ይድረስ ለሁላችን! – —ፊልጶስ

ማህበራዊ መገናኛ አውታሮች የዘመኑ የስልጣኔ ውጤቶች ናቸው። በአግባቡ የተጠቀሙበት ለህዝባቸው ብልፅግናን፣ እድገትንና  አብሮነት   አስገኝቶላቸዋል። የኛ ቢጤዎች ግን በተቃራኒው ህዝብን ለመለያየት፣ ድህነትንና ኋላቀርነትን ለማስፋፋት፤  ብሎም አገርን ለማፍረስ እየተጠቀምንበት እንገኛለን።  ዓለምን ያስተሳሰረውና የመረጃ ምንጭ የሆነው ማህበራዊ  መገናኛ  ለጎሰኞችና ለሆድ አደሮች ጥይትና ቦምብ ሆኖ እያገለገለ ነው።

በገዥዎች እኩይነትና ኋላ ቀርነት፤ እንዲሁም በእኛ ቸልተኝነትና  የተደገስልንን እልቂት በአግባቡ ባለመረዳታችን ምክንያት ፤ አሁን የኢትዮጵያ ህዝብ ”በጋለ የብረት ምጣድ ላይ  ተጥዶ ”፤  መውጫና መግቢያ አ’ቶ፤ በያአቅጣጫው ጦርነት ተለኩሶበት፣  በመኖርና ባለምኖር ውስጥ  ይገኛል። አገራችንም አንድ ሱማሊያዊ  ምሁር ከናይሮቢ እንዳሉት፤–” ኢትዮጵያ ህዝብ አላት፤ መንግሥት ግን የላትም’—”።

ታዲያ በዚህ ፈታኝ  ወቅት  እንደ ዜግ  ብንችል ወገናችንና አገራችን ለመታደግ ያለንን አቅምና ችሎታ ሁሉ አሰባስበን ለህሊናችን የድርሻችን እንደመወጣት፤   በማህብራዊ መገናኛ አውታሮች  ላይ ተጥደው፤ በተለኮሰው የዘረኝነትና የጥፋት እሳት ላይ ነዳጅ  የሚያርከፈክፋ ብዙዎች ናቸው። የጥላቻና የመንደርተኝነት ቅርሻታቸውን ይተፋሉ። እንዱ ሃይማኖት በሌላው ላይ እንዲነሳና እንዲገዳደል ሳይታክቱ ይሰብካሉ።  ፍለጠው፣ ቁረጠው፣ ግደለው፣ ወዘተ እያሉ መርዛቸውን ይረጫሉ።   በዚህም የማህበራዊ  መገናኛ  አውታሮችን በአጋባቡ ያልተርዳው ወገን፤  በወገኑ ላይ ይነሳል።የገዥዎቻችን መሳሪያ ይሆናል። ይህንንም  በተለይም ላለፋት  ዓመታት   መግደልንና መገደል፤ መፈናቀልና መሳደድን እስክንለምደው ድረስ አይተናል። ሰምተናል።

በአሁኑ ሰዓት በቲክቶክ፣ በፌስቡክ፣ በዮትዮብ፣  በቴሊግራም ፣ ወዘተ የሚተላለፋት መልዕክቶችን  በአብዛኛዎቹ የጥላቻና  ህዝብን በህዝብ ላይ የሚነሳሱ ፤ እጅግ ጸያፍና   ፍጽም   ግብረ-ግብነት የጎደላቸው ብቻ ሳይሆኑ፤ በአንድ ሃማኖት ተከታዮች  መሃከል እንኳን ልዮነትን እየፈጠሩ  የእግዚአብሔርን  ቤት የጥላቻ መድረክ  አድርገውታል።

ታዲያ የሚገርመው  እነዚህ በጥላቻና በተሳዳቢነታቸው የተካኖ ሰዎች ብዙ ሺ ተከታይ ማፍራታቸው ሳይበቃ፤ ሙገሳና ውዳሴ እያገኙ፤ መድርኩን መቆጣጠር መቻላቸውና እኛም በቀጥታም ቢሆን በተዘዋዋሪ፤ ዝምታን መምረጣችን፣ በህግ ፊት እንዲቀርቡ ባለማድረጋዥን፤  በአጠቃላይ  ማድረግ የሚገባንን ባለማድረጋችን፤  መነገርና ዜና መሆን የሚገባው የአገርና  የአህዝብ አንገብጋቢ የህልውና ጉዳይ ተዘንግቶ፤  የእነሱ ወደቀ ሲባል ሞተ፣ ተከሰሰ ሲባል- ታሰረ፣ ታሰረ ሲባል ተገደለ፣ ተገደለ ሲባል- አረገ፤  ተሰበረ፣ ተንኮታኮተ፣ ወዘተ  እያሉ የሚነዙት  ወሬ  አየሩን ተቆጣጥሮት ይገኛል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ምድራዊ እረኛ ያጣች ሃገረ ኢትዮጵያ!!

ብዙዎቹ የማህበራዊ የመገናኛ አውታሮች  የጥላቻና የስድብ  ”አምባሳሮች” በምዕራቡ ዓለም የሚኖሩና እነሱን በሰውነታቸው ተከበረው፣ ህግና ሥረዓት ባለበት አገር እየኖሩ ነው፤ የገንዛ አገራቸውንና ወገናቸውን ግን ርስ – በርሱ ተባልቶ እንዲተላለቅና አገር አልባ እንዲሆን ሌት ተቀን  ባልተገራ አንደበታቸው  ሲያቀረሹ ውለው የሚያድሩት።

በአገኙት አጋጥሚ ቁርስራሽ ሳንቲያም  የሚያተርፋ ከመሰላቸውና ህዝብን ያጋድልልናል ብለው ካሰቡ ማህበራዊ መገናኛ አውታሮች ላይ ተቸክለው ሲያላዝኑ ይውላሉ። ያድራሉ።   ተራው ህዝብም ”ለዜና” የተሰጠው ርዕስና የሚዘላብዱት ወሬ ”ፍየል ወዲህ  ቅዝምዝም ወዲያ” ቢሆንም ከመከታተልና ከራሱ አልፋ ለሎቹም ቢጤውቹም ማካፈሉን አያቆምም። እንዲያውም በተከተዮቻቸው ዘንድ ‘አንዱን ጎሳ ወይም ሃይማኖት እንኳሰው ፤ የሌላውን ጎሳ ወይም ሃይማኖት ደግሞ አሞካሽተው ”  የሚያወሩትን የጥላቻና የግብዝነት ወሬ አየሰሙ ያጀግኗቸዋል።  ይኽም “ብዙ በልቶ ብዙ ለማበት፤ ብዙ ተግቶ ብዙ ለመሽናት” የሚያስችላቸውን  የበርገርና የውስኪ  ወጫቸውን ይሸፍንላቸዋል።

በዚህ ሰዓት በማህበር መገናኛ አውታሮች  ውስጥ የምንቀሳቀስ ግለሰቦና  በጥላቻ የታወርን  ሆድ አደሮች ወደ ህሊናችን እንመለስ።   ዛሬም አልረፈደም። አገራችን ገደል አፋፍ ላይ ባለችበትና ጠላቶቿ መውጫና መግቢያ ባሳጧት ወቅት፣ ገዥዎቻችን  በህዝብ ደም በሚነግዱበት ወቅት፤ ከምንግዜውም በተለየ የስከነ ፣ እውነትነት ያለውና  አገርን እና ህዝብን አደጋ ላይ የማይጥል፣ ገንቢ ሃሳቦችን መለዋውጥ ሲኖርብን፣ በተቃራኒው ያለን ሰዎች ቆም ብለን ብናስብ፣ አለያም ዝም ብንል እስተዋአጾ እንዳደረግን ይቆጠረል።

በኢትዮጵያችን እስከ አሁን በመንግሥት ደረጃ በተዘራው የጥላቻና የከፋፍለህ ግዛው ትርክት የፈሰሰው ደም  በየተኛም አገር አልታየም። አሁንም እየሄድንበት ያለው መንገድ ተባበረን ለአንድነት ለአንደነት  በኅላፊነት ካልቆምን ተያይዘን ገደል የምንገባው ሁላችንም መሆናችን የምናየው ሃቅ ነው።  እናም ‘ባካችሁ! — – ማህበራዊ መገናኛ   አውታራን   ከልዮነት ይልቅ-  ለአብሮነትን፡ ከጥላቻ ይልቅ ፍቅርን፡  ከመናናቅ ይልቅ መከባበርን፤ ከማፍረስ ይልቅ መገባትን ፣ ከእኩይነት ይልቅ ሰናይነትን፣ በአጠቃላይ ለአገርና ለወገን የሚበጅ ስራ እንስራበት።

ለሁላችን ትምህርት ሊሆን ይችላል ብየ ስላመንኩ፤  ከዚህ በታች ያለውን ብዙው ግዜም በተለያየ መንገድ የሚተረከውን  የፈላስፋውን የሶቅራጥስን መልዕክት እንጠቀምበት እላለሁ።

ሶቅራጠስ እና “ ወዳጁ”

በአንድ ወቅት አንድ “ወዳጅህ ነኝ” የሚል ሰው መጥቶ ሶቅራጦስን፤

” ስለ አንድ ወዳጅህ የሰማሁት ደስ አይልም።” አለው፡፡

ሶቅራጦስ ግን ዝም አለ፡፡

ሰውየውም እንደገና፤  “ይገርማል ከ’ርሱ አይጠበቅም፤ በጣም ገርሞኛል!’’ አለው፡፡

ሶቅራጦስም ፤ ‘’ስለ ወዳጄ ልትነግረኝ የፈለግከውን ልሰማው የምችለው

ሶስት ጥያቄዎች አሉኝ፤ እነርሱን ስትመልስልኝ ብቻ ነው።›› አለው፡፡

ወዳጅህ ነኝ የሚለው ስለ ወዳጁ የሚነግረው ሰውየም ተስማማ፡፡

ሶቅረጦስ፤  “የመጀመሪያው ጥያቄዬ የእውነት ጥያቄ ነው። ስለወዳጄ የሰማኸው መቶ -በመቶ እውነት ነው ወይ?” አለ፡፡

ሰውየውም፤ “ መቶ በመቶ እርግጠኛ መሆን አልችልም፥፥” አለው፡፡

ሶቅራጦስም፤ “ልትነግረኝ የፈለግከው እርግጠኛ ያልሆነ ነገር ነው።” ቀጥሎም፤

“ሁለተኛው ጥያቄዬ የመልካምነት ነው፡፡ የምትነግረኝ መልካም ነገር ነው ወይ?”አለው፡፡

ሰውየውም፤ “እርሱማ መልካም አይደለም፥፥” አለው፡፡

ሶቅራጦስም፤

“1ኛ እውነትነቱ ያልተረጋገጠ፤

2ኛ መልካም ያልሆነ ነገር ልትነግረኝ ፈልገሃል፡፡ ሶስተኛ ጥያቄ አለኝ?›› አለው፡፡

ሰውየውም፤ “እሺ!” አለ፡፡

ሶቅራጦስም፤ “ለእኔ የሚጠቅመኝ ነገር አለው ወይ?” አለው፡፡

ሰውየውም፡- “የለም” ብሎ መለሰ፡፡

ሶቅራጦስም በመጨረሻ፡-

‹‹1/እውነትነቱ ያልተረጋገጠ

2/መልካም ያልሆነ፤

3/ለእኔ የማይጠቅም ነገር አልሠማም›› አለው፥፥ ” ይባላል፡፡

እንግዲህ እውነትነቱ ያልተረጋገጠ፣ መልካም ያልሆነና በአገራችንና በመከረኛው ወገናችን  ሰላምና አንድነትን  በማያመጣ ላይ  ጊዜን ማጥፋትና  ህዝብን ከህዝብ ማጋጨት፤ ከሰው ፍርድ ብናመልጥም ፤ ከራስ የህሊና ፍርድ ግን አናመልጥም። ከሁሉም በላይ ደግሞ የማይቀረው የእግዚአብሔር ፍርድ አለ። በአጠቃላይ የእስከ አሁኑ የማህበራዊ መገናኝ  አጠቃቀማችን  የህዝባችን መከራ አራዝሞታል። የኢትዮጵያዊነት ትግላችን የግመል ሽንት አድርጎታል። የኢትዮጵያን ትንሣኤ እንደ ጥላቻን ስንቀርበው አርቆብናል።

ስለዚህም  ማህበራዊ መገናኛን ለአገርና ለወገን መድህን፤ ብሎም  ለሁላችንም ለሰው ልጅ ለሚጠቅም ምግባር እንጠቀምበት።   ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን እንታደግበት።

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኖራለች!!

———-//—-ፊልጶስ

ግንቦት 2015

3 Comments

  1. ውድ ወዳጄ አቶ ፊልጶስ፣

    ነገሩን አሳምራለሁ ብለህ የባሰውን አበላሸኸው። አንድ ሁለት ሰዎች የሚናገሩትን ተመርኩዘህ የቀድሞውን የህወሃትንንም ሆነ የአሁኑን አገዛዝ የሚቃወሙና በስራቸውም የሚወነጅላቸውን ሰው ሁሉ እነውክለዋለን በሚሉት ብሄረሰቦቻችው ላይ የጥላቻ ዘመቻ እንደቀሰቀሱና እንደሚቀሰቅሱ አድርገህ ነው የጻፍከው። ይህ አግባብ አይደለም። የተለያዩ ጽሁፎችን በደንብ አገላብጠህ፣ ወይም አንብበህ ከሆነ የሚሰነዘረው ክስም ሆነ ውንጀላ በወያኔና በአቢይ አገዛዝ ላይ ብቻ ነው። አንዳቸውም በትግሬም ሆነ በኦሮሞ ብሄረሰብ ተወላጅ፣ በምስኪኑ ህዝብ ላይ ጥላቻን ሲቀሰቅስና ወደ ርስ በርስ ጦርነት እንዲያመራ የሚያደርግ ስራ ሲሰራ በፍጹም አልታየም፤ አልተሰማም። እንዲያውም ምስኪኑ የትግሬም ሆነ የኦሮሞ ብሄረሰብ በስሙ የሚነግዱ እንወክለዋለን የሚሉና ከውጭ ኃይሎች ጋር ያበሩና የውክልና ጦርነት የሚያካሂዱ ፍዳውን እያሳዩት ነው የሚል መልዕክት ነው ሲተላለፍ የከረመውና፣ አሁንም የሚተላለፈው። በተለይም ወጣቱ የትግሬም ሆነ የኦሮሞ ብሄረሰብ ተወላጅ እንዳይማርና እንዳያውቅ በአጉል ቅስቀሳ አደንቁረውታል፤ የሙያ ማስልጠኛ ከመክፈትና በየአካባቢያቸውም ሰፋ ያለ የስራ መስክ ከመፍጠር ይልቅ ጥቂት ኤሊቶች እየተዝናኑ፣ በብዙ ሺሆች ወታደሮች እያሰለጠኑና እያሰማሩ ህዝባችንን ለርስ በርስ ጦርነት እየጋበዙት ነው የሚል ነው። እንደመሰለኝ ከሆነ በህወሃትና በአቢይ አገዛዝ ላይ የሚሰነዘረውን ቅስቀሳ በጠቅላላው በትግሬና በኦሮሞ ብሄረሰብ ተወላጆች ላይ እንደሚሰነዘር አድርገህ የምትቆጥር ከሆነ ጽሁፎችን በደንብ አታነብም፤ ያነበብክ ከሆነ ደግሞ በደንብ አትገነዘብም ማለት ነው። በሌላ ወገን ደግሞ እነ ህወሃትና እነ አቢይ አህመድ ለምን ተወነጀሉ፣ የሚያዋጣን እርቅ ነው የምትል ከሆነ በግልጽ ተናገር። እንደዚህ የምትል ከሆነ መመዘኛህ ምን እንደሆነና፣ እርቅ ይደረጋል ከተባለ ይህን ያህል ወንጀል የፈጸሙ ሰዎች በምን ዕውቀትና ህሊና ሊሰሩ እንደሚችሉ ማሳየት መቻል አለብህ። ዝም ብለህ ከአንዳንድ ሰዎች አባባል በመነሳት ወደ አጠቃላይ ድምደማ አትድረስ። ሳይንሱ በፍጹም አይፈቅድም።

    ፈቃዱ በቀለ

  2. ጤና ይስጥልኝ አቶ ፈቃዱ በቀለ፤
    ለሰጡኝ አስተያየት እግዚአብሔር ይስጥልኝ።
    መልዕክቴን የተረዱበት መንገድ አከብራለሁ። ግን በአግባቡ ያነበቡትና የተረዱት አልመሰለኝም። በድጋሜ ቢያነቡት መልካም ነው።
    ከዚሁ ጹሁፍ የሚከተሉት ስንኞች እንኳን ያንብቡት አይመስለኝም።
    —-ዓለምን ያስተሳሰረውና የመረጃ ምንጭ የሆነው ማህበራዊ መገናኛ ለጎሰኞችና ለሆድ አደሮች ጥይትና ቦምብ ሆኖ እያገለገለ ነው።
    በገዥዎች እኩይነትና ኋላ ቀርነት፤ እንዲሁም በእኛ ቸልተኝነትና የተደገስልንን እልቂት በአግባቡ ባለመረዳታችን ምክንያት ፤ አሁን የኢትዮጵያ ህዝብ ”በጋለ የብረት ምጣድ ላይ ተጥዶ ”፤ መውጫና መግቢያ አ’ቶ፤ በያአቅጣጫው ጦርነት ተለኩሶበት፣ በመኖርና ባለምኖር ውስጥ ይገኛል። አገራችንም አንድ ሱማሊያዊ ምሁር ከናይሮቢ እንዳሉት፤–” ኢትዮጵያ ህዝብ አላት፤ መንግሥት ግን የላትም’—”።

    ለማንኛውም የኔ እምነትና መልዕክት ህዝብን የሚከፋፍልና የአገርን አንድነት የሚጎዳ ቅስቀሳ ለማንም አይበጅም። ማተኮር ያለብን በገዥዎቻችና መንደርተኛ ቡድኖች ላይ ነው። ብልጽግናም ሆነ የጡት አባቱ ወያኔና የጎሳ ፖለቲካ ማስወገድ የቅስቀሳችንም ሆነ የትግላችን ማእከል መሆን አለበት የሚል ነው። እናም በድጋሜ ያንብቡት።

    አመሰግናለሁ
    ፊልጶስ

  3. ውድ ወንድሜ አቶ ፊልጶስ፣
    ጽሁፍህን በደንብ ተመልክቼዋለሁ። አገዛዙን ብቻ የሚመለከት ሳይሆን ሌሎችንም፣ በፌስቡክ፣ በቲክቶክና በሌሎች ሚዲያዎች ላይ፣ አንተ እንደምትለው የጥላቻ ቅስቀሳን የሚያራግቡትንም ጭምር ነው። ይህ ዐይነቱ አቀራረብ ለአቢይ አገዛዝና ለግብረአበሮቹ እንደመሳሪያ ሊጠቀሙበት ይችላሉ። እነሱ የሚሰሩትን ወንጀል በሌላው ላይ ሊለጥፉ ይችላሉ። ስለሆነም ከአጻጻፍ ስልት አንፃር በአገዛዙና በግብረአበሮቹ ላይ ብቻ ማትኮሩ እነሱን ነጥሎ ለመዋጋት ያመቻል የሚል ዕምነት አለኝ። በሌላ ወገን ግን አንዳንዶች አላስፈላጊ ጽንሰ-ሃሳቦችን በመሰንዘር የጠራ ትግል እንዳይኖር እንቅፋት መፍጠራቸው የማያጠራጥር ነው። ይህንንም በቅጡ እየተገነዘብኩኝ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share