ዶክተር አብይ ቤተ መንግስቱን ለማስዋብ 850 ቢሊዮን ብር መድበው ስራ ተቋራጭ ቀጥረው ወድ ስራ እንደገቡ ተሰምቷል። ይህ ፕሮጀክት እስኪጠናቀቅ ወደ አንድ ትሪሊየን ብር ይፈጃል ማለት ነው። ይህ ፕሮጀክት በሃገሪቱ ውስጥ ከሚካሄደው ግዙፍ ፕሮጀክት ማለትም ከአባይ ወንዝ ግድብ ፕሮጀክት በፋይናንስ ወጪው ይበልጣል።
እኔ እንደ ዜጋ ይህንን ፕሮጀክት የምቃወመው በሚከተሉት ምክንያቶች ነው
1. ሀገሪቱ በመፈናቀልና በረሃብ አደጋ ላይ ናት። ስለሆነም ቅድሚያ ዜጎችን የማቋቋም ስራ የሃገሪቱ ኢመርጀንሲ ተግባር ነው። ከዚህ ሲለጥቅ፣
2. ሃገሪቱ እንዲህ ያለ ከባድ ወጪ ማውጣት ያለባት ልማታዊና አምራች በሆነ ጉዳይ ላይ ነው። ለምሳሌ በደርግ ጊዜ የነበረን የነዳጅ ማጣሪያ ሃሰብ ላይ ቀርቷል። አሁን ላለፉት ሰላሳ አመታት ኢትዮጵያ የነዳጅ ማጣሪያ ስለሌላት ድፍድፍ ትገዛና ያንን ድፍድፍ ደግሞ በተሻለ ዋጋ ሊያጣራ የሚችል ካምፓኒ ፈልጋ አጣርታ ነው የምታስገባው። ይህ ችግር ሃገሪቱን ለተደራራቢ ወጪ ዳርጓታል። እንደ ዱሮው የነዳጅ ማጣሪያ ቢኖረን
ሀ. በነዳጅ ማጣራት ጊዜ የሚገኘው ዝቃጭ ለአስፋልት ሬንጅ ስለሚሆን ይህንን ምርት ከውጭ ከመ ግዛት ያተርፈናል። የውጭ ምንዛሬ እንድንቀንስ ያደርገናል።በቀላሉ ሬንጅ ማምረት እንችላለን።
ለ. ዝቃጩ ቫዝሊንን ጨምሮ ለሌሎች ምርቶች ግብአት በመሆኑ ከዝቃጩ ብዙ ነገር እንሰራበታለን። ብዙ ዶላር እናተርፋለን።
ሐ. ድፍድፉን ራሳችን ማጣራት ስንጀምር የነዳጅ ምርቱን የደንስቲ density ልዩነቱን ተከትሎ ከሚገኘው ትርፍ ብዙ ገንዘብ እናተርፋለን።
ስለዚህ ኢትዮጵያውያን ልክ እንደ አባይ ግድብ ገበታ ለሃገር እንበለው ሌላም ስም እንስጠው ብቻ ተረባርበን ይህንን ማሽን መግዛት ላይ ነው ማተኮር ያለብን። ይህ የዶክተር አብይ የጫካ ፕሮጀክት ይህንን ማሽን ሊተክል ይችላልና የሃገር ሃብት አምራች ነገሮች ላይ እንዲውል ፓርላማውም ምሁሩም ዝም ማለት የለበትም። ሀይ መባል አለበት። እንዲህ አይነት የቀበጠ ስራ ሲስራ ዝምታ በተለይ ከምሁሩ አይጠበቅም። ሰልፍ ወጥተን ይህንን ሰውዬ ሀይ ማለት አለብን። ለውጥና ሽግግር መጠየቅ አለብን። የሃገር ሃብት መጫወቻ አይሁን ጎበዝ። ያለንን ሪሶርስ በአግባቡ መጠቀም አለብን።
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ
#Ethiopia
ገለታው ዘለቀ