“ድንቅ ” ሌክቸር!

T.G (ጠገናው ጎሹ)

 

“ምነው እሸቱን   ለቀቅ አድርገው እንጅ” ከማለት ጀምሮ የውግዘትና የመርገም ናዳ ሊያወርዱ የሚችሉ ወገኖች ቁጥር ቀላል እንደማይሆን በሚገባ እረዳለሁ። ለዚህ ያለኝ ምላሽ  ይህ አስተያየቴ ህዝብ ከሚገኝበት ፖለቲካ ወለድ  አስከፊ፣ አስጨናቂና አሳፋሪ  ሁኔታ አንፃር ሲታይ አንዳንድ የእሸቱ አስተሳሰቦችና አካሄዶች ሚዛናዊነትን ወይም የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረትን የሳቱ በመሆናቸው ላይ እንጅ ከእሸቱ የግል ሰብእና፣ ህይወት፣ አስተሳሰብና አመለከካት ፣ አኗኗር፣ እምነት፣ ወዘተ ላይ ፈፅሞ አይደለምና አይጭነቃችሁ የሚል ነው።

 

“አይ በምንም ሁኔታ እሸቱንና መሰሎቹን መተቸት ጭፍን ጥላቻና ጨለምተኝነት ነው” ከሚል የድንቁርና ወይም የየዋህነት ተሟጋችነት ጋር ግን ፈፅሞ አልስማማም። አገርን ወይም ህዝብን አስመልክተን በምንሰጠው ሃሳብና በምናደርገው ድርጊት ውስጥ የተሳሳተ ወይም የተንሻፈፈ ወይም በመሬት ላይ ያለውን ግዙፍና መሪር እውነታ እንደሌለ ቆጥሮ በስሜት እየጋለበና እያስጋለበ መሠረታዊና የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረትን ከሚጠይቀው የጋራ ጉዳያችን ሊያንሸራትተን የሚችለውን መንገድ በሂሳዊ አስተያየት መሞገትንና መሟገትን መልመድ አለብን የሚል ፅዕኑ እምነት አለኝ።

 

እሸቱ መለሰ “ውድ ወገኖቼ የመጨረሻ ቃሌን ስሙኝ” በሚል (10/21/23) ያቀረበውን ቪዲዮ ተከታተልኩት ።  “እኔ ስኬታማ እንደሆንኩ ስኬታማ ለመሆን ከፈለግህ  ቁጭ ብለህ አታማር” ይላል የቪዲዮው ሌክቸር ።  እንደ አጠቃላይ እውነት (general truth) ሌክቸሩን መቀበል አያስቸግርም። የዚህ አይነቱ ዲስኩር  ወይም ሌክቸሩ ችግር ግልፅ የሚሆነው ከአጠቃላይ እውነትነት አልፈን በፖለቲካ ወለድ ወንጀል ክፉኛ ወደ ተበከለው የመሬት ላይ እኛነታችን አውርደን ከምር ለመረዳት ስንሞክር ነው።

 

ትውልድ ገዳይ በሆነ ሥርዓት ተሰቅዞ የተያዘውን ትውልድ ምንም ጥረት እንደማያደርግ (“ድዱን በማስጣት የሚደሰት እንደሆነ “) ፣ የፈጣሪውን ሃያልነትና ርዳታ የማይጠይቅ እና የማያውቅ እንደሆነ፣ ምንም አይነት የፈጠራ ፍላጎትና ችሎታ እንደሌለው ፣ ወዘተ አድርጎ ለማሳየት የሞከረበትን ሌክቸር በጥሞና ለሚገመግም ወገን ይህ ትውልድ በምንምና እንደምንም (by any means) ራሳቸውን ስኬታማነት ላይ ያገኙና የሚያገኙ ግለሰቦችና ቡድኖች አንደበት መፍቻና መሠልጠኛ እየሆነ እንደሆነ ለመረዳት አይከብደውም።

 

ስኬትን እጅግ ፈታኝ ከሆነው ነባራዊው እውነታ ውጭ የሚገኝ ጉዳይ እንደሆነ አድርገው ሌክቸር  እንስጣችሁ የሚሉ ወገኖችን ለምንና እንዴት ሳይሉ የአድናቆት ግትልትል ማግተልተል በእጅጉ የሚሳሰብ ጉዳይ ነው ። ለዘመናት በመጣንበትና አሁንም በባሰ አስከፊነት  በምንገኝበት የፖለቲካ ሥርዓት ሥር ሆነንም “ስኬት በስኬት ለመሆን የሚግደን ነገር የለም” ብሎ መቀበል  ልክ የሌለው ድንቁርና ወይም እያወቁ አሳሳችነት ነው። ለፈጠራ እና ለስኬት ምቹ ሁኔታን ከመፍጠር ይልቅ ተቃራኒውን የሚያደርግ ሥርዓተ ፖለቲካ ሥር በሰደደበትና በተንሰራፋበት ሁኔታ ውስጥ “ከፈለጋችሁና ከጣራችሁ እንደ እኔ ስኬት በስኬት ትሆናላችሁ”  የሚልን ስብከት ለመረዳትና ለመቀበል  በእጅጉ ያስቸግራል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የትግራይ ጉዳይ፤ በረከተ መርገም - ሰማው በላይነህ!

 

እጅግ አስከፊ በሆነ የፖለቲካ እውነታ (tragic political reality) ውስጥ የራስን ስኬት በምሳሌነት ወስዶ ጥረት ላደረገና ለሚያደርግ ሁሉ በጣም የሚቻል እንደሆነ ሌክቸር ማድረግ አጠቃላይ እውነትን በተወሰነ ጊዜና ሁኔታ ውስጥ ከሚገኘው መሪር እውነታ ጋር እየቀላቀሉ “እውነታው ይህና ይህ ብቻ ነውና በፈጣሪና በእኔ ይሁንባችሁ እመኑኝ” ማለት ወይ የአስተሳሰብ ቁንፅልነት ወይም ግብዝነት ወይንም ደግሞ ግልብ ስሜትን በመኮርኮር የሶሻል ሚዲያ ንግድን የማሳለጥ  ዘዴ  ነው የሚሆነው ።

 

ከነፈተናውም ቢሆን ጥረት ማድረግን ማበረታታት አንድ ነገር ነው። ጥረትንና ስኬታማነትን የሚገድል ሥርዓተ ፖለቲካ የመኖሩን ነባራዊ ሁኔታ ተረድቶ ይህንኑ እንዴት መቋቋም ወይም መጋፈጥ እንደሚቻል ምንም አይነት ቃል ሳይተነፍሱ የራስን ስኬት ለሁሉም የሚሠራ ተምሳሌት እያደረጉ ሌክቸር ማድረግ ወይ ድንቁርና ወይም የሁሉን አውቃለሁ ግብዝነት ወይንም ልክ የሌለው የግል ዝና እና ስኬት ፍለጊነት ነው።

 

የጥረትና የፈጠራ በሩን ያለ መራር ትግል እንዳይከፈት አድርጎ የዘጋውን የእኩይ ፖለቲካ ሥርዓትን የማስወገዱ ጥረት ስኬታማ እስካልሆነ ድረስ ስኬት የአገርና የብዙሃኑ መሆኑ ይቀርና የተወሰኑ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ይሆንና እነርሱንም የአድርባይነት ወይም የርካሽ ህዝበኝነት ሰለባ በማድረግ የባርነት ዘመንን ያራዝማል። ለዚህ ነው እንደ እሸቱ አይነቱን የስኬታማነት ሌክቸር ካላስፈላጊ ይሉኝታ ወይም እጅግ ከተጋነነ ሙገሳ ወጥቶ ሂሳዊ በሆነ ምልከታ ማየትና ማሳየት ተገቢና አስፈላጊ  የሚሆነው።

 

ይህ ትውልድ መወቀስም ካለበት የራሱን የነፃነትና የፍትህ ታሪክ በመሥራት ችሎታውንና እውቀቱን ተጠቅሞ ለራሱም ሆነ ለአገሩ ስኬትን ለማላበስ የሚያስችል አመች ሁኔታ (favorable environment) ለመፍጠር ባለመቻሉ እንጅ በወንጀለኛና በሙሰኛ ሥርዓት ሥር እየጓጎጥክም ቢሆን ለምን እንደ እኔ/እንደ እኛ ስኬት በስኬት አልሆንክም በሚል የግብዝነት አቀራረብ መሆን አልነበረበትም ። መሆንም የለበትም።

 

እሸቱ ሃይማኖታዊ እምነትን ከገሃዱ ዓለም ማህበራዊና ሥነ ልቦናዊ እይታ ጋር እያቀላቀለ ባቀረበው ሌክቸር ውስጥ ለዘመናት የዘለቀውና በአሁኑ ወቅትም በእጅጉ አስከፊና አስፈሪ እየሆነ የቀጠለው የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ እንኳንስ የአኗኗር ስልትን በአዳዲስ ፈጠራ ለማሻሻል የእለት እንጀራን አሸንፎ በህይወት መቆየትን በእጅጉ ፈታኝ የማድረጉን መሪር እውነታ አንድም ቦታ ላይ ሳት ብሎት አላነሳም (አልጠቆመንም) ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ከ400 በላይ የተባባሩት መንግስታት ድርጅት መኪናዎች ለጦርነት ሲውሉ የት ነበራችሁ?- ዜጠኛ ሄርሜላ አረጋዊ

 

እሸቱ ይህንን በራሱ ስኬታማነት ከልክ ባለፈ የተለጠጠውን (የተጋነነውን) ሌክቸሩን እያስደመጠን ያለው የ12ኛ ክፍል መለቀቂያ ፈተና ከወሰደው ከ8 መቶ ሽ በላይ የዚህ ወጣት ትውልድ አባል 3+ % ብቻ እንዲያልፍ በማድረግ ከፍተኛ የትውልድ ገደላ በተደረገበት እና ትውልድ በሞላ አስከፊ ተስፋ መቁረጥ ውስጥ በሚገኝበት መሪር ወቅት ነው። ይህንን የፖለቲካ ወለድ ወንጀል ውጤት የሆነውን እጅግ አስከፊና አስደንጋጭ እውነታ አሳምሮ የሚያውቀው እሸቱ ግን “ከራስ ስንፍና ካልሆነ በስተቀር” ስኬታማነት የሚቻል መሆኑን ከእርሱ እንድንማር 1ኛ ፣ 2ኛ ፣ ወዘተ እያለ በጠቀሳቸው ማሳያዎቹ ይነግረናል/ይሰብከናል።

 

ለነገሩ በተወሰነ ሙያና በሆነ አጋጣሚ ስኬታማነትንና ታዋቂነትን ማግኘት ማለት ሃይማኖታዊ እምነትን ጨምሮ ሁሉንም ያወቅን እየመሰላቸው ከእኛ ወዲያ ላሳር የሚሉ ወገኖችን አደብ ግዙ ከማለት ይልቅ በየአዳራሹ፣ በየአደባባዩ ፣ በየሶሻል ሚዲያውና በየአጋጣሚው ወደ አምልኮ የሚጠጋ ሙገሳ ለጋሾች ሆነን ለመቀጠል ፈቃደኞች እስከሆን ድረስ  የእነርሱ ስኬት የሌላውም ስኬት ሊሆን ያልቻለበትንና የማይችልበትን ነባራዊና  መሪር  ሁኔታ ግምት ውስጥ ሳያስገቡ የስብከት  አተላ  ሊግቱን ቢቃጣቸው የሚገርም አይደለም።

 

ተወለድኩበት፣ አደግሁበት እና ፊደል ቆጥሬ አደግሁበት የሚለው የአገሩ ህዝብ በፖለቲካ ወለድ ወንጀል ምክንያት የገዛ ምድሩ ምድረ ሲኦል ስትሆንበት እያየ እንኳን ከምር እግረ መንገዱንም  አስገንዝቦን ለማለፍ የሞራል ወኔው የሚጎድለው ሰው ስለ ምን አይነትና ስንት አይነት ስኬት ሌክቸር እንደሚያደርግ ለመረዳት ያዳግታል።

በጣም የሚያሳዝነው ደግሞ ለዚህ አይነት መሬት ላይ ካለው ሰፊና አስከፊ መሪር እውነት ውጭ ለሚደሰኩረው የስኬት ምንነትና እንዴትነት ሃይማኖትን (ፈጣሪን) ጨምሮ ዋቢውና ተባባሪው ለማድረግ የሄደበት ርቀት ነው። አዎ! ርግጥ ነው አብዛኛው የመሠረታዊ እውቀት ጉድለት (lack of being well informed) ያለበት እንደ እኛ አይነት ማህበረሰብ ለዚህ አይነት ስሜታዊነት ለሚያጠቃው ስብከትና ዲስኩር በቀላሉ  ተጋላጭ ቢሆን የሚገርም አይደለም። ከዚህ እጅግ አስቀያሚ  ሁኔታ ሰብረን  መውጣትና ጥረታችን የሚወልደውን ስኬታማነት በአግባቡ የሚያስተናግድ ሥርዓተ ፖለቲካ እውን ማድረግ ካለብን ብቸኛው መውጫ መንገድ የምንገኝበት ፈተኝ ሁኔታ ሁለንተናዊና ውስብስብ መሆኑን አውቀን ለተገቢው ሁለንተናዊ ለውጥ እውን መሆን  ሁለገብ ጥረት ማድረግ ነው።

 

አዎ! የአገራችን ህዝብ እጅግ አስከፊና አስፈሪ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ስለ መኖሩ ለማወቅና ለማሳወቅ አንዳችም የሞራል ወኔ ሳይኖረው በየቦታውና በየክፍለ ዓለሙ እየዞረ እንደ ሃይማኖታዊ እምነት የመሰሉ እጅግ ስሜትን የሚስቡ ጉዳዮችን እያዘጋጀና እድሜ ለዘመኑ ቴክኖሎጅ በአሽብራቂ ገፅታ እያሳየ “ይህንን ያህል ሰብስክራይበር አገኝሁ” በሚል ስኬቴን ተመልከቱልኝ ከማለት አልፎ ፈጣሪን ጨምሮ ከመከረኛው ህዝብ ተነጥሎ እርሱ ጋር የሚዞር ዝና እና  የተለየ ጥቅም ፈላጊ ማስመሰሉን “ተው በቅጥ አድርገው” ለማለት የማይደፍር ትውልድ የሸፍጥ ኑሮና አኗኗር ሰለባ ሆኖ ይቀጥላታል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  እጅ አንስተው ማሉ፣ ከኦህዴድ ጋር ወግነው በህዝብ ላይ እጅ አንስተው ዱላ አሳረፉ - ግርማ ካሳ

 

አዎ! የፈጣሪ ምድር የምንላት የአገረ ኢትዮጵያ ህዝብ እንኳን ለማመን ለማሰብም በሚከብድ ሁኔታ ውስጥ በሚገኝበት በዚህ ወቅት የባህር ማዶ ገዳምና ቤተ እምነት የማሠራት ዘመቻውን ያለምንም ጥያቄ ተቀበል ሲለው ከንፈር እየመጠጠ የሚቀበል እና ይህንን ካላደረገ የገነት በር እንደሚዘጋበት ሲነግረረው (ሲሰበከው) ምነው አደብ ግዛ እንጅ ለማለት የሚሳነው ትውልድ የታላቁ አገራዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን አድራጊ ሳይሆን ከንቱ ናፋቂ ሆኖ ቢቀጥል ያሳዝን እንደሆነ እንጅ የሚገርም አይሆንም።

 

እውነት ነው ሃይማኖታዊ እምነትን ጨምሮ እጅግ ስሜትን የሚስቡና ጥያቄ ማንሳትን እንደ ሃጢአተኝነት ሊያስቆጥሩ የሚችሉ ርዕሰ ጉዳዮችን  ለሶሻል ሚዲያ ቢዝነስ ማሳለጫነት በመጠቀም ረገድ ከእሸቱ ውጭ የተሳካለት ሌላ ሰው ያለ አይመስለኝም።

 

አዎ! በእርግጥ ለስኬት ጥረት የግድ ነው። ጥረትን ስኬታማ ለማድረግና ለማስደረግ የሚያስችል ወይም የሚያግዝ ሁኔታ ጨርሶ በሌለበት የአገዛዝ ሥርዓት ውስጥ “ያልተሳካላችሁ  ወይም  የወደቃችሁ እንደ እኔ ጥረት ስለማታደርጉና የፈጣሪን ተአምራዊ ሥራ ስለማትቀበሉ ነው “የሚል አይነት እጅግ ግብዝነት የተሞላበት ስብከት ከቶ የትም አያደርስም።   ይህ አይነት ስብከት ሲቀርብለት ያለምንም ጥያቄ የሚቀበል ትውልድ የራሱን እጣ ፈንታ እያበላሸ የመሆኑን መሪር እውነት ተረድቶ በእውነተኛና ትክክለኛ   ፍኖተ  እምነት ፣ነፃነት፣  ፍትህና ርትዕ ፣ ሰላም ፣ ፍቅር፣ እና የጋራ ብልፅግና ላይ መሰባሰብ ይኖርበታል።

 

ለዘመናት ከመጣንበትና አሁንም በአስከፊ ሁኔታ ከቀጠለው ፖለቲካ ወለድ መከራና ውርደት አዙሪት ሰብረን በመውጣት የተሻለ ሥርዓተ ማህበረሰብን እውን ማድረግ ካለብን ከመሪሩ  እውነታ እየሸሹ ስለ  ሰላምና ስለ ፅድቅ ሌክቸር እናርጋችሁ የሚሉንን ወገኖች ከቻልን አደብ እንዲገዙ በመንገር እና ቢያንስ ደግሞ ወደ አምልኮ የሚጠጋ  ሙገሳን በቅጡ በማድረግ አስፈላጊነት ላይ መግባባት ይኖርብናል።

4 Comments

  1. ጠገናው ጎሹን ዘመድ ቢኖር ትኩስ የፈለቀ ጠበል ፈልጎ መውሰድ ነው እንጅ ምን ይባላል፡፡ እሸቱን አንድም በውጭ ሃገር ገዳም አሰራህ ሁለትም ጥረት ማድረግ የስኬት ቁልፍ ነው ብለሃል ብሎ መወንጀል ምን ይሉታል? እሸቱ የህዝብ ሰው ነው ህዝብ አክባሪ ነው፡፡ ጠገናው ሲያረጅ የእረፍት ጊዜውን የሚያሳልፍበት ከአምላኩ የሚገናኝበት ገዳም ማሰራቱ ወንጀሉ ምኑ ላይ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ጉዳይ ከሚከነክነው ዜጋ እሸቱ አንዱ ነው ምንም እንኳን ኢትዮጵያ እግር ከወርች የታሰረችበት ዘመን ቢሆንም፡፡ ባስቸጋሪ ሁኔታም ቢሆን የስኬት ቁልፉ አሁንም ጥረት ነው፡፡ ደግነቱ ጽሁፉን ሰው አላነበበውም፡፡ እስቲ እንዲህ አገራችን ውጥንቅጧ በወጣበት ጊዜ የእሸቱ መልካም ስራ በክፋት ተተርጉሞ የሚጻፍበት ነው? አይ የኛ ህዝብ

  2. ከሁሉም በፊት አስተያየት ሰጭው/ዋ በተረዳኸው/ሽው እና ባመንክበት/ሽበት መጠንና አይነት ለሰጠኸው/ለሰጠሽው አስተያየት በእውን አመሰግናለሁ! በየትኛውም ጉዳይ ላይ ስንነጋገር እንዲህ አይነት የሃሳብና የአተያይ ግጭት እንኳንስ በእንደኛ አይነት ማህበረሰብ በአንፃራዊነት በዴሞክራሲያዊ ባህልና ሁለንተናዊ በሆነና በላቀ የእድገት ደረጃ ላይ በሚገኝ ማህበረሰብ ውስጥም የሚጠበቅና ነውና ከቶ ሊገርመን የሚገባ ነገር አይደለም ።

    ተፈላጊው ነገር የምንለውንና የምንባባለውን ጉዳይ በደምሳሳው ወይም ለግለሰቦች ባለን አድናቆት ላይ ብቻ ተመሥርተን ሳይሆን ጉዳዩኑ ከአለንበት የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረትን የግድ ከሚለው ግዙፍና መሪር እውነታ (huge and bitter reality) አንፃርም ለመረዳትና ሃሳብን ለመሰንዘር ፈቃደኛና ዝግጁ ከመሆኑ ላይ ነው።

    እንደ መግቢያ ይህንን ካልኩ ለእሰጥ አገባ ሳይሆን ግልፅ ካልሆንኩ ግልፅ ለመሆን የሚከተለውን ልበል፦

    1) በውጭ አገር ገዳም ወይም ሌላ ማህበረሰባዊ ጠቀሜታ ያለው ነገር መሥራትና ማሠራት አያስፈልግም የሚል እጅግ ደምሳሳ የሆነ አስተያትን በፍፁም አልወጣኝም። ይህን አንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ደጋግሜ በሰፊውና በአፅንኦት የገለፅኩትን መከራከሪያ እንደሌለ በመቁጠር ወይም ለመረዳት ባለመፈለግ ፀረ-ገዳም ወይም ፀረ ሌላ ጠቃሚ ተቋም በሚል ቁንስል ሃሳብ ማስተጋባት ፈፅሞ አይጠቅመንም! እናም አስተያየት ስንሰጥ የተባለውን ወይም የተነገረውን ጉዳይና የተባለበትን መሠረታዊ ምክንያት ልብ እያልን ቢሆን መልካም ነው። በዚህ የአስተሳሰብ ሸፋፋነት ምክንያት ለዘመናት ቀመጣንበትና አሁንም ከተዘፈቅንበት አዙሪት ከቶ አንወጣም።

    2) ጥረት የማድረግ አስፈላጊነት የሚያጠያይቅ አጠቃላይ እውነት (general truth) እንደሆነ የገለፅኩበትንና የእሸቱን አቀራረብ የተቸሁበትን ልብ በማለትና በዚያው አረዳድ መጠንና አይነት ገንቢ የሆነ ትችትና የወደፊትነት ሃሳብ ቢቀርብ እንዴት ሸጋ ነበር?

    አንድን ነገር ትእግስቱም ሆነ ሚዛናዊነት ሳይኖረን ግለሰቦችንና የሚያደርጓቸውን በጎ ነገሮች ወደ ፍፁምነት እያስጠጋን በእነርሱ ላይ የሚሰጥን ትችት እንደመርገምት በመቁጠር ፈፅሞ የትም አንደርስምና ቆም እያልንና ትንፋሽ እየወሰድን መራመዱ ለራሳችንም ሆነ ለአገራችን ወይም ለወገናችን ይጠቅማል።

    3) ለፖለቲካ ወለዱ ግዙፍና እጅግ መሪር የአገር ቤት ውስጥ ጉዳይ ምንም አይነት ድርድር ሊቀርብበት የማይገባ የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረት መስጠት ሲገባን “ባህር ማዶ ዘመናዊ ገዳም ሠርቶ ወይም አሠርቶ ሲያረጁ ማረፊያና ከአምላክ ጋር መገናኛ ማድረግ” የሚለውን መከራከሪያ እንኳንስ ሁሉንም የሚያውቀው እውነተኛው አምላክ ቅንና ሚዛናዊ ህሊና ያለው ሰውም ፈፅሞ የሚቀበለው አይደለም። አይሆንምም ። ለመግለፅ በሚያስቸግር መከራ ውስጥ ለሚገኘው ወገን ቀድሞ በመድረስ የመታደግ ዘመቻ ላይ ከመረባረብ ይልቅ እንኳንስ ባህር ማዶ አገርቤትም እጅግ ዘመናዊና ብዙ የሃብት ወጭ (resource) የሚጠይቅ የእምነት ተቋም እገነባለሁ የሚለውን ዘመቻ የሚባርክ እውነተኛ አምላክ የለም። ማረፊያውም አያደርገውም። የመከረኛውን ህዝብ ሰቆቃ፣ መከራ እና የደም እንባ (የምድር ላይ ሲኦል) ረግጦ (ችላ ብሎ) የሚሠራ ህንፃን ባርኮና ቀድሶ ቤቱ የሚያደርግ እውነተኛ አምላክ የለም። ለዚህ ነው የእሸቱን “የትፀድቃላችሁ” ዘመቻ ተቀብሎ ለማስተጋባት በእጅጉ የሚከብደው።

    4) የኢትዮጵያ ጉዳይ እሸቱን ፈፅሞ አይከነክነውም ወይም አያሳስበውም የሚል ደምሳሳ ትችት አላቀረብኩም ። አላቀርብምም። እርሱን ብቻ ሳይሆን አገር ምድሩን የሚያሳስበውን ጉዳይ ለመዋጋት የሄደበትና እየሄደበት ያለው አካሄድ ግን የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረትን በእጅጉ የሳተ ነውና ሊታረም ይገባል ነው የአስተያየቴ ጭብጥ ። ችግሩ የአስተሰባችንና የውይይታችን ባህል የጋራ በሆነው ጉዳይ ላይ ሳይሆን እገሌ/እገሊት የሚያደርገው/የምታደርገው ሁሉ መልካምነት አለበትና እርሱን/እርሷን መተቸት ከስህተትነት ያለፈ ክፉ ነገር ነው በሚል እጅግ የማይጠቅም አስተሳሰብ ሰለባዎች መሆናችን ነው።
    “አገር ውጥንቅጥ ውስጥ ባለችበት እሸቱ መልካም ሥራ እየሠራ ስለሆነ ፈፅሞ አትተቹት” የሚልን እጅግ የወረደ አስተሳሰብ ለመረዳት የሚቻል አይመስለኝም ። እደግመዋለሁ! እየሠራ አይደለም የሚል ደምሳሳ አስተያየት ፈፅሞ አልወጣኝም። ያልኩትና እያልኩ ያለሁት የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረትን ፈፅሞ የሳተ አስተሳሰብና አካሄድ ሊታረም ይገባል ነው።

    5) በሚሠራው ሥራ ውስጥ መልካም ነገር መኖሩ እንደ ተጠበቀ ሆኖ ለዘመናት ከዘለቀውና ከአምስት ዓመታት ወዲህ ደግሞ ለማሰብም በሚከብድ ሁኔታ ከቀጠለው ፖለቲካ ወለድ ሁለንተናዊ መከራና ሰቆቃ አንፃር ሲታይና ሲገመገም በቁጥር ቀላል ያልሆኑ ዘመቻዎቹ የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረትን የሳቱ ብቻ ሳይሆን አገር ቤት ውስጥ ምንም እንዳልተፈጠረ የሚያስመስሉና የሚያሳስቱ ናቸውና በአግባቡ ሊተቹና ሊታረሙ ይገባል ማለት እንዴት ፀበል ፍለጋ እንደሚያስፈልገው አላውቅም ። ወደ አምልኮ የተጋና የሚጠጋ ሙገሳና ሆይ ሆይታ ለዚህ ትውልድ ብቻ ሳይሆን ለራሱም አይጠቅመውም ። ለራስም ቢሆን “ወጣ ወጣና እንደ ሸንበቆ…። ” መሆንን ይመጣልና አደብ እየገዙ መራመድ ጥሩ ነው።
    6) ለስኬት ጥረት ያስፈልጋል ማለቱበራሱ ትክክል አይደለም አላልኩም። ያልኩትና አሁንም የምለው ትክክል መሆኑ እንደ ተጠበቀ ሆኖ እንኳን ህይወትን የተሳካ ለማድረግ ራሱ በህይወት መቆየትንም በእጅጉ ብርቅየ እንዲሆን ያደረገውን የእኩያን ዥዎች ሥርዓት ግምት ውስጥ ሳያስገቡ “ለፈጣሪ ተዥ ከሆናችሁና ጥረት ካደረጋችሁ …” እያሉ መስበክ እና የተወሰኑ ግለሰቦች ስለ ተሳካላቸው “ጣሩ ትበለፅጋላችሁ” ማለት በእጅጉ ጎደሎና አሳሳች ስብከት ስለሆነ ሊተች ተገቢ ነው የሚል ነው።

    7) ፀበል እንደሚያስፈልገኝ የተነገረኝ ምክር በፀበል እናምናለን እያልን ፀበልን የግልብ ስሜታችን ትችት ማድመቂያ ማድረግ ቢያንስ ከሞራል አንፃር ነውር መሆኑን ነው የሚነግረኝ። ለሃሳብ ልውውጣችን ባህል እድገትም ፈፅሞ አይበጅም! በበኩሌ እንኳን ከልብ ለሚያምን ፈውስ ሊሆን ስለሚችለው ፀበል ሌላም ነገር ቢባል ፈፅሞ አይገርመኝም ! በእገሌ ወይም በእገሊት ላይ ሂሳዊ ትችት መሰንዘርህ/ሽ የጤንነት አይደለምና ፀበል ያስፈልግሃል/ያስፈልግሻል የሚል መከራከሪያ ማቅረብ ቅዱስ ነው የምንለውን ነገር ማራከስ ነው የሚሆነው።

    8) “አስተያየትክን ሰው አላየውም” የሚለው ብዙም የሚያሳስበኝ ጉዳይ አይደለም። የምፅፈው እገሌ ያነብልኛል ወይም አያነብልኝም እያልኩ ወይም ሊያነብ የሚፈልገውንና የሚችለውን ሰው ቁጥር እያሰላሁ ሳይሆን አንድም ሰው ያንብበው የአገራችን ህዝብ በፖለቲካ ወለድ ወንጀል ምክንያት የገዛ ምድሩ ምድረ ሲኦል ስትሆን የምታዘበውን እጅግ ግዙፍና መሪር እውነታ በተረዳሁትና በምችለው መጠንና አይነት መግለፅ ነውና “የአይነበብልህም” ዘመቻው አያሳሰበኝም። አስተያየት ሰጨው (Akale) አስተያየቴን ያጣጣልኩ መስሎት/መስሏት የሰነዘረው/የሰነዘረችው መሆኑን በሚገባ ስለምረዳ ፈፅሞ አይገርመኝም።

    ለማንኛውም የሃሳብ ልውውጥን ከዚህ በተሻለ አቀራረብ እንዲሆን በማድረግ ለጋራ አገራዊ ጉዳያችን ከነልዩነታችንም ቢሆን የጋራ መፍትሄ አምጠን ለመውለድ እንደምንችል ተስፋ እያደረግሁ እና አስተያየት ሰጭውንም/ሰጭዋንም በድጋሜ እያመሰገንኩ ልሰናበት!!!

  3. ምንድነው አገራዊ ጉዳይ? አንድን የስርአቱ አካል ያልሆነ በጎ አድራጊና ስንምግባር ያለውን ዜጋ ጥምብ እርኩሱን ማውጣት ነው አገራዊ እሳቤ? ወይስ ኢኮኖሚ፤ፖለቲካ፤ማህበራዊ ኑሮ ግምባታ፤ከግጭት መውጣትን ታሪክ አጣቅሰህ ጽፈህልን ነው? የአንተ እውነትና እይታ ላንተ ነው ለሌሎች ሌላ ነው ።ኢትዮጵያ ውስጥ ካለው ውጥንቅጥ እሸቱን በተመለከት እረፍት ነስቶህ ተጨንቀህ ተጠብበህ የጻፍከው ነገር ግራ የሚያጋባ ነው። አማራው ያለ ርህራሄ ይታረዳል፤አገር በቁሙ ይሸጣል።ወሮበሎች ባለስልጣን ስራ ሰርተው የማያውቁ የስራ ልምድ እንዲያገኙ ጠቅላዩ ሹሞ ስራን ያጨመላልቃሉ ዜጋን ያስመርራሉ። በመላው ኢትዮጵያ ሰው ልጁን የሚያበላው አጥቶ በየቀኑ የራሱን ህይወት የሚቀጥፈው ዜጋ ስፍር ቁጥር የለውም። አማራው ክልል 7 ሚሊዮን የሚግመቱ ህጻናት ትምህርት ቤት አይሄዱም ላንተ ግን ከዚህ ሁሉ ጎልቶ የታየህ እሸቱ ነው። እዚህ ላይ ያባከንከውን ሃይል አዳነች አቤቤ ቀጀላ መርዳሳ፤አብይ መሃመድ፤ሽመልስ አብዲሳ፤አገኘሁ ተሻገር ብርሃኑ ነጋ ላይ ቢሆን ስሜት ይሰጥ ነበር እንግዲህ የጻፍከውን በግንዛቤህ ጽፈሃል እኔም በግንዛቢዬ አንብቤዋለሁ ቀጥልበት።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share