የኢትዮጵያ ህዝብ ትህነግ/ወያኔ መራሹን ፋሽታዊ ቡድን በህዝባዊ አመፅ ሲያስወግድና የብልፅግና መንግስት የኢትዮጵያን መንግስታዊ ስልጣን ለመቆጣጠርና ብሎም ለማፅናት በተጓዘባቸው የአምስት አመታት ጉዞ ውስጥ ዋነኛው የትግሉ ሞተርና ደጀን በመሆን ወደር የለሽ መስዋዕትነት የከፈለው የአማራ ወጣት፣ የአማራ ምሁርና ፖለቲከኛ፣ የአማራ ልዩ ሃይልና ፋኖ መሆናቸውን ወዳጅም ሆነ ጠላት በይፋ የመሰከረው ሀቅ ነው።
የዶ/ር አብይ አህመድ መንግስት የአማራን ህዝብ መሰረታዊ እድሜ ጠገብ ፍትሃዊ ጥያቄዎች በአደባባይ ቆጥሮና ሰፍሮ እንደተረከበ መናገር የጀመረውና ለጥያቄዎቹም ምላሽ ለመስጠትም ይምልና ይገዘት የነበረው ወደ ስልጣን ከወጣበት ከመጋቢት 2010 ዓ.ም ጀምሮ ነው።
በተለይም ፋሽስቱ ትህነግ/ወያኔ የሀገር መከላከያ ሰራዊትን በማጥቃቱና የሰሜን ዕዝን አባላትን በደረቅ ሌሊት በጀምላ በመጨፍጨፉ ምክንያት መንግስት በጠራው የክተት አዋጅ ኢትዮጵያ ሀገሩን ለማዳንና ህዝቡን ከጥፋት ለመታደግ ቀድሞ የተሰለፈውና የጦር ግንባር ላይ የደረሰው የአማራ ልዩ ሃይል፣ የአማራ ፋኖና ወጣት፣ በአጠቃላይ የአማራ ህዝብ ለመሆኑ ከማንም በላይ ምስክሮቹ ጠ/ሚ አብይ አህመድና በህይወት የተረፉት የሰሜን ዕዝ አባላት ናቸው።
በተለይም ትህነግ/ወያኔ ዳግም እንዳያንሰራራ ሆኖ አከርካሪው እንዲሰበርና ለአንዴና ለመጨረሻ ግዜ እንዲንበረከክ የአማራ ልዩ ሃይልና ፋኖ ተጋድሎና ሚና በጀግንነትና በጀብዱ የተሞላ እንደ ነበር ምስክሮቹ እነ ኢታማጆር ሹሙ ብርሃኑ ጁላና ምክትላቸው አበባው ታደሰ ብቻ ሳይሆኑ የወያኔ የጦር መሪዎች ጭምር ነበሩ።
የአማራ ህዝብ ከትህነግ/ወያኔ መንበርከክ ማግስት ሀገር ሰላም ሆና ለዘመናት የታገለላቸውና ውድ ልጆቹ የተሰውለት የማንነት፣ የፍትህ፣ የእኩልነትና የዲሞክራሲ ጥያቄዎቹ ይመለሱልኛል በሚል በጉጉት በመጠባበቅ ላይ ነበር።
በተለይም ህዝባችን የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ሙሉ በሙሉ እንዲተገበር ነቅቶ በሚጠብቅበትና በሚጠይቅበት ወቅት የክልሉን አንፃራዊ ሰላምና መረጋጋት ለማተራመስ የብልፅግና መንግስት በ አለፉት 9 ወራት ብቻ የሚከተሉትን ክህደቶች በአማራ ህዝብና በክልሉ ላይ ፈፅሟ።
1ኛ. የአማራ ልዩ ሃይልን ከሁሉም ክልል ለይቶ ለማፍረስና ለመበተን የተደረገው የእብሪትና ህገ-ወጥ ዘመቻ፣
2ኛ. የአማራ ህዝብን ብቻ ለይቶ የዜግነት መብቱን በመግፈፍና ኢሰብአዊ በሆነ ሁኔታ ወደ አዲስ አበባ እንዳይገባና እንዳይወጣ በመከልከልና በማዋከብ የተከፈተበት የዜግነት መብት ገፈፋ፣
3ኛ. በአዲስ አበባና አካባቢዋ የሚኖሩ የአማራ ተወላጆችን ቤት በጀምላ በማፍረስና ጎዳና ላይ በመበተን የተፈፀመበት ፍፁም አረመኔያዊ ግፍና በደል፣
4ኛ. በተለይም የኦሮሞ ክልላዊ መንግስትና ብልፅግና ፓርቲ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክ ቅዱስ ሲኖዶስን ለመከፋፈልና ለማዳከም በከፈቱት አሳፋሪና አስነዋሪ ጥቃት ሀገርና ህዝብን ጥቁር ማቅ ከማስለበስ አልፎ በአማራ ህዝብ ቀደምት ዕምነቱና በትውፊቱ ላይ የተከፈተ ጥቃት መሆኑ፣
5ኛ. ከላይ በዝርዝር የተጠቀሱትንና ሌሎችንም የአማራ ህዝብ ሰላማዊ ጥያቄዎችና ብሶቶች አንግበው የሚታገሉና የተቃውሞ ድምፃቸውን ያሰሙ የአማራ ወጣቶች፣ ምሁራን፣ ጋዜጠኞች፣ የማህበረሰብ አንቂዎች፣ ፖለቲከኞችና፣ ባለሃብቶች በጀምላ በማሰርና በማሰቃየት፣
6ኛ. በመጨረሻም የአማራ ልዩ ሃይልን ከህግ አግባብ ከመርህ ውጭ አፈርሳለሁ በሚል የተቀሰቀሰው ግጭት ሳይረጋጋና ክልሉ ሰላም ርቆት በሚገኝበት ሁኔታ ፋኖን ትጥቅ አስፈታለሁ በሚል ሰበብና አላስፈላጊ ትንኮሳ አጠቃላይ ክልሉን ሆን ተብሎ ወደ አለመረጋጋትና ወደ ቀውስ ለማስገባት የብልፅግና መንግስት በህዝባችን ላይ የከፈተው ሁለገብ ጦርነት፣
በአጠቃለይ በተቀነባበረና በተጠና ሁኔታ የአማራ ህዝብ ላይ የተከፈቱ መንግስታዊ ጥቃቶች፣ ሽብሮችና፣ ማዋከቦች በእጅጉ ያሳዘነንና ያስቆጣን ከመሆኑ ባሻገር፥ ይህ ፀረ-ሰላምና ፀረ-ህዝብ ድርጊት በህዝባችን ላይ የተፈፀመ የብልፅግና መንግስት ይፋዊ ክህደት ነው ብለን እንድናምን አስገድዶናል።
በመሆኑም የአማራ ልዩ ሃይል አባላት፣ የአማራ ፋኖ፣ የአማራ ወጣቶችና፣ መላው ህዝባችን ይህን የብልፅግና መንግስት የክህደት ጥቃት ለመመከትና የዜግነት መብቱን ለማስከበር በሁሉም የአማራ መሬቶች ላይ እያደረጉት የሚገኙት ትግል የአማራ ህዝብ የህልውና ትግል ነው ብለን በፅኑ እናምናለን። ስለሆነም፦
1ኛ. አሁን በአማራ ህዝብ ላይ እየደረሰ ለሚገኘው እልቂትና በክልሉ ላይ ለሚደርሰው ማንኛውም የሰው ህይወት መጥፋት፣ የንብረት ውድመት፣ የሰላም እጦትና ኪሳራ ሁሉ ተጠያቂው ጠ/ሚ አብይ አህመድና በእርሳቸው የሚራው የብልፅግና መንግስት ነው!
2ኛ. ፋኖ የሀገር ዘብ፣ ፋኖ የሀገር አለኝታ፣ ፋኖ የህዝብ ልጅ፣ ፋኖ አራሽ ቀዳሽ ተኳሽ ጀግና ነው! ፋኖ እስከ አሁን በተጓዘበት ብስለት የተሞላበት አማራዊ ጀግንነትና ጨዋነት ትግሉን እጠናክሮ እንዲቀጥል አደራ እያልን፥ የብልፅግና መንግስት በአማራ ክልልና በሀገራችን ላይ ያነገሰውን ስርአት አልበኝነት እያስተካከለና ስርአት እያስያዘ ትግሉን በታላቅ ሀገራዊ ሃላፊነትና በህዝባዊ አደራ እንዲያካሂድ በአንክሮ አናሳስባለን።
3ኛ. በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ የምትገኙ ውድ የአማራ ልጆች! ዛሬ በብልፅግና መንግስት የገጠመን ክህደት አዲስ አይደለም። ነገር ግን ከምን ግዜውም በላይ የአማራ ህዝብ ብሶትና በደል ጫፍ ላይ በደረሰበት ወቅት መሆኑ በቀላሉ በአንድነት እንድንቆም አድርጎናል። ስለሆነም አንድነታችን አጠንክረን በሁሉም አቅጣጫ የተቃጣብንን ጥቃት በመመከትና መልሶ በማጥቃት የአማራን ህዝብ እኩልነትና ዲሞክራሲያዊ መብቶች እናረጋግጣለን። መገናኛችን የድላችን ጫፍ ላይ ይሁን!
4ኛ. የብልፅግና መንግስት በአማራ ህዝብና በክልሉ ላይ የከፈተውን ወታደራዊ ወረራና ዘመቻ በአስቸኳይ እንዲያቆምና ጦሩንም ወደ ካምፑ እንዲመልስ እናሳስባለን!
5ኛ. ለዘመናት ሲንከባለሉ የቆዩትና እስከ ዛሬ ድረስ ምላሽ ያላገኙት የአማራ ህዝብ መሰረታዊ የማንነት፣ የፍትህ፣ የአኩልነት፣ የሀገር ባለቤትነትና፣ የዜግነት ጥያቄዎች በአስቸኳይ ምላሽ እንዲሰጣቸው እናሳስባለን!
6ኛ. በግፍና በጀምላ የታሰሩ የአማራ ወጣቶች፣ ምሁራን፣ ጋዜጠኞች፣ የማህበረሰብ አንቂዎች፣ ፖለቲከኞችና፣ ባለሃብቶች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱና በእነዚህ ወገኖች ላይ የተጀመረው ማሰቃየት በአስቸኳይ እንዲቆም እናሳስባለን!
7ኛ. መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በግልፅ እንደሚያውቀውና እንደሚከታተለው የአማራ ህዝብ በብልፅግና መንግስት አማካኝነት በማንነቱ ላይ በይፋ ተዘምቶበታል፣ በቤተክርስቲያኑ ላይ ተዘምቶበታል፣ በሀገሩ ባለቤትነቱ ላይ ተዘምቶበታል፣ በሀገሩ ላይ በነፃነት እንዳይንቀሳቀስ ተዘምቶበታል፣ በህልውናው ላይ ተዘምቶበታል፣ ወዘተ ስለሆነም የኢትዮጵያ ህዝብ ስለፍትህና ርትዕ ሲል ከወገኑ ከአማራ ህዘብ ጎን እንዲቆም ጥሪ እናቀርባለን!
8ኛ. የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የህዝብና የሀገር ሰላምና ደህንነት ዘብ እንጂ የብልፅግና መንግስት ስልጣን ጠባቂ አንዳልሆነ እናምናለን። “በህዝብ የተመረጠ መንግስት” በእብደትና በሴራ ተጠልፎ ሰላማዊ ህዝብ ላይ ጦር ሲያዘምት ቆሞ ማሰብና ማስተዋል የእያንዳንዱ መለዮ ለባሽ ሃላፊነትና ግዴታ ነው። ስለሆነም የብልፅግና መንግስት በክህደት ናውዞ በአማራ ህዝብ ላይ ያወጀውን የጦርነት አዋጅ በመቃወምና ትዕዛዙንም ባለመቀበል ከህዝባችሁ ጎን እንድትሰለፉ ጥሪ እናቀርባለን!
9ኛ. ትግሉ ህዝባዊ ነው! የአማራ ህዝብ ላይጨርስ አይጀምርም! ስለሆነም በሁሉም አቅጣጫ የተጀመረው ፍትሃዊ ትግልና እራስን ከጥቃት የመከላከል ዘመቻ በሁሉም መስክ ተጠናክሮ እንዲቀጥልና የአማራ ህዝብ ጥያቄዎች ተቆጥረውና ተሰፍረው ፍትሃዊ ምላሽ እስኪያገኙ ድረስ ከህዝባችን ጎን በመቆም ትግሉ የሚጠይቀውን ማንኛውንም ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ መሆናችንን ስናረጋግጥ ታላቅ ኩራት ይሰማናል!
ድል ለአማራ ህዝብ! ድል ለፋኖ!
ልሳነ ግፉዓን ድርጅት
ሃምሌ 28/2015 ዓ.ም