ከገዛ ራሳችን ግዙፍና መሪር እውነታ እየሸሸን ሃይማኖትን መደበቂያ የማድረጉ አስቀያሚ እኛነታችን ይብቃን!

November 23, 2023

ጠገናው ጎሹ

እንደ ሰው በሰላም ለመወለድ ፣ ለማደግ፣ ለመኖር ፣ ለመማር እና የእውቀትና የክህሎት ባለቤቶች ለመሆን እድሉ ቢሰጣቸው እንኳንስ አንድ ወይም ሁለት ወይም ሦስት ቤተ ርስቲያን ወይም ገዳም ወይም መስጊድ መላ አገራቸውን የወርቃማ ህይወት ወይም አኗኗር ባለቤት ሊያደርጉ የሚችሉ አያሌ ሚሊዮን እምቦቃቅላዎች (ህፃናትና ታዳጊዎች) የገዛ አገራቸው ምድረ ሲኦል ስትሆንባቸው አያሌ ሚሊዮን ንፁሃን ዜጎች በገዛ አገራቸውና ቀያቸው መፈጠርን (ሰው መሆንን)  የሚያስጠላ ወይም “ምነው ሰው ሆነን ባልተፈጠርን” የሚያሰኝ  እጅግ መሪር ፈተና ሲያ ጥማቸው አያሌ ሚሊዮን አማኞች በባለጌና ጨካኝ የጎሳ አጥንት  ስሌት ፖለቲካ ሥርዓት ዘዋሪዎች እና በአድርባይ (በምንደኛ) የሃይማኖት መሪዎች ተብየዎች እጅግ  አስቀያሚ መተሻሸት ግራ የሚያጋባ ብቻ ሳይሆን በእጅጉ ልብን የሚሰብር ሲሆንባቸው  ፣  የሃይማኖት አገልጋዮችና ተከታዮች ፈጣሪን የሚማፀኑባቸው ቤተ እምነቶችና አንጡራ (መተኪያ የሌላቸው)  ህይውቶቻቸው (ህልውናዎቻቸው) የጨካኝ ገዥዎች ሰይፍ ዒላማዎች ሲሆኑባቸው

ህልውናን ከባለጌና ጨካኝ ገዥ ቡድኖች የመከላከልን እርምጃ  ለሁሉም ዜጎች የምትበጅ የጋራ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን  እውን  ከማድረግ ታሪካዊና የተቀደሰ ዓላማ ጋር ይዘው የተነሱና ለዚሁም ሊተካ የማይችለውን ህይወታቸውን ጨምሮ እጅግ ከፍተኛ መስዋእትነት በመክፈል ላይ የሚገኙትን ወገኖች የሚደግፍና የሚበረታታ ህብረተሰብ እንደ ወንጀለኛና ሃጢአተኛ ተቆጥሮ  የርካሽ ፕሮፓጋንዳና የጭካኔ ርምጃ ሰለባ ሲሆን እና ፣  በአጠቃላይ ትውልዳዊው የመከራና የውርደት ቸነፈር  ለማመን ቀርቶ ለማሰብም በሚከብድ ሁኔታ እየሰፋና እየከፋ ሲሄድ በእውነተኛ የአርበኝነት (ጊዜና ሁኔታ በማይሽረው የወገንንና የአገር አፍቃሪነት) ስሜት የሚከታተልና የሚገነዝብ የአገሬ ሰው  ከዚህ የበለጠ የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረትና ርብርብ የሚጠይቅ አገራዊ ጉዳይ እንደሌለና እንደማይኖር በፅዕኑ ያምናል የሚል ፅዕኑ እምነት አለኝ። አለመታደል ወይም የፈጣሪ ቁጣ ሆኖብን ሳይሆን ከየትኛውም ጊዜና ሁኔታ የከፋና የከረፋ የተረኛና ጨካኝ የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ሥርዓት ዘዋሪዎችን እንደ ማህበረሰብ ወይም እንደ ህዝብ የጋራ በሆነና በጋራ በሆነ የአንገዛም ባይነት ተጋድሎ በቃችሁ ለማለት ባለመቻላችን የመከራው ጊዜና አስከፊነት እየተራዘመ ነውና ከመቸውም ጊዜና ሁኔታ በበለጠ ሊያሳስበንና ሊያስቆጣን ይገባል።

አዎ! ምንም እንኳ ይበል (እሰየው) የሚያሰኝ በመላው አገርና ወገን ወዳድ ወገኖች (ዜጎች) የተደገፈና የታገዘ እና የግፍ ፅዋ አስከፊነት የወለደው የአማራ ፈኖዎች ተጋድሎ እያየን መሆኑ እውነት ቢሆንም ይበልጥ የተራዘመ ጊዜን መውሰድ የሌለባቸውና በእጅጉ የተጠነከሩ እና ወደ ኋላ የማይመለሱ የትጥቅ ትግልሎችን ፣ የፖለቲካ ጥበቦችን  እና የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረቶችንና የጋራ ርብርብቦችን የሚጠይቁ  ሥራዎች እንዳሉብን ለአንዳፍታም መዘናጋት አይኖርብንም።

ለዚህ ነው በሃይማኖት ስም እየማሉና እየተገዘቱ ፈጣሪ “ከማነኛውም ቤተ መቅደስ በላይ ቤተ መቅደሴ ነው” የሚለው ህዝበ አዳምና ሔዋን  በባለጌና ጨካኝ ገዥ ቡድኖች እና በግብረ በላዎቻቸው ለመግለፅ በሚከብድ ሁኔታ እየፈረሰ (እየተደረመሰ)  ባለበት በዚህ መሪር እውነታ ወቅት በባህር ማዶ እንገነበዋለን ለሚሉት “ታሪካዊ” የቤተ ክርስቲያንና የገዳም  ፕሮጀክት “አያሌ ሚሊዮን ዶላር ካልሰጣችሁን የፅድቁ በር ይዘጋባችኋል ” ለሚል እጅግ የወረደና አዋራጅ  ዘመቻ ተውኔት የቀድሚያ ቅድሚያ ትኩረት ሰጥተው ሌት ተቀን ዶላር የሚለምኑትን (የሚሰበስቡትን) ወገኖች ቢያንስ በግልፅ ቋንቋ ነውር ነው ማለት ከተገቢም በላይ ተገቢ የሚሆነው።

አዎ! እየተነጋገርን ያለነው በእውነት ስለ እውነት ከሆነ ለተንቦረቀቀ የግልና የቡድን “ብልፅግና” ማሳለጫነት በሚገለገሉበት ማህበራዊ  ሚዲያ ህዝበ አማኙ ከሰው ሠራሽ (ከፖለቲካ ሠራሽ) መከራና ሰቆቃ ሰብሮ ይወጣ ዘንድ ታላቅ ሚና ያለውን ታላቁን መጽሐፍ (መጽሐፍ ቅዱስን) መሬት ላይ ከሆነውና እየሆነ ካለው ግዙፍና መሪር እውነታ ጋር ፈፅሞ በማይገናኝ አኳኋን እየጠቀሱና እያነበነቡ “ባህር ማዶ ቤተ ክርስቲያንና ገዳም ዛሬውኑ ካላሠራን የሲኦል እራቶች (ሰለባዎች) መሆናችን ነው” በሚል እጅግ ግልብና አሳሳች በሆነ እና መከራን ይበልጥ በሚያራዝም ዘመቻ ላይ የተጠመዱ ወገኖችን አሁንም አደብ ግዙ ማለት የግድ ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ሆድ ያባውን ብቅል ያወጣዋል - ከመርሐጽድቅ መኮንን አባይነህ

ሰሞኑን ከወደ ኳታር እየታዘብነው ያለውነው የሶሻል ሚዲያ ሽር ጉድ፣ መነባንብ፣ ዝማሬ፣ እልልታ ፣ የመጽሐፍ ቅዱስና የትውፊት ጥቅስ ጋጋታ፣ ግልብና የተሳከረ አዋቂዎችና ታዋቂዎች ነን ባይነት፣ ወዘተ የሚነግረን ቁም ነገር ቢኖር በገዛ ምድራችን (በገዛ አገራችን) ለዘመናት ከሆነውና እየሆነ ካለው እጅግ ግዙፍና መሪር እውነታ እየሸሸን ባህር ማዶ እናሠረዋለን በምንለው ቤተ ክርስቲያንና ገዳም ዘመቻ ስም የምናካሂደውን  እጅግ የተንሸዋረረ አስተሳሰባችንና አካሄዳችን ነው።

አሁንም የሰበብ ድሪቶ እየደረትን ከመሪሩ እውነታ ለመሸሽ ካልፈለግን በስተቀር ከተሰጣቸው ሃይማኖታዊ ሃላፊነትና ተልእኮ ከፍተኛነት አንፃር ሲገመገም ከሲኖዶሱ አባላት የሚጀምረው አስከፊና አስፈሪ ውድቀት ብዙ የሚያነጋግረን እየሆነ መጥቷል።መናገርና መነጋገርም አለብን።

ቀኖና እና ዶግማ እያሉ ሲሰብኩን (ሲያስተምሩን) የኖሩት የሃይማኖት መሪዎች ራሳቸው አፍርሰውና እያፈረሱ እረኞቻችሁ ነን ከሚሉን ጳጳሳትና ሊቀ ጳጳሳት መካከል አንዱ የሆኑት አቡነ ኤርምያስ ይህን ሰሞን የገቡበት እጅግ ከባድ ወለፈንዲነትና የተምታታ አስተሳሰብም (highly hypocritic and delusional way of thinking) የዚሁ አጠቃላይ ውድቀታችን አካል መሆኑን የማይረዳ ባለቅንና ሚዛናዊ ህሊና ባለቤት ወገን ከቶ የሚስተው (የሚያጣው) አይመስለኝም ።

ሁለት ፈፅሞ የሚቃረኑ እውነታዎችን ማለትም በአንድ በኩል ባለጌና ጨካኝ ገዥ ቡድኖችን (መንግሥት ተብየውን) እና በሌላ በኩል ደግሞ ከዘመን ጠገብ መከራና ውርደት ለመላቀቅ እልህ አስጨራሽ ተጋድሎ የሚያደርገውን ህዝብ (በፋኖ ሃይሎች የሚመራውን ተጋድሎ) የገለፁበትና ያስቀመጡበት ሁኔታ ከለበሱት ልብሰ ሊቀ ጳጳስ እና ከያዙት መስቀል በስተቀር የእውነተኝነት (የአርበኝነት ) የሃይማኖት መሪነትን ወይም የህዝብ እረኝነትን ፈፅሞ አያንፀባርቅም።

ይህ ቀጥተኛና ግልፅ ሂሳዊ አስተያየቴ የሚያስደነግጣቸው ወይም እግዚኦ የሚያሰኛቸው የዋህ አማኝ ወገኖች ቁጥር የትየለሌ እንደሚሆን በሚገባ እረዳለሁ ። ወደድንም ጠላንም መሬት ላይ ያለው ግዙፍና መሪር እውነታ ይኸው ነውና እውነተኛ ክርስቶሳዊያን ነን የምንል ከሆነ የሚሻለው ሃየገዛ ራሳችንን መሪር ሃቅ  መጋፈጥ እና  ዘወትር በውድቀት አዙሪት ውስጥ ከመጓጓጥ (ከመማቀቅ) የሚገላግለንን ሥራ መሥራት ነው እንጅ ሃላፊነቱንና ተልእኮውን ያልተወጣና የማይወጣ የሃይማኖት መሪ ለምን ይተቻል በሚል እግዚኦ ማለትና ሃጢአት ያልሆነውን ሃጢአት እያስመሰሉ ፈጣሪን ጨምሮ ኢምክንያታዊና ጨካኝ በትር የሚያነሳ ማስመሰል ፈፅሞ ትክክል አይደለም።

ሊቀ ጳጳሱ በብዙ የሚዲያ መስኮቶች ቀርበው “ትክክለኝነታቸውን” ለማፅናት ያደረጉት ጥረት ትዝብትን እንጅ አድናቆትን አላስገኘላቸውም። የፀፀትንና የይቅርታን ታላቅ ሰብአዊ እሴትነት አዘውትረው የሚሰብኩንን ያህል ባይሆንም እንኳ አንፃራዊ በሆነ የሞራል ከፍታ “አዎ! ልጆቼ አወንታዊ ንግግሬ እንደተጠበቀ ሆኖ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ ስህተቶችን በመሥራቴ መልካም አርአያነት ጎሎኛልና ይቅርታ እጠይቃችኋለሁ” የሚያሰኝ ወኔ የማጣታቸው ጉዳይ በእጅጉ ያሳዝናል። ማሳዘን ብቻ ሳይሆን በእጅጉ ያሳስባልም።

አሁንም ይህንን ለማለት የሚያስችል ወኔ አምጦ በመውለድ ይቅርታ ጠይቆ ስህተትን የማረም አርአያነት የሃይማኖት መሪዎች ባህሪና ተግባር መሆኑን ከማሳየት ይልቅ የሰበብ ድሪቶ እየደረቱ በተለመደው የአባትነት እሳቤ የሚቀጥሉ ከሆነ የሚያስከትለው  አሉታዊ ተፅዕኖ በእርሳቸውና በመሰሎቻቸው ብቻ ሳይሆን ታላቅና ታሪካዊ በምንለው ሃይማኖት ላይ ጭምር ነው የሚሆነው። ይህ ደግሞ ሃይማኖቴን አከብራለሁና እጠብቃለሁ ለሚል አማኝ ከባድ ፈተና ነው የሚሆነው።

በእውነት ስለ እውነት ከተነጋገርን ባለጌና ጨካኝ የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ሥርዓት ዘዋሪዎች (አራጊና ፈጣሪ ቡድኖች) በሥልጣነ መንበር ላይ እየተፈራረቁ አደንቁረው የገዙትና የሚገዙት አብዛኛው አማኝ ወገን ከፈጣሪ የተሰጠውን ረቂቅ የማሰቢያ አእምሮና ብቁ የማከናወኛ አካል እየተጠቀመ እና የፈጣሪውን እገዛ እየጠየቀ (እየተማፀነ) እንደሰው ሰው ሆኖ የሚኖርበትን ሥርዓተ ማህበረሰብ እውን እንዳያደርግ በሃይማኖት ስም የቅድሚያ  ቅድሚያ ትኩረቱንና የጋራ ርብርቡን ምስቅልቅሉን እያወጡበት ያሉትን ወገኖች ለምንና እንዴት ብሎ ለመጠየቅ ቢሳነው ያሳዝን እንደሆነ ከቶ አይገርምም።

አዎ! በአሁኑ ወቅት እያየነውና እየሰማነው ያለነው እጅግ አስቀያሚና አደገኛ ሁኔታ በአንድ በኩል  ከዘመን ዘመን እየተበላሸ የመጣውን የሃይማኖት መሪዎች  አድርባይነትና አስመስሎ የመኖር አስቀያሚ ባህሪ እና በሌላ በኩል ደግሞ የተረኛ ገዥ ቡድኖችን የጭካኔ አገዛዝ ሰይፍ በመሠረታዊ እውቀትና አቋም በተደገፈ  ማንነትና እንዴትነት ለመጋፈጥና በድል አድራጊነት ለመወጣት  ያለመቻላችን አካል (ውጤት) ነው። ይህንን መሪር እውነታ  አምነንና ተቀብለን ተገቢውን  አድርገን ለመገኘት ዝግጁዎችና ቁርጠኞች ሆነን እስካልተገኘን ድረስ የክስተቶችን የትኩሳት መጠን እየተከተልን በምናውጀው ፀሎት፣ ፆም፣ ምህላ (እግዚኦታ) ፣ ቅዳሴ፣ ዝማሬ፣ ቅኔ (ይህም በትክክል ከተደረገ ነው) የሚመጣ አንዳችም በጎ ለውጥ አይኖርም። ከዚህ እጅግ ፈታኝና አስቀያሚ የመሬት ላይ እውነታ የሚነሳ ግልፅና ቀጥተኛ ሃሳዊ አስተያየቴን የሃይማኖት አባትን እንደመዳፈርና የሃጢአት ወይም የሰይጣን  መንገድን እንደመምረጥ  የሚቆጥሩ ወገኖች ቁጥር የትየለሌ እንደሚሆን በሚገባ እገነዘባለሁ። ይህም ለምን? እንዴትና ወዴት? ብሎ ለመጠየቅ የሚያስችል መሠረታዊ እውቀት እንዳይኖረው  ከተደረገ (not well informed ) አማኝ  የሚጠበቅ ነውና አይገርምም። የሚገርመው ቢያንስ ፊደል ቆጠርኩ የሚለውም ከዚሁ  የአስተሳሰብ ጉድለት ሰብሮ በወጣ አማኝነትና ተከታይነት  ሃይማኖቱንና አገሩን ለመታደግ ትርጉም ያለው ሥራ ለመሥራት አለመቻሉ ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የኃይል መቋረጥ እያሰከተለ ያለው ቀውስ

የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረትንና ርብርብ የሚጠይቀውን እና ፈጣሪም የሚፈልገውን የአገርና የህዝብ ጉዳይ እንደሌለ ቆጥሮ “ባህር ማዶ ለምንሠራውና ለምናሠራው ድንቅና ታሪካዊ ቤተ ክርስቲያን ወይም ገዳም ዶላር ስጡን” የሚልንና እንቅልፍ የሚያሳጣን ዘመቻ የሚባርክ እውነተኛ አምላክ ሊኖር እንደማይችል ለማወቅ ነብይ ወይም የሃይማኖት ሊቀ ሊቃውንት መሆንን አይጠይቅም። የሚጠይቀው እውነተኛ (ክርስቶሳዊ) አማኝነትን፣ ቅንና አስተዋይ ህሊናን፣ ሚዛናዊና ትውልድ ተሻጋሪ የፖለቲካ ሰብእናን ፣ የሞራልና የሥነ ልቦና ልእልናን ፣ ተንቦርቃቂ (ልክ የሌለው) የግልና የቡድን ፍላጎትን የመቆጣጠር ፈቃደኝነትንና አቅምን ፣ ወዘተ ብቻ ነው። ይህንን እጅግ መሠረታዊና ጊዜ ሊሽረው የማይገባው እሴት  ነው እጅግ አብዛኛው ፊደል የቆጠረ የማህበረሰብ አካል የሳተውና እየሳተው ያለው።

 እናም፦

ይህ መከረኛ ህዝብ ከሚገኝበት እጅግ ግዙፍና መሪር ሁኔታ በሰብሮ ለመውጣት ይችል ዘንድ የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረትንና ርብርብን በሚቻለው መጠንና አይነት ሁሉ ከማገዝ  ይልቅ ፦

ሀ) ባህርና ውቅያኖስ እያቋረጡ በመብረር ይህንን ያህል ገንዘብ (ዶላርቀርቶናልና   ይህንኑ  ብታመጣ  (ብትሰጥየመንግሥተ  ሰማያት  መግቢያ  ቁልፍን   ትረከባለህ”  የሚሉትን  የሃይማኖት ተቆርቋሪ ተብየዎች  አደብ ግዙ ብሎ በግልፅና በቀጥታ ለመንገርና ለመነጋገር የሚቸገር አማኝ የስም ወይም የተለምዶ አማኝ እንጅ እውነተኛ ክርስቶሳዊ አማኝ ሊሆን ከቶ አይችልም። አዎ!  ይህ መከረኛ ህዝብ ከሁሉም የምትበልጡ ቤተ መቅደሶቸ  እናንተው ናችሁ  የሚል ታላቅ ቃል የተገባልንን  ሰብአዊ ፍጡራን   የግፍ ግድያና የቁም ሞት  ሰለባዎች እየሆን ባለንበት እጅግ ግዙፍና መሪር እውነታ ውስጥ  ለባህር እና ለውቅንያኖስ ማዶ ቤተ ክርስቲያን ወይም ገዳም መግዣ፣ ማሠሪያና ማስፋፊያ ካላመጣችሁ በረከትና ፅድቅ ቀረባችሁ  ማለት ፈፅሞ ትክክል እንዳልሆነ ለመረዳትና ለማሳወቅ እስካልቻለ ድረስ ሃይማኖትን ጨምሮ እውን ሊያደርገው የእውነተኛ ነፃነትና ፍትህ ሥርዓት አይኖርም።

በእንዲህ አይነት ፈፅሞ የቅድሚያ ትኩረትንና የጋራ ርብርብ የሚጠይቀውን ጉዳይ ወደ ጎን ትቶ የሚሠራ ቤተ ክርስቲያንና ገዳምን የሚባርክና ማደሪያው የሚያደርግ እውነተኛ አምላክ ፈፅሞ የለምና እነዚህ በሃይማኖት ስም ልክ የለሽ የግልና የቡድን ብልፅግና ቅዠታቸውን እውን ለማድረግ የሚታትሩትን ደካሞች በቃችሁ ማለት የፅድቅ እንጅ የመርገምት መንገድ አይደለም።

ለ) በሥልጣነ መንበሩ ላይ እየተፈራረቁ በህዝብ (በአገር) ላይ መግለፅ የሚያስቸግር የመከራና የውርደት ዶፍ ሲያወርዱ ከኖሩትና እያወረዱ ከቀጠሉት የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኛ ገዥ ቡድኖች ጋር እየተገለባበጡና እየተሻሹ እጅግ ታላላቅና ጊዜ የማይሽራቸው የሃይማኖታዊ እምነት እሴቶችን የሚያጎሳቁሉ የየትኛውም ሃይማኖት ተቋማት መሪዎችን ፣ ሊቃውንትን፣ ሰባኪዎችንና ባለሌላ ማእረግ አባላትን በግልፅና ገንቢ በሆነ አቀራረብ አደብ ግዙና የተጣለባችሁን የእረኝነት ሃላፊነትና ተልእኮ ተወጡ ማለት የእውነተኛ ክርስቶሳዊነት ባህሪና ሃላፊነት ነው።

ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ተጠቅሞ የትኛውንም ግለሰብ ወይም ቡድን የርካሽ ፖለቲካ ቁማሩ መሣሪያ የማድረግ ጉዳይ  ከዚህ መንግሥት ተብየ አካል  የማይጠበቅ ይመስል ሰሞኑን አቡነ ኤርምያስን መንግሥት እንዳሳሳታቸው አድርጎ ለመከላከል የተደረገውንና የሚደረገውን ጉንጭ አልፋ እመኑን ባይነት ቢያንስ በግልፅና በቀጥታ ነውር ነው ለማለት የሞራል አቅም ካጣን ስለየትኛው የተሟላ ነፃነት እንደምንናፍቅና እንደምንሰብክ ለመረዳት በእጅጉ ያስቸግራልና ዙሪያውን ከመዞር ሃቁን እናጋፈጥ። በነፍስም ሆነ በሥጋ የሚበጀን ይኸውና ይኸው ነውና ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ኑ! እንወቃቀስ-1 እንድ ጊዜ ጥንቃቄ! - ቴዎድሮስ ጌታቸው

የሊቀ ጳጳሱ አስቀያሚ ወለፈንዲነትን (ugly paradox) አባል ከሆኑበት ሲኖዶስ አስነዋሪና አሳሳቢ ውድቀት ነጥሎ ለማሳየት መሞከር እና እንኳንስ በሊቀ ጳጳሱ ደረጃ  ለማነኛውም አስተዋይና ሚዛናዊ ህሊና ላለው ተራ የአገሬ ሰው ግልፅና ግልፅ የሆነውን የአገራችን መሪር እውነታ ከእውቀት ማነስ እንደሆነ አድርጎ ለማሳመን መከጀል ከስህተት ላይ ስህተት መሆኑን በግልፅና በቀጥታ መንገርና መነጋገር የግድ ነው።

ሊቀ ጳጳሱ በህወትና በብልፅግና (ለሁለት በተሰነጠቀው ኢህአዴግ መካከል) በተካሄደው ጦርነት ጊዜ እዚያው ይኖሩበት ከነበረው ህዝብ ጋር መቆየታቸውና የሚችሉትን ማድረጋቸው ከአንድ የሃይማኖት መሪ የሚጠበቅ አነስተኛው ሃላፊነትና ተልእኮ ሆኖ ሳለ  በአግባቡ እውቅና ከመስጠትና ከማበረታት አልፎ የሰማእትነት ገድል እንደፈፀሙ አድርጎ መለጠጥ የሚነግረን ቁም ነገር ቢኖር   የሃይማኖት መሪን ጨምሮ የትኛውም በሃላፊነት ላይ የተቀመጠን ሰው ወይም አካል እንደ አማኝ ወይም እንደ ተከታይ ለምንና እንዴት ብሎ ለመጠየቅ ያለመቻላችን ደካማነት የሚያስከትለውን አሉታዊ ውጤት ነውና ከምር ራሳችንን መጠየቅ እንደሚያሻን ነው። አዎ! በአግባቡ አካፋን አካፋ ማለትን ( to call as it is) ለአባቶች እንደማይሠራ ብቻ ሳይሆን ሃጢአት እንደሆነ አድርጎ ለማሳመን መሞከር ለሰማያዊውም ሆነ ለምድራዊው ዓለም ፈፅሞ አይበጅምና ለሃይማኖት መሪዎችም ይህንኑ በግልፅና በአግባቡ መንገር ወይም ማሳወቅ የአስፈላጊ ነው።

በአጠቃላይ ከዘመን ጠገቡና በእጅጉ አስከፊና አስፈሪ እየሆነ ከሄደው የገዛ ራሳችን የውድቀት ወይም የቀውስ አዙሪት ሰብረን መውጣት ካለብን በዴሞክራሲ ስም ወንጀል የሚፈፅመውን የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ሥርዓትን እና ሃይማኖታዊ ሃላፊነታቸውንና ተልእኳቸውን በአግባቡ ከመወጣት ይልቅ ከገዥዎች ጋር እየተሻሹ እጅግ ታላቅ የሆነውን ሃይማኖታዊ እሴት በእጅጉ ፈተና ውስጥ የጣሉትን የሃይማኖት መሪዎችና  ወገኖች  በግልፅ፣ በቀጥታና በአግባቡ በቃችሁ ማለት የግድ ነው።

ለዚህ ደግሞ በአሁኑ ወቅት እየተካሄደ ያለውን እና በአንፃራዊነት ከየትኛውም ጊዜ የተሻለ ትርጉም ባለው ሁኔታና ሁሉንም ነፃነትና ፍትህ ፈላጊ ኢትዮጵያዊ በማያገል አኳኋን እየተካሄደ ያለውን የፋኖ ተጋድሎ ይበልጥ አሳማኝና አገራዊ የማድረጉ ጉዳይ ልዩ ትኩረትንና የጋራ ርብርብን የሚጠይቅ መሆኑን አምኖ ወደ ፊት መራመድን ይጠይቃል።

ሰላምን የማይፈልግ እና ጦርነት የሚወድ ባለጤናማ ህሊና ሰው ያለ ይመስል ደምሳሳ የሆነ የሰላም ሰባኪነትና የጦርነት አውጋዥነት ዲስኩር  ከቶ የትም አያደርሰንምና  እውነተኛና ዘላቂ ሰላም እንዴትና በነማን እውን ይሆናል? የሚለውን እጅግ ፈታኝ ጥያቄ ወቅቱንና ሁኔታውን በሚመጥን አቋምና ቁመና መመለስ የግድ ነው።

ሰላምና ዴሞክራሲ የሚሰፍንበት ሁኔታ ይፈጠር ዘንድ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ከማድረግ ይልቅ በህዝብና ለህዝብ ተቆርቋሪ በሆኑ ወገኖች ላይ ጨካኝ ሰይፋቸውን መጠቀም ዋነኛ የሥልጣን መቆያና የአገርን ሃብት መዝረፊያ ያደረጉ ባለጌና ጨካኝ የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ሥርዓት ዘዋሪዎችን (አራጊና ፈጣሪዎችን) ለማስወገድ ጦርነት አይቀሬ መሆኑ እየታወቀ ገዳዩንና ተገዳዩን የሰላም ፀሮችና ጦርነት የናፋቂዎች አድርጎ ለመሳል (ለማሳየት) መሞከር   እውነተኛና ዘላቂ ሰላምንና እድገት በፍፁም አያረጋግጥም።  ሃይማኖትን ለዚህ አይነት አተረጓጎም ፣ አስተሳሰብና አካሄድ በሚያመች ሁኔታ እየተጠቀሙ “የሰላምና የፅድቅ  አባቶች ነንና ለምን ከመስመራችን እንድንወጣ ትጠይቁናላችሁ” የሚለው ምሬትና ርግማን ትክክለኛ የሆነ መንፈሳዊም ሆነ ዓለማዊ  ስሜት የለውም።

ከዚህ ግዙፍና መሪር እውነታ እየሸሹ ባህር ወይም ውቅያኖስ ማዶ ለሚሠራ ቤተ ክርስቲያንና ገዳም በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር የመሰብሰብ ተውኔተ ዘመቻ ላይ መጠመድም የእውነተኛ ክርስቲያንነት ባህሪና ድርጊት አይደለምና ልብ ያለው ልብ ይበል!

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share