February 17, 2007
35 mins read

ከታሪክ ማህደር: የሥነ – ጽሑፍ መምሕር፣ ገጣሚ እና የተውኔት ጠቢቡ አንጋፋው ደራሲ ዳኛቸው ወርቁ

ህዳር 22 ቀን 1987 ዓ.ም

የሥነ – ጽሑፍ መምሕር፣ ገጣሚ እና የተውኔት ጠቢቡ አንጋፋው ደራሲ ዳኛቸው ወርቁ በተወለደ በ 59 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩበት ዕለት ነበር።

317364318 688043632954360 8056035879933616026 n 2➳ ስለደራሲ ዳኛቸው ወርቁ ህይወትና ሥራዎች

ዳኛቸው ልክ እነደ አባቱ ተራማጅ የሚባል ሰው ነበር። የዳኛቸው አባት አቶ ወርቁ በዛብህ ገና በወጣትነት እድሜው በድሬደዋ በኩል በባቡር ወደ ጅቡቲ ተጉዞ፣ ከዛም ወደ አውሮፓ ተሻግሮ ፈረንሳይ ገብቶ፣ በአንደኛው የዓለም ጦርነት የፈረንሳይ ወታደር ሆኖ የተዋጋ! በውጊያውም የቆሰለ፣ከዚያም በማዕድን ቁፋሮና በሆቴል መስተንግዶ ኑሮውን የገፋ ሰው ነበር። አቶ ወርቁ ከስደት ኑሮ ሲመለስ ትዳር መስርቶ ጎጆ ቀልሶ መኖር ጀመረ። ልጆችም ተወለዱ። ከተወለዱት ልጆች መካከል ደግሞ አንዱ አወዛጋቢው ደራሲ ዳኛቸው ወርቁ ነበር።

የዳኛቸው እናት ልጇን የተገላገለችው አገር በጣሊያን ወረራ ምጥ ተይዛ በምትሰቃይበት ዘመን ነበር። የካቲት 16/1928 ዓ.ም

ከደብረሲና ወጣ ብላ በምትገኝ አንዲት ገጠር ውስጥ። በፈረንሳይ አገር የኖረው የዳኛቸው አባት ለትምህርት የነበረው ቦታና ግንዛቤ ላቅ ያለ ስለነበር ቤተሰቡን ይዞ ወደ ደብረሲና አቀና። በዛም ዳኛቸው የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን እስከ ስድስተኛ ክፍል ተከታተለ። 7ኛ እና 8ኛ ክፍልን ደግሞ በቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ትምህርት ቤት በአዲስ አበባ ተምሮ ሊሴ ገ/ማርያም ት/ቤት ገባ። ሊሴ ግን ለዳኛቸው ባህሪ የሚመች ዓይነት ት/ት ቤት ሆኖ ስላላገኘው ትምህርቱን አቋርጦ ወደ ደብረሲና ተመለሰ።

ዳኛቸው በልጅነቱ የአባቱን ባህሪ እያጠና፣ የእናቱን ተረቶች እያዳመጠና እያብሰለሰለ ነበር ያደገው። ወደ ደብረ ሲና ከተመለሰ በኋላ ግን ከአባቱ ጋር ሊጣጣሙ አልቻሉም። “ከጓደኞቼ ጋር እንደልብ ጊዜ እንዳላኣሳልፍ ጫና ታደርግብኛለህ” ብሎ ወደ ደብረ ብርሃን ኮበለለ። ድብረ ብርሃንም ብዙ አልቆየም ትምህርቱን ለመቀጠል ወደ አዲስ አበባ ተመልሶ ኮተቤ መምህራን ኮሌጅ ገባ። በኮተቤ መምህራን ኮሌጅ በትምህርት ላይ እንዳለ ዳኛቸው ከባድ የጉሮሮ ህመም አጋጠመው። ለህይወቱ ያሰጋ የጉሮሮ ህመም! ይድናል ብሎ የጠበቀም አልነበረም! ዳኛቸው ግን ለመለዓከ ሞት እጁን ሳይሰጥ ቀረ። ዳነና ከተኛበት ዳግማዊ ምንሊክ ሆስፒታል ወጣ። ይህ አጋጣሚ ለዳኛቸው ቤተሰቦች የልጃቸው ዳግም ልደት ነበር።

317775033 688043756287681 7678679821175211489 n 2ዳኛቸው ከጉሮሮ ህመሙ ሲያገግም ኮከበ-ጽባህ መምህርነት ገባ ። ሁለት ዓመት በኮከበ-ጽባህ አስተምሮ ሀረር ዘለቀ። በሀረር መድኃኔዓለም ት/ት ቤት እያስተማረ “ሰቀቀንሽ እሳት” የሚል ትያትር ጽፎ ለመድረክ አበቃ። በተገኘችው ገንዘብ ደግሞ በድብረ ብርሃን ከጓደኞቹ ጋር ያሳለፈውን ህይወት የምትተርከው “ሰው አለ ብዬ!” መጽሀፉ ታተመች። በሀረር እያለ ዳኛቸው በጋዜጦች ላይ ጽሁፎቹን ያስነብብ ነበር። የሚያስነብባቸው ጽሁፎች ያነበባቸው መጻህፍት ላይ ያለውን ምልከታ የሚዳስሱ ነበሩ።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለመጀመሪያ ጊዜ በአማርኛ ቋንቋና ስነ-ጽሁፍ ለማስተማር ሲወስን ዳኛቸው ከሀረር ገስግሶ ስድስት ኪሎ ደረሰ። ከመጀመሪያዎቹ የቋንቋና ስነ-ጽሁፍ ትምህርት ክፍል ተማሪዎችም አንዱ ለመሆን በቃ። ለሁለተኛ ዲግሪ ትምህርቱ ደግሞ ወደ ውጭ አገር አቀና። ዳኛቸው ከ Iowa state university በ ስነጥበባት (fine arts) የሁለተኛ ዲግሪውን ያገኘ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ሲሆን ይኅው ዩኒቨርሲቲ ለዳኛቸው ወርቁ ከዓመታት ብኋላ Honorary fellow of the International writers workshop Association of Iowa University ክብርን ሸልሞታል።

ዳኛቸው የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርቱን አጠናቆ ሲመለስ ነበር አነጋጋሪ የሆነው መጽሀፉ “አደፍርስ” የተወለደው።

አደፍርስ በወቅቱ ከተለመደው የአማርኛ ስነ-ጽሁፍ ያፈነገጠ መጽሀፍ ነበር። ታትሞ ገበያ ላይ በአምስት ብር ዋጋ ቢቀርብም፣ ሰው አደፍርስን ገዝቶ ሊያነብ አልቻለም። ዳኛቸው አከፋፋዩ ጋር ሄደና ጠየቀ …. እንዴት ነው?

“አንባቢው ዋጋው ተወደደብኝ” አለ። ሲል መለሰ አከፋፋዪ።

“አሉ? እንግዲያው ከአሁን ጀምሮ መጽሀፉ ላይ የዋጋ ማስተካከያ አድርጊያለሁ። ካሁን በኋላ የመጽሀፉ ዋጋ 10ብር ነው።” አከፋፋዩ የሚሰማውን ማመን አቃተው። “በአምስት ብር አልሸጥ ያለ መጽሀፍ ጭራሽ አስር ብር?!” ዳኛቸው ጥሎት ወጣ።

በሌላ ጊዜ ተመለሰና እንደገና ጠየቀ። “ኸረ! በጭራሽ እየተሸጠ አይደለም” አለ አከፋፋዩ። “እንግዲያው መጽሀፉ ዋጋው 15ብር ገብቷል” አለ ዳኛቸው። 5ብር አልሸጥ ያለውን መጽሀፍ 15ብር አስገብቶት አረፈው። አከፋፋዩ ግን ፈጽሞ 15ብር አይገባውም ብሎ ተከራከረ። “እንደውም ተወው የኢትዮጵያ ህዝብ የኔን መጽሀፍ አንብቦ ለመረዳት 20 ዓመት ይፈጅበታል”….ብሎ መጽሀፍቱን እንዳለ ለቃቅሞ ቤቱ ወሰዳቸው።

አደፍርስን ቤቱ ድረስ ሄደው በ15ብር የገዙት ሰዎች ግን ነበሩ። ከነዚህ መካከል ደራሲ ሳህለ-ሥላሴ ብርሃነ ማርያም አንዱ ናቸው። በሌላ በኩል በአደፍርስ መጽሀፍ ዙሪያ የሚስተናገዱት ሂሶች ጉራማይሌ ነበሩ። አንዳንዱ አደፍርስ ድንቅ ልቦለድ ነው ብሎ ሲያዳንቅ። ሌላው ደግሞ አደፍርስ የአማርኛን ስነ-ጽሁፍ ያደፈረሰ፣ቅጣንባሩ የጠፋ፣ ቲርኪ ሚርኪ ጽሁፍ ነው ሲል አጣጣለ። እንደነ አቤ ጉበኛ ያሉት ጭራሽ አደፍርስን በአሽሙር የሚነካ መጽሀፍ እስከማሳተም ደረሱ። “ጎብላንድ አጭበርባሪው ጦጣ” የተሰኘው የአቤ ጉበኛ መጽሀፍ በቀጥታ አደፍርስን ለማንቋሸሽ ታስቦበት የተጻፈ መጽሀፍ ነበር።

➠ ለክብሩ የሚጨነቀው ዳኛቸው

በአንድ ወቅት ዳኛቸው ወርቁ ከዶ/ር አምሳሉ አክሊሉ ጋር በጋራ ሆነው አንድ “የአማርኛ ፈሊጣዊ አነጋገሮች ” የሚል መጽሀፍ አዘጋጁ። መጽሀፉን ያሳትም የነበረው ኩራዝ አሳታሚ ድርጅት የመጽሀፉ ረቂቅ ሲጠናቀቅ አንድ ነገር ጥያቄ ሆነበት። ከሁለቱ ደራሲያን የማናቸው ስም ነው ከላይ መስፈር ያለበት? ለዚህ ጥያቄ አንድ መፍትሄ ተገኘ፣ በአመርኛ ፊደል ቅደም ተከተል መሰረት የሚቀድመውን በስማቸው የመጀመሪያ ፊደል ለይቶ ማስቀመጥ። ይኼ አካሄድ ውጭ አገርም የሚሰራበት ነው። በዚህ መሰረት የዶ/ር አምሳሉ ስም ስለቀደመ ስማቸው ከላይ ሰፈረ፣ የዳኛቸው ደግሞ ከታች። ዳኛቸው መጽሀፉን ባየ ጊዜ ተናደደ። “ከፊል የሆነውን ስራ የሰራሁት እኔ፣ በየትኛው መስፈርት ስፍራችሁ ከብዶ ቢታያችሁ ነው፣ ስሙን ከስሜ በላይ የሰቀላችሁት?” አለ። መስፈሪያውን ነገሩት፣ አልተቀበላቸውም። የሆነው ሆኖ መጽሀፉ ተሰራጭቶና ተሸጦ አለቀ።

ለሁለተኛ ኅትመትም ታሰበ፤ ግና የጋሽ ዳኛቸው አለቅጥ መናደድ ያሳሰባቸው አንዳንድ የድርጅቱ አርታኢያን፤ ቀጥለን ደግሞ በተራው የአምሳሉን ስም ዝቅ እናድርገው ሳይሉ፣ የሁለቱን ስም በመጀመርያ ረድፍ ላይ አሰፈሯቸው፤ ትይዩ! እናም መጽሐፉ ወጣ፡፡

የጋሽ ዳኛቸው ፊት እና ልብ ግን አልተፈታም፤ ከድርጅቱ ሠራተኞች አንዱ የሆኑት ጋሽ አስፋው ዳምጤ አገኙት፤ “መጽሐፉ በጣም እየተሸጠ ነው፤ አንተ ግን ብንጠብቅህም አትመጣም፤ ብርህን ፈርመህ ውሰድ እንጂ!” አሉት፡፡

“ሁለተኛ ደጃችሁ አልደርስም!”

“ ምነው?”

“ያደረጋችሁትንማ ታውቁታላችሁ…”

“ብዙ ሺህ ብር’ኮ ነው ያለህ!”

“እንዴትም ቢሆን ግድ የለኝም፤ ነፍሴ ተቀይማችኋለች”

“ከዚህ በፊት ያሣተምንልህ ‘የጽሑፍ ጥበብ መምሪያ’ ም ብዙ ሺህ ቅጂ ነበር የታተመው፤ አሁን አልቋል፤ መጥተህ ገንዘብህን መውሰድ ብቻ …”

“አልፈልግም አልኩህኮ!”

“ያ መጽሐፍ ሌላ፤ ይኼ ሌላ፤ በዚህኛው መቼ ተጣላን?”

“እናንተጋ የሚያደርሰኝ ጉዳይ እንዲኖር አልፈልግም”

“ኧረ ባክህ …”

“በጭራሽ፤ ወስኛለሁ!”

“የለፋህበትና እንቅልፍ ያጣህበት ነገር አይደል?”

“ከዚህ በላይ በዚህ ጉዳይ ላይ መወያየት የለብንም!”

ዝምታ ሆነ፤ ድርጅቱን ወክሎ መልዕክት እያደረሰ ያለው ሰው ያልተለመደ ነገር ገጥሞታል – እዚህ፡፡

‘ተዉት! ቁጣው ሲቀዘቅዝና ኩርፊያው ሲገፈፍ ይመጣ ይሆናል’ ተባለ፡፡

ሳይሆን ቀረ፤ ጋሽ ዳኛቸው ወርቁ እግሩንም ልቡንም ከደጃቸው አራቀ – በአቋሙ ፀና፡፡ … ሞተ …

የድርጅቱ ሠራተኞች ወደ ሀዘንተኞቹ ቤት ገቡ፤ ልጆቹን አገኙ፤ ‘የአባታችሁ ገንዘብ እኛ ዘንድ አላችሁ …’ አሏቸው፤ ሕጋዊ ወራሽ ናቸውና መረጃቸውን ይዘው ሄዱ፤ ከድርጅቱ ቢሮ የወጡት በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ብሮችን ይዘው ነበር፡፡እንዲህ ነበር ዳኛቸው ወርቁ.

➠ የዳኛቸውና ስብሃት ገ/እግዚአብሔር ወዳጅነት..

አንድ ቀን አንድ ነገር ተፈጠረ፡፡ በወቅቱ የነበሩ ምሑራን አንድ የውይይት መድረክ ዘረጉ፤ ከንግግር ወይም ከጽሑፍ አቅራቢዎች መካከል አንዱ የሆነው ጋሽ መንግሥቱ ለማ ግን ውይይቱ አንድ ቀን ሲቀረው በጉባኤው እንደማይገኝ አስታወቀ፤ ታዳሚው ተነግሮታል፤ አንድ ተሟጋች ብዕረኛ ግን ጐድሏል፣ የፕሮግራሙ አስተባባሪ የሆነው ጋሽ ሰሎሞን ደሬሳ ተናደደ፤ ‘ይኼ ሰውዬ አጉል አደረገን፤ ልፋታችንን አንካሣ አደረገው’ አለ፡፡ የሚያደርጉት ግራ የገባቸው እነዚህ የዝግጅቱ ኃላፊዎች ክፍተቱን እንዴት መድፈን እንደሚቻል እያሰላሰሉ ሳለ፣ ‘ለምን እኔ እሱን ተክቼ አልገባም፤ ጉዳዩ አይመጥነኝም ወይ?’ አለ ጋሽ ስብሃት፡፡

የጋሽ ሰለሞን ፊት በራ፤ ፈካ፤ ፕሮግራሙ ሄደ፤ በኋላ ጋሽ ስብሃት በጨወታ መሃል፣ ‘በነገራችን ላይ፣ በቅርቡ የሚገርም ልቦለድ አንብቤያለሁ፤ ‘አደፍርስ’ የሚባል! የመጽሐፉ ደራሲ የሆንከው ሰው በአካል አላውቅህም፤ እዚህ ካለህ እንኳን ደስ አለህ፤ ተሣክቶልሃል፤ ከሌለህም የምታውቁት ሰዎች አድናቆቴን አድርሱልኝ፤ አማርኛ ስሜትን የመግለጽ አቅም የሌለው ይመስለኝ ነበር፤ ልክ እንዳልሆንኩ ዳኛቸው ወርቁ አሣይቶኛል፤ ብራቮ!’ አለ – አጨበጨበለት፡፡

አንድ ቀን፣ ግንባሩ የማይፈታና ፊቱ ጠቃጠቆ የወረሰው ሰው ጋሽ ስብሃት ፊት ቀረበ – ‘ዳኛቸው ነኝ!’ አለው፤ ተዋወቁ፤ ‘ስላንተ አንድ መድረክ ላይ እንዲህ ብዬ ነበር፤ መልዕክቱ ደርሶሃል?’ አለው፡፡ ዳኛቸውም፣ ‘እኔ በዝግጅቱ ታዳሚ ነበርኩ! ሰምቼሃለሁ፤ አመሰግናለሁ!’ አለው፡፡ ወዳጅነት ተፀነሰ፡፡

ከብዙ ጊዜያት በኋላ ጋሽ ስብሃት ከሥራ ተሰናበተና ዳኛቸው ቢሮ ሄደ፡፡ ‘የምትችል ከሆነ፣ አሁን ሥራ ስለሌለኝና ያለ ሥራ ቤተሰቤን ማስተዳደር ስለማልችል፣ ደሞዝ የምበላበት አጋጣሚ እስኪፈጠር ድረስ፣ የልደታ ቀን እየመጣሁ ካንተ ብር ልበደር፣ የምትችል ከሆነ!’ አለው፡፡

“በየወሩ ስንት ትፈልጋለህ?” የሚል ጥያቄ አስከተለ – ጋሽ ዳኛቸው፡፡

“አምሳ ብር በቂዬ ናት”

“በቂህ ናት?”

“ናት!”

ለአስራ አንድ ወራት ጋሽ ስብሃት እየተመላለሰ የተበጀለትን ብር መውሰድ ቀጠለ፤ ከዚያ ሥራ አገኘ፤ ከመጀመሪያው የደመወዝ ቀን ከተቀበለው ብር የተወሰነውን ይዞ ጋሽ ዳኛቸው ፊት መጣ፡፡

“ምንድነው?”

“የተበደርኩት፤ ይኸው፤ ከዕዳዬ ይቀነስልኝ!”

“ምን ማለትህ ነው?” አለው ጋሽ ዳኛቸው፣ ላለመቀበል እያንገራገረ፡፡

“አንተ እንጂ ምን ማለትህ ነው?”

“ጓደኞች አይደለንም እንዴ? ከወዳጅ የሚጠበቀውን ነው ያደረግሁልህ፤ ልክፈልህ ስትለኝ ትንሽ እንኳን አታፍርም? ይኼ ድፍረት ነው፤ ኪስህ ውስጥ ክተተውና ይዘህ ሂድ” …ተቆጣ፡፡

“ይኸውልህ” ብሎ ጀመረ – ጋሽ ስብሃት ተረጋግቶ፤ “ይህንን ካልተቀበልከኝና ዕዳዬን ስከፍል ካላስተናገድከኝ እኔ ደግሞ አንድ ነገር አደርጋለሁ፤ ሁለተኛ ምንም ቢቸግረኝ አንተጋ አልመጣም፡፡ ነጻ ሆኜ የሆዴን እንዳጫውትህ ከፈለግህ የምሰጥህን ተቀበል፤ አለበለዚያ በቸገረኝ ጊዜ አልመጣብህም፡፡ እንዴት ብድር ብዬ የወሰድኩብህን ስከፍልህ ወዲያ በል ትለኛለህ? ለመክፈል በመብቃቴ ደስታ ሊሰማህ ሲገባ”

ጋሽ ዳኛቸው አሁን ፊቱ ተፈታ፡፡ ‘እንግዲያውስ እንተጋገዝ፤ የተወሰነውን ልሰርዝልህ?”

“ባይሆን እንደሱ ይሻላል” ተያይዘው ወጡ፤ በብሩም ተገባበዙበት፡፡

አንድ ቀን ጋሽ ስብሃት ሹራቡን አውልቆ፣ አናቱ ላይ ጠምጥሞና በጠራራ ጸሐይ ፌስታሉን ይዞ ሲሄድ ከጋሽ ዳኛቸው ጋር ተገናኙ፤ ሰላምታ ከተለዋወጡ በኋላ፣ ‘ምን ሆነህ ነው እንዲህ የሆንከው?’ ብሎ ተቆጣ – ጋሽ ዳኛቸው – የጋሽ ስብሃትን ያልተበጠረ ጸጉር፣ የጎፈረ ጺምና ግዴለሽነት የበዛው አለባበስ አይቶ፡፡

“ምን የሆንኩት?” አለ ጋሽ ስብሃት፡፡

“ለምንድነው እራስህን እንዲህ የምትጥለው? ጠላቶችህ ይህንን ሲያዩ ደስ የማይላቸው ይመስልሃል?”

“አይ ዳኛቸው፣ እኔ ምን ጠላት አለኝና?” አለ ፈገግ ብሎ፡፡

“ምን ጠላት አለኝና? ባይኖርህስ እራስን መጠበቅ ማንን ገደለ?” ብሎ ግሳጼውን ቀጠለ፡፡

አንድ ቀን ደግሞ – በሰባዎቹ መጀመሪያ – ተያይዘው ወደ ሶደሬ ሄዱ፡፡ “አንድ የጀመርኳት ረጅም ልቦለድ አለች፤ ለማንም እንዳትናገር! ሃሳቧን ሰርቀው አልከስክሰው ሊሰሩብኝ ይችላሉ፤ ለማንም እንደማትናገር ቃል ከገባህልኝ የመጀመሪያዎቹን ምዕራፎች አነብልሃለሁ” አለው፤ አነበበለት፤ አጀማመሩ ድንቅ ነበር፤ አካሄዱንም ተረከለት፤ “ይህችማ አደፍርስን የምታስረሳ ናት” አለው፤ ዳኛቸው ሞራል ተሰማው፡፡

ሌላ ቀን ተገናኙ፡፡ “ምነው ቀጣይ ምዕራፎችን ለማስነበብ ችላ አልከኝሳ?” አለው፡፡ መልስ አልሰጠውም፡፡ “አጠናቀህ ልትሰጠኝ ነው? ወይስ እርግፍ አድርገህ ትተኸዋል?” አለው ጋሽ ስብሃት፡፡

“ምን ነካህ፤ አብደሃል እንዴ? እንዴት በዚህ ጊዜ እንዲህ ያለ ጥያቄ ትጠይቀኛለህ?”

“ምነው?”

“በገባሁ በወጣሁ ቁጥር የሀገሬ ወጣቶች ሲረፈረፉ፣ ደማቸው በየመንገዱና በየቦዩ ሲጎርፍ እያየሁ ተረጋግቼና ተመስጬ ልቦለድ የምጽፍ ይመስልሃል?” አለው፤ ክምር እሬሣና የደም ጎርፍ እፊቱ የመጣበት ይመስል ዕንባ አቀርዝዞ፡፡

“ይልቁንስ አንተ ምንም ሣይመስልህ ስትጽፍ ይገርመኛል” አለ ጋሽ ዳኛቸው፡፡

“እኔማ በአል ቶሎ ቶሎ ስለሚመጣብኝ ነው፤ ጽሑፍ መተዳደሪያዬ እንደሆነ አታውቅም?”

“ይገርመኛል” ይላል ጋሽ ስብሃት፡፡ “ዳኛቸው ለብዙዎች እሾህ ነበር፤ እሾህ መልኩን እሾህ ገጹን ነው የሚያሳያቸው፤ ወይም ያሳየናል የሚሉት፤ ለእኔ ግን ጽጌረዳ ውበቱን ጽጌረዳ መልኩን ነው ያሳየኝ፤ ተመቻችተን ነበር – ልብ ለልብ ተግባብተን፤ ነፍስ ለነፍስ ተዋድደን፡፡”

➠ የዳኛቸው አሳዛኝ መጨረሻ

ሞገደኛ ደራሲ እንደነበር የሚነገርለት ዳኛቸው ወርቁ በተለይም በህይወቱ የመጨረሻ ዓመታት ደስታ ርቆት በድንገት ህዳር 22 ቀን 1987 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል። በወቅቱ የሞቱ ዜና ለአድናቂዎቹ አስደንጋጭ ነበር።

➠ የሣህለሥላሴ ብርሃነማርያም ማስታወሻ

ኅዳር 22 ቀን 1987 ዓ.ም ምሽት ላይ፣ ሁለት ደራስያን በተለያየ ሰዓት ሣህለ ሥላሴ ብርሃነ ማርያም ቤት ሥልክ ደወሉ፤ ከዚያም ጋሽ ዳኛቸው ከዚህ ዓለም የመለየቱን ዜና አረዷቸው፡፡ በማግሥቱ ከ11 እስከ 12 ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ አስከሬኑ እንደሚሸኝና የቀብር ቦታውም ደብረሲና መሆኑን ነገሯቸው፡፡ ይህ በሆነ በማግሥቱ የሆነውን ነገር እንዲህ ይገልጹታል፡፡

‘ከሌሊቱ በ 11 ሰዓት ተነስቼ ምኒልክ ግቢ አጠገብ ወደሚገኘው ቤቱ አመራሁ፤ እዚያ ስደርስ አምስት የሚሆኑ የግል አውቶሞቢሎችና ጥቂት ሰዎች፣ ከሰላሣ የማይበልጡ (አብዛኞቹ የሰፈር ሴቶች መሰሉኝ) በአካባቢው ቆመው አየሁ፡፡ ሌሎች አሥር የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ ከዚያው አጠገብ ከቆመው መለስተኛ አውቶቡስ ውስጥ ገብተው ተቀምጠዋል፡፡

የአስከሬኑ ሣጥን በአውቶቡሱ ጣሪያ ላይ በሸራ ተሸፍኖ ታስሯል፡፡ በአካባቢው አንድ ሰው ብቻ ሲነፋረቅና ዕንባውን ሲጠርግ ተመለከትሁ፤ ግራና ቀኝ ፊትና ኋላ ብመለከት አንድም የማውቀው ሰው የለም፤ ትላንትና ደውለው ያረዱኝ ወዳጆቼ በዚያ የሉም፤ እጅግ በጣም ተገረምኩ፤ አዘንኩምም፡፡

‘አደፍርስ’ንና ‘ዘተርቲን ሰን’ን የሚያህሉ ድርሰቶች ያቀረበልን የብዕር ሰው አስከሬኑ የሚሸኘው በዚህ ሁኔታ ነው ወይ? ወይንስ ዳኛቸው ወርቁ እራሱን አግልሎ ስለሚኖር ወዳጅ ዘመዶቹ የሥራ ባልደረቦቹና ደራስያኑ ጭምር ዜና እረፍቱን በጊዜ ሳይሰሙ ቀሩ ስል አሰብኩ፡፡

የሆነው ሆኖ ከንጋቱ አሥራ ሁለት ሰዓት ገደማ ሲሆን አስከሬኑን የጫነው መለስተኛ አውቶቡስ ወደ ደብረሲና ለመጓዝ መንቀሳቀስ ሲጀምር በሃሳቤ፤ ነፍስህን ይማረው፤ የዘላለም እረፍት አግኝ ብዬ ተሰናብቼው ወደ ቤቴ አቅጣጫ አመራሁ’

➠ የደራሲ ዳኛቸው ወርቁ ሥራዎቹ

ዳኛቸው ወርቁ ሲነሳ ሁለት ሥራዎቹ በጉልህ ይነሳሉ። አንድ የአማርኛና አንድ በእንግሊዘኛ ቋንቋ የጻፈው ልቦለድ። የአማርኛው አወዛጋቢው መጽሀፍ “አደፍርስ” ሲሆን የእንግሊዘኛው ደግሞ “the thirteenth sun” ይሰኛል። ይህ የእንግሊዘናው መጽሀፍ እንግሊዝ አገር ነበር የታተመው።ከእንግሊዘኛ ቋንቋ በተጨማሪ በሌሎች የውጪ ቋንቋዎች ተተርጉሞ የታተመ ሲሆን መጽሀፉ በጭብጡ ከአደፍርስ ጋር ብዙም የሚራራቅ እንዳልሆነ ደራሲ ሣህለ-ሥላሴ ብርሃነ ማርያም በአንድ ወቅት በጻፉት ጽሁፍ ገልጸዋል። እንዲህ ይላሉ ሣህለ -ሥላሴ ስለመጽሀፉ…

“የዳኛቸው ወርቁ ሌላው ዐቢይ ሥራ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ደርሶት እንግሊዝ አገር የታተመውና “The Thirteenth Sun” የተሰኘው መጽሐፍ በብዙ የአውሮጳውያን ቋንቋዎች ተተርጉሞ እንደታተመም ዳኛቸው ራሱ አጫውቶኛል። መሠረተ ሀሳቡ ከ“አደፍርስ” ጭብጥ እጅግም የራቀ አይደለም።

በጥንታዊት ኢትዮጵያ አስተሳሰብና በዛሬይቱ ኢትዮጵያ አስተሳሰብ (በቀድሞው ትውልድ እምነትና በዛሬው ትውልድ አመለካከት) መሀከል ባለው ግጭት ላይ የተገነባ ልብወለድ ነው። በእኔ አስተያየት በትረካው ረገድ “The Thirteenth Sun” ከ“አደፍርስ” ላቅ ያለ ሲሆን በቋንቋው ውበት ግን አደፍርስ ይበልጣል።”

ዳኛቸው ገና በልጅነቱ ነበር የድርሰት መክሊት ባለቤት መሆኑን ያስመሰከረው። ገና በ 13 ዓመት እድሜው በደብረ ሲና የአንደኛ ደረጃ ተማሪ ሳለ “ያላቻ ጋብቻ ፣ ትርፉ ኀዘን ብቻ” የተሰኘ ትያትር ደርሶ ለመድረክ አብቅቶ ነበር። ኮተቤ የመምህርነት ኮርስ ወስዶ በመምህርነት ሥራ ከተሰማራ በኋላም “ሰቀቀንሽ እሳት” የተሰኘ እና “ሰው አለ ብዬ ” የተሰኙ የተውኔት ስራዎችን የደረሰ ሲሆን፣ “ሰው አለ ብዬ” የተሰኘች ድርሰቱ የህትመት ብርሃን ለማየት በቅታለች።

ዳኛቸው በ 1953 ዓ.ም በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፍ ትምህርቱን እየተከታተለ የአራተኛ ዓመት ተማሪ ሳለ በረዳት መምሕርነት ጭምር በዩኒቨርሲቲው ያገለገለ ሲሆን፣ ተመርቆ እስከወጣበት ጊዜ ድረስ በወቅቱ የተማሪው የለውጥ እንቅስቃሴ ውስጥ በመሳተፍ ከዘመነኞቹ የኮሌጁ ገጣሚዎች ከነታምሩ ፈይሳ፣ ዮሐንስ አድማሱ፣ አበበ ወርቄ፥ ይልማ ከበደ፣ ኢብሳ ጉተማ፣ ኃይሉ ገብረዮሐንስ(ገሞራው)፣ መስፍን ሀብተማርያም፣ … ጋር እንደ «ወጣቱ ፈላስማ» በመሳሰሉ ግጥሞቹ የለውጥ ሐሳቡን ያስተጋባ ገጣሚም ነበረ።

ዳኛቸው በአሜሪካ ኦሃዮ ዩኒቨርሲቲ ሳለ አጫጭር ልቦለዶችን ደርሶ ማሳተም የቻለ ሰው ነበር። በአገር ቤትም ቢሆን “ትበልጭ” የተሰኘ ተውኔቱ በታላቁ የቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ትያትር ቤት ለመድረክ በቅቶለታል። ከውጪ ከተመለሰ በኋላ በቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ በቋንቋ መምህርነት ሲያገለግል ከነጌታቸው ኃይሌ፣ አብርሃም ደመወዝ፣ ዮሐንስ አድማሱ፣ ኃይሉ ፉላስ … ጋር በመሆን ‹‹የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፍ ክፍል››ን ያደራጀ፣ ወጣት የሥነ ጽሑፍ ባለሙያዎችን በማደራጀት አስተዋጽዖ ያደረገ … ምሁር ነበር፡፡

ከዚህ በተጨማሪም፣ በወቅቱ ይታተሙ በነበሩት ‹‹የዛሬይቱ ኢትዮጵያ››፣ ‹‹የኢትዮጵያ ድምጽ›› እና ‹‹አዲስ ዘመን›› ጋዜጦችም የኢትዮጵያን ሥነ ጽሑፍ የተመለከቱ ስራዎችን በማቅረብና የወጣት ደራሲያንን ሥራዎችን በመሔስ ለሀገሪቱ ሥነ-ጽሑፍ ዕድገት ምሁራዊ ኃላፊነቱንና ተልዕኮውን ተወጥቱዋል፡፡

«አደፍርስ» የተሰኘው ልብ ወለዱ ከዩኒቨርሲቲው የሥራ ባልደረቦችና የአስተዳደር አካላት ጋር የነበረውን ግንኙነት ያደፈረሰበት ዳኛቸው፣ ዩኒቨርሲቲውን ለቆ በጥቁር አንበሳ ሁለተኛ ደረጃ ትምሕርት ቤት እንዲሁም በፈረንሳይ ኮሌጅ እስከ 1966 ዓ.ም. የአማርኛ ቋንቋና ሥነ ጽሑፍ አስተምሯል። ኋላም «በኢትዮጵያ ደረጃዎች መዳቢ ድርጅት» በትርጉም አዋቂነት፣ በሕዝብ ግንኙነት ኃላፊነትና በኢንዱስትሪ ፕሮጀክት አገልግሎት ሹምነት ለ 15 ዓመታት አገልግሎ፣ በ 1983 ዓ.ም. ጡረታ ወጣ።

ዳኛቸው የዛሬዎቹን ወጣት ኢትዮጵያውያን በጥበቡ ዘርፍ የሚታደጉ “የሥነ ጽሑፍ ጥበብ መመሪያ” እና “የአማርኛ ፈሊጦች” መጽሐፍትን ያሳተመ፣ ለሀገሪቱ ቋንቋ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያላቸውን «የማርክሲዝም ሌኒንዝም መዝገበ ቃላት» እና «የሳይንስና ቴክኖሎጂ መዝገበ ቃላት» የመሳሰሉ ጥልቅና ምጡቅ ሥራዎች ዝግጅት ላይ በመሳተፍ ምሁራዊ ግዴታውን የተወጣ ሰው ነበር።

➳ ማጠቃለያ ከዳኛቸው ወርቁ ሥራዎች መካከል፡-

  1. አደፍርስ (ልብወለድ)
  2. እምቧ በሉ ሰዎች (ግጥምና ቅኔ)
  3. ሰቀቀንሽ እሳት (ተውኔት)
  4. ሰው አለ ብዬ (ተውኔት)
  5. ትበልጭ (ተውኔት)
  6. ያላቻ ጋብቻ ፥ትርፉ ሐዘን ብቻ (ተውኔት)
  7. ማሚቴ (ልብወለድ)
  8. The Thirteenth Sun
  9. የጽሑፍ ጥበብ መመሪያ (ምርምር)
  10. Shout lt from the Mountain Top (ያልታተመ – ልብ ወለድ) … ይጠቀሳሉ፡፡

#ታሪክን_ወደኋላ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

ከነፃነት ዘገዬ የአራት ኪሎው ኦነግ ሸኔ ከቁጥር ጋር እንደተጣላ ዕድሜውን አገባደደ፡፡ ኦነግ/ኦህዲድ ዛሬም ሆነ ዱሮ፣ በቤተ መንግሥትም ይሁን በጫካ ቁጥር ላይ ያለው አቋም ምን ጊዜም ያስደንቀኛል፡፡ ደግሞም እየባሰባቸው እንጂ ሲቀንሱ አይታዩም፡፡ ጥቂት

80 ቢሊዮን ብር ስንት ብር ነው?

በላይነህ አባተ ([email protected]) መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ምዕራባውያን የኢትዮጵያን ልጆች እያታለሉና እየደለሉ ከእምነታቸው ለመንጠቅ ሲቃጡ በ1951 ዓ ም ባሳተሙት ‘መድሎተ አሚን ወይም የሃማኖት ሚዛን ጥልቅ መጽሐፍ ሽፋን ላይ ሕዝብ ልቡናውን፣ ዓይኑን፣ ጀሮውንና

ሰው ሆይ!

“በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ።”  መዝሙረ ዳዊት 39:1 ወንድሙ መኰንን፣ ኢንግላንድ 15 January 2025 መግቢያ የአገር መሪ፣ በስሜታዊነት እንዳመጣለት አይዘረግፍም። እያንዳንዷ ንግግሩ እየተሰነጠቀች ትታይበታለች። ንግግሩ ቁጥብ መሆን

ከተዘራ ያልታረመ አንደበት የጠቅላይ ሚኒስትር አነጋጋሪ ንግግሮች

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

Go toTop