ኤፍሬም (emadebo@gmail.com)
የመሬት ላራሹን መፈክር አንግቦ በ1950ዎቹና 60ዎቹ የፊውዳሉን ሥርዓት መሰረት እየሸረሸረ የመጣው የኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴ በፊውዳሉ ሥርዓትና በጭሰኛው መካከል የተካሄደ የመደብ ትግል አካል ነው። ይህ አብዛኛውን አገር ውስጥና በውጭ አገሮች የሚገኘውን የኢትዮጵያ ተማሪዎች አቅፎ የተጀመረውና ለሁለት አስርተ አመታት የተካሄደው እንቅስቃሴ የአብዮቱ መባቻ አካባቢ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ጭቆና የ”መደብ ጭቆና” ነው በሚሉና የለም ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ጭቆና የ”ብሔር ጭቆና” ነው በሚሉ ኃይሎች ለሁለት ተከፈለ።
የ1966ቱ አብዮት ከፈነዳ በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የመደብ ጭቆና ነው የሚሉ ኃይሎች “ላብአደር” እና “ወዝ አደር” በሚል ቃል ጎራ ለይተው በየከተማው ሲገዳደሉ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የብሔር ጭቆና ነው የሚሉ ኃይሎች ደሞ መሳሪያ እንስተው የጫካ ውስጥ ትግል ጀመሩ።ወታደራዊው ደርግ መኢሶንን ተጠቅሞ ኢህአፓን ካጠፋ በኋላ መኢሶንንም አስወግዶና የኋላ ኋላ ኢሠፓን መስርቶ 17 አመት ሥልጣን ላይ ቆየ። የደርግ መንግስት የኢትዮጵያን ማህበራዊ፣ኤኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች ማስወገድ የሞከረው የማንንም ትብብርና ዕርዳታ ሳይፈልግ ብቻውን በራሱ መንገድ ስለነበር ኢትዮጵያን ከድጡ ወደ ማጡ ከመውሰድ ውጭ የኢትዮጵያ ህዝብ የጠየቀውን የመብት፣ የፍትህ፣ የነጻነትና የዲሞክራሲ ጥያቄ፣ በተለይ “ህዝባዊ መንግስት ይቋቋም” የሚለውን የረጂም ግዜ ጥያቄ ሳይመልስ በ1983 ዓም በብሔር ኃይሎች ተሸንፎ ከሥልጣን ተወገደ።
በህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ መሪነት በግንቦት 1983 ዓም አራት ኪሎን የተቆጣጠሩት የብሔር ኃይሎች ኢትዮጵያን በብሔር የሸነሸነ አዲስ ህገ-መንግስት ጽፈው የዛሬዋን ትግሬ፣ኦሮሞ፣ አማራ፣አፋር፣ሱማሌ፣ቤንሻንጉል ወዘተ እያለች እርስ በርስ የምትገዳደል ኢትዮጵያን ፈጠሩ። በዛሬዋ ኢትዮጵያ ውስጥ እኔ ኢትዮጵያዊ ትግሬ ነኝ፣ እኔ ኢትዮጵያዊ ኦሮሞ ነኝ ወዘተ ከሚል ድምፅ ይልቅ እኔ ትግሬ ነኝ፣ እኔ ኦሮሞ ነኝ የሚል ድምፅ እያየለ በመምጣቱ ባለፉት 40 አመታት ተወልዶና በዘር ግድግዳ ታጥሮ ያደገው ኢትዮጵያዊ+
ህወሓት በህዝባዊ ትግል ከሥልጣን ከተወገደ በኋላ የምናያት ያለፉት አምስት አመታት ኢትዮጵያ ደሞ በሁሉም ነገር ግራ የተጋባች ኢትዮጵያ ናት። በዛሬዋ ኢትዮጵያ በአንድ በኩል ዜጎች ሲገደሉና ሲታፈኑ፣የእምነት ተቋሞች ሲቃጠሉና አባቶች ሲታረዱ ዝም ብሎ የሚመለከት የብልፅግና መንግስት አለ፣ በሌላ በኩል ደሞ ይህ መንግስት ይሰር፣ይግደል፣ ይስቀል፣ ያፍርስ ወይም ያፈናቅል በጭፍን የሚደግፉትና “አቢቹ” ሺ አመት ኑርልን የሚሉ ደጋፊዎች አሉ። በሁለተኛ ደረጃ የብልፅግናን መንግስት ከመቃወም ውጭ የነገ ራዕይም አላማም የሌላቸው ብዙ ሰዎች አሉ። በሦስተኛ ደረጃ ደሞ እሱ ያመጣውን እሱ ይወስደዋል እያሉ የራሳቸውን ህይወት ብቻ የሚኖሩ ሰዎች አሉ። ኢትዮጵያ የእነዚህ ሁሉና የሌሎችም አገር ናት፣ ኢትዮጵያ የተረጋጋችና ሰላም የሰፈነባት አገር ስትሆን የሚጠቀው በየትኛውም ጎራ የተሰለፈው ኢትዮጵያዊ ነው። ታዲያ ለምንድነው ሁሉም ኢትዮጵያዊ በፖለቲካ አመለካከቱ ቢለያይም ለኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት ግን አብሮ የማይሰራው?
ህወሓት ኢሀዴግ የሚባል ፈረስ ሰርቶ ኢትዮጵያን ለ27 አመት እንዳሰኘው እንደጋለበ ሁሉ፣ ዛሬም የኢትዮጵያ ህዝብ የሚኖረው “ብልፅግና”ን የፈጠርነው ሥልጣን ከኦሮሞ እጅ እንዳይወጣ ለማድረግ ነው እያሉ ፊት ለፊት የሚናገሩና የተናገሩትን በተግባር እያሳዩን ያሉ መሪዎች ባሉበት አገር ውስጥ ነው። በአዲስ አበባና በዙሪያዋ የተካሄደው ከፍተኛ የቤት ማፍረስ ዘመቻ፣ የሸገር ከተማ ምስረታ፣በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤ/ክ ላይ የሚደረገው ዘመቻና አዲስ አበባ ውስጥ ያለምንም አገራዊ ስምምነት ወይም በአንድ ቡድን ውሳኔ ብቻ አፋን ኦሮሞ በትምህርት ቤቶች ውስጥ እንዲሰጥ መደረጉ የፖለቲካ ሥልጣን የኛ ነው የሚሉ የኦሮሞ ባለሥልጣኖች በማን አለብኝነት ከወሰዷቸው እርምጃዎች ጥቂቶቹ ግን ዋናዋናዎቹ ናቸው።
ደርግ ከንጉሳዊ ሥርዓት ወደ ግዜያዊ ወታደራዊ መንግስት ሽግግር ሲያደርግ፣ በቀኃስ ሥርዓት ውስጥ የነበሩ ቴክኖክራቶች ነበሩት። የደርግን መንግስት የተካው ህወሓትም ቢሆን ውስጡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እንቅስቃሴ አባላት የነበሩና የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ጨርሰው ሰራተኛ የነበሩ ሰዎች ነበሩበት። ዛሬ ኢትዮጵያን የሚመሩ ሰዎች ግን በህወሓት የጨለማ ዘመን የመላ መላ ትምህርት የተማሩ፣ይህ ነው ተብሎ ሊነገር የሚችል ዕውቀት የሌላቸው፣ ልምድ የሌላቸው፣ አርቀው የማይመለከቱ፣ የኢትዮጵያን ህዝብ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ባህል በጥልቅ የማይረዱ፣ ያለመረጃ ውሳኔ የሚወስኑ ችኩሎችና፣ ችኮዎች ናቸው። አገራችን ኢትዮጵያ በአጭር ግዜ ውስጥ ከአንድ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ለሞት፣ለስደትና ለረሃብ ከዳረገ የእርስ በርስ ጦርነት ወደ ሌላ ጭራሽ አገርን የመበታተን ችሎታ ወዳለው የእርስ በርስ ጦርነት የተሸጋገረችው ከአፍንጫቸው ጫፍ ርቀው የማያስቡ ችኩሎችና ችኮዎች ተሰባስበው ያለምንም ከልካይ አገር እየመሩ ስለሆነ ነው።
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ጨርሼ ዩኒቨርሲቲ የገባሁትና የስራ አለምን የተቀላቀልኩት በደርግ ዘመን ስለሆነ የደርግን ሥርዓት ኖሬዋለሁና ከየትኛውም ሥርዓት የበለጠ አውቀዋለሁ። የህወሓት ሥርዓት ተጀምሮ እስኪያልቅ ኢትዮጵያ ውስጥ ባልኖርም፣ የህወሓት ክፋትና ተንኮል ባህር ተሻጋሪ ነውና ህወሓትን ከሩቅም ቢሆን አውቀዋለሁ። አሁን በሥልጣን ላይ ያለውን መንግስት ግን ሲጀመር ጀምሮ አውቀዋለሁ፣በተለያዩ አጋጣሚዎች ከክልል እስከ ፌዴራል ድረስ ከሚገኙ ከተለያዩ ባለሥልጣኖች ጋር ተገናኝቶ የማውራት ዕድል አጋጥሞኛል።
ከአፄ ቴዎድሮስ እስከ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሤ ድረስ የነበሩት የኢትዮጵያ መሪዎች ዛሬ BA,BSC,MA,PHD እያልን በምንጠራው የትምህርት ደረጃ አልተማሩም፣ ነገርግን የአገርኛው ትምህርትና በቤተሰብ ደረጃ ተኮትኩተው ያደጉበት መንገድ አስተዋዮች፣ብልሆችና አርቆ አሳቢዎች እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። በደርግ ዘመን የነበሩ መሪዎችም ብዙዎቹ ወታደራዊ መኮንኖች ስለነበሩ የአመራር ትምህርቱም ችሎታውም ነበራቸው። በቅርብም በርቀትም ካወኳቸው ሦስት ሥርዓቶች ውስጥ በዘመናዊ ትምህርትም በወታደራዊ ትምህርትም የረባ ዕውቀት ሳይኖራቸው ማዕረጉን ብቻ የተሸከሙ፣አርቀው የማያስቡና አፋቸው እንዳመጣ የሚለፈልፉ መደዴዎች ተጠራቅመው የሚገኙት ዛሬ እራሱን ብልፅግና ብሎ በሚጠራው ሥርዓት ውስጥ ነው። ይህ የሚያሳየን ዛሬ አገራችን ኢትዮጵያን የገጠማት ችግር ምንጩ ክፋት ብቻ ሳይሆን አለማወቅም መሆኑን ነው። ክፋትና አለማወቅ ሲገናኙ ደሞ ምን ያክል አደገኛ እንደሆኑ የዛሬዋን ኢትዮጵያ ማየቱ ይበቃል።
የብልፅግና መሪዎች አርቀው የሚያስቡ ቢሆን ኖሮ ሁለት አመት እርስ በርስ ያጫረሰን የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት አይኖርም ነበር። ህወሓት ከሥልጣን ከተወገደ በኋላ ወደ ሥልጣን ለመመለስ ሙከራ ማድረጉ እንደማይቀርና ይህንን ለማድረግ ደሞ በሥልጣን ላይ በነበረበት ዘመን ያከማቸው ከፍተኛ ገንዘብ፣ የዲፕሎማሲ ድጋፍና ወታደራዊ ኃይል እንዳለው ለዛሬዎቹ ህወሓት አርግዞ ለወለዳቸው የብልፅግና መሪዎች ከ2010 ዓም ጀምሮ ተነግሯቸዋል። ህወሓት በሁመራ በኩል የጦር መሳሪያ እያስገባ መሆኑና ወታደራዊ ዝግጅት እያደረገ መሆኑንም ጦርነቱ ከመጀመሩ ከ18 ወር በፊት ተነግሯቸዋል። ግን ሞኝ ማሰብ የሚጀምረው ጎርፉ ሳይመጣ ሳይሆን መጥቶ ከወሰደው በኋላ ነውና የኛም የዋሆች ከህወሓት ጋር ጦርነት የገጠሙት ህወሓት በሰሜን ዕዝ ላይ ያንን አስቃቂ ዕልቂት ከፈጸመ በኋላ ነው። ስለዚህ ለሰሜን ኢትዮጵያው ዕልቂት ተጠያቂዎች የጦርነቱ አባቶች ህወሓቶች ብቻ ሳይሆኑ፣ የ120 ሚሊዮን ህዝብ አገር መሪ ሆነው ይህንን ህዝብ ከጥፋት የሚታደግ ምንም አይነት ዝግጅት ያላደረጉ የብልፅግና መሪዎችም ናቸው፣ ያውም ሁለት አመት ሙሉ እየተነገራቸው!
የብልፅግና ድንቁርና ህወሓቶች ከፍተኛ የጦርነት ዝግጅት ሲያደርጉ አያዩ የትም አይደርሱም ብለው ንቀው ማለፋቸው ብቻ አይደለም። ሁለት አመት የፈጀውና ከፍተኛ የህይወት፣ የአካል፣ የቁሳቁስና የአገር ኃብት መስዋዕትነት ተከፍሎበት ህወሓትን ያለ ልምዱና የለ ባህሉ እናንተ ማሩኝ እንጂ ትጥቅ ፈትቼ ሰላማዊ ህይወት እኖራለሁ ያሰኘ ወሳኝ ወታደራዊ ድል (Decisive Military Victory) በሃላላ ኬላው ስምምነት ውኃ እንዲበላው ማድረጋቸውና፣ ህወሓት አሁንም የስጋት ምንጭ እንዲሆን ያስቻለውን ወታደራዊ ኃይል እንደያዘ መንግስት ሆኖ እንዲቀጥል መፍቀዳቸው ነው።
የፕሪቶሪያው ስምምነት የተፈረመው የኢትዮጵያን ህዝብ በሚጠቅም (In terme of the Ethiopian people) ነው። የፕሪቶሪያው ስምምነት ተግባራዊ የሆነበት መንገድ ግን የኢትዮጵያን ህዝብ ጥቅምና ፍላጎት በሚጻረር መንገድ ነው፣ ስምምነቱን ተግባራዊ ሲደረግ በወዳጅነት ፓርክ የታዩ ትርዕቶችም እጅግ በጣም አሳፋሪዎች ነበሩ። የህወሓት ታጣቂዎች ትጥቅ አልፈቱም፣ ወደ ስላማዊ ህይወት ሽግግር አላደረጉም። ጌታቸው ረዳ የሚመራው የሽግግር መንግስት የተቋቋመው ህወሓት ከህወሓት ጋር ተነጋግሮ ነው እንጂ በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት የኢትዮጵያ መንግስትና ህወሓት ተነጋግረው አይደለም፣ ደግሞም የጌታቸው ረዳ መንግስት በስምምነቱ መሰረት ሁሉን አቀፍ መንግስት ሳይሆን የጦርነቱን አባቶች ያቀፈ መንግስት ነው።
አሜሪካ የገባሁት በማርች 1992 ዓም ነው። አሜሪካ ገብቼ North, South, Democrats, Republicans, Liberals and Conservatives የሚለውን የአሜሪካ የፖለቲካ ባህልና ይህንን ባህል ተከትሎ የተፈጠረውን ማህበራዊ ባህል ለማወቅ ብዙ ግዜ አልፈጀብኝም። እነዚህን ነገሮች ማወቅ የቻልኩት እየኖርኩባቸው በቴሌቪዥኑ፣ በመጋዚኑ፣ በጋዜጣው፣በተማርኩባቸው ኮሌጆችና በኖርኩባቸው አካባቢዎች ነው እንጂ ስራዬ ብዬ ለማወቅ ፈልጌ ባደርኩት ጥረት አይደለም።
በ2010 ዓም ሚያዚያ ወር ኢትዮጵያን ያክል ትልቅ አገር የመምራት ሃላፊነት የተሸከሙት የዛሬዎቹ የኢትዮጵያ መሪዎች ግን ባጠቃላይ የኢትዮጵያን ህዝብ ስነልቦናዊ ዘይቤ በተለይ ደሞ የሰሜን ኢትዮጵያን ህዝብ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ባህል (Societal & Political Culture) ከስድስት አመታት በኋላ ዛሬም የተረዱ አይመስልም፣ ለዚህ ነው ብልፅናዎች የሚመሩት የማያውቁትን ህዝብ ነው እየተባለ በተደጋጋሚ የሚነገረው!
የኢትዮጵያ መንግስና የህወሓት ኃይሎች ባደረጉት ሁለት አመት የፈጀ መራራ ጦርነት ከፍተኛ መስዋዕትነት የከፈሉትና ጨካኞቹ የህወሓት ኃይሎች ከፍተኛ የንብረት፣ የህይወትና የስነ ልቦና ጥፋት ያደረሱት አፋርና አማራ ክልል ውስጥ ነው። ይህንን ጥፋት የዚህ ጽሁፍ ጸሃፊ ደሴና ኮምቦልቻ ከህወሓት ኃይሎች ከጸዱ ሳምንት በማይሞላ ግዜ ውስጥ ደብረሲና፣ሸዋ ሮቢት፣አጣዬ፣ኮምቦልቻ፣ደሴ፣ሃይቅ፣ባቲ፣ ካሳጊታ፣ጭፍራ፣ሚሌና ሰመራ ድረስ ሄዶ በአይኑ ተመልክቷል። ሰሜን ሸዋ ውስጥ የአባትና ልጅን ህይወት በአንድ ጀምበር የቀጠፈ ጦርነት ተካሂዷል። ህወሓት በተለይ አማራ ክልል ማይካድራ፣ቆቦ፣መርሳ፣ሃይቅ፣ወልዲያ፣ኮምቦልቻና ጭና ውስጥ የብዙዎችን ህይወጥ የቀጠፈ የጦር ወንጀል ፈጽሟል። የህወሓት ታጣቂዎች ወጣት ሴቶችን ወላጆቻቸው ፊት ደፍረዋል፣ ልጅ እያየ ወላጅን፣ባል እያየ ሚስትን ረሽነዋል። የፕሪቶሪያው ስምምነት አገርን በሚጎዳና አሳፋሪ በሆነ መልኩ የህወሓትና የብልፅግና መሪዎች ተቃቅፈው ሽልማት እየተለዋወጡ ተግባራዊ የሆነው፣ አማራና አፋር ክልል ውስጥ የብዙ እናቶችና አባቶች ዕምባ ሳይደርቅና የተሰበሩ ልቦች ሳይጠገኑ ነው።
ትናንት ከወልዲያ እስከ ሰሜን ሸዋ ድረስ የአማራን ህዝብ ብቻ ሳይሆን ከብቱንና ማሳውን ጭምር የጨፈጨውና በአለም አቀፍ ደረጃ በተደረገ ስምምነት ትጥቁን እንዲፈታ የተወሰነበት ህወሓት፣ በአንድ በኩል ትጥቁን ሳይፈታ፣ በሌላ በኩል ደሞ ጦርንቱን የጀመሩና ጦርንቱን በከፍተኛ ደረጃ የመሩ ግለሰቦች እንደገና ትግራይ ውስጥ ሥልጣን እንዲይዙ መደረጉ ለአማራ ህዝብ ስጋት መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው። እነ ጌታቸው ረዳ ሥልጣን ይዘውና አገር ውስጥም ውጭ አገርም ላለ ደጋፊያቸው የታጠቀ ኃይል እንዳላቸውና ምዕራብ ትግራይን ለማስመለስ እንደሚሰሩ በሚሰብኩበት ወቅት አማራን ትጥቅህን ፍታ ማለት ደሞ የአማራን ህዝብ ባህልና ይህ ህዝብ በጥንታዊቷም በዘመናዊቷም ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ቦታ አለማወቅ ነው።
እኔ የተወለድኩት ይርጋለም ያደኩት አዋሳ ውስጥ ነው። የሲዳማ ህዝብ ባብዛኛው የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝብ ከጦር መሳሪያ ጋር ያለው ባህል የሰሜን ኢትዮጵያ ህዝብ ከመሳሪያ ጋር ካለው ባህል እጅግ በጣም ይለያያል። ሰሜን ኢትዮጵያ በተለይ አማራው መሳሪያ ጌጡ ነው፣ይህንን ጌጥ የሚነካበትን ኃይል እንኳን ከፍተኛ የህልውና ስጋት አለብኝ ብሎ በሚያምንበት ግዜ በሰላሙም ግዜ ቢሆን ይፋለማል እንጂ አማራ ትጥቅህን ፍታ ሰለተባለ ብቻ የሚፈታ ህዝብ አይደለም። ይህ ደሞ በረጂም ግዜ ሂደት ከገጠሙት ታሪካዊ አጋጣሚዎች ጋር እየተገነባ የመጣ ባህል እንጂ ክፋት፣ህገወጥነት ወይም ጋጠወጥነት አይደለም። ብልፅግናዎች መረዳት የተሳናቸው ይህንን እውነት ነው። እንዲህ ሲባል ግን አማራን ትጥቅ ለማስፈታት በመጀመሪያ ደረጃ በደረጃ መወሰድ ያለባቸው እርምጃዎች መወሰድ ነበረባቸው ለማለት ነው እንጂ አማራ ክልል በአገር አቀፍ ደረጃ የወጣን ህግ ጥሶ መሳሪያ ተሸክሞ ይኑር ማለት አይደለም። በነገራችን ላይ የአሜሪካንን ህዝብ ብንመለከት በተለይ በተለምዶ “The South” እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የሚኖረው ህዝብ ካሁን በኋላ መሳሪያ መያዝ አይቻልምና መሳሪያህን አስረክብ ቢባል፣ ይህንን ካለ አካል ጋር ጦርነት ይገጥማል እንጂ ትጥቁን አያስረክብም። በደቡቡ የአሜሪካ ክፍል አንዳንዱ ቤተሰብ ውስጥ ካለው የሰው ቁጥር የመሳሪው ቁጥር አምስት ግዜ ይበልጣል።
የትግራይ ጦርነት ከቆመ ከወራት በኋላ የኢትዮጵያ መንግስት የክልል ልዩ ኃይሎች መሳሪያ መፍታት አለባቸው ብሎ ህግ ማውጣቱ የሚደገፍ ነው። ግን የክልል ልዩ ኃይሎችን መሳሪያ ፍቱ የሚል ህግ ማውጣትና ህጉን ተግባራዊ ማድረግ እጅግ በጣም የተለያዩ ነግሮች ናቸው። ሌላው የብልፅግና መሪዎች ያልገባቸው ወይም አልታይ ያላቸው እውነት ይህ ነው። እዚህ ላይ በጣም የሚገርመው ብልፅግናዎች የክልል ልዩ ኃይል መሳሪያ ይፍታ የሚል ህግ ባወጡ ማግስት እየሮጡ የሄዱት እስካፍንጫው የታጠቀና ብዛት ያለው ልዩ ኃይል ወዳላችው ኦሮሚያና ትግራይ ክልሎች ሳይሆን ከህወሓት ጋር በተደረገው ጦርነት አብሯቸው ወደ ቆመውና ኢትዮጵያንም እነሱንም ከጥፋት ወዳደነው ከልል ነው።
ዛሬ ኢትዮጵያን ወደማፈራረስ እየሄደ ያለውና አመት ሊሞላው ትንሽ ግዜ የቀረው ጦርነት የተጀመረው፣ አማራውን በቁጥጥር ስር ካደረግን ሌላው አያስቸግረንም ከሚል የተንሸዋረረ አመለካከትና የአማራን ታሪክ፣ ባህልና ስነልቦና መረዳት ካለመፈለግ የተነሳ ነው። እንግዲህ ይታያችሁ አገራችን ኢትዮጵያን ሞት አፋፍ ላይ ይዞ የሄደውን የትግራይን ጦርነትም፣ ዛሬ የኢትዮጵያን ህልውና ከፍተኛ አደጋ ላይ የጣለውን በአማራ ክልል የሚካሄደውን ጦርነትም በሚገባ ለተመለከተ ሰው በሁለቱም ጦርነቶች ውስጥ የብልፅግናዎች ሸፋፋ ጭንቅላትና የክፋት ልብ አለበት።
ባለፈው የካቲት ወር አጋማሽ ወሮ አዳነች አቤቤ ጎንደር ሄደው መንግስት ከፋኖ ኃይሎች ጋር ድርድር የሚቀመጠው ፋኖ ትጥቁን ከፈታ ብቻ ነው ብለው ሲናገሩ ተደምጠዋል፣ ጠሚ አቢይም ፋኖ ትጥቁን ሳይፈታ ድርድር ብሎ ነገር የለም ብለዋል። ከ2011 ዓም ጀምሮ ወለጋና ሸዋ ውስጥ፣ ባለፉት ሁለት አመታት አርሲ ውስጥ፣በቅርቡ ደግሞ በአዲስ አበባ አካባቢ ያለምንም መከልከል የሰላማዊ ዜጎችን ህይወት ከሚቀጥፈውና ንብረት ከሚዘርፈው ሸኔ ጋር ሁለት ግዜ ታንዛኒያ ውስጥ ድርድር ሲቀመጡ ወሮ አዳነችና ጠሚ አቢይ ስለሸኔ ትጥቅ መፍታት አፋቸውን አልከፈቱም . . . ለምን? ለምንድነው አምስት አመት ሙሉ ህዝብን ለጨፈጨፈውና አሁንም እየጨፈጨፈ ላለው ሸኔ ያልቀረበው ጥያቄ መንግስትን እራሱን ከአደጋ ላዳነው ፋኖ የቀረበው?
የአማራ ክልል ጦርነት የተጀመረው የህልውና አደጋ አለብኝ ብሎ የሚያምነው የአማራን ህዝብ ወይም ፋኖን በኃይል ትጥቅ የማስፈታት ሙከራ በመደረጉ ነው። ፋኖ ትጥቄን አልፈታም ብሎ ጦርነት የገጠመው ደሞ ከህወሓትም ከሸኔም አማራው ላይ ያነጣጠረ የህልውና አደጋ አለና የዚህ አደጋ ስጋት ሳይቀንስና የአማራ ህዝብ በህይወት የመቀጠል መብት ዋስትና ሳይኖረው ትጥቅ መፍታት የማይታሰብ ነው በማለቱ ነው። እንግዲህ ይታያችህ አገር እንመራለን የሚሉ ብልፅግናዎች ትጥቅህን ፍታ ሲሉት እሞታለሁ እንጂ የህልውና ስጋት እያለብኝ ትጥቄን አልፍታም ያለን ኃይል ነው ትጥቅ ሳትፈታ ካንተ ጋር ቁጭ ብለን አንደራደርም የሚሉት!
ከህወሓት ጋር ፕሪቶሪያ ውስጥ የተደራደረው፣ ህወሓት በድርድሩ ስምምነት መሰረት ትጥቁን ሳይፈታ መንግስት እንዲመሰርት የፈቀደውና፣ ታንዛኒያ ውስጥ ሁለቴ ህዝብን ከሚጨፈጭፈው ሽኔ ጋር ቁጭ ብሎ የተደራደረው የብልፅግና መንግስት ለምንድነው የፋኖ ትጥቅ መፍታት የድርድሩ ቅድመ ሁኔታ ሳይሆን የድርድሩ ውጤት እንዲሆን ያልፈለገው? መልሱ ቀላል ነው። ብልፅግናዎች የሚፈልጉት ፋኖን ደካማ አድርገው ከደካማ ፋኖ ጋር እነሱ ባስቀመጡት መንገድ መደራደር ነው እንጂ ከፋኖ ጋር ቁጭ ብለው የአማራንም የኢትዮጵያንም ችግር በሚፈታ መንገድ መደራደር አይደለም። ይህ ደሞ እንኳን እቺን የዝንብ ጠንጋራ አውቃለሁ ብሎ ጉዞ ለጀመረውና የሩቢኮንን ወንዝ ሊሻገር ጥቂት ለቀረው ፋኖ የሚዋጥ አይደለም።
ብልፅግናዎች ከአንድ አመት በፊት ፋኖን ትጥቅ እናስፈታለን ብለው አማራ ክልል ውስጥ የጀመሩት ጦርነት . . .
- የኢትዮጵያን መከላከያ ሠራዊት ህዝባዊ መሰረትነት እየናደ ነው
- የኢትዮጵያን መከላከያ ሠራዊት የአገር መከታ ሳይሆን የአንድ ቡድን መሳሪያ እያደረገው ነው
- የማምረትና የምርት ክፍፍል ስራ እንዲስተጓጎል እያደረገ ነው
- ስደት፣ መፈናቀልና ረሃብን እያስፋፋ ነው
- ውጭም አገር ውስጥም ያለው የአማራ ህዝብ ኢትዮጵያዊነቱን እንዲጠይቅ እያደረገ ነው
- የፋኖን ህዝባዊ መሰረት እያሰፋው ነው
- አገራዊ አንድነትን እያላላ ነው
- የኢትዮጵያን ህልውና እየተፈታተነ ነው
ከፋኖ ኃይሎች ጋር በሚደረግ ጦርነት የኢትዮጵያ መንግስት ያሸንፋል የሚል ትንሽም እምነት የለኝም፣ ፋኖ ግን እየተዋጋ ለረጂም ግዜ የመቆየት ህዝባዊ መሰረት እየገነባ መሆኑ ከቅርብም ከሩቅም የሚታይ እውነት ነው። ለዚህ ነው ከፋኖ ጋር የሚደረግ ጦርነት ለኢትዮጵያ እንደ አገር ቀጣይነት ትልቅ አደጋ አለው ብዬ በድፍረት የምናገረው። ስለዚህ የኢትዮጵያ መንግስት ሁሌ እንደሚናገረው አላማው የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት ማስቀጠልና፣ የበለጸገች ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን መገንባት ከሆነ፣ ለህወሓትና የሸኔ የሰጠውን የድርድር ዕድል ለፋኖ ኃይሎችም የሩቢኮንን ወንዝ ከመሻገራቸው በፊት ያለምንም ቅደም ሁኔታ መስጠት አለበት። ይህ የማይሆን ከሆነ ግን ብልፅግናዎች ወይ ተገድደው ይደራደራሉ፣ አለዚያም የብልፅግና ህልውና ያከትማል . . . . . የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ!!!