ብሥራት ደረሰ
ምንም ነገር የመጻፍ ፍላጎት የለኝም፡፡ ጊዜው ሀገራችን ልትወለድ ምጥ የበዛት በመሆኑ ከመጻፍ ይልቅ የነገሮችን አካሄድ በጥሞና የመከታተያ እንደሆነ አምናለሁ፡፡ ላለፉት አራት አሠርት ዓመታት ገደማ ብዙ ብለናል፡፡ አሁን በክፉም ሆነ በደግ የገነኑ ሰዎች ወደ መድረክ ከመዝለቃቸው ብዙ ዓመታት አስቀድመን ስለሀገራችን መፃዒ ሁኔታ ሣይቀር ጥቂት የማንባል ወገኖች ብዙ ለፍልፈናል፡፡ ከጮህንበት ውስጥ አብዛኛው በተግባር ታይቶ የሀገር ትንሣኤው ብቻ ይቀራል፡፡ ይህ ነባራዊ ክስተት ደግሞ በቅርቡ እውን ይሆናል፡፡ የሀገር ጠላቶችም ግብዓተ መሬታቸው ይፈጸማል – ዓለም እያዬ!!
በዚህን አስቸጋሪ ወቅት ነው እንግዲህ ዝም ማለት ያላስቻለኝ ነገር የተፈጠረው፡፡ ነገሩ ትናንት ማታ ነው፡፡ አንድ ሚዲያ ስከታተለል ታጋይ አርበኛ ዘመነ ካሤ ሲናገር ሰማሁና ሙሉውን አዳመጥኩት፡፡ ጥሩ ንግግር ነው፡፡ ነገር ግን የእስክንድርን ስም ሲያነሳ “ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ” ብሎ እንደቀላል ነገር ሲናገር ስሜቴ ተረበሸ፡፡ እኔ ዘመነን ብሆን “አርበኛ ፋኖ እስክንድር ነጋ” እል ነበር – “አክቲቪስት፣ ጋዜጠኛ፣ ታላቁ እስክንድር…” የሚለው ቀርቶበት አሁን በተሠማራበት የትግል መስመሩ ቢጠራ ማንም አይጎዳም፤ መከባር ደግሞ ከቤት ይጀምራል፡፡ “ከአነጋገር ይፈረዳል፣ ከአያያዝ ይቀደዳል” እንዲሉ መላ ሕይወቱን ለሀገሩ የገበረን ሰው በዚህ መልክ አሳንሶ መጥራት ለኔ የሸተተኝ ነገር አለ፡፡ እርግጥ ነው እስኬው ጋዜጠኛ ነበር፡፡ አሁን ግን አይደለም፡፡ አሁን ሌላ ነው፡፡ የፋኖ አደራጅና ትልቅ ሥራ በመሥራት ላይ የሚገኝ ሁለመናውን ለኢትዮጵያ ትንሣኤ የሰጠ እንደማንኛውም የፋኖ አባል ሁሉ ውድ ልጃችን ነው፡፡ ጋዜጠኛ መባል ከነበረበት በፊት ነው፡፡ አሁን ግን ይህን ዕንቁ ሰው ወደ ጋዜጠኝነት ሙያ መመለስ ውስጠ ወይራው አልገባኝም፡፡ ለምን?
የኢትዮጵያ ትንሣኤ ብዙ አሣር እንዳለበት ይገባኛል፡፡ በአንድ ጎራ ባሉ ወገኖች ግን ይህ አሣር መቀነስ አለበት፡፡ ካለፈው ተሞክሯችን መማር አለብን፡፡ እዬዬም ሲደላ ነው፡፡ አማራንና ኢትዮጵያን ክፉኛ እየጎዳት ያለው ይሄ የኢጎ ጉዳይ ነው – ራስን ከፍ አድርጎ የመገመትና ለሌሎች ዝቅተኛ ግምት የመስጠት አባዜ ክፉኛ እያወከን ይገኛል፡፡ ብዙ ሚሊዮን አማራን በነፍሰ ሥጋው እየተጫወተበት ያለው አስጠሊታ ነገር የድል ሽሚያና የሥልጣን ፍቅር ነው፡፡ በዚህ ረገድ አማራ አልታደለም፡፡ ብዛቱና ዕውቀት ጥበቡ እያለው በትንሾች እንደክርስቶስ የሚወገረው የራሱ ልጆች አልስማማ ብለው እርስ በርስ ስለሚናናቁና እንደጅብ ስለሚዘራጠጡ ነው፡፡ መጥፎ ጠባይ፡፡
አራት ኪሎ የሚችለው አንድ ሰው ነው፡፡ 15 ሚሊዮን ፋኖ ቢኖር ሁሉም አራት ኪሎ አይገባም፡፡ 100 ሽህ የፋኖ መሪ ቢኖር ሁሉም ያቺን የምታሳብድና የምታቃዥ ወንበር አይዝም፡፡ በጊዜ የጮኸ ጅብ አያሳድረኝም የሚባለው አለነገር አይደለም፡፡ በረሃ እያለ በአልደፈርም ባይት የሚኩነሰነስና በብዙ አጃ የሚቆነን ሰው አራት ኪሎ ቢገባ ምን ሊያሳየን እንደሚችል ከወዲሁ ይታወቃልና ከዚህ ዓይነቱ መጥፎ ጠባይ እንድትርቁ ምክራችን የሚያስልጋችሁ ወገኖቻችንን ከአሁኑ እንመክራለን፡፡ ሰው ዐይን ውስጥ አትግቡ፡፡ ትሁት ሁኑ፡፡ ትኅትናችሁ ወደላይ ያውጣችሁ፡፡ ላዩን ከፈለጋሁ ደግሞ ታቹን ምረጡ፡፡
አሁን ደግሞ የወቅቱ ትኩረት የወንበር ጉዳይ ሳይሆን የኅልውና ጉዳይ ነው፡፡ መጀመሪያ የመቀመጫየን ብላለች ዝንጀሮ፡፡ አማራ በመሆኑ ምክንያት ተወልዶ እንዳያድግ ጽንስ ከሆድ እየተቀደደ በቢላ በሚቀረደድበት ሰዓት፣ አማራ ቆሞ ብቻ ሳይሆን ታሞ ተኝቶም መኖር እንዳይችል ከያለበት በኦሮሞ እየታደነ በሚታጨድበት ወቅት፣ የአማራ ምድር የሚባለው ሳይቀር በኦህዲድ መከላከያ ተወርሮ ዜጎች ቀን ከሌት እየታጨዱ በሚገኙበት ዘመን፣ አዲስ አበባ መግባት ለአማራ ህልም በሆነበት ሁኔታ፣ የአማራ ቤትና ሰውነት በተረኛ ዘረኞች እየፈራረሰና አማራ ሎተሪ አዙሮ ወይም ዘበኝነት ተቀጥሮ እንኳን መኖር ባልተፈቀደለት ወቅት… እንዲህ ዓይነት ቅንጡ የሥልጣን መራኮት ከአሁኑ ሲታይ በርግጥም የአማራው መረገም ሥር የሰደደ እንደሆነ መረዳት አይከብድም፡፡
ስለዚህ እባክህን ዘመነ ሆይ! እባችሁን ዘመነዎች ሆይ! መጀመሪያ በየቀኑ ለምንታረደው ዜጎች ቅድሚያ ስጡ፡፡ የሥልጣን አራራውና ሽኩቻው ይደርሳል፡፡ ሀገር ሲኖር ለሚደርስ ነገር ጠላቶች እስኪስቁባችሁ ሳይቀር አትወዛገቡ፡፡ አማራን አማራ እንዲህ እየጠለፈው የትም አይደረስም፡፡
ሁሉም ነገር እንደሚጠራ አውቃለሁ፡፡ አማራዊነት እንደሚያሸንፍ ዘመነ ጫካ ከመግባቱ በፊት ብዙ ተጮሆበታል፡፡ የሚያበሳጨኝ ግን በዚህን ወቅት እንኳን ከብአዴን ተምሮ አማራነትንና ኢትዮጵዊነትን ከማስቀደም ይልቅ የግል የሥልጣንና የጥቅም ፍላጎትን በማስቀደም ለትዝብት በሚዳርግ ሁኔታ የሚሠራው የጭቡ ሥራ ነው፡፡ ይገርማል፡፡ ፋኖን እግዚአብሔር ከውስጥም ከውጭም ይጠብቀው፡፡
በመጨረሻም እንዲህ ልበልና ልጨርስ፡፡ በምንም ምክንያት ይሁን በምን አማራን ሊከፋፍልና ለኦሮሙማው የዘር ፍጂት ዳርጎ ሁሉንም አማራ ተራ በተራ ለማስፈጀት የሚንቀሳቀስ ሆዳም አማራ የእነፕሮፌሰር አሥራትና የእነአሣምነው ጽጌ ዐፅም እሾህ ሆኖ ይውጋው፡፡ የአማራን ኅልውና ለግል ጥቅም የሚሸጥ አስመሳይና የውስጥ ባንዳ ዘር አይውጣለት፡፡ እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ፡፡