“የምንቀምሰው ባለመኖሩ የተረዳነውን ድስት ሳይቀር ለመሸጥ ተገደናል” በአማራ ክልል ያሉ ተፈናቃዮች

መሐመድ ሰይድ ይባላሉ። ኑሯቸውን በደቡብ ወሎ ዞን፣ ሐይቅ ከተማ አካባቢ በሚገኝ ቱርክ ካምፕ ተብሎ በሚጠራው የተፈናቃዮች መጠለያ ካደረጉ ሰባት ወራት ተቆጥረዋል።

መሐመድ የአምስት ልጆች አባት ናቸው። ባለቤታቸውን ጨምሮ ሰባቱ የቤተሰብ አባላት የተጠለሉት እዚሁ ካምፕ ውስጥ ነው።

በጊዜያዊ መጠለያው ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንደሚገኙ የገለጹት አቶ መሐመድ፣ የሚደረግላቸው ድጋፍ ከተቋረጠ ሁለት ወራት መቆጠሩን ይናገራሉ።

“ምንም የሚላስ የሚቀመስ የለም። አሁንማ የምናደርገው ሲጠፋን ነፍሳችንን ለማቆየት ለመገልገያ የተሰጠንን ፍራሽ፣ ብረት ድስት እና ሌሎች እቃዎችን ሳይቀር እየሸጥን ነው” ይላሉ።

አስቸኳይ ድጋፍ የማይደረግላቸው ከሆነም በርካታ ሕጻናት እና እናቶች ሕይወታቸውን ሊያጡ ይችላሉ ብለው አቶ መሐመድ ይሰጋሉ።

ቀደም ብሎ በቂ ባይሆንም የዱቄት እና የስንዴ እርዳታ ይሰጣቸው እንደነበር የሚናገሩት እኚህ አባት፣ “አሁን ግን ድጋፍ የሚባል ጭራሽኑ የለም” ይላሉ።

እርሳቸው እንደሚሉት የተፈናቀቃዮቹ መጠለያው ከከተሞች የራቀ በመሆኑም ከአካባቢው ነዋሪዎች እርዳታ ለመጠየቅም ሆነ የተገኘውን የቀን ሥራ ለመስራት የማይቻል ሆኖባቸዋል።

ልጆች እንጀራ ለመለመን የአንድ ሰዓት የእግር መንገድ ለመጓዝ ተገደዋል።

“ሁሉም በረሃብ እየተሰቃየ ነው። ከሰሞኑ በረሃብ ምክንያት እናትዬዋ የምታጠባው አጥታ የአንዲት ሕጻን ሕይወት አልፏል” ብለዋል።

ሌላኛዋ እዚያው መጠለያ ውስጥ የሚገኙት ተፈናቃይ ወ/ሮ መሬማም ልጆቻቸውን ይዘው ነው ቤት ንብረት ያፈሩበትን አካባቢ ጥለው የወጡት።

ከዚያ ሕይወታቸውን ለማትረፍ ቢወጡም አሁንም የገጠማቸው ችግር ፈታኝ ነው ይላሉ።

“የምግብ ችግር አለብን ። እንጮኻለን…እንጮኻለን…ምግብ ግን የሚሰጠን የለም” በማለትም የሚደርስላቸው አካል እንዳላገኙ ተናግረዋል።

እኚህ እናት እንደሚሉት በጊዜያዊ መጠለያው ውስጥ በቆዩባቸው ሰባት ወራት ውስጥ የስንዴ እርዳታ የተሰጣቸው ሦስት ጊዜ ብቻ ነው። ባለፉት ሁለት ወራት ውስጥ ግን ምንም ያገኙት ድጋፍ የለም።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ግልጽ አቤቱታ: ጉዳዩ ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ ሕግ በመጣስ ወንጀል ክስ ተመስርቶባቸው አለምዐቀፍ ፍርድቤት እንዲቀርቡ ስለመጠየቅ

ያሉበት ቦታ ከከተሞች የራቀ በመሆኑ ወደ ከተማ ሄደው ሥራ ለመሥራት ተቸግረዋል።

“ካለንበት ቦታ ወደ ደሴ እና ሐይቅ ከተሞች ለመሄድ ለመኪና መቶ ብር እንጠየቃለን” ሲሉም ያሉበትን ሁኔታ ለቢቢሲ አስረድተዋል።

በመጠለያው ከ3 ሺህ በላይ ሴቶች የሚገኙ ሲሆን፣ “ረሃብ ላይ ነው ያለነው” ሲሉ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ተማጽነዋል።

“ያዘነ እየሰጠን፣ ሙቅም አገኘን፣ ቂጣም አገኘን በእሱ ነው እስካሁን ነፍሳችንን ያቆየነው። የሚቦካ እንኳን ማግኘት አይታሰብም” ይላሉ።

እነዚህ ቤተሰቦች የተፈናቀሉት በኦሮሚያ ክልል፣ ምዕራብ ወለጋ ዞን፣ ጊምቢ ወረዳ፣ ቶሌ ቀበሌ ብሔር ተኮር ጭፍጨፋ ከተፈፀመ በኋላ ነበር።

በጥቃቱም በርካታ ወዳጅ ዘመዶቻቸውን እንዳጡ ይናገራሉ።

በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ የተለያዩ ዞኖች ውስጥ በተለያየ ጊዜ በታጣቂዎች በተፈፀሙ ማንነትን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች በርካቶች ተገድለዋል።

በምዕራብ ወለጋ ዞን፣ ጊምቢ ወረዳ፣ ቶሌ ቀበሌ ሰኔ 11/ 2014 ዓ.ም በአማራ ተወላጆች ላይ በተፈፀመው ጭፍጨፋ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸው ይታወሳል።

ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት፣ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ጥቃቱን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ ከ400 በላይ ሰዎች መገደላቸው እና በርካቶች መቁሰላቸውን የገለጸ ሲሆን፣ የዐይን እማኞች እና ሌሎች መገናኛ ብዙኃን ደግሞ ቁጥሩን ከ500 በላይ አድርሰውታል።

“ጠባሳው እንዴት ጠፍቶ ለመመለስ እናስባለን?”

ወደ ቀያቸው ስለመመለስ በቢቢሲ የተጠየቁት አቶ መሐመድ፣ ““አሰቃቂው ግድያ ሕጻናት ፊት ሳይቀር ነው የተፈፀመው።የደረሰብን በደል እና ጠባሳ እንዴት ጠፍቶ ለመመለስ እናስባለን?” ሲሉ ጥያቄውን በጥያቄ መልሰዋል።

በጥቃቱ ካጧቸው ወዳጅ ዘመዶቻቸው ባለፈ ለዓመታት ያፈሩት ቤት ንብረታቸው ላይ ዘረፋ እና ውድመት እንደደረሰ የሚናገሩት ተፈናቃዩ፣ “ብንመለስስ ከምን ልንጀምር ነው? ነገ ከነገ ወዲያስ ሰላም እንሆናለን ብለን እንዴት እናስባለን?” ይላሉ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ማሩኝ›› የምትልበት ከመምጣቱ በፊት ‹‹በቃኝ›› በል!

“ጎተራ ሙሉ እህል፣ ከስምንት በሬ እስከ አስራ አምስት በሬ ጥለን ነው የመጣነው። ምን ይቆየናል ብለን እንመለሳለን? እኔ ልቦናየም አይከጂልም” ሲሉ የመመለስ ሃሳብ እንደሌላቸው ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ የመንግሥትን እርዳታ ጠባቂም መሆን አይፈልጉም። ይልቁኑ ሰላም ወዳለበት አካባቢ ሕይወት እንዲመሠርቱ እና ሠርተው ራሳቸውን የሚችሉበት መንገድ እንዲመቻችላቸው ነው የሚፈልጉት።

ወ/ሮ መሬማም ከዚህ የተለየ ሃሳብ የላቸውም።

አሁን ላይ ግን መንግሥት እና የእርዳታ ድርጅቶች በአፋጣኝ ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው ጠይቀዋል።

ከዚህ ቀደም የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ዶ/ር ይልቃል ከፋለ ከኦሮሚያ ክልል ተፈናቅለው በክልሉ ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ወደ ኦሮሚያ ክልል ለመመለስ ከስምምነት ላይ መደረሱን ገልጸው ነበር።

ርዕሰ መስተዳድሩ ይህን ያሉት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአማራ ክልልን ከወከሉ ተመራጮች እና ከክልሉ ምክር ቤት አባላት ጋር የካቲት 26/2015 ዓ.ም. በባሕርዳር ከተማ ውይይት ባደረጉበት ወቅት ነው።

ርዕሰ መስተዳድሩ በንግግራቸው፣ “እነዚህ ዜጎች የኦሮሚያ ክልል ነዋሪ ናቸው፤ የተፈናቀሉት በክልሉ ውስጥ ባለ ችግር ምክንያት ነው” በማለት የኦሮሚያ ክልል እነዚህን ተፈናቃዮች ደኅንነቱ በተጠበቀ ቦታ የማቋቋም ኃላፊነት እንዳለበት ማመልከታቸው ይታወሳል።

ይሁን እንጂ ተፈናቃዮችን የመመለስ አሊያም መልሶ የማቋቋም እንቅስቃሴ አልታየም።

ተፈናቅለው ለሚገኙት ሰዎች የሚቀርበውን እርዳታ እና መልሶ ማቋቋምን በተመለከተ በዚሁ ዙሪያ ከሚሰሩት ከአማራ ክልል እና ከፌደራል መንግሥት ተቋማት ምላሽ ለማግኘት ቢቢሲ ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

ተፈናቃዮች በአማራ ክልል

ባለፉት ዓመታት በኦሮሚያ ክልል የሚፈፀሙ ማንነትን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችን ሽሽት እንዲሁም ከሰሜኑ ጠርነት ጋር በተያያዘ የተፈናቃሉ ዜጎች በአማራ ክልል ተጠልለው ይገኛሉ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  " ማነው የተካደው ?! " በሰርካለም ፋሲል - ግርማ ካሳ

በክልሉ በሚገኙ የተለያዩ ዞኖች ውስጥ ተበትነው እንዲጠለሉ የተደረጉት ተፈናቃዮች የሚደረግላቸው ድጋፍ ባለመኖሩ ለከፋ ችግር መጋለጣቸውን በተደጋጋሚ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ከ67 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች እንደሚገኙ በተነገረበት በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ውስጥ በምግብ እና በመድሃኒት እጥረት የበርካታ ሰዎች ሕይወት ማለፉም ተዘግቧል።

የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፕሮግራሞች ማስተባባሪያ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት አቶ እያሱ መስፍን በክልሉ ከ1.2 ሚሊየን በላይ ተፈናቃዮች እንደሚገኙ ከዚህ ቀደም ለቢቢሲ ገልጸዋል።

እንደ ኃላፊው ከሆነ ከእነዚህም መካከል አብዛኞቹ ተፈናቃዮች ከ2010 ዓ.ም. ጀምሮ ማንነትን መሠረት ባደረጉ ጥቃቶች ሳቢያ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ከኦሮሚያ ክልሎች የተፈናቀሉ፣ እንዲሁም በጦርነቱ ሳቢያ ከቀያቸው ተፈናቅለው ወደነበሩበት ያልተመለሱ ናቸው።

የክልሉ መንግሥት፣ ሕዝቡ፣ ባለሃብቶች ድጋፍ ለማድረግ ጥረት እያደረጉ ቢሆንም በቂ ድጋፍ ማድረግ አለመቻሉንም ተናግረው ነበር።

“ከፌደራል መንግሥት ድጋፍ ቢደረግም የሚቀርበው እርዳታ፣ የድጋፍ ፈላጊዎችን ቁጥር መሠረት ያደረገ አይደለም” ሲሉም ያለውን ችግር አስረድተዋል።

ቢቢሲ ከፌደራል መንግሥት አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን ማብራሪያ ለመጠየቅ ያደረገው ተደጋጋሚ ሙከራ ስልካቸው ባለመነሳቱ አልተሳካም።

BBC

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share