June 25, 2023
ጠገናው ጎሹ
ነገረ አስተሳሰባችንና ነገረ ሥራችን ሁሉ ባለጌና ጨካኝ ገዥ ቡድኖች እየተፈራረቁ የሚያወርዱብንን መከራና ውርደት ማስቆም በሚያስችል ፅዕኑ ራዕይ ፣ መርህ፧ ዓላማ ፣ ስትራቴጅ፣ ግብ ፣ እቅድ፣ አደረጃጀት እና የተግባር ውሎ ላይ የተመሠረተ ባለመሆኑ ቀንና ሌሊት የሚፈራረቁበትን ስዓታት እንኳ ሳይጠብቅ ከሚንጠን የሃዘን ማእበል ፣ በደም እንባ ጎርፍ ከሚያጥለቀልቀን አስፈሪ ሁኔታ፣ አሰቃቂው የእኩያን ገዥዎች ሥርዓት ከሚተፋብን የእሳት እቶን ፣ ለዘመናት ከዘለቀውና አሁንም ለማመን በሚያስቸግር ሁኔታ እያሸማቀቀን ካለው የድህነትና የተመፅዋችነት ሃፍረት ፣ ገዳይዮችንና አስገዳዮችን እየተማፀን ከቀጠልንበት ከፉ አዙሪት ፣ የገዛ ራስ ስንፍና እና ውድቀት የሚያስከትለውን ጉስቁልና የሚፀየፈውን ፈጣሪን ሳይቀር ካልወረድክ እያልን ከቀጠልንበት አሳፋሪና አስከፊ አባዜ ሰብረን ለመውጣት በሚያስችል አቋምና ቁመና ላይ አይደለንምና ከምር ቆም ብለን ማሰብን የግድ ይለናል።
ቀዳሚው ተጠያቂ እና የነፃነትና የፍትህ ትግል ዒላማ የባለጌና ጨካኝ የጎሳ/የመንደር አጥንት ስሌት ፖለቲካ ገዥ ቡድኖች ሥርዓት የመሆኑ እውነትነት እንደ ተጠበቀ ሆኖ የዚሁ ሥርዓት “የተሃድሶ ለውጥ ገድል” ፍቅር ሰለባ ለመሆን ፈቃደኛ ሆኑት እንደ ኢዜማ አይነት ተቀዋሚ (ተፎካካሪ) ተብየ ቡድኖችም (አካላትም) ከሃላፊነትና ከተጠያቂነት የሚያመልጡበት መውጫ መንገድ ፈፅሞ የለም። አይኖርምም። የገዳይ፣ የአስገዳይና የአገዳዳይ ገዥ ቡድኖች አጋሮች ብቻ ሳይሆኑ ቀጥተኛ ግብረ በላዎች ናቸውና። አዎ! በንፁሃን ደም የጨቀየ ግብረ በላነት!!!
ይህንን ግልፅና ግልፅ የሆነ የፖለቲካ አስተሳሰብ ድህነት፣ የሞራል ዝቅጠት እና የቁም ሙትነት በአስመሳይ የመግለጫ ጋጋትና የዲስኩር ድሪቶ ለመሸፋፈን መሞከር ከደመ ነፍስ እንስሳት በታች የሚያደርግን ፍላጎት ለጊዜው ያረካ እንደሆን እንጅ ፈፅሞ አያዛልቅም!
የሚያዛልቀው ከዘመን ጠገቡና በአሁኑ ጊዜ ደግሞ እንኳን ለማመን ለማሰብም በሚከብድ ሁኔታ በተረኞች ከቀጠለው ሥርዓት ጋር የፈፀሙትን እኩይ (ያልተቀደሰ) አጋርነት (ጋብቻ) አፍርሶ በእውነተኛ ፀፀትና ይቅርታ በእጅጉ የበደሉትን መከረኛ ህዝብ መካስ ብቻ ነው።
ለሩብ ምእተ ዓመት ህሊናቸውን ሸጠው ሲያገለግሉት የቆዩትን ህወት መራሽ የባለጌዎችና የጨካኞች ሥርዓት በተረኝነት ተቆጣጥረው ለማመን የሚያስቸግር የጭካኔ ሰይፋቸውን በመከረኛው ህዝብ ላይ ካሳረፉት ኦህዴዳዊያን/ኦነጋዊያን/ኦሮሙማዊያን/
ከቀናት በፊት ተዘጋጅቶ የተሰራጨውን የኢዜማ መግለጫ በስሜት ከመጋለብ ክፉ የፖለቲካ ልክፍት ወጥቶ በቅጡ (ሂሳዊ በሆነ አስተሳሰብ ወይም ምልከታ) ላነበበና ለታዘበ የአገሬ ሰው በአብይ አህመድና በካምፓኒው ማለትም ኦህዴድ/ኦነግ/ብልፅግና “መቶ በመቶ እተማመናለሁ” በሚል የመከራውና የውርደቱ ዘመን እንደሚራዘም ካደረጉ የኢዜማ ፖለቲከኞች ለርካሽ ህዝባዊነት (ተወዳጅነት) ሲባል የሚሰራጨውን የመግለጫ ጋጋት ከምር ወስዶ “ጠንካራ ፣የበሰለ፣ የተሻለ፣ ወዘተ” እያሉ ማራገብ ከመሬት ላይ ካለው እጅግ መሪር እውነታ ይልቅ በወረቀት ላይ ነብር እየደነዘዙ የሰቆቃውን ዘመን ማራዘም ነው የሚሆነው።
እንዲህ አይነቱ የልክ ልኩን ነገሩት ወይም የልክ ልኳን ነገሯት ወይም የልክ ልካቸውን ነገሯቸው የልጆች ጨዋታ አይነት ፖለቲካ የባለጌና ጨካኝ ገዥ ቡድኖች መሳለቂያዎችና ሰለባዎች አድርጎናልና ይበቃናል።
እጅግ ልክ የሌለው አድርባይነት ከተጠናወተው የፖለቲካ አስተሳሰብና ከዘቀጠ ሞራል የመነጨው “የመቶ በመቶ የመተማመን” ትርክት ለተፈፀመውና እየተፈፀመ ላለው ምድራዊ ሰቆቃ የራሱን አስተዋፅኦ የማድረጉን መሪር ሃቅ ፈፅሞ ማስተባበል አይቻልም።
ከልብ የሆነ ይቅርታ ለመጠየቅና ከገባበት የፖለቲካ የወንጀለኛ ገዥዎች ክለብ ራሱን ለማግለል ወኔው የጎደለው ኢዜማ እየሞነጫጨረ የሚያነብልንና የሚያስነብበን መግለጫ ፈፅሞ ስሜት አይሰጥም! ከባለጌና ጨካኝ ፍቅረኞቹ (ኦህዴዳዊያን/ኦነጋዊያን/ብልፅግናዊያን) በምንና እንዴት የተሻለ እንደሆነ ለመረዳትም ሆነ ለማስረዳት ፈፅሞ አይቻልም።
አዎ! አገር ለንፁሃን ዜጎቿ (ልጀቿ) ምድረ ሲኦል ስትሆን ምን አደርጋችሁ ተብለው ሲጠየቁ “የጥናት፣ የምክር እና የማስጠንቀቂያ ሰነድ እያዘጋጀን (እየሰነድን) አቅርበናል” በሚል ምላሽ ራሳቸውን እንደ የነፃነትና የፍትህ ተሟጋቾች (ታጋዮች) አድርገው ሊያሳምኑን ሲሞክሩ ህሊናቸውን ጨርሶ የማይጎረብጣቸው ፖለቲከኞች የተሰባሰቡበት ኢዜማ በፖለቲካ ወለድ ወንጀል ለበሰበሰውና ለከረፋው ሥርዓት እድሜ መራዘም ጉልህ ድርሻ ማበርከቱን ለማስረዳት ማስረጃና መረጃ ፍለጋ መድከም አያስፈልገንም።
በእውነት ስለእውነት ከተነጋገርን እጅግ አደገኛ በሆነ የፖለቲካ አስተሳሰብ ካንሰርና መግለፅ በሚያስቸግር የሞራል ዝቅጠት የተበከለውን ሥርዓተ ኦህዴድ/ኦነግ/ብልፅግና “በሰላማዊ ህዝባዊ አልገዛም ባይነት መታግልና ኮርነር ማድረግ ፈፅሞ የመፍትሄ አካል ስላልሆነ ( ዮሃንስ የሚባል የኢዜማ አመራር አባል ከኢሳት ሞጋቾች ኘሮግራም አዘጋጅ ጋር ያደረገውን ቃለ ምልልስ ልብ ይሏል) ትክክለኛው አካሄድ በጥናት ላይ የተመሠረተ ሰነድ (የይፈፀምልን አቤቱታ) እየሰነዱ ማቅረብና መግለጫዎቸን ማውጣት ነው” በሚል ሊያሳምኑን (ሊያቂሉን) ሲሞክሩ ህሊናቸውን ጨርሶ የማይኮሰኩሳቸው የፖለቲካ “ሊቆች” የተሰባሰቡበት ኢዜማ ከመልካም ዜግነትና ከማህበራዊ ፍትህ ጋር ምን አይነት ዝምድና (ግንኙነት) እንዳለው ለመረዳት ፈፅሞ አይቻልም።
እናም በፅዕኑ የታመመ የፖለቲካ ክለብ (ሥርዓት) ሽፋን ሰጭ ሆነው እያለ የፈዋሽነት ወይም የመፍትሄ አካልነት መግለጫ የማዥጎድጎድ ፖለቲካ ጨዋታ ተጫዋቾችን (ተዋንያንን) በግልፅና በቀጥታ በቃችሁ ለማለት እስካልቻልን ድረስ የመከራውና የውርደቱ ዘመን አያጥርምና ልብ ያለው ልብ ይበል!!!