የዚህ ጽሁፍ ሀሳብ የመጣልኝ አንድ የሀገራዊ ትግሉን ለማንቀሳቀስ በተደረገ ውይይት ላይ አንዳንድ ሰዎች እየተነሱ “እነሱ እንዲህ ቢያደርጉ” የሚሉ ሀሳቦች ሲሰነዝሩ ነበር። “እኔ ምን ላድርግ” ሳይሆን እነሱ የሚለው ሳናውቀው ውስጣችን ገብቷል።
ፋኖ ከጅምሩ ይህ ሀሳብ አደጋ እንዳለውና “ከነጻ አውጪና ነጻ ወጪ ትርክት” መፋታት አለብን በማለት ብዙ ተወያይቷል። ትግሉ ለውጥ ማምጣት ካለበት የኢትዮጵያ ህዝብ እያንዳንዱ “አራሽ፣ ተኳሽ፣ ቀዳሽ” መሆን አለበት ተባለ። ይህ ጥልቅ ፍልስፍና የቋጠረ ጽንሰ ሀሳብ ነው። ለፋኖም ፈጣን እድገት “ እነሱ ይሄንን ቢያደርጉ” ከሚለው እሳቤ ተላቆ እኔ እኛ ምን እናድርግ ወደሚለው ስላደገ ነው።
የኢትዮጵያ ህዝብ ለሶስት ሺ ዘመን በነጻነት የኖረው ከገነት ጦር ትምህርት ቤት ወይንም ከሀረር አካዳሚ በተመረቁ መኮንኖች ሳይሆን በራሳቸው መተማመን ባላቸው “አራሽ፣ ቀዳሽ እና ተኳሽ” ዜጎች ነበር። በሰንበት ነጭ ለብሰው ከነሱ በላይ ሀያል ልኡል ፈጣሪ አለ ብለው ተንበርክክው የሚጸልዩ የሚቀድሱ፣ ግፍ፣ ሀጥያት፣ ጭቡ መዘዝ አለው ብለው የሚያምኑ። በራሳቸው ላይ ሊደረግ የማይፈልጉትን በሌላ ላይ የማያደርጉ፣ ትልቅ የሞራል ልዕልና ያላቸው ሰዎች በመሆናቸው ነበር።
በአዘቦት ቀን ደግሞ ቁምጣቸውን ታጥቀው ሞፈራቸውን ጨብጠው አፈር የሚገፏ፣ አርሰው የሚያበሉ ሲሆኑ ሀገር ሲወረር፣ ፍትህ ሲጓደል ደግሞ ጭስ የጠጣውን ጎራዴ፣ ጋሻና መውዜራቸውን ይዘው የሚዘምቱና ለነጻነታቸው ማንም ሳይሆን እራሳቸው ብቻ እንደሆኑ የተረዱ ሰዎች ስለነበሩ ነው።
ዘመናዊ የአውሮፓውያን ትምህርት ሊያጠፋ የሞከረው ይሄንን ነው። ዘመናዊ ጦር ተቋቋመና ተኳሽነት ለሆለታና ለሀረር አካዳሚ ሰዎች ብቻ ይተው ተባለ።
ዘመናዊ ትምህርት ቤት ተቋቋመና ገበሬ በየ ጥላው ስር፣ በየ ገዳሙ፣ በየ የኔታ ታዛ ስር ሀሁን መቁጠር ዳዊት መድገም ቀረ። ትምህርት ለራስ ጥቅም መሆኑ ቀረና ተቀጥሮ ሌላን ለማገልገል ሆነ።
ሁለቱ ተወስደው ለህዝቡ የተተወው አፈር መግፋቱ ብቻ ሆነ። በዚህ ምክንያት በማጨው፣ በሱማሌ ጦርነት፣ በኤርትራ አማጭ፣ በህወሀት ታጣቂ የሚሸነፍ። እንደነ ብርሀኑ ጁላ አይነት አፈሙዝ ሲያዩ እጃቸውን ወደላይ የሚሰቅሉ የፈሪዎች መሰባሰቢያ ሆነ። በዚህ ምክንያት በወያኔ ተሸንፎ ተበተነ። አሁንም ይህ ነው ጉዞው።
የሚያሳዝነው ፊደል የቆጠረው፣ ሀረር የጦር አካዳሚ የገባው አባቱን ገበሬ ወንድሙን ናቀ። ይሁንና ሁሌም ይህ ፊደል የቆጠረ ጦር ሲሸነፍ የሚጠራው ያው ገበሬውን ነበር። የሱማሌን ጦር ለማባረር ሶስት መቶ ሺ ህዝባዊ ሰራዊት ተመመ፣ ዘመተ፣ አባረረ።
የፋኖ ጽንሰ ሀሳብ አቀንቃኞች የጠፋውን የተናቀውን የተረሳውን “አራሽ፣ ተኳሽ፣ ቀዳሽ” ጽንሰ ሀሳብ አቧራውን አራግፈው ማንኛውም ኢትዮጵያዊ አራሽ ተኳሽ ቀዳሽ እንዲሆን ትምህርት ተሰጠ።
ቀዳሽ
ቀዳሽ ማለትም ቤተ ክርስቲያን ማገልገል ሳይሆን intelectual የሀሳብ የእውቀት ባለቤት መሆን ነው። በጥንታዊ ግብጽም scribe የሚባሉት በኢትዮጵያ ደግሞ የአይምሮ ስራ የሚሰሩት ቀዳሽ ይባላሉና።
አሁን ማሰብ መምራት ከኮሌጅ ሰርቲፊኬት የተስጣቸው ነጻ አውጪዎች ብቻ ሳይሆን ሁሉም ባንገቱ ላይ ጭንቅላት የተገጠመለት ሁሉ መሆኑን ፋኖዎች ተቀበሉ። ስለዚህ በየቦታው የነ ብርሀኑ ጁላን ጦር እንደ ቆቅ የሚያስደነብረው እያንዳንዱ ፋኖ ሀሳቢና የሀሳብ ሰው በመሆኑ ነው። ከላይ ወደታች፣ ከመሪ፣ ከፓሊት ቢሮ ከነጻ አውጪ ሊቀመንበር ጠባብ ጭንቅላት የሚመነጭ ሳይሆን ከእያንዳንዱ የፋኖ ታጋይ የሚመነጭ ነው
ለዚህ ነው ዛሬ ከደንብ ልብሱ በስተቀርና ኮኮቡ ውጪ እያንዳንዱ ፋኖ ከተማራኪው ብርሀኑ ጁላ ወይንም ህወሓት በጉዲፈቻ ካሳደገው ጄኔራል አበባው የማያንሰው። የሀሳብ ሰው/ቀዳሽ/ ያስባል፣ ያቅዳል፣ ይተገብራል። በጦርነት መሀከል ለውጥ ሲመጣ አስቦ ራሱን አሰላለፍ ይቀይራል። አለቃው መሪው በዚህ ሂድ በዚህ አጥቃ የሚለው አይጠብቅም። ለዚህ ነው ትግሉ ሲጀመር የተንቀሳቀሰው 55ሺ ፋኖ እንደ ተራ ወታደር ሳይሆ እንደ 55ሺ ጀነራል የተንቀሳቀሰው። በ6 ቀን ውስጥ የመሳሪያ መጋዘን ዘርፎ፣ እስር ቤት አፍርሶ እስረኛ ነጻ አውጥቶ የብአዴንን መዋቅር አፈራርሶ የተመለሰው። ሁሉም ስለሚያስብ ተናቦ 54 ከተማ ተቆጣጥሮ ያለ ጀነራልና ኮለኔል ትዕዛዝ ተጠቃቅሶ ከተማን ጥሎ የወጣው።
ፋኖ ከመአከል በጀነራል ትዕዛዝ ሳይሆን በራሱ አይምሮ አስቦ አስልቶ ተከራክሮ ወስኖ የሚያጠቃ በመሆኑ መንግስት ከመአክል ወደ እዝ የሚፈስ መረጃ ያለው መስሎት እንቅልፍ አጥቶ ያድራል። ይሁንና የሚጠለፍም የሚደመጥም ከላይ ወደታች የሚፈስ መረጃ የለም።
ለዚህ ነው ፋኖ ለአብይ አንደርብ የሆነበት። ሲጥል፣ ሲገል፣ ሲቆጣጠር እንጂ በሬዱዮ ሲያወራ ሲንቀሳቀስ የማይታያቸው።
የፋኖ ትእዛዞች የሚተላለፏት በዋትስአፕ ይሆናል ብለው ኢንተርኔቱን ወ/ሮ ፍሬህይወት ታምሩ እንድታጠፋ ተነገራት። ይህም የፋኖ አመራር በስልክ ትእዛዝ ሲሰጥ ለማድመጥና ለማጨናገፍ ነበር። ይህ ውጤት አላመጣም፣ መብረቃዊ ጥቃቱ ቀጠለ። በስልክ ሀሙሲትን፣ ደንበያን፣ መራቤቴን፣ ምንጃርን፣ ደብረ ማርቆስን ጎንደርን ነገ ጥዋት እናጥቃ ሲባል በስልክ ለማድመጥ ነበር። የፋኖ መብረቅ ሲመታ እንጂ ሲያጉረመርም አይሰማም።
አብይ ከዛ ፍሬ ህይውትን ስልኩንም አጥፊው አላት ስልኩም ጠፋ። ይህ ፋኖን ሳይሆን የብአዴን አሽመደመደው። በየቦታው ያለ የብአዴን ተቀላቢ ፋኖ በዚህ በኩል እየመጣ ነውና አምልጡ ብለው ማሳበቅ እንኳን የሚችሉበት መንገድ ተዘጋ።
ከዛ በላይ በአማራ ክልል ደሞዝ የሚከፈለው ሲቩል ሰርቪስ፣ ፓሊሱ፣ ዩኒቨርስቲ መምህሩ፣ የባንክ ሰራተኛው፣ ደህንነቱ፣ ሰላዩ በኢንተርኔትና በስልክ መዘጋት ከስራ ውጪ ሆነ። መንግስት አይኑን ጨፍኖ የገባበት ጦርነት ትጥቅ ማስፈታት ቀርቶ ወደ ማስታጠቅ ተቀየረ።
በጠባብዋ በአብይ ጭንቅላት የሚመራው ትግል ሙሉ በሙሉ በኢንተርኔትና ስልክ በመዘጋት ብአዴን እጅና እግሩ ታስሮ በየ ቢሮው እንዲቀመጥና ስለ ፋኖ ሲያማ እንዲውል አደረገው። ስልክ መዘጋት ይልቁንም ፋኖን ወደ መንፈስነት ቀየረው። በትናንሽ የስልክ ሰላምታና ጭውውት መሀል የምትገኘውን ቆሎ፣ ፍሬ ልኬልሀለው ወዘተ ፍንጭ ጠፋች።
የብአዴን ካድሬዎች የወታደራዊ ሬዲዮ ይሰጠን ብለው ቢጠይቁ ብርሀኑ ጁላ ስትማረኩ የሬድዮ መገናኛ ለፋኖ እናስታጥቀው ነወይ የምትሉት ብለው እንቢ አሉ። ስለዚህ ብርሀኑ ጁላ አይኑን ጨፍኖ ጆሮውን በጥጥ ጠቅጥቆ ወደ አማራ ክልል የሚልከው ሰራዊት በሚያሳዝን አይነት መንገድ እየረገፈ ነው።
ፋኖ በራሱ አሳቢ ማለትም ቀዳሽ ባይሆን ኖሮ ግንኙነት ሲቋረጥ ትዕዛዝ ሲጠብቅ ይጠቃል፣ ይመታል፣ ይፈርሳል ብለው ነበር። ይሁንና ጠባቂ ሳይሆን አሳቢና ወሳኝ በመሆኑ ይሄው ትግሉ ተፉጠነ እንጂ አልተዳከመን። እኛም የምንከታተለው ዛሬ ሌሊት አስር ሰአት ላይ ፋኖ አራት ኪሎን፣ ለገጣፎ ወይንም ደሴ እንደሚያጠቃ አናውቅም። ስለዚህ ሚስጥርም አይባክንም።
ተኳሽ
ሁለተኛው የኢትዮጵያ ህዝብ በዘመናዊነት ሰበብ እንዲጥል የተደረገው ተኳሽነትን ነበር። የግድ ከገነት ጦር ትምህርት ቤት፣ ከሁርሶ፣ ከብላቴ ወይንም ከብር ሸለቆ መመረቅ ለተኳሽነት ቅድመ ሁኔታ ተደርጎ ነበር።
የፋኖ መሪዎች ይህ ስህተት ነው የቀየሩት። የኢትዮጵያ ወቷደር ለመሆን ለዘመናት አባት ለልጁ፣ ታላቅ ወንድም ለትንሽ እያስተማረ እንጂ ልጁን ሆለታ ወይንም ብላቴና ልኮ አይደለም የሚያሰልጥነው። ተኩስ የሚያስተምረው አባቱ አጎቱ እንጂ ግድ የሁርሶ መቶ አለቃ ወይንም ሻምበል አይደለም። ስለዚህ ስልጠና በግድ በዳስ ተቀምጦ ግራ ቀኝ ሰልፍ በመማር፣ ሰላምታ መስጠት ልብስ መተኮስና ስልፍ ማሳመር ሳይሆን መፍታት መግጠም፣ ትንፋሽን ዋት አድርጎ አልሞ መተኮስ ነው። ይህ ደግሞ አባት ለልጁ እውቀቱንም ጠመንጃውንም የሚያወርሰው ብሂል ነው። ስለዚህ የፋኖም ስልጠና በየቤቱ እንዲሆን ተወሰነ።
መንግስት ስልጠና የፈቀደበት ግዜ በምንጃር፣ በቡልጋ፣ በደብረብርሀን፣ በደሴ በጎንደር ወዘተ በአደባባይ ስልጠና ተደርጓል። ከዛ አብይና አበባው ዘመነ ካሴን እንገላለን ፋኖን ትጥቅ እናስፈታለን ብለው ከዘመቱበት ቀን ጀምሮ ስልጠና ባደባባይ ተከለከለ። ከዛ በአደባባይ በስታዲዮም ሳይሆን በቤት፣ በጓዳ፣ በሰፈር፣ በመንደር ሆነ። ለተኩስ ብቻ ቆላ ወርዶ በመተኮስ ሆነ።
ለዚህ ነው ይህ ሁሉ ፋኖ ከየት መጣ እስኪባል ድረስ የአማራን ከተሞችና ገጠሮች በአንድ ግዜ ያጥለቀለቀው። አባት ለልጁ ፋኖ ለጓዱ እሳት ዳር ቁጭ አርጎ ስልጠና ይሰጣል። አሁንም በየቤቱ በየመንደሩ ስልጠናው ቀጥሏል። እድሜ ለብርሀኑ ጅሎ የነበረው የጥይትና ይክላሽ ችግር ተፈቷል።
ከጥይትና ክላሽ ቀጥሎ የሰው ቁጥር አስፈላጊ ነው። ይህ ችግር መንግስት ቀይ ሽብር በማወጁና በተቆጣጠራቸው ከተሞች በንጹሀን ላይ ነጻ እርምጃ በመውሰዱ የሰው ሀይል እጥረት የለም። ያመነበትም የፈራውም ፋኖን ተከትሎ ወጥቷል። የሚቀጥለው ዘመቻ በኮማንዶና ደረጃ በሰለጠነ ፋኖ ነው። ስለዚህ እንደ ጥንቱ ፋኖ የሀሳብ ሰው/ ቀዳሽ ከሆነ፣ አንድ ስው ተኳሽ ከሆነ ነጻነቱን ለመቀዳጀ አራሽም መሆን አለበት።
አራሽ
አራሽም እንደ ቀዳሽ ጥልቅ ጽንሰ ሀሳብ ከጀርባው አለ። ይሄም እራስን መቻል ነው (self sufficiency) ። ፋኖ ጠመንጃ ገዝቶ የሰጠው ስው የለም። የመጀመሪያዎቹ ስልጠናዎች ሲሰጡ ጠመንጃ የሌለው ስው አናሰለጥንም ተብሎ ብዙ ተመልሷል። ከዛ ሄዶ በሬውን ሸጦ፣ ባጃጁን ሸጦ፣ እቁብ ሰብስቦ፣ ዘመድ አዝማድ አስገድዶ ጠመንጃውን ገዝቶ ወደ ስልጠና የተመለሰው። ጎንደር የመጀመሪያው ህወሀትን ለማስቆም ሲዘምቱ ምንሽር፣ ክላሽ፣ መውዜር የያዙ ነበሩ። የዛሬውን ቁጥር ባላውቅም የደብረ ብርሀን ባህርዳር ጎንደርና ወሎ፣ጎጃም እና 54 ከተሞች ዘመቻ ሲካሄድ 55ሺ ክላሽ ታጣቂ ተንቀሳቅሷል። ይህንን ክላሽ የገዛለት ማንም የለም። ማስፈታትም ያልተቻለው ለዚህ ነው።
አራሽ ማለት እራሱን የሚመግብ እራሱን የሚያስታጥቅ እራሱን የሚያለብስ ማለት ነው።
ለዚህ ነው ፋኖ በውጪ እርዳታ ላይ ያልተመሰረተው። ግማሹ ንብረቱን ሸጦ፣ እቃውን ሸጦ ትጥቁን ቀለቡን ይዞ ወደ ጫካ የገባው። ለዚህ ነው የማይዘርፈው የማይቀማው። ባንክ መዝረፍ ወታደር ካንፕን ከመደምሰስ በጣም ቀላል ነው። ግን የባንክ ብር አላጓጓውም። እንዲያውም ባንክ እንዳይዘረፍ ዘብ ቆመ።
ህዝብም ይሄንን ስላወቀ አካፍሎ ያበላል ያስጠልላል ጥይት ይሰጣል።
ፋኖ ከባለ ሀብቶችና ከውጪ ኢትዮጵያውያን ድጋፍ ለማግኘት ብዙ ሞክሮ ነበር። አንድ ባለ ጸጋ አንድ ብር አልስጠውም፣ ጥቅማቸውን መንግስት ይቀማናል ብለው ፋኖም የትም አይደርስም ብለው ምንም አልረዱም። የዲያስፓራውም ድጋፍ ከድል ቦሀላ ተነቃቃ እንጂ ትግሉን ለማስጀመር የሚያስችል የሳተላይት ስልክ እንኳን የላከ የለም። አሁን ግን ተነቃቅቷል ሁሉም የሚችለውን እያደረገ ነው ። ይህንን ስል ቀድሞ ገብቶት ያገዘ የለም ለማለት አይደለም። ከጅምሩ የገባቸው ያላቸውን የረዱ አርቆ አሳቢዎች ነበሩ። ይሁንና ጥቂት ነው።
ፋኖ ግን ለድል የሚበቃው ቀዳሽ፣ ተኳሽ እና አራሽ የሚለውን የአባቶቻችንን ጽንሰ ሀሳብ አቧራውን አራግፎ ስለ ተላበስ ነው። ይህንን ጽንሰ ሀሳብ 120 ሚሊዮኑም ኢትዮጵያዊ ሊያጠናው ሊረዳውና ሊለብሰው ይገባል። ሁሉም ኢትዮጵያዊ ነጻ አውጪ መጠበቅ ማቆም አለበት። ነጻ እራስን ማውጣት እንጂ ማንም ነጻነትን አይሰጥም።
ስለዚህ ነጻነት የሚፈልግ ስው አራሽ መሆን አለበት። ይህ ማለት መሬት መቆፈር ሳይሆን በራስ ሀብት ጉልበትና ጥረት ላይ የተመሰረተን ትግል ማካሄድ ነው። ይህ እነሱ ብር ቢልኩ፣ ራዲዮ ቢልኩ፣ ቀለብ ቢልኩ፣ እንዲህ ቢያደርጉ ከማለት ያድነናል። ሁሉም እጅ እግር አለው። ባለው ሀብትና ጉልበት መታገል አለበት።
ሁሉም ለመብቱ ተኳሽ መሆን አለበት። ተኳሽ ማለት ቃታ መሳብ ብቻም አይደለም። የተግባር ሰው መሆን ማለት ነው። ጸሀፊ በብእሩ፣ ዶ/ር በመርፌው፣ የህግ ባለሞያው በጥብቅናው፣ መምህሩ በማንቃት፣ ነጋዴው በብሩ፣ ውጪ ያለው በሰልፍ በተቃውሞው በመዋጮው፣ ወታደሩ አልታዘዝን ወንጀል አልፈጽምን በማለት፣ አቃቤ ህጉ በሀሰት አልከስም፣ ዳኛው አልፈርድም በማለት ነው። ተኳሽ ማለት ይህ ነው። እኔ ፋኖ ነኝ ማለት በዚህ ነው።
አራሽ ደግሞ እነሱ እንዲህ ቢያደርጉ ሳይሆን እኔ ምን ላድርግ። ለነጻነቴ መብቴ ሀገሬ ወገኔ ባንዲራዬ ምን ላድርግ ማለት ነው። ዛሬ መቶ ብር የረዳ ሁለት ጥይት ገዛ ማለት ነው። ነጻ የምንወጣው ሁላችንም አራሽ ተኳሽ ቀዳሽ ስንሆን ብቻ ነው። እነሱ እንዲህ ቢያደርጉ ለ50 አመት ተሞክሮ ነጻነት አላመጣም።
ስለዚህ እርሶስ ለመብቶና ነጻነትዎ አራሽ ተኳሽ ቀዳሽ ለመሆን ተዘጋጅተዋል? ቢዘጋጁ ይሻላል። የሩዋንዳ የፓል የካጋሜ ፓትርዬቲክ ፍሮንት ወደ ኪጋሌ ሲጠጋ የሁቱ ሚሊሻዎች 900 ሺ ንጹሀን ቱሲዎችን አርደው ጠበቋቸው። አሁንም እነ አዳነች አቤቤና እነ ሽመልስ አብዱሳ አብዮት ጠባቂ እያሰለጠኑ ያሉት ሊያርዷችሁ ነውና ብትዘጋጁ ከመታረድ ትድናላችሁ።
ዝግጅቱ ድግሞ ቀላል ነው። መጀመሪያ ቀዳሽ መሆን ነው። ይህ ማለት ለራስ ለሚስት ለልጅ ህይወት ፋኖ ግንቦት ሰባት ኢህአፓ ሳይሆን እራስ ማሰብ አለብህ ማለት ነው። የአዳነች አቤቤና የሽመልስ ልዩ ሀይል ለጭፍጨፋ ሲመጣ ተስልፌ እታረዳለሁ ወይስ መጥረቢያዬን ይዤ በሬን ዘግቼ ልጆቼን አድናለሁ ብሎ ማሰብ ማለት ነው። ስለዚህ የቤት የሰፈር የመንደር የቀበሌ የከተማ የመከላከል እቅድ በየአንዳንዱ ጭንቅላት መጎልበት አለበት። እነሱ እንዲህ ቢያደርጉ በህይወት አያስቀጥልህም። ከወለጋ ተማሩ። መንግስት እንዲህ ቢያደርግ፣ ሰራዊቱ ቢመጣ፣ የአለማቀፍ ሀይል ቢያወግዝ እያሉ ታረዱ በዶዘር ተቀበሩ። መጨረሻው ከራሳቸው በቀር ማንም እንደማይደርስላቸው ሲረዱ፣ ዱላቸውን ዘነዘናቸውን ማጭዳቸውን ታጥቀው እራሳቸውን መከላከል ገቡ። ይሄው የጅምላ ግድያውን አስቆሙ።
ለነገ አትበል። ነገ ጥዋት ሚስቴል ሊያርድ ልጄን ሊደፍር ሀይል ቢመጣ ምን አደርጋለሁ ብለህ ጠይቅ። ከዛ ከጎረቤትህ ከሰፈርህ ሰው ጋር ሆነህ እራስህን ልጅህን ሚስት እንዴት ለመከላከል እንዳለብህ አስብ ተዘጋጅ። ያልጠረጠረ ተመነጠረ ተብሏልና እንዳትመነጠር። ፋኖ የተፈጠረው ያደገው ወለጋ ላይ የሚያርደው የትልጠቀ ሀይል ቢመጣ ምን አደርጋለሁ ብሎ ስለጠየቀ ነው። ይህንን ሲጠይቅ መልሱ መዘጋጀት፣ መታጠቅና መታገል መሆኑ ቁልጭ ብሎ ታየው። አብን ኢዜማ መንግስት ይጠብቅብል ቢል ይትልረድ ነበር።
በድጋሜ የአዲስ አበባ ናዝሬት አሰላ ጎባ ጅማ ድሬደዋ ሻሸመኔ ህዝብ ከወለጋ ሰዎች ተማሩ። መንግስትን አምነው ታረዱ። ቁርጣቸውን ሲያውቁ ግን አራሽ፣ ተኳሽ፣ ቀዳሽ ሆነው እራሳቸውን እየተከላከሉ ነው።
ስለዚህ ነጻ አውጪ የምትጠብቅ ሁሉ ተነስና እራስህን አደራጅ። አራሽ ተኳሽ ቀዳሽ ሁን። ይህንን አልሰማ ብለህ ብትታረድ በፌስ ቡክ ሻማ ይበራልሀል እንጂ ፍትህ አታገኝም። ንቃ!