በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com
እንኳን ኢትዮጵያውያን ዓለም እንደሚያውቀው የአምስት ሺ ዘመኑ የኢትዮጵያ ታሪክ የፋኖ የነፃነት ተጋድሎ ታሪክ ነው፡፡ የፋኖ የነፃነት ታሪክ የጀመረው ዛሬ ብቸኛ የሆነው የአፍሪካ የግዕዝ ፊደል በቅኝ ገዥዎች የላቲን ፊደል በመፋቅ ላይ ባለበት ዘመን ብቻ እንዳልሆነ የታወቀ ነው፡፡
ታሪክ እንደሚያስተምረው አውሮጳውያን አፍሪካን የተቆጣጠሩት በነፍጥ ሳይሆን ከአምስት ያልበለጡ “ሰባኪዎች” በየአገሩ እየላኩ ፊደላቸውን፣ የውሸት ሃይማኖትና ባህላቸውን እየጋቱ እንደነበር እንደ ቹኒያ አቼቤ ያሉ ጸሐፊዎች በታሪክ ቀመስ መጻሕፍቶቻቸው እንዳስተማሩ አንብቦ መረዳት ነው፡፡* የራሱ ያልሆነውን ፊደል፣ ሃይማኖትና ባህል የተጋተ ደግሞ ጋቺዎቹን ወይም ጌቶቹን ለመምሰል ቢጥርም አምላክ እነሱን አርጎ ስላልፈጠረውና እነሱን መሆን ስለማይችል ምርጫው እስከ ዳግም ምጣት የአካል ወይም የመንፈስ ባርያ መሆን ብቻ ነው፡፡
ቅኝ ገዥዎች ኢትዮጵያንም በተመሳሳይ መንገድ ቅኝ ተገዥ ለማድረግ ሰላዮችን ሰባኪ ወይም አማካሪ እያስመሰሉ በተለያዬ ጊዜ ልከው ነበር፡፡ የሩቁን ትተን የቅርቡን እንኳ ብናስታውስ ፋኖው አጤ ቴዎድሮስ በግዞት ያስቀመጣቸው ሰላዮች ለቅኝ ግዛት ዓለማ የተላኩ ነበሩ፡፡ ቅኝ ገዥዎች ኢትዮጵያን እንደ ሌሎች አገሮች በፊደል፣ በሃይማኖትም ሆነ በባህል ሰባኪዎች ቅኝ መግዛት ያልቻሉት ኢትዮጵያ ከእነሱ የበለጠ የረቀቀና ያማረ ፊደል፣ የቀን አቆጣጠር፣ ሃይማኖትና ባህል ስላላትና የዚህ መንፈሳዊ ሐብት ጠባቂቆች በተለይም ፋኖ የሆኑ ሼሆች፣ የቤተክርስትያን ሊቃውንት፣ ጳጳሳት፣ መነኩሳት፣ ቀሳውስትና ሊቃውንት ሕዝባቸውን በማንቃትና ለቅኝ ገዥ “ሰባኪዎች”ን ድባቅ የሚመታ መልስ በቃለም በጽሑፍም በመስጠት ነበር፡፡ ተቅርቦቹ ፋኖ ሊቃውንት አንዱን ብንጠቅስ አርበኛው ሊቀ ሊቃውንት መላከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ለእነዚህ ሳያምኑ ሰባኪ ለሆኑ ቅኝ ገዥዎች “ኮኮሐ ሃይማኖትና” መድሎተ አሚን” የሚባሉ ተነበው የማይጠገቡ መጻሕፍት ጽፈው ማሳፈር ብቻ ሳይሆን ጥልቅ ትምህርት እንደሰጧቸው ሥራቸው ምስክር ነው፡፡
ቅኝ ገዥዎች ካለነፍጥ ኢትዮጵያን በሰባኪዎች ቅኝ ለማድረግ የነበራቸው ተስፋ ሲሟጠጥ በነፍጥ ቅኝ ለማድረግ በተለያዬ ጊዜ ሞከሩ፡፡ በሌላ አነጋገር በመንፈሳዊ ኃይል ድባቅ ሲመቱ በአካላዊ ኃይል ኢትዮጵያ ለማንበርከክ ደጋግመው ሞክሩ፡፡የቅደም አያቶቻችን ታሪክ እንደሚመሰክረው መንፈሱ ፋኖ የሆነ ሰው አካሉም ፋኖ ነው፡፡ የመንፈስ ፋኖነት የሚገነባው የራስ የሆነ መንፈሳዊ ሐብት ሲኖር ነው፡፡ የኢትዮጵያ ፊደላት፣ ቋንቋዎች፣ የቀን አቆጣጠር ቀመር፣ ሃይማኖቶችና ባህሎች መንፈሳዊ ሐብት ናቸው፡፡ በምጣኔ ሐብት ሊበለጥግ ቢችልም የራሱ መንፈስ የሌለው ሕዝብ በፋኖነት ወይም በነፃነት ኮርቶ ይኖራል ተብሎ የማይታሰብ ነው፡፡ የደቡብ አፍሪካ ሕዝብ ዛሬ የአካል ነፃነት አለው የሚባል ነው! በመንፈስ ግን ዛሬም የሌሎችን ፊደል፣ የቀን አቆጣር፣ ቋንቋ፣ ባህልና አመጋገብ የሚጠቀም ነው፡፡ በእነዚህና በሌሎች መንፈሳዊ ሐብቶች የተወረረ ሕዝብ አንገቱን ቀና አርጎ በሙሉ ልብ የሚራመድበት ዘመን ይመጣል ማለት ዘበት ነው፡፡
እንኳን ኢትዮጵያ ውስጥ ከውጪ የተወለዱት የኢትዮጵያ ልጆች ሳይቀር አንገታቸውን እንደ ከንች ቀጥ አርገውና ደረታቸውን እንደ ጋሻ ነፍተው እምቢኝ እንዳለ ፋኖ አየተጎማለሉ የሚሄዱት ከኢትዮጵያ አርሶ አደር፣ የቤተክርስትያን ሊቃውንት፣ ሼሆች፣ ጳጳሳት፣ መነኮሳት፣ ቀሳውስት፣ ዲያቆናት፣ ነጋዴዎች፣ ወጣቶች፣ አዛውንት፣ ወይዛዝርት፣ ሌሎችም የሕብረተስብ ክፍሎች በወጡ ፋኖዎች ታጋድሎ በተጠበቀው የመንፈሳዊ ሐብት ነው፡፡ አለዚያማ የግዕዝ ፊደልን ተፍተህ የላቲን ፊደልን ስትጋት ፈልገህ ቅኝ ተገዥነንትን ወይም ባርነትን መረጥክ እንጅ ነፃነትህ ከምኑ ላይ ነው? የራስህን የቀን አቆጣጠር ትተህ በሌሎች መቁጠር ስትጀምር ሰተት ብለህ ለጌቶች በባርነት ሰገድክ እንጅ ክብርህ ከምኑ ላይ ነው? በተመሳሳይ መንገድ ባህልና እምነት ከቤትህ ሞልቶ ተርፎ ከሌሎች ጉርሻ ለማግኘት እንደ ውሻ ከተልከሰከስክ እምነትና ማተብህ ከምኑ ላይ ነው?
የነፃነት ትርጉም የገባው እንደሚረዳው ከፊሉ የኢትዮጵያ ግዛትና ሕዝብ በእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ከወደቀ ከሰላሳ ዓመታት በላይ ሆነው፡፡ በእዚህ በእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ከወደቀው የኢትዮጵያ ክፍል ነፃነቷን ጠብቋት የኖረው ፋኖአዊ መንፈሳዊ ሐብቷ እየጠፋ ነው፡፡ የዘፈን ዳርዳርታው እስክስታ ነው እንደሚባለው ፊደሏን፣ ቋንቋዋን፣ ባህሏንና ሃይማኖቷን የቅኝ ገዥዎች መንፈሳዊ ሐብት እየተካ ለቅኝ ተገዥነት እያመቻቸን ነው፡፡ በሃይል መክረው ያልተሳካላቸው ቅኝ ገዥዎችና ወራሪዎች እንደ ሌሎች አፍሪካዊ አገሮች አንገታችንን አቀርቅረን የምንሄድ የመንፈሳዊ ሐብት ባርያዎች ሊያደርጉን እየተጉ ነው፡፡ በየትኛውም ዓለም ወደር የሌላቸው የስብእና፣ የሽምግልና፣ የቃል አክባሪነት፣ የእርቅና የይቅርታ ባህሎቻችን በእሬሳ ጎታች አውሬኣዊነት፣ በወስላታ ኤፍሬም ይሳቃዊ አስታራቂነት፣ በሚዘገንን ቃላ አባይነት፣ በቁማርተኛ እርቅ፣ በወለወልዳ ይቅር ባይነትና ጭልጥ ባለ የማያባራ ክህደት እየተተኩ ነው፡፡ መንፈሳዊ ሐብቱን ያጣ ሕዝብ ደሞ ለባርነት ተንበርካኪ እንደሆነ በባርነት በኖሩት በርካታ አገሮች የታዬ ነው፡፡ ስለዚህ ራሱም ሆነ ልጅ የልጆቹን በባርነት ቀንበር ለለማሳነቀ የሚፈልግ ሁሉ በፋኖ የነፃነት መንፈስ እንደገና የመጠመቂያ ጌዜው ነገ ሳይሆን ዛሬ ነው፡፡
ከጥንት ጀምሮ ነፃነት አደጋ ውስጥ በገባበት ጊዜ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚከፈለው ፋኖና ባንዳ ተብሎ በሁለት ብቻ ነው፡፡ ተመሐል ሆኖ ዝም ብሎ እንደ አሳማ ሲዝቅ ኖሮ ለመሞት የቆረጠ ሁሉ በተዘዋዋሪ ባርነትን የመረጠ ባንዳ ነው፡፡ ፋኖነት የነፃነት መንፈስ ስለሆነ እንኳን ተምድር እየኖሩ ተማርስ እየኖሩም የሚተገበር ቅዱስ ምግባር ነው፡፡ እያረሱ፣ ከበት እየጠበቁ፣ እየተማሩ፣ እያስተማሩ፣ እየነገዱ፣ ቤተክርስትያን እየቀደሱ፣ መስጊድ እየሰገዱ፣ መስሪያ ቤት እየሰሩ፣ ኩሽና ወጥ እየሰሩ፣ ውሀ እየቀዱ፣ ክክ እየከኩ፣ ኩበት እየለቀሙ፣ እየጰጰሱ፣ ሺህ እየሆኑ፤ እየቀሰሱ፣ እየደቆኑ፣ እየመነኮሱ ወዘተፈ ሁሉ ፋኖ መሆን የሚቻል ነው፡፡ ቅድመ አያቶቻችን ይኸንን ስለማድረጋቸው ትተውን ያለፉት ተዝቆ የማያልቅ አካላዊና መንፈሳዊ ሕብት ምስክር ነው፡፡ የደብረ ሊባኖስ ገዳም ፋኖ መነኮሳት መጽሐፍ መነኮሳት “ሰይጣንን መር ብለህ ቁንጮን ያዘው**” ብሎ ባዘዘው መሰረት መውዚር አንግተውና ዝናር ታጥቀው መር በማለት የሰይጣኑን ፋሽሽት ቁንጮ ይዘው እንዳስጎሩት ታሪክ ምስክር ነው፡፡ ቅድመ አያት አጥንትና ደሙን ገብሮ ያስረከበን የመንፈሳዊና ቁሳዊ ሐበት አለመጠበቅ በምድርም በሰማይም የሚያስጠይቅ ዕፀጽ ነው፡፡
የዛሬው ከአምስቱ ዘመን ሆነ ከዚያ በፊት ከነበረው ይከፋል! አሁን የደረሰብን የነፃነት አደጋ ከበፊቱ ሁሉ የከፋ መሆኑን በአይኗ ብብረቷ ያየነው ቢሆንም የታሪክ ምሁሩ ፕሮፌሰር ሃይሌ ላሬቦም ደጋግመው ተናግረውታል፡፡ በቅርቡ ባደረጉት ቃለ ምልልስም ለዚሁ አጽንኦት ሰጥተውና ፋኖን እንደ መሲህ ቆጥረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ፋኖን እንዲደገፍ ፋኖም አድማሱን ኣስፍቶ መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ አቅፎ ይኸንን ከመቼውም ጊዜ የከፋ አደጋ እንዲያስወግድ ተማፅነዋል*፡፡
ከበፊቱም የክፋ ነፃነት አደጋ ላይ ሲሆን ደሞ ተሁሉም ኢትዮጵያዊ ፋኖነት ይጠበቃል፡፡ ነፃነት አደጋ ላይ ሲወድቅና ሰይጣን ሲወር እንደ አምስቱ ዘመን እንኳን የሰው ልጅ ወንዙ፣ ጋራው፣ ሜዳው፣ ሸለቆው፣ ሸንተረሩ፣ የቀንድ ከብቱና የየጋማ ከብቱም ፋኖ ይሆናል፡፡ ሬዲዮኑና ተሌቪዥኑ፣ ጋራውና ሽንተረሩ ሁሉ የነፃነት አውታር የሆኑትን ቀረርቶና ፉከራ ሌተ ተቀን ሳይታክት ያስተጋባል፡፡ ከመቼው ጊዜ የበለጠ አገርና ነፃነት አደጋ ላይ ሲወድቁ ፋኖን የሚቃወም ወይም የማይደግፍ ከነፃነት ባርነትን የመረጠ ባንዳ ተብሎ በምድር በተከታታይ ትውልድ በሰማይም በመለኮት ሲረገምና ሲኮነን እስከ ዘላለም ይኖራል፡፡
ፋኖነት የእምነት ጥንካሬ፣ የቃል ኪዳን ፅናት፣ የነፃነት መሰረት፣ የፍትህ ምንጭና የመንፈስ ልእልና ቁንጮ ነው፡፡ እግዚአብሔር የኢትዮጵያንን ሕዝብ ከፋኖነት መንፍሰ ከመራቅ ያድነው፡፡ አመሰግናለሁ፡፡
ዋቢ፡-
* Books of Chinua Achebe: Things Fall Apart, No longer at Ease, There Was A Country etc
** ማር ይስሃቅ ገፅ 106፡ እግዚአብሔር ሳንፈራ ሳንበርድ ጸላታችንን (ሰይጣንን ማለቱ ነው) እንገጥመው ዘንድ ያዝዛልና ሳይቀድምህ ቅደመው…ትወጋው ዘንድ መር ብለህ ቁንጮውን ያዘው”
***ኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትሩ እንደሚሉት አዲስ “የጋራ ትርክት” አያስፈልጋትም–የታሪክ ምሁሩ ፕሮፈሰር ሃይሌ ላሬቦ – (amharic-zehabesha.com)
ህዳር ሁለት ሺ አስራ ስድስት ዓ.ም.