  በተለይም በማኑፋክቸሪንግ ወይም በማሽን ኢንዱስትሪ ላይ ከማትኮር ይልቅ የፍጆታን ዕቃዎች ለማምረት የተቋቋሙት ኢንዱስትሪዎች ለሰፊው ህዝብ የሚሆን በቂና አስተማማኝ የስራ መስኮች ሊከፍቱ አልቻሉም። በዚህም ምክንያት የተነሳ የውስት ገበያ(Home Market)ሊዳብርና ሊስፋፋ አልቻለም። እንደሚታወቀው አንድ አገር ጠንካራና የተስፋፋ፣ እንዲሁም በየጊዜው ሊያድግ የሚችል የኢንዱስትሪ መስክ ሲኖራት ብቻ ነው የሰፊውን ህዝብ ፍላጎት በማሟላት ማስተሳሰረም የሚቻለው። አንድ አገር በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተና ውብ ውብ የሆኑ ባህላዊ ከተማዎች ሲኖሯት ነው በቀላሉ በውጭ ኃይሎች መደፈር የማትችለው። ከላይ የተዘረዘሩት መሰረታዊ ነገሮች ተግባራዊ ለመሆን ባለመቻላቸው  አዲስና የተገለጸለት፣ እንዲሁም ውስጠ-ኃይሉ የጠነከረ የህብረተሰብ ኃይል ብቅ ማለት አልቻለም። አፄ ኃይለስላሴና አገዛዛቸው እሳችውን ሊተካና አገርን በጸና መሰረት ላይ ለመገንባት የሚችል ኃይል ማስልጠን አልቻሉም። ዕድገቱም ያልተሰተካከለ ስለሆነና አገሪቱ ያላትን የተፈጥሮ ሀብት በሚገባ መጠቀም ባለመቻሏ እንደ ወሎ በመሳሰለው ክፍለ-ሀገር በብዙ ሺሆች የሚቆጠር ህዝብን ለሞት የዳረገ ረሃብ ተከሰተ። ይህ ሁኔታና ቀስ በቀስም በከተማዎች የሚታየው የስራ-አጥነትና ከቤንዚን ዋጋ መናር ጋር የተፈጠረው የኢኮኖሚ ቀውስ የአፄውን አገዛዝ መሰረት ማናጋት ጀመረ። ይህ ጉዳይ የተማሪው እንቅስቃሴ አንግቦ ከተነሳው የመሬት ለአራሹ ጥያቄ ጋር በመያያዝ የየካቲት 66 ዓ.ም አብዮት ፈነዳ። በዚህም ምክንያት የተነሳ አፄ ኃይለስላሴ ከስልጣናቸው እንዲወርዱ ተደረገ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ዘመቻ ዲያስፓራ!.- በየጐንቻው!

አብዮቱ ከፈነዳበት  ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ አገራችንና ህዝባችን የመረጋጋትን ዕድል ሊያገኙ በፍጹም አልቻሉም። በጊዜው የተፈጠረውን አዲስ ሁኔታና የጥገና ለውጥን ለማስተናገድ የሚችል ኃይል ባለመኖሩ ኢትዮጵያችንና ህዝባችን በጭንቀት ውስጥ ገቡ። ቀደም ብሎ የአድዋን ድል ያልተረዳውና ብሄራዊ ስሜትን ያላዳበረው አንዳንድ ኃይል አዲስ የተፈጠረውን ሁኔታ በመጠቀም ኢትዮጵያችንንና ህዝባችንን ጭንቀት ውስጥ ከተቷቸው።  ጦርነቱ ከውስጥና ከውጭ በመጧጧፍ በጊዜው ስልጣንን ለያዘው የደርግ አገዛዝ መፈናፈኛ ሊሰጠው አልቻለም። ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር በማተኮሩ አገርን በጋራ ለመገንባትና ኢትዮጵያችንን በጠንካራ መሰረት ላይ ለማቆም አልታቸለም። የደርግ አገዛዝም በተለይም በውስጥ ኃይሎች በአንድ በኩል በጦርነት በመጠመዱ፣ በሌላ ወገን ደግሞ በሲቪሉ ቢሮክራሲ ውስጥም ሆነ በሚሊታሪውና በጸጥታው ውስጥ በተሰገሰጉ ለሲአይኤ በሚሰሩ ኃይሎች ስለተጠመደና አገርን የማፍረስ ተንኮል ይሰራ ስለነበር በድሮው የአገዛዝ መልኩ ሊገዛ አልቻለም። ደርግ በአነሳሱና፣ በጠቅላላው ቢሮክራሲው በአንዳች ዐይነት አገርንና ህብረተሰብን ሊያስገነባ በሚችል ፍልስፍና ሳይንሳዊ ዕውቀት የሰለጠኑ ባለመሆናቸውና ከታች ወደ ላይ በምሁራዊ ሂደት ውስጥ በማለፍ ብሄራዊ ባህርይን ያዳበሩ ስላልነበሩ በተለይም ከውጭ የሚሸረበውን ተንኮል ለመቋቋም የሚያስችል ብቃትነት አልነበራቸውም። በመሆኑም የደርግ መወደቅና አገራችንም በሌላ ብሄራዊ ነፃነቷንና አንድነቷን በሚፈታተኑ ለውጭ ኃይሎች ተገዢ በሆኑ የብሄረሰብን አርማ አንግበው በሚታገሎ ኃይሎች እጅ መውደቋ የታሪኳ ዕጣ ፈንታ ነው ማለት ይቻላል። ይህ ፅንፈኛና ፀረ-ኢትዮጵያና የጠቅላላው ጥቁር ህዝብ ጠላት የሆነው ኃይል ህወሃት ወይንም ወያኔ በመባል የሚታወቅ ነው። ዋና ዓላማውም ለውጭ ኃይሎች ተቀጣሪና ተላላኪ በመሆን ታሪካችንን ማጉደፍና ህዝባችንና አገራችንን በቀላሉ ሊወጡ የማይችሉት  ፈተና ውስጥ መጣል ነው።

ወያኔ ስልጣንን ከጨበጠ በኋላ ተግባር ላይ ያዋለው የጎሳ ፌዴራሊዝም የሚሉት ፈሊጥ የኢትዮጵያን ዕድገት የመቶ ዓመት ያህል ነው ወደ ኋላ የጎተተው። በህዝባችን ዘንድ አለመተማመን እንዲፈጠር ያደረገ ነው። ወያኔ ለከፋፍለህ ግዛው እንዲያመቸው ተግባራዊ ያደረገው ይህ ዐይነቱ የጎሳ ፌዴራሊዝም በመሰረቱ የተጠነሰሰው በአሜሪካና በእንግሊዝ ኢምፔሪያሊስት ኃይሎች ነው። የእነሱም ዋና ዓላማ እንደ ኢትዮጵያ የመሰለችን የብዙ ሺህ ዐመታት የስልጣኔ ታሪክና የዳበረ ባህል ያላትን አገር ማዳከምና የመጨረሻ መጨረሻም መበታተን ነው። በአጭሩ የሰለጠነችና በሳይንስና በቴክኖሎጂ ያበበች፣ እንዲያም ሲል ውብ ውብ ከተማዎች የሚኖሯት አገር እንዳትፈጠር ነው።  ስለሆነም ወያኔን ስልጣን ለማውጣት የተፈለገውና የተሳካው ሰፊው ህዝባችን ኃይሉን በመሰብሰብ፣ በመተባበርና በመተጋገዝ መንፈስ ጠንካራ አገር እንዳይገነባ ለማድረግ በነጩ የኦሊጋርኪ መደበ የተሸረበ ሴራ ነው። ምክንያቱም አንድ ህዝብ ሲተባበርና ሲተጋገዝ፣ እንዲሁም በአንድ መንፈስ ተነሳስቶ አገርን መገንባት ለኢምፔሪያሊስት ኃይሎች የሚገቡበትን መንገድ ስለሚዘጋባቸው ነው። ስለሆነም ይህ ዐይነቱ መተባበርና በጋራ መንፈስ መደራጀት ተግባራዊ መሆን የለበትም። ሰፊው ህዝብ መማርና መንቃት የለበትም። አስተሳሰቡ ሁሉ ተበታትኖ መኖር አለበት። ከየት እንደመጣ፣ ለምን በዚህች ዓለም ላይ እንደሚኖርና፣ ምንስ ማድረግ እንዳለበትና ወዴትስ እንደሚያመራ ማወቅ የለበትም። እንደከብት የሚነዳና የሚጠመዘዝ ህዝብ መሆን አለበት። ይህ ዐይነቱ ሁኔታ ኤክስፐርት ነን ለሚሉ በኢ-ሳይንሳዊ የኢኮኖሚ ፖሊሲ በሰለጠኑና ለሚመሩ የውጭ ኃይሎች የሚያመች ነው። የአንድን አገር ሀብት እንደፈለጋቸው ለመበዝበዝ ያመቻቸዋል። አካባቢን የሚያውድምና ማህበራዊ ግኑኝነትን የሚበጣጥስ ሁኔታ ይፈጠራል። በዚህ መልክ  አገራችን ለዝንተ-ዓለም የጥሬ-ሀብት አምራች ብቻ በመሆን የካፒታሊስቱን ዓለም ስትመግብ ትኖራለች። በዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ስር ወደቃ የጥሬ-ሀብቷ የምትበዘበዝ አገር ደግሞ በቀላሉ መፍትሄ የማይገኝለት የአካባቢና፣ የማህበራዊና የባህላዊ ቀውስ ውስጥ ትወድቃለች። ህዝባችን በአገሩ ውስጥ ያለውን የጥሬ-ሀብት በስነ-ስርዓት እያወጣ እስከመጨረሻው ድረስ እዚያው በማምረት ህብረተሰብአዊ ሀብት እንዳይፈጥር ይታገዳል ማለት ነው። በዚህም ምክንያት የተነሳ ከታች ወደላይ እንደሰንሰለት መያያዝ ያለበት የኢኮኖሚ ዕድገት ሁለ-ገብ በሆነ መልክ አይተገበርም ማለት ነው።

ልዩ ልዩ ዕውቀትና ብቃትነት ያለው ምሁራዊ ኃይል ባልዳበረበት አገር ውስጥ በቀላሉ በነፃ ገበያ ስም ተግባራዊ የሚሆነው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ከጎሳ ፌዴራሊዝም ጋር በመዳበል አገርን የሚያዳክምና የሚያፈርስ ስነ-ልቦና እንዲፈጠር ያደርጋል። አታላይ፣ ሸዋጅ፣ ዕምነት የማይጣልበት፣ በፕሪንሲፕል የማይመራ፣ ደሃና ሽማግሌዎችን የማያከብርና በራሱ ዓለም ውስጥ የሚኖር፣ ከየት እንደመጣና ወዴትስ እንደሚጓዝ የማያውቅ፣  ለምን እንደተፈጠረ የማይገነዘብ የህብረተሰብ ክፍል ይፈጠራል። በዚህ ዐይነት መንፈስ የተቀረጸ ህብረተሰብአዊ ኃይል በተስፋፋበት አገር ውስጥ ደግሞ ስልጣን ላይ ያለው አገዛዝ ከውጭ ኃይሎች ጋር በመተባበርና ከእነሱ ትዕዛዝ በመቀበል ሁሉንም ነገር እንደፈለገው ማድረግ ይችላል። የአገርን ሀብት ሲሸጥና ሲያስበዘብዝ የሚጠይቀውና የሚጋፈጠው ኃይል ስለማይኖር በዚያው ይገፋበታል። በተራና ባልሰለጠነ ፖሊስ ደሃው ህዝብ ሲመታና ከቤቱ ወጥቶ በየሜዳው ላይ ሲጣል እንዳላየ ዝም ብሎ ያልፋል። ደሃው ህዝብ ቤቱ ውስጥ ተኝቶ ወይም ቤቱ ውስጥ ተቀምጦ ቤቱ በግሬደር ሲፈርስበት ዝም ብሎ ይመለከታል። ለምድን ነው እንደዚህ የሚደረገው? ማንስ መብት ሰጥቷችኋል?  እንዴትስ ይህ ዐይነቱ ድርጊት በ21ኛው ክፍለ-ዘመን ይደረጋል? የህግ የበላይነትስ በዚህች አገር ውስጥ አይታወቅም ወይ? መንግስት የሚባለው ነገርስ ህዝብን ተንከባካቢ ከመሆን ይልቅ እንዴት እንደዚህ ዐይነት ነገር ሲደረግ ዝም ብሎ ያያል? እየተባለ ጥያቄዎችን ለማንሳት የሚችል ኃይል ለመፈጠር ባለመቻሉ የዛሬው ዐይነቱ ሁኔታ  መከሰቱ ይህን ያህልም የሚያስገርም አይደለም።

ወያኔ ስልጣን ላይ ከወጣ በኋላ ተግባራዊ ያደረጋቸው የጎሳ ፌዴራሊዝምና የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና የተቀረው የምዕራቡ ካፒታሊስት አገሮች ፕሮጀክቶች ናቸው ማለት ይቻላል ነው። ስንቶቻችንስ ይህ ዐይነቱ አታላይ ሂደት ገብቶናል? ያም ሆነ ይህ  በሂደት ላይ የነበረን የህብረ-ብሄር(Nation-State) አገነባብ ወደ ኋላ በመቀልበስ በጎሳ ላይ የተመሰረተ “አገር ለመገንባት” መጣር ውስጣዊ ግኑኝነትንና ኃይልን ያላላል፣ ያዳክማልም። በሎጂክና በዲያሌክቲክ ላይ የተመሰረተ ክርክርና ውይይትን ከማስቀደም ይልቅ ወደ ጠብ ጫሪነት የሚያመራ ህብረተሰብአዊ ኃይል እንዲፈጠር ያደርጋል። አንድ ህብረተሰብ እንዴት ከታች ወደላይ ቀስ በቀስ እንደተገነባ የማያውቅ ስለሚሆን የዛሬይቱ ኢትዮጵያ በኃይል ብቻና በማስገደድ አንድ የሆነች አገር እንደሆነች አምኖ ይቀበላል። ታሪክን ከሳይንስ አንጻር መመርመር ባልተለመደበትና እንደባህልም ባልተወሰደበት አገር ውስጥ ደግሞ የተሳሳተ ትረካን ማስፋፋቱ ቀላል ይሆናል። “ተጨቁናችኋል፣ ተገዳችሁ ነው በአንድ ባንዲራ ስር የተጠቃለላችሁት፣ ከዚህ በፊት የነበራችሁን ወርቅ ወርቅ የመሳሰሉ ባህሎችና ስልጣኔዎች በአዲስ ወራሪ ኃይል ፈርሰውባችኋል፣ ተገዢ ለመሆን በቅታችኋል፣ ስለሆነም ነጻ ከመውጣት ወይም ደግሞ የራሳችሁን ዕድል በራሳችሁ ከመወሰን በስተቀር ሌላ አማራጭ መንገድ የላችሁም” እየተባለ ይነፈሳል።  ሁሉም ይህንን ዕውነት አድርጎ ስለሚቀበል በተለይም ተጨቁነናል የሚሉ የህብረተሰብ ክፍሎችን ወይም የዚኸኛው ወይም የዚያኛውን የጎሳ ኤሊት ማስተማርና ማስረዳት በፍጹም አይቻልም። አብዛኛውም ከዕውቀት ርቆ የሚገኝ እንደመሆኑ መጠንና ሆዱን ከመሙላት በስተቀር መንፈሱን ሊያድሱለት የሚችሉ መጽሀፎችን ስለማያነብ መነታረክን ያስቀድማል። በቀላሉ ወደ ጠብ ጫሪነት ያመራል። በአጭሩ ወያኔና የዛሬው በአቢይ አህመድ አገዛዝ የሚመራው ጽንፈኛ ኃይል ይህንን ዐይነቱን የመነታረክን ባህል ነው ያስፋፉትና የሚያስፋፉት። የጎሳ ፌዴራሊዝምም ሆነ የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ምን እንደሆኑና ምንስ ዐይነት አሉታዊ ተፅዕኖና አገርን የማፍረስ ኃይል እንዳለቸው ሳያወጡና ሳያወርዱ ነው ተግባራዊ ያደረጓቸውና የሚያድርጓቸው።

ወያኔ በአሜሪካኖችና በተቀረው የምዕራቡ ዓለም ተገዶ በዓለም አቀፍ የገንዘብና(IMF) የዓለም ባንክ(World Bank) ተወካይነት የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲን ተግባራዊ ሲያደርግ ምን ዐይነት አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ውጤት ሊያመጣ እንደሚችል ለማውጣትና ለማውረድ ጊዜም አልነበረውም፤ ፍላጎትም አልነበረውም።  ህወሃት እንደ ነፃ አውጭ ድርጅት በሚሊታሪ ኃይል ከመደራጀቱና ስልጣንን በኃይል ለመያዝ ትግል ከማድረጉ በስተቀር ልዩ ልዩ ለአገር ግንባታ የሚያግዙ ዕውቀቶችን፣ ማለትም የፍልስፍናን፣ የፖለቲካን ቲዎሪ፣ ልዩ ልዩ የኢኮኖሚ ቲዎሪዎችንና ፖሊሲዎችን፣ እንዲሁም የሶስዮሎጂ መጽሀፎችን በማጥናትና በመመራመር በውስጡ ክርክር የሚያደርግ ድርጅት አልነበረም። ስለሆነም እንደዚህ ዐይነቱ በእነ ዓለም የገንዘብ ድርጅትና በዓለም ባንክ የረቀቀውን ኢ-ሳይንሳዊ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ ሲያደርግ ከምን አንፃር እንደተነሳ ቀድሞውኑ ለመገመት ያስችገራል። ይሁንና በነፃ ገበያ ስም ተሳቦ ተግባራዊ የሆነው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ለምዝበራና በሀብት ለመደለብ  አመቺ ሁኔታን እንደፈጠረለት የማይታበል ሀቅ ነው። ይህ ዐይነቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲ በካፒታሊዝም የዕድገት ታሪክ ውስጥ፣ በምዕራብ አውሮፓም ሆነ በአሜሪካ ተግባራዊ ሆኖ ስለማያውቅ፣ ከዚያም በኋላ እንደ ጃፓንና ደቡብ ኮሪያ የመሳሰሉት በቴክኖሎጂ የበለጸጉ አገሮች ውስጥ ተግባራዊ ያላደረጉት ሰለሆነ፣ ወደ ኋላ በቀረና ከእጅ ወደ አፍ(Subsistence  Economy) በሚታረስበት የኢኮኖሚ ክንዋኔ ውስጥ ተግባራዊ በሚሆንበት ጊዜ የስራ-ክፍፍልን ከማዳበር ይልቅ የተበጣጠሱና ሰፋ ላለ የሀብት ምስረታ የማያመቹ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች ይስፋፋሉ። ሆቴል ቤቶችና ቡና ቤቶች መክፈት፣ የሱቅ በደረቴ መስፋፋትና ለጠቅላላው የኢኮኖሚ መሰረት የማይሆኑ እንደመጠጥና የስኳር ፋብሪካ የመሳሰሉ መተከላቸው በመሰረቱ  በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ ለተመሰረተ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የሚያመቹ አይደሉም። ሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ እንዲሁም ማኑፋክቸር በማይስፋፋበት አገር ውስጥ ደግሞ አንድን ህዝብ የሚያስተሳስር ሰፋ ያለና የሚንቀሳቀስና የሚያድግ ጠንካራ ኢኮኖሚ መገንባት በፍጹም አይቻልም። በዚህ ዐይነቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲና እንቅስቃሴ ደግሞ ጠንካራ አገር መገንባት በፍጹም አይቻልም። በማንኛችንም ዘንድ መታወቅ ያለበት ጉዳይ አንድ ጠንካራ ህብረ-ብሄር ሊገነባ የሚችለው ለፈጠራ በማያመቹ፣ ለልዩ ልዩ ባህሎች መዳበር መሰናክል በሚሆን  የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲን ወይም ደግሞ የዓለም ኮሙኒቲው ነኝ የሚለው በሚያስፋፋው የነፃ ገበያ ፖሊሲ አማካይነት አይደለም።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ከዱቄት እስከ ሰብዓዊ አንበጣነት!! (የኢትዮጵያ ‹‹ሰብዓዊ ድሮኖች›› መነሳት) መነሻ! - ቴዎድሮስ ጌታቸው

ለማንኛውም ይህ ዐይነቱ የኒዎ-ሊበራል ወይም የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ በመባል የሚታወቀው ለወያኔና ለጥቂቶች  የህወሃት ካድሬዎች ሀብትን ለመዝረፍና ለመደለብ፣ የተወሰነውን ደግሞ ወደ ውጭ እንዲያሸሹ አመቺ ሁኔታን ሊፈጥርላቸው ችሏል። ሙሉ በሙሉ በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና በግብረአበሮቹ ቁጥጥር ስር የወደቀው የህዋሃት አገዛዝ አሽከር በመሆንና ሀብትን በማዘረፍ፣ በዚያውም መጠንም የዋሁን ሰፊ ህዝብ ወደድህነት ዓለም ውስጥ ሊጥለው ችሏል።፟ ትላልቅ ፎቅ ቤቶች ለመስራት ሲባል  በአንዳንድ አካባቢዎች ኗሪው ህዝብ ለብዙ አስርት ዓመታት ከኖረበት ቀየው እንዲፈናቅለ በመደረግ  ወደ መቆሻሻ መኖሪያ ቦታዎች እንዲጣል ተደርጓል። በወያኔ 27 ዓመታት የአገዛዝ ዘመን ህዝባችን እጅግ አስቀያሚ ወደ ሆነ፣ በ21ኛው ክፍለ-ዘመን፣ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ዘመን በማይታሰብ ሁኔታ ውስጥ እንዲወድቅ ተገዷል። ጥቂት ነው የማይባል የህብረተስብ ኃይል ከቆሻሻ ቦታዎች ምግብን እየፈላለገ እንደሚገብ ተገዷል። በሌላ ወገን ደግሞ እንደ ሼራተን፣ ብሉ ሬዲስንና ስካይ ላይን በሚባሉ ሆቴል ቤቶች ውስጥ ምግቦች ተትረፍርፈው ይቀርባሉ። በአጭሩ ወያኔና የበላይ አዛዦቹ በአገራችን ምድር ዝብርቅርቅ ሁኔታዎችን ነው የፈጠሩልን።  በነፃ ገበያ ስም ተሳቦ ተግባራዊ የሆነው የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ  በምንም ዐይነት የስራ ክፍፍል እንዲዳብርና የውስጥ ገበያ እንዲስፋፋ ያደረገ አይደለም። በዚህ ዐይነቱ በተለይም የግልጋሎት መስኩን በሚያስፋፋ የኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካይነትም በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ውድድርና ፈጠራ ሊታዩ አልቻሉም። በአንፃሩ ቶሎ ቶሎ ብሎ በገንዘብ ለመደለብ ሲባል በንግድ መስክና በሌሎች ለሰፊው ህዝብ በቂ የስራ መስክ ሊከፍቱ በማይችሉ የተዝረከረኩና ውስጣዊ ግኑኝነት በሌላቸው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች ላይ መሰማራት ነው ዋናው ፈሊጥ ለመሆን የበቃው። ከዚህ ጋር ተያይዘው የተስፋፉት ባህልን ለማደስ የማይችሉ የብልግናን መስኮች፣ ሆቴል ቤቶችና የዕፅ ንግድና የጨአት መቃሚያ ቤቶች፣ እንዲሁም ከኦርቶዶክስና ከእስልምና ሃይማኖት ጋር የማይጣጣሙ እንደገብሮ-ሰዶማዊነት የመሳሰሉት በመስፋፋታቸው በተለይም የወጣቱ ትውልድና የተወሰነው የንዑስ ከበርቴው መንፈስ ሊላላ ቻለ። ማድረግና መደረግ በሌላቸው ነገሮች መሀከል ያለውን ልዩነት እንዳያውቅ ተደረገ። ናኦሚ ክላይን The Shock Doctrine በመባል በሚታወቀው መጽሀፏ የአሜሪካ የነፃ ገበያ አቀንቃኞች (Ideologists)   መንፈሱ ከትራዲሽናል እሴቶች የፀዳና ጭንቅላቱ የታጠበ የህብረተሰብ ኃይል በማንኛውም አገር መፈጠር አለበት ብለው የሰበኩት በአገራችንም ምድር ዕውን ሊሆን በቃ። እነሱ በሚፈልጉት መልክ መንፈሱ በተበላሸ መልክ የተቀረጸ አዲስ የህብረተሰብ ኃይልን ለመጠምዘዝና ለማዘዝ፣ እንዲሁም ጠቅላላውን እሴትንና ግብረ-ገብነትን ልምጥፋት ይቻላል። በእግዚአብሄር የሚያመልክ ሳይሆን በሰይጣን የሚያመልክ ትውልድ ይፈጠራል። ይህ ዐይነቱ ትውልድ ደግሞ ለሁለት ሺህ ዐመታት ያህል አንድን አገር እንደ አገርና ህብረተሰብ እንዲመሰረትና እንዲገነባ ያደረጉና፣ ህዝብን ያስተሳሰሩና ለመንፈሳዊነት መዳበር እጅግ አስፈላጊ የሆኑ እንደ ኦርቶዶክስ የመሳሰሉ ሃይማኖቶች መወገድ አለባቸው። እነዚህን የመሳሰሉት ከትውልድ ወደ ትውልድ የተላለፉ እሴቶችና ሃይማኖት ደብዛቸው ሲጠፋ የውጭ ኃይሎች ገብተው እንደፈለጋቸው መጨፈር ይችላሉ፤ በዚያው መጠንም ብልግናን ያስፋፋሉ። በቀላሉ ሊገዛና ለማስተዳደር የማይቻል ህብረተሰብ እንዲፈጠር ያደርጋሉ።  በዚያውም የአገር ወዳድነት-ስሜት፣ ፍቅርና መተሳሰብ ይሸረሸራሉ። ከመረዳዳትና ከመተሳሰብ ይልቅ ሁሉም በየፊናው ገንዘብ አሳዳጅ በመሆን በተለይም ደሃውንና ደካማውን የህብረተሰብ ክፍል ዞር ብሎ የሚያየው አይኖርም።  ይህ ዐይነቱ አካሄድ ነው ለዛሬው ውዝግብ መሰረቱን የጣለውና ለአደጋም የጋረጠን።

የህውሃት አገዛዝ ከወደቀና በአዲስ ኃይል ከተተካ በኋላ አዲስና ብሩህ ሁኔታ ይፈጠራል የሚል ዕምነት ነበረን። አብዛኛዎቻችን በደስታ ፈንድቀን ነበርን። መልኩን አሳምሮና ተኳኩሎ ብቅ ያለው አዲሱ ኃይል  ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ  እያለ የሁላችንንም ልብ በላ። ኢትዮጵያ ታደሰች፣ በአዲሱ መሪያችንም በመመራት አዲስ የታሪክ ምዕራፍ የሚከፈትባት አገር የመሰለን ብዙዎች ነበርን። የቃለ-መጠይቆች ጋጋታ፣ የዩትብ ቻናሎች ውይይትና ክርክር ሁሉ ያስተጋቡት የነበረው አዲስና ሊበራል የሆነ አገዛዝ የተፈጠረ አስመስሎት ነበር። ሁላችንም ተታለልን፤ አንዳችንም የተሸወድን አለመሰለንም ነበር። ጥያቄዎችንም አላነሳንም። በጭፍን መንፈስ በመመራት ሁሉንም ነገር ለአዲሱ መሪያችን ለቀቅነው። በራስ ከመመካትና በነፃ አስቦ ለዕውነተኛ  ነፃነት ከመታገል ይልቅ ሁሉም ነገር “ለሊባራሉና ብሩህ አስተሳሰብ ላለው” ፣ ፈገግ እያለ ለሚያታልለን፣ እግዚያብሄር ከላይ ወደታች እንደጣለልን ነገር አፋችንን ከፍተን መከተልን ተያያዝነው። የኋላ ኋላ ጥያቄዎችን ስናነሳ በዚያው ግለሰብን በማምለከ በገፋው የሚነዳ ኃይል እንደጠላት መታየት ጀመርን። ድሮ አብረን የምንበላ ጓደኛሞች  ተኮራረፍን። በተለይም ተማርን ነን የሚሉት በጭፍን በመመራት፣ የመማርን ጉዳይ በጥያቄ ውስጥ እንድናስቀምጠው ተገደድን። ይሁንና ይህ ዐይነቱ በጭፍን አንድን ግለሰብ ማምለክ ከፊዩዳላዊ አስተሳሰብና ከተሳሳተ የዕውቀት አቀሳሰም ጋር የተያያዘ ለመሆኑ መገንዘቡ ይህን ያህልም ብዙ ጊዜ አልፈጀብንም። ለዚህ ዐይነቱ አንድን ግለሰብ በጭፍን መከተልና ማመን ደግሞ ኢምፔሪሲዝም ወይም ፖዘቲቭ ሳይንስ በመባል የተመሰረተው የትምህርት ዐይነት ነው። በነገሮች ላይ መተሳሰር እንዳለ የማያምን የትምህርት አሰጣጥ ዘዴ ነው። ሁሉም በየፊናው የሚሯሯጥ፣ አንደኛው በሌላኛው በአዎንታዊም ሆነ በአሉታዊ መልክ የሚገለጽ ተፅዕኖ አይኖረውም የሚል ነው። የታሪክን ሂደት በቅጡ እንድንገነዘብ የሚያደርግ አይደለም። በትላንትናውና በዛሬው፣ እንዲሁም በነገው መሀከል መተሳሰር እንዳለ አይቀበልም። በተለያዩ ጊዜያት መሀከል በረቀቀ መልክ የሚኖር ግኑኝነት(Time Binding) እንዳለ አይቀበልም። ሁሉም ነገር ከዛሬው አንፃር ብቻ ነው የሚታየው። ስለሆነም በዚህ ዐይነት የትምህርት አሰጣጥ ዘዴ የሰለጠኑ ሰዎች በቀላሉ የመታለል ዕድል ያጋጥማቸዋል። በተሸብረቀረቁ ነገሮች በቀላሉ ይታለላሉ። የነገሮችን  ሂደት ረጋ ባለና በጠለቀ መንፈስ የመመርመር ኃይል የላቸውም። እንደ አቢይ የመሳሰሉት ሸዋጅ ሰዎች በሚናገሩት ቃላት፣ ይሁንና ሳይንሳዊ ይዘት በሌላቸው አነጋገሮች በቀላሉ ያታለላሉ። ወንዱም ሴቱም በመታለል ሳያውቀው አገር አፍራሽ ይሆናል። ይህ ሁኔታ ነው ባለፉት ስድስት ዓመታት የተፈጠረው።

ለማንኛውም የአቢይና የግብረ-አበሮች አገዛዝ፣ ወይም ደግሞ የኦነግ አገዛዝ ልክ እንደወያኔው አገዛዝ የአሜሪካና የተቀረው የምዕራቡ ዓለም ፕሮጀክቶች ለመሆናቸው ለአብዛኛዎቻችን ይህን ያህልም ግልጽ አይደለም። በተለይም አቢይ አህመድ የአሜሪካና የሳውዲ አረቢያ ፕሮጀክት ለመሆኑ የተረጋገጠ ጉዳይ ነው። ይህንን ጉዳይ ለመረዳት አቢይ ስልጣን ላይ ከወጣ በኋላ የተከተለውን ፖሊሲ ማጤን ያስፈልጋል። ይኸውም ወያኔ ከዘረጋውና ካዳበረው የጎሳ ፌዴራሊዝም ፈቀቅ አለማለቱ ነው። በሁለተኛ ደረጃ፣ ግልጽ ያልሆነለትንና ሊገባው የማይችለውን የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ የሙጥኝ ብሎ መያዙ ነው። ይህ ዐይነቱ አካሄዱ ደግሞ ለራሱና ለተቀረው የኦሮሞ ኤሊት የሚያመቸው ነው። በዚህ ዐይነቱ ከፋፋይና አገርን የሚያዳክም ፖሊሲ ብቻ ነው ስልጣን ላይ ለመቆየት የሚችለው። ከዚያም አልፎ በመሄድ ከወያኔ ጋር የነበረውን ውስጣዊ ግኑኝነት በፍጹም አልበጠሰም።  በብዙ ነገሮች ከእነሱ ጋር እየተናበበ የሚሰራ ነው የሚመስለው። ይህ በእንደዚህ እያለ ራሱን ችሎ የወጣ በሽመልስ አብዲሳ የሚመራ የፈረጠመ አገዛዝ አገራችንን ወደ ከፍተኛ አደጋ ውስጥ የጣለ ነው። አቢይ አህመድና ሺመልስ አብዲሳ በሚከተሉት በተሳሳተ ትረካ ላይ በተመሰረተ “ፖለቲካ”  አማራጭና ተፎካካሪ ኃይል ብቅ እንዳይል ለማድረግ ችለዋል። በተለይም በአካባቢያቸ ያለውን ኃይል አኮላሽተውታል። በመሰረቱ ይህ ዐይነቱ ፖለቲካ፣ ፖለቲካ ብለን ከጠራነው ጠቅላላውን ኢትዮጵያን የሚያዳክም ሲሆን፣ በዚያው መጠንም የኦሮሞን ህዝብ  ጥቅም ሳይሆን ለአሜሪካንና ለአረቦች ታዛዥና ሀብትን አስበዝባዥ የሆነ በኦሮሞ ስም የሚነግድ አመጸኛ ኤሊት እንዲወጣ አድርጎታል። ጭንቅላቱ የታጠበ ወይም ደግሞ በጭንቅላቱ ውስጥ ምንም ነገር የሌለው ኃይል ስልጣንን በመቀዳጀት አገርን እንዳለ በማፈራረስ ላይ ይገኛል። በተለይም ህወሃት በአሜሪካኖች አቀነባባሪነት በስሜኑ ዕዝ ላይ ተኩስ ከፍቶ ከገደላቸውና ጦርነትም ከተቀሰቀስ በኋላ አቢይ አህመድ የተጓዘበትን መንገድ ማጤኑ በጣም አስፈላጊ ነው። ይኸውም የወያኔ ኃይል ሶስት ሳምንት በማይሞላ ጊዜ ውስጥ ከተበታተነና ከተዳከመ በኋላ እንደገና እንዲንሰራራ አመቺ ሁኔታን ፈጥሮለታል። የኢትዮጵያ ወታደር ከመቀሌና ከአካባቢው እንዲወጣ ከተደረገ በኋላ ወያኔ ኃይሉን በመሰብሰብና በመደራጀት ነው እንደገና በተለይም በአማራው ወገናችን ላይ ጦረነትን ለመክፈት የቻለው። በተለይም በወሎና በአፋር ህዝብ ላይ ያደረሰው ዕልቂት የሚታወቅ ጉዳይ ነው።

በአጭሩ አቢይ  አህመድ የሚባለው እጅግ አደገኛ ስይጣናዊ ሰው ስልጣንን ከጨበጠ ጀምሮ ህዝባችን እረፍትን አግኝቶ አያውቅም። ቤተክርስቲያናት ወድመዋል፤ አሁንም ይወድማሉ፤ ዲያቆኖችና ቄሶች ተገድለዋል፤ አሁንም ይገደላሉ፤ የተቀሩትም ተሰደዋል። የኦርቶዶክስ ኃይማኖት እንደጠላት በመታየት ሊከፋፈል የሚችልበት ሁኔታ ተዘጋጅቶለታል። አቢይ አህመድና ግብረአበሮቹ በማያገባቸው ቦታ ውስጥ ሰተት ብለው በመግባት ከኢትዮጵያና ከአንድነቷ ጋር ተነጥሎ ሊታይ በማይችለው በኦርቶዶክስ ሃይማኖት ላይ ከፍተኛ ዘመቻ በማካሄድ ቤተክርስቲያኗን ለማዳከም ያላደረጉትና የማያደርጉት ሙከራ የለም።  አቢይ አህመድ ከዚህ አልፎ በመሄድ አገሪቱ በሶስት እንድትከፋፈል ከአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ትዕዛዝን በመቀበል ይህን ተግባራዊ ለማድረግ የማይሸርበው ነገር የለም። አቢይ አህመድ በራሱ ጭንቅላት የሚመራ ሳይሆን በአሜሪካኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስተር በብሊንከንና በጆርጅ ሶሮን በሃብታሙ የሚመራ ሰው ነው። ዋና ዓላማውም በስንትና ስንት ትግልና መስዋዕትነት የተገነባችውንና  የቆንጆ ህዝብ አገር የሆነችውን፣ የሚያማምር የተፈጥሮ አቀማመጥና ባህል ያለውን አገርና ህዝብ ለአንዴም ለመጨረሻም ጊዜ ለመበታተን የተነሳ አደገኛ ኃይል ነው። እነአቢይ እንደሚነግሩን ከሆነ እኛ የምናውቃትንና አባቶቻችንና እናቶቻችን ያስተላለፉልን ኢትዮጵያ በማፈራረስ እነሱ በሚፈልጉት የብልጽግና መንፈስ፣ ይሁንና ደግሞ በብልግናና በስይጣናዊ መንፈስ በመመራት የረክሰችና የተዋረደች ኢትዮጵያን “ለመገንባት”ነው። መንፈሳዊ ተሃድሶን የሚቀናቀንና ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ ዕድገት የማያመች በዘረፋ ላይ የተመሰረተ አገር ነው ለመገንባት የሚፈልጉት እንጂ የበለጸገችና የእያንዳኑን ዜጋ መብት የምታስጠብቅና ፍላጎቱንም የምታሟላ ኢትዮጵያ አይደለም። በዚህ ዐይነት አካሄዳቸውም በአውሮፓ ምድር ውስጥ በአስራአምስተኛውና በአስራሰባተኛው ክፍለ-ዘመን ብቅ ያሉትን ሬናሳንስና ኤንላይተንሜንት የሚባሉትን መሰረታዊ አስተሳሰቦች የሚቀናቀኑ ናቸው። በሬናሳንስም ሆነ በኢንላይተንሜንት አስተሳሰብ አርቆ ማሰብና( Rational Thinking) ሎጂካዊ አስተሳሰብ ለአንድ ህብረተሰብ ግንባታ በጣም አስፈላጊ ናቸው። የአንድ አገር ግንባታ በሁለ-ገብና በሳይንሳዊ ዕውቀት መደገፍ አለበት።  የእነ አቢይ የብልጽግና አካሄድ ግን ይኸኛውን ሳይንሳዊውንና ለሰው ልጅና ለህብረተሰብ በጣም አስፈላጊ የሆነውን መሰረተ-ሃሳቦች የሚቀናቀን ነው። በጉልበትና በሽወዳ፣ እንዲሁም በመለፍለፍ የሚያምን ነው። ዕውነተኛ ግለሰብአዊ ነፃነትንና ማህበራዊ መተሳሰብን የሚያጎናጽፍ አይደለም። ይህ ዐይነቱ አካሄድ ጠቅላላውን ህዝባችንን የሚጎዳና ለዝንተ-ዓለም እየተናቆረ እንዲኖር የሚያደረገው ነው። ጥቂቶች ካልሆኑ በስተቀር ማንም ተጠቃሚ አይሆንም።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ጨለማውን ከማውገዝ አንድ ሻማ ማብራት -መስቀሉ አየለ

ወያኔ የሰፊውን የትግሬ ብሄረሰም ጥቅም አስጠባቂ ያልሆነውን ያህል፣ አቢይና ግብረአበሮቹ፣ እንዲሁም እነጃዋርና የተቀረው ደንቆሮ የኦሮሞ ኤሊት በሙሉ የኦሮሞን ብሄረሰብ ጥቅም የሚያስጠብቁ አይደሉም። በስሙ እየነገዱ ደሀና ደንቆሮ ሆኖ እንዲቀር የሚያደርጉት ናቸው። አንድ ብሄረሰብ ነኝ የሚል ከሌላው በመነጠል አይደለም የራሱን ጥቅም የሚያስጠብቀው፤ ሳይንሱም አይፈቅድም። ክሌላው ጋር በንግድ አማካይነት፣ በምርት ቦታ፣ በትምህርት ቤቶችና በልዩ ልዩ የመገናኛ መስኮች ሲገናኝ ብቻ ነው ማንኛውም ግለሰብ እንደሰው ሊታይና ውስጣዊ ኃይል ሊያገኝ የሚችለው። ከሌላው ጋር ሲገናኝና ሲጋባ ብቻ ነው ቋንቋንና ልዩ ልዩ ባህሎችን ማዳበር የሚችለው። ራሱን ነጥሎ፣ ይህ የእኔ ብቻ  ነው የሚል የአንድ ህብረተሰብ ክፍል አካል የመጨረሻ መጨረሻ ይጎዳል፤ ይጠቃልም። አንድ ዐይነት አስተሳሰብ በተስፋፋበትና እያንዳንዱ ብሄረሰብ ራሱን አግልሎ በሚኖርበት አካባቢ የስራ-ክፍፍልና ፈጠራዎች በፍጹም ሊዳብሩ አይችሉም። ወያኔ ቀድሞ፣ አሁን ደግሞ አቢይ አህመድና ግብረአበሮች ይህንን ዐይነቱን የተፈጥሮንና የህብረተሰብን ህግ በመጣስ በብዙ ሚሊዮኖች ድር የተሳሰረን ህዝብ በብሄረሰብ ነፃነት ስም አሳበው ለመነጣጠል ነው የሚፈልጉት። በዚህ አካሄዳቸው በይበልጥ የሚጎዳው የኦሮሞ ብሄረሰብ ነኝ የሚለው ምስኪኑ ደሃ ህዝብ ነው። አንድ ሰሞን በቦረና የተከሰተው ድርቅና ረሃብ የሚያረጋግጠው ይህ ሁኔታ ለአዲሱ የኦሮሞ ኤሊት ደንታ እንደማይሰጠው ነው።  አዲሱ ኤሊት በቪላ ቤት ውስጥ ሲኖርና ጥሩ ጥሩ ምግቦች ሲመገብ፣ ደሃው ህዝብ ይራባል።  አንድ ነገር በአገራችን ምድር ቢፈጠር ደግሞ እነ አቢይ አህመድማ ግብረ-አበሮቹ ወደ ውጭ ለመሸሽ ቀድሞውኑ ተዘጋጅተዋል። ሀብት አሽሸዋል፤ ቤትም ገዝተዋል፤ ልጆቻችውንም አሽሸተዋል። ስለሆነም አክራሪ የሆነው የኦሮሞና የትግሬ  ወጣት ቆም ብሎ ማጤን አለበት። ዝም ብሎ ከመነዳት ይልቅ ራሱን መጠየቅ አለበት። የነገሮችን ሂደት ለመገንዘብ መማርና ማወቅ አለበት። ከወያኔ፣ አሁን ደግሞ ከእነ አቢይ አህመድና ጃዋር የሽወዳና የማጭበርበር ፖለቲካ መላቀቅ አለበት። ሰው መሆኑን ማረጋገጥ አለበት። ማንም ሰው ብሄረሰብ ሆኖ የተፈጠረ እንደሌለ መገንዘብ አለበት። ባጭሩ ራሱን ማግኘት አለበት።

ስለሆነም ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ ትንሽ ትልቅ ሳይባል የእነ አቢይ አህመድን አገርን የመከፋፈልና የመበታተን አካሄድ በማጤን በአንድነት በመነሳት አገሩንና ራሱን ከአደጋ ማዳን አለበት።  በተለይም ወታደሩና የፀጥታው ኃይል በእነ አቢይ አህመድ መላ-ቅጥ በሌለው አገዛዝና አገርን በሚያፈራርስ አካሄድ የሚታለልና የሚታዘዝ መሆን የለበትም። አቢይ አህመድ ለማንኛውም ብሄረሰብ ዕድገትና የኑሮ መሻሻል የቆመ አይደለም። ለዝንተ-ዓለም ስልጣን ላይ ለመቆየት ብቻ የሚታገል ፍጡር ነው። እንደዚህ ዐይነቱ በስልጣን ጥም የሰከረ ሰው አንድን ርዕዮተ-ዓለም ወይም የጎሳን ጥያቄ ተገን በማድረግ ስልጣን ላይ ለመቆየት የሚፈልግ እንጂ እንወክለዋለው የሚለውን ጎሳ ጥያቄ የሚመልስ አይደሉም። በአጠቃላ ሲታይ የኦሮሞ ኤሊቶች ዕውቀት ስለሌላቸውም አንዱን ጎሳ ከሌላው ጋር በማጋጨት ስልጣናቸውን ላልመልቀቅ የሚታገሉ ናቸው። አቢይ አህመድና ግብረ-አበሮቹ ከውጭ ወራሪ ኃይል በባሰ መንገድ አገርን የሚያፈራርሱና ባህልንም የሚያወድሙ ናቸው። ስለሆነም የጊዜውና አንገብጋቢው ጥያቄ እንደነዚህ ዐይነት ሰዎችን ከስልጣን ላይ ማስወገድ ብቻ ነው።

ከውጭ ሊወረን የሚፈልግ ኃይል ብቻ ሲመጣ መነሳት ሳይሆን፣ ዛሬ አገራችንን ከውስጥ ሆኖ ለማፈራረስ ታጥቆ የተነሳ የተደራጀ ኃይል ስላለ እሱን ማስወገድ የመጀመሪያው ተግባር መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። አንድ አገር አንድ ጊዜ ከፈራረሰ በኋላ የውጭ ኃይሎች መጫወቻ ስለሚሆን እንደገና መልሶ መገንባት በፍጹም አይቻልም። ስለሆነም እናቶቻችንና አባቶቻችን የጣሉልንን አደራና የጥንካሬ መንፈስ በማደስ በመተባበር አገራችንን ከዚህ ዐይነቱ የጭራቅ ኃይል ማዳን አለብን። አቢይ ራሱን ለማዳን ሲል ሲስቅ በፍጹም አለመታለል። እሱንም ከእንግዲህ ወዲያ እንደ አገር መሪ ማየት መቆም አለበት። ተመርጫለሁ በማለትና በህገ-መንግስቱ እያሳበበ እንደነቀርሳ በሽታ አገራችንን ከውስጥ ሲሰረስረን ዝም ብሎ ማየት የወንጀሉ ተባባሪ መሆን ነው። በተለይም ለአቢይ የምታጎበድዱ የብአዴን ሰዎች እስካሁን ድረስ ጭቁኑ የአማራ ህዝባችሁ በመንግስት በተደራጀ የኦነግ/ሸኔ በሚባል የመጠሪያ ስም በሚንቀስቀስ ኃይል ሲገደል፣ ሲታረድና ተፈናቅሎ ሲሰደድ ዝምባልችሁ ስታዩ ከርማችኋል። አንዳንዶቻችሁም የራሳችሁን ህዝብ እንደወራሪ ኃይል እያያችሁ እዚያ ማን ሂድ አለህ በማለት በህዝባችሁ ላይ አሹፋችኋል። መታወቅ ያለበት ጉዳይ የኦሮሞ ብሄረሰብ ወደ ወለጋና ወደሌሎች የአገሪቱ ግዛቶች ከመስፋፋቱ በፊት የአማራው ብሄረሰ ከአስራ-አራተኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ፣ በተለይም የኦርቶዶክስን ሃይማኖት ለማስተማር ሲሰማራ ነበር። በየሄደበትም ቦታ አካባቢዎችን ሲያለማና ተገባቶና ተዋልዶ የኖረ ህዝብ ነው። ራሱን አግልሎ የሚኖር ብሄረሰብ አልነበረም። ስለሆነም የአማራውን ብሄረሰብ እንደመጤ ማየቱና በእሱ ላይ ዘመቻ ማድረጉ የህብረተሰብን አገነባብ ታሪክ ካለማወቅ የሚነዛ ወሬ ነው።

ያም ተባለ ይህ ሁላችንም በእንደዚህ ዐይነቱ የተሳሳተ ትረካ መጠመድ የለብንም። ወያኔና አቢይ አህመድ ከእነ ግብረአበሮቹ የአሜሪካኖችና የተቀረው የካፒታሊስት አገሮች፣ እንዲሁም የአረብ አገሮች ስራ አስፈጻሚዎች መሆናቸውን በመገንዘብ በአንድነት መነሳት አለብን። በሚሆን በማይሆን ነገር ጭንቅላታችንን መጥመድ የለብንም። መማርና ማወቅ ነው ከአደጋና ከተንኮል ሊያድነን የሚችለው። ይህ ሲሆን ብቻ ነው ለሁላችንም የምትሆንና ለተከታታዩ ትውልድ የሚተላለፍ ጠንካራ አገር መገንባትና ማስተላለፍ የሚቻለው። ስለሆነም ከሁለት አንዱን መምረጥ አለብን፤ ይኸውም ኢትዮጵያ ስትፈራርስና ህዝቦቿ ሲሰደዱ ማየት፣ አሊያም በዕውቀት አማካይነት ኃይላችንን በማስተባበር የአድዋ ጀግኖች የጣሉልን መንፈስና ታሪክ እንደገና በማደስ ለአዲስቱ ኢትዮጵያ መታገል። ክተግባባንና ከተባበርን የማይቻል ነገር ስለሌለ ስው መሆናችንን በዓለም ፊት ማረጋገርጥ አለብን። የተሃድሶና የኢንላይተንሜንት እንቅስቃሴዎች እንደሚያስተምሩን፣ ራስን ማወቅ፣ ለዚህ ደግሞ በተከታታይ ማጥናትና መመራመር፣ የነገሮችን ሂደት በሚገባ ማየት፣ በዲሲፕሊን መመራት፣ ሀቀኛ መሆን፣ የራስን ሳይሆን የአገርንና የህዝብን ጥቅም ማስቀደም፣ ማንኛውንም ነገር በሆይ ሆይ ሳይሆን በጥንቃቄ መስራት፣ በገንዘብ አለመታለል፣ ተንኮልን ከጭንቅላት ውስጥ ነቅሎ ማውጣት፣ ለሌላው ሰው አሳቢ መሆን፣ አለሁ አለሁ ብሎ አለመታየት፣ በተፈጥሮና በሰው መሀከል ግኑኝነት እንዳለ በመረዳት በተፈጥሮ ላይ ዘመቻ አለማደረግ፣ ጥበብን ማስቀደም፣ በስነ-ምግባርና በሞራል መመራት። የአድዋም ድል መልዕክትና መመሪያ ይህ ነው። እንደ አፄ ምኒልክ አስተዋይና አርቆ አሳቢ መሆን፣ ለማንም ሳያደሉ ሁሉንም በእኩል ማየት፣ ፍትሃዊነትን ማስቀደም። እነዚህ መሰረተ.ሃሳቦች ናቸው የአፄ ምኒልክ መመሪያዎች።

ለማንኛውም ዛሬ አገራችንና ህዝባችን ከተደቀኑበት አደጋ ስንነሳ የአድዋን የ128ኛው ዓመትን ድል በዓል እንደገና ስናከብር በተደበላለቀ ስሜትና ግራ በመጋባት መንፈስ ነው። ይሁንና ግን የዛሬው የጨለማ ሁኔታ እንደሚያልፍ አንዳችም ጥርጣሬ እንዲኖረን አይገባም። ዛሬ ያቧረቁና በአጉል ብልጣብልጥነት ደስታን የተጎናጸፉ የሚመስላቸው ሰዎች ኃይለኛ ነፋስ እንደሚወስደው ነገር ይበናሉ። መሳቂያና መሳለቂያ ይሆናሉ። ድርጊታቸው ሁሉ ከዕውቀት ማነስና ራስን-ካለማወቅ የመነጩ በመሆናቸው የመጨረሻ ኑሯቸው ሀዝንና መጨማደድ ይሆናል። በታሪክ ውስጥ ስፊ ህዝብን አሰቃይቶና በህዝብ አላግጦ ሳይዋረድ ከስልጣኑ የተወገደ የለም። በፖለቲካ ዓለም ውስጥ ቂም-በቀልነት ቦታ ባይኖረውም እነ ወያኔና አቢይ አህመድ የውጭ ተላላኪዎች በመሆን የአገራችንን ታሪክ ማርከሳቸውና ህዝባችንን ማዋረዳቸው ከተጠያቂነት የሚያስመልጣቸው መሆን የለበትም። በህግ ፊት የሚጠየቁበት ዘመን መምጣቱ አይቀርም። ለዚህ ሁሉ መፍትሄው ጠንካራና በጠላቶቿ የማትገበርና ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ለማስተናገድ የምትችል ዲሞክራሲያዊና ጠንካራ አገር መገንባት ነው። ከጎሳና ከሃይማኖት ባሻገር አብዛኛዎቻችን ኢትዮጵያችን እንድትፈረካከስ አንፈልግም። ከብዙ ዓመታት የማያቋርጥ ጦርነትም ህዝባችን መላቀቅና እፎይ ብሎ መኖርን ይፈልጋል። አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ፍላጎቱና ምኞቱ አንድ ነው። በሰላም መኖር፣ ቤተሰብ መመስረት፣ ልጆች ወልዶና አስተምሮ ደስታን መጎናጸፍ፣ የስራ ዕድል በማግኘት ራሱን ችሎ መኖር ነው። ማንኛችንም፣ ከዚኽኛው ወይም ከዚያኛው ጎሳ ብንመጣምና በሃይማኖት ብንለያይም እንደሰው ለመኖር ከፈለግን ላይ ከተዘረዘሩት ሃቆች ልናመልጥ አንችልም። ይህም ማለት፣ መብላትና መጠጣት አለብን፤ መኖርም አለብን። ለመብላትና ንጹህ ውሃ ለማግኘት ደግሞ የግዴታ መስራት አለብን። የስራ መስኮችም መከፈት አለባቸው። ለዚሁ ሁሉ ቁልፉ ደግሞ ሰላም ማግኘትና በሰለጠነ መልክ አገርን ማስተዳደር ነው። ለዚህ ደግሞ የሰለጠነ አገዛዝና መንግስታዊ መዋቅር ያስፈልጋል። የሰለጠኑ ሰዎች ስልጣንን ሲቀዳጁ ብቻ ነው አገርን በሰለጠነ መልክ ማስተዳደርና ጠንካራ አገር መገንባት የሚቻለው። በዚህ መንፈስ ብቻ ነው አገራችንን መገንባትና ለተከታታዩ ትውልድ ማስተላለፍ የምንችለው።  መልካም ግንዛቤ!!

 

fekadubekele@gmx.de

www.fekadubekele.com

 

3 Comments

 1. Dr.Fekadu
  Thank you for the timely eye -opener and balanced messages about our Ethiopian heritage and history. The Adwa anniversary and others I attended at Debre Berhan I attended three years ago inspired me very much. I was part of that generation condemning the emperors and our own great patriotic Amhara ethnic groups. All the western evil capitalists are using this agenda as revenge for their defeat at Adwa to suppress our spirit. I plan to write about reformation, for good or bad, that we wrongly condemn our noble kings  Zera Yakob top Mienilk.
  Please keep up your great contribution for the true emancipation and progress of our misfortune Ethiopia.
  Sincerely,
  Eddie aka Adefris Habte Mekasha
  Community Leader and Chaplain

 2. እንደሁለዬውም ዶር ፍቃዱ በቀለ በአገራችን ና በህዝቧ ላይ የደረሰውን አሳፋሪ ገፅ ከምክንያታዊና ሳይንሳዊ አመለካከት ሲተነትኑ ይህ የመጀመሪያቸው አይደለም:: እሳቸውን የመሰለ ምሁር ማግኘታችን የሚያጽናና ቢሆንም የሚሰጡትን ትምህርትና ምክር ተቀብሎ በተግባር የሚገልፅ የተደራጀ ማህበረሰብ አለመኖሩ አሳዛኝና አሳፋሪ ነው:: አንዱ ድክመታችንና ላለንበት ብሎም ሊመጣ ለሚችለው አደጋ የሚዳርገን ለእነ ዶር ፍቃዱ አይነቶች አገር ወዳድ ምሁራን ክብርና ቦታ አለመስጠታችን ምክራቸውንም አለመቀበላችንና በተግባር አለመግለጣችን ነው:: በተለይም ተምሬአለሁ የሚለው እሳቸውንም ጭምር በድርጅት መልክ አለመሰብሰባቸው ለውድቀታችን የድርሻውን አበርክቷል::
  አሁንም ቢሆን በተነተኑት ሳይንሳዊ የለውጥ ህሳቤ የሚመራ የፖለቲካ ተቋምና እንቅስቃሴ መኖር አለበት:: በብሶትና በቁጭት ብቻ የሚደረግ ትግልና የሚከፈል መስዋእትነት ብቻውን ለስር ነቀል የስርአት ለውጥ አያበቃም:: ትግሉ በፍልስፍና የታገዘ ራእይ የነደፈ ካልሆነ የቡድን ሽኩቻ ይሆንና ከድጡ ወደ ማጡ የመግባት ዕድሉ ከፍተኛ ነው::
  ከዓለም አቀፉ የወራሪ ዘንዶ አፍ ልንወጣና የዳግም አድዋ ድል ባለቤቶች ልንሆን የምንችለው ታሪክና መልካም ባህላችንን አክብረን ከዘመናዊ አገር ወዳድ የፖለቲካ የኤኮኖሚና የማህበረሰብ ፍልስፍና ጋር አጣምረን ስንነሳ ብቻ ነው:: በግብተኛና በብሶት ብቻ የሚደረግ ትግል ምንም እንኳን ፍትሃዊ ቢሆንም ለዘላቂ እድገትና ብሔራዊ ነፃነት አያበቃንም:: ለተረኛ ተላላኪ ቡድን የሥልጣን መሰላል ላለመሆን
  ዋስትና የለም::ለዚያ መዳኛው የምናደርገው ትግል ከእውቀት ጋር የተሳሰረ መሆን አለበት :: አሁን የሚደረገው የፋኖ ትግል ለዚያ መረማመጃ እንዲሆን እንጂ የመጨረሻ ግብ ተደጎ መታዬት የለበትም:: የወታደራዊ ድሉ ለፖለቲካውና ለኤኮኖሚው ነፃነት እንዲያበቃ ሆኖ መቀረፅ ይኖርበታል:: ችግሮችን በግልፅ እያወጡ መወያዬት ህዝቡም እንዲያውቀው ማድረግ ይበልጥ አመኔታና በራስ የመተማመንን አቅም ይፈጥራል:: በቀድሞ አካሄድ በቡድንና በጭፍራ ህሳቤ መንጎድ ላለፉት አረመኔ የደርግ የወያኔና አሁን ላለው የኦነጋውያን አገር አጥፊ ስርአቶች ስለዳረገን ያ እንዲደገም መፍቀድ አይኖርብንም::
  በሰከነና ሳይንሳዊ በሆነ አመለካከት የወደፊቷ ኢትዮዽያ የምትፈጠርበትን ዴሞክራሲያዊ አሰራር መተግበር ተገቢ ነው:: ይህንን እንደ ቅንጦት ወይም ፋኖን እንደመቃወም እዬቆጠሩ በጭፍን እንሂድ ማለት ውድቀትን መጋበዝ ይሆናል::የዶር ፍቃዱም አስተምሮ ይህንኑ ብሔራዊ ነፃነት የምናስከብርርበት ብቸኛ መንገድ የሚያብራራ ሲሆን ከልምድና ከእውቀት ጋር የተያያዘ ምክራቸውን ስለሰጡን ላመሰግናቸው እወዳለሁ
  ከአክብሮት ጋር
  አገሬ አዲስ

 3. አገሬ አዲስ አልሽን ሳንታደስ በቆየን ነበር ያልሽው ትክክል ነው በገበሬው ታክስ ተምረው ዱፍትርናውን ተቀብለው ሀገር በማጥፋት ረገድ ከወታደሩ በላይ በሀላፊነት መጠየቅ ይገባቸዋል እላለሁ። በአንጻሩ የሀገራቸው ነገር ቁጭት ውስጥ ከትቷቸው እንዲህ ያለ ትምህርት ሰጭ ዜጎችንም ሳናመሰግን. አናልፍም። ጠንካራ ምሁር ሁኖ ኢትዮጵያን ከወደደ ቴዎድሮስ ጸጋዬ፣ኤርምያስ ለገሰ፣ ስታሊን ገስላሴ ሞገስ ዘውዱ በነጠላና በቅንብር ከምድረገጽ ያጠፉታል። በዚህ ሳያበቁ የስብጥር ተኩስ ከፍተው አደናብረው ወንጀለኞችን እንዲደባለቁ ጫና አድርገው ካዋረዷቸው መሀል እነ ዶር ዳኛቸውን የመሰሉ ምሁራኖችም ነበሩን። ከአደናባሪዎቹ ትልቁን ድርሻ የያዘው በረቀቀ ትግሬያዊ ተንኮል የርእዮት ሚዲያ ባለቤት አቶ ቴዎድሮስን የሚያክለው የለም። ኢትዮጵያውያን እንደዚህ ያሉ በሰው ደም የሚነግዱ ክፉዎች ዘንድ መሄዳቸው ይገርማል ። እኔ እንኳን ብርሀኑ ነጋ በለጠ ሞላ አረጋዊ በርሄ የተባሉትን ካየሁ በሗላ ምሁር ማለት አምታቶ ያገኘው ዲፕሎማ ያለመሆኑን ከተገነዘብኩ ቆየሁ።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share