የአደዋ ድል በተሃድሶና በኢንላይተንሜንት መነፅር ሲታይ ! –  ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)

 መጋቢት 1 2023
ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)

እ.አ አ በ1896 ዓ.ም ጣሊያን ለመጀመሪያ ጊዜ  አገራችንን ስትወር በጊዜው የነበረውን ደካማ አገር፣ የጠነከረ የመንግስት አወቃቀርና አመራር አለመኖር በመገንዘብ ነበር። እንደሚታወቀው በወቅቱ ኢትዮጵያ ከጣሊያን ጋር ስትወዳደር በቴክኖሎጂና በጦር ኃይል ወደ ኋላ የቀረች ነበረች። ህዝቡን የሚያስተሳስረውና በአንድነት የሚያስነሳው ልዩ ልዩ ተቋማት አልነበሩም። በተለይም በሰሜኑ ክፍል የሚገኘው ህዝብ አብዛኛው በግብርና የሚተዳደር ነበር። ከዚህም በላይ ሁኔታውን ከባድ የሚያደርገው አፄ ምኒልክ ስልጣንን ሲይዙ በተለይም በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በመሳፍንቶች መሀከል ይደረግ የነበረው ትግልና የኋላ ኋላ በአፄ ቴዎድሮስ ድል አድራጊነት ቢቋጭም ይህንን ያህልም የበረደ አልነበረም።  አብዛኛው መሳፍንት እዚያው በዚያው የሚያስብ እንጂ አገራዊና ብሄራዊ ስሜትን ያዳበረ አልነበረም። በሌላ አነጋገር፣ ሙሉ በሙሉ በማዕከላዊና በአንድ ንጉሰ-ነገስት ጥላ ስር የመገዛት ፍላጎት አልነበረውም። በዚህና በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ ጣሊያን ኢትዮጵያን ለመውረርና ድል በመቀዳጀት አገራችንን ሙሉ በሙሉ የመቆጣጠር ዕድል ነበራት።

እንደሚታወቀው ጣሊያን ከሌሎች የቅኝ-አገዛዝ ኃይሎች ጋር፣ ማለትም ከስፔይን፣ ከፖርቱጋል፣ ከእንግሊዝና ከፈረንሳይ ጋር ስትወዳደር  ኋላ ብቅ ያለችና በአፍሪካ ውስጥም አንድንም አገር የቅኝ ግዛቷ ያደረገች አልነበረችም። ስለሆነም ልክ እንደሌሎች የምዕራብ አውሮፓ አገሮች የራሷ የሆነ የቅኝ ግዛት እንዲኖራት የምትመኝ ነበረች። ለዚህ ደግሞ በጊዜው በማንም የአውሮፓ ኃይል ቅኝ-ግዛት ያልሆነችው ኢትዮጵያ አመቺ ነበረች። አብዛኛዎቻችን እንደምናውቀው ቀደም ብሎም ሆነ በኋላ ላይ የአውሮፓ ኃያል መንግስታት በጀርመኑ ቻንስለር በኦቶ ቢስማርክ አማካይነት በ1884 ዓ.ም በርሊን ተጋብዘው ሲወያዩ ዋና ዓላማቸውም በጊዜው አልሰለጠነም የሚሉትን አህጉር እንዴት አድርገው እንደሚቀራመቱ ነበር።  በእነሱ ዕምነት የአፍሪካ ህዝብ ያልሰለጠነ፣ ንጉሳዊ ወይም ሌላ የሰለጠነ አገዛዝ የሌለው፣ ሃይማኖት ያልነበረውና፣ እዚህና እዚያ እንደ አውሬ እየዘለለና ፍራ-ፍሬ በመለቃቀምና በአደን የሚኖር ነበር። ስለሆነም በእነሱ ግምት ይህንን ያልሰለጠነ ህዝብ ማስልጠን ያስፈልጋል የሚል ነበር። ይሁንና በዚህ አሳበው ወደ አፍሪካ ቢመጡና ብዙ አገሮችንም በቁጥጥራቸው ስር ለማድረግ ቢችሉም፣ ድብቅና ዋናው ዓላማቸው የአፍሪካን ህዝብ ለማስልጠንና ለማስተማር፣ ከተማዎችንና መንደሮችን ለመገንባት፣ የባቡር ሃዲድ ለመዘርጋትና በስራ-ክፍፍል ላይ የተመሰረተ የዳበረ ኢኮኖሚና የሰለጠነ ተቋማት ለመገንባት ሳይሆን የእፍሪካን የጥሬ-ሀብት ለመዝረፍ ነበር።

ከ18ኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ በእንግሊዝ ምድር የተጀመረው የኢንዱስትሪ አብዮት በፈረንሳይና  ኋላ ደግሞ በጀርመን ምድር ተቀባይነትን በማግኘት በመሀከላቸው የጦፈ ውድድር ይደረግ ነበር። አብዛኛዎቹ የአውሮፓ አገሮች ኢንዱስትሪዎችን ቢተክሉምና ዘመናዊነት የሚባለውን ፖለቲካ ቢከተሉም ኢንዱስትሪዎቻቸውን ለማንቀሳቀስ የሚረዳ የጥሬ-ሀብት አልነበራቸውም። ስለሆነም የግዴታ የተለያዩ የጥሬ-ሀብቶችንና፣ በአውሮፓ ምድር ሊበቅሉ የማይችሉትን እንደ ቡና፣ ካካኦና ኦቾሎኒ፣ እንዲሁም ሌሎች የትሮፒካል ፍራፍሬዎችና የቅባት እህሎችን ለማግኘት የሚችሉት ከአፍሪካ አህጉር ብቻ ነበር።  በመሆኑም ያላቸው አማራጭ አፍሪካን መቀራመትና በቁጥጥራቸው ስር በማድረግ ሀብቷን መዝረፍ ነው። የጣሊያንም አካሄድ ከዚህ የተለየ አልነበረም። ጣሊያን በደንብ የተደራጀ ኃይል የነበራትና ቀደም ብሎ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ግዛት መሬት በመከራየት የያዘችውን ቦታ በማስፋፋትና ራሷን በማጠንከር ኢትዮጵያን በቀላሉ ለመያዝና በቁጥጥሬ ስር ለማድረግ እችላለሁ የሚል ግምት ብቻ ሳይሆን የጸና ዕምነት ነበራት።

የውጫሌው ውል ስምምነት ከፈረሰ በኋላ አፄ ምኒልክ ያላቸው ዕድል እንደምንም ብለው የጦር መሳሪያ ከዚህና ከዚያ በማግኘት፣ አልተባበራቸውም ያላቸውን የመሳፍንት አገዛዝ በማባበልና አገር ማስቀደም ያስፈልጋል በሚለው ጠቢባዊ አካሄዳቸው፣ ህዝባቸውም ከጎናቸው እንዲሰለፍና የተቻለውን እንዲያድረግ በማድረግ ራሳቸውና እትጌ ጣይቱ ጦሩን በመምራትና በመዝመት ቀስ በቀስ የጣሊያንን ጦር በመግጠም መግቢያና መውጫ ካሳጡት በኋላ ጣሊያን ባልጠበቀውና ባላሰበው ሁኔታ የተደራጀውን ኃይልና የተሻለ አዘገጃጀት አለኝ የሚለውን የወራሪ ኃይል አንኮታክተው በመጣል ለመጀመሪያ ጊዜ የጥቁር ህዝብ በንጉሳዊ አመራሩ በመመራት በነጭ ወራሪ ኃይል ላይ ድልን ለመቀዳጀት ቻለ። በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥም አዲስ ምዕራፍ ተከፈተ። ይህ ዐይነቱ ድልና የህዝቡም መሰባሰብ አዲስ ለምትገነባው ኢትዮጵያ መሰረት ሊሆን ቻለ።

አፄ ምኒልክና የተቀሩት አርበኞቻቸው ድልን ከተቀዳጁ በኋላ፣ በተለይም የአገራቸውን ደካማ ጎን የተረዱት መሪ የግዴታ አገራቸውን ዘመናዊ ማድረግ ነበረባቸው። በሳቸውም ዕምነት ሆነ ከህብረ-ብሄር አገነባብ ታሪክ እንደምንማረው አንድ አገር በድጋሚ ለመወረር የማትችለው በጸና መሰረት ላይ ስትገነባ ብቻ ነው። ስለሆነም በአፄ ምኒልክ ተነሳሽነትና አርቆ አሳቢነት ህዝቡን የሚያስተሳስር የኢኮኖሚ መሰረት ለመጣል ቻሉ፡፡ የባቡር ሃዲድ መዘርጋት፣ ድልድዮችንና መንገዶችን መስራት፣ ትምህርትቤቶችንና ክሊኒኮችን መክፈት፣ የፖስታ ቤት መክፈት፣ የማዕከላዊ ባንክ በመክፈት በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት የሚኖረው የመገበያያ ገንዘብ ማተም… ወዘተ. እነዚህና ሌሎች ተግባራዊ የተደረጉት እርምጃዎች በሙሉ የዘመናዊነትና ህዝብን በአዲስ መንፈስ የማስተሳሰር መሰረቶች ናቸው። በእነዚህም አማካይነት ነው አንድ አገር እንደ አገር ሊገነባ የሚችለውና በህዝቡም ዘንድ የአገራዊነት ስሜት ሊዳብር የሚችለው። በዚህም የተነሳ ነው ቀስ በቀስ የኢትዮጵያዊነት ስሜት ሊዳብር የሚችለውና፣ የቻለው።

በአብዛኛዎቻችን ዘንድ ይህንን ያህልም ግንዛቤ ያላገኘው አፄ ምኒልክና አርበኞቻቸው ህዝባቸውን ከጎናቸው አሰለፈው በወራሪው ጣሊያን ላይ ያንን የመሰለ ድል ቢቀዳጁም፣ ከድል በኋላ ተግባራዊ ካደረጓቸው የዘመናዊነት ፖሊሲዎች ባሻገር አንድን አገር ለመገንባት የሚያስችል የተማረ ኃይልና ተቋማት በጣም ወሳኝ ነው። በሰለጠነ ኃይልና በሰለጠኑ ተቁማት ብቻ ነው ለሰፊው ህዝብ ልዩ ግልጋሎቶችን መስጠት የሚቻለው። ህዝቡንም ለማስተማር፣ በተለያየ የሙያ ዘርፎች ለማስልጠንና በምድር ላይ ያለውን የጥሬ-ሀብትና የሰው ኃይል ለማንቀሳቀስ የሚቻለው፤ የሰለጠነ ኃይል ሲኖርና ዘመናዊነት ማለት ምን ማለት ነው? እንዴትስ ነው ቀስ በቀስ በስርዓት የሚተገበረው?  የሚለውን መሰረተ-ሃሳብ የተረዳ ኃይል ሲኖር ብቻ ነው። በዚህም መሰረትና ከተለያዩ አካባቢዎችና ምሁሮች የሚመጡትን ሃሳቦች በማሰባሰብ፣ በማውጣትና በማውረድ ነው ቀስ በቀስ የሰለጠነና በጠንካራ መሰረት ላይ ሊቆም የሚችል አገር መገንባት የሚቻለው:: በጊዜው የአፄ ምኒልክ ኢትዮጵያን ዘመናዊ የማድረግ ፍላጎት ግልጽ ቢሆንም ሰፋ ያለና የተገለጸለት የምሁር ኃይል አልነበረም። ይህም ማለት አፄ ምኒልክ ስልጣንን ሲጨብጡና ከአደዋ ድል በኋላ የዘመናዊነትን ፖሊሲ ተግባራዊ ለማድረግ ሲነሱ ከዜሮ መነሳት ነበረባቸው። አፄ ምኒልክም ዕድሜያቸው የገፋና በመጨረሻም በመታመማቸው ህልማቸውንና ዓላማቸውን ሙሉ በሙሉ ለማገባደድ አልቻሉም። እንደሚታወቀው የህብረ-ብሄር ወይም የአንድ አገር ግንባታ በአንድ ንጉሰ-ነገስት ወይም በአንድ ትውልድ የሚጠናቀቅ ሳይሆን፣ በተከታታይነት በተከታታዩ ትውልድ መተግበር ያለበት ጉዳይ ነው።

ያም ሆኖ አፄ ምኒልክ የጣሉት መሰረት የኋላ ኋላ ከ1940ዎቹ አጋማሽ ላይ ጀምሮ በአፄ ኃይለስላሴ ተግባራዊ በመሆን በተለይም ከ1950ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ በኢትዮጵያ ምድር ውስጥ አዲስ ዐይነት ለውጥ ሊመጣና ህዝቡንም ቀስ በቀስ ለማስተሳሰር ችሏል። የሙዚቃ አብዮት፣ የቲያትር ቤቶችና ሲኒማ ቤቶች መከፈት፣  የስነ-ጽሁፍ መዳበር፣ ልዩ ልዩ ህንጻዎች መሰራት፣ የምግብ ቤቶችና ሆቴል ቤቶች መከፈት፣ የንግድ እንቅስቃሴ መዳበር፣ ማዕከለኛ ኢንዱስትሪዎች እዚህና እዚያ መከፈትና ስራ ለሚፈልገው የስራ ዕድል መስጠት፣ የዕደ-ጥበብ ስራዎች ማበብ፣ ትምህርት ቤቶችና በተለይም የዕደ-ጥበብ ሙያ ማስልጠኛ መቋቋም፣ ዩኒቨርሲቲና ኮሌጆች መከፈት፣ የመገናኛ መንገዶች መስፋፋት፣ አዲስና ዘመናዊ ቢሮክራሲ መቋቋም፣ አገሪቱን ከወራሪ ኃይል የሚከላከል ወታደራዊ ኃይልና ማሰልጠኛ አካዳሚ መክፈት፣ ፖሊሶችን ማሰልጠን፣ እነዚህና ሌሎች ከ1950ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ መከናወን የጀመሩት የዘመናዊነት መሰረቶች በእርግጥም ህዝባችንን ለማስተሳሰርና መንፈሱንም ለማጠንከር ችለዋል። የአንበሳ ምልክት ያለበት የአረንጓዴ ቢጫና ቀይ ባንዲራ የአገራችን መለያ መሆን፣ እነዚህና ሌሎች ነገሮች በሙሉ ለጊዜው ውስጣዊ ጥንካሬ የሰጡን ነበሩ።

ይሁንና ግን ይህ ዐይነቱ አካሄድ የራሱ የሆነ ጉድለት እንዳለው የማይካድ ሃቅ ነው። ዕድገትና ዘመናዊነት የሚባሉት ነገሮች በእኩል ደረጃ በአገሪቱ ምድር የተካሄዱ አልነበሩም። የተተከሉትም ኢንዱስትሪዎች የማደግና የመስፋፋት ኃይል አልነበራቸውም። ለስልጣኔንና ለዕድገት የሚሆን የሳይንስና የቴክኖሎጂ ጉዳይ አትኩሮ አልተሰጠውም። በዚህም ምክንያት የተነሳ አዲስና የተገለጸለት፣ እንዲሁም ውስጠ-ኃይሉ የጠነከረ የህብረተሰብ ኃይል ብቅ ማለት አልቻለም። አፄ ኃይለስላሴ እሳችውን ሊተካና አገርን በጸና መሰረት ላይ ለመገንባት የሚችል ኃይል ማስልጠን አልቻሉም። ዕድገቱም ያልተሰተካከለ ስለሆነና አገሪቱ ያላትን የተፈጥሮ ሀብት በሚገባ መጠቀም ባለመቻሏ እንደ ወሎ በመሳሰለው ክፍለ-ሀገር በብዙ ሺሆች የሚቆጠር ህዝብን ለሞት የዳረገ ረሃብ ተከሰተ። ይህ ሁኔታና ቀስ በቀስም በከተማዎች የሚታየው የስራ-አጥነትና ከቤንዚን ዋጋ መናር ጋር የተፈጠረው የኢኮኖሚ ቀውስ የአፄውን አገዛዝ መሰረት ማናጋት ጀመረ። ይህ ጉዳይ የተማሪው እንቅስቃሴ አንግቦ ከተነሳው የመሬት ለአራሹ ጥያቄ ጋር በመያያዝ የየካቲት 66 ዓ.ም አብዮት ፈነዳ። በዚህም ምክንያት የተነሳ አፄ ኃይለስላሴ ከስልጣናቸው እንዲወርዱ ተደረገ።

አብዮቱ ከፈነዳበት  ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ አገራችንና ህዝባችን የመረጋጋትን ዕድል ሊያገኙ በፍጹም አልቻሉም። በጊዜው የተፈጠረውን አዲስ ሁኔታና የጥገና ለውጥ ለማስተናገድ የሚችል ኃይል ባለመኖሩ ኢትዮጵያችንና ህዝባችን በጭንቀት ውስጥ ገቡ። ቀደም ብሎ የአደዋን ድል ያልተረዳውና ብሄራዊ ስሜትን ያላዳበረው አንዳንድ ኃይል አዲስ የተፈጠረውን ሁኔታ በመጠቀም ኢትዮጵያችንንና ህዝባችንን ጭንቀት ውስጥ ከተቷቸው።  ጦርነቱ ከውስጥና ከውጭ በመጧጧፍ በጊዜው ስልጣንን ለያዘው የደርግ አገዛዝ መፈናፈኛ ሊሰጠው አልቻለም። ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር በማተኮሩ አገርን በጋራ ለመገንባትና ኢትዮጵያችንን በጠንካራ መሰረት ላይ ለማቆም አልታቸለም። የደርግ አገዛዝም በተለይም በውስጥ ኃይሎች በአንድ በኩል በጦርነት በመጠመዱ፣ በሌላ ወገን ደግሞ በሲቪሉ ቢሮክራሲ ውስጥም ሆነ በሚሊታሪውና በጸጥታው ውስጥ በተሰገሰጉ ለሲአይኤ በሚሰሩ ኃይሎች ስለተጠመደና አገርን የማፍረስ ተንኮል ይሰራ ስለነበር በድሮው የአገዛዝ መልኩ ሊገዛ አልቻለም። ደርግ በአነሳሱና፣ በጠቅላላው ቢሮክራሲው በአንዳች ዐይነት አገርንና ህብረተሰብን ሊያስገነባ በሚችል ፍልስፍና የሰለጠኑ ባለመሆናቸውና ከታች ወደ ላይ በምሁራዊ ሂደት ውስጥ በማለፍ ብሄራዊ ባህርይን ያዳበሩ ባለመሆናቸው በተለይም ከውጭ የሚሸረበውን ተንኮል ለመቋቋም የሚያስችል ዕውቀትና የዓለም አቀፍ ፖለቲካን የመረዳት ኃይል  አልነበራቸውም። በመሆኑም የደርግ መወደቅና አገራችንም በሌላ ብሄራዊ ነፃነቷንና አንድነቷን በሚፈታተኑ ለውጭ ኃይሎች ተገዢ በሆኑ የብሄረሰብን አርማ አንግበው በሚታገሎ ኃይሎች እጅ መውደቋ የታሪኳ ዕጣ ፈንታ ለመሆን በቃ። ይህ ፅንፈኛና ፀረ-ኢትዮጵያና የጠቅላላው ጥቁር ህዝብ ጠላት የሆነው ኃይል ህወሃት ወይንም ወያኔ በመባል የሚታወቅ ነው። ዋና ዓላማውም ለውጭ ኃይሎች ተቀጣሪና ተላላኪ በመሆን ታሪካችንን ማጉደፍና ህዝባችንና አገራችንን በቀላሉ ሊወጡ የማይችሉት  ፈተና ውስጥ መጣል ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  አገር እንዲህ ኾናም አትቀርም (በጽዮን ግርማ)

ወያኔ ስልጣንን ከጨበጠ በኋላ ተግባር ላይ ያዋለው የጎሳ ፌዴራሊዝም የሚሉት ፈሊጥ የኢትዮጵያን ዕድገት የመቶ ዓመት ያህል ወደ ኋላ የጎተተ ነው። በህዝባችን ዘንድ አለመተማመን እንዲፈጠር ያደረገ ነው። ወያኔ ለከፋፍለህ ግዛው እንዲያመቸው ተግባራዊ ያደረገው ይህ ዐይነቱ የጎሳ ፌዴራሊዝም በመሰረቱ የተጠነሰሰው በአሜሪካኖችና በእንግሊዞች አገርን አድካሚና በታታኝ ኃይሎች ነው። ሰፊው ህዝባችን ኃይሉን በመሰብሰብ፣ በመተባበርና በመተጋገዝ መንፈስ ጠንካራ አገር እንዳይገነባ የተደረገ የነጮች ሴራ ነው። ምክንያቱም አንድ ህዝብ ሲተባበርና ሲተጋገዝ፣ እንዲሁም በአንድ መንፈስ ተነሳስቶ አገርን መገንባት ለኢምፔሪያሊስት ኃይሎች የሚገቡበትን መንገድ ስለሚዘጋባቸው ነው። ስለሆነም ይህ ዐይነቱ መተባበርና በጋራ መንፈስ መደራጀት ተግባራዊ መሆን የለበትም። ሰፊው ህዝብ መማርና መንቃት የለበትም። አስተሳሰቡ ሁሉ ተበታትኖ መኖር አለበት። ከየት እንደመጣ፣ ለምን በዚህች ዓለም ላይ እንደሚኖርና፣ ምንስ ማድረግ እንዳለበት ማወቅ የለበትም። እንደከብት የሚነዳና የሚጠመዘዝ መሆን አለበት። ይህ ዐይነቱ ሁኔታ ኤክስፐርት ነን ለሚሉ በኢ-ሳይንሳዊ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ለሚመሩ የውጭ ኃይሎች የሚያመች ነው። የአንድን አገር ሀብት እንደፈለጋቸው ለመበዝበዝ ያመቻቸዋል። አካባቢን የሚያውድምና ማህበራዊ ግኑኝነትን የሚበጣጥስ ሁኔታ ይፈጠራል። በዚህ መልክ  አገራችን ለዝንተ-ዓለም የጥሬ-ሀብት አምራች ብቻ በመሆን የካፒታሊስቱን ዓለም ስትመግብ ትኖራለች። በዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ስር ወደቃ የጥሬ-ሀብቷ የምትበዘበዝ አገር ደግሞ በቀላሉ መፍትሄ የማይገኝለት የአካባቢና የማህበራዊ ቀውስ ውስጥ ትወድቃለች። ህዝባችን በአገሩ ውስጥ ያለውን የጥሬ-ሀብት በስነ-ስርዓት እያወጣ እስከመጨረሻው ድረስ እዚያው በማምረት ህብረተሰብአዊ ሀብት እንዳይፈጥር ይታገዳል ማለት ነው። ልዩ ልዩ ዕውቀትና ብቃትነት ያለው ምሁራዊ ኃይል ባልዳበረበት አገር ውስጥ በቀላሉ በነፃ ገበያ ስም ተግባራዊ የሚሆነው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ከጎሳ ፌዴራሊዝም ጋር በመዳበል አገርን የሚያዳክምና የሚያፈርስ ስነ-ልቦና  እንዲፈጠር ያደርጋል። አታላይ፣ ሸዋጅ፣ ዕምነት የማይጣልበት፣ በፕሪንሲፕል የማይመራ፣ ደሃና ሽማግሌዎችን የማያከብርና በራሱ ዓለም ውስጥ እየኖረ፣ ለምን እንደሚኖር የማያውቅ የህብረተሰብ ክፍል ይፈጠራል። በዚህ ዐይነት መንፈስ የተቀረጸ ህብረተሰብአዊ ኃይል በተስፋፋበት አገር ውስጥ ደግሞ ስልጣን ላይ ያለው አገዛዝ ሁሉንም ነገር እንደፈለገው ማድረግ ይችላል። የአገርን ሀብት ሲሸጥና ሲያስበዘብዝ የሚጠይቀውና የሚጋፈጠው ኃይል ስለማይኖር በዚያው ይገፋበታል። በተራና ባልሰለጠነ ፖሊስ ደሃው ህዝብ ሲመታና ከቤቱ ወጥቶ በየሜዳው ላይ ሲጣል እንዳላየ ዝም ብሎ ያልፋል። ደሃው ህዝብ ቤቱ ውስጥ ተኝቶ ወይም ቤቱ ውስጥ ተቀምጦ ቤቱ በግሬደር ሲፈርስበት ዝም ብሎ ይመለከታል። ለምድን ነው እንደዚህ የሚደረገው? ማንስ መብት ሰጥቷችኋል?  እንዴትስ ይህ ዐይነቱ ድርጊት በ21ኛው ክፍለ-ዘመን ይደረጋል? የህግ የበላይነትስ በዚህች አገር ውስጥ አይታወቅም ወይ? መንግስት የሚባለው ነገርስ ህዝብን ተንከባካቢ ከመሆን ይልቅ እንዴት እንደዚህ ዐይነት ነገር ያደርጋል? እየተባለ ጥያቄዎችን ለማንሳት የሚችል ኃይል ለመፈጠር ባለመቻሉ የዛሬው ዐይነቱ ሁኔታ  መከሰቱ ይህን ያህልም የሚያስገርም አይደለም።

ወያኔ ስልጣን ከመያዙም በፊትም ሆነ ስልጣን ላይ ከወጣ በኋላ ተግባራዊ ያደረጋቸው የጎሳ ፌዴራሊዝምና የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና የተቀረው የምዕራቡ ካፒታሊስት አገሮች ፕሮጀክቶች ናቸው ማለት ይቻላል ነው። ስንቶቻችንስ ይህ ዐይነቱ አታላይ ሂደት ገብቶናል? ያም ሆነ ይህ  በሂደት ላይ የነበረን የህብረ-ብሄር(Nation-State) አገነባብ ወደ ኋላ በመቀልበስ በጎሳ ላይ የተመሰረተ “አገር ለመገንባት” መጣር ውስጣዊ ግኑኝነትንና ኃይልን ያላላል፣ ያዳክማልም። በሎጂክና በዲያሌክቲክ ላይ የተመሰረተ ክርክርና ውይይትን ከማስቀደም ይልቅ ወደ ጠብ ጫሪነት የሚያመራ ህብረተሰብአዊ ኃይል እንዲፈጠር ያደርጋል። አንድ ህብረተሰብ እንዴት ከታች ወደላይ ቀስ በቀስ እንደተገነባ የማያውቅ ስለሚሆን የዛሬይቱ ኢትዮጵያ በኃይል ብቻና በማስገደድ አንድ  አገር እንደሆነች አምኖ ይቀበላል። ታሪክን ከሳይንስ አንጻር መመርመር ባልተለመደበትና እንደባህልም ባልተወሰደበት አገር ውስጥ ደግሞ የተሳሳተ ትረካን ማስፋፋቱ ቀላል ይሆናል። ተጨቁናችኋል፣ ተገዳችሁ ነው በአንድ ባንዲራ ስር የተጠቃለላችሁት፣ ከዚህ በፊት የነበራችሁን ወርቅ ወርቅ የመሳሰሉ ባህሎችና ስልጣኔዎች በአዲስ ወራሪ ኃይል ፈርሰውባችኋል፣ ተገዢ ለመሆን በቅታችኋል፣ ስለሆነም ነጻ ከመውጣት ወይም ደግሞ የራሳችሁን ዕድል በራሳችሁ ከመወሰን በስተቀር ሌላ አማራጭ መንገድ የላችሁም እየተባለ ይነፈሳል።  ሁሉም ይህንን ዕውነት አድርጎ ስለሚቀበል በተለይም ተጨቁነናል የሚሉ የህብረተሰብ ክፍሎችን ወይም የዚኸኛው ወይም የዚያኛውን የጎሳ ኤሊት ማስተማርና ማስረዳት በፍጹም አይቻልም። አብዛኛውም ከዕውቀት ርቆ የሚገኝ እንደመሆኑ መጠንና ሆዱን ከመሙላት በስተቀር መንፈሱን ሊያድሱለት የሚችሉ መጽሀፎችን ስለማያነብ መነታረክን ያስቀድማል። በቀላሉ ወደ ጠብ ጫሪነት ያመራል። በአጭሩ ወያኔና የዛሬው በአቢይ አገዛዝ የሚመራው ጽንፈኛ ኃይል ይህንን ዐይነቱን የመነታረክን ባህል ነው ያስፋፉትና የሚያስፋፉት። የጎሳ ፌዴራሊዝምም ሆነ የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ምን እንደሆኑና ምንስ ዐይነት አሉታዊ ተፅዕኖና አገርን የማፍረስ ኃይል እንዳለቸው ሳያወጡና ሳያወርዱ ነው ተግባራዊ ያደረጓቸውና የሚያደርጓቸው።

ወያኔ በአሜሪካኖችና በተቀረው የምዕራቡ ዓለም ተገዶ በዓለም አቀፍ የገንዘብና(IMF) የዓለም ባንክ(World Bank) ተወካይነት የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲን ተግባራዊ ሲያደርግ ምን ዐይነት አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ውጤት ሊያመጣ እንደሚችል ለማውጣትና ለማውረድ ጊዜም አልነበረውም። ህወሃት እንደ ነፃ አውጭ ድርጅት በሚሊታሪ ኃይል ከመደራጀቱና ስልጣንን በኃይል ለመያዝ ትግል ከማድረጉ በስተቀር ልዩ ልዩ ለአገር ግንባታ የሚያግዙ ዕውቀቶችን፣ ማለትም የፍልስፍናን፣ የፖለቲካን ቲዎሪ፣ ልዩ ልዩ የኢኮኖሚ ቲዎሪዎችንና ፖሊሲዎችን፣ እንዲሁም የሶስዮሎጂ መጽሀፎችን በማጥናትና በመራመር በውስጡ ክርክር የሚያደርግ ድርጅት አልነበረም። ስለሆነም እንደዚህ ዐይነቱ በእነ ዓለም የገንዘብ ድርጅትና በዓለም ባንክ የረቀቀውን ኢ-ሳይንሳዊ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ ሲያደርግ ከምን አንፃር እንደተነሳ ቀድሞውኑ ለመገመት ያስችገራል። ይሁንና በነፃ ገበያ ስም ተሳቦ ተግባራዊ የሆነው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ለምዝበራና በሀብት ለመደለብ  አመቺ ሁኔታን እንደፈጠረለት የማይታበል ሀቅ ነው። ይህ ዐይነቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲ በካፒታሊዝም የዕድገት ታሪክ ውስጥ፣ በምዕራብ አውሮፓም ሆነ በአሜሪካ ተግባራዊ ሆኖ ስለማያውቅ፣ ከዚያም በኋላ እንደ ጃፓንና ደቡብ ኮሪያ የመሳሰሉት በቴክኖሎጂ የበለጸጉ አገሮች ተግባራዊ ያላደረጉት ሰለሆነ፣ ወደ ኋላ በቀረና ከእጅ ወደ አፍ(Subsistence Economy) በሚታረስበት የኢኮኖሚ ክንዋኔ ውስጥ ተግባራዊ በሚሆንበት ጊዜ የስራ-ክፍፍልን ከማዳበር ይልቅ የተበጣጠሱና ሰፋ ላለ የሀብት ምስረታ የማያመቹ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች ይስፋፋሉ። ሆቴል ቤቶችና ቡና ቤቶች መክፈት፣ የሱቅ በደረቴ መስፋፋትና ለጠቅላላው የኢኮኖሚ መሰረት የማይሆኑ እንደመጠጥና የስኳር ፋብሪካዎች የመሳሰሉ መተከላቸው በመሰረቱ  በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ ለተመሰረተ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የሚያመቹ አይደሉም። ሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ እንዲሁም ማኑፋክቸር በማይስፋፋበት አገር ውስጥ ደግሞ አንድን ህዝብ የሚያስተሳስር ሰፋ ያለ፣ የሚንቀሳቀስና የሚያድግ ጠንካራ ኢኮኖሚ መገንባት በፍጹም አይቻልም። በዚህ ዐይነቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲና እንቅስቃሴ ደግሞ ጠንካራ አገር መገንባት በፍጹም አይቻልም። በማንኛችንም ዘንድ መታወቅ ያለበት ጉዳይ አንድ ጠንካራ ህብረ-ብሄር ሊገነባ የሚችለው ለፈጠራ በማያመቹ፣ ለልዩ ልዩ ባህሎች መዳበር መሰናክል በሚሆን  የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲን ወይም ደግሞ የዓለም ኮሙኒቲው ነኝ የሚለው በሚያስፋፋው የነፃ ገበያ ፖሊሲ አማካይነት አይደለም።

ለማንኛውም ይህ ዐይነቱ የኒዎ-ሊበራል ወይም የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ በመባል የሚታወቀው ለወያኔና ለጥቂቶች  የህወሃት ካድሬዎች ሀብትን ለመዝረፍና ለመደለብ፣ የተወሰነውን ደግሞ ወደ ውጭ እንዲያሸሽ አመቺ ሁኔታን ሊፈጥርለት ችሏል። ሙሉ በሙሉ በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና በግብረአበሮቹ ቁጥጥር ስር የወደቀው የህዋሃት አገዛዝ አሽከር በመሆንና ሀብትን በማዘረፍ፣ በዚያውም መጠንም የዋሁን ሰፊ ህዝብ ወደድህነት ዓለም ውስጥ ሊጥለው ችሏል። ትላልቅ ፎቅ ቤቶች ስለሚሰሩ እየተባለ በአንዳንድ አካባቢዎች ኗሪው ህዝብ ለብዙ ዓመታት ከቀየው እንዲፈናቀል በመደረግ  ወደ መቆሻሻ መኖሪያ ቦታዎች እንዲጣል ሆኗል። በወያኔ 27 ዓመታት የአገዛዝ ዘመን ህዝባችን እጅግ አስቀያሚ ወደ ሆነ፣ በ21ኛው ክፍለ-ዘመን፣ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ዘመን በማይታሰብ ሁኔታ ውስጥ እንዲወድቅ ተገዷል። ጥቂት ነው የማይባል የህብረተስብ ኃይል ከቆሻሻ ቦታዎች ምግብን እየፈላለገ እንደሚገብ ተገዷል። በሌላ ወገን ደግሞ እንደ ሼራተን፣ ብሉ ሬዲስንና ስካይ ላይን በሚባሉ ሆቴል ቤቶች ውስጥ ምግቦች ተትረፍርፈው ይቀርባሉ። በአጭሩ ወያኔና የበላይ አዛዦቹ በአገራችን ምድር ዝብርቅርቅ ሁኔታዎችን ነው የፈጠሩልን።  በነፃ ገበያ ስም ተሳቦ ተግባራዊ የሆነው የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ  በምንም ዐይነት የስራ ክፍፍል እንዲዳብርና የውስጥ ገበያ እንዲስፋፋ ያደረገ አይደለም። በዚህ ዐይነቱ በተለይም የግልጋሎት መስኩን በሚያስፋፋ የኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካይነትም በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ውድድርና ፈጠራ ሊታዩ አይችሉም። በአንፃሩ ቶሎ ቶሎ ብሎ በገንዘብ ለመደለብ ሲባል በንግድ መስክና በሌሎች ለሰፊው ህዝብ በቂ የስራ መስክ ሊከፍቱ በማይችሉ የተዝረከረኩና ውስጣዊ ግኑኝነት በሌላቸው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች ላይ መሰማራት ዋናው ፈሊጥ ሆነ። ከዚህ ጋር ተያይዘው የተስፋፉት ባህልን ለማደስ የማይችሉ የብልግናን መስኮች፣ ሆቴል ቤቶችና የዕፅ ንግድና የጨአት መቃሚያ ቤቶች፣ እንዲሁም ከኦርቶዶክስና ከእስልምና ሃይማኖት ጋር የማይጣጣሙ እንደገብሮ-ሰዶማዊነት የመሳሰሉት በመስፋፋታቸው በተለይም የወጣቱ ትውልድና የተወሰነው የንዑስ ከበርቴው መንፈስ ሊላላ ቻለ። ማድረግና መደረግ በሌላቸው ነገሮች መሀከል ያለውን ልዩነት እንዳያውቅ ተደረገ። ናኦሚ ክላይን The Shock Doctrine በመባል በሚታወቀው መጽሀፏ እንደምታስተምረን የአሜሪካ የነፃ ገበያ አቀንቃኞች(Ideologists) መንፈሱ ከትራዲሽናል እሴቶች የፀዳ አዲስ የህብረተሰብ ክፍል መፈጠር አለበት። በምትኩ ጭንቅላቱ በነፃ ገበያና ገንዘብ በማሳደድ መጠመድ አለበት። በዚያውም የአሜሪካንን የአኗኗር ስልት ዘይቤው ማድረግ አለበት። እነሱ በሚፈልጉት መልክ መንፈሱ የተቀረጸ አዲስ የህብረተሰብ ክፍል ብቅ በማለት የአሜሪካንን ጥቅም የሚያስጠብቅ መሆን አለበት።  የእግዚአብሄርን መኖር በመካድ በሰይጣን የሚያመልክ ትውልድ መፈጠር አለበት። ይህ ዐይነቱ የህብረተሰብ ኃይል ደግሞ ለሁለት ሺህ ዐመታት ያህል አንድን አገር እንደ አገርና ህብረተሰብ እንዲመሰረትና እንዲገነባ ያደረጉና፣ ህዝብን ያስተሳሰሩና ለመንፈስ መዳበር እጅግ አስፈላጊ የሆኑ እንደ ኦርቶዶክስ የመሳሰሉ ሃይማኖቶችን ያስወግዳቸዋል፤ ቄሶችንና ዲያቆኖችን  እንደዋና ጠላት በማየት ያሳድዳቸዋል።  እነዚህን የመሳሰሉት ከትውልድ ወደ ትውልድ የተላለፉ እሴቶችና ሃይማኖት ደብዛቸው ሲጠፋ የውጭ ኃይሎች ገብተው እንደፈለጋቸው መጨፈር ይችላሉ፤ በዚያው መጠንም ብልግናን ያስፋፋሉ። በቀላሉ ሊገዛና ለማስተዳደር የማይቻል ህብረተሰብ እንዲፈጠር ያደርጋሉ።  በዚያውም የአገር ወዳድነት-ስሜት፣ ፍቅርና መተሳሰብ ይሸረሸራሉ። ከመረዳዳትና ከመተሳሰብ ይልቅ ሁሉም በየፊናው ገንዘብ አሳዳጅ በመሆን በተለይም ደሃውንና ደካማውን የህብረተሰብ ክፍል ዞር ብሎ የሚያየው አይኖርም።  ይህ ዐይነቱ አካሄድ ነው ለዛሬው ውዝግብ መሰረቱን የጣለውና ለአደጋም የጋረጠን።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ለቂም በቀል ያልታጨ ማንነት - በቀለ         

የህውሃት አገዛዝ ከወደቀና በአዲስ ኃይል ከተተካ በኋላ አዲስና ብሩህ ሁኔታ ይፈጠራል የሚል ዕምነት ነበረን። አብዛኛዎቻችን በደስታ ፈንድቀን ነበርን። መልኩን አሳምሮና ተኳኩሎ ብቅ ያለው አዲሱ ኃይል  ኢትዮጵያ እያለ የሁላችንንም ልብ በላ። በአዲሱ መሪያችንም በመመራት አዲስ የታሪክ ምዕራፍ የሚከፈት የመሰለን ብዙዎች ነበርን። የቃለ-መጠይቆች ጋጋታ፣ የዩትብ ቻናሎች ውይይትና ክርክር ሁሉ ያስተጋቡት የነበረው አዲስና “ሊበራል መሪ” የመጣ መስሎ ነበረን። አስር ጊዜ ኢትዮጵያ በምንም ዐይነት አትፈርስም እያለ ሲነግረን አምነን ተቀበልነው። አንዳችንም የተሸወድን አለመሰልንም። ጥያቄዎችንም አላነሳንም። በጭፍን መንፈስ በመመራት ሁሉንም ነገር “ለአዲሱና ለሊበራሉ መሪያችን” ለቀቅነው። በራስ ከመመካትና በነፃ አስቦ ለዕውነተኛ  ነፃነት ከመታገል ይልቅ በጭፍን መነዳት ጀመርን።  አንዳንዶቻችን ደግሞ ጉልበት ወደ መሳም አመራን። ፈገግ እያለ ለሚያታልለን፣ እግዚያብሄር ከላይ ወደታች እንደጣለልን ነገር አፋችንን ከፍተን መከተልን ተያያዝነው። አንዳንዶቻችን የኋላ ኋላ ጥያቄዎችን ስናነሳ በዚያው ግለሰብን በማምለከ በገፋው የሚነዳ ኃይል እንደጠላት መታየት ጀመርን። ድሮ አብረን የምንበላ ጓደኛሞች  ተኮራረፍን። በተለይም የተማርን ነን የሚሉት በጭፍን በመመራት፣ የመማርን ጉዳይ በጥያቄ ውስጥ እንድናስቀምጠው ተገደድን። ይሁንና ይህ ዐይነቱ በጭፍን አንድን ግለሰብ ማምለክ ከፊዩዳላዊ አስተሳሰብና ከተሳሳተ የዕውቀት አቀሳሰም ጋር የተያያዘ ለመሆኑ መገንዘቡ ይህን ያህልም ብዙ ጊዜ አልፈጀብንም። ለዚህ ዐይነቱ አንድን ግለሰብ በጭፍን መከተልና ማመን ደግሞ ኢምፔሪሲዝም ወይም ፖዘቲቭ ሳይንስ በመባል ላይ የተመሰረተው የትምህርት አሰጣጥ  ለመሆኑ ወዲያውኑ ለመገንዘብ ቻልን። ፖዘቲቭ ሳይንስ በነገሮች መሀከል መተሳሰር እንዳለ የማያምን የትምህርት አሰጣጥ ዘዴ ነው።  ሁሉም በየፊናው የሚሯሯጥ አንደኛው በሌላኛው ላይ በአዎንታዊም ሆነ በአሉታዊ መልክ የሚገለጽ ተፅዕኖ አይኖረውም የሚል ነው። ለምሳሌ ፖለቲካ፣ የፖለቲካና የመንግስት አወቃቀር በኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ተፅዕኖ አይኖራቸውም። ንቃተ-ህሊናም ቦታ የለውም። አንድ ነገር ከተለወጠ ወይም ከተስተካከለ የሌላው መሻሻል አያስፈልግም የሚል ነው።  የታሪክን ሂደት በቅጡ እንድንገነዘብ የሚያደርግ አይደለም። በትላንትናውና በዛሬው፣ እንዲሁም በነገው መሀከል መተሳሰር እንዳለ አይቀበልም። በተለያዩ ጊዜያት መሀከል በረቀቀ መልክ የሚኖር(Time Binding) ግኑኝነት እንዳለ አይቀበልም። ሁሉም ነገር ከዛሬው አንፃር ብቻ ነው የሚታየው። ስለሆነም በዚህ ዐይነት የትምህርት አሰጣጥ ዘዴ የሰለጠኑ ሰዎች በቀላሉ የመታለል ዕድል ያጋጥማቸዋል። በተሸብረቀረቁ ነገሮች በቀላሉ ይታለላሉ። የነገሮችን  ሂደት ረጋ ባለና በጠለቀ መንፈስ የመመርመር ኃይል የላቸውም። እንደ አቢይ የመሳሰሉት ሸዋጅ ሰዎች በሚናገሩት ቃላት፣ ይሁንና ሳይንሳዊ ይዘት በሌላቸው አነጋገሮች በቀላሉ ያታለላሉ። ወንዱም ሴቱም በመታለል ሳያውቀው አገር አፍራሽ ይሆናል። ይህ ሁኔታ ነው ባለፉ አምስት ዓመት የተፈጠረው።

ለማንኛውም አቢይና የግብረ-አበሮቹ፣ ወይም ደግሞ የኦነግ አገዛዝ ልክ እንደወያኔው አገዛዝ የአሜሪካና የተቀረው የምዕራቡ ዓለም ፕሮጀክቶች ለመሆናቸው ለአብዛኛዎቻችን ይህን ያህልም ግልጽ አይደለም። በተለይም አቢይ አህመድ የአሜሪካና የሳውዲ አረቢያ ፕሮጀክት ለመሆኑ የተረጋገጠ ጉዳይ ነው። ይህንን ጉዳይ ለመረዳት አቢይ ስልጣን ላይ ከወጣ ጀምሮ የተከተለውን ፖሊሲ ማጤን ያስፈልጋል። ይኸውም ወያኔ ከዘረጋውና ካዳበረው የጎሳ ፌዴራሊዝም ፈቀቅ አለማለቱ ነው። በሁለተኛ ደረጃ፣ ግልጽ ያልሆነለትንና ሊገባው የማይችለውን የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ የሙጥኝ ብሎ መያዙ ነው። ይህ ዐይነቱ አካሄዱ ደግሞ ለራሱና ለተቀረው የኦሮሞ ኤሊት የሚያመቸው ነው። በዚህ ዐይነቱ ከፋፋይና አገርን የሚያዳክም ፖሊሲ ብቻ ነው ስልጣን ላይ ለመቆየት የሚችለው። ከዚያም አልፎ በመሄድ ከወያኔ ጋር የነበረውን ውስጣዊ ግኑኝነት በፍጹም አልበጠሰም።  በብዙ ነገሮች ከእነሱ ጋር እየተናበበ የሚሰራ ነው የሚመስለው። ይህ በእንደዚህ እያለ ራሱን ችሎ የወጣ በሽመልስ አብዲሳ የሚመራ የፈረጠመ አገዛዝ አገራችንን ወደ ከፍተኛ አደጋ ውስጥ የጣለ ነው። አቢይና ሺመልስ አብዲሳ እንደ አማራጭ አድርገው የሚከተሉት አካሄድ በአንድ አገር ውስጥ ተፎካካሪ ኃይሎች እንዳሉ ነው ያስመሰላቸው። በመሰረቱ ይህ ዐይነቱ አካሄድ ጠቅላላውን ኢትዮጵያን የሚያዳክም ሲሆን፣ በዚያው መጠንም የኦሮሞን ህዝብ  ጥቅም ሳይሆን ለአሜሪካንና ለአረቦች ታዛዥና ሀብትን አስበዝባዥ የሆነ በኦሮሞ ስም የሚነግድ አመጸኛ ኤሊት ሊወጣ የቻለበትን ሁኔታ እንመለከታለን። በተለይም ህወሃት በአሜሪካኖች አቀነባባሪነት በስሜኑ ዕዝ ላይ ተኩስ ከፍቶ ከገደላቸውና ጦርነትም ከተቀሰቀስ በኋላ አቢይ የተጓዘበትን መንገድ ማጤኑ በጣም አስፈላጊ ነው። ይኸውም የወያኔ ኃይል ሶስት ሳምንት በማይሞላ ጊዜ ውስጥ ከተበታተነና ከተዳከመ በኋላ እንደገና እንዲያንሰራራ አመቺ ሁኔታን ፈጥሮለታል። የኢትዮጵያ ወታደር ከመቀሌና ከአካባቢው እንዲወጣ ከተደረገ በኋላ ወያኔ ኃይሉን በመሰብሰብና በመደራጀት ነው እንደገና ሊወረን የቻለው። በተለይም በወሎና በአፋር ህዝብ ላይ ያደረሰው ዕልቂት የሚታወቅ ጉዳይ ነው። በሌላ ወገን የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና ግብረአበሮች እንደወያኔ የመሰለውን ጽንፈኛ ኃይልና አብይንም ጭምር የሚደግፉት የእነሱን ቤት ስራ ስለሚሰሩላቸው ነው። በአፄ ምኒልክ የተመራው ጀግናው ሰራዊት በነጩ ኃይል ላይ ድልን በመቀዳጀቱ እስካሁን ድረስ ይቆጫቸው ስለነበር አሁን ቂም-በቀል የሚወጡበትን አጋጣሚ ጊዜ አግኝተዋል። እንደፈለጉ የሚጠመዝዟቸውንና የሚያዟቸውን በማስታጠቅና በገንዘብ በመደገፍ ኢትዮጵያችን እንደ አገር እንዳትኖር ለማድረግ ቀን ከሌት ይሰራሉ። በፕሬዚደንት ፑቲን የሚመራው አገዛዝ በቆራጥነት የአገሩን ብሄራዊ ነፃነት ለማስጠበቅ ሰላሳ የሚሆኑ የኔቶ አገሮች ጋር ሲዋጋ፣ የእኛዎቹ ውሾች ለአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ታዛዥ በመሆን አገራችንን ለመበተን በትጋት ይሰራሉ።

በአጭሩ አቢይ የሚባለው እጅግ አደገኛ ኃይል ስልጣንን ከጨበጠ ጀምሮ ህዝባችን እረፍትን አግኝቶ አያውቅም። ቤተክርስቲያናት ወድመዋል፤ ዲያቆኖችና ቄሶች ተገድለዋል፤ ተሰደዋልም። የኦርቶዶክስ ኃይማኖት እንደጠላት በመታየት ሊከፋፈል የሚችልበት ሁኔታ ተዘጋጅቶለታል። አቢይና ግብረአበሮች በማያገባቸው ቦታ ውስጥ ሰተት ብለው በመግባት ከኢትዮጵያና ከአንድነቷ ጋር ተነጥሎ ሊታይ በማይችለው የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ላይ ከፍተኛ ዘመቻ በማካሄድ ቤተክርስቲያኗን ለማዳከም ያላደረጉትና የማያደርጉት ሙከራ የለም።  አቢይ አህመድ ከዚህ አልፎ በመሄድ አገሪቱ በሶስት እንድትከፋፈል ከአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ትዕዛዝን በመቀበል ይህን ተግባራዊ ለማድረግ የማይሸርበው ተንኮል የለም። አቢይ አህመድ በራሱ ጭንቅላት የሚመራ ሳይሆን በአሜሪካኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስተር በብሊንከንና በጆርጅ ሶሮን በሃብታሙ የሚመራ ሰው ነው። ዋና ዓላማውም በስንትና ስንት ትግልና መስዋዕትነት የተገነባችውንና  የቆንጆ ህዝብ አገር የሆነችውን፣ የሚያማምር የተፈጥሮ አቀማመጥና ባህል ያለውን አገርና ህዝብ ለአንዴም ለመጨረሻም ጊዜ ለመበታተን የተነሳ አደገኛ ኃይል ነው። እነአቢይ እንደሚነግሩን ከሆነ እኛ የምናውቃትንና አባቶቻችንና እናቶቻችን ያስተላለፉልን ኢትዮጵያ በማፈራረስ እነሱ በሚፈልጉት የብልጽግና መንፈስ፣ ይሁንና ደግሞ የብልግና መንፈስ ለመገንባት ነው የሚፈልጉት። መንፈሳዊ ተሃድሶን የሚቀናቀንና ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ ዕድገት የማያመች በዘረፋ ላይ የተመሰረተ አገር ነው ለመገንባት የሚፈልጉት ማለት ነው። በዚህ ዐይነት አካሄዳቸውም በአውሮፓ ምድር ውስጥ በአስራአምስተኛውና በአስራሰባተኛው ክፍለ-ዘመን ብቅ ያሉትን ሬናሳንስና ኤንላይተንሜንት የሚባሉትን መሰረታዊ አስተሳሰቦች የሚቀናቀኑ ናቸው። በሬናሳንስም ሆነ በኢንላይተንሜንት አስተሳሰብ አርቆ ማሰብና( Rational Thinking) ሎጂካዊ አስተሳሰብ ለአንድ ህብረተሰብ ግንባታ በጣም አስፈላጊ ናቸው።  የእነ አቢይ የብልጽግና አካሄድ ይኸኛውን ሳይንሳዊውንና ለሰው ልጅና ለህብረተሰብ በጣም አስፈላጊ የሆነውን መሰረተ-ሃሳቦች የሚቀናቀን ነው። በጉልበትና በሽወዳ፣ እንዲሁም በመለፍለፍ የሚያምን ነው።  ይህ ዐይነቱ አካሄድ ጠቅላላውን ህዝባችንን የሚጎዳና ለዝንተ-ዓለም እየተናቆረ እንዲኖር የሚያደርገው ነው። ጥቂቶች ካልሆኑ በስተቀር ማንም ተጠቃሚ አይሆንም።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የሚያሸንፈው ፋኖ ወይስ መንግስት?

ወያኔ የሰፊውን የትግሬ ብሄረሰም ጥቅም አስጠባቂ ያልሆነውን ያህል፣ አቢይና ግብረአበሮቹ፣ እንዲሁም እነጃዋርና የተቀረው ደንቆሮ የኦሮሞ ኤሊት የኦሮሞን ብሄረሰብ ጥቅም የሚያስጠብቁ አይደሉም። በስሙ እየነገዱ ደሀና ደንቆሮ ሆኖ እንዲቀር የሚያደርጉት ናቸው። አንድ ብሄረሰብ ነኝ የሚል ከሌላው በመነጠል አይደለም የራሱን ጥቅም የሚያስጠብቀው፤ ሳይንሱም አይፈቅድም። ክሌላው ጋር በንግድ አማካይነት፣ በምርት ቦታ፣ በትምህርት ቤቶችና በልዩ ልዩ የመገናኛ መስኮች ሲገናኝ ብቻ ነው እንደሰው ሊታይና ውስጣዊ ኃይል ሊያገኝ የሚችለው። ከሌላው ጋር ሲገናኝና ሲጋባ ብቻ ነው ቋንቋንና ልዩ ልዩ ባህሎችን ማዳበር የሚችለው። ራሱን ነጥሎ፣ ይህ የእኔ ብቻ  ነው የሚል የአንድ ህብረተሰብ ክፍል አካል የመጨረሻ መጨረሻ ይጎዳል፤ ይጠቃልም። አንድ ዐይነት አስተሳሰብ በተስፋፋበትና እያንዳንዱ ብሄረሰብ ራሱን አግልሎ በሚኖርበት አካባቢ የስራ-ክፍፍልና ፈጠራዎች ሊዳብሩ በፍጹም አይችሉም። ወያኔ ቀድሞ፣ አሁን ደግሞ አቢይና ግብረአበሮች ይህንን ዐይነቱን የተፈጥሮንና የህብረተሰብን ህግ በመጣስ በብዙ ሺሆች የተሳሰረን ህዝብ በብሄረሰብ ነፃነት ስም አሳበው ለመነጣጠል ነው የሚፈልጉት። በዚህ አካሄዳቸው በይበልጥ የሚጎዳው የኦሮሞ ብሄረሰብ ነኝ የሚለው ምስኪኑ ደሃ ህዝብ ነው። ሰሞኑን በቦረና የተከሰተው ድርቅና ረሃብ የሚያረጋግጠው ይህ ሁኔታ ለአዲሱ የኦሮሞ ኤሊት ደንታ እንደማይሰጠው ነው።  አዲሱ ኤሊት በቪላ ቤት ውስጥ ሲኖርና ጥሩ ጥሩ ምግቦች ሲመገብ፣ ደሃው ህዝብ ይራባል።  አንድ ነገር በአገራችን ምድር ቢፈጠር ደግሞ እነ አቢይ ወደ ውጭ ለመሸሽ ቀድሞውኑ ተዘጋጅተዋል። ሀብት አሽሸተዋል፤ ቤትም ገዝተዋል፤ ልጆቻችውንም አሽሸተዋል። ስለሆነም አክራሪ የሆነው የኦሮሞና የትግሬ  ወጣት ቆም ብሎ ማጤን አለበት። ዝም ብሎ ከመነዳት ይልቅ ራሱን መጠየቅ አለበት። የነገሮችን ሂደት ለመገንዘብ መማርና ማወቅ አለበት። ከወያኔ፣ አሁን ደግሞ ከእነ አቢይና ጃዋር የሽወዳና የማጭበርበር ፖለቲካ መላቀቅ አለበት። ሰው መሆኑን ማረጋገጥ አለበት። ብሄረሰብ ሆኖ የተፈጠረ እንደሌለ መገንዘብ አለበት። ባጭሩ ራሱን ማግኘት አለበት።

ስለሆነም ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ ትንሽ ትልቅ ሳይባል የእነ አቢይን አገርን የመከፋፈልና የመበታተን አካሄድ በማጤን በአንድነት በመነሳት አገሩንና ራሱን ከአደጋ ማዳን አለበት።  በተለይም ወታደሩና የፀጥታው ኃይል በእነ አቢይ በጭፍን የሚታለልና የሚታዘዝ መሆን የለበትም። ከውጭ ሊወረን የሚፈልግ ኃይል ብቻ ሲመጣ መነሳት ሳይሆን፣ ዛሬ አገራችንን ከውስጥ ሆኖ ለማፈራረስ ታጥቆ የተነሳ  የተደራጀ ኃይል ስላለ እሱን ማስወገድ የመጀመሪያው ተግባር መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። አገር አንድ ጊዜ ከፈራረሰ በኋላ የውጭ ኃይሎች መጫወቻ ስለሚሆን እንደገና መልሶ መገንባት በፍጹም አይቻልም። ስለሆነም አባቶቻችንና እናቶቻችን የጣሉልንን አደራና የጥንካሬ መንፈስ በማደስ በመተባበር አገራችንን ከዚህ ዐይነቱ የጭራቅ ኃይል ማዳን አለብን። አቢይ ራሱን ለማዳን ሲል ሲስቅ በፍጹም አለመታለል። እሱንም ከእንግዲህ ወዲያ እንደ አገር መሪ ማየት መቆም አለበት። ተመርጫለሁ በማለትና በህገ-መንግስቱ እያሳበበ እንደነቀርሳ በሽታ አገራችንን ከውስጥ ሲሰረስረን ዝም ብሎ ማየት የወንጀሉ ተባባሪ መሆን ነው። በተለይም ለአቢይ የምታጎበድዱ የብአዴን ሰዎች እስካሁን ድረስ ጭቁኑ የአማራ ህዝባችሁ በመንግስት በተደራጀ የኦነግ/ሸኔ በሚባል የመጠሪያ ስም በሚንቀስቀስ ኃይል ሲገደል፣ ሲታረድና ተፈናቅሎ ሲሰደድ ዝምባልችሁ ስታዩ ከርማችኋል። አንዳንዶቻችሁም የራሳችሁን ህዝብ እንደወራሪ ኃይል እያያችሁ እዚያ ማን ሂድ አለህ በማለት በህዝባችሁ ላይ አሹፋችኋል። መታወቅ ያለበት ጉዳይ የኦሮሞ ብሄረሰብ ወደ ወለጋና ወደሌሎች የአገሪቱ ግዛቶች ከመስፋፋቱ በፊት የአማራው ብሄረሰ ከአስራ-አራተኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ፣ በተለይም የኦርቶዶክስን ሃይማኖት ለማስተማር ሲሰማራ ነበር። በየሄደበትም ቦታ አካባቢዎችን ሲያለማና ተጋብቶና ተዋልዶ የኖረ ህዝብ ነው። ራሱን አግልሎ የሚኖር ብሄረሰብ አልነበረም። ስለሆነም የአማራውን ብሄረሰብ እንደመጤ ማየቱና በእሱ ላይ ዘመቻ ማድረጉ የህብረተሰብን አገነባብ ታሪክ ካለማወቅ የሚነዛ ወሬ ነው።

ያም ተባለ ይህ ሁላችንም በእንደዚህ ዐይነቱ የተሳሳተ ትረካ መጠመድ የለብንም። ወያኔና አቢይ አህመድ ከእነ ግብረአበሮቹ ጭምር የአሜሪካኖችና የተቀረው የካፒታሊስት አገሮች፣ እንዲሁም የአረብ አገሮች ስራ አስፈጻሚዎች መሆናቸውን በመገንዘብ በአንድነት መነሳት አለብን። በሚሆን በማይሆን ነገር ጭንቅላታችንን መጥመድ የለብንም። መማርና ማወቅ ነው ከአደጋና ከተንኮል ሊያድነን የሚችለው። ይህ ሲሆን ብቻ ነው ለሁላችንም የምትሆንና ለተከታታዩ ትውልድ የምትተላለፍ ጠንካራ አገር መገንባትና ማስተላለፍ የሚቻለው። ስለሆነም ከሁለት አንዱን መምረጥ አለብን፤ ይኸውም ኢትዮጵያ ስትፈራርስና ህዝቦቿ ሲሰደዱ ማየት፤ አሊያም ደግሞ በዕውቀት አማካይነት ኃይላችንን በማስተባበር የአደዋ ጀግኖች የተዉልንን መንፈስና ታሪክ እንደገና በማደስ ለአዲስቱ ኢትዮጵያ መታገል። ክተግባባንና ከተባበርን የማይቻል ነገር ስለሌለ ስው መሆናችንን በዓለም ፊት ማረጋገጥ አለብን። የተሃድሶና የኢንላይተንሜንት እንቅስቃሴዎች እንደሚያስተምሩን፣ ራስን ማወቅ፣ ለዚህ ደግሞ በተከታታይ ማጥናትና መመራመር፣ የነገሮችን ሂደት በሚገባ ማየት፣ በዲሲፕሊን መመራት፣ ሀቀኛ መሆን፣ የራስን ጥቅም ሳይሆን የአገርንና የህዝብን ጥቅም ማስቀደም፣ ማንኛውንም ነገር በሆይ ሆይ ሳይሆን በጥንቃቄ መስራት እንዳለብን መገንዝብ፣ በገንዘብ አለመታለል፣ ተንኮልን ከጭንቅላት ውስጥ ነቅሎ ማስወጣት፣ ለሌላው ሰው አሳቢ መሆን፣ አለሁ አለሁ ብሎ አለመታየት፣ በተፈጥሮና በሰው መሀከል ግኑኝነት እንዳለ በመረዳት በተፈጥሮ ላይ ዘመቻ አለማድረግ፣ ጥበብን ማስቀደም፣ በስነ-ምግባርና በሞራል መመራት። የአደዋም ድል መልዕክትና መመሪያ ይህ ነው። አባቶቻችንና እናቶቻችን በአደዋ ላይ የተቀዳጁት ድል ሰብእዊነትንም ነው የሚያስተምረን። እንደ አፄ ምኒልክ አስተዋይና አርቆ አሳቢ መሆን፣ ለማንም ሳያደሉ ሁሉንም በእኩል ማየት፣ ፍትሃዊነትን ማስቀደም። ብሄራዊ ነፃነታችንን ለማስጠበቅ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ሁለ-ገብ ኢኮኖሚ መገንባት። ከተማዎችንና መንደሮችን ባህላዊና ጥበባዊ በሆነ መልክ መገንባት።   እነዚህ  ናቸው  የአፄ ምኒልክ  መሰረተ-ሃሳቦችና መመሪያዎች።

ለማንኛውም ዛሬ አገራችንና ህዝባችን ከተደቀኑበት አደጋ ስንነሳ የአደዋን የ127ኛው ዓመትን ድል በዓል እንደገና ስናከብር በተደበላለቀ ስሜትና ግራ በመጋባት መንፈስ ነው። ይሁንና ግን የዛሬው የጨለማ ሁኔታ እንደሚያልፍ አንዳችም ጥርጣሬ እንዲኖረን አይገባም። ዛሬ ያቧረቁና በአጉል ብልጣብልጥነት ደስታን የተጎናጸፉ የሚመስላቸው ሰዎች ኃይለኛ ነፋስ እንደሚወስደው ነገር ይበናሉ። መሳቂያና መሳለቂያ ይሆናሉ። ድርጊታቸው ሁሉ ከዕውቀት ማነስ የመነጨ በመሆኑ የመጨረሻ ኑሯቸው ሀዝንና መጨማደድ ይሆናል። በታሪክ ውስጥ ስፊ ህዝብን አሰቃይቶና በህዝብ አላግጦ ሳይዋረድ ከስልጣኑ የተወገደ የለም። በፖለቲካ ዓለም ውስጥ ቂም-በቀልነት ቦታ ባይኖረውም እነ ወያኔና አቢይ የውጭ ተላላኪዎች በመሆን የአገራችንን ታሪክ ማርከሳቸውና ህዝባችንን ማዋረዳቸው ከተጠያቂነት የሚያስመልጣቸው መሆን የለበትም። በህግ ፊት የሚጠየቁበት ቀን መምጣቱ አይቀርም። ለዚህ ሁሉ መፍትሄው ጠንካራና በጠላቶቿ የማትገበርና ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ለማስተናገድ የምትችል ዲሞክራሲያዊ አገር መገንባት ነው። ከጎሳና ከሃይማኖት ባሻገር አብዛኛዎቻችን ኢትዮጵያችን እንድትፈረካክስ አንፈልግም። ከብዙ ዓመታት የማያቋርጥ ጦርነትም ህዝባችን መላቀቅና እፎይ ብሎ መኖርን ይፈልጋል። አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ፍላጎቱና ምኞች አንድ ነው። በሰላም መኖር፣ ቤተሰብ መመስረት፣ ልጆች ወልዶና አስተምሮ ደስታን መጎናጸፍ፣ የስራ ዕድል በማግኘት ራሱን ችሎ መኖር ነው። ማንኛችንም፣ ከዚኽኛው ወይም ከዚያኛው ጎሳ ብንመጣምና በሃይማኖት ብንለያይም እንደሰው ለመኖር ከፈለግን ላይ ከተዘረዘሩት ሃቆች ልናመልጥ አንችልም። ይህም ማለት፣ መብላትና መጠጣት አለብን፤ መኖርም አለብን። ለመብላትና ንጹህ ውሃ ለማግኘት ደግሞ የግዴታ መስራት አለብን። የስራ-መስኮችም መከፈት አለባቸው። ለዚሁ ሁሉ ቁልፉ ደግሞ ሰላም ማግኘትና በሰለጠነ መልክ አገርን ማስተዳደር ነው። ለዚህ ደግሞ የሰለጠነ አገዛዝና መንግስታዊ መዋቅር ያስፈልጋል። የሰለጠኑ ሰዎች ስልጣንን ሲቀዳጁ ብቻ ነው አገርን በሰለጠነ መልክ ማስተዳደርና ጠንካራ አገር መገንባት የሚቻለው። በዚህ መንፈስ ብቻ ነው አገራችንን መገንባትና ለተከታታዩ ትውልድ ማስተላለፍ የምንችለው።  መልካም ግንዛቤ!!

 

fekadubekele@gmx.de

www.fekadubekele.com

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share