October 22, 2023
5 mins read

የዳግማዊ አጤ ምኒልክ መታሰቢያ ሀውልት የቆመው/የተተከለው ከዛሬ 93 ዓመታት በፊት ጥቅምት 22 ቀን 1923 ዓ.ም ነበር፡፡

ጥቅምት 22 ቀን 1923 ዓ.ም

በዛሬዋ_ዕለት

398544306 884596386632416 2617273651797652080 nከ 93 ዓመት በፊት ልክ በዛሬዋ ቀን የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የንግሥ በዓል ዋዜማ ፤ የንጉሠ ነገሥት የዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ ሐውልት በመናገሻ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን አጠገብ ፤ ለበዓል የመጡት እንግዶች በተገኙበት ሥርዐት፣ የሐውልቱን መጋረጃ የመግለጥ ክብር ለብሪታንያ ንጉሥ ወኪል ለ(ዱክ ኦፍ ግሎስተር) ተሰጥቶ ሐውልቱ የተመረቀበት ዕለት ነበር።

ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ምኒልክ የአባታቸውን የዳግማዊ አጤ ምኒልክን ስራና ውለታ ቀጣዩ ትውልድ ያስበውና ይዘክረው ዘንድ … ማስታወሻ የሚሆን የመታሰቢያ ሐውልት ለማሰራት አሰቡ፡፡

ሐውልቱንም በጀርመናዊው መሃንዲስ ሙሴ ሄንትል አማካኝነት አስጠንተው፤ ከጀርመን ተቀርፆ እንዲመጣ አዘዙ፡፡ ሀውልቱ የተመደበለት ቦታ ተደልድሎ ከተዘጋጀ በኋላ ገና ሳይተከል/ሳይቆም ንግሥቲቱ መጋቢት 22 ቀን 1922 ዓ.ም አረፉ፡፡

በመሆኑም የንግሥቲቱን እረፍት ተከትሎ ንጉሰ ነገሥት ለመሆን እየተዘጋጁ የነበሩት አልጋ ወራሽ ንጉሥ ተፈሪ መኮንን፣ ከዛሬ 93 ዓመታት በፊት (ጥቅምት 22 ቀን 1923 ዓ.ም) ሐውልቱ በታላቅ ክብረ በዓል እንዲተከል አደረጉ፡፡

በሐውልቱ ላይ አፄ ምኒልክ ካባ እንደለበሱ አንባር አጥልቀው በእጃቸው ጣምራ ጦር ይዘው በፈረሳቸው በ‹አባ ዳኘው› ላይ ተቀምጠው በግርማ ሞገስ ይታያሉ፡፡ የሐውልቱ ቁመት ከተፈጥሮ አካላዊ መጠን በላይ ሲሆን ‹አባ ዳኘው› ፊቱን ወደ ሰሜን መልሶ በኋላ እግሮቹ ቆሞ፣ የፊት እግሮቹን ወደላይ አንስቶ ይታያል፡፡ ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅት በ 1929 ዓ.ም ወድቆ/ፈርሶ ነበር፡፡

ብርሃኑ ድንቄ ‹‹የአምስቱ የመከራ ዓመታት አጭር ታሪክ›› በሚለው መጽሐፋቸው ጣሊያኖች የአፄ ምኒልክን ሐውልት እንዴት እንዳፈረሱት እንደሚከተለው ገልፀውታል፡፡ ‹‹ … በቅድሚያ ሐውልቱ ያለበትን አካባቢ ረጅም እንጨት እየማገሩ በቆርቆሮ ሲያጥሩ ሰነበቱ …. ይህንን ያየው የአዲስ አበባ ሕዝብ ‹‹ሊያፈርሱት ነው›› ብሎ እርስ በእርሱ በሐዘን መነጋገሩን ቢሰሙ ‹‹ልናድስ›› ነው ብለው አስወሩ፡፡ ሁሉንም ነገር ካመቻቹ በኋላ ግን በየበሩ በታንክ ጭምር ጥበቃ አጠናክረው … ወደ ማታ የአራዳን አካባቢ በታንክ አጥረው በባውዛ ሌሊቱን ከተማውን እየተቆጣጠሩ በሌላ ኃይል ደግሞ ሐውልቱን ሲያፈርሱ አድረው ሲነጋጋ ወደ አልታወቀ ቦታ ወስደው ቀበሩት፡፡ ሕዝቡ እድሜና ፆታ ሳያግደው ሐዘኑን ይገልጽ እንደነበር አዛውንቶች ይመሰክራሉ …

በጊዜው የአዲስ አበባ ነዋሪ የነበረው የሃንጋሪው ዶክተር ላዲ ስላስ ላቫ እንደፃፈው፣ ሐውልቱ ከፈረሰበት ቦታ ቆመው ያለቅሱ የነበሩትን ሰዎች የጣሊያን ወታደሮች በኃይል ይበትኑ እንደነበር ገልጿል፡፡

በሌላ ዘገባ ደግሞ አንድ ሕፃን ልጅ ሲያለቅስ ጣሊያኖች ደርሰው ለምን እንደሚያለቅስ ቢጠይቁት ‹‹የንጉሱን ምልክት ስላወረዳችሁ ነው›› ብሎ እንደመለሰላቸውና ጣሊያኖችም ከሙሶሊኒ ሌላ ንጉሥ እንደሌለው በመንገር ልጁን ገርፈው እንዳባረሩት ተገልጿል፡፡ ጣሊያኖች ሐውልቱን ካፈረሱ በኋላ ሰው ሳያይ ሸፍነው በመውሰድ በታላቁ ቤተ-መንግሥት አዳራሽ ጀርባ ቀበሩት …››

የፋሺስት ወራሪ ኃይል ከኢትዮጵያ ከተባረረ በኋላም፣ ሐውልቱ ከተቀበረበት ቦታ ወጥቶ እንደገና ታድሶና ተጠግኖ ሚያዝያ 27 ቀን 1934 ዓ.ም ቀድሞ በነበረበት ቦታ እንዲቆም ተደረገ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም፣ በ1988 ዓ.ም የአድዋ ድል መቶኛ ዓመት ሲከበር ሐውልቱ ጥገና ተደርጎለት እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

#ታሪክን_ወደኋላ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop