January 2, 2024
134 mins read

ለዶ/ር መስፍን አረጋ “ዮናስ ብሩ፤ የጭራቅ አህመድ አዛኝ ቅቤ አንጓች” በማለት ለሰጠው ዘለፋ የቀረበ ሳይንሳዊ ትችት! – ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)

ጥር 02   2024

ዶ/ር መስፍን አረጋ በዮናስ ብሩ ላይ ያለውን ቅሬታ “ዮናስ ብሩ፣ የጭራቅ አህመድ አዛኝ ቅቤ አንጓች “ በሚለው አርዕስት ስር በታህሳስ 17፣ 2023 በዘሃበሻ ድረ ገጽ ላይ ያወጣውን ጽሁፉን ፣ በተለይም የእስክንድር ነጋንና የሻለቃ ዳዊትን ስም ለማጥላላት ያደረገውን ሙከራ የሰጠውን መልስ አነበብኩት። ዶ/ር ዮናስ ብሩ የሁለቱን ግለሰቦች ስም ሲጠቅስ ከምን የፖለቲካ ርዕይ በመነሳት እንደወነጀላቸው በፍጹም ግልጽ አላደረገም። የራሱንም የፖለቲካ አቋም ወይም የፖለቲካ ርዕይና ፍልስፍና ምን እንደሆነ በፍጹም አላስታወቀም። የቀኝ፣ የግራ፣ የኮሙኒስት፣ ወይም የሶሻሊስት፣ የሊበራል፣ የኮንሰርቫቲቭ ወይም ሌላ የፖለቲካ አመለካከት እንዳለውና እነሱ ያራምድሉ ብሎ ከሚገምተውና ከሚያስበው ጋር በማገናዘብ ሲተቻቸው አይታይም። በሌላ ወገን ግን ግለሰቦችን በትዊተር ዝም ብሎ  እንደጠየቀና በተለይም አብዛኛዎቹ ስለእስክንድር የሰጡት መልስ “እንደሚያምኑትና የፀና አቋምም እንዳለውራሱን ለመሰዋት የተዘጋጀ፣ እንደ ማህተመ ጋንዲ ያለ፣ የሚከበር፣ ጀግና፣ ሀቀኛና ታላቅም  እንደሆነ”  እንደተናገሩ ነው ዮናስ ብሩ የሚነግረን። ይህ ዐይነት አጠያየቅ ተገቢ ነው ወይም ተገቢ አይደለም የሚለውን ወደ ጎን በመተው በመሰረቱ በዮናስ ብሩም ሆነ በሻለቃ ዳዊት  መሀከል ይህንን ያህልም የሃሳብ ወይም የርዕዮተ-ዓለም ልዩነት ያለ አይመስለኝም። ዮናስ ብሩም ሆነ ሻለቃ ዳዊት “በአሜሪካን የበላይነት፣ በሊበራል ዲሞክራሲ አስተሳሰብና ዲሞክራሲን በዓለም አቀፍ ደራጃ አራማጅነትና፣ ለሰላም መቆም” እንደሚያምኑ ግልጽ  ነው። በሌላ አነጋገር፣ አሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና ግብረአበሮቹ ዓለምን ለመግዛትና በተለይም የሶስተኛውን ዓለም የጥሬ ሀብቶችን ለመቆጣጠር የሚያስፋፉትን የነፃ ንግድ ፖሊሲ፣ በመሰረቱ ፀረ-ሳይንስና ፀረ-ቴክኖሎጂ፣ እንዲሁም የተሟላ ዕድገት ተቀናቃኝ የሆነውንና የዓለም ማህበረሰብ በሙሉ በአንድ ወጥ ህግ  ወይም ደንብ መሰረት(Rules Based Order) መመራት እንዳለበት ጫና የሚደረገውን ይህንን በመቃወም ዮናስ ብሩም ሆነ ሻለቃ ዳዊት አንዳችም ቦታ ላይ ሀተታና ትምህርታዊ ጽሁፍ በመጻፍ አላስነበቡንም። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ በተለይም አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች ነፃ ወጡ ከተባለበት ከ1960ዎቹ ጀምሮ የተሳሳተ ወይም ኢ-ሳይንሳዊ የሆነና፣ ወደ ውስጥ ያተኮረንና የተስተካከለና የተሟላ ዕድገትን የማያመጣውን በተለያዩ ጊዜያት የተለያየ ስም የያዙ በመሰረቱ በይዘት አንድ የሆኑ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ብለው የሚጠሩትን በዓለም ኮሙኒቲው ተገደው ያደረጓቸው የቱን ያህል ዛሬ እንደምናየው በሁሉም አቅጣጫ የሚገለጽ መቀመቅ ውስጥ እንደከተታቸው በመጻፍና ሰፋፊ ሀተታዎች በመስጠት አላስነበቡንም።

ከእነዚህ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ውስጥ  አንዱ አገር አፍራሽና ባህልን አውዳሚ የሆነው የኢኮኖሚ ፖሊሲ “የተቋም መስተካከያ የኢኮኖሚ ፖሊሲ” (Structural Adjustment Programs) በመባል የሚታወቅ ሲሆን፣ ይህም ፖሊሲ የአፍሪካ ኢኮኖሚስቶችና የሳይንስ ሰዎች በ1980 ዓ.ም በሌጎስ ከተማ ላይ በመገናኘት ከብዙ ቀናት ጥናትና ውይይት በኋላ የደረሱበትና፣ አህጉሩንም ካለበት ቀውስ ሊያወጣው ይችላል ብለው ያመኑበትን  „The Lagos Plan for Action“ ብለው ያወጡትን በመቃወም የወጣ መሆኑ ይታወቃል። የአፍሪካ መንግስታትም ይህንን የአፍሪካ ምሁራን ያወጡትን ሳይሆን የግዴታ “የዓለም አቀፍ ኮሙኒቲው” የሚለውን ተግባራዊ ማድረግ እንዳለባቸው ጭነት እንደተደረገባቸው የሚታወቅ ጉዳይ ነው። ቀደም ብሎ ከዘይት ዋጋ መወደድ ጋር በተያያዘ በዓለም አቀፍ ደረጃ የዶላር መትረፍረፍና የፋይናንሺያል ገበያው በገንዘብ መደለብ የተነሳ የአፍሪካን አገሮች ቀስ በቀስ የዕዳ ወጥመድ ውስጥ እንዲገቡ ከተደረገ በኋላ፣ የተቋም ፖሊሲው ሲካተትበት እነዚህ አገሮች የባሰ የዕዳ ወጥመድ ውስጥ እንደገቡ የሚታወቅ ጉዳይ ነው። በዕዳ የተበተቡ የአፍሪካ አገሮች ዕዳውን ማሸጋሽግ(Debt Rescheduling) አለባቸው እየተባለ እንደገና ከዓለም የገንዘብ ድርጅት ገንዘብ በመበደርና ዕዳውን በመክፈል የወለድ ወለድ(Compound Interest) እንዲከፍሉ በመገደድ ከዕዳ ወጥመድ ውስጥ ለመላቀቅ እንዳልቻሉ እንመለከታለን። ይህንንና ሌሎችንም ጉዳዮች በሚመለከት የአፍሪካ አገሮችና የአገራችንም ተቆርቋሪ በመሆን ሁለቱም ምሁራን በዝርዝር ለንባብ ያቀረቡት አንዳችም ጽሁፍ የለም። ከዚህም በላይ በአንዳንድ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ በእስላም አክራሪዎችም ሆነ የጥሬ-ሀብትን ለመቀራመት የሚካሄደው የርስ በርስ ጦርነት የውክልና ጦርነት ወይም የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም  በቀጥታ እጁ እንዳለበት እየታወቀ አንዳችም ሀተታ ወይም ጥናታዊ ጽሁፍ ከዮናስ ብሩም ሆነ ከሻለቃ ዳዊት የቀረበ ነገር የለም። ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ በ2918 ዓ.ም በጦርነት የምትማምቀው አፍሪካ” በሚለው አርዕስት ስር የጻፈውን ካነበቡኩኝ በኋላ ወደ 18 ገጽ የሚጠጋ ትችታዊ ጽሁፍ ለንባብ በማቅረብ ካነበቡት ውስጥ ሁሉም በጽሁፍ ሚዛናዊነትና ትክክለኝነት እንደተደሰቱ ገልጸውልኛል። በእኔ ዕምነትና የፀና አቋም በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ የሚካሄደው ጦርነት በሙሉ ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ እንደሚለው የአፍሪካውያን ሳይሆን የአሜሪካኖችና የአውሮፓውያን ነው የሚል ነው። ጽሁፉን በቀጥታ የድረ-ገጼ ውስጥ በመግባት ልዩ ልዩ ጥናቶች በሚለው ስር ማግኘት ይቻላል።

በተጨማሪም የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም በኢትዮጵያ ላይ የተጫወተውን አገር አፍራሽ ሚና፣ እንዲሁም ወያኔንና ሻቢያን ስልጣን ላይ በማውጣት የጎሳ ፌዴራሊዝም ተግባራዊ እንዲሆን ግፊት ስለማድረጉና፣ ይህንንም አማራጭ የሌለው መፍትሄ  እንደሆነ አዲስ አበባ የነበረው የአሜሪካን አምባሳደር እንዳበሰረ ይህንን አስመልክቶ ከዮናስ ብሩም ሆነ ከሻለቃ ዳዊት አንዳችም መግለጫና ሀተታ በፍጹም አልተሰጠም። ወያኔና ሻቢያ አዲስ አበባ ከመግባታቸውና ስልጣንን ከመረከባቸው በፊት ወያኔ፣ ሻቢያና ኦነግ በኸርማን ኮኸን ሰብሳቢነትና መሪነት ለንደን ላይ እንደተሰበሰቡና ኢትዮጵያን በጎሳ ፌደራሊዝም ስለመሰነጣጠቁ ጉዳይና፣ ይህንንም ተግባራዊ ስለመደረጉ ጉዳይ፣ ወያኔም ይህንን ሲቀበል ብቻ ስልጣን ላይ መውጣት እንደሚችልና፣ ይህም እንደቅድመ ሁኔታ እንደቀረበለት እየታወቀ ይህንን አስመልክቶ ከሁለቱም ግለሰቦች አንዳችም ተቃውሞና ሀተታ በፍጹም አልተሰጠም። በሁለቱ ግለሰቦች የጎሳ ፌዴራሊዝም ማርቀቅና ተግባራዊ ማድረግ የወያኔ አሻጥር ስራ ብቻ ነው ተብሎ በሁለቱም ግለሰቦች የታመነው።

ወያኔም አገርንና ባህልን አውዳሚ፣ እንዲሁም ሰፊውን ህዝብ ወደ ድህነት የሚገፈትረውንና የገፈተረውን የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲን(Structural Adjustment Programs) አስመልክቶ ከዮናስ ብሩም ሆነ ከሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ ይህንን የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምን አሉታዊ ሚናና አገርን በሁለመንታዊ ጎን የሚያፈራርስ የኢኮኖሚ ፖሊስ ብለው የሚጠሩትን፣ በመሰረቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ያለሆነን፣ ይህንን አስመልክቶ ምንም ዐይነት ሀተታና መግለጫ በፍጹም አልሰጡም። ወያኔ ስልጣን ላይ ከመውጣቱም በፊት ሆነ ስልጣን ላይ ከወጣ በኋላ ተግባራዊ ያደረጋቸው “ፖለቲካዎችና የኢኮኖሚ ፖሊሲ” በሙሉ ከአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ዕውቅና ውጭ ናቸው የሚል አስተሳሰብ በሁለቱም ዘንድ ሲንፀባረቅ ይታያል። የወያኔም ፖለቲካ፣ ፖለቲካ ካልነው የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚያስፋፋው ኢ-ዲሞክራሲያዊና የጦረነት ፖሊሲ ጋር በጥብቅ የተያያዘ ለመሆኑ ለሁለቱ ምሁራን ግልጽ የሆነላቸው አይመስልም። ስለሆነም በሁለቱ ግለሰቦች መሀክል ይህንን ያህልም የርዕዮተ-ዓለም ልዩነት በፍጹም አላይም።  በሌላ ወገን ግን የዮናስ ብሩን ተገቢ ትችት በተለይም ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ “ኢትዮጵያ የአማራ ነች… ኢትዮጵያን እዚህ ያደረሳት አማራ ነው” በመቀጠልም ”ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት አማራ አማራ የሚሸት መንግስት ነው” የሚለው አነጋገር ፖለቲካዊ ያልሆነ ብቻ ሳይሆን እጅግ አደገኛ አባባልም ለመሆኑ አምንበታለሁ።  በእርግጥ በአማራው ላይ የደረሰው በደልና አሁንም የሚፈጸምበት ውርጅብኝ ሁላችንንም ቢያሳስበንምና የግዴታም ይህ ዐይነቱ ፋሺሽታዊ አገዛዝ በአስቸኳይ ከስልጣን እንዲወርድ ብንታገልም እንደዚህ ዐይነቱን ፖለቲካዊ ያልሆነና በህብረተሰብ ግንባታ ሂደት ውስጥ ትክክል ያልሆነን አባባል ለተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብም ሆነ ለራሱ ለአማራው ብሄረሰብ የሚጠቅመው አይደለም። ለግለሰብ ነፃነትና ለህግ-የበላይነት መከበርና ለጠቅላላው ህዝብም የሚጠቅም ዕድገት በአገራችን ምድር ዕውን እንዲሆን እንታገላለን የምንል ከሆነ የግዴታ አካሄዳችንና አጻጻፋችን በሙሉ ኢትዮጵያ የሁሉም ብሄረሰቦች አገር እንደሆነችና፣ ሁሉም በመከባበር አዲስና የተከበረች ኢትዮጵያን መገንባት እንዳለባቸው ማስተማር አለብን። እስላሙም ሆነ ክርስቲያኑ፣ ከዚኸኛው ወይም ከዚያኛው ብሄረሰብ የሚወለድ በሙሉ በአንድነት በመነሳት በጋራ አገራቸውን መገንባት አለባቸው የሚል የፀና ዕምነት አለኝ። አንዱ የሌላውን ሃይማኖት ሲያከብርና፣ በተለያዩ ብሄረሰቦች መሀከልም መከባበርና መፈቃቀር ሲኖር ብቻ ነው በሳይንስና በቴክኖሎጂ የሚደገፍ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ሊጠቅም የሚችል ሁለ-ገብ ኢኮኖሚ መገንባት የሚቻለው። ለዚህ ዋናውና ተቀዳሚው ቅድመ-ሁኔታ ደግሞ በአገራችን ምድር የሰላም መስፈንና በብሄረሰብ ላይ የተመሰረተ የጎጠኝነት አስተሳሰብ ሲወገድ ብቻ ነው። ባጭሩ ዘመኑ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ዘመን እንደመሆኑ መጠን፣ በተለይም ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ የመሳሰሉ አገሮች ከዜሮ በመነሳት የሚሰሯቸው አያሌ የስልጣኔ ስራዎችና የአገር ግንባታ ተልዕኮዎች ስላሏቸው ማንኛውም በአማራ ስም የሚነግድ ግለሰብም ሆነ ቡድን ከእንደዚህ ዐይነቱ ጎጂና ከፋፋይ አስተሳሰብ መራቅ አለበት። አስተሳሰባችን ሁሉ በስሜት ላይ የተመረኮዘ መሆን የለበትም። በሰለጠነና በአርቆአስተዋይነት መንፈስ ስንመራ ብቻ ነው በአገራችን ምድር ሰላምን ማስፈንና አገርን መገንባት የምንችለው።

እስክንድር ነጋ ይህንን በሚመለከትና በሌሎች የዓለም አቀፍ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ የሰጠው ሀተታ ወይም ጽሁፍ ስለሌለ ለመተቸትም ሆነ አስተያየት ለመስጠት አልችልም። ያለበትም ሁኔታ በጣም አደገኛና አስቸጋሪ ስለሆነ በእሱ ላይ አስተያየት ከመስጠት ለመቆጠብ ተገድጃለሁ። በሁለቱ ግለሰቦች ላይ ያተኮርኩት በየጊዜው ለድረ-ገጾች መጣጥፎችን ስለሚያቀርቡ ነው። ይሁንና ግን እስክንድር ነጋ የህውሃትንም ሆነ የፋሺሽቱን የአቢይ አህመድን አገዛዝ ፋሺሽታዊና ከፋፋይ ድርጊቶች፣ እንዲሁም ህዝብን ከቤቱ እያባረሩ ሜዳ ላይ እንዲወድቅ ያደርጉ የነበረውን ፀረ-ህዝብ ድርጊታቸውን በመኮነንና በመዋጋት እንደተጋፈጣቸውና ለዚህም ቆራጥ ድርጊቱ ብዙ መንገላታት እንደደረሰበት የሚታወቅ ጉዳይ ነው። ይህንን ሀቅ ይህ ፀሀፊ በሚገባ ይገነዘባል። የእኔ አስተያየትና የፀና አመለካከት ግን እነዚህ ዐይነት በህውሃትም ሆነ በአቢይ አህመድ የፋሺሽቱ አገዛዝ የተፈጸሙትና የሚፈጸሙት ፀረ-ህዝብና ፀረ-አገር ድርጊቶች በሙሉ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ከሚከተለው ዓለምአቀፋዊ የሶሻል ዳርዊንዝም ድርጊቶች ተነጥለው መታየት የለባቸውም የሚል ነው።  በተለይም በግሎባላይዜሽንና በነፃ ንግድ ስም አሳቦ ኢ-ሳይንሳዊ የሆነ ወይም ህዝባዊ ሀብት የማይፈጥር፣ ድህነትንም ሊቀርፍ የማይችልና የተስተካከለ የኢኮኖሚ ዕድገት በሁሉም አገሮች እንዳይዳብር ማድረግ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና የተቀሩት የካፒታሊስት አገሮች ዋናው ዓላማ ሰለሆነ ይህንን በተጨባጭ የሚታይና ህዝብን ሰቆቃ ውስጥ የሚከተውን በቁጥር ውስጥ ሳያስገቡ ለአንድ አገርና ህዝብ ነፃነት እታገላለሁ ማለት ትልቅ ታሪካዊ ወንጀል እንደመፈጸም ይቆጠራል የሚል ዕምነት አለኝ። በተለይም ወያኔ ስልጣን ላይ ከወጣ ጊዜ ጀምሮ በአዲስ አበባም ሆነ በሌሎች ትላልቅ የኢትዮጵያ ከተሞች እንደ አሸን የፈለቁት የቆሻሻ መኖሪያ ቦታዎችና፣ ሰፊው ህዝባችንም በእንደዚህ ዐይነቱ ለዐይን በሚዘገንን ቦታዎች እንዲኖር መገደዱ የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ዋናው መገለጫ መሆኑን መዘንጋት የሌለበት ጉዳይ ነው። እንደዚህ ዐይነቱ ህዝብን በቆሻሻ ቦታዎች ወይሞ በፓርኮችም ውስጥ እንዲያድር ማድረግ በአሜሪካንም ትላልቅ ከተማዎች፣ በተለይም እንደ ሎሰአንጀለስና ኒዎርክ በመሳሰሉት ከተማዎች የተስፋፋና በግልጽም የሚታይ ጉዳይ ነው።  በሌላ ወገን በብዙ ሺሆች የሚቆጠሩ ሰዎች መጠለያ አጥተው በየፓርኩና በየመንገዱ ሲያድሩ በባይደን የሚመራው የአሜሪካን መንግስት ዩክሬይንን በተለያዩ የጦር መሳሪያዎች ለማስታጠቅና በሩሲያም ላይ ድልን መቀዳጀት አለባት በሚል ጦርነቱ ከተከፈተ ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ወድ 44 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዝብ በዕርዳታ መልክስ ሰጥቷል። እንደዚሁም የጀርመን መንግስት 17 ቢሊዮን ኦይሮ ለዩክሬይን አገዛዝ በዕርዳታ መልክ ሰጥቷል። በአሁኑ ወቅት በሁለቱም አገሮች ውስጥ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ይታያል። ይሁንና በዚህ ዐይነቱ ጦርነትን ማፋፋም ስትራቴጂ ዩክሬይን በፍጹም ማሸነፍ እንደማትችል የታወቁ የሚሊታሪና የጦር ተንታኞች ይገልጻሉ። እንደምናየውም በብዙ ሺሆች የሚቆጠሩ ንጹህ የዩክሬንያን ዜጎችና ወታደሮችም ጭምር በየቀኑ እየረገፉና ከተማዎችም እየወደሙ ነው። በአሁኑ ጊዜ ዩክሬይን የሚሰራና የሚንቀሳቀስ ኢኮኖሚ በፍጹም የላትም። ስለሆነም ህዝቡ በፍርሃት ስለተዋጠና የመኖር ዕድሉ የመነመነ ሰለሆነ ወደ አቃራቢያው አገሮች በተለይ ወደ ጀርመን እየፈለሰ ነው። ከዩክሬይንም ወደ ጀርመን የሚመጡትን ዜጎችን ለማስተናገድና የስራ ቦታም ለማሲያዝ እንደዚሁ በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠር ኦይሮ የጀርመን መንግስት ያወጣል። በዚህ መልክ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚያስፋፋው ጦርነትና ኢ-ሳይንሳዊ የሆነ የኢኮኖሚ ፖሊሲ አብዛኛውን የዓለም ደሃ ህዝብ የሚጎዳ ብቻ ሳይሆን ከማንኛውም ህብረተሰብአዊ ስራዎችና ባህላዊ ክንዋኔዎች እንዲገለልና ሞራሉም በመሰበር እንደ ነፃ ዚጋ እንዳይቆጠር ከማድረግ ጋር በጥብቅ የተያያዘ ነው፤ የሰብአዊ መብትንም በከፍተኛ ደረጃ የሚፃረር ድርጊት ነው። ይህ ዐይነቱ ሰፊውን ህዝብ ከቤቱ እያባረሩ ቆሻሻ ቦታዎች ላይ እንዲኖርና ከዚያው ምግብ እየፈለገ እንዲመገብ ማድረግ ትችታዊ አመለካከት ባላቸው የከተማ ዕቅድ አውጭዎችና የሶስይሎጂ ምሁራን የኒዎ-ሊበራል የከተማ ዕቅድ(Neo-Liberal Urban Project) በመባል ይታወቃል። ይህ ዐይነቱ የህንጻ አገነባብ በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ በአንዳንድ ቦታዎች ሬል ስቴትና ስማርት ሲቲ በሚል ስም በመስፋፋት ሰፊውን ህዝብ ከመሀል ከተማ እያባረረና ወዳለመዱበት ቦታ እየሄዱ እንዲኖሩ እያስገደዳቸው ለመሆኑ በገሃድ የሚታይ ጉዳይ ነው። ይህ ዐይነቱ የሪል ስቴት አሰራር ኢ-ማህበራዊ፣ ኢ-ባህላዊ የሆነና እንዲሁም ብልግናና ሌሎች የውንብድና አሰራሮችን የሚያስፋፋ ነው። የህንጽ አሰራሩም እንደዘመናዊነት ይቆጠራል ቢቆጠርም ለዕውነተኛ ስልጣኔ የማይስማማና መንፈስንም የሚያድስ አይደለም። ይህ ዐይነቱ የህንጻ አሰራር በቀጥታ ከኒዎ-ሊበራሊዝም የኢኮኖሚ ፖሊሲ ጋር በጥብቅ የተያያዘ ሲሆን፣ ከበስተጀርባውም ማን እንዳለበት ለማወቅ በጣም ያስቸግራል።

በሌላ ወገን ይህ ጸሀፊ ወያኔ በተለይም የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲን ተግባራዊ ማድረግ ከጀመረመበት ጊዜ ጀምሮ አሉታዊ ሚናውን አስመልክቶ በተለያዩ አገር ቤትውስጥ በሚታተሙ መጽሄቶች ላይ፣ እንደ አውራምባ ታይምስና ጦቢያ፣ እንዲሁም በውጭ አገር በሚገኙ እንደ ኢትዮ-ሚዲያ፣ ሳተናውና ዘሃበሻ በሚባሉ ድረ-ገጾች ላይ በዝርዝር በመተንተን አንባብያን የነገሩን አደገኛነት እንዲረዱት ለማብራራት ሞክሯል። በተጨማሪም የነፃ ንግድ ፖሊሲን አስመልክቶና፣  በተለይም ኢትዮጵያ “የዓለም የንግድ ድርጅት” (WTO) አባል ለመሆን ያቀረበችውን ማመልከቻ በመቃወምና ምክንያቱን በማስረዳት በሰፊው ለማብራራት ሞክሯል። እንዲሁም በእንግሊዘኛ ቋንቋ ከሰላሳ ገጽ በላይ በሚሆን ሀተታ የነፃ ንግድ ፖሊሲን ጠንቅነትና፣ የማንኛውም በዚህ ስም የሚንቀሳቀስ ድርጅት አባል መሆን የሚያስከትለውን አሉታዊ የኢኮኖሚና የህብረተሰብ ጠንቅ፣ እንዲሁም የሚያስከትለውን የባህል ውድመት ለማብራራት ሞክሬያለሁ። በተጨማሪም  African Predicaments and the Method of Solving them Effectively“  በሚለው መጽሀፌ ውስጥ የአፍሪካ አገሮች በዓለም አቀፍ ኮሙኒቲውና በአፈቀላጤዎቻቸው፣ ማለትም በዓለም የገንዘብ ድርጅትና(IMF) በዓለም ባንክ(World Bank) ተገደው ተግባራዊ ያደረጓቸው የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች በሙሉ ወደ ውስጥ ያተኮረና በሳንይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ጠንካራና ሰፋ ያለ ኢኮኖሚ ማስገንባት እንዳላስቻላቸው ለማሳየት ሞክሬያለህ። ይህንንም ከካፒታሊስት አገሮች የኢኮኖሚና የአገር ግንባታ፣ እንዲሁም ከጃፓንና ከደቡብ ኮሪያ ሰፋ ያለ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ የኢኮኖሚ ዕድገት ጋር በማነፃፀር አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች ተግባራዊ ያደረጓቸው የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች በሙሉ የካፒታሊዝምን የኢኮኖሚ ዕድገት ህግና የውስጥ አሰራር ስልት እንደሚፃረር አመልክቻለሁ። እነዚህ ሁሉ ጽሁፎች ደረጃ በደረጃ  www.fekadubekele.com   በሚለው ድረ ገጽ ላይም በሚገባ ሰፍረዋል። ታዲያ ይህ ሁሉ ስራ የአገርን ህልውና  እንደ መከላከል የሚታይና የፖለቲካ ትግልም አንዱ አካል አይደለም ወይ? ለፖለቲካ ስልጣን ትግል ሲካሄድ የነገሮችን ውስብስብነትና፣ በተለይም እንደኛ ባሉ አገሮች ስልጣን ላይ የሚወጡ አገዛዞች በራሳቸው አስተሳሰብና ፖሊሲ ለመራመድ እንደማይችሉና፣ ይህንንም በሰፊው በማተት ለአንባቢያን በጽሁፍም ሆነ በመጽሀፍ መልክ ማቅረቡ ዋናው የፖለቲካና የነፃነት፣ እንዲሁም የብሄራዊ ነፃነት ትግል ዋናው ተግባር ሊሆን አይችልም ወይ?

ወደ ዮናስ ብሩ መሰረታዊ አስተሳሰብ ጋ እንምጣ። ዮናስ ብሩ ስለፖለቲካል ራሺናሊቲ ሲነግረን ከምን አንፃር በመነሳት ይህንን ግዙፍ ፅንሰ-ሃሳብ እንደሚጠቀምና፣ ከእስክንድርም ሆነ ከሻለቃ ዳዊት፣ እንዲሁም ከሌሎች የሚለይበትንና  ምን ዐይነትስ ፖለቲካል ራሺናሊቲ እንደሚጠብቅ ግልጽ አላደረግልንም። በአጠቃላይ የፅንሰ-ሃሳቡን አመጣጥ ስንመለከት በግሪክ ስልጣኔ ዘመን የፈለቀና  በተለይም በአውሮፓ ምድር በ15ኛው ክፍለ-ዘመን በሬናሳንስ ጊዜ፣ በኋላ ደግሞ በ17ኛው ክፍለ-ዘመን በኢንላይተንሜንት እንቅስቃሴ ዘመን በተለይም ስለሰው ልጅ ባህርይና ስለ ዕውቀት አፈላለቅ ክርክር በሚደረግበት ዘመን ለፖሊተከኞች እንደመመሪያ እንዲወሰድ የዳበረ ትልቅ አስተሳሰብ ነው። ከዚህም በላይ የፖለቲካ ራሺናሊዝም ዲስፖታዊ አገዛዝን፣ ወይም የአንድን ግለሰብ የፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ በመቃወም ማንኛውም አገዛዝ በህግ-የበላይነት በመገዛትና የሪፓብሊካንን አስተሳሰብ በማስፋፋት ግለሰብአዊ ነፃነት መከበር እንዳለበት በታላላቅ ፈላስፋዎች ቅስቀሳ የተደረገበትና ቀስ በቀስም ተቀባይነት ያገኘ መሰረታዊ መመሪያ ነው። በዚህም መሰረት ስልጣን የያዘ ግለሰብ በሙሉ ስልጣን ያዝኩኝ በማለት መመፃደቅ ያለበት ሳይሆን ራሱም የህግ ተገዢ በመሆን ህዝብንና አገርን ማገልገል እንዳለበት የሚያሳስብ ነው።  ራሺናሊዝም የሚለው ጽንሰ-ሃሳቡም ከሰብአዊነት(Humanism) ተነጥሎ መታየት የሌለበት መሰረታዊ ጉዳይ ሲሆን፣ ፅንሰ-ሃሳቡም ከፍትሃዊነት ጋር የተያያዘና ከጉልበት ይልቅ የጭንቅላትን ወይም በፍልስፍና ላይ የተመሰረተና ችግርን ፈቺ ሳይንሳዊ የአሰራር ጥበብን የሚያስቀድም ነው። ሰብአዊነት የሚለው አስተሳሰብ ደግሞ የሰው ልጅ ከእንስሳ የሚለይበት መገለጫ ሲሆን፣ የሰውን ልጅ አንቀው ከያዙት ልማዳዊ የአኗኗር ወይም የትንግርት ስልቶችና ከእልከኝነት በመላቀቅና አዕምሮውን ክፍት በማድረገና ለትችትም ዝግጁ በመሆን ለሁለ-ገብ ዕድገት እንቅፋት ከሆኑ ከኋላ-ቀር ስርዓቶችና አስተሳሰቦች በመላቀቅ በማሰብ ኃይሉ አማካይነት በሁሉም መልክ የሚገለጽ አዲስ የአኗኗር ስልት ማዋቀርና ከተማዎችንና መንደሮችን መንፈስን እንዳይረብሹ ሆነው ከተፈጥሮ ጋር በመያያዘ መሰራት እንዳለባቸው የሚያስተምር ታላቅ መመሪያ ነው። ይህ ዐይነቱ ዕድገትም በማቴሪያል ብቻ የሚገለጽ ሳይሆን የሰው ልጅ መንፈሱንም በማጎልበስ እየተፈቃቀረና የተፈጥሮ ጠላት ሳይሆን የተፈጥሮ ጓደኛ በመሆን ከሞላ ጎደል ስምምነት(Harmonius) ያለበትን ህብረተሰብ መመስረት ማለት ነው።

ይሁንና ይህ ዐይነቱ ከሰብአዊነት ጋር የተያያዘው ራሺናሊዝም ወይም የአርቆ-አሳቢነት ፅንሰ-ሃሳብ ባለፉት ሁለት መቶ ዓመታት  ከካፒታሊዝም ዕድገትና ዓለም አቀፋዊ ባህርይ መውሰድ ጋር ልዩ ዐይነት ባህርይ እየወሰደ ለመምጣት ችሏል። በተለይም የአውሮፓ የቅኝ ገዢዎች ይህንን ዐይነቱን የአርቆ-አሳቢነት መርሆ ለመከተል ባለመቻላቸው የአፍሪካን ዕድገት ወደ ኋላ ለመጎተት ችለዋል። ተፈጥሮንም ሆነ የሰውን ልጅ ወደ ተራ ተበዝባዥነት በመለወጥ በአምላክ ምስል የተፈጠረውን የሰው ልጅ በማሰብ ኃይሉ ራሱ በመሰለው መንገድ አዲስ ማህበረሰብ እንዳይመሰርትና እንዳይገነባ ሊታገድ በቅቷል። ስለሆነም  ፖለቲካ ራሺናሊዝም የሚለው ፅንሰ-ሃሳብ ባለፉት ሁለት መቶ ዓመታት፣ በተለይም ደግሞ ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ በተከሰተው ልዩ ዐይነት የሆነ የኃይል አሰላለፍ እንዳለ ደብዛው ሊጠፋ ችሏል። ከአርቆ-አሳቢነት ይልቅ አመጽና ማስፈራራት ቦታውን በመያዝ በተለይም አላደጉም ወይም በማደግ ላይ ያሉ አገሮች የሚባሉት ህልውናቸው ሊገረሰስ በቅቷል። በእነዚህ ደካማ አገሮች ውስጥ ስልጣን ላይ የሚቀመጡ አገዛዞችና የመንግስታት መኪናዎች፣ ማለትም የሚሊተሪው፣ የፀጥታው፣ የፖሊስና የሲቭል ቢሮክራሲውም በግሎባል ካፒታሊዝም ወይም በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ቁጥጥር ስር በመወደቅ ሁለ-ገብና ሚዛናዊነት ያለው ዕድገት እንዳይመጣ ማገድ ብቻ ሳይሆን፣ አገሮችም የተለያዩ ማህበረሰባዊ፣ የሃይማኖትና የጎሳ ግጭቶች የሚፈለፈልባቸው መድረኮች በመሆን ሰፊው ህዝብ ተረጋግቶ እንዳይኖር ለመደረግ በቅቷል። ማንኛውም አገር ከባህሉና ከእሴቱ ውጭ አንድ ወጥ አመለካከትና የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ ማድረግ አለበት በማለትና ከፍተኛ ጫና በማድረግ፣ ይህንን የአሜሪካን ኤሊት የብልግና አካሄድ አልቀበልም ያለ ሁሉ እንደጠላት በመታየት ሁለ-ገብ ጦርነት ይታወጅበታል። በቬትናም በ1960ዎቹ ዓመታት በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም የተካሄደው ጦርነትና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ የቬትናምን ህዝብ የጨረሰው ጦርነትና መሬቱም እንዳያበቅል ኤጀንት ኦራንጅ(Agent Orange) የሚባል በጣም መርዛማ የሆነ የተበጠበጠ ኬሚካል መርጨት የአሜሪካንን የፖለቲካ ኤሊት መንፈሰ-አልባነትና አረመኔያዊ ባህርይ የሚያረጋግጥ ነው። የኬሚካሉ መዘዝ አሁንም ቢሆን በጉልህ የሚታይና፣ በብዙ ሺሆች የሚቆጠሩ አዳዲስ የሚወለዱ ህጻናት ካለጆሮ፣ ካለአፍንጫና ካለዐይን፣ ወይም በሌላ የአካል ጉድለት እንደሚወለዱ የሚታወቅ ጉዳይ ነው። በመሰረቱ ቬትናምንና አሜሪካንን ምንም የሚያገናቸው ነገር የለም። ቬትናም አሜሪካ ድረስ በመዝለቅ በአሜሪካ ላይ ጦርነትን አላወጀችም። ይህ ዐይነቱ የማንአለኝበት ባህርይ ምንድነው የሚያሳየን። የአውሮፓውና የአሜሪካ የፖለቲካ ኤሊት፣ እንዲሁም የሚሊተሪ-ኢንዱስትሪ ውስብስብ(Military Industrial Complex) በሶስት መንፈስን በሚያድስና ከአውሬ ባህርይ በሚያላቅቅ ሂደት ውስጥ ቢያልፉም ጭንቅላታቸው አሁንም ቢሆን የሰብአዊነትን ባህርይ እንዳልተላበሰ ነው የሚያረጋግጠው።  የጀርመኑ ፈላስፋና ገጣሚ የነበረው ታላቁ ፍሪድሪሽ ሺለር እንደሚለን፣ ከአሪስቶተለስ ጀምሮ ስለ ዲሞክራሲ ብዙ ሰምተናል፤ ብዙም ተጽፏል። ይሁንና ግን አሁንም ቢሆን የሰው ልጅ ከአረመኔያዊ ባህርዩ በፍጹም አልተላቀቀም ይላል። ለሰው ልጅ ዕድገትና ስራን ለማቃለል ሳይንስና ቴክኖሎጂ አስፈላጊ የሆኑትን ያህል እንደ ሩሶው የመሳሰሉት ፈላስፋዎች  እነዚህ በራሳቸው ብቻ የግዴታ የስልጣኔ መገለጫዎች እንዳልሆኑ ያመለክታሉ። ለማለትም የሚፈልገው በሳይንስና በቴክኖሎጂ ዕድገት የተነሳ የስው ልጅ መንፈስ ርኅሩህ ለመሆን እንዳልቻለ፣ በተለይም ስልጣን ላይ የሚወጡና አገርን እንገዛለን የሚሉ ወደ አረመኔነት ሊለወጡ እንደሚችሉ ነው። በአንደኛውና በሁለተኛው የዓለም ጦርነቶችና፣ ከዚያም በኋላ በተወሳሰቡና በረቀቁ ቴክኖሎጂዎች በመደገፍ የሰውን ልጅ እንዳለ ማጨድ የሚያረጋግጠው ሳይንስና ቴክኖሎጂ የግዴታ የስልጣኔ መገለጫዎች መሆናቸው ቀርቶ የጥቂት ሰዎች ውስጣዊ ፍላጎት ማርኪያ ለመሆን እንደሚችሉ ነው።  በተለይም የቴክኖሎጂን አጠቃቀም ጉዳይ ስንመለከት ለቴክኖሎጂ ግኝት መሰረት የጣሉት እንደነ ጋሊሌዮ፣ ኬፕለር፣ ዲካ፣ ላይብኒዝና ኒውተን፣ እንዲሁም አይንስታየንና ሌሎችም ሳይንቲስቶችና የቴክኖሎጂ አፍላቂዎች ሳይንሳዊ ምርምር ሲያደርጉና ራሳቸውንም ሲያስጨንቁ የሰውን ልጅ በጊዜው ከሚኖርበት ከጨለማና ከእንስሳ በማይተናነስ የአኗኗር ዘዴ በማላቀቅ በቴክኖሎጂ አማካይነት ምርታማነትን በማሳደግና አዳዲስ የአኗኗር ስልት በማዳበር ሰው መሆኑን እንዲገነዘብ ለማድረግ ብቻ  ነበር። በሌላ አነጋገር፣ ታላላቅ ፈላስፋዎችም ሆነ ሳይንቲስቶች የሰውን ልጅ ከጨለማ ለማውጣት ሲታገሉና ለቴክኖሎጂ ግኝት ሳይንሳዊ የምርምር መሰረት ሲጥሉ ምርምራቸው ወደ መጥፎ ነገር ይለወጣል ብለው በፍጹም አልገመቱም ነበር። እንደ አቶም ቦምብ፣ የባይሎጂና የኬሚካል የጦር መሳሪያዎች በመፈጠርና በመሰራት የሰውን ልጅ ለመጨረስ ጠቀሜታ ላይ ይውላሉ በለው በፍጹም አላሰቡም ነበር። ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎችም በዚህ ፍጥነትና ምጥቀት በመፈጠርና በመሰራት የዓለምን ህዝብ ማስፈራሪያ ይሆናሉ ብለው በፍጹም አላለሙም ነበር። ይሁንና በካፒታሊዝም ውስጣዊ ሎጂክና የአገዛዝ አወቃቀር የተነሳ መንፈሳቸው ቀና በሆኑና ልዩ  ዐይነት ተልዕኮ ባላቸው ግለሰቦች የተፈጠሩ ቴክኖሎጂዎች ለጥፋት እንዲውሉ ተደርገዋል። ይሁንና ይህ ዐይነቱ ቴክኖሎጂን ሰውን ለማስፈራሪያና ለመግደያ መጠቀም በእኛ ኢትዮጵያውያንና በተቀረው በምስኪኑ የዓለም ህዝብ ልክ እንደ ተፈጥሮ ህግ በመወሰድ ሲወደስ ይገኛል።

ከዚህም ባሻገር በአብዛኛዎቹ የካፒታሊስት አገሮች ውስጥ በራሱ የካፒታሊዝም ውስጠ-ኃይልና ሲወርድ ሲዋረድ በመጣ የጥቂቶች ምሁራዊ ጥረት የተነሳ የሊበራሊዝም አስተሳሰብ ቢዳብርምና ሰፋ ያለ የሲቭል ማህበረሰብ ቢፈጠርም፣  የሊበራሊዝም ፅንሰ-ሃስብ ግን በውጭ ፖለቲካው ላይ የሚሰራ አይደለም። ይህም ማለት እያንዳንዱ አገር ነፃ እንደመሆኑ መጠን የራሱን ኢኮኖሚ፣ ባህል፣ የከተማ አገነባብ፣ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ጉዳይና፣ እንዲሁም በየአገሮች ውስጥ የሚኖረውን ሰፊ ህዝብ አስመልክቶ ደረጃ በደረጃ መወሰድ ስላለበት የአገር ግንባታና ድህነትን ለአንዴም ለመጨረሻም ጊዜ ማስወገድ የሚለውን ተፈጥሮአዊና የህብረተሰብ ህግ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም የፖለቲካና የሚሊተሪ ኤሊቱም ሆነ የአውሮፓ ካፒታሊዝም ኤሊቶች በፍጹም አይቀበሉም። ሁሉንም ነገር እኛ መደንገግ አለብን፤ ማንኛውም አገር ከእኛ ቁጥጥርና ፈቃድ ውጭ የፈለገውን ነገር ማድረግ አይችልም የሚል የፀና አስተሳሰብ በአሜሪካን የፖለቲካና የሚሊተሪ-ኢንዱስትሬ ውስብስብ ጭንቅላት ውስጥ ተቀርጿል። ይህ ዐይነቱ ዲስፖታዊ አስተሳሰብ ወይም አመለካከት ደግሞ በመሰረቱ ታላላቅ የአውሮፓ ፈላስፋዎች፣ ማለትም ላይብኒዝ፣ ካንት፣ ሄገል፣ ጎተና እንዲሁም አንዳንድ የእንግሊዝ የኢንላየተንሜንት አፍላቂዎችና አስተማሪዎችን ያፈለቁትንና ያስተማሩትን መመሪያ የሚቃወም ነው። በካንትም ዕምነት ዘለዓለማዊ ሰላም(Perpetual Peace)  በሚለው መጽሀፉ ውስጥ ሊያስተምረን የሚሞክረው በዓለም አቀፍ ደረጃ ዘለዓለማዊ ሰላም ሊሰፍን የሚችለው ማንኛውም አገር የሌላውን አገር ልዕልና ሲያከብርና በውስጡ ፖለቲካው ጣልቃ ያልገባ እንደሆነ ብቻ ነው ብሎ አጥብቆ ያሳስባል። ስለሆነም ይላል ካንት፣ አንድ የበላይነት የሚሰማው ወይም ኃያል ነኝ የሚል አገር የግዴታ ደካማና ያላደገውን አገርም ነፃነቱን ማክበር አለበት ይላል።  በዚህ መንፈስ መገዛት ሲቻል ብቻ ነው በአገሮች መሀከል ሰላም ሊስፍን የሚችለው። ይህንንም መሰረተ-ሃሳብ ያፈለቁትና ያዳበሩት ኮሙኒስቶች ሳይሆኑ- በጊዜው ኮሙኒዝም የሚባል አስተሳሰብ የሚታወቅ አልነበረም ንፁህ መንፈስና ጠለቅ ያለ ዕውቀት ያላቸው ፈላስፋዎች ናቸው።

በየአገሮች መሀከል ሊኖር የሚገባው ግኑኝነት ልክ ካንት ባለው መልክ መዋቀር ሲገባው በተለይም የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና አፈቀላጤዎቹ፣ ማለትም የዓለም የገንዘብ ድርጅትና(IMF) የዓለም ባንክ(World Bank)፣ እንዲሁም የአሜሪካን የጥሬ-ሀብት ተቀራማች ትላልቅ ኩባንያዎች የሶስተኛው ዓለም ተብለው በሚጠሩ አገሮች ውስጥ አገዛዞችን በማባለግና በገንዘብ በመግዛት የየአገሬውን ህዝብ በሰላም ሰርቶ እንዳያድርና ስርዓት ያለው ማህበረሰብ እንዳይገነባ ከፍተኛ እንቅፋት ፈጥረውበታል። የዚህ ዐይነቱ የጥሬ-ሀብት ቅርምትና አገዛዞችን በማባለግ ኢ-ሳይንሳዊ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ እንዲያደርጉ ማስገደድ በየአገሮች ውስጥ መጠነ-ሰፊ የስራ አጥ ቁጥር እንዲፈጠርና አገዛዞችም አገሮቻቸውን ለማስተዳደር የማይችሉበት ሁኔታ እንዲፈጠር ተደርጓል። በየአገሩ መኖር፣ መስራትና ራሱንና ቤተሰቡን ማስተዳደር የማይችለው ደግሞ ከየአገሩ እየተሰደደ በተለይም ወደ አውሮፓና ወደ አሜሪካ እንዲሰደድ ለመደረግ በቅቷል። በዚህም ምክንያት የተነሳ በየአገሮች ውስጥ እየገባ አገዛዞችን እንደፈለገው የሚበውዘው የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና አፈቀላጤዎቹ ሳያስቡት በአገራቸው ውስጥም ከፍተኛ የጎሳ ቅይጥ እየፈጠሩና ነጭ ነኝ የሚባለው  የህብረተሰብ ክፍል  በአገሩ ውስጥ ተዝናንቶ ሊኖር የማይችልበት ሁኔታ እንዲፈጠር ለመደረግ በቅቷል። በተለይም በአሜሪካን በአንዳንድ ከተማዎች ውስጥ የላቲኖ ህዝብ፣ የህንድና የቻይናዎች ቁጥር እየጨመረ በመምጣት በአጭር ዓመታት ጊዜ ውስጥ የነጩ ህዝብ ቁጥር ከሌላው ከውጭው ከመጣው ጋር ሲወዳደር በቁጥር በከፍተኛ ደረጃ ዝቅ እንደሚል ግልጽ እየሆነ መጥቷል። ባጭሩ እንደዚህ ዐይነቱ ከአርቆ-አሳቢነት ውጭ በማንአለኝበት የሚካሄድ የውጭ ፖለቲካ የመጨረሻ መጨረሻ ማንም የሚነካኝ  የለም የሚለውንም ኃይል መንግስት ቀስ በቀስ ከስሩ እንደሚቦረብረውና የበላይነት ዘመኑን በከፍተኛ ፍጥነት እንደሚያሳጥረው ነው።

ከዚህ ሁኔታ ስንነሳ በአገራችን ምድር በፅንሰ-ሃሳብና በአመለካከት ዙሪያ በማንኛውም የትምህርት ዘርፍ የጠራ አቋምና ትግል የማካሄድ ልምድ ስለሌለ ከፍተኛ አለመግባባት አለ። አንዱ በጥሩ እንግሊዘኛ ወይም በጥሩ አማርኛ ሲጽፍ በጣም ጥሩ ትንተና እንዳቀረበ ተደርጎ ይወሰዳል። እዚህ አውሮፓ ውስጥ ክሪቲካል አመለካከት የሚባል ነገር አለ። ማንኛውም አነጋገርና ጽሁፍ በሳይንስ መነፅር መመርምርና መነበብ አለባቸው። አስቸጋሪው ነገር በሶሻል ሳይንስ ዘንድ፣ በተለይም በኢኮኖሚክስ ዘንድ ብዙ የተምታቱ ነገሮች ስላሉ አብዛኛዎቻችንም በፍልስፍናና በሶስዮሎጂ ዕውቀቶች ያልሰለጠን ስለሆንና ከትምህርት ዘርፋችን ወጣ ብለን ሌሎች ሰነ-ጽሁፎችንና ዕውቀቶችን የማንበብ ልምድ ስለሌለን በምድር ላይ የሚታዩ ነገሮችን ለማየት አንችልም፤ ወይም እያየን እንዳላየ ሆነን እናልፋለን። ባጭሩ ቆም ብለን ይህ ዐይነቱ አስቀያሚ ሁኔታ እንዴት ሊፈጠር ቻለ? ምክንያቱስ ምንድነው? ብለን በፍጹም የመጠየቅ ልምድና ባህልም የለንም። ስለሆነም  ስለፖለቲካል ራሺናሊቲ በሚወራበት ጊዜ የዚህን ፅንሰ-ሃሳብ አመጣጥና ከምን ነገር እንደተያየዘና፣ በየትኛውም ክፍለ-ዘመን እንደፈለቀ ማወቅና ማስረዳትም በጣም ያስፈልጋል። ይሁንና ፅንሰ-ሃሳቡ ደግሞ የግዴታ ዘለዓለማዊ እንደሆነና ከጭንቅላት ተሃድሶና ራስን መልሶ መላልሶ ከመጠየቅ ጋር በጥብቅ የተያያዘ ነው። ዮናስ ብሩ ግልጽ ማድረግ የነበረበትም ይህንን ጉዳይ ከአገራችን ተጨባጭ ሁኔታና ሰፋ ካለ የፖለቲካ እንቅስቃሴ አለመኖርና የመንፈስ ተሃድሶ ተግባራዊ  ካለመሆን ጋር  ነበር ማያያዝ የነበረበት። ለማንኛውም እኔ እስከሚገባኝ ድረስ ፖለቲካል ራሺናሊቲ ከሰብአዊነት እንቅስቃሴ ጋር የተያያዘ ሲሆን፣ ይህ በራሱ ደግሞ አንድን ህብረተሰብ ከተለያዩ አንፃሮች በመመርመርና እንደማህበረሰብ ለመቆም የሚጎድሉቱን ነገሮች በማጥናት አስፈላጊዎችና ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ ፖሊሲ ነክ ነገሮችን ማዳበርና ወደ ተግባርም እንዲመነዘሩ እንቅስቃሴ ማድረግ ነው። ይህ ዐይነቱ አስተሳሰብም በአንድ ግለሰብ ጫንቃ ላይ ብቻ የሚጣል ሳይሆን በብዙ ሰዎች ትከሻ ላይ በመውደቅ በልዩ ልዩ የዕውቀት ዙሪያ በመሰባሰብ ጥናት ማካሄድና መፍትሄም ሊሆኑ ይችላሉ የሚባሉ ነገሮችን መሰንዘር በጣም አስፈላጊ ነው። ባጭሩ ከአንድ ግለሰብም ሆነ ከሁለት ሰዎች ወይም ከአንድ ድርጅት ፖለቲካል ራሺናሊት መጠበቅ ቢያንስ ከአውሮፓው የኢንላይተንሜንት እንቅስቃሴ ታሪክ ሲታይ ሊያስኬድ የሚችል ነገር አይደለም። የራስን የጠራ የፖለቲካ ርዕይ ሳያስታውቁና በተለያየ የህብረተሰብን ጥያቄዎች በሚመለከቱ ነገሮች ላይ ለምሳሌ የፖለቲካ አደረጃጀት፣ የፖለቲካ ተቋማት ግንባታ፣ ሰለመንግስት መኪና አወቃቀርና ዲሞክራሲያዊ ባህርይ እንዲኖረው ሰለማድረግ ጉዳይ፣ በመንግስት አማካይነት ጠቅላላውን ህዝብ የሚጠቅም ሀብት እንዴት ሊፈጠር ይችላል? መንግስትስ በኢኮኖሚውና በማህበራዊ ነክ ነገሮች ላይ ምን ዐይነት ሚና ሊጫወት ይችላል? የኢኮኖሚ ዕድገትንና የስራ-መስክን መፈጠር ጉዳይ በሚመለከት የግለሰቦችስ ሚና እንዴት ይታያል? እንዴትስ ሊነቃቁና ሊደገፉ ይችላሉ? ከዚህም ባሻገር ሊሰራ የሚችለውን ህዝብ በማንቀሳቀስ እንዴት ተደርጎ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከተማዎችን፣ መንደሮችን፣ ልዩ ልዩ ተቋማትን፣ የህዝብ መኖሪያ ቤቶችንና ባህላዊ የገበያ አዳራሾችንና የባህል ተቋማትን…ወዘተ. መገንባት ይቻላል? ገንዘብና ሌሎች ሪሶርሶችንስ በምን መልክና ዘዴ በማንቀሳቀስ ተግባራዊ ማድረግ ይቻላል?  በእነዚህ መሰረታዊ ነገሮች ላይ መወያየት የፖለቲካል ራሺናሊቲና የሰብአዊነት መሰረተ-ሃሳቦች ናቸው። ባጭሩ በጠቅላላው አገርን ስለመገንባት ጉዳይ የራስን አቋም በግልጽ ሳያስቀምጡ ወይም በሀተታ መልክ ሳይጽፉ ከሌላው ሰው ፖለቲካ ራሺናሊቲ መጠበቅ እኔ ብቻ ነኝ ራሺናሊ ማሰብ የምችለው ብሎ እንደመመጻደቅ ይቆጠራል።

ዮናስ ብሩ ይህንን ጉዳይና በተለይም ለሁላችንም ግልጽ እንዲሆንልን ራሱ የሚያራምደውን የፖለቲካ ርዕዮተ-ዓለም ቢነግረን ኖሮ ምናልባት ምንነቱን ልንረዳው እንችል ይሆናል። ካለበለዚያ እንዲያው በደፈናው በራሺናሊቲ ስም ከፍተኛ ወንጀል ስለሚሰራ የግዴታ የራስን የፖለቲካ አቋም መናገር ያስፈልጋል። የፖለቲካ አቋም ሲባልም ቀኝ፣ ግራ፣ ፋሺሽስት፣ ወይም ኮንሰርቫቲቭ…ወዘተ. እያሉ በግልጽ ማስቀመጥ ያስፈልጋል። በጥሩ የእንግሊዘኛም ሆነ የአማርኛ ቋንቋ ተጽፈው የሚነበቡ ነገሮች አንባቢውን ስለሚያወናብዱ በይዘትና በፖለቲካ ርዕይ መሞላት ያለባቸው ይመስለኛል። በዚያን ጊዜ ማን በምን ርዕይ ላይ ተመስርቶና ለምን ዓላማ እንደሚታገል ማወቅ ይቻላል። በሌላ ወገን ግን የዮናስ ብሩን አመለካከት እንደተረዳሁትና ከእኔም ጋር በኢ-ሜይል ልውውጥ ባደረገልኝ ሃሳብ መሰረት በአጠቃላይ ሲታይ ደሃ ህዝብን እንደሚጠላ ነው። የቀኝ አስተሳሰብም ያለውና ሙሉ በሙሉ በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም የበላይነት የሚያምን ነው። ይህ አመለካከቱ ደግሞ የግዴታ የፖለቲካል ራሺናሊዝምን አስተሳሰብ የሚቃረን ነው።  በተለይም ፕሮፌሰር ጄፈርሲ ሳክስ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስለሰፈነው የድህነት መስፋፋት ያደረገውን በጣም ግሩም ቪዲዮ ካዳመጥኩኝ በኋላ ለዮናስ ብሩ ሊንኩን ልኬለት የሰጠኝ መልስ ደሃን እንደሚጠላ ነው። ሁላችንም እንደምናውቀው ደግሞ ከደሃ አገር የመጣንና አብዛኛዎቻችንም ከደሃ ቤተሰብ የተወለድን በመሆናችን ደሃው ህዝባችንን ልንጠላው አንችልም። ባያልፍለት ነው እንጂ ደሃም ሰው እንደማንኛውም ሰው በእግዜአብሄር አምሳል የተፈጠረ ነው። ምናልባትም ደሃ የሚባለው ሰው የመማር ዕድል ቢያጋጥመው ኖሮ ከሌላው የተሻለ የማሰብ ኃይል ሊኖረው ይችላል። ለማንኛውም የተማርነውና የምንማረው ደሃው ህዝባችንን ለመናቅና በሱ ላይ ለመኩራራት ሳይሆን የሱ አለኝታ በመሆን ከድህነቱ እንዲላቀቅ መንገዱን በማሳየት የስልጣኔ ባለቤት እንዲሆን ለማድረግ ነው። ታላላቅ ፈላስፋዎችና ሳይንቲስቶችም የሚያስተምሩን ይህንን ነው።

ለማንኛውም ፖለቲካል ራሺናሊቲ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ፣ በአጠቃላይ ሲታይ በአስተዳደር ፍትሃዊነት የሚገለጽና፣ ኢ-ሳይንሳዊና አገር አፍራሽ በሆነ የኢኮኖሚ ፖሊሲ የሚከሰት ማህበራዊ መዛባትንና ያልተስተካከለ የሀብት ክፍፍልን የሚቃወም ነው። በፖለቲካል ራሺናሊቲ መሰረተ-ሃሳብ መሰረት በተለይም በኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካይነት የሚከሰት ኢ-ፍትሃዊነት፣ ሚዛናዊነት ያጣ የሀብትና የገቢ ክፍፍል ለማህበራዊ ሁኔታ መደፍረስ ዋናው ምክንያት ስለሚሆን የፖለቲካል ራሺናሊቲ መመሪያዬ ነው የሚል ግለሰብ የግዴታ ከሚበደለው ህዝብ ጎን በመቆም ጥብቅናውን ማስመስከር አለበት።  ፖለቲካል ራሺናሊቲ  የግለሰብ መብትን በማወቅ ዲስፖታዊ አገዛዝንም የሚቃወም ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ የተንሰራፋውን እኔ ብቻ ነው የማውቀው፣ የእኔን ሃሳብ ብቻ ተቀበሉ የሚለውንም የበላይነት መንፈስ የሚቃወም ነው። በተለይም በአሁኑ ዘመን ብዙ ነገሮች ለተራው ሁዝብ ግልጽ ሆነው በማይገኙበት ዘመንና በፍጆታ ምርትና በቴክኖሎጂዎችም መንጋጋት የተነሳ የሃሳብ ውዥንብርነት በተስፋፋበት ዘመን፣ በተለይም ቴክኖሎጂን ተገን አድርገው የዓለምን ህዝብ የሚያሰቃዩትን የግዴታ በቲዎሪና በኢምፔሪካል ደረጃ እያጠኑ ማቅረብና ማስረዳት ያስፈልጋል። ስለሆነም እንደ ካፒታሊዝምና ኢምፔሪያሊዝም የመሳሰሉትን ሳይንሳዊ ፅንሰ-ሃሳቦች በማጥናትና በሰፊው በመጻፍ ማንኛውም ግለሰብ እንዲረዳው አድርጎ ማቅረብ ያስፈልጋል። በተለይም በእነዚህ ሁለት መሰረታዊ ፅንሰ-ሃሳቦች ላይ ጥራት ሳይኖርና በየጊዜውም ሀተታ ሳይሰጡ ስለፖለቲካ ራሺናሊቲ ማውራት በፍጹም አይቻልም።  ባለፉት ስድሳና ሰባ ዓመታት እነዚህን ጽንሰ-ሃሳቦች በሚመለከትና፣ በተለይም የሰው ልጅ ህይወት ምን መምሰል አለበት በሚለው ላይ ሰፋፊና የጠለቀ ጥናት ስለተካሄዱ ሁለቱን ፅንሰ-ሃሳቦች የግራ-ቀደም አስተሳሰቦች ነው ብሎ ማጥላላት ልክ ትልቅ የታሪክ ወንጀል እንደመስራት ይቆጠራል። ጽንሰ-ሃሳቦችም ከእኛ በብዙ ሚሊዮን ማይሎች ርቀው በሄዱ ምሁራን የፈለቁና የዳበሩ ስለሆነ ማንኛውም ለህዝብና ለአገር ነፃነት እታገላለሁ የሚል ግለሰብም ሆነ ድርጅት ሁሉ የእነዚህን ፅንሰ-ሃሳቦች ምንነት ሳይረዳ ለአንድ ብሄረሰብም ሆነ ለግለሰብአዊ ነፃነት እታገላለሁ ሊል አይችልም።

ከዚህ አጠር መጠን ያለ የፖለቲካ ራሺናሊቲ አስተሳብ ስነሳ ዮናስ ብሩ አንድም ቦታ ላይ የአሜሪካንን የአመጽ ፖለቲካና፣ በተለይም የሚቆጣጠራቸውን የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅትና(IMF) የዓለም ባንክን(World Bank) ተገን በማድረግ ተግባራዊ እንዲደረግ አገሮችን የሚያስገድደውን የኒዎ ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተቃውሞ አያውቅም። በዚህም ላይ ግልጽ አመለካከት የለውም። ራሱ ለተወሰኑ ዓመታት በዓለም  ባንክ ውስጥ ተቀጥሮ ይሰራ ስለነበር በቀጥታ አገር አፍራሽ የሆነንና ህዝብን ደሃ የሚያደርግ የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ በተጨባጭ ተግባራዊ ሲያደርግ ነበር የከረመው። የአሜሪካንንም የውጭ ፖሊሲ፣ በኢራክ፣ በአፍጋኒስታን፣ በሊቢያና እንዲያም ሲል ከወያኔ ወይም ከህውሃት ጎን በመሰለፍ አገራችንን ሲያፈራርስ አንድም ቦታ ላይ ይህንን የአመጽ ፖሊሲ በመቃውም ድምጹን ያሰማበት ጊዜ የለም። በተለይም አሜሪካን በሱዳን በኩል ለወያኔ መሳሪያ እያቀበለ አማራው እንዲጨፈጨፍ ሲያደርግ ይህንን ኢ-ሰብአዊና የጣልቃ-ገብ የእሜሪካንን ኢምፔሪያሊስታዊ ፖለቲካ በፍጹም አልተቃወምም። የዮናስ ብሩን አንዳንድ ጽሁፎች ሳነብና በአንዳንድ ጋዜጠኞች ሲጋበዝ የሚሰጣቸውን ሀተታዎች ሳዳምጥ ዝም ብላችሁ የአሜሪካንና የተቀረውን የምዕራብ አውሮፓ ካፒታሊስት አገሮችን ፖለቲካ አትተቹ ነው የሚለን፤ የሚፈጽሙትን ወንጀል በሙሉ አሜን ብላችሁ ተቀበሉ ነው የሚለን። ኃይል ያለው የፈለገውን (Might is Right)  የማድረግ መብት አለው በሚለው የሚያምን ነው። ይህ ዐይነቱ አስተሳሰብ ደግሞ ሶፊስታዊና እነ ፕሌቶ ከዛሬ ሁለት ሺህ ዓመት በፊት አጥብቀው ይዋጉ የነበረውን አደገኛና የተሙለጨለጨ አሰተሳሰብ የሚመስል ነው። ታዲያ የዮናስ ብሩ የፖለቲካል ራሺናሊቲ ምኑ ላይ ነው?

እንደሚታወቀው በአገራችን ምድር በፖለቲካ ርዕይ፣ በፖሊሲና በአንዳች እሴት ዙሪያ ተደራጅቶ ለዚህ ርዕይ ነው የምታገለው፣ ለሰፊው ህዝብም አስተማማኝ ተስፋ ለመስጠት የምችለው ይህንን ዐይነቱን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ደረጃ በደረጃ ተግባራዊ በማድረግ ነው ተብሎ ትግልና ክርክር ስለማይደረግ የአብዛኛዎቻችን አመለካከት በተቋም ደረጃ በተሰባሰበ ድርጅት አካባቢ ሳይሆን ያለን አትኩሮና ዕምነት በታወቁ አንዳንድ ግለሰቦች ዙሪያ ነው። ይህ ዐይነቱ ከህብረተሰብ ግንባታና ከሳይንስ አንፃር ትክክል ያልሆነ አካሄድ በተለይም በአለፉት 40 ዓመታት ወደማይሆን ግብግብና ኩርፊያ፣ እንዲያም ሲል ወደ ስም መጠፋፋት ሊያበቃን ችሏል። አብዛኛው ነገር በአንዳንድ ግለሰቦች ዙሪያ ስለሚሽከረከርና እነሱንም ወደ ማምለክ ስለሚደረሰ በድርጅትና በዕውቀት ዙሪያ መሰራት ያለባቸው የአንድን ህብረተሰብ ችግር ወይም የተወሳሰቡ ችግሮችን ለመፍታት ያመቻሉ በሚባሉ ፖሊሲ ነክ ነገሮችና ሳይንሳዊ ጥናቶች ላይ ይህንንም ያህልም ትኩረት ስለማይሰጥ ዝም ብለን ብቻ ካለመመሪያና የቲዎሪ መሰረትና ሳይንስ ዝምብለን እንጋልባለን። በአብዛኛዎቻችንም ዘንድ ያለው ዕምነት የአንድ ህብረተሰብ የተወሳሰቡ ችግሮች፣ በተለይም እንደ ኢትዮጵያ በመሰለ አገር ያሉ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ የፀጥታ ጉዳይ፣ የባህልና የስነ-ልቦና መከስከስ ጉዳይ፣ እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍም ሆነ ለማስተካከል የሚያስፈልጉ ተቋማት ያለመኖር ጉዳይ አንድ ግለሰብ ወይም ቡድን ብቻ ስልጣንን ቢይዝ የሚፈታው ነው የሚመስለን። ወይም ደግሞ በጥብቅ እንደተከታተልኩት አብዛዎቻችንን  የሚከነክነን የህብረተሰባችንና የህዝባችን ጥያቄዎች መመለስ ጉዳይ  ሳይሆን  አንድ የምንጠላውና በእርግጥም የተወሳሰቡ ችግሮች ውስጥ የሚከተን ኃይል ወይም ግለሰብ ከተወገደና በሌላ ግለሰብ ወይም ቡድን ቢተካ የምንፈልገው ነገር የሚሳካ ይመስለናል። ይህ እንደማይሆን ግን በአገራችን ብቻ ሳይሆን በአብዛኛዎቹ የሶስተኛው ዓለም ተብለው በሚጠሩ አገሮች ውስጥ የሚታይና ህዝቦችን የባሰ የሚያደኽይና አቅመቢስም እንደሚያደርግ የተረጋገጠና በገሃድም የሚታይ ነው። ለዚህ ዋናው ምክንያት ደግሞ በየአገሮች ውስጥ ያለው የንቃተ-ህሊና ጒዳይ ከዜሮ በታች በመሆኑ ነው።

በአውሮፓ የፓርቲዎች የአደረጃጀት ታሪክ ሂደት ውስጥ በፍጹም የሞናርኪዎች(Absolute Monarchs) አገዛዝ ዘመን ካልሆነ በስተቀር ፖለቲካ የሚባለው ነገር በአንድ ግለሰብ ዙሪያ መሽከርከር ካቆመ ከመቶ ዓመት በላይ አልፎታል። ፖለቲካ የሚባለውም ነገር አገር መገንቢያና ህዝብን የሚያሳትፍ መሆኑ በተለይም በፓርቲ ደረጃ በተደራጁ ቡድኖች ዘንድ ከፍተኛ ግንዛቤ ከገባ ዘመናት አስቆጥሯል። ስለሆነም ፖለቲካ የሚባለው ነገር በአንድ ግለሰብ ዙሪያ የሚሽከረከር ሳይሆን በፓርቲና በተቋማት ደረጃ መሆን እንዳለበት ከፍተኛ ግንዛቤ አለ። ስለሆነም በተቋም ወይም በድርጅት ደረጃ፣ በአንዳች ዐይነት ቲዎሪና ርዕይ፣ እንዲሁም የህዝብን ችግር ለመፍታት ያስችላል በሚባል ፖሊሲ ዙሪያ የሚሰባሰቡ ግለሰቦች የሚመሰርቱት ድርጅት ወይም ፓርቲ ተከታታይነት ያለው ነው። በዚህም ምክንያት ማንኛውም ግለሰብ፣ ለምሳሌ የፓርቲ ሊቀመንበር በሌላ ሊተካ እንደሚችልና፣ እሱም የህዝብን ጥያቄ ለመፍታት የማይችል ከሆነና በፓርቲው ውስጥ ተቀባይነት ከሌለው ስልጣኑን እንደሚለቅ የተለመደ ነገር ነው። ተቀባይነት የሌለው የፓርቲ ሊቀመንበር ውረድ፣ ስልጣንህን ልቀቅ ቢባል በፍጹም ሊያንገራግር አይችልም። ይህ ዐይነቱ አካሄድም የተለመደ አይደለም። ይህ ዐይነቱ የፓርቲዎች አደረጃጀትና በጠራ ርዕይና በፖሊሲ ዙሪያ መሰባሰብ ለአንዳንድ ፓርቲዎች ተከታታይነት እንዲኖራቸው አስችሏቸዋል። ለምሳሌ የሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ ዕድሜ ከ155 ዓመታት በላይ ሲሆን፣ እንደ ክርስቲያን ዲሞክራቲክ ፖርቲ የመሳሰሉት ደግሞ ከሰባና ከሰማንያ ዓመታት በላይ ዕድሜ አላቸው። እንዲሁም ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ የተመሰረቱ ፓርቲዎች የ70ና የአርባ ዓመታት ዕድሜ ማስቆጠር ችለዋል። ወደእኛ አገር ስንመጣ ፓርቲዎች በጠራ የፖለቲካ ርዕይና የህብረተሰብ ችግርን ሊፈታ ይችላል በሚባል ፖሊሲ አካባቢ የተሰባሰቡ ስላልሆነ ሳንወድ በግድ የግዴታ የግለሰቦች ስም ጎልቶ ይታያል። ጎልቶ የሚታየው ሰውም የመሰረተው ፓርቲ ተከታታይነት እንዲኖረውና እሱም አንድ ነገር ቢሆን እሱን ሊተካ የሚችል ሰው ሳያዘጋጅ አንድ ነገር በሚፈጠርበት ጊዜ ፓርቲው እንዳለ የመበታተን አደጋ ይደርሰዋል። ለምሳሌ የግንቦት ሰባትንና በአብዮቱ ዘመን ስማቸው ገኖ የወጣውን የመኢሶን፣ የኢሃፓንና የኢሃድን፣ እንዲሁም የኢሳፓን ዕጣ ማየቱ ብቻ ይበቃል። እነዚህ ሁሉ ድርጅቶች የመጨረሻ መጨረሻ ሊወድቁና ደብዛቸው ሊጠፋ የቻለው ከረጅም ዓመታት የሳይንስና የቲዎሪ ጥናት በኋላ የተመሰረቱ ባለመሆናቸው ነው። አብዛኛዎች ድርጅቶችም ሰለፖለቲካ ኢኮኖሚክስ፣ ስለሶስዮሎጂ፣ ስለሳይንስና ስለቴክኖሎጂ አስፈላጊነት ይህን ያህልም ጥናት አላካሄዱም፤ እነዚህም ዕውቀቶች አንድን ህብረተሰብ ለመገንባት አስፈላጊ ለመሆናቸው ግንዛቤ ያላቸው አይመስልም። ባጭሩ ፖለቲካን ከዕውቀት ነጥለው በማየታቸውና ድርጅቶቻቸውን በጥቂት ግለሰቦች ወይም በአንድ ግለሰብ ዙሪያ ብቻ እንዲሰባሰቡ በማድረጋቸው ህዝባዊና አገራዊ ጥፋት አስከትለው የመጨረሻ መጨረሻም ራሳቸውም ሊጠፉ ችለዋል።

ለማንኛውም በመስፍን አረጋ ላይ  ያለኝ ትችት፣ ዮናስ ብሩን አስመልክቶ የሰጠው ትችት ከፖለቲካ ርዕይና ከኢምፔሪካል አንፃር ስመለከተው የተሳሳተ መሆኑ ብቻ ሳይሆነ ተራ ዘለፋ ነው። ከሳይንስ የአሰራር ስልት ተገቢ የሆነ አቀራረብ አይደለም። ሌላው በሚገባ በቁጥር ውስጥ መግባት ያለበት ጉዳይ ማንኛውም በፖለቲካ ስም የሚንቀሳቀስና አንድ ድርጅትንም ሆነ አገርን እወክላለሁ የሚል ስህተት ሲሰራ ሲታይ፣ ወይም ካሳይንስና ከራስሽናል አስተሳሰብ አንፃር ትክክል ያልሆነ አነጋገር ሲናገር ወይም መግለጫ ሲሰጥ ዝም ተብሎ ሊታለፍ አይገባውም። መታወቅ ያለበት አገር አንድ አገርና ህዝብ የአንድ ግለሰብ ወይም የአንድ ድርጅት የግል-ሀብቶች አይደሉም። ስለሆነም ማንኛውም ሰለፖለቲካ ዕውቀት አለኝ፣ የአገሬና የህዝቤም ጉዳይ ያገባኛል የሚል በተገቢው መንገድ ቅሬታውን ማሰማትና አስተያየትም የመስጠት መበት አለው።

ወደ ዋናው ቁም ነገር እንምጣ። በተለይም “የአማራው ህዝብ የህልውና  ትግል በውጭ መንግስታት ተሰሚነቱን ማግኘት የጀመረው የዲፕሎማሲው ትግል ከተጀመረ በኋላ ነው”  የሚለው ከፖለቲካ ሳይንስ አንፃርና የምዕራቡ ካፒታሊስት ዓለም፣ በተለይም ደግሞ አሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም በኢትዮጵያ ላይ ከተከተለውና ከሚከተለው የብዙ አስር ዓመታትን ያስቆጠረ ተግባራዊ ፖለቲካ(Practical Politics) አንፃር ሲታይ በጣም ስህተት ነው። አሜሪካን በተለይም ከ1945 ዓ.ም የበላይነትን ከተቀዳጀበት ጊዜ ጀምሮ በጣም በረቀቀ መልክ በተለይም የሶስተኛው ዓለም ተብለው የሚጠሩ አገሮችን በእሱ የርዕዮተ-ዓለም ተፅዕኖ(Sphere of Influence)  ለማምጣት የተከተላቸውን የኢኮኖሚ፣ የሚሊታሪ፣ የፀጥታና የፖለቲካ  አካሄዶች በፍጹም ከግምት ውስጥ ያስገባና፣ ይህም የአሜሪካን ኤምፔሪያሊዝም መገለጫውና የበላይነትን የሚቀዳጅበት ዘዴው መሆኑን መስፍን አረጋ በድንብ የተረዳው አይመስልም።  ይህ ዐይነቱ የተፅዕኖ ፖለቲካም በየአገሮች ውስጥ የሚካሄደውን ዕድገትና አንድን ህዝብ የተሟላ ነፃነት እንዲኖረው ለማድረግ ተግባራዊ መሆን የሚገባቸውን ሁለ-ገብ የዕድገት ስትራቴጂ ማጨናገፊያ ዘዴ ነው። ይህንን ጉዳይ በሚመለከት “John Galtung;  Imperialism and Structural  Violence” በሚለው በጣም ግሩም መጽሀፉ ውስጥ አስቀምጦታል። ሌሎችም እንደዚሁ በኢምፔሪያሊስት አገሮችና በሶስተኛ ዓለም መንግስታት መሀከል የነበረውንና ያለውን ግኑኝነት፣ ይህም ለተሟላና ለተስተካከለ ዕድገት፣ እንዲሁም ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት ማበብ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደጣለባቸውና፣ እንደሚጥልባቸው፣ በዚህም ምክንያት የተነሳ ከድህነትና ከኋላ ቀርነት በቀላሉ ሊላቀቁ እንዳልቻሉ በሰፊው ተጽፎ ይገኛል። ይህ ብቻ ሳይሆን የሶስተኛው ዓለም ተብለው በተጠቃለለ መልክ የሚጠሩ አገዛዞች በሙሉ ከታች ወደ ላይ ቀስ በቀስ እየተኮተኮቱ የተገነቡና ሁለ-ገብ ዕድገት እንዲፈጠር አመቺ ሁኔታዎችን የሚፈጥሩ አገዛዞች ሳይሆኑ አምባገነኖች ወይም ፋሺሽቶች ናቸው። ይህም ማለት የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና በሶስተኛው ዓለም አገሮች ያሉ አምባገነናዊ ወይም ፋሺስታዊ አገዛዞች በሙሉ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው። ስለሆነም የአገራችንም የመንግስት መኪና አወቃቀር ከአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ተፅዕኖ ቁጥጥር ውጭ ያልሆነና፣ በተለይም የወያኔም ሆነ የአቢይ አገዛዝ የአሜሪካን አሻንጉሊትና ሎሌዎች ናቸው።

ከዚህ አጭር ሀተታ  ስንነሳ  የመስፈን አረጋና  የሌሎችም አካሄድ በዲፕሎማሲ ትግል የአሜሪካኑና የተቀረውን የምዕራብ አውሮፓ ካፒታሊስት አገሮች ፖለቲካ እናስቀይረዋለን፤ ለኛ ደሃ ህዝብ ርህሩህ ልብ እንዲሰጣቸው ለማድረግ እንችላለን  የሚለው አባባል ከራሱ ከካፒታሊስት የኢኮኖሚ ስርዓትና ከኢምፔሪያሊዝም የተፈጥሮ ባህርይ አንፃር ሲታይ  በፍጹም የሚሰራ አይደለም። ምክንያቱም ኢምፔሪያሊዝም በበላይነት ስለሚያምንና የእሱ ዘለዓለማዊ ሎሌ ሆነን እንድንቀር ስለሚፈልግ ብቻ ነው። ይህ የኢምፔሪያሊዝም ባህርይ ስለሆነ በመለመማጥ የሚሰራ አይደለም።  መስፍን አረጋ ምናልባት የአገራችንን የፖለቲካ ሁኔታ በደንብ ተከታትሎ እንደሆን፣ አሜሪካንና የተቀሩት የካፒታሊስት አገሮች በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ከፍተኛ ደባ የሰሩ ናቸው። አብዮቱ ሲፈነዳ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ አሸባሪ ኃይሎችን በማስታጠቅ በቀይና በነጭ ሽብር ዘመቻ ውስጥ ተሳትፈዋል። ለብዙ ሺህ ወጣቶችም መሞት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተጠያቂ ናቸው።  ከዚያም በኋላ ሶማሊያ ኢትዮጵያን እንድትወር በቀጥታ ሰይድ ባሬን በማስታጠቅ በህዝባችንና በአገራችን ላይ ከፍተኛ ጉዳት ለማድረስ በቅተዋል። አሜሪካንና የተቀረው የምዕራቡ ካፒታሊስት አገሮች ወያኔን፣ ሻቪያንና ኦነግን፣ እንዲሁም ኢድህን በማስታጠቅና በመምከር የደርግ አገዛዝ በአጠቃላይ ጦርነት ውስጥ እንዲዘፍቅ ለማድረግ በቅተዋል። በዚህም ምክንያት ደርግ ወደ አውሬነት እንዲለወጥ በማድረግ አጠቃላዩ ዕድገት ተዘናግቶ ሁሉም ነገር ወደ ጦርነት እንዲያመራ ለመደረግ በቅቷል። በዚህ ዐይነቱ የእርስ በርስ ጦርነትም መጠኑ የማይታወቅ የስው ህይወት ጠፍቷል፤ በተጨማሪም እንደዚሁ መጠኑ የማይታወቅ ለሁለ-ገብ ዕድገት ሊያገለግልና ህዝባችንን ከድህነት አውጥቶ አገራችንና ህዝባችን በጠንካራ መሰረት ላይ እንዲራመዱ ለማድረግ የሚችለው የጥሬ-ሀብትና በብዙ መቶ ሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ለአላስፋላጊ ጦርነት እንዲውል ተደርጓል። ይህም ጉዳይ አሜሪካን በሁለተኛው ዓለም ጦርነት በአሸናፊነት ከወጣ ጊዜ ጀምሮ የሚከተለው የአንድን አገር ህዝብ በብሄርና በሃይማኖት በመከፋፈል እርስ በራሳቸው እየተፋጁ እንዲኖሩ ከሚያደርገው ሰይጣናዊ ተግባሩ ውስጥ አንደኛውና ተቀዳሚው ስራው ነው። በዚህ ዐይነቱ ሰይጣናዊ ስራም ነው የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና የተቀረው የምዕራብ አውሮፓ የካፒታሊስት አገሮች የበላይነታቸውን ይዘው ለመቆየት የሚችሉት። በጸጥታውና በሚሊታሪው፣ እንዲሁም በስቪል ቢሮክራሲው ውስጥ ባላቸው ሰዎች አማካይነት የተነሳ  በጊዜው ይሰራ የነበረውን የጋፋት የጦር ፋብሪካ እንዲከሽፍ የመንግስት ግልበጣ ይጠነስሱ ነበር። ይህም ጉዳይ በአንድ አገር ወዳድ መኮንን  በመጽሀፍ መልክ በሚገባ ተብራርቶ ተጽፎ ለንባብ ቀርቧል። የደርግ አገዛዝም ሊወድቅ የቻለው አሜሪካኖች ውስጥ ለውስጥ ባስቀመጧቸው የስለላ ሰዎች ነው። እነዚህም ደግሞ ኢትዮጵያውያን ናቸው። ወያኔ በአሜሪካንና በእንግሊዝ ድጋፍ ስልጣን ላይ ሲወጣ ዋናው ዓላማውም ኢትዮጵያን በጎሳ በመከፋፈል ከውስጥ ማዳከምና ሀብትን መበዝበዝ ነው። ይህም ዕቅድ የአሜሪካኖችና የእንግሊዞች ነው። ባጭሩ ወያኔና የተቀረው እንደነ ክፍሌ ወዳጆ የመሳሰሉት የባንዳ ልጆች ተግባራዊ ያደረጉት ነገር የአሜሪካኖችንና የእንግሊዞችን አገርን የማውደም ፕሮጀክት ነው።  ወያኔ ስልጣን ላይ ከመውጣቱ በፊት በኸርማን ኮኸን ሊቀመንበርነት ለንደን ላይ በተደረገው ስብሰባ ህወሃት፣ ሻቢያና ኦነግ በተካፈሉበት ስብሰባ ላይ የጎሳ ፌዴራሊዝም ተግባራዊ እንዲሁን ያስገደዱት አሜሪካኖች ናቸው። ከህብረ-ብሄር ግንባታ አንፃር የቱን ያህል የኋሊት ጉዞ እንደሆን መስፍን አረጋ የሚገባው ይመስለኛል። ከዚያም ባሻገር  ወያኔ ስልጣንን ሲጨብጥ ለምዝበራ የሚያመች የኒዎ-ሊበራል የሚባል አገር አፍራሽ የኢኮኖሚ ፖሊሲ(Fast Food Economic Policy) ተግባራዊ እንዲያደርግ በዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት(IMF) አማካይነት ተረቆ ቀርቦለታል።  ይህንን አገር አፍራሽ የኢኮኖሚ ፖሊሲም ተግባራዊ ሲያደርግ ብቻ ነው የእነሱን ዕርዳታ ሊያገኝ የሚችለው። እንዳየነውና ብዙ ጥናቶችም እንደሚያረጋግጡት ይህ ዐይነቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲና የኢኮኖሚ ዕርዳታ ብለው የሚጠሩት ነገር አንድን አገር በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ሁለ-ገብ ኢኮኖሚ እንድትገነባ በፍጹም አያስችላትም። እንዲያውም ድህነትን የሚያስፋፋና ኋላቀርነትን የሚያጠነክር ለመሆኑ በአገራችን ምድር ያለው ተጨባጩ የህዝባችን የኑሮ ሁኔታ ያረጋግጣል። መስፍን አረጋ ስለፖለቲካል ኢኮኖሚክስ ህግ የሚገባው ከሆነ አንድ አገር በዚህ ዐይነቱ ፖሊሲ ድህነትን ልትቀርፍና ታላቅ አገርም ልትገነባ በፍጹም አትችልም። ፖሊሲው ድህነትን ከማስፋፋት ባሻገር ባህልንንም አውዳሚ ለመሆኑ የአገራችንን ሁለመንታዊ ሁኔታ ለተከታተለ ሊገነዘበው ይችላል። በአገራችን ያለው ትልቁ ችግር በተበላሸና ኢ-ሳይንሳዊ የኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካይነት ሊከስቱ የሚችሉ የስነ-ልቦናና የባህል ውድመቶች በፍጹም አይጠኑም። በተጨማሪም በተበላሸ የኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካይነት ከሶስዮሎጂ አንፃር ውስጠ-ኃይሉ ከፍ ያለና ፈጣሪ የሆነ (Pioneer Spirit) ያለው የህብረተሰብ ክፍል የሚፈጠር ሳይሆን የታወቀው የግብጹ ኢኮኖሚስት ፕሮፌሰር ሳሚር አሚንና አሜሪካዊው ጉንደር ፍራንክ ሉምፐን ቡርዧዋዚ(Lumpen Bourgeoisie) ብለው የሚጠሩትና ብልግናን የሚያስፋፋና የአገርን ሀብት የሚያወድም የህብረተሰብ ክፍል ነው የሚፈጠረው። ይህም ክስተት ባለፉት ሰላሳ አራት ዐመታት በአገራችን ምድር ዕውን የሆነና የተረጋገጠ ጉዳይ ነው። ከላይ እንዳልኩት ይህም ጉዳይ ከሶስዮሎጂ አንፃር ስለማይጠና እንደ ቁም ነገር አይወሰድም ወይም ደግሞ ዝም ብሎ ይታለፋል። ስለሆነም እንደዚህ ዐይነት ምሁራዊ ድክመት ባለበት አገር ውስጥ ይህ ዐይነቱ ስርዓተ-አልባኘነት ስር እየሰደደ በመሄድ በጊዜው መወሰድ የሚገባቸው የዕርማት ዕርምጃዎች ተግባራዊ አይሆኑም።

ስለሆነም በአገራችን ምድር የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚክ ፖሊሲ ተግባራዊ ከሆነ በኋላ አገራችን በጣም ነው የረከሰችው። ግብረ-ሰዶማዊነት በከፍተኛ ደረጃ ነው በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊስፋፋ የቻለው። የእኛ ሴት ልጆች የሚሆኑት ወደ ሴተኛ አዳሪነት የተለወጡት ይህ ዐይነቱ ኢ-ሳይንሳዊ  የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ ከሆነ በኋላ ነው። በተጨማሪም ወጣቱ ወደ ድረግና ወደ ጨአት ቃሚነት የተለወጠው ይህ ዐይነቱ ፖሊሲ ተግባራዊ ከሆነ በኋላ ነው። ሌላው ጉዳይ ይህ ዐይነቱ ፖሊሲ ለወጣቱ የስራ መስክና የሙያ ማስልጠኛ ዕድል ለመክፈት ባለመቻሉ የእኛ ሴት ልጆች የሚሆኑት ለግርድና ወደ አረብ አገሮች ልክ እንደባሪያ የተሸጡበትን ሁኔታ እንመለከታለን። በወያኔና አሁን ደግሞ በአቢያ አህመድ አገዛዝ ድጋፍ በአገራችን ምድር ዘመናዊ የባሪያ ሽያጭ በከፍተኛ ደረጃ እንደተስፋፋ ይታወቃል። በዚህ ዐይነቱ ዘመናዊ የባሪያ ንግድ በብዙ ሺሆች የሚቆጠሩ እህቶቻችን ወደ አረብ አገሮች በመሰደድ ዕድላቸው ተቀጥፏል። በብዙ ሺሆች የሚቆጠሩም ህይወታቸውን እንዲጠፋ ለመደረግ በቅቷል። ባጭሩ አሜሪካና ግብረ-አበሮቹ የሚፈልጉትን አገርን የማሽመድመድ፣ ህዝብን የማድኽየትና የማደንቆር ስራ ነው ወያኔ፣ አሁን ደግሞ አብይ አህመድ ተግባራዊ ያደረጉትና የሚያደርጉት።  የአሜሪካና የተቀረው የምዕራብ አውሮፓ ካፒታሊስት አገሮች ዋናው ፍላጎት በነፃ ገበያ ስም አሳቦ በአንድ አገር ውስጥ የበሰለና አገር ወዳደ የሆነ ምሁራዊ ኃይል እንዳይፈጠር ማድረግ ነው። በዚያውም እንደኛ ያለው አገር የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት እንዳትሆን መንገዱን መዝጋት ነው። መስፍን አረጋ ይህንን ሁሉ በሚገባ የተከታተለና የመዘገበ ይመስለኛል። አንድ ሰው ይህንን ሲረዳ ብቻ ነው አማራ ነኝ፣ የአማራንና የፋኖዎችን ትግል እደግፋለሁ ሊል የሚችለው። ከዚህም በላይ ወያኔ ስልጣን ላይ በነበረበት ጊዜ በአማራው ላይ ከፍተኛ የጥላቻ ዘመቻ አካሂዷል። አማራውን ጭራቅ አድርጎ በመሳል በተቀሩት ብሄረሰቦች ዘንድ እንዲጠላ ያላደረገው ሙከራ የለም። በዚህም ድርጊት የእንግሊዝና የአሜሪካን፣ እንዲሁም የተቀሩት የምዕራቡ አውሮፓ የስለላ ሰዎች ቄስ መስለው በመግባት ይህንን ዐይነቱን ጥላቻ ያካሂዱ ነበር። አማራዎች ይንቋችኋል እያሉ ነበር የሚነግሯቸው። ከዚህ በተጨማሪ ወያኔ 27 ዓመታት ያህል ስልጣን  ላይ በነበረበት ጊዜ በተለይም በወልቃይት ጠገዴ ወንድሞቻችንና እህቶቻች ላይ ያን ያህል ዕልቂት ሲያደረስ አሜሪካንና ግብረአበሮቹ ተባባሪዎች ነበሩ። የአማራ ሴቶችም እንዳይወልዱ ልዩ የማምከኛ መድሃኒት ይወጉ ነበር። ዋናው ተባባሪና ደጋፊ ቢልጌት የሚባለው መንፈሰ-አልባው ሰው ነው። ይህ ሁሉ የአሜሪካኖች ፕሮጀክት ነው። የአማራው ህዝብ በቁጥር መቀነስ አለበት የሚል ስትራቴጂ ነው።

ወያኔ በህዝብ ትግል ተገፍቶ ከስልጣን ሲወገድ አቢይ አህመድ ስልጣኑን እንዲረከብና ወያኔ የጀመረውን አገር የማፈራረስ ፕሮጀክት እንዲያገባድድ የተደረገው በአሜሪካኖች ፈቃድና ትዕዛዝ ነው። ሳውዲ አረቢያኖችም አሉበት። ይኸው እንደተከታተልነው አቢይ አህመድ ስልጣን ላይ ከወጣበት ቀን ጀምሮ የኦርቶዶክስ ቄሶችን ሲያሳድድና ሲገድል፣ ቤተክርስቲያናትን ሲያወድም አሜሪካኖችም ሆነ የተቀረው የምዕራቡ ካፒታሊስት አገሮች በሚገባ ያውቃሉ። በተዳጋጋሚ ሰስላማዊ ሰልፍና በፔትሽን መልክም ድምጻችንን ብናሰማም ማንም የሰማን የለም። የእነሱ ፍላጎትም የእኛን እሮሮ መስማት ሳይሆን አገራችን ስትፈራርስ መደሰት ነው። ወያኔ ከስልጣን ላይም ከተባረረ በኋላ በከፈተው ጦርነት እዚህ ጀርመን አገር የፖለቲካ አማካሪዎች ይሉ የነበረው ከኢትዮጵያ ብቻ ወደ ስድስት ሚሊዮን የሚጠጉ ስደተኞች ሊመጡ ስለሚችሉ እንጠባብቅ እያሉ ነበር የሚያወሩት። ይህም የሚያረጋግጠው በአገራችን ምድር የእርስ በርስ ጦርነት እንዲመጣ የማይሸርቡት ሴራ የለም  ማለት ነው። ወያኔ ጦርነቱን እንዲከፍት የተደረገውና ከመክፈቱ በፊት ወደ ስምንት መቶ የሚጠጉ መኮንኖች እንዲያልቁ የተደረገው በአሜሪካኖችም ሴራ ነው። ጦርነቱንም ከከፈተና በአጭር ጊዜ ውስጥ  ከተዳከመ በኋላ አሜሪካኖች በሚያቀብሉት መሳሪያ ነው ለማንሰራራት የቻለው። የእነ አቢይ እጅም አለበት። ይህም የሚያረጋግጠው አማራው በከፍተኛ ደረጃ ማለቅ አለብት። አካባቢው ወደ ጦርነት ቀጠና መለወጥ አለበት የሚለው ስትራቴጂም ሌላው  የአሜሪካኖችና የተቀረው የምዕራቡ ካፒታሊስት አገሮች ስትራቴጂ  ነው።

አቢይ አህመድ የአማራውን ልዩ ኃይልና ፋኖዎችን ትጥቅ አስፈታለሁ ብሎ ከሰባት ወራት በፊት በከፈተው ጦርነት ያህን ያህል ህዝብ ሲያልቅ ተው አላሉትም። እንዲያውም እንዲገፋበት ነው የሚያበረታቱት የነበረው። በእነሱ ዕምነት የአገር ወዳድነት ስሜት ያለው የአማራው ማህበረሰብና የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታዮች ስለሆኑ በከፍተኛ ደረጃ መዳከም አለባቸው። ይህ ሲሆን ብቻ  ነው ፍላጎታቸውን ተግባራዊ ማድረግ የሚችሉት። ሃይማኖትና ሞራል የሌለው የህብረተሰብ ክፍል በመፍጠር  ነው የፈለጉትን ማድረግ የሚችሉት። አሜሪካኖችና የተቀረው የምዕራቡ ዓለም በሊበራል ዲሞክራሲ ስለሚያምኑ ሞራል አላቸው ብሎ ማሰብ የዋህነት ብቻ ሳይሆን የእነሱንም የህሊና አወቃቀር አለማወቅ ነው። ይህ ዐይነቱ ሰይጣናዊ አስተሳሰብና ኢ-ሞራላዊ ተግባር በታወቁ የአሜሪካኖች ሳይንቲስቶችና ፈላስፋዎችች፣ እንዲሁም በምዕራብ አውሮፓ የታወቁ ምሁራን የሚወገዝ ነው። በእነሱ ዕምነትም የአሜሪካንና የምዕራብ አውሮፓ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የሚሊታሪና የፀጥታ ኤሊት አገሮቻቸውንም ሆነ የዓለምን ማህበረሰብ ወዳልሆነ አቅጣጫ እየመሩትና የኑሮንም ትርጉም እንዳይረዱት እያደረጉ ነው እየተባለ የሚጻፈው። በዚህ ዐይነቱ የተባለሸና ኢ-ሞራላዊ አካሄድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዘመናዊ የሆነ የንዑስ ከበርቴው ፋሺዝም በመስፋፋት ምስኪኑ ህዝብ መቀመጫና መቆሚያ እንዲያጣ ለመደረግ በቅቷል። በዚያው መጠንም አዳዲስ ፋሺሽታዊ ኃይሎች በመፈጠር ህዝቦችን እንዲያሹ ይደረጋሉ። በአገራችንም ያለው ሁኔታ የሚያረግግጠው ይህንን ነው። በተለይም ሀብታም የሆኑ የኢትዮጵያ ወንዶች ጋጠ-ወጥነትና በሴቶችና በህጻናት ላይ የሚፈጽሙት ግፍ መረኑን የለቀቀ ነው።

የኢኮኖሚ ፖሊሲውን አሉታዊ ተፅዕኖ ስንመለከት የአገራችን ገንዘብ ከዶላር ጋር ሲነፃፅር አርቲፊሻል በሆነ መልከ በክፍተኛ ደረጃ እንዲቀንስ በመደረጉ በአገራችን ምድር ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ሊታይ ችሏል። የዓለም የገንዘብ ድርጅትና የዓለም ባንክ ኤክስፐርቶች እንደሚሉት የአገራችን ብር ከዶላር ጋር ሲነፃፀር በመቀነሱ አገራችን ወደ ውጭ የምትልከው የምርት ብዛት በፍጹም አልጨመረም። ስለሆነም የንግድ ሚዟኗም አልተስተካከለም። ይባስ ብሎ በከፍተኛ ደረጃ ለመዛባት በቅቷል.። ይህ ብቻ ሳይሆን አገዛዙ ከውጭ የተበደረው ብድር በከፍተኛ ደረጃ በማደጉ የተነሳ ይኸው እንደምንያው ብድሩን በጊዜው ለመክፈል የማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል። ከውጭ የሚመጣው ብድር ደግሞ ወደ ውስጥ የአገርን ገበያን ለማስፋፋት ተብሎ ስለማይውልና በዚህም አማካይነት ወደ ውጭ የሚላክ ተወዳዳሪ የሚሆን በሳይንስ የተደገፈ የቴክኖሎጂ ውጤት ለዓለም ገበያ ሰለማይቀርብ አገራችን በንግድ ልውውጥ አማካይነት የምታገኘው የውጭ ምንዛሪ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። በሳይንስና በቴክኖሎጂ የማይደገፍ ኢኮኖሚ ደግሞ ሁልጊዜ በዕዳ እየዘፈቀና የባሰውኑ አገዛዙ የአንጀት አጥብቂኝ ፖሊሲ ተግባራዊ እንዲያድርግ እንደሚገደድ የአገራችንም ሆነ የሌሎች አገሮች የኢኮኖሚም ሁኔታ በሚገባ ያረጋግጣል። ስለሆነም ዛሬ አገራችን ትልቅ ዕዳ ውስጥ ገብታ የአቢይ አህመድ አገዛዝ መሽመድመድ ውስጥ የገባው በኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊስ አማካይነት ነው። ሌላው የሚያስቀው ደግሞ ቦንድ በመሸጥ የኢንዱስትሪ ፖለቲካ ተግባራዊ አደርጋለሁ ብሎ መገመቱ ያላዋቂነትን ነው የሚያረጋግጠው። ከታች ወደ ላይ በመነሳት፣ ወይም ከኋላ የመያዝ ስትራቴጂን በመከተል የኢንዱስትሪ ፖለቲካን ተግባራዊ ያደረጉ አገሮችን የኢኮኖሚ ግንባታ ታሪክ ስንመለከት ቦንድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ላይ በመሸጥ አይደለም በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ሰፋ ያለ የካፒታሊስት ኢኮኖሚ ወይም የገበያ ኢኮኖሚ ብለው የሚጠሩትን መገንባት የቻሉት። ውጤታማ የሆኑ የአንዳንድ አገሮችን ኢኮኖሚ ዕድገት ለማወቅ ለሚፈልግ ከታች የተዘረዘሩትን መጽሀፎች መመልክት ያስፈልጋል። ለማንኛውም በአገራችን ምድር ያለው ትልቁ ውዥንብር  ስለገንዘብ ያለን አስተሳሰብ በጣም ደካማ መሆኑ ብቻ ሳይሆን በካፒታሊስት አገሮች ቁጥጥር ስር የወደቀው የዓለም ገበያና ተቋማቶቻቸው በምን ዐይነት ሎጂክ እንደሚሰሩ አለማወቅ ነው። ለምሳሌ የገንዘብን ወይም የወረቀት ገንዘብን የዕድገት ታሪክ ስንመለከት በተለይም በእንግሊዝ አገር የውስጡ ገበያ እያደገና እየተስፋፋ ሲመጣ የግዴታ በወርቅ የሚደገፍ የወረቀት ገንዘብ ማተም አስፈለገ። ምክንያቱም ወርቅም ሆነ ብር(Silver) የተፈጥሮ ሀብት እንደመሆናቸው መጠን እንደልብ ማግኘት ስለማይቻልና፣ አብዛኛውን ጊዜም ከውጭ የሚመጡ ስለነበር ይህ ሁኔታ ለውስጥ ገበያው ማደግና መስፋፋት አመቺ አልነበረም። ስለሆነም የግዴታ በወርቅ የተደገፈ የወረቀት ገንዘብ ማተም አስፈለገ። ማዕከላዊ ባንክ በማቋቋምና የኢኮኖሚውን ዕድገት ለማፋጠን ሲባል በክሬዲት ስይስተም አማካይነት የኢንዱስትሪ ተከላንና የውስጥ ንግድን ለማፋጠን ተቻለ። ገንዘብም ከኢኮኖሚው ጋር እየተሳሰረ ሲመጣ በፍጥነት የመሽከርከር ኃይልም እያገኘና እየጠነከረም መምጣት ቻለ።  የኋላ ኋላ ግን ወርቅ ራሱ እንደልብ ስለማይገኝና በንግድ ልውውጥ አማካይነት ወደ ውጭ ይፈስ ስለነበር በመጀመሪያ እንግሊዝ በወርቅ ያልተደገፈ የወረቀት ገንዘብ ማተም ተገደደች። አሜሪካንም እንዲሁ ከ1971 ዓ.ም ጀምሮ በወርቅ የማይደገፍ የወረቀት ገንዘብ ማሰራጨት ጀመረ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የማንኛውም አገር ገንዘብ በወርቅ ያልተደገፈና  ውስጣዊ ዋጋ(Intrinsic Value) የሌለው ለመሆን በቃ። ይህም ማለት የማንኛውም አገር ገንዘብ፣ ዶላርም ጭምር በወርቅ የተደገፈ ወይም ልዩ ነገር ውስጡ ያለው ሳይሆን ከጥጥ የሚሰራ ነው። ይሁንና ግን እንደየቴክኖሎጂው ሁኔታና ከማተሚያ ዋጋ አንፃር የአንዳንድ አገሮች ብር ማለፍ ያለበትን ክንዋኔ ስለማያልፍ ኖቱ ይህን ያህልም ጥንካሬ ላይኖረው ይችላል። ለማንኛውም አብዛዎች ኢትዮጵያውያን የአሜሪካን ዶላር ወይም ኦይሮ ልዩ ዐይነት ምስጢር ያላቸው ይመስል ዶላር ከሌለን ኢኮኖሚውን ማሳደግ አንችልም በማለት አገራችንን መቀመቅ ውስጥ ከተዋታል። በዚህም ምክንያት የተነሳ በተለይም የተወሰነው የህብረተሰብ ክፍል በአገራችን ገንዘብ ላይ አመኔታ እንዳይኖረው ለመደረግ በቅቷል። ያም ተባለ ይህ አንድ አገር ኢኮኖሚዋን ስርዓት ባለው መልክ ማሳደግ የምትችለው በራሷ ገንዘብና ይህንን በክሬዲት መልክ የትናንሽና የማዕከለኛ ኢንዱስትሪ ለመትከል ለሚፈልጉ ዝቅ ባለ ወለድና ከረጅም ጊዜ አንፃር መክፈል እንዲቻል አስፈላጊው ሁኔታ ሲዘጋጅ ብቻ ነው። በተለይም በአገር ውስጥ በብዛት የሚሽከረከረው ገንዝብ ወይም በየቤቱ ውስጥ የተቀመጠው ወደ ባንኩ ዘርፍ ሊመጣ የሚችልበትን ሁኔታ መፍጠር አስፈላጊ ነው። ገንዘብ ያላቸው ቤት ከማስቀመጥ ወይም ደግሞ ዝምብለው ለቅንጦት ዕቃዎች ከሚያወጡ ባንኮች ውስጥ ቢያስቀምጡ ወለድ ስለሚያገኙና ተጠቃሚም ስለሚሆኑ በቂ ገቢ የሚያገኘው ወይም ደግሞ በንግድ አማካይነት ብዙ ትርፍ የሚያገኝ የተወሰነውን ባንክ ውስጥ ቢያስቀምጥ ይህ ሁሉ በብድር መልክ ለመዋዕለ-ነዋይ ለሚያውሉ ኢንቨስተሮች በብድር መልክ ሊሰጥ ይችላል። ይህ ሁሉ ነገር ተግባራዊ ሊሆን የሚችለው ግን ይህ ዐይነቱ ሰይጣናዊ የአቢይ አገዛዝና ግብረአበሮቹ ከስልጣን ሲወገዱ ብቻ ነው።

የየአገሮችን የኢኮኖሚ ዕድገት፣ የከተማ ግንባታዎችን፣ የበባሩ ሃዲድ ስራዎችንና ማስፋፋትን ታሪክ ስንመለከት በጊዜው የዓለም ገበያ የሚባል ነገር በሌለበትና ለንግድ መገበያያ የሚሆን አንድ ተቀባይነት ያለው ገንዝበ ባልተፈጠረበት ዘመን በተለይም የካፒታሊስት አገሮች ቀስ በቀስ የየራሳቸውን የወረቀት ገንዘብ በማተምና የጀርባ አጥንት ወርቅ እንዲሆን በማድረግና ወደ ውስጥ ባስፋፉት የክሬዲት ሲይስተም ነው ስርዓት ያለው የኢንዱስትሪ ፖለቲካ ማካሄድ የቻሉት። ችግሩ ግን የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም አሸናፊ እየሆነና የበላይነትን የመቻል ዕድሉ  እያየለ ሲመጣና  ሲታየው በብሬተን ውድስ ላይ በኬይንስና በኋይት፣ በእንግሊዙና በአሜሪካኑ ተወካዮች መሀከል በተደረገው ክርክር የኬንይስ አስተሳሰብ በምንም ዐይነት የአንድ አገር ከረንሲ የዓለም የንግድ የመገበያያና የሪዘርብ ከረንሲ እንዳይሆን ነበር አጥብቆ የተከራከረው። ምክንያቱም የአንድ አገር ከረንሲ በዓለም አቀፍ ደረጃ ብቸኛው የመገበያያና የሪዘርብ ከረንሲ ከሆነ አንድ አገር ያለውን የበላይነት በመጠቀም የየአገሮችን ዕድገት ያደናቅፋል የሚል ነው። በኬይንስ ዕምነትም ከማንኛውም አገር ቁጥጥር ውጭ የሆነ አርቲፊሻል ከረንሲ ባንኮር ብሎ የሚጠራው ጠንካራ ኢኮኖሚ ባላቸው አገሮች የሚደገፍ ገንዘብ የመገበያያና የሪዘርብ ከረንሲ ቢሆን ሌሎች አገሮችም የማደግ ዕድል አላችው የሚል ነው። ይህ እንዳይሆን የፈለገው የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም የግዴታ ዶላር ብቸኛው የመገበያያና የሪዘርብ ከረንሲ እንዲሆን አስገደደ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ፣ በተለይም የኒዎ-ሊበራል የነጻ ገበያ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ከ1980ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ በማታለልና በማስገደድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ እንዲሆን ከተደረገ ጀምሮ በተቋም ፖሊሲ(Structural Adjustment Programs) አማካይነት በተለይም አንዳንድ የአፍሪካ አገሮች፣ ለምሳሌ እንደጋና፣ የኋላ ኋላ ደግሞ ህወሃት ስልጣን ከያዘ ጊዜ ጀምሮ ገንዘባቸውን ከዶላር ጋር ሲነፃፀር እንዲቀንሱ(Devaluation) ተገደዱ። በዓለም የገነዝብ ድርጅት(IMF) እንደ ኢትዮጵያ ያለች አገር ኢኮኖሚዋ በጣም ደካማ ስለሆነ ገንዘቡም ከዶላር ጋር ሲነፃፀር ዋጋው ከፍ (Overvalued) ያለ ስለሆነ የገንዘቡ ዋጋ ቢቀንስ ወደ ውጭ የሚላከው ምርት የበለጠ ገዢ ያገኛል የሚል ተራ ሎጂክና በአብዛኛውም ጊዜ በተለይም የጥሬ-ሀብት እያመረቱ ሳይፈበረክ ወደ ውጭ ለሚልኩ አገሮች የማይሰራ የኢኮኖሚ ሎጂክ ነው። ታዲያ ይህንን ለመረዳት የማይፈልጉ የአገራችን ኢኮኖሚስቶችና አገዛዞች የኢትዮጵያን ገንዘብ ቢያንስ ከአምስት ጊዜ በላይ በሚበልጥ ከዶላር ጋር ሲወዳደር እንዲቀንስ በማድረግ የዋጋ ንረት እንዲፈጠርና የአገራችንም ኢኮኖሚ ስርዓት ባለውና በተስተካከለ መንገድ እንዳያድግ ለማድረግ በቅተዋል። ይህ ሁኔታ ደግሞ የጥቁር ገበያ እንዲስፋፋ አስችሎታል። የአገዛዙ ሰዎችም በጥቁር ገበያ ላይ በመሰማራት አንድ ዶላር ማዕከላዊ ባንኩ ከደነገገው በላይ በኢትዮጵያ ብር በመመንዘር የኢትዮጵያ ብር በከፍተኛ ደረጃ የመግዛት ኃይሉ እንዲቀንስ ለማድረግ በቅተዋል። ይህ ጉዳይ በታወቁ የአፍሪካ ኢኮኖሚስቶችም የተተቸና ለምን የኢትዮጵያ የማዕከላዊ ባንክ ሰዎች ፋንታዚ የላቸውም? በማለት ትዝብት ውስጥ ያስገባን ጉዳይ ነው።

ይህ ሁሉ ጉዳይ የሚያያዘው የቱን ያህል አገራችን ነፃ እንዳልሆነችና በራሱ የማሰብ ኃይልም ለመንቀሳቀስ የሚችል አገዛዝና ኢኮኖሚስቶች እንደሌላት ነው። የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚ የሚባለውም በዚህ መልክ ነው አገሮችን የባስ ዕዳ ውስጥ የከተታቸውና የሚከታቸው። ስለሆነም ኢትዮጵያ በውጭ ንግዷ በፍጹም አልተሻሻለችም፤ የንግድ ሚዛኑም በከፍተኛ ደረጃ ተናግቷል። ይህም ማለት ወደ ውጭ ከምትልከው ይልቅ ወደ አገር ቤት ውስጥ የምታስገባው ልዩ ልዩ ዐይነት ምርቶች በብዙ እጅ እጥፍ ይበልጣሉ ማለት ነው። ወደ አገር ውስጥ ከሚገቡት ዕቃዎች ደግሞ የቅንጦት ዕቃዎች፣ ለምሳሌ በጣም ውድ የሆኑ መኪናዎች፣ ልብሶች፣ ጌጣጌቶችና በጣም ውድ የሆኑ መጠጦች፣ እንደውስኪ፣ ሻምፓኝና ኮኛክ ‹የመሳሰሉት ይገኙበታል። እነዚህ የቅንጦት ዕቃዎች ደግሞ ለኢንዱስትሪ ተከላ የሚያስፈልጉ ማሽኖችንና ሌሎች የመለዋወጫ ዕቃዎችን መግዢያ ገንዘብ ስለሚጋሩ የግዴታ የውስጥ ገበያው በጥራትም ሆነ በብዛት እንዳያድግና መልክ እንዳይዝ አድርጎታል።  ይህ ብቻ ሳይሆን አገሪቱ ወደ ውጭ ከምትልከው የጥሬ ሀብቶች በቂ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ስለማትችል የግዴታ በተደጋጋሚ ዕዳ ውስጥ እንድትዘፍቅ ለመገደድ ችላለች።

ለማንኛውም የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም በኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚክ ፖሊሲ አማካይነት አገራችን በዕዳ እንድትተበተብና  የውጭ ንግድ ሚዛኑም በከፍተኛ ደረጃ እንዲናጋ ካደረገና፣ ለወያኔም ሆነ ለአቢይ አገዛዝ ድጋፍ ከሰጠና ህዝባችንን ካደኸየና፣ ኢኮኖሚውም በሳይንስና በቴክኖሎጂ ተደግፎ እንዳይንቀሳቀስ ካደረገና ህዝባችንንም ካስጨረሰ በኋላ አሁን አሁን አሜሪካም ሆነ የተቀሩት የካፒታሊስት አገሮች የአማራውን ድምጽ እየሰሙ ነው የሚለው አነጋገር በፍጹም አይገባኝም። እንደዚህ ብሎ ሲጻፍ ደግሞ ፋኖዎችና በጠቅላላው የአማራው ህዝብ የሚያደርጉትን ቆራጥና ዕልክ አስጨራሽ ትግል እንደመናቅና ካለአሜሪካኖች ድጋፍ ውጤታማ ሊሆን አይችልም እንደማለት ነው። ይህ ዐይነቱ አባባል ህዝብን መናቅና መስደብ ነው። ሌላው መታወቅ ያለበት ጉዳይ የዲፕሎማሲ ትግል ብሎ ነገር የለም፤ ዲፕሎማሲ ሳይንስም አይደለም። አሜሪካም ሆነ ግብረአበሮቹ በዲፕሎማሲ የሚያምኑ አይደሉም። ዲፕሎማሲ ሲሉም የእኛን የበላይነት ተቀበል፤ እኛ የምንልህን ዝም ብለህ ስማና ተግባራዊ አድርግ ማለታቸው ነው። አሜሪካኖችም ሆነ የተቀረው የምዕራቡ ካፒታሊስት ዓለም በፖለቲካ አያምኑም። የእነሱ ፖለቲካ አሸባሪ ኃይሎችን ስልጣን ላይ እያወጡ አገር እንዲፈራርስና እሴትም እንዲበጣጥስ ማድረግ ነው። ስለሆነም የውጭው ፖለቲካ ዲፕሎማሲያዊ በሆነ መልክ መንቀሳቀስ ከጀመረ ወዲህ ነው የአማራው ትግል ተደማጭነት ማግኘት የቻለው የሚለው ይህ ዐይነቱ አባባል ሎጂክና ሳይንሳዊ መሰረት የሌለው ነው። የዓለም ፖለቲካ በሎጂክና በሳይንስም የሚንቀሳቀስ ሳይሆን ጉልበት ያለውና ማጭበርበር የሚችል ብቻ ነው ዓለምን እንደልቡ ለማሽከርከር  የሚችለው።  ዲፕሎማሲ የሚለው አባባል በእኛ ኢትዮጵያውያን መንፈስ ውስጥ ስለተቀረፀም በቀላሉ ከዚህ ዐይነቱ በሽታ መፈወስ በፍጹም አይቻልም።  ሌላው መታወቅ ያለበት ጉዳይ፣ እንበልና ፋኖዎችና የአማራው ልዩ ኃይል ግንባር የሚባሉት ስልጣን ላይ ቢወጡ የወያኔም ሆነ የአቢይ አህመድ አገዛዝ እስካሁን ድረስ ሲያራምዱ የነበረውን አገር አፍራሽ ፖለቲካና የኢኮኖሚ ፖሊሲ በዚያው ይቀጥሉበታል ወይ? ወይስ ይህንን ሁሉ በመቀልበስ አገራችንን በአዲስ መልክ ያዋቅራሉ? የኢኮኖሚው ፖሊሲ ጉዳይስ ከአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ተፅዕኖና ቁጥጥር ውጭ በመሆን ከድህነትና ከኋላ-ቀርነት የሚያላቅቅ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ይዋቀራል ወይ? ወይስ አሁንም እንደትላንትናው የኒዎ-ሊበራል  አገር አፍራሽና ህዝብን የሚያደኸይ የኢኮኖሚ ፖሊሲ በድሮው መልኩ ይቀጥላል?  ይህንን ጉዳይ ለዲፕሎማሲ ትግል የተመደቡት ሰዎችና ራሱ መስፍን አረጋም እንዲያብራሩልን እጠይቃቸዋለሁ። ከዚህ በተረፈ መስፍን አረጋ የሳይንስ ሰው እንደመሆኑ መጠን፣ እንደመሰለኝ ባልሳሳት ከፍዚክስ ጋር ግኑኝነት ያለው ይመስለኛል፣ ለምን ኃይለኛ ቃላት እንደሚጠቀም ወይም ዘለፋን እንደሚያስቀድም አይገባኝም። ይህ ዐይነቱ ዘለፋዊ አቀራረብ በምንም ዐይነት ለሳይንዊ ወይም ለፖለቲካል ዲስኮርስ የማያመችና ጊዜያችንንም በመዘላለፍ እንድናጠፋ የሚያደርገን ነው። እኛ ተማርን ከሚባሉ ሰዎች በተቻለ መጠን መቅረብ ያለበት ጽሁፍ ሳንይሳዊ ትንታኔ መሆን ያለበትና በአገራችን ምድር የሚታዩትን ችግሮች በሚገባ እያነበቡና የችግሮችን ምክንያቶ ከተረዱ በኋላ ተቀራራቢ የሆኑ መፍቴሆች ለመፈለግ የሚያስችል መሆን አለበት። የምስፍን አረጋን ጽህፍ ሳነብ ራሴም እንድፈራ አደረገኝ። ይህም ማለት እኛ የምናፈቅራቸውን ሰዎች ወይም እንደመሪዎቻችን የምንመካባቸውን ግለሰቦች በሳይንሱ መንገድም የተቸ ሁሉ የፍየል ወጠጤ ይዘፈንበታል እንደማለት ነው። ስለሆነም የምንጽፋቸውን ነገሮች በሙሉ የሰውየውን ፐርሰናሊቲ ሳይነኩ መጻፉ ራስንም ያስከብራል።

ለማንኛውም እኔ በበኩሌ ፋኖዎች የሚያደርጉትን የሞት የሽረት ትግል የምደግፍ ነኝ። ፈልገው ሳይሆን ተገደው ወደ ጦር ትግል ውስጥ እንደገቡም አውቃለሁ። ትግላቸውም ተገቢና የኦሮሞማው ዘራፊና አገር አፍራሽ ኃይል ከስልጣን ላይ መወገድ አለበት እላለሁ። ይህ ዐይነቱ ትግል ከአጠቃላዩ ሁኔታ ጋር መያያዝ አለበት የሚል ዕምነት አለኝ። አሜሪካኖችን እንደ አጋር አድርጎ መቁጠር ከፍተኛ የዋህነት ብቻ ሳይሆን ሰለ ዓለም ፖለቲካ አካሄድ በሚገባ አለመገንዘብ ነው የሚል ሳይንሳዊ ዕምነት አለኝ። ሌላው መነሳት ያለበት ጥያቄ ምን ዐይነት ኢትዮጵያን ነው የምንፈልገው? ብለን ራሳችንን መጠየቅ አለብን። ስለሆነም ፋኖዎች የሚያደርጉት ትግል ከፍተኛ ጥንቃቄ የተሞላበት መሆን አለበት። አሜሪካኖችን እንደ አጋር ከቆጠርን ጠቅላላው ትግል የውሃ ሽታ ይሆናል። እንቅስቃሴያቸው ሁሉ በፍጹም መታወቅ የለበትም። ስኬታማ የሆኑ የአንዳንድ አገሮችን ትግል የተከታተለና ያጠና ትግላቸውን በሚስጥር በመያዝ ብቻ ነው  የመጨረሻ መጨረሻ ባሸናፊነት በመውጣት ጠንካራ አገርና ኢኮኖሚ መገንባት የቻሉት። የዲፕሎማሲ ትግል ማካሄድ አለብን ብለው ወዲህና ወዲያ አላሉም። በተረፈ መልካም ግንዛቤ!!

ለተጨማሪ ማስረጃ ከታች የተቀመጠውን ድረ-ገጼን ተመልከቱ።

www.fekadubekele.com

ttps://www.youtube.com/watch?v=Tyff-Cc5w4E&t=51s

 

 

ጠቃሚና መነበብ ያለባቸው መጽሀፎች

  1. Alexander S. Kohanski; The Greek Mode of Thought in Western Philosophy, London & Toronto, 1983
  2. Albrecht Dihle; The Theory of will in Classical Antiquity, London, 1982
  3. Bade Onimode; A Political Economy of the African Crisis, London & New Jersey, 1991
  4. Basil Blackwell; The Rise and Decline of Western Liberalism, New York, 1984
  5. Binyamin Appelbaum; The Economists᾽ Hour; False Prophets, Free Markets, and the Fracture of Society, New York, 2019
  6. Bryan Magee; Philosophy and the real World, London, 1973
  7. Catherine Cowley; the Value of Money: Ethics and the World Finance, London 6 New York, 2006
  8. David S. Landes; The Unbounded Prometheus: Technological Change and Industrial Development in Western Europe from 1750 to the Present,
  9. David S. Landes; The Wealth and Poverty of Nations: Why Some are Rich and Some so Poor, New York & London, 1999
  10. A Brett; International Money and Capitalist Crisis: The Anatomy of Global Disintegration, London, 1983
  11. Erik Reinert; How Rich Countries Got Rich … and Why Poor Countries Stay Poor, London, 2007
  12. Frederick Soddy; Wealth, Virtual Wealth and Debt: The Solution of the Economic paradox, London, 1983
  13. Jacob Soll; Free market: The History of An Idea, New York, 2022
  14. Ludwig Edelstein; The Idea of Progress in Classical Antiquity, Baltimore, 1967
  15. Lionel Robbins; The Theory of Economic Policies in English Classical Political Economy, London,1965
  16. Morris Kline; Mathematics and the Search for Knowledge, New York, 1985
  17. Naomi Klein; The Shock Doctrine, London, 2007
  18. Nicholas Rescher; Process Metaphysics; An Introduction to Process Philosophy, USA, 1996
  19. Paul Mason; Post capitalism: A Guide to our future, UK, 2015
  20. Robert Kuttner; Can Democracy Survive Global Capitalism? New York 2018
  21. Stjepan G. MeŠtroviċ; The Barbarian Temperament: Toward a postmodern critical theory, London 6 New York, 1993
  22. Stuart Corbridge; Capitalist World Development: A Critic of Radical Development Geography, New Jersey, 1986
  23. K. Seung; Plato Rediscovered; Human Value and Social Order, USA, 1996
  24. Tom Burgis; The Looting Machine; Warlords, Tycoons, Smugglers, and the Systematic theft of Africa`s Wealth, London, 2016
  25. Vivian Walsh & Harvey Gram; Classical and Neoclassical Theories of General Equilibrium, New York, 1980
  26. Waltenegus Dargie; The Reason for Life, London & New York, 2018

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ¹⁵ የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ ፥ ¹⁶ ተራራዎችንና   በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን ፤ ¹⁷ ታላቁ የቁጣው ቀን  መጥቶአልና ፥ ማንስ ሊቆም ይችላል ? አሉአቸው ። ራእይ 6 ፤  15_17 ይኽ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ። የኢየሱስን ልደት ሰናከብር የየሐንስ ራእይን ማንበብ ጠቃሚ ይመስለኛል ። ምክንያቱም በመጨረሻው ዘመን

ከኢየሱስ የፍርድ ቀን በፊት በህሊናችን ውስጥ ፍቅርን ለማንገስ እንጣር 

የምጣኔ ሀብታዊ ፍጥ፣ የፖለቲካ፣ የእውነትና የሰብአዊ መብት ታጋይ፣ የአመኑበትን ነገር ለመናገር እንደ ፖለቲከኛ በቃላት ሳያሽሞነሙኑ ቀጥታ የሚናገሩት የሀገሬ ኢትዮጵያ ታላቅ ሰው ነበሩ “ዘር ቆጠራውን ተዉት፤ የአባቶቻችሁን ሀገር ኢትዮጵያን አክብሩ!”  አቶ ቡልቻ ደመቅሳ

ሀገር ወዳዱ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ

January 6, 2025
ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። ) “ገብርዬ ነበረ

ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ?

January 3, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ዛሬ እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር ጥር 1ቀን 2025 ዓ/ም ነው ። አውሮፓውያኑ አዲስ ዓመትን “ሀ” ብለው ጀምረዋል ። አዲሱን ዓመት ሲጀምሩም ከልክ ባለፈ ፈንጠዚያ ነው ። ርቺቱ ፣ ምጉቡና መጠጡ

ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። )

Go toTop