ይድረስ ለወጣቱ! የጎሰኝነት ስካር አላፊ ደስታ እንጅ ዘላቂ ሰላም አያስገኝም!

September 13, 2023

88y9y9hh9 1 1

  • የወጣትነት መግገለጫው ዘርና ኃይማኖት መሆን ይችላልን?
  • ላንተ ለ25 አመቱ የሶማሌ ወጣት፣ ከ 60 አመት ሌላ ሶማሌና ከ 25 አመት ጉራጌ የቱ ነው አንተን የሚመስለው?
  • ላንቺስ አማርኛ ለምታቀላጥፊው የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ  የኑሮ ጓደኛ ስትመርጪ ቋንቋዬን ካልተናገረ  ብለሽ ነው ወይስ ፀባይና  አስተሳሰብ፣ ቁመናና  የደስደስ አይተሽ ነው?
  • ሽማግሌ የዩኒቨርሲቲ መምሕር ከኦሮሞነቱ ተነስቶ፣ “ሚስትህ ኦሮሞ ካልሆነች ፍታት!” ወይም “ቋንቋህን ከማይናገር ጋር አትነጋገር!” ሲል፤ መሰሉ ጎሰኛ ደግሞ፣ ካንተ ጎሳ በስተቀር  ሌላዉን ኢትዮጵያዊ “ግደለው! ቁረጠው!” ሲልህ፣ በአንክሮ ምንድን ፈልገው ነው? ትላለህ ወይስ ወይስ በስሜት ሆ! ብለህ ገጀራ ይዘህ ትወጣለህ? ዘረኝነት፣ጎሰኝነት ድንቁርና ነው። ድንቁርና ብዙ መልክ አለው፤ እያወቁ ማጥፋትና፣ በዕዉቀት እጥረት መሳሳት ትልቅ ልዩነት አላቸው።

ስለዚህ ወጣቱ ለምን አላወቅህም? ተብሎ መከሰስ የለበትም። ለምን አልጠየክም? ለምን አልመከርክም?  ተብሎ ግን ኃላፊነት መውሰድ ይኖርበታል። በአሁኑ ጊዜ የአለምን  ሁሉ መረጃ በኪሳችን ዉስጥ ፣ በአንዲት ስልክ አምቀን በያዝንበት ዘመን፣ አጣርተን ጠይቀን አዕምሮአችንን ለማስፋት መረጃ ጎደለን ለማለት አንችልም፤ ሞልቷል። ዕድገት ማለት፣  ስልጣኔ ማለት ለመወያየት አዕምሮን ከፍቶ፣ ተነጋግሮ፣ ዙርያ አካባቢን መርምሮ፣ በትብብር ችግርን መፍታት፣ አዲስ ነገር ማፍለቅ ነው እንጅ …እዚህ ተወለድኩ ብሎ እንደ እምብርቱ በመንደር በየጓሮው ተቀብሮ መኖር… የወጣት ተፈጥሮ ነው?

በርግጥ የታመቀ የድኅነት ቁጭት፣ ተምሮ ስራ ማግኘት ያለመቻሉ ብስጭት፣ አድልዎ በየመልኩ በገነነበት ዘመን፣ የራሱን የቀን ተቀን ችግር ለመወጣት ስለሚያተኩር፣ ውስብስብ ፖለቲካና ዴማጎጊን አብሰልስሎ ለመተንተን ሁኔታው አይጋብዝም። ሰላም ስላጣ ስሜቱ ቢቀድመው አይገርምም።  ለዚህም ነው ይህንን የሚያዉቁ ክፉ ጎሰኞች የራሳቸውን ኑሮ አመቻችተው በአንተና በመሰልህ ምስኪን መካከል ግጭት ፈጥረው ስልጣንና ሃብት የሚሰበስቡት። በድሮዎቹ አውሮጳዉያን ቅኝ ገዥዎች የተፈተነች ዘዴ ናት። እንግሊዞች በዚህ የተካኑ ናቸው፤ ሕንድን ለሁለት ከፍለው፣ ኃይማኖትን ተጠቅመው እስከዛሬ ወንድማማቾቹ ሕንድና ፓኪስታን እንደተናቆሩ ይኖራሉ። የቡሩንዲና የሩዋንዳ እልቂት መነሻም የቤልጅየምና የጀርመን የቅኝ ገዥነት ቅርምት ነው። አንዱን ነገድ፣ ቱትሲውን ሴማዊ ብሎ አስጠግቶ፣ የተገለለው የሁቱ ነገድ ደግሞ በቱትሲ ምሁራን ላይ የመረረ ጥላቻ አሳድሮ መግባባት ቀረና ነገሩ ከረረ! በዚህ ሁሉ የዘረኞች ሴራ የተጨራረሰው ግን ወንድማማቹ ሕዝብ ነው። በዚህ ሂደት ውስጥ ምሁሩ የተጫወተው አስጸያፊ ሚና፣ በራድዮ ኮሊን ጣቢያና በሌሎችም መገናኛዎች የተሰበከው የጥፋት የዝልፍያ ፕሮፓጋንዳ ለሰው ልጅ ሁሉ ማስጠንቀቅያ የሚሰጥ ትምህርት ነው።

ዘረኝነት/ጎሰኝነት ግን ስሜት የሚገዛው ጥልቅ ድንቁርና ስለሆነ በታሪክ ትምህርትም ሆነ  በምክንያታዊነት  መረጃ አይበገርም።   (የዶ/ር አሰፋ ነጋሽ ን ስለ አክራሪ ብሔርተኝነት የጻፉትን እንዳያችሁት እገምታለሁ።)  የተሳሳተ ትምህርትን ትምህርት ይፈታዋል፤ ጎሰኝነት ግን በጅምላ ቱጃሩንም ድሃውንም፣ አረመኔውንም ሥልጡንንም ሳይለይ ስለሚጠቀልል፣ አክራሪ ብሄረተኛነት የግለሰቦችን ህሊና ይሰርቃል፣ ይሸረሽራል፤ መንጋ ያደርጋል። ስለሰብዓዊ መብት ለማሰብ ብዙ ረቂቅ ሃሳቦችን አስተውሎ ለመንቃት ጊዜ ይፈጃል። ቢሆንም ወጣቱ መጠየቅ ያለበት ነግሮች አሉ። በአንድ የጅኦግራፊ ከበባ፣ በአንድ አገር ውስጥ እጣ ፈንታው የተሳሰረበት ድኃ ሕዝብ ከችግሩ ለመላቀቅ ጎሰኛ መሪዎቹን አጅቦ መተላለቅ ነው ያለበት ወይስ የሚያስተባብረውን አማካይ ፈልጎ የጋራ ጠላቱን፣ ድንቁርናና፣ ድህነትን ቢዋጋ ያዋጣል? ከባድ ጥያቄ እኮ አይደለም! ሌላም ደጋፊ ጥያቄ አለ፤ ወጣቱም ሆነ ሕዝብ በአጠቃላይ ከመሪዎቹ መጠበቅ ያለበት በልቶ፣ ንጹህ ውሃ ጠጥቶ፣ መጠለያ አግኝቶ በሰላም መኖሩን ዋስትና የሚሰጠውን መሬት ላይ ያለውን  ሁኔታ ነው ወይስ ግደለው! ጨርሰው! የሚለውን አመራር?  በኢትዮጵያም ሆነ በብዙ ሌሎች የአፍሪካ አገሮች ሳይደጋገፉ መኖር በምንም አይነት አይቻልም።

በጦርነትም አሸናፊና ተሸናፊነት ትርጉም የለውም! ወይ የዘለአለም ጦርነት ይወለዳል፣ ድኅነትን ዘለአለማዊ ያደርጋል ወይም ያንዱ ሃብታም አገር ጥገኛ ሆኖ መሪዎቹ የበለጠ እየከበሩ፣ በጌቶቻቸው አገር እየተዝናኑ፣ ሕዝቡ የባሰ ሁለተኛ ዜጋ ሆኖ ይማቅቃል። አሳዛኙ የኛ ታሪክ፣  ሁልጊዜም መሪዎችና ስልጣን የያዙት ከሕዝብ የወጡ መሆናቸውን በፍጥነት ስለሚረሱ፣ ምስኪኑን ሕዝብ በአሉባልታ አነሳስተው፣ አጫርሰው እነሱ ወይ ከአገር ወጥተው ይጠፋሉ ወይም ካባቸውን ለዉጠው እንደገና ይረግጡታል! የቅርቡን የወያኔን ታሪክ በአርምሞ ማየት ነው! ከእርስ በርስ ጦርነታችን የሚያተርፈው ማነው? የሚለው ጥያቄ ወሳኝ ነው! ማነው ወሬውንና የሐሰት ስብከቱን ከመስማት ይልቅ፣ መለስ ብሎ በተግባር የሚካሄደውን፣ እናት አባትህ ላይ የሚደርሰውን፣ ጎረቤትህ ላይ የሚፈጸመውን፣ የምታየውን መገምገም ወደ እውነታው ይመራሃል። ምናልባት በዘር፣ በቋንቋ ተጠልሎ የቡድን ተገን ልበሙሉነት ይሰጥ ይሆናል፤ በርግጥ የወጣትነት አንዱ መለያ ጓደኛ ቡድን መቀላቀል ነው። ሆኖም ከመሰሎችህም ክፉና ደግ ስላለ በስመ ጎሳ የሁሉም ጓደኛ አትሆንም። ልበሙሉነት ሌሎችን በጭፍን መከተል ሳይሆን ከአስተዳደግ፣ ከራስ የውስጥ ዝንባሌ ጋር የተያያዘ ነው። መንጋ ውስጥ በመንጋጋት አይፈጠርም።

ባለፉት ጦርነቶች ያተረፉት መቼስ የሞተው ወንድምህ፣ የተሰደዱት አሮጊት እናትህ ሊሆኑ አይችሉም። ማሳው ተቃጥሎ፣ አሁን ደግሞ ማዳበርያ የተከለከለው ገበሬም ሊሆን አይችልም። በዋጋ መናር በልቶ ማደር የሚከብደው ከተሜም ሊሆን አይችልም። በቋንቋው ተለይቶ ቤቱ እላዩ ላይ የፈረሰበት ደካማ አይደለም። ለሆዳም ባለስልጣን ጉቦ የሚያጎርሰውም ሃብታም ኢትዮጵያዊ ነጋዴም አይደለም። አሻፈረኝ ብሎ ጫካ የገባውም ወንድምህ ሊሆን አይችልም። በሐሰት ትርክት፣ ታውሮ የመንግስት ጠበንጃ ይዞ የራሱን የዘር ግንድ ሳያጣራ ወንድሙን ጠላት ብሎ የሚገድል፣ እህቱን የሚያፍን፣ እናቱን የሚደፈር ወሮበላም ተመችቶታል ማለት አይቻልም ስካር አላፊ ደስታ እንጅ ዘላቂ ሰላም አ ያስገኝም።  የጎሳ ስካር፣ የሃብት ስካር፣ የሥልጣን ስካር፣ ሁሉም ያው ነው።

ምናልባት  በአሸናፊነት  የሚወጣው   የኢትዮጵያውያን ደም ምናቸዉም ያልሆነው፣ ከውጭ ሆነዉ የሚያባሉን ባእዳን ብቻ ናቸው። ይህ በተደጋጋሚ በአለም ታሪክ ያየነው ስለሆነ ለማሰረጃ ከጎረቤት አገሮች ጀምረን፣ መካከለኛው ምሥራቅን ይዘን፣ ምሥራቅ አውሮጳን አይተን፣ የደቡብ አሜሪካን ታሪክ መቃኘት ይበቃል። ወጣቱን በጅምላ ማየትም አሳሳች ነው። ጎበዝ ተማሪና ሰነፍ ተማሪ እንዳለ ሁሉ፣  አዕምሮው ሰፊና ጠባብ ወጣት አለ። ብዙ ጥያቄዎችን የሚያነሳ፣ አመዛዝኖ የራሱን ውሳኔ የሚከተል አለ። ስሜቱን አዕምሮው የሚገዛው ሰው ማንኛውንም ውሳኔ ቢወስድ፣ ስኅተት መሆኑ እንኳን በሁዋላ ቢገለጽ፣ እንደመንጋ ስላልተነዳ በራሱ ጥንካሬ እረፍት ያገኛል። ለበደል፣ ለዘረኝነት ከምገዛ ጦሜን አድራለሁ ብሎ የሚነሳም የነቃ ወጣት ሞልቷል። እንደዚህ ያለው ወጣት የትብብርና የድርጅትን ወሳኝነት፣ የአላማ ጽናትን ይርረዳል። የመምራትም ሆነ በስራ ክፍፍል የመመራት ብቃትን ያዳብራል። በያንዳንዱ ክፉ ዘመን ውስጥ፣ የራሱን ጥቅም ትቶ ለሰብዓዊነት የሚታገል ነበረ። ናዚዎችን ሲታገሉ የሞቱ ብዙ ሺህ ጀርመኖች ነበሩ።በጣሊያንም፣ በራሳችን አኅጉር አረመኔውን የአፓርታይድ አገዛዝ የታገሉ ነጮችም ነበሩ።

ወጣቱ የመጭው ጊዜ ባለቤት ነው። ስለሆነም ዛሬ ታላላቆቹ የሚያበላሹትን አሻፈረኝ ለማለት ግንዛቤ ያስፈልገዋል። በየተሰማራበት መስክ ኃላፊነቱን አርቆ አስቦ፣ ለልጆቼ፣ ለወደፊቱ ትውልድ ምን ጥቅም አተርፋለሁ ብሎ  ቢያስብ ከብዙ ስኅተቶች ይድናል። የታሪክ አተረጓጎም በአጠቃላይ አሻሚ ሊሆን ቢችልም፣ ከታሪክ የምንማረው አንዱ፣ ለውጥ አይቀሬ ስለሆነ፣ ቁምነገሩ ባለፈው መነታረክ ሳይሆን ተወያይቶ አዲስ መፍትሔ ማግኘት መሆኑን ነው። ኢትዮጵያ ብዙ ጥሩም፣ መጥፎም የታሪክ ምሳሌዎች አሏት! አሁን አገራችን ከገደል አፋፍ ላይ ቆማ መተከዝ ከጀመረች 30 አመት አለፋት። አገራቸውን በደማቸው አድነው ይኸው እኛ እንድንኖርባት ያቆዩን ጀግኖች ነበሯት። ኤርትራው፣ ትግሬውና አማራው በሰሜን ያልተሳሰረበት ታሪክ የለም። ደቡቡ፣ ምስራቁ፣ ምዕራቡ ከሰሜኑ ጋር ያልተጋባበት፣ አብሮ ያልኖረበት ጊዜ አለ? እርስ በርስ ተዋግቶ፣ ተመልሶ ተጋብቶ ያልተዋለደ አለ? አብሮ ያልገዛበት ጊዜ አለ? በአንጻሩ፣ ሌሎች ደግሞ እንድንበታተን ምለው፣ ከጠላቶቻችንም ጋር አብብረው እስካሁን ሁሉንም እያባሉ የሚኖሩም አሉ። ዋነኛው መሳሪያቸው ደግሞ የሃሰት ትርክትና ስሜት መቀስቀሻ እኩይ ፕሮፓጋንዳ ነው። ኢትዮጵያ የብዙ ደም ቅይጥ አገር ናት። ምሁር ነኝ ፣ ነቅቻለሁ ብለህ ወንድምህን ስታስገድል፣ የአያትህን፣ ወይም የምጅላትህን ደም ታጠፋለህ። አባትህን ከእናትህ ዘር ስትነጥል፣ ግማሽ አካልህን ታጣለህ፣ የሌለ ትርክት ተግተህ  አፈሙዝ ስታነሳ፣ አፈር ፈጭተህ ያደግኸውን አብሮ አደግህን ታጣለህ፣ ከትዳር ጓደኛህን ትለያያለህ። ዘርህ ይጠፋል! ጥላቻን፣ ቂምን፣  ለልጅህ፣ ለልጅ ልጅህ፣ ለብዙ ትውልዶች ታስተላልፋለህ።

1 Comment

  1. ጠ/ሚሩ በየደረሰበት ስለ ህዳሴና ስለ መጪው የኢትዮጵያ ከፍታ ሲናገር እልፎች እየታሰሩ፤ እየተገደሉ፤ ሌሎች ደግሞ ወደ ወለጋ (ደንቢደሎ) ኮሌጅ ለትምህርት ሲሄድ ታፍነው ከተወሰድ እንሆ ወራታት ተቆጥረዋል። በሃገሪቱ ውስጥ ስላለው ትርምስ ግን ምንም የሚናገረው ነገር የለም። የሚገርመው ልክ እንደ በፊቶቹ እብድ ፓለቲከኞች ” እናሸንፋለን” ሲል መሰማቱ የእብደቱን ከፍታ ሰማይ ያደርሰዋል። በኢትዮጵያ ፓለቲካ ታሪክ ውስጥ ያሸነፈ አንድም ሃይል የለም። የጠገበውን አውርዶ የተራበውን መተካት ለውጥ አይባልም። ሰው እንዴት ነው እርስ በእርሱ ተጋሎና ተቃምቶ አሸነፍኩ የሚለው? ትላንት ኢትዪጵያን ሲኦል ድረስ ወርደን እናፈርሳታለን ያለውን ጌታቸው ረዳንና ወያኔን አቅፎ ዛሬ ፋኖንና አማራን የሚያሳድደው የኦሮሞ ስብስብ ምን እሚሉት ፓለቲካ ነው እንዲህ ጭንቅላታቸው ላይ የወጣው? ታዳጊ ልጆችን ከመንገድ እየጠለፉና እያፈሱ ለመከራ መዳረግ ለኦሮሞ ህዝብ ብልጽግናና ሰላም ይጠቅማል ብለው የሚያስቡ እብዶች ሰው መሆናቸው ቀርቶ አውሬ ሆነዋል። ለነገሩ ሃበሻው እብድ ነው። በየሄደበት ሁሉ በዚህም በዚያም እየተቧቀሰ ዞሮ ተመልሶ ያስጠለላቸውን መንግስት ይህን ግፍ አደረሱብን፤ ጨፈጨፉን ሲሉ መስማት ያማል። ግን ነገርን በቡጢና በጠበንጃ ብቻ ሊፈታ የሚታገል የሙት ፓለቲካ አመታት ተቀየሩ አልተቀየሩ ያው በጎሳውና በዘሩ፤ በቋንቋው ተከፋፍሎ አንድ የጊዜውን መንግስት ደግፎ ሌላው አይ አይመችም በማለት ቢቀጣቀጡ ጉድ አያስብልም። ሰው የኖረበትን ይመስላልና። ትላንት በሃገር ቤት ውስጥ በየፓለቲካ ድርጅቱና በመንግስት መዋቅር ውስጥ ስር ሲያስሩ፤ ሲገድሉ፤ ሲደበድቡ የነበሩ የፓለቲካ ትራፊዎች ዛሬ ላይ በውጭ ሃገር ሆነው ያስጠለላቸውን ሃገር ቢያምሱ ጉድ አይባልም። ብዙው ታሞ ነውና ባህር የተሻገረው!
    በዓለም ዙሪያ በነጩና በአረቡ በቆዳ ቀለማቸው ተገለው እንግልትና መከራ ለሚደርስባቸው በዓለም ላይ ላሉ ጥቁር ህዝቦች እንደመፋለም ውጊያችን ሁሉ በራፋችን ላይ ሆነና ወዳጅ ሲስቅ ጠላት ደግሞ በቅርብም በሩቅም እሳት እያቀበለን ስንተላለቅ ደግመው ተመልሰው አስታራቂ መስለው ይሰለፋሉ። አሁን በፋኖና በወታደሩ መካከል ያለው ግጭት በጭራሽ መፈጠር ያልነበረበት ግጭት ነው። ግን በዚህም በዚያም ጎራ እያሉና ባለጊዜዎቹ የሰውን መብት ገፈው እኛ የማንገፋ ተራራ ነን በማለታቸው ምክንያት ዛሬ ሰው እየገደለ ይሞታል። የሚያሳዝነው በጠ/ሚሩ ዙሪያ ያሉ ሰዎች እንዴት እውነት አፍጣ እየመሰከረችላቸው ዝም ብለው እንደ ከብት አብረው ይነዳሉ? ሰው ኑሮ አስመርሮት፤ ዘመድ አዝማድ በዘሩ ተመንዝሮ ታፍኖ፤ የምታጠባ እናት ጭምር ታስረው፤ ተገለው፤ ተደብድበው እንዳላዪ፤ እንዳልሰሙ ዝም ማለት በህዋላ በምንም ሂሳብ ከተጠያቂነት ማምለጫ አይኖረውም። አቶ ሬዲዋን ” የሚሉሽን ብትሰሚ ገቢያ ባልወጣሽ” ብሎ የተረተብን ከወያኔ ጋር በናይሮቢ ሂሳብ ሰርቶ የአማራ መሬትን ለማስረከብ ቃል ስለገባ ነው። እነዚህ ነፎዞች የሽቅብ ይሁን የቁልቁል ሂሳቡን የሚደምሩት ውጤቱ ግን ባዶ ነው። በታሪክ ወልቃይት፤ ራያና ጠለምት የትግራይ ሆነው አያውቁም። ታዲያ ይህና ሌላውም የኦሮሞ ሴራና የአማራ ጥላቻ ፓለቲካ በቆሰቆሰው እሣት አሁን ሰራዊት እየላኩ መፋለሙ መደመርን ሳይሆን መቀነስን ነው የሚያሳየው። ለዚህ ነው የአማራ ገበሬ ታግሶ ታግሶ ሲነሳ እንዲህ ብሎ ያቅራራው። “አጋግመውና እርጥቡን ከደረቅ መንደድስ አይነድም ጭሶ|2|ይለቅ ያለው። ዛሬ የሚሞቱት የታጠቁት ብቻ አይደሉም፤ አርሰው የሚያበሉን፤ ወልደው ያሳደጉን እናቶች እህቶችና ህጻናት አልፎ ተርፎም እንስሳት ጭምር ናቸው።
    2016 አሃድ ብሎ ቀኑን ጀምሯል። አንድ የግዕዝ አዲስ አመት ሲለው ሌላው ደግሞ የኢትዮጵያዊያን አዲስ ዓመት ይለዋል። ይህ ኢትዮጵያ ለሚለው ስም ያላቸውን ጥላቻ ያሳያል። እንክሮ ፓለቲካ ሁልጊዜ እኔ የምለውን ብቻ ተቀበል ነው የሚለው። የዘር ፓለቲካ የውሻ ፓለቲካ ነው። ዝንተ ዓለም መነካከስ። ግፍ የሚፈጸምበት ህዝብም ሆ ብሎ ሲነሳ ድሮን፤ አውሮፕላን፤ ሄሊኮፕተር፤ ቀይ ለባሽ ነጭ ለባሽ አያስቆመውም። ጊዜ እያለ ስለ ሰላም መከሮ በሰላም መኖር አማራጭ አይገኝለትም። መልካም አዲስ ዓመት!

Leave a Reply

Your email address will not be published.

185706
Previous Story

የግንባር መረጃ!/ ደቡብ ጎንደር ጋሳይ፣ እስቴ፣ አንዳቤት!/ ኦራሉ ከነ ተተኳሹ ተማረከ!

Oromo 6 1 1 1
Next Story

ኢትዮጵያን ያለ ኢትዮያዉያን ማሰብ እንዴት ይሆናል ?

Go toTop