October 22, 2023
24 mins read

ስለ ጀግናው ተዋጊ ሞላ መላኩ  ጽኑ የፋኖ ሕይወትና አይበገሬነት

ከግርማ ብርሃኑ (ፕሮፌሰር)

ይህ የጀግናው ሞላ መላኩ አጭር ታሪክ ነው። የቆራጥ ተዋጊነቱ መዘከሪያና የታማኝ ፋኖነቱ ምስክርነት የሚነገርበት፣ አይበገሬነቱ በወርቅ ቀለም ተከትቦ ለታሪክ የሚቀመጥበትና ለትውልድ የሚተላለፍ መወድስ ነው።

የዚህ ፋኖ ወጣት ጀግንነትና እስከ መስዋእትነት ቅጽበቷ ያሳየው የጀብድ ጥግ ሲወሳ፡ ይሶርፋል፤  ከራስ ጠጉር እስከ እግር ጥፍር ይነዝራል። በዚህም ልክ ጀግንነት አለ ወይ፡ በዚህስ ደረጃ አለመፍራት ይቻላል ወይ ብሎ ያስጠይቃል። የሞላ መላኩ የመጨረሻ ቃላት የጀግንነትም የመጨረሻ መግለጫው ቃላት ናቸው። የአካል ዝለት፡ የጉልበት ድካም፡ የቁስል ህመም ያላበረደው ወኔ፥ ከአለትም የጠጠረ እንደ እሳት የሚፋጅና ሽንፈትን የማያውቅ ጽኑ መንፈስ፥ ፋኖነትን ሊመሰክሩ፡ ቃላት ፡ ፍርሃት አለዝቦት በማያውቅ አንደበት ተገፈታትረው ሲወጡ፡ የታየበት ትንግርት ነው።

ፋኖ ሞላ መላኩ የተሰዋበትን ዜና ከሰማሁ በኋላ እንግዳ በሆነ ሁኔታ ጥልቅ ሀዘንም ጥልቅ ኩራትም ተደባልቆ ተሰማኝ። ጀግንነቱ፥ ድፍረቱ፥ ጠላቱ ሊገድለው መሆኑን እያወቀ እንኳን የጥፍር ቆሻሻ ያህል ጉዳይ አለማለቱ አኮራኝ። ፈክር ፈክር አስባለኝ! መንተርተር ቁጭ ብድግ ማለት ከጀለኝ። ቆራጥነቱ፥ የሞትን ጽዋ ሊጋታት ተጎትቶ ሲወሰድ አለመዝረክረኩ፡ እስከመጨረሻው ማምረሩን ሳስብ የወንድነት ልክ ሞቀኝ። ይህንን እንደ ሽህ የሚቆጠር ደምመላሽ ጀግና ማጣት ደግሞ ሆድ አስባሰኝ። አዘንኩ አስለቀሰኝ። እነዚህን የስሜት ማእበሎች ከተሻገርኩ በኋላ ቤተሰቦቹን ማፈላለግ ጀመርኩ። ከሞላ እናት ከወ/ሮ ሙሃሊት ነጋሽና ከታላቅ ወንድሙ ከተስፋ መላኩ ጋር በስልክ የመነጋገር እድልም አገኘሁ። ሁለቱም የሚኖሩት ወልዲያ አጠገብ የሚገኝ ዶሮ-ግብር የሚባል አካባቢ ነው። የመላኩ አባት ከዚህ አለም በሞት ከተለዩ በርካታ አመታት ተቆጥረዋል። ቤተሰቡ እንደማንኛውም የአማራ አርሶ አደር ጥሮ ግሮ አዳሪ ነው።

በ2014 ወያኔ በአማራ ሕዝብ ላይ የሰነዘረው ጥቃት ትኩረቱ የክልሉን መሠራታዊ ተቋማት ማውደም ብቻ ሳይሆን በርካታ ቤተሰቦችን ለችግርና ለስቃይ መዳረግም ነበር። ለወያኔ ሕዝባዊ ሠራዊት ዘርፎ ማጓዝ የፖለቲካ ቁማሩ እና የጦርነቱም ዋና ግብ ነበርና ምንም እንዳይተርፍ ተደርጎ መወሰድ የሚችለው ተወስዶ ሊወስዱት ያልቻሉትን ደግሞ አውድመውታል። የዚህ ዘመቻ ልዩ ተጠቂዎች ደግሞ በአማራነታቸው የተነሳ፣ ሰብአዊ ክብራቸውን ተገፍፈው የግብረ-ሥጋ ጥቃት የተፈጸመባቸው ሴቶች ናቸው። በዚያ ወቅት ፋኖ ክልሉን ከወያኔ ወረራ ነጻ ለማውጣት ከማእከላዊ መንግሥት ጎን ተሰልፎ ተዋግቷል፤ ግን ይህ ትብብር እድሜው አጥሯል። በጦር “አሸናፊነቱ” የተወጠረው የኃያልነት ስሜት ከፋኖ ውለታ ጋር ያለው ንክኪ እረፍት ስለሚነሳው፤ ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ ከወያኔ ጋር የነበረውን ዊጊያ እንዳቆመ ሠራዊቱን ፋኖ ላይ አዘመተ። ለዚህም የፈጠረው አሻጥር ያው የታወቀውን የቆሸሸ የብሔር ግጭት ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በኦሮሞነቱ ብቻ የሚደግፉትና በተለይም በኦሮሞ የበላይነት “ርእዮተ-አለም” የተመረዙት አክራሪ የኦሮሞ ወጣቶች አማራ ላይ ያላቸውን ጥላቻ ጠንቅቆ ያውቃል። ይሄንንም በመጠቀምና የጥላቻን እሳት በማቀጣጠል ሠራዊቱን በአማራ ክልል ስላዘመተ፡ ፋኖ ራሱን ከተቃጣበት ጥቃት ህዝቡን እንዲከላከል ተገድዷል።

ወጣት ሞላ መላኩ ፋኖን የተቀላቀለው በ2014ቱ የወያኔ ወረራ ጊዜ ነበር። ወንድሙ እንደገለጸው፤ ሞላ መላኩ በወረራው ጊዜ በተፈጸመው ጭፍጨፋ፣ አሰቃቂና መጠነ ሰፊ የሆነ የሰብአዊ-መብቶች ጥሰት ጥልቅ የሆነ ሃዘን ተሰምቶት ነበር፤ ለዚህም መነሻ ነው ብሎ ያምን የነበረው በተግባር የተተረጎመው የብሔር ፌደራሊዝምን ነበር። የተለያዩ ታጣቂ ብሔርተኛ ቡድኖች በአማሮች ላይ የፈጸሟቸው አብዛኛዎቹ የጅምላ ጭፍጨፋዎች በዜና እንኳን ሳይነገሩ እንዲሁ በጸጥታ የታለፉ ናቸው። ሞላ በኖረበት አካባቢ በስፋት፤ በብሔር ጥላቻ ላይ ያተኮሩ ጥቃቶች መደረግና የጅምላ መቃብሮች መገኘት በየሳምንቱ የሚነገሩ መርዶዎች ነበሩ።

ፋኖዎች የወያኔን ወረራ ለመመከት ላደረጉት የጀግንነት ተጋድሎ አልተሸለሙም አልተሾሙም። የአብይ አህመድ መንግሥት ትኩረት የፋኖ ተዋጊዎችንና የአማራ ልዩ ኃይልን ትጥቅ ማስፈታት ብቻ ነበር። ይህ ድርጊት ነበር በሞላ መላኩ ዘንድ በመንግሥት የመከዳት ስሜት እንዲፈጠር ያደረገው፤ ብሎም ሥርአቱ የማይታመን፣ ዘረኛና የአማራን ሕዝብ ህልውና አደጋ ላይ የሚጥል ነው ብሎ በመደምደም ወደ ፋኖ እንዲመለስ ያነሳሳው። ከመሰዋቱ በፊት ለስምንት ወራቶች የመንግሥትን ኃይል ወደ ኋላ የመመለስ ተጋድሎ አድርጓል።

የትግል አጋሮቹ እንደሚገልጹት በወኔው፣ በቆራጥነቱና ባልበገርባይነቱ የብዙዎች ምሳሌ ነበረ። በቀኝ ጀርባው ተመትቶ እስኪወድቅ ድረስ ታናሽ ወንድሙ እስከመጨረሻው ከጎኑ አልተለየውም። ይሄ የሆነው ከኦሮሞኛ ተናጋሪ ወታደሮች ጋር በተካሄደ የጦፈ ፍልሚያ ነበር። ታናሽ ወንድሙ [አድሞ መላኩ] ቁስለኛ ወንድሙን በጀርባው አዝሎ ወልዲያ ሆስፒታል አድርሶታል። እድል አግኝቼ ያናገርኋቸው የፋኖ ታጋዮች እንዳሉት፤ ሞላ ከመቁሰሉ በፊት በርካታ ወታደሮችን ጥሏል። የማይበገረው ቆራጥነቱ በጓዶቹ ዘንድ ክብር ሰጥቶታል። ያሰበውንና የጀመረውን ሁሉ በሙሉ ልብና ጽናት የሚፈጽም ሰው እንደነበረ ወንድሙም አረጋግጦልኛል።

ከብዙ አመታት በፊት በሽህ የሚቆጠሩ ኪሎሜትሮችን በእግሩ ተጉዞና በትንሽ ጀልባ ቀይ ባህርን ተሻግሮ ሳውዲ አረቢያ በመድረስ፤ የተለያዩ ሥራዎችን ሲሠራ ከቆየ በኋላ በጤና ጉድለት ምክንያት ወደ አገሩ ተመልሶ እንደገባም አድሞ አጫውቶኛል። ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት ብቸኛ እናቱንና ቤተሰቡን በእርሻ ሲረዳ ቆይቷል። ከጦርነቱ በኋላም ባለፉት ሶስት አመቶች ከፋኖነቱ ጎን ለጎን፤ እየተመላለሰ ቤተሰቡን በእርሻ ሥራ መርዳቱን አልተወም ነበር። የአብይ አህመድ ወታደሮች ያለምንም እርህራሄ ከብቶችን በሙሉ ነድተው፣ የጎተራ እህልም ሆነ ማዳበሪያ ጠራርገው ዘርፈው ሲሄዱ ሞላ በአይኑ አይቷል።

ሞላ፡ በወንድሙ ጀርባ ታዝሎ ሆስፒታል ከደረሰ በኋላ የተለያዩ የህክምና ርዳታ መስጫዎች ተሰክተውለት፤ እናቱ ከጎኑ ሳይጠፉ ክትትል ተጀምሮለት ነበር። ሆኖም ግን፤ “በጦፈው ፍልሚያ ላይ ጀብዱ የሠራ ፋኖ ወጣት ህክምና ላይ ነው” የሚል መረጃ ተሰራጭቶ ኖሮ፤ ሆስፒታሉን ኦሮሞኛ ተናጋሪ ወታደሮች በመውረር ፈትሸው ሲያገኙት፤ የእርዳታ መሳሪያዎቹን በጣጥሰውና ሰባብረው፤ እናቱን አንገላትተውና የህክምና ባለሙያዎችን ክብር ነስተው ወዳልታወቅ ቦታ ይዘው በመውሰድ አንገቱን እንደቆረቱት ተሰምቷል። ከታላቅ ወንድሙም የሰማሁት ይሄንኑ ሲሆን፤ ከሌላ ምንጭ ደግሞ የወታደር መኪና በአስከሬኑ ላይ እንደተነዳበትም ሰምቻለሁ። ቃላት የማይገልጸው አረመኔነት ነው የሚፈጸመው!

ሞላን ከሆስፒታል ይዘውት ሲሄዱ በአማራነቱና በአሳምነው ጽጌ ብርጌድ ባልደረባነቱ እንደሚኮራ ሲናገር ተሰምቷል። ሊገድሉ ጎትተው ሲወስዱት ቅንጣት ፍርሃት አልታየበትም። ይልቁንም ያመነበትን እና እስከመስዋእትነት የዘመተበትን አላማ በመፈክርነት ጩሆ ያሰማ ነበር። ለመኖር ብሎ አልዋሸም። በተያዘበት የጭንቅ ደቂቃዎች “አዎን ፋኖ ነኝ!” ነበር ያላቸው። ሀሞተ-ክቱ ሞላ መላኩ አልተፍረከረከም። በማያውቀው ቋንቋ እየተውረበረቡ ሲይዙት ምህረት እንደማይደረግለት ጠንቅቆ ያውቃል። “አማራ ያሸንፋል! ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!” የሚሉ መፈክሮችን ሲያሰማ ግን ምድር ያርድ ነበር። ገዳዮች ቋንጃቸው እየተብረከረከ ነው ወደ ልዩ ቦታ የወሰዱት። በህክምና ላይ ያለውን ቁስለኛ ለመያዝ ብረት ለብሶ እና እስከ አፍንጫው ታጥቆ የዘመተው ወታደር፡ ሞላን ባዶ እጁን እንኳን ይፈራው ነበር።

“አወ ፋኖ ነኝ!” የሚል መልስ ሲሰጣቸው ዐይን የሚያንሸዋርር የጆሮ መብረቅ ነበር የመታቸው። እነርሱ ምስኪን ንጹን ዜጎችን እንደ አደን እንስሳ እያሳደዱ መግደል እንጅ ከተዋጊ ፊት ቀርበው ጀግናን በድምጹ ሰምተውት አያውቁምና ሊተኩሱበት አቀባብለውም ተጨማሪ ኃይል በአየርና በባህር ካልተጨመርላቸው በስተቀር የዚህን ጀግና በቁጥጥር ስር መዋል ማመን አልቻሉም ነበር። የመከላከያው ብርጌድ በሞላ መላኩ ላይ ጥይት ተኩሶም ፍርሀቱ ስላልወጣለት፡ ጀግናውን ፋኖ እንደገደለ ለተጨማሪ ማረጋገጫ አንገቱን ቆርጧል። በዚህም አላበቃም። የቆራረጡትን ሰውነቱን አስፋልት ላይ አድርጎ መኪና ነድተውበታል። በዚህ ያሉበትን በማያውቁበትና የሚያደርጉትን በማያስተውሉበት ደረጃ ደንግጠው በነበረ ሰአት፡ የሚያስታውሱትን ሰው የሚገድል ነገር በሙሉ ፈጽመውበታል። በዚህ ልክ ሙሉ የመንግስት ጦርን ያሽመደመደና አቅል ያሳተ ሌላ  የገድል ታሪክ ሰምቼ አላውቅም።

መከላከያ ሰራዊት ተብየው በሰጠመበት ፍርሀት ውስጥ የሚይዘውን የሚጨብጠውን ያጣበት፥ የሚችለውን ያህል የተደነባበረበትና የተንቦጫቦጨበት ከፍተኛ ድንጋጤ ነው። ሞላ መላኩ የተሰዋበት ሁኔታ ፈጽሞ የወታደራዊ እርምጃ መልክ የለውም። የቡከን ፈሪ እና ድንጉጥ አቅመቢስ እርምጃ ነው። የገደሉት መሆኑንም ለማመን ምናልባት ሳምንት ወስዶባቸው ሊሆን ይችላል። ከፍርሃትና ከድንጋጤ የተነሳ ደመነፍስ የነበሩት ወታደሮች ለመረጋጋት ሳምንትም ከበቃቸው! ፋኖን በዚህ ደረጃ እየፈሩት ለምን እንደሚገጥሙት ግን ይገርመኛል። በእርግጥ የዘመቱት የአገዛዙ ሰራዊት በሙሉ በሚባል ደረጃ  ሙትና ምርኮኛ ሁነዋል። ምናልባትም ይህ ሊሆን ይችላል ፍርሃታቸውን ያባባሰውና የአስከሬን አንገት ቆርጦ ድጋሜ በመኪና እስከመግጨት ያደረሳቸው።

ይህን ክስተት በአደባባይ የተመለከተው ህዝብ ታዲያ የሚዛን ዘንጉ በእጁ ነውና አንድ ፋኖ ከአንድ ብርጌድ መከላከያ ጋር ተመዛዝኖ ሚዛን ሲደፋ አዬ። ጀግንነት በጦር መሳሪያ ብዛትና ትልቅነት እንደማይገኝ ታዬ። ጀግንነት መንፈሳዊ ነገር መሆኑን ሞላ መላኩ ባዶ እጁን በገዳዮቹ መዳፍ ገብቶ አሳየ። ፋኖነት እስከዚህ ግፍ ጽዋ ለመጋት ወስኖ መነሳት እንደሆነ አስመሰከረ። በቃላት ብቻ፡ ማንነቱን በመናገር ብቻ ሰራዊቱን አጓሸው። ለእውነትና ለማንነት የሚከፈል የህይወት ዋጋ ጽድቅ መሆኑን የታዘበው ህዝብም የሙያ ማንነት ሳይለያየው በአንድነት ወገነለት። የዚህ ጀግና አሟሟት በመቶዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች፣ ሃኪሞችን ጨምሮ የፋኖን ትግል እንዲቀላቀሉ አነሳስቷል።

ጥንትም ዛሬም የፋኖ መነሻው የፍትህ መጥፋት መሆኑን የሞላ ታሪክ ይመሰክራል። ሞላ ጀግና ተዋጊ ብቻ አልነበረም፤ አገሪቷ የምትገኝበትን አደጋ በጥልቅ በመረዳት ማስረዳት የሚችልም ነበር። ፋኖነት እንዲሁ  አሻፈረኝ ባይ ታጣቂነት ብቻ ሳይሆን፤ ፋሽስታዊ ጎሰኝነትን፣ ጠባብ ብሔረትኝነትን፣ አፓርታይድን፣ የአገር ውስጥ ቅኝ-ገዥነትንና ማንኛቸውንም በውሸት ህጋዊ አዋጆች የተደገፉ የፖለቲካ ሙሰኝነቶችን አጥብቆ የሚጠላ ምሁራዊ እንቅስቃሴ ነው። የሚያቀነቅነውም፤ ሕዝብን ማገልገልን፣ አገር-ወዳድነትንና ለመላው አገራችን መልካም ራእይን ነው። የሚያውቁት እንደሚናገሩት ሞላ መላኩ እነዚህን መርሆዎች የተከተለ ፋኖ ነበር።

የዛሬው የፋኖ ንቅናቄ ገጽታ፤ በጣሊያን ወረራ ጊዜ ኢትዮጵያዊያን ተባብረው ለነጻነት ያደረጉትን ተጋድሎና የተመዘገበውን የፋኖን ጀግንነትም ያስታውሳል። የዛሬው ንቅናቄም ራሱን የዚያን ዘመኑ ትግል ወራሽ አድርጎ ነው የሚያየው፤ የተለያዩ ኢትዮጵያዊያንም ይሄንን በመደገፍ ግፍና ፍትህ-አልባነትን ለመቋቋም ስለመታገል ግጥም ገጥመው ሲዘፍኑ ይሰማል። ስለ ሞላ መላኩም ገና ይዘፈናል፥ ይሸለላል።

ያለ ምንም ክፍያና በአነስተኛ መተዳደሪያ እየኖረ ራሱን አስታጥቆ የሚንቀሳቀስ ወዶ ዘማች ቢሆንም፤ ኢትዮጵያን ለመበታተንና አማራን ለማጥፋት በሚካሄደው ጦርነት ላይ፤ ፋኖ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል ኃይል መሆኑን እያስመሰከረ ነው። በአማራ ክልል ውስጥ በተሰገሰገው የጠላት ኃይል ላይ በርከት ያሉ ተስፋ ሰጭ ድሎችንም አስቆጥሯል። ጠላት የትም ቢገባና ምንም ያህል ጠንካራ መከለያ ለራሱ ቢገነባም፤ የአማራ ሕዝብ ደህንነት እስኪረጋገጥና የፋሽስት ኃይሎች በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የሚያወርዱት ስቃይ እስኪያበቃ ድረስ ፋኖ የሚያደርገውን ተጋድሎ በጽናትና በጀግንነት ይቀጥላል። ፋኖዎች ለዝና ሳይሆን ሕዝባቸውን ከጥፋት ለማዳን ስለሚዋጉ የተፈሩና የተከበሩ ተዋጊዎች ናቸው። ስነ-ልቦናቸው የአማራን ማንነትና ኢትዮጵያን ጠባቂነትን ያንጸባርቃል።

ለራሱ መሰሰት የማያውቀውንና ለወገንና ለአገር የተሰዋውን ሞላ መላኩ ለማወደስ፤ ከትውልድ ትውልድ የሚሸጋገሩና ምንጊዜም የማይጠወልጉ የፈኩ አበቦች ተተክለዋል። ጀግኖቻችን፤ በተወለዱበት በቀያቸው በሰላም ባረፉበት እንድናስባቸው፤ ምሽቱም ሆነ ንጋቱ የሰላም እረፍታቸው በዋሽንት ይዜማል። የሞላ መላኩ እና የሌሎቹም የፋኖ ሰማእታት ሕይወት የምናወድስበት የመታሰቢያ ቀን ይሰየማል። ግና የትኛው የሙዚቃ ቅላጼ፤ የቱ ሽለላና ሙገሳ፥ የትኛውስ ሀውልትና መታሰቢያ ለመላው የአማራ ሕዝብ የከፈሉትን መስዋእትነት ይገልጽ ይሆን? ስንትስ ገና ያልታወቁ መሰዋታቸውም ያልታወቀ በበረሀና በጥሻ ውስጥ የቀሩ ይኖሩ? ለእነዚህ ሁሉ ጀግኖቻችን የምስጋና ቦታውስ የት ይሆን? ኗሪ ስንት እዳ አለበት! ሰማእታቱማ ዐረፉ።

ስለዚህ ወንድማችን ዛሬ ላይነሳ ተኝቷል። ያልተዘፈነለት ጀግና፤ ሀብትም ዝናም ያልነበረው፤ ግን የብዙዎች ሕይወት ላይ ተጽእኖ ያሳረፈ፣ ለበርካታ ወጣት ፋኖዎች መነሳሳት ምክንያት የሆነ፤ ከዚያ በላይ ደግሞ የተከበረ ሕይወት የኖረ ሀቀኛ ሰው።

ሞላ መላኩ እንደማንኛውም ሰው አልነበረም። በርካታ ለመማረር የሚያበቁ ችግሮችን አሳልፏ። በገዛ አገሩ ብዙ መከራ አይቷል፤ በጎረቤት በአካባቢው፣ በክልሉ የበርካታ አማሮች ሕይወት በግፍ ተቀጥፏል። ይሄ ሁሉ ሆኖ በሰላሳ አራት አመቶቹ አንድም ጊዜ ለራሱ አድልቶ ሲያማራር ሰምቶ እንደማያውቅ ታላቅ ወንድሙ ይመሰክራል። እውነተኛ ያልተዘመረለት ጀግና!

Girma Berhanu (Professor) teaches at the Department of Education and Special Education,
University of Gothenburg, Sweden. He can be reached via e-mail : [email protected]

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

የድሮ መሪዎች ያላደረጉትን ምሁር ጳጳሳቱ ያላስተዋሉትን ከፈረሰች ጎጆ ከባልቴት ቤት ገብቶ ክብሩን ዝቅ አድርጎ ውሀዋን ጠጥቶ ምግቧንም ተጋርቶ ያላለቀሰ ሰው ያንን ትይንት አይቶ ማን ይኖራል ከቶ? በዉሸት ፈገግታ ፊቱን አስመስሎ ፀሀይ የበራበት

ሰው በሰውነቱ – ከ ይቆየኝ ስሜ

የአማራ ፋኖ በጎጃም ምክትል የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ የነበረው እና አሁን ላይ በአማራ ፋኖ በጎጃም የሁለተኛ (ተፈራ ) ክፍለጦር ሰብሳቢ የነበረው ፋኖ ዮሐንስ አለማየሁ በክብር ተሰዋ። የአማራ ህዝብ የተጋረጠበትን የህሎና አደጋ ለመቀልበስ ያለ

ከአማራ ፋኖ በጎጃም የተሰጠ የሐዘን መግለጫ ታጋይ ይሰዋል ትግል ይቀጥላል !

January 22, 2025
ዳግማዊ ጉዱ ካሣ “ይድረስ ለእገሌ” ማለቱ ሰለቸኝና ተውኩት እንጂ ዛሬም መጻፍ የፈለግሁት የአማራን ዕልቂት ለመታደግና የኢትዮጵያን ትንሣኤ ለማብሰር እየተዋደቁ ላሉት ወገኖቼ ነው – በፋኖም ይሁን በሌላ ስም፡፡ ኢትዮጵያን ወደቀደመ ክብሯ ለመመለስ የነገድና

ጀልባዋ አትሰምጥም፤ የሚሰምጥ ግን አለ!

[ማስታወሻ ከፍል አንድ፣ በዘሐበሻ ድረ ገጽ ላይ ኦፍ ጃዋር አንድ ኢትዮጵያ ተብሎ በእንግልዝኛ ወጥቷል] (https://zehabesha.com/of-jawar-and-ethiopia/) ባለፈው ሰሞን፣ ጃዋር መሐመድ ከደረጀ ኃይሌ ጋር  በነገራችን ላይ ክፍል ሁለት ባደረገው ቃለ ምልልስ ላይ ተመስርቼ ገንቢ አስተያየት ጽፌ በኢንግሊዝኛው ዘሐበሻ ድረ ገጽ ላይ አሳትሜ ነበር። አስተያየቴ በዚህ ቃለ ምልልስ

ስለ ጃዋርና ኢትዮጵያ (ክፍል ሁለት)

January 20, 2025 ጠገናው ጎሹ የአቤ ጎበኛው አልወለድም ለወገኖቹ መብት መከበር ሲል ባደረገው ጥረት ምክንያት እንደ ወንጀለኛ ተቆጥሮ ይሙት በቃ በፈረዱበት ጊዜ በምላሳቸው መልካም  አድርጎ ስለ መገኘት እያወሩ በድርጊት ግን ተቃራኔውን የሚያደርጉ ሁሉ

ወዮ ለመከረኛው የአገሬ ህዝብ እንጅ  ታየማ ታየ ነው

መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ “ ሰው የሰነፎችን ዜማ ከሚሰማ ይልቅ የጠቢባንን ተግሣጽ መስማት ይሻለዋል። ”   — መክብብ 7፥5 እስቲ ቆም ብለን በማሰብ  ራሳችንን እንፈትሽ ።  እንደ ሰው ፣ የምንጓዝበት መንገድ ትክክል ነውን ? ከቶስ ሰው መሆናችንን እናምናለንን ? እያንዳንዳችን ሰው መሆናችንን እስካላመንን ጊዜ ድረስ ጥላቻችን እየገዘፈ

 ለሀገር ክብርና ብልፅግና ብለን ፤ ቆም ብለን በማሰብ ፤ ህሊናችንን ከጥላቻ እናፅዳ

                                                         ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)                                                       ጥር 12፣ 2017(January 20, 2025) ጆ ባይደን ስልጣናቸውን ለማስረከብ ጥቂት ቀናት ሲቀራቸው በአሜሪካን ምድር በጣም አደገኛ የሆነ የኦሊጋርኪ መደብ እንደተፈጠረና፣ የአሜሪካንንም ዲሞክራሲ አደጋ ውስጥ ሊጥለው እንደሚችል ተናግረዋል።  ጆ ባይደን እንዳሉት በተለይም በሃይ ቴክ

አሜሪካ ወደ ኦሊጋርኪ አገዛዝ እያመራ ነው! ጆ ባይደን ስልጣን ለመልቀቅ ጥቂታ ቀናት ሲቀራቸው የተናዘዙት!!

Go toTop