November 6, 2023
38 mins read

ሃይማኖታዊ እምነት እና የተግዳሮቱ አሳሳቢነት!

November 5, 2023

ጠገናው ጎሹ

እንደ የገሃዱ ዓለም እውነታና እንደ አጠቃላይ እውነት ከሆነ ተግዳሮት (challenge) በራሱ መጥፎ ነገር አይደለም ። አይሆንምም።  ተግዳሮት ከቁጥጥር ውጭ በሆነ ወይም በገዛ ራሳችን ደካማነት ምክንያት ወደ አጠቃላይ  ውድቀት  ወይም ቀውስ ሲሸጋገር ነው አስከፊ የሚሆነው።

ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻልን ከማሳየት ይልቅ በተቃራኒው አስከፊ በሆነ የቀውስ (የውድቀት) አዙሪት ውስጥ እንድንዘፈቅ ካደረጉን ዋነኛ ምክንያቶች አንዱ ከቁጥጥራችን ውጭ የሆነ  ተግዳሮት ገጥሞን ሳይሆን ልክ ከሌለው የጎሳ አጥንት ስሌት የፖለቲካ ደዌ ለመላቀቅ እንችል ዘንድ ትርጉም ያለው የጋራ ተጋድሎ ለማድረግ አለመቻላችን ነው። ለዘመናት የዘለቅንበትና የዓለም ምፅዋዕት ተመፅዋቾች ሆነን የቀጠልንበት የድርቅና የርሃብ ቸነፈርም ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትንና መልካም አስተዳደርን እውን ለማድረግ ያመቻላችን አስከፊ ውድቀት የወለደው እንጅ የሃይማኖት መሪዎችና ሰባኪዎች እንደሚሉን ፈጣሪ ሊቀጣን ስለፈለገ ያመጣው ሰቆቃዊ ተግዳሮት ፈፅሞ አይደለም። ሊሆንም አይችልም። ማሰቢያ ከሚሆን ረቂቅ አእምሮና ማከናወኛ ከሚሆን ብቁ አካል ጋር በአምሳሉ የፈጠረንን  አምላክ እገዛ እየጠየቅን ለዘመናት ከመጣንበትና ከአምስት ዓመታት ወዲህ ደግሞ ለማሰብም በሚከብድ ሁኔታ አስከፊ እየሆነ የቀጠለውን ፖለቲካ ወለድ መከራና ውርደት በጋራ ጥረትና ተጋድሎ ለማስወገድ እና ለሁላችንም የምትበጅ ዴሞክራሲያዊት አገር እውን ማድረግ ሲያቅተን ሃይማኖትን ጨምሮ የተለያዩ ሰንካላ ሰበቦችን እየደረትን የምናቀርበውን እግዚኦታ የሚሰማ ፈጣሪ የለም። እውነተኛው ፈጣሪ የሚሰማውና የሚያግዘው ከሌሎች ፍጡራን በተለየ የተፈጠረበትን ዓላማ ተረድቶ የራሱን ሃላፊነትና ግዴታ የሚወጣውን ሰብአዊ ፍጡር ነው።

የሃይማኖት መሪዎቻችንና አስተማሪዎቻችን ይህንን ግዙፍና መሪር እውነታ  ተረድተው የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነትና ተልእኮ ባለመወጣታቸው በባለጌና ጨካኝ ገዥ ቡድኖች አስቀያሚ የፖለቲካ አዙሪት ውስጥ በመጓጎጥ ላይ ይገኛሉ ።

አዎ!  ከነችግሮቻችንም ቢሆን የረጅም ዘመን ታሪክ እንዳላት አገር ዜጎች (ልጆች) ዘመን ጠገብና አስከፊ የሆነውን ተግዳሮት በቅጡ ተቋቁመንና ትምህርት ወስደን  ለሰማያዊውም ሆነ ለምድራዊ ህይወት የሚበጅ ሥርዓተ ማህበረሰብ እውን ለማድረግ እንችል  ዘንድ መሠረታዊ ከሆነው ሰብአዊ ወይም ተፈጥሯዊ  መብት አንፃር መወጣት ያለባቸውን ግዙፍና ጥልቅ ሃላፊነት ሊወጡ ይገባቸው የነበሩ  የሃይማኖት ተቋማት  መሪዎች  በዚህ እጅግ አስቸጋሪና አስፈሪ ወቅትም ከባለጌና ከጨካኝ የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኞች ሰለባነት ራሳቸውን ነፃ ለማድረግ ያለመቻላቸው  መሪር እውነታ በእጅጉ ያሳዝናል፤ ያሳፍራልም።  ።

እንደ አንድ የአገሩን መሠረታዊና ዘመን ጠገብ የሆኑ አዎንታዊና አሉታዊ ሁኔታዎችን ለመረዳት እንደሚችል እና ሁኔታዎቹ የተስተናገዱበትንና እየተስተናገዱበት ያለውን አስተሳሰብና አካሄድ በመከታተል ለማወቅ አቅሙና ችሎታው በፈቀደ ልክ ጥረት እንደሚያደርግ ተራ ግለሰብ  (ordinary person) ሃይማኖታዊ እምነትን ጨምሮ በማነኛውም ርዕሰ ጉዳይ ላይ ስንነጋገር የርዕሰ ጉዳዩ ልዩ ባህሪን ፣ዲሲፕሊንን፣ ዓላማንና ተልእኮን ግምት ውስጥ የማስገባቱ አስፈላጊነት እንደጠበቀ ሆኖ ትክክል የሆነውን ትክክል ለማለት እና ስህተት የሆነውን ደግሞ ስህተት ነው ለማለት መመዘኛችን መሆን ያለበት በምክንያታዊነትና አግባብነት ባለው አቀራረብ ላይ የተመሠረተ መሆኑ ወይም አለመሆኑ እንጅ ሂሳዊ ትችት የሚቀርብበት ግለሰብ ወይም የሚቀርብባቸው ግለሰቦች ወይም መሪዎች አይደፈሬነት ወይም አይተኬነት  (indispensability/absolute necessity) መሆን የለበትም የሚል ፅዕኑ እምነት አለኝ።

መሠረታዊ የሆኑ የዶግማ ፣ የቀኖና እና ተያያዥነት ያላቸው እሴቶች  እንደ ተጠበቁ ሆነው  ስህተት ወይም ድክመት  የሚታይባቸው (የሚስተዋልባቸው) የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች ከተጠየቅና ከእንጠያየቅ ሂሳዊ ትችት ነፃ (immune) ሊሆኑ አይገባቸውም ። እንዲሆኑ መፍቀድም ትክክል አይሆንም (አይጠቅምም)። ይሁኑ ብንል እንኳ በሃይማኖት ስም ከገዛ ራስ ግዙፍና መሪር እውነታ የመሸሽና ራስንን ብቻ ሳይሆን ተከታይንም ጨምሮ መደለልና ማሳሳት  ነው የሚሆንብን። በታላቁ መጽሐፍም እውነትን እውነት እና ሃሰትንም ሃሰት በሉ “ ተባለ እንጅ የትምህርት ደረጃን፣ የሥልጣን ተዋረድን፣ የሥራና የሙያ ልምድን ፣ የእድሜ ቁጥር ብዛትን፣ የዓለማዊ ወይም የመንፈሳዊ  የሥልጣን ማዕረግን ፣ ወዘተ መመዘኛዎች  እያደረጋችሁ እውነት ወይም ሃሰት በሉ አልተባለም።

ይህ ግዙፍና ጥልቅ ሃይማኖታዊ፣ ሞራላዊ ፣ባህሪያዊ፣ ሥነ ምግባራዊ፣ ሥነ ልቦናዊና ማህበራዊ እሴት በየዘመኑ በሥልጣነ መንበር ላይ በሚፈራረቁ እኩያን ገዥዎች በእጅጉ መጎሳቆል ከጀመረ ዘመናትን አስቆጥሯል። በእጅጉ የሚያሳዝነውና እንደ ማህበረሰብ የሚያሳፍረው ለዘመናት ከዘለቅንበት ልኩን ወይም መስመሩን ከሳተ የሃይማኖትና የፖለቲካ የመደበላለቅ አስቀያሚና አደገኛ ሁኔታ ተላቀን ሁሉም በሚያገባውና በሚያገናኘው ጉዳይ ላይ የየራሱን ተሳትፎና አስተዋፅኦ ከማድረግ ይልቅ ይበልጥ አስከፊና አደገኛ በሆነ መደበላለቅ ውስጥ የመገኘታችን ጉዳይ ነው። ለዚህም ነው ሊያጋጥም ከሚችል ተግዳሮት አልፈን እጅግ አስከፊና አደገኛ በሆነ የውድቀት አዙሪት ውስጥ በመጓጎጥ ላይ እንገኛለን። ለዚህም ነው ከዚህ እጅግ አስቀያሚና አደገኛ ሁኔታ በመውጣት በትክክለኛው ፍኖተ ነፃነትና ፍትህ ላይ በመሰባሰብ እና የፈጣሪን እገዛ በመጠየቅ ለሁላችንም እና ሃይማኖትን ጨምሮ ለሁሉም አይነት ነፃነቶቻችን የሚበጅ ሥርዓት እውን ለማድረግ እሳካልቻልን ድረስ በምድርም ሆነ በሰማይ ሰሚ በሌለው እሮሮና እግዚኦታ  ፈፅሞ የትም አንደርስም ማለት  ትክክል የሚሆነው።

በሃይማኖታዊ እምነት ረገድ ስለ አጋጠመንና እያጋጠመን ስላለው ተግዳሮት አስተያየት ስሰነዝር ሃይማኖት በፖለቲካ ተፅዕኖ ዒላማ ሥር የወደቀበት አስከፊ የታሪክ ሂደት አልነበረም እያልኩ አይደለም።  ለዚህ እውነትነት በወራሪና ፉሽት ኢጣሊያ እና በጭራቃዊው የሂትለሩ ዘመን የነበረውን ሃይማኖትን በመሣሪያነት የመጠቀም እጅግ አስከፊ የታሪክ እውነታ በማሳየነት መጥቀስ ይቻላል። አዎ! የሞሶሎኒን ፉሽስትና ወራሪ ሃይል “ባርከውና ቀድሰው” የላኩ እና የሂትለርን እጅግ አሰቃቂ አስተሳሰብና ተግባር ደግፈው የቆሙ በስም የሃይማኖት አዋቂዎች የሚመስሉና በተግብር ግን አደገኛ ደንቆሮዎችና አረመኔዎች የሆኑ የሃይማኖት መሪዎችና ሰባኪዎች ነን ባዮች እንደነበሩ ይታወቃል። ይህንን ለማሳያነት ጠቀስኩት እንጅ   ከዚያም በፊትም ሆነ በኋላ ሃይማኖታዊ እምነት ከፖለቲካ ሥርዓት ተፅዕኖ ፍፁም ነፃ የሆነበት ዘመንና ሥርዓት ነበር ወይም አለ ለማለት አይደለም።

ያደረጋቸው ታላላቅና ከቶ ዘመን የማይሽራቸው አወንታዊ አስተዋፅኦዎች እንደተጠበቁ ሆነው የእኛ ታሪክም ከዚህ አይነት አስቸጋሪ ሂደት ነፃ የሆነበት ጊዜና ሁኔታ አልነበረም ።

በዓለም እስከ ጦርነት በደረሱ የፖለቲካ ሥልጣን ሽኩቻዎች ውስጥ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ እና ፍትሃዊና ፍትሃዊ ያልሆነ ጦርነት በሚል ሃይማኖት ያልተገኘበትን ጦርነት በአንፃራዊነት ካልሆነ በስተቀር በፍፁማዊነት ማግኘት  የሚቻል አይመስለኝም። የአገራችን እውነታም የአሉታዊነት ወይም የአወንታዊነት ደረጃው ይለያይ እንጅ ከዚህ አይነት የታሪክና የፖለቲካ ፈተና የተለየ (exception) አይደለም።

ይህ የሆነውና የሚሆነው ፖለቲካን የመጨቆኛና የዝርፊያ መሣሪያ ያደረጉትና የሚያደርጉት እኩያን ገዥዎችና ፖለቲከኞች እና የተጨቋኙ ማህበረሰብ የንቃተ ህሊና እና የተግባር ድህነት እንጅ ፖለቲካ በራሱ መጥፎ ወይም አጥፊ  በመሆኑ እንዳልሆነ ሁሉ በሃይማኖት ረገድ ያለው ፈተናም በመሪዎች የቃልና የተግባር አርአያዎች ሆኖ ያለመገኘት ደካማነት እና ለምንና እንዴት ብሎ መጠየቅን እንደ ሃጢአት እንዲቆጥር በተደረገው ምዕመን ድክመት ምክንያት እንጅ ሃይማኖት በራሱ የችግር ምክንያት እንዳልሆነ ግልፅ መሆን አለበት። ለዘመናት ከመጣንበትና በአሁኑ ጊዜ ለማሰብ በሚከብድ ሁኔታ ተዘፍቀን ከምንገኝበት  የመከራና የውርደት ምንነትና ማንነት ሰብረን ለመውጣትና ለሁላችንም እና ለሁሉም ሃይማኖታዊ እምነቶቻችን ነፃነት የሚበጅ ሥርዓተ ፖለቲካ እውን ለማድረግ ካልቻልንባቸው ዋነኛ ምክንያቶች አንዱ ይህ አይነቱ አስቀያሚ  የአስተሳሰብና የአካሄድ መዘበራረቅ (መደበላለቅ) ነው።

እርግጥ ነው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትም ቢሆን ሃይማኖትና መንግሥት እንዳይደበላለቁ የሚያደርግ ህግና ደንብ ስለሚኖረው፣ የዚህኑ ተግባራዊነት የሚያረጋግጡ ተቋማት ስለ ሚኖሩት እና ህዝብም ይህንን በመረዳት ለተግባራዊነቱ ስለሚተባበር እንጅ ተግዳሮቱ ጨርሶ የለም ወይም አይኖርም ማለት አይደለም።

እንደ ትክክለኛው የፅንሰ ሃሳብ ምንነት፣ ለምንነት፣ እንዴትትነት እና ወዴትነት ትርጉም ከሆነ ሊቀ ዲያቆናት  ሊቀ ካህናት፣ ሊቀ መዕምራን፣ ሊቀ ጠበብት፣ ሊቀ ሊቃውንት፣ ዶክተር ፣ ፕሮፌሰር  ማለት እጅግ ሰፊና ጥልቅ የሆነ ሰብዕና ምንነትና እንዴትነት እሴት ነው። ወደ መሬት ወርዶ በእርሱ (በፈጣሪ) አምሳል የተፈጠረው ሰብአዊ ፍጡር (ወገን) ከባለጌና ጨካኝ ሥርዓት ነፃ በመውጣት የእውነተኛ አምላክ እውነተኛ አማኝ እና ለአገሩም ቀድሞ ደራሽ እንዲሆን ለማስቻል ተገቢውን ድርሻ በተገቢው ሁኔታ መወጣት የተሳነው የሃይማኖት መሪነትና አስተማሪነት ከቶ የትም አላደረሰንም ፤ አያደርሰንምም። በፈሪነት፣ በአድርባይነት፣ በአስመሳይነት እና ልክ በሌለው የራስ ወዳድነት ክፉ ደዌ የተበከለውን ማንነትና እንዴትነት ፀአዳ በሆነ አለባበስና ለጆሮ በሚጥም ስብከት ፣ ትክክለኛ ይዘት በሚጎለው የክብረ በዓል ሽር ጉድ እና ዝማሬ ማፅዳት ፈፅሞ አይቻልም ። እውነተኛው ፈጣሪም አይቀበለውም።

አዎ! ስለ ወገኑ መከራና ሰቆቃ ሲል ሰማእት እስከ መሆን ለመድረስ በአፍ ብቻ ሳይሆን በሃይማኖታዊ አርበኝነት መንፈስ ቆሞና ፀንቶ መገኘትን የሃይማኖታዊ እምነት መሪነት ሃላፊነትና ግዴታ መሆኑን ለአንድ አፍታም ቢሆን የሚረሳ ወይም ችላ የሚል ፓትርያርክነት ፣ሊቀ ጳጳስነት፣ ጳጳስነት ፣ እና ባለሌላ ማእረግ አባልነት (አገልጋይነት) በመንበረ ሥልጣን ላይ ከሚፈራረቁ የጎሳ/የቋንቋ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ሥርዓት ዘዋሪዎች ሰለባ ከመሆን አዙሪት ሰብሮ ለመውጣት ከቶ አይቻለውም።

ለብዙ ዓመታት ከዘለቅንበትና በተለይም ከአምስት ዓመታት ወዲህ ደግሞ በሃይማኖታዊ እምነት (በተለይም ኦርቶዶክስ ተዋህዶን) ላይ እንኳንስ ለማመን ለማሰብም በሚከብድ ሁኔታ  የመከራና የውርደት ናዳ እያደረሰ ካለው ግዙፍና መሪር እውነታ አንፃር የሃይማኖቱ መሪዎች   የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት አለመወጣታቸውን “አባቶቻችን መንቀፍ ነውር ነው” በሚል የዋህነት ወይም ትክክል ያልሆነ ፍርሃት የምናልፈው ከሆነ ፈጣሪ ከሁሉም ፍጡራን ለይቶ ከረቂቅ አእምሮና ብቁ አካል ጋር የፈጠረበትን ዓላማ ከንቱ ማድረግ ነው የሚሆንብን ።

ለሃይማኖታዊ ዶግማ እና ቀኖና  መከበርና በአጠቃላይ የቤተ ክርግቲያኗ ደህንነት ይጠበቅ ዘንድ ለመጠየቅ  ከል (ጥቁር) ለብሰህ አደባባይ ወይም ጎዳና ላይ ውጣና እጆችህን ወደ ፈጣሪ ዘርግተህ ጩህ ባሉት መሠረት ከወጣው ህዝበ ክርስቲያን መካከል የተገደለ፣ የተደበደበ፣ የታሰረ፣ ከሥራው የተባረረ መኖሩን ተከታትሎ ለማወቅና ተገቢውን ለማድረግ የተሳነው መሆኑ አልበቃ ብሎ  ገዳዩ/አስገዳዩ እና ጉዳት አድራሹ ገዥ ቡድን መሆኑ እየታወቀ በቀጥታና በግልፅ  ተጠያቂ ከማድረግ ይልቅ እጅግ ስንካላና ደምሳሳ በሆነ “ከሚመለከተው ጋር እየተነጋገርን ነው” በሚል አገላለፅ አድበስብሶ (አለባብሶ) ማለፍ ለሃይማኖት አመራር ፈፅሞ አይመጥንም።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የመስቀል በዓል አከባበርን በተመለከተ ከሸፍጠኛና ጨካኝ ገዥ ቡድኖች የተሰጣቸውን የማስጠንቀቂያ (የማስፈራሪያ) ኦሬንቴሽን/ገለፃ ተቀብለው በዚህ በዓል ላይ በዓሉን ከሚገልፁ ቃላት ፣ ምልክቶችና ቀለሞች በስተቀር የሚናገርና ይዞ የሚገኝ ካለ “እኛ ከደሙ ንፁህ ነን” የሚል አይነት  ማስጠንቀቂያ በመስጠት በዓሉን በይዘት ሳይሆን በፎርም (በቅርፅ) ለመሸፈን የተደረገው ሙከራ በዓሉን የሚገባውን ክብርና ሞገስ እንዳያገኝ አድርጎታል ። መቸም የገዛ ራሳችንን መሪር እውነት መቀበልና መጋፈጥ ሲያቅተን ነውር ያልሆነውን እንደነወር ወይም ሃጢአት ያልሆነውን እንደ ሃጢአት መቁጠርን መሸሸጊያ እያደረግን ስለምንቸገር ነው እንጅ ይህ አስተያየቴ የመስቀል በዓል አከባበርን ከማቀለል ጋር ጨርሶ ግንኙነት የለውም ። እያልኩ ያለሁት እናንት የሃይማኖት መሪዎች ሃይማኖቱ ከገጠመውና እየገጠመው ካለው ከባድ ፈተና አንፃር ሃላፊነታችሁን ባለመወጣታችሁ ምክንያት ሃይማኖታዊ በዓላት በባለጌና ጨካኝ ገዥ ቡድኖች መልካም ፈቃድና ፍላጎት ቁጥጥር ሥር እንዲወድቁ  አድርጋችኋልና  ቆም ብላችሁ ራሳችሁን ፈትሹ ነው።

ከሰሞኑ ደግሞ ተካሄደ የተባለው የሲኖዶስ ስብሰባ ቤተ ክርስቲያኗ ፣ አማኞቿና በአጠቃላይ ህዝብ ከሚገኙበት እጅግ ግዙፍና አስከፊ ሁኔታ አንፃር ሲታይ (ሲገመገም) እዚህ ግባ የሚባል ወይም ከተለመደው ተደጋጋሚና አሰልች መግለጫ ያለፈ ፋይዳ ያለው ውጤት እንካችሁ ሳይል የመጠናቀቁ አሳዛኝ ሁኔታ የሚነግረን  ቁም ነገር ቢኖር ለዘመናት ከዘለቅንበትና አሁን ደግሞ እጅግ በባሰ አኳኋን ተዘፍቀን ከምንገኝበት ክፉ የውድቀት አዙሪት ሰብረን ለመውጣት ብዙና አስቸጋሪ ተግዳሮቶች የሚጠብቁን መሆኑን ነው ።

ወደ ሌላው የክርስትና ሃይማኖት ዘርፍ (sect) መሪዎችና ሰባኪዎች ስናልፍ የምንሰማውና የምናየው በእጅጉ የባሰ እንጅ የተሻለ አይደለም ።  ወደ    ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመሸጋገር የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶቻችንን በቅጡ መጋፈጥ ባለመቻላችን ምክንያት “እግዚአብሔር በቤተ መንግሥት ዙፋኑን ዘርግቶ  በአብይ አህመድ አማካኝነት ሥራውን እየሠራ ስለሆነ አትረብሹ” የሚሉ የፕሮቴስታንት እምነት ፓስተሮችንና ነብይዮች ነን ባይ ወገኖችን እየሰማንና እያየን ነው። የአገዛዙ ቤተ መንግሥት በእነርሱ ሰዎች ቁጥጥር ሥር መሆኑን እንደ ታሪካዊ ድል   በመቁጠር ይህንን “ድል” እቀለብሳለሁ የሚል ከመጣ እልቂት እንደሚሆን በይፋና በግልፅ ቋንቋ እስከ መናገር የሄዱበት ርቀት በእጅጉ አስደንጋጭ ነው።

ከአንደ ሳምንት በፊት አዲስ ኮምፓስ በተሰኘ የሶሻል ሚዲያ በቀረበ ፕሮግራም ላይ የኢቫንጀሊካል ቤተ ክርስቲያን ፕረዝደንትና ፓስተር ነው የተባለና ፃድቁ የሚባል ሰው ያለምንም ይሉኝታ እና ሃላፊነት በጎደለው ግብዝነት የተናገረውን ለሰማ ባለ ቅንና ሚዛናዊ ህሊና ባለቤት የአገሬ ሰው በእጅጉ ይረብሸዋል ። በእውን እንዲህ አይነቱን ሰው ልጄ ብሎ የሚቀበል እውነተኛ አምላክ አለ እንዴ? የሚል መሪር ጥዩቄም ያስነሳል። ቃል በቃል ለመጥቀስ ባልችልም የንግግሩ ጭብጥ የሃይማኖቱ ተከታዮች እንደ አሁኑ በፖለቲካው ውስጥ ዘልቀው የገቡበት ጊዜ ኖሮ እንደማያውቅ፣ በዚህም ምክንያት በሌሎች ለእልቂት ካቴጎራይዝ እንደተደረጉ እና ሥልጣን ላይ ያሉት ፌል ካደረጉ ( ከወደቁ) እነርሱም እንደሚወድቁ በየድርጅቱና በየመሥሪያ  ቤቱ ለሚገኙ ተከታዮቹ እንዲነገራቸው  የሚል መልእክት ሲያስተላልፍ መስማት እጅግ ከባድ የህሊና ህመም ይፈጥራል  ። ለነገሩ አብይ አህመድ ራሱ እንደ አገር መሪነቱ በሆነውና እየሆነ ባለው ሁሉ  አዝናለሁ አለማለቱ አልበቃ ብሎት የአሰቃቂ አገዳደል ሰለባ በሆኑ ንፁሃን ላይ “ችግኝ ብንተክል ጥላ ይሆናቸዋል” በሚል የማላገጡን ድፍረት በግልፅና አግባብነት ባለው አቀራረብ ቢያንስ ነውር ነው የሚል የሃይማኖት መሪ ለማየትና ለመስማት ባልታደልንበት መሪር እውነታ ውስጥ እንደ ፃድቁና ዮናታን የመሰሉ ፓስተርና ነብይ ተብየዎች የሚነግሩን የቁርጣችሁን እወቁ ፉከራ የሚገርም አይሆንም።

የእስልምናው ሃይማኖትም ከዚህ እንኳንስ ፈጣሪ (አላህ) ቅንና ሚዛናዊ ህሊና ያለው ነፃነትና ፍትህ ፍላጊ የአገሬ ሰው ከሚፀየፈው የጎሳና የቋንቋ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማር ምርኮኝነት አላመለጠም።  በሙስሊም ኢትዮጵያዊያን ግንባር ቀደም መሪነትና በሌሎች ሃይማኖት ተከታዮች ኢትዮጵያዊያን ተሳታፊነት የወቅቱን ህወሃት መራሽ የኢህአዴግ ሥርዓት “ድምፃችን ይሰማ” በሚል መሪ መፈክር ከተካሄዱት የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች አንዱ እንደነበር የትናንት ትውስታ ነው። በዚያ ምክንያት ታስረው ለነበሩት ሙስሊም ወንድሞች ይደረግ የነበረው ድጋፍና ትብብርም እንዲሁ ። ህወሃት መራሹ ኢህአዴግ ህወሃትን ቀንሶ ብልፅግና በሚል በንፁሃን ደምና ሰቆቃ የጨቀየውን መንበረ ሥልጣን በበላይነት የተቆጣጠረው  የኦህዴድ/የኦሮሙማ ቡድን በመሪው በአብይ አህመድ ግልፅና ቀጥተኛ ጣልቃ ገብነት መፈንቅለ መጅሊስ ሲደረግበት እምነቴንና የእምነቴን የበላይ አካል ጉዳይ ለእኔ ተውልኝ የሚል ሰላማዊ የሆነ የምር ተቃውሞ  የአለማንሳቱ  ጉዳይ የሚነግረን ሃይማኖታዊ ተቋማትና መሪዎቻቸው የሸፍጥና የጭካኔ ፖለቲካ ሥርዓት ሰለባ ሆነው የመቀጠላቸውን መሪር እውነት ነው።

የሃይማኖታዊ እምነት ተቋማት  ተግዳሮቶችን አስከፊነትና የመሪዎቻቸውን ሃላፊነትን የመወጣት ውድቀት ከሚያሳዩን ሌሎች ማሳያዎች መካከል አንዱ በሰላም ምልክትነት የምንጠቀምባትን ርግብ በአርማነት የሚጠቀመውና በአንፃራዊነት ጥሩ የሆነ የወረቀት ላይ ተልእኮና ዓላማ ያለው የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ (Inter -Religious Council of Ethiopia) በሚል የሚጠራው አካል እንኳንስ በወረቀት ላይ ካስቀመጠው ተልእኮና ዓላማ አንፃር እንደማነኛውም የሃይማኖትና የአገር ጉዳይ እንደሚያሳስበው ግለሰብ ወይም ቡድን ወይም ድርጅት ትርጉም ያለው የያሳስበኛል  መግለጫ ለማውጣት  ያልቻለ የመሆኑ አስቀያሚ እውነታ ነው።  በእንዲህ አይነት ወለፈንዲነት (hypocrisy) የተበከሉ የሃይማኖት አካላት ባሉበት የሃይማኖት ነፃነትን ጨምሮ ሁሉም መሠረታዊ መብቶች የሚከበሩበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን ይሆናል ማለት ራስን ማታለል ነውና እጅግ ቢዘገይም ከአሁን ጀምሮ በቃን ማለት ያስፈልጋል።

የገዛ ራሳችንን ዘመን ጠገብ ደጋግሞ የመውደቅ ግዙፍና መሪር እውነት በግልፅ፣ በቀጥታ    እና ገንቢነት ባለው አቀራረብ ከመጋፈጥ ይልቅ የሰበብ ድሪቶ እየደረትን የሃይማኖታዊ እምነት ተቋማትን መሸሻና መደበቂያ በማድረግ ከልክ ያለፉ የግልና የቡድን ፍላጎቶቻችንን ከማሳደድ ክፉ አባዜ ከተጠመድን ዘመናት ተቆጠሩ ። በእግዚአብሔር የተሾሙ የህዝብ እረኞች እንደሆኑ ሌት ተቀን የሚሰብኩን የሃይማኖት መሪዎችና አስተማሪዎች የውድቀት አስተሳሰባችንና አካሄዳችን በቅጡ ተገንዝበው መወጣት ያለባቸውን ሃላፊነት ከመወጣት ይልቅ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከእኩያን ፖለቲከኞች ጋር እየተሻሹ ለምንና እንዴት ተብለው ሲጠየቁ “ለሰላምና ለአገር ስንል ነው” የሚል እጅግ አሳሳች (synical) መከራከሪያ ሊያሳምኑን ሲሞክሩ በአግባቡ ለመቆጣት ካልቻልን ነፃነትንና ፍትህን መመኘታችን ምኞት ብቻ ሆኖ ነው የሚቀረው።

እጅግ ግዙፍና ጥልቅ የሆነ ተልዕኮና ሃላፊነት የተጣለባቸው የሃይማኖት ተቋማትና መሪዎቻቸው ደጋግሞ ከመውደቅ አስከፊና አሳፋሪ አዙሪት ሰብሮ ለመውጣት ያለመቻላቸው መሪር እውነት አሁንም ቀጥሏልና ከምር ተነጋግረን ከምር የሆነና ዘላቂ የሆነ ፍኖተ መፍትሄ ፈልገን ማግኘት አለብን።

 የዓለማዊና የሃይማኖታዊ እውቀትና ክህሎት (ምሁርነት) የየራሳቸው የሆነ የአስተሳሰብ፣ የአረዳድ፣ የአሠራር ፣ ወዘተ ሁኔታ ያላቸው መሆኑ እንደተ ጠበቀ ሆኖ ሁለቱም ግን አንድ ትልቅና የተቀደሰ የሚያገናኛቸው ጉዳይ አለ። እርሱም የሰው ልጆች ሁሉ በተፈጥሮ ባገኙት እና ይበጀናል ብለው በተስማሙበት ሰው ሠራሽ ህግና ሥርዓት መሠረት በነፃነት፣ በፍትህ እና አስተማማኝና ዘላቂ በሆነ የጋራ ልማት መኖር ይችሉ ዘንድ የየበኩላቸውን ጥረት የማድረግ አስፈላጊነት ነው።

ከዚህ እጅግ ጥልቅና የተቀደሰ አስተሳሰብና አካሄድ ውጭ የሚኖረው እውቀት ወይም  ክህሎት የማቴሪያላዊ (የገንዘብና የቁስ) “ባለፀጋነት” ህልምን ከማሳካት አያልፍም ።

ረቂቅ የሆነው ባህሪውና ሥራው እንደተጠበቀ ሆኖ የክርስቶስ አስተምህሮቶቹ በእኩያን ገዥዎች ለምድር ላይ ሰቆቃ የተዳረጉት ጎስቋሎች (ምስኪኖች) በአምሳሉ እንደ ተፈጠሩ ሰብአዊ ፍጡሮች በነፃነትና  እንዴኖሩና ከሞት በኋላ ተስፋ የሚያደርጉትን ዓለም እንዲወርሱ እንጅ በባዶ ሃይማኖታዊ ስብከትና መነባንብ የተጀቦኑ አልነበሩም ።

በሃይማኖትም ሆነ በሌላው የህይወታችን ሂደት የሚገጥሙንን ተግዳሮቶች ማስወገድ አይቻልም። የማይቻለው አይቀሬ ስለሚሆኑ ብቻ ሳይሆን በማያቋርጥ ሁለንተናዊ የእድገት ሂደት ውስጥ ከሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች ወይም ፈታኝ  ሁኔታዎች የምናገኛቸው ተሞክሮዎች የቀጣይ የእድገት ግሥጋሴዎቻችን ግብአቶች ስለሚሆኑን ነው። ተግዳሮቶቻችን ወደ አስከፊነት ደረጃ እየተሸጋገሩ የውድቀት አዙሪት ሰለባዎች የምንሆነው በአብዛኛው በራሳችን የተሳሳተ አስተሳሰብና አካሄድ እንጅ ከቁጥጥር ውጭ በሆኑ ምክንያቶች አይደለም። ለዘመናት ከመጣንበትና አሁንም እጅግ አስከፊ በሆነ ሁኔታ ከቀጠለው ፖለቲካ ወለድ መከራና ውርደት ሰብረን ለመውጣት ካልቻልንባቸው ምክንያቶች አንዱ  ከዚሁ መሠረታዊ እውነት ጋር የተያያዘ ነው።

በፈጣሪ አምሳል የተፈጠረው የሰው ልጅ የተሰጠውን ልዩ አቅምና ችሎታ ተጠቅሞ በነፃነት ይኖር ዘንድ  እንዲያግዙት ሃላፊነት የተሰጣቸው የሃይማኖት መሪዎች የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን በወቅቱና በአግባቡ በመጋፈጥ ትክክለኛ የመፍትሄ ሃሳብ  አምጦ ከመውለድ ይልቅ ከባለጌና ጨካኝ ገዥዎች  ጋር እየተሻሹ የመከራውንና የውርደቱን እድሜ  እንዲራዘም የሚያደርጉትን  አስተዋፅኦ እንዲያቆሙ ማሳሰብና መጠየቅ የፅድቅ እንጅ የኩነኔ መንገድ አይሆንም።

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop