‹‹ በርካታ ሰዎች የሰሌዳ ቁጥር በሌላቸው መኪኖች ጭምር በጅምላ ታስረው፣ ወደ አዋሽ አርባ እየተወሰዱ ነው ›› – ኢሰመጉ

‹‹ መንግስት፣ ክርስቲያን ታደለ፣ ካሳ ተሻገር፣ በቃሉ አላምረው እና አባይ ዘውዱ ታስረው የሚገኙበትን ቦታ ያሳውቅ ›› – ኢሰመጉ

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ(ኢሰመጉ) ‹‹ የሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት አባሉ ክርስቲያን ታደለ፣ የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባሉ ካሳ ተሻገር፣ ጋዜጠኛ በቃሉ አላምረውና አባይ ዘውዱ ታስረው የሚገኙበትን ቦታ ለቤተሰቦቻቸውና ለጠበቆቻቸው እንዲያውቁ እንዲደረግ ›› ጠይቋል፡፡

ጉባዔው ይህን የጠየቀው ነሐሴ 26 ቀን 2015 ዓ.ም ‹‹ በአዲስ አበባ ከተማ ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እና በአማራ ክልል እየተፈጸሙ ያሉ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች በአስቸኳይ ሊቆሙ ይገባል ›› ሲል ሰይሞ ባወጣው መግለጫ ነው፡፡

ኢሰመጉ ‹‹ አሁንም ድረስ የጅምላ እስሮች በአዲስ አበባ ከተማ እየተፈጸሙ ነው ›› ብሏል፡፡

‹‹ እነዚህ እስሮች የህግ ስነስርዓትን ያልተከተሉ እና አንዳንዶቹም አስገድዶ የመሰወር ባህሪ ያላቸው ናቸው ›› የሚለው ኢሰመጉ ‹‹ ከታሳሪ ቤተሰቦች ባገኛቸው መረጃዎች በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በአዲስ አበባ ፖሊስና በፌደራል ፖሊስ አንዳንዶቹም የሰሌዳ ቁጥር የሌላቸውን መኪናዎች ጭምር በመጠቀም ከተያዙ በኋላ ወደ አፋር ክልል አዋሽ አርባ እንደሚወሰዱ ›› ተገልፆልኛል ባይ ነው፡፡

ጉባዔው ‹‹ ይህንን ጉዳይ አስመልክቶ ለተለያዩ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት በደብዳቤ ማብራሪያ ቢጠይቅም ይህ ሪፖርት እስከተዘጋጀበት ጊዜ ድረስ ምላሽ ማግኘት አለመቻሉን ›› አመልክቷል፡፡

‹‹ ከእዚሁ ጉዳይ ጋር ተያይዞ ሐምሌ 28 ቀን 2015 ዓ.ም የተያዙት የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት አባል ክርስቲያን ታደለ እና የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባል ካሳ ተሻገር ከተያዙበት ጊዜ አንስቶ በፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ታስረው ከቆዩ በኋላ ነሀሴ 15 ቀን 2015 ዓ.ም ልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ተብሎ ሲጠበቅ የነበረ ቢሆንም ፖሊስ ሁለቱንም ግለሰቦች ፍርድ ቤት ሳያቀርብ መቅረቱን ›› አስታውሷል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የኦነግ ታጣቂ ጦር የ100 ዓመት ሽማግሌን በአሰቃቂ ሁኔታ በቤታቸው ውስጥ እንደገደለ ኢሰመጉ ገለፀ

‹‹ ይህ ሪፖርት እስከተዘጋጀበት ጊዜ ድረስ ያለመከሰስ መብታቸው አልተነሳም እንዲሁም ያሉበትን በግልጽ ለማወቅ አልተቻለም፡፡ ›› ብሏል፡፡

‹‹ ሐምሌ 30 ቀን 2015 የአልፋ ሚዲያ የበይነ መረብ መገናኛ ብዙኃን መስራች እና ባለቤት የሆነው ጋዜጠኛ በቃሉ አላምረው እና ነሀሴ 04 ቀን 2015 ዓ.ም በፌደራል ፖሊስ አባላት የተያዘው ጋዜጠኛ አባይ ዘውዱ ›› መታሰራቸውን በተመሳሳይ ያስታወሰው መግለጫው ‹‹ ጋዜጠኛ አባይ ዘውዱን አስመልክቶ በተሰበሰበ መረጃ መሰረት ጋዜጠኛው በሐምሌ 15 ቀን 2015 ዓ.ም ወደ አዋሽ አርባ መወሰዱን ቤተሰቦች ከተለያዩ ምንጮች እንደሰሙ ነገር ግን ማረጋገጥ እንዳልቻሉ ›› ነግረውኛል ብሏል፡፡

ጋዜጠኛ በቃሉ አላምረው ግን ይህ ሪፖርት እስከሚዘጋጅበት ጊዜ ድረስ ያለበትን ማወቅ እንዳልቻሉ ገልጸውልኛል ሲሉ ይፋ አድርጓል፡፡

‹‹ በአዲስ አበባ ከተማ የሚደረጉ የአስገድዶ መሰወር ባህሪ ያላቸው እስሮች በአስቸኳይ እንዲቆሙ ›› ያሳሰበው ኢሰገሙ ‹‹ የፌደራል ፖሊስ አባላትና የአዲስ አበባ ፖሊስ አባላት በከተማው የሚፈጽሙትን ህግን ያልተከተለ የጅምላ እስር እንዲያቆሙና ስልጣናቸውን አላግባብ ከመጠቀም እንዲቆጠቡ፣ ይህንንም የሚፈጽሙ አባላት በህግ እንዲጠየቁ ›› ሲል ጠይቋል፡፡

መረጃው የአሻም ቲቪ ነው።

1 Comment

  1. ጎበዝ ሰሌዳ ከየት ይምጣ ትግሬዎች ከአማራና ከአፋር ክልል የሰረቁት እኮ ነው ንብረትነቱ ወደ ባለቤቶቹ እንዲመለስ ኦነጎች መጣር አለባቸው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share