ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ ብፁዓን ናቸው።
“ራስህን በእውነት አስጊጥ፣ በሁሉም ጉዳይ እውነትን ብቻ ለመናገር ሞክር፣ የሚጠይቅህ ማንም ይሁን ማን ለሐሰት ድጋፍ እትስጥ። አንተ እውነቱን በመናገርህ የሚናደድብህ ሰው ቢኖር እንዳትዝን፤ ይልቁንም “ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ ብፁዓን ናቸው፥ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና /ማቴ 5፥ 10/ በሚለው የጌታህ ቃል ራስህን አጽናና ።
/ቅዱስ ገናዲየስ ዘቁስጥንጥንያ /
መምህር ኃይለ ማርያም የታፈሩት ክህነት መነገጃ ለሚያደርጉት አይሰጥ በማለታቸው ነው። መምህር ኃይለ ማርያም የታፈኑት ቤተ ክርስቲያንን ቤተ ክርስቲያን ከሚያሰኙት ዋናው ሥርዓተ ክህነት በቀኖና ቤተ ክርስቲያን ይፈጸም በማለታቸው ነው። መምህር ኃይለ ማርያም የታፈኑት በመምህር አምላክ ሲመተ ኤጲስ ቆጶሳት ይዘግይ በማለታቸው ነው። መምህር ኃይለ ማርያም ሥራቸውን ከመሥራት ኃላፊነታቸውን ከመወጣት፣ ቃለ እግዚአብሔር ከማስተማር እና ለቤተ ክርስቲያን ጥብቅና ከመቆም ውጭ ወንጀል የሚፈጽሙ ሰው አይደሉም።
ስለዚህ ያሳፈኗቸው አሁኑኑ ጵጵስናን በጫና ማሰጠት የሚፈልጉ፣ እውነት ስትነገር የሚደነብሩ፣ ክህነትን ለፖለቲካ እና ለጥቅም መነገጃ ማድረግ የሚፈልጉ እና ይህም እንዲፈጸም የጥቅም ትስስር ባላቸው አካላት ጥቆማ መሆኑን ለመረዳት አያስቸግርም።
እንኳን በዚህ ዘመን እና በእኛ ሀገር ይቅር እና በየትኛውም ዘመን እና ሁኔታ የተፈጸመ ድብቅ ምክር እና ተንኮል ሁሉ መገለጡ አይቀርም። የማይገለጥ የተከደነ፣ የማይታወቅ የተሠወረ የለም ተብሏልና። ስለዚህ መምህሩን ፍቷቸው። እውነትንም አጥብቃችሁ አታሳድዷት። ሐሰትንና ተንኮልንም አታክብሯት። በኋላ ለፍርድ አሳልፈው ይሰጧችኋልና።