የአብይ አህመድ ከሥልጣን መወገድና የሽግግር መንግሥት አስፈላጊነት (ለውይይት የተዘጋጀ) – አማረ ተግባሩ (ዶ/ር)

#image_title

“ለኔ አብይ አህመድ ሞተዋል። የምመስላቸው በአሜሪካን አገር የሞት ፍርድ ወይም እድሜ ልክ እስራት እንደተፈረደበት dead man walking እንደሚባሉት ነው። አብይ አህመድ ይበላሉ፣ ይጠጣሉ፣ ይተኛሉ ይነሳሉ፣ ይሄዳሉ ይቀመጣሉ አንጂ በቁማቸው ሞተዋል። እኔ ሰአቴን የማየው መቼ ከቤተ መንግሥት … [ተጎትተው] እንደሚወጡ ብቻ ነው” ታምራት ነገራ ፈይሳ የቀድሞ “አዲስ ነገር” ጋዜጣ ባለቤትና ዋና አዘጋጅ፣ የማህበራዊ ሜዲያ ባለሙያና አወያይ ከ”ተራራ ኔትወርክ #Ethiopia# Terara Network” ጋር ባደረገው ውይይት “The PM is a dead Man Walking” በሚል ሳምንታት በፊት ከተናገረው የተወሰደ።

1.የህልውና አደጋ የተጋረጠባት አገር
ኢትዮጵያ ከባድ የሆነ የህልውና አደጋ ገጥሟታል። በአብይ አህመድ አገዛዝ ሳቢያ እየከፋ የሄደው የብሄር ግጭቶች፣ ጥላቻና መከፋፈል ሀገራችንን ሁለንተናዊ ቀውስ ውስጥ በመዝፈቅ፣ የጋራ ቤታችን የምንላትን አገራችንን በመፈራረስ ጫፍ ላይ አድርሷታል። በድህነትና ጉስቁልና የሚሰቃየው የትኛውም የኢትዮጵያ ዜጋ፣ አብዛኛው የብሄር ብሄረሰብ አባላት፣ በኦርቶዶክስ ተዋህዶና እስልምና እምነት ውስጥ ያሉ ንፁሃን፣ ከአብይ አህመድ ኦነጋዊ አገር አፍርሶ (“deconstruct”) መልሶ የመስራት (“construct”)፣ ሄገሞኒክና አምባገነን አገዛዝ ምን አተረፉ ብለን ብንጠይቅ ምንም እንዳላተርፉ ግልፅ ሆኗል። የሚሊዮኖች ኢትዮጵያውያን ሞት ፣ ረሃብ፣ ጉስቁልና፣ ሰቆቃ፣ የሚዘገንን እልቂት፣ መፈናቀል፣ ጦርነትና ስደት የምናየው የቀን ተቀን ሃቅ ነው። በስሙ የሚነገድበት ሰፊው የኦሮሞ ህዝብም ሁለንተናዊ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶቹ እንዳልተከበሩለት፣ እንደቀሩት ኢትዮጵያዊ ወገኖቹ ሰላማዊና የተረጋጋ ህይወት ተነፍጎ ድምፀ አልባ እንደሆነ በርካታ መርጃዎች ያሳያሉ። ባጭሩ ኢትዮጵያውያን ሁሉ በኑሮ ውድነት፣ በረሀብ፣ ስራ አጥነት፣ ከቤት ንብረታቸው በመፈናቀል፣ የእምነት ስፍራቸው እየፈራረሰ፣ ሰብዓዊ መብታቸው እየተደፈረ፣ እየታፈኑና እየተገደሉ፣ ገዳማትና መነኮሳት ሳይቀሩ የጦርነት ዒላማ ሆነው ሊቀጥሉ አይችሉም። ለዚህ ሁሉ የህልውና አደጋ ተጠያቂው የአብይ አህመድ አመራር ክሽፈት መሆኑ ግልፅ ነው። ሰሞኑን መንግሥታዊ ያልሆነው ኢሰመኮ ሊቀ መንበር ያሬድ ሃይለ ማሪያም በአዲስ ድምፅ” ቴሌቪዥን ቀርቦ ከጋዜጠኛ አበበ በለው ጋር ቀርቦ ባደረገው ቃለ ምልልስ የህልውና አደጋው ምን ደረጃ ላይ እንደደረስ እንደሚከተለው ገልጾታል[ Director of the Ethiopian Human Rights Defenders Center and Liaison Official of Defend Defenders with the African Union]፡-

“በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ እጅግ የሚዘገንን የሰብዓዊ መብት ጥስት የተፈፀመው ባለፉት አምስት አመታት ነው። ሰላማዊው የፖለቲካ ትግል ምህዳር በገዥው ፓርቲ የጠበበ ነው ከማለት ይልቅ ጨርሶ የተዘጋ ነው ማለት ይቻላል። ዛሬ ባገራችን የብሄራዊ ደህንነት አደጋ ገዥው ፓርቲ ራሱ ነው። የብሄራዊ ደህንነት ስጋት ቀልባሽ ከመሆን ይልቅ ሥጋቱን አጅግ አስፈሪ ወደ ሆነ ደረጃ በመግፋት ዋነኛው ምክንያት መንግሥት ነው። እንዳውም ይህንን የብሄራዊ ደህንነት ሥጋት ለመቀልበስ የሚሟሟተውን ዜጋ በማሳደድና ማጥቃት ላይ የሚገኘው መንግሥት ነው”።

2.አማራጩ ምንድነው?
አገሪቱ ከተጋረጠባት የህልውን አደጋ ለመወጣት ያለው አማራጭ ባገር ውስጥና በውጭ ባሉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የቀረበውን አብይ አህመድን ከሥልጣን ባስቸኳይ የማስወገድና የሽግግር መንግሥት የመመስራት ጥሪ መቀበል ነው። ዛሬ ይህንን የሽግግር መንግሥት አማራጭ በአንድ ድምፅና በጋራ ሲቀርብ የምንሰማው የአብይ አህመድን አገዛዝ ገና በማለዳው፣ በተቃውሞ ይመለከቱት ከነበሩት ፖለቲከኞችና የማህበራዊ ሜዲያ አክቲቪስቶች ብቻ አይደለም። እንዳውም ይህንን ጥሪ እጅግ አጠናክረውና በአሳማኝ መረጃና ትንተና አስደግፈው በማቅረብ ላይ የሚገኙት እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ለአብይ አህመድ አገዛዝ ድጋፋቸውን ሲስጡ የነበሩ ወገኖች ናቸው። ጠንካራ ደጋፊዎቹ ከነበሩት መካከል በማህበራዊ ሜዲያ ከመታገዝ ባሻገር አለም አቀፍ ፖለቲካዊና የፋይናንስ ድጋፍ በማሰባሰብ፣ ግንባር ቀድም ሚና የተጫወቱ ጎምቱ ምሁራን፣ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪዎች፣ ጋዜጠኞችና፣ የኪነ ጥበብ ሰዎች ይገኙበታል። አልፎ ተርፎም ከምክር ቤት አባል አንስቶ እስከ ኦነግ/ሸኔ ድረስ አብይ ከሥልጣን እንዲወርድና የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም እስከመጠየቅ ተደርሷል። ጥቂቶቹን በስም ለመጥቀስ ያህል የአብይ አህመድ ጠንካራ ደጋፊዎች ከነበሩት መካከል የኢሳት ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ንኣምን ዘለቀ አንዱ ነው። ሌላው ደግሞ ዶ/ር ዮናስ ብሩ የቀድሞ የአለም ባንክ ሲንየር ኢኮኖሚስት፣ የአፍሪካ ልማት ባንክ ሲንየር አማካሪና በአብይ አህመድ የተቋቋመውን የኢኮኖሚ አማካሪ ካውንስል በኢንተሪም ሊቀ መንበርነት ይመሩ የነበሩት ይገኙበታል። በተለይ እነኚህ ከላይ ስማቸው የተጠቀሰው የአብይ አህመድ ልዩ እንግዳ በመሆን እውቅና የተቸራቸው ነበሩ። ከነኚህ ሌላ የአብይ አህመድ ደጋፊዎች የነበሩ የሕግ ባለሙያዎች መካከል የአፍሪካ የሰላም እርቅ ተቋም ዋና ዳይሬክተር የንጉሥ ጦና የልጅ ልጅ ዶ/ር ሸዋፈራሁ ኩራቱ አብይ ከሥልጣን እንዲወርድ የቀረበውን ጥሪ ብቻ ሳይሆን በአማራ ክልል የተያዘውን የህልውና ትግል ይደግፋሉ። በዚህ የህግ ባለሙያነትና ፖለቲካል አክቲቪስትነት የሚታወቁት እንደ አበበ ገላውና ገለታው ዘለቀ የሽግግር መንግሥት ጥያቄን ሲደግፉ፣ ከሌሎችም እውቅ የሚድያ ሰዎች መካከል ደግሞ በመካከለኛው ምስራቅ ሜዲያ ሞኒቴሪንግና ፖሊትካል አክትቪስት ሱሌማን አብደላን የመሳሰሉት በአብይ መንግሥት ላይ ይቅርታ የለሽ ተቃውሞ በማሰማት ላይ ይገኛሉ። ሌላው የአብይንና ሽመልስ አብዲሳን ከሥልጣን መወገድ በቀጥታ አያንሳው እንጂ የኦሮሞን ህዝብ ጥቅም የማይወክሉ፣ እነኚህ መሪዎች ኦሮሞ እንደ ህዝብ በጥላቻና በቀል አይን እንዲታይ ከማድረግ ያለፈ በምንም መልኩ መሠረታዊ ጥቅምና ፍላጎቱን እንዳላረጋገጡለት ድምፅ በማሰማት ላይ የሚገኘውን የሰላም ሚኒስቴር ሚንስትር ዴ ኤታ አቶ ታየ ዳንዳአን መጥቀስ ይቻላል[ የአቶ ታዬ ደንዳኣን ፌ ቡክ ገጽ ሜይ 28 ቀን 2023 “ የድሀን ቤት እና ቤተ- እምነቶችን ተለዋጭ መፍትሄ ሳይሰጡ ማፍረስ ብልግና ነው” በሚልና በሜይ 29 ቀን 2023 ደግሞ “የታፈነው አአጣር እውነት” በሚል ያጋሩትን ይመልከቱ።]። በተረፈ ባለፉት 5 ወራት በአዲስ አበባ ዙሪያ በተዘዋወርኩበትና ከክልል ከተሞች ከመጡ ዜጎች ጋር በተለያየ አጋጣሚ ስገናኝ የሰማሁት እሮሮ ሰማይ የነካ ነው ማለት እችላለሁ። ተራው ህዝብ ስለ አብይ አህመድ (ሽመልስ አብዲሳንና አዳነች አቤቤ ጨምሮ) የተሰማውን መንገፍገፍ የሚገልፅበትን የጥላቻና እርግማን ቋንቋ ላዳመጠው ይህ ሰው በገዛ ፈቃዱ ስልጣኑን መልቀቅ በተገባው ነበር የሚያሰኝ ነው። አብይ አህመድና የሱ ሹማምንት ከጥቂት ኦነጋዊ ልሂቃንና ከአገዛዙ ተጠቃሚ ከሆኑ አድር ባዮች በስተቀር ሰፊ የህዝብ ድጋፍ እንዳሌለው እርግጠኛ መሆን ይቻላል። ሰሞኑን የምግብ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው 20 ሚልዮን ለሚጠጉ በረሀብ ለተጎዱ ዜጎች መድረስ የሚገባውን ከUSAID የተለገሰውን የስንዴ እርዳታ የመከላከያ ሠራዊቱን ለመቀለብና ወደ ሶማልያና ኬንያ በመላክ የውጭ ምንዛሪ ማግኚያ ማድረጉ ሲጨመርበት አብይና ግብረ አበሮቹ ላንዲት ቀናትም ቢሆን በሥልጣን መቀመጥ የማይገባቸው ወንጀለኞች ለመሆናቸው አያጠያይቅም።

ተጨማሪ ያንብቡ:  አደገኛው የከተማ ላይ ከተማ ምስረታ ፕሮጀክት (መርሐጽድቅ መኮንን አባይነህ)

3.የሽግግር መንግስት
ከሁሉ አስቀድሞ በዛሬው ያገራችን ተጨባጭ ሁኔታ የሽግግር መንግስት ምስረታን የሚፃረሩ ሀይሎች በሁሉም መስክ የፎረሸና ተስፋ የቆረጠ መሪ እንዳሻው የሚያደርጋት፣ መንግሥት አልባ አገር ላይ እንዳለን ከመቀበል ይልቅ ችግሩን አቃለው የሚመለከቱ ናቸው። አብይ አህመድ የአእምሮ ጤናው የሚያጠራጥር፣ ፅንፈኛንቱንና ላንድ ብሄር መቆሙን ያልደበቀ ለመሆኑ በባሌ፣ ወለጋና በሌሎችም አጋጣሚ ያደረጋቸው ንግግሮች ምስክር ናቸው። ይህም ሆኖ ጉልበት ኖሮት፣ አንበርክክኮና ራሱም ተደላድሎና ተረጋግቶ መግዛት የማይችል፣ የልማት ሥራ በእቅድ ከመምራት ይልቅ በሙስና የተዘፈቀ፣ የኑሮ ውድነቱን ለመግራት፡ ዳር ድንበር የመጠበቅ ግዴታውን መወጣት የማይችል ነው። ይህንን መራራ እውነት ወደድንም ጠላንም ልንውጠው ይገባል ።

እኔ እንደሚገባኝ የሽግግር መንግስት ከፍተኛ ጥበብና ጥንቃቄ የሚጠይቅ፣ የሌሎች አገሮችን ልምድ ካገራችን ሁኔታ ጋር ለማገናዘብ እውቀት፣ የዳበረ ክህሎትና የህዝብ አመኔታ ባላቸው አካታች ሃይሎች አሰባሳቢነትና አመራር የሚተገበር አገራዊ አደራ የተቀበለ፣ ጊዜያዊ አስተዳደር ማለት ነው። አገሮች ከፍተኛ አለመረጋጋትና የመፍረስ አደጋ ውስጥ ሲገቡ፣ ዘርፈ ብዙ ቀውስ ሁሉንም ህዝቦች ከዳር እስከዳር ሲያናውጥ፣ ከዚያ ለመውጣት ሲታሰብ የሽግግር መንግስት እንደ አማራጭ ይቀርባል። የዚህ አማራጭ ጥቅሙ የተካረሩ የፖለቲካና በትጥቅ የተደገፉ ትግሎችንና ተቃውሞዎችን በማዳመጥ፣ ማንም ላይ በማይገደብ ነፃ ውይይት ለማለዘብና ለማቀራረብ ይረዳል። ይህ የሽግግር መንግሥት የተረጋጋ፣ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና የህግ የበላይነት የስፈነበት ሥርዓት ለመዝርጋት የሚያስችል አስተማማኝ ሁኔታ በመፍጠር፣ በተቀመጠለት የጊዜ ሰሌዳ ሃላፊነቱን ከተወጣ በኋላ በብሄራዊ ምርጫ ለሚቋቋም መንግሥት ሥልጣኑን በማስረከብ ራሱን ያከስማል። ለማስታወስ ያህል አብይ አህመድ ወደ ሥልጣን እንደመጣና ”አሻግራችኋዋለሁ” የሚል የተስፋ ቃል በተደጋጋሚ ሲቸረን በነበረበት ወቅት የሽግግር መንግሥትን በተመለከተ የተለያዩ ሞዴሎችና ልምዶች በየውይይት መድረኩ እየቀረቡ በርካታ ውይይቶች ይደረጉ ነበር። አሁንም እነኚህን ሞዴሎችና ልምዶች እንደ ግብዓት መጠቀም ይቻላል።
4.ቅድመ ሁኔታ
ሀ) በቅድሚያ ጥሪ ሊደርግ የሚገባው ለብልፅግና ፓርቲ አባላት ነው። በዚህ በኦሮሙማ የበላይነት በሚመራው መንግሥት ውስጥ ባለ ድርሻ አካላት ሆነው ከምናያቸው መካከል በግልፅም ሆነ በተዘዋዋሪ፣ አገሪቱ የገጠማትን የህልውና አደጋ የተገነዘቡ እንዳሉ ብዙ ምልክቶችን ማየት ይቻላል። በዚያው ፓርቲና መንግሥት በተደበላለቀበት ማዕቀፍ ውስጥ የሚገኙት እነኚህ ወገኖች ብቻቸውን እንዳልሆኑና ወደ ህዝብ ሊጠጉ እንዲችሉ ማበረታቻውን (incentive) define ማድረግና በግልፅ ማሳየት ተቀዳሚ ተግባር ነው። ለሀገር ደህንነት ሲባል የፓለቲካ የአመራር ለውጥ ለማድረግ እንዲደፍሩና ጠቅላይ ሚንስትሩን ከሥልጣን አውርደው ሁሉን አቀፍ ለሆነ የሽግግር መንግሥት ምስረታ ጥሪን እንዲደግፉ ቅስቀሳ ማድረግ ያስፈልጋል።
ለ) መንግሥት ወደ አማራ ክልል ያዞረውን ጦርነት ሙሉ በሙሉ ማቆምና ከፌደራልም ይሁን ከኦሮምያ ክልል አውጣጥቶ ወደ አማራ ክልል ያስገባውን ሠራዊት ማስወጣት ይኖርበታል። በአማራ ክልል የተቀሰቀስውን በትጥቅ የተደገፈ ተጋድሎ (resistance) “በፅንፈኝነት” ብቻ የሚመለከትበትና የሚፈርጅበትን ርዕዮተ ዓለም መልሶ መመርመር ይኖርበታል። በበኩሌ የአማራው ጥያቄ እንደ ህዝብ የታወጀበትን እልቂትና ጥቃት ተደራጅቶና ታጥቆ ለማስከበር ሳይወድ በግድ ተገፍቶ የገባበት የህልውና ትግል እንጂ ማንንም በመጤና ጠላትነት ፈርጆ የተነሳ የብሄርተኝነት ጥያቄ ነው ብዬ አላምንም። በተለይ ባለፉት አምስት አመታት በማንነቱ ምክንያት መፈናቀል፣ ግድያ፣ የንብረት መውደም የደረሰበትና ለማያባራ መፈናቀልና ስደት የተጋለጠ ሕዝብ ነው። በተለይም በአማራ ክልል ያለውም ችግር የክልሉ መሪዎች አይወክሉኝም ከሚል የአመራር ለውጥ ከመጠየቅ የመነጨ ነው። ስለዚህም ለሽግግር መንግሥቱ ምስረታ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ሌሎች እንደ ኦነግ ሸኔ ለመሳሰሉ የታጠቁ ሃይሎች ያሳየውን ሰላማዊ የድርድር መንፈስ በአማራ ክልል ለሚንቀሳቀሱ የታጠቁ ሃይሎች የማሳየት ፈቃደኝነቱን በተግባር ማረጋገጥ አለበት። በየትኛውም ክልል ያሉ ልዩ ሃይሎችን ትጥቅ የማስፈታት እንቅስቃሴ ምቹና አንዱ በሌላው ላይ የሚሰማውን ስጋትና ጥርጣሬ በማርገብ ርስ በርስ ለመተማመን የሚያስችል ሁኔታ እስከሚፈጠር ድረስ እገዳ ሊደረግበት ይገባል።
ሐ) የሽግግር መንግሥት ምስረታን አሳክተው አገሮቻቸውን ለዴሞክራሲያዊ ምርጫ ያበቁ እንደ ቱኒዝያ፣ ባንጋላዴሽ (በተደጋጋሚ) እና ማላዊ የመሳሰሉ አገሮች ሽግግሩን የመሩላቸው ከፖለቲካ ወገናዊነት ነፃ የሆኑና የህዝብ አመኔታ ያላቸው፣ የሰበዓዊ መብት ተከራካሪዎች፣ ምሁራንና ሊሂቃን ብቻ አልነበሩም። በሽግግሩ ወቅት የወታደራዊ መከላከያ፣ ፀጥታና ኢንተለጀንስ ተቋማትን በተመሳሳይ ከፖለቲካ ወገናዊነት ነፃ የሆኑና የህዝብ አመኔታ ባላቸው የቀድሞ መከላከያ ሠራዊትና የኢንተለጀንስ መኮንኖች የበላይነት እንዲመራ ማድረግ ችለዋል። የአብይ አህመድ መንግሥት ራሱ የያዘውን የጦር ሃይሎች ጠቅላይ አዛዥነትንም ሆነ ሌሎች በመከላከያው፣ ፖሊስን ኢንተለጀንሱ ላይ በአዛዥነት የተቀመጡ መኮንኖች የሽግግሩ ሂደት እስከሚጠናቀቅ ድረስ በቀድሞ የመከላኪያ፣ ፖሊስና ኢንተለጀንስ መኮንኖች የበላይነት ቁጥጥር (supervision & monitoring) ሥር እንዲገቡ መደረግ ይኖርበታል። ሽግግሩ እስኪጠናቀቅ ዳር ድንበርን ከወራርም ሆነ ሠርጎ ገብ ለመከላክል፣ የውስጥ ደህንነትና ፀጥታ ለማስከበር የሚወሰድ ማንኛውም እርምጃ የነዚህ የቀድሞ መከላከያ ሠራዊት፣ ፖሊስና የደህንነት አዛዦችና መኮንኖች እውቅናና approval ያስፈልጋል።
መ) በአዲስ አበባም ሆነ “ሸገር” በሚል በሚመሰርተው ከተማ የሚደረጉ ቤቶችን፣ ቅርሶችን፣ አብያተ ክርስትያናትም ሆነ መስጂዶችን የማፍረስ፣ ቤተ መንግሥት የማነፅና የመሳሰሉት ማንኛውም የማፈናቀልም ሆነ የአገር ሀብት ያለ ህጋዊ ቁጥጥርና ፍትህ የሚንቀሳቀስበት እንቅስቃሴ መቆም አለበት። ዜጎች ወደ አዲስ አበባ የመግባትና የመውጣት መብታቸው ተመልሶ መከበር ከቅድመ ሁኔታዎች አንዱ መሆን ይኖርበታል።
ሠ) የወልቃይት፣ ጠለምትና ራያ ጉዳይ ፍትሃዊና ዜግነትና ማንነት የማይጠላልፉበት፣ በመቻቻል ላይ የቆመ ሐገ መንግሥታዊ መፍትሄ እስኪገኝለት ድረስ አሁን ያለውን status quo ትሕነግ እንዲቀበል ማስማማት ካልሆነም ማስገድድ ይገባል። በአብይ አህመድ መንግሥት ከለላ በመጠቀም በእጅ ጥምዘዛም ሆነ በጉልበት እነኚህን ግዛቶች መልሶ ወደ ትግራይ ክልል ለመጠቅለል የሚያደርገውን ማንኛውም እንቅስቃሴ አካባቢውን ማለቂያ የለሽ ጦርነት ውስጥ መልሶ እንደሚጨምራትና ሰለማዊ ሽግግር የሚባል ነገር የማይታሰብ እንደሚያደርገው ትሕነግ ወደደም ጠላ እንዲዋጥለት ማድረግ ያስፈልጋል።
ረ) በኢትዮጵያ የሚደረግው ሽግግር ሳይጀመር ቀውስ (non starter) ውስጥ እንዳይገባ ከኤርትራ መንግሥት ጋር ያለውን ግንኙነት በተመለከተ የሚታየውን ውጥረት ማርገብ የግድ ይሆናል። በዚህ በኩል የአብይ አህመድ ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ መንግሥት ጋር የያዘውን flirtation፣ ትሕነግም ወደ ቀድሞው ወታደራዊ ቁመና ተመልሶ ለኤርትራ ስጋት የማይሆንበት ሁኔታ ላይ እንዲገኝ፣ ወታደራዊ ቁመናው ከቁጥጥር ውጭ እንዳይገባና ኤርትራንም የአማራንም ሆነ አፋር ክልልን መልሶ ለማጥቃት እንዳይችል ማድረግ የአብይ አህመድ መንግሥት ሟሟላት ያለበት ቅድመ ሁኔታዎች በይመስለኛል።
5.ሕገ መንግሥት
አሁን ለገባንበት የህልውና ስጋት መሰረታዊው ምክንያት የመነጨው በብሄር ማንነት ላይ የቆመው ሕገ መንግስትና በዚሁ ሕገ መንግሥት የተዋቀረው የመሬትና አገር ባለቤትነትን ለብሄር/ብሄረሰቦች ብቻ የሰጠው ሕገ መንግሥት መሆኑ አያከራክርም። የሽግግር መንግሥቱ የመጨረሻ መዳረሻ በኢትዮጵያዊ ዜግነት ማንነት ላይ ያጠነጥነና ሌሎች ማንነቶች የማይጠላለፉበት ሕገመንግስትና ሕገ መንግስታዊነት ማረጋገጥ ነው። ስለዚህም ሕገ መንግሥት የማርቀቅም ሆነ የማሻሻል፣ ይህንንም ሕገ መንግሥት ለውይይት የማቅረብ ሃላፊነት የሚወድቀው በሽግግር መንግሥቱ ላይ ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ኢትዮጵያ ዛሬ ሩዋንዳን ካሸነፈች ተሳታፊ ትሆናለች

የሕገ መንግሥትን ጉዳይ በቀላሉ የምንመለከተውና በቀላል የአንቀፆች መሻሻል የምንወጣው አይደለም። የሀሳብና የፍልስፍና ክለሳ የሚጠይቅ ከባድ ሃላፊነት ነው። ወደ ሕገ መንግሥት ማርቀቅም ሆነ ማሻሻል ከመገባቱ በፊት ምክክርና ተግባቦት (consensus) ሊደረስባቸው የሚገባ፣ ከማንነት ሌላ የዜጎችን ህልውና እጅግ አድርገው የፈተኑ በርካታ ህብረ ብሄር ጥያቄዎች መኖራቸውን መቀበል ይጠይቃል። እነኚህን አሰባስቦ ሲስተማታይዝ በማድረግ የአጀንዳ ቅደመ ተከተላቸውን ጠብቀው ለውይይትና ምክክር በማቅረብ ተግባቦት (consensus) ሲደረስባቸው ወደ ሕገ መንግሥት የሚመተረጎሙበትና የሚመነዘሩበት አሰራር (practice) እውቀቱ ያላቸው ኤክስፕርቶች እንዲወጡት ማድረግ ይቻላል። ከዚህ ሂደት መጠናቀቅ በኋላ የሕገ መንግሥቱ ረቂቅ የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲመክርበትና በሬፈራንደም እንዲያፀድቀው ማድረግ ይጠይቃል።

አሁንም እንደገና ለማስታወስ አብይ አህመድ ወደ ሥልጣን ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ የሕገ መንግሥት ረቂቅና ይህንን የቃል ኪዳን ሰነድ እንደምን መከለስ እንደሚገባው ጠቃሚ ሃሳቦችን ያቀፉ ዶኩሚነቶች ቀርበዋል። የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን ከተቋቋመም በኋላ ያሰባሰባቸውና በመረጃ ቋቱ የያዛቸው በርካታ ጉዳዮች አዲስ ወይም አንድ አይነት hybrid የሆነ ሕገ መንግሥት ረቂቅ ላይ ለመድረስና በሕግ የበላይነት ላይ የቆመ ሥርዓት ግንባታ ሽግግር ለማድረግ ግብዐት ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል።
6.ማጠቃለያ
በውጭ አገር የሚገኙ በድርጅትም ሆነ በማህበራዊ ሜድያ ዙሪያ የተደራጁ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በአገር ውስጥ ያለውን ትግል ሊተኩት እንደማይችሉ ሳይታለም የተፈታ ነው። ይህም ሆኖ አገር ውስጥ ለሚካሄደው ሰላማዊ የእምቢተኝነትና ህልውና ትግል አጋዥ በመሆን ወሳኝ ሚና መጫወት ይችላሉ። በተለይ በውጭ የሚኖረው ኢትዮጵያዊና ትውልደ ኢትዮጵያዊ ያለው ጠንካራ ጉልበት በአብይ መንግሥት ላይ ተጨማሪና ጠንካራ ጂኦፖለቲካልና ፋይናንሽያል ጫና እንዲደረግበት ውጤታማ ሥራ መስራት ነው። ከሰብዓዊ እርዳታ በስተቀር ማንኛውም ለአገዛዙ ትንፋሽ የሚሰጥ የውጭ አርዳታም ሆነ በremittance መልክ በመንግሥት ባንኮችና የፋይናንስ ተቋማት የሚገባ የውጭ ምንዛሪ የዝውውር እገዳ በማድረግ የአብይ አህመድ መንግሥት ሳይወድ በግድ ለሽግግር መንግስት ድርድር እንዲንበረከክ ተፅዕኖውን ማበርታት ያስፈልጋል። በዚህ መልክ በውስጥ ከሚደረግው ትግልና ጥሪ ጋር ተቀናጅቶና ተደጋግፎ የተጋረጠውን የህልውና አደጋ ከመታደግ በስተቀር ሌላው አማራጭ ሁሉ አብቅቷል ይህ ጉዳይ በሽምግልና የሚፈታ ሳይሆን በአገዛዝ ለውጥ የሚፈታ ብቻ ነው። ምናልባት ባልተጠበቁና ለመተንበይ አስቸጋሪ በሆኑ ምክንያቶች ሂደቱ ባጭር ጊዜ ተጠናቆ አብይ አህመድን የማስወገዱ ትግል እስከ መጭው ብሄራዊ ምርጫ ሊራዘም ይችላል። ይህንን አጋጣሚ ከተግዳሮት ይልቅ እንደ እድል በመቁጠር ህብረ ብሄራዊ ትግሉን አቀናጅቶ በጋራ ግንባር ለመምራትና የመጭው አገራዊ ምርጫ ውጤትም ለዴሞክራሲያዊና ህገመንግሥታዊ ሥርዓት ግምባታ ብቃትና ዝግጁነቱን ያለው መንግሥት ለመመስራት በበቂ ለመዘጋጀት ይረዳል።
a.tegbaru@gmail.com

ተጨማሪ ያንብቡ:  ለአሜሪካ ደፋር ጫና የአንድ ተራ ዜጋ ምላሽ - መነሻ (አንድነት ይበልጣል - ሐዋሳ)

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share