ሚያዝያ 17 ቀን 2015 ዓም(25-04-2023)
ዘመቻ ብዙ አይነት መልክና ይዘት እንዲሁም አሰላለፍ አለው።የጤና ዘመቻ፣የኤኮኖሚ ዘመቻ፣የነጻነት ዘመቻ፣አገር የማዳን ዘመቻ እንዳለ ሁሉ በተቃራኒውም አገር የማፍረስ፣ሕዝብ የማጫረስ ዘመቻ፣የኤኮኖሚ ዘረፋ ዘመቻ፣የማህበረሰብ ቀውስና መከፋፈልንም በሚያስከትል መንገድ የሚካሄድ ዘመቻ መኖሩ አይካድም።
እንደአለመታደል ሆኖ እኛ ኢትዮጵያውያን ከላይ የተዘረዘረዘሩትንና ያልተዘረዘሩትን ከያቅጣጫው የሚመጡ ብዙ የጥፋት ዘመቻዎችን ስናስተናግድ ኖረናል ፤አሁንም እዬኖርን ነው።የዘመቻው ሁሉ ውጤት የሚጠናቀቀው ደግሞ በአሰላለፍና በትግሉ ጥንካሬ መጠን ነው።ችግሩን ያላወቀ ትክክለኛ የዘመቻ ዓላማ አውቆ ለድል የሚያበቃ እቅድና ስልት ሊነድፍ አይችልም።ከዚያም አልፎ ለጥፋት ሃይሎች ዘመቻ ምርኮኛና የተመቼ ይሆናል።
አገራችን ኢትዮጵያ ካላት የረጅም ዘመን የነጻነት ባለቤትነትና ባለብዙ ታሪክ ከመሆኗ ጋር የተጣጣመ የእድገትና የዴሞክራሲ ባለቤት ለመሆን አልቻለችም።ከዚያም ባለፈ ባለንበት 21ኛው ክፍለዘመን ለዓለም የእርሃብ፣የስደትና የግጭት ምሳሌ ና ማስፈራሪያ ከሆነች ውሎ አድሯል።ይህ ሁል ሊሆን የቻለው ከራሳቸው ጥቅም በላይ ለአገርና ለሕዝብ በማያስቡ እራስ ወዳዶችና አምባገነኖች መዳፍ ስር በመውደቋ ነው።አሁንም በባሰ ብሎም አገሪቷን በሚጠሉና ለማፈራረስ ተግተው በሚሠሩ ቡድኖች መዳፍ ሥር በመውደቋ ከነበረው ሁሉ ለከፋ ውድቀት ተጋልጣ ትገኛለች ።ያንን ለማከናወን በተለያዩ አቅጣጫዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ዘመቻ ተከፍቶባታል።
የአገሪቱን ሃብትና የተፈጥሮ ጸጋ ከበዝባዦች ጋር ተመሳጥሮ በመዝረፍ፣አገርን ማራቆት አንዱ ዘመቻ ሲሆን ከሁሉም በላይ ግን ተጠናክሮ የቀጠለው አደገኛው ዘመቻ ሕዝቡን በጎሳ ማንነቱ ከፋፍሎ ማጋደልና በጠላትነት እንዲሰለፍ የማድረጉ ዘመቻ ዋናው ነው። ለዚያም ግብአት መንደርደሪያ አገር ወዳዱን በተለይም አማራውን በተናጠል እያሳደዱ መጨረስ፣ ዘሩ እንዳይተርፍ የተጸነሰ ሳይቀር ሆድ ቀዶ ማጨንገፍ፣ከኖረበት ቦታ ማፈናቀል፣ንብረቱን መቀማትና ማውደም፣በከፈለው ግብር የተቋቋመውን የአገር መከላከያና የመገናኝ እንዲሁም የደህንነት ቢሮ በመቆጣጠር የወንጀሉ ፈጻሚና አስፈጻሚ ማድረግ።
በአገር ውስጥና በውጭ አገር የሚኖረውን ማህበረሰብ በልዩልዩ መንገድ ከፋፍሎ በተለይም ለጥቅምና ለስልጣን የሚቋምጡትን ደካሞችና እራስ ወዳዶች በማይረባ ጥቃቅን ድርጎ እዬደለሉ በባንዳነት እንዲሰለፉ ማድረግ።
ትኩረታችንን በውጭ አገር በተከፈተው የጥፋት ዘመቻ ብናደርግ፣እንደሚታወቀው የጥፋት ሃይሉ ከምዕራባውያን ጋር በአሜሪካን መሪነት የሚያደርገው ጸረ ኢትዮጵያ እንቅስቃሴ ከማንም የተደበቀ ሚስጢር አይደለም።የጥፋት ሃይሎቹ ካለምዕራባውያን በተለይም ካለአሜሪካኖች እውቅናና ድጋፍ በነሱ ጉልበት ብቻ አሁን ካሉበት ደረጃ ላይ ለመድረስ ባልቻሉም ነበር።ሁለተኛው የብርታት ምንጫቸው የአገር ወዳዱ መዝረክረክና በአግባቡ ለተከፈተበት የጥፋት ዘመቻ ከስብሰባና ከውግዘት ውጭ ተገቢና ተመጣጣኝ መልስ የሚሆን በተግባር የተገለጸ ዘመቻና ዝግጅት ባለማድረጉ ነው።እርግጥ ነው በረደኝ፣ ሞቀኝ፣ደከመኝ፣ ሰለቸኝ ሳይል ዝናብ፣ቁርና ሃሩር ሳያግደው ለዓመታት የሚጮኸው ኢትዮጵያዊ መኖሩ ባይካድም ከስብሰባና በሰላማዊ ሰልፍ ከማውገዝ ባሻገር በተጨባጭ መሬት ላይ የሚታይ ድርጅታዊ እንቅስቃሴና ዘመቻ ሲያደርግ አይታይም።ቢያደርግም በጎጥና በመንደርተኝነት ስሜት እዬተሰናከለ መዳከሙ አይካድም።ተቃውሞው፣ገንዘብ መሰብሰቡ ሳያንስ ያንን ተቃውሞ ከፍ ወዳለ ድርጅታዊ እንቅስቃሴ ካላሻገረው የአገር አጥፊዎቹን ዘመቻ በውስጥም በውጭም ማሸነፍ አይቻልም።ስለዚህም ለተደራጀው የጥፋት ዘመቻው ምላሽ የሚሰጥ ከጎጥና ከመንደር ህሳቤ የጸዳ የተደራጀ ሕዝባዊ የለውጥ ዘመቻ መክፈት ለነገ የማይባል ግዴታ ነው።
የጥፋት ሃይሉ ከሚዘምትበት ዘመቻ መካከል ማህበረሰቡን በሚያማልሉና በሚከፋፍሉ እንቅስቃሴዎች በኩል እንደሆነ መታወቅ አለበት።የኦሮሙማው ተረኛ ቡድን በውጭ አገር ዲያስፖራውን ለመከፋፈል እቅድ ማውጣቱ አይዘነጋም።ሰርጎ በመግባት በእድር፣በመረዳጃ፣በእስፖርት፣በዘፈንና ትያትር በመሳሰሉት ትኩረት ለማስቀዬር ዘመቻ ተጀምሯል። ያንን ዘመቻ መቋቋምና ማደናቀፍ ፣የሁሉም አገር ወዳድ የጊዜው ዘመቻ መሆን አለበት።በቅርቡ በሆላንድ ውስጥ እነዚህ እንቅስቃሴዎች በመካሄድ ላይ ናቸው።
1 ከሁለት ዓመት በፊት ለብዙ ዓመታት የኖረውና ማህበረሰቡን ሲያገለግል፣የአገራችንንም የፖለቲካ ጉዞ እዬተከታተለ ብዙ አስተዋጽኦ ሲያደርግ የነበረ አንጋፋና ታዋቂ በአመስተርዳም የኢትዮጵያውያንን ማህበር በሴራ አዳክመው እንዲፈርስ ተደርጓል።አፍራሾቹም ካለው መንግሥት ጋር እጅና ጓንት ሆነው ለመስራት በአገርቤትና በውጭ መረባቸውን ዘርገው የቀረውን የማህበር ዋና አካል ለማፍረስ ወይም ለመቆጣጠር ደባ በመምታት ላይ ናቸው።ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ የማህበሩን ተጠሪዎች ስብሰባ ጥሩ በማለት ማህበሩን ለመንጠቅና ለጎሰኛው መንግሥት መሳሪያ ለማድረግ መንጋዎቻቸውን በመቀስቀስ ላይ ናቸው።
2 ከወራቶች በፊት የዘፋኞች ቡድን መጥቶ በትግራይ ተወላጆች በኩል በተደረገ ተቃውሞ የተያዘው አዳራሽ ውሉን ሰርዞ በትንሽ የሰፈር አዳራሽ ውስጥ 16 ታዳሚ በተገኘበት ሁኔታ ተሰናክሏል።
3 ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኡትሬክት በተባለው ከተማ በሜይ 6 ቀን 2023 ከአገር ቤት በመጡ ተዋንያን የሚቀርብ ትያትር በ40 ኤሮ ክፍያ ለማሳዬት ሽርጉድ እዬተባለ ነው።በዚያም አላበቃም እንቅስቃሴውን በማስፋት ለብዙ ጊዜ ሲካሄድ የነበረውን ጤናማ ዝግጅት በመጥለፍ በሚመጣው የበጋ ወር ከጁላይ 26-29 ድረስ በአውሮፓ ደረጃ በአመስተርዳም ከተማ የሚካሄድ የእስፖርትና ባህል ዝግጅት በመካሄድ ላይ ነው።ከ10 ዓመት በፊት በተመሳሳይ ደረጃ በተከናወነ ዝግጅት የተገኘ ገንዘብ በጥቂት ሰዎች ተሰርቆ ብዙ ጭቅጭቅ እንዳስነሳ አይዘነጋም፣የለመደች ጦጣ እንዲሉ የዚያው ስርቆት አካል የነበሩ ከአዲስ መጦች የስርዓቱ ተላላኪዎችና ከኤምባሲ ጋር ተባብረው በእስፖርት ሽፋን ለመንግሥት ሽፋን ለመስጠት ሽርጉድ እያሉ ነው።
ጤነኛ አይምሮ ያለው ሰው ዘፈንና ትያትር እንዲሁም እስፖርት አይጠላም።እነዚህ ለአይምሮና ለአካል ጠቃሚና ተመራጮች ናቸው።ጥያቄው ግን መቼ፣በማንና እንዴት ለምንስ ተግባር የሚሉትን ከግንዛቤ ውስጥ ያስገባ መሆን አለበት።እንኳንስ እነዚህን የመሳሰሉ ማህበረሰብአዊ እንቅስቃሴዎች ይቅርና እዬዬም ሲደላ ነው እንደሚባለው በቅጡ ለማልቀስም ቦታ፣ጊዜና ሁኔታን ይጠይቃል።አሁን አገራችንና ወገናችን የሚገኙበት ሁኔታ አስረሽ ምችው የምንልበትና የምንዝናናበት ወቅት አይደለም።ጊዜያችን፣እውቀታችን ገንዘባችን ለተፈናቀለው፣ለአገር አንድነት፣ ለሰብአዊነት፣ለፍትህና ለእኩልነት ለሚታገለው ወገናችን መሆን ይኖርበታል። የአገር አንድነት ሲረጋገጥ፣፣ሕዝብ በሰላምና በፍቅር መኖር ሲችል፣ሃሳቡን በስነጽሁፍ፣በትያትርና በሙዚቃ ሲገልጽ ወዘተ በዚያ ጊዜ ለአስረሽ ምችው እንደርስበታለን።
መንግሥት ተብዬው አገር አጥፊ ቡድን ለዘረጋው ዘመቻ አገር ወዳዱ የመልስ ምት የሚያደርግበትን ዘመቻ ውሎ ሳያድር መጀመር አለበት። የጥፋት ዘመቻው በብዙ መልኩ የሚካሄድ እንደመሆኑ መጠን ምላሹም እንደዚያው ባለብዙ መልክ መሆን ይኖርበታል።በፖለቲካው፣ በወታደራዊ፣በኤኮኖሚው፣በማህበረሰብ ጥያቄና እንቅስቃሴ፣ የመልስ ዘመቻው መጠናከር አለበት።ለዚያም እርስ በርሱ እዬተናበበ ተመሳሳይ እርምጃ ለመውሰድ ይችል ዘንድ አንድ ዓለም አቀፋዊ ንቅናቄ የሚያካሂድ አካል መፍጠር ይኖርበታል።አገር አጥፊዎቹ የሚፈልጉትን የሚያደርጉትና እውቅና የሚቸራቸው በመደራጀታቸው ነው።እኛንም ለጥቃት የዳረገን በአንድ ድርጅት ጣራ ስር አለመደራጀታችን ነው።ለዚያ መንደርደሪያ ይሆነን ዘንድ በቅርባችን የሚንቀሳቀሱትን የመንግሥት ተላላኪዎች አደብ ማስገዛት ይኖርብናል።የሰው ልጅ ለሚያርድ፣አገር ለመበታተን ለተነሳ ቡድን ድጋፍና ሽፋን የሚሰጥ ግለሰብም ሆነ ስብስብ በቅርባችን እያለ ስለ አገር ማሰቡ ከንቱ ውዳሴ ይሆናል። በእርቀት ላይ ጠመንጃ ከደቀነ ጠላት ይልቅ በአጠገብ ሰንጢ የመዘዘ ጠላት ይበልጥ አደገኛ ነው።በዚህ ተግባር ላይ የተሰማሩትን መክሮ መመለስ ካልተቻለ አስፈላጊው ማህበረሰብአዊ እቀባ ሊጣልባቸው ይገባል።ስለሚወሰደው እቀባ ዬዬከባቢው ማህበረሰብ ተወያይቶበት ሊወስን ይገባል።
በተጨማሪም የጥፋት እጃቸው በሁሉም አቅጣጫ ስለሚዘረጋ በንቃት መከታተሉ ከአደጋ ያድናል።የምሁር ካባ ካጠለቁት አድርባዬች በተጨማሪ ቤተእምነቶች ሳይቀሩ በነሱ የተበከሉ ላለመሆናቸው ማረጋገጫ የለም።ጳጳስም፣ቄስም ዲያቆንም ምእመንም፣ኢማምም፣ደረሳም፣መጅሊስም መስለው ይቀርባሉ። ለትንሽ ጥቅማ ጥቅም፣ አገር ሳይኖር ሊኖሩ ለማይችሉበት ለቁራሽ መሬትና ለበሰበሰ፣ውሃና መብራት ብቻም ሳይሆን ንጽህናው ላልተጠበቀ መኖሪያ ቤት{ኮንዶ) ሲሉ ህዝባቸውን አሳልፈው የሚሰጡ ደካሞች የጥፋት ሃይል መኖራቸውን አንዘንጋ።ዓይናችን ሁሉንም፣ ዙሪያ ገጠሙን የሚያይ የንስር ዓይን ይሁን፣መጃጃልና የዋህነት ይብቃ! ወቅቱ ሚናና ጎራ የሚለዩበት ወቅት ነው።ሁለት ቦታም ላይ ሆኖ መንፈራጠጥ ወይም ጅዋጅዌ የሚጫወቱበት ወቅት አይደለም።
ለሁለገብ ዘመቻ እንዘጋጅ!
አገሬ አዲስ