❝እኔ ኢትዮጵያዊያንን አላምንም ከራሴ ጀምሮ” በዓሉ ግርማ ፥ የቀይ ኮከብ ጥሪ ፥ ገፅ 234

❝እኔ ኢትዮጵያዊያንን አላምንም ከራሴ ጀምሮ። በጭንብል ተሸፍነን የምንኖር ህዝቦች ነን። ለሰው የምናሳየው ገፅታና እውነተኛው ባህሪያችን የተለያዩ ናቸው። እንደ ተረታችን ፣ ስነ ፅሁፋችንና ንግግራችን ባህርያችንም ሰምና ወርቅ ነው …

    ❝በዚህ ላይ ደግሞ ክፉውና በጎውን ነገር አንዱን ከሌላው ለይተን የምናይበት መለኪያ የለንም ፤ የማንኛውም ነገር መሠረታዊ መለኪያችን የግል ጥቅማችን ነው። ለዚህም ነው ተንኮል የሚበዛው፤ መተማመን የሌለው፤ የወዳጅነት ወይም የጓደኝነት ትርጉሙ የማይታወቀው ፤ ሀሜት አሉባልታና እርስ በዕርስ መበላላት የሚበዛው። ኢትዮጵያዊያን ስንባል የምናውቀው መርህ አንድ ብቻ ነው ፤ የግል ጥቅም! ከራስ በላይ ነፋስ ፤ እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል… ሰውን ማመን ቀብሮ ፥ ይሉታል ከነተረቱ። የሚያሳዝን ነው…
    ❝ለግል ጥቅማችን የሚበጅ ከሆነ እንዋሻለን። ስንዋሽ ህሊናችንን ቅንጣት ታህል አይቆረቁረንም። እንዴት አድርጎ ለግል ጥቅም የተገዛ ህሊና ሊቆረቁረው ይችላል ?
    ❝ለተንኮል አንመለስም የምንሸርበው ተንኮል ጓደኛን፤ ወዳጅን ፤ የስጋ ዘመድን አይለይም ቅናት ባህላችን ነው።
    ❝ምግባር የሚባለውን ነገር በአፍ ካልሆነ በቀር በተግባር አናውቀውም። በአጠቃላይ ክፉውንና በጎውን ለይቶ የሚያይ ህሊና የለንም፤ ያስተማረንም የለም። የተማርነው ነገር ቢኖር በአደባባይ ሰው መስሎ መታየትን ነው፤ ሰው መሳይ በሸንጎ ይሉ የለም? በአደባባይ ሁሉም ጨዋ፣ ልበ ሙሉ፣ ጀግና፣ አትንኩኝ ባይ፣ ኩሩና ቅን፣ በጎ አሳቢና ታማኝ፣ አስተዋይና ትሁት ነው። በአደባባይ የምናጠልቀው ጭንብል ይህ ነው። በግል ኑሮአችን ግን ከስብቅ ፣ ከምቀኝነት ፣ ከተንኮል፣ ከቅናት ፣ ለውሸት፣ ከአሉባልታና ከሀሜት፣ ለግል ጥቅም ለመልከስከስና ለመልፈስፈስ ከፍርሃትና ከአድር ባይነት ርቀን አንገኝም። መለያ ባህርያችን ግብዝነት ነው። የግብዝነት ጭንብል አጥልቀን ነው የምንኖረው። ያለ ጭንብል እናስቀይማለን… ወይም እናምራለን፤ አይታወቅም። ያለ ጭንብል ታይተን አናውቅማ!
 በዓሉ ግርማ ፥ የቀይ ኮከብ ጥሪ ፥ ገፅ 234
ተጨማሪ ያንብቡ:  ግልጽ ደብዳቤ ለሰማያዊ ፓርቲ አመራር አባላት (አማኑኤል ዘሰላም)

1 Comment

  1. በልጅነቴ ከህሊና ደወል ጀምሮ ድንቅ መጽሃፍቱን በማንበብ ያደግሁ ከልጆቹ ጋር ኮሌጅ በመማር ጉዳታቸው ያየሁ የደራሲ በአሉ ግርማ ይህ ትንታኔ ለእኛ ኢትዮጲያዊያን ብቻ ሳይሆን ለሁሉም የሰው ዘር የተሰጠ መለያ ነው:: ትልቁ መጽሃፍም ሁሉም በድሏል ይላልና ወደቀናው መንገድ በመመለስ በክፋት እርስ በርሳቸው የተላለቁ አውሮፓዊያን አሜሪካዊያን እስያውያን ሆነ አፍሪካዊያን ወደከፍታው ሊመጡ እንደሚችሉ እምነቴም ትልቁ ቅዱስ መጽሃፍም ይመሰክራልና በዚህ ህዝባችንን የመጉዳት ትንታኔ ይቁም እንሰማራ እንመለስ::
    ፓስተር ኤዲ /አደፍርስ ሃብቴ መካሻ
    https://stmarkomaha.org/immpact/

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share