ምንም እንኳን ለተፈናቃዮች ዘላቂ መፍትሔ ማፈላለግን በተመለከተ መንግሥት ተቀዳሚ ኃላፊነት ያለበት ቢሆንም የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም የዘላቂ መፍትሔ ጥረቶች ስኬታማ እንዲሆኑ የማገዝ ኃላፊነት አለባቸው
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ/ኮሚሽኑ) ለሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ዘላቂ መፍትሔ ማፈላለግን አስመልክቶ ከፌዴራል እና ከክልል መንግሥታት ተቋማት፣ በኢትዮጵያ ከሚገኙ የተለያዩ ኤምባሲዎች፣ ከተባበሩት መንግሥታት ኤጀንሲዎች፣ ከዓለም አቀፍ የልማት ተቋማት እንዲሁም ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች ጋር በቅርቡ ውይይት ማድረጉ ይታወሳል። በዚህ የውይይት መድረክ የዕለቱ የክብር እንግዳ የነበሩት እና በወቅቱ ኢትዮጵያን ሊጎበኙ የመጡት የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጽሕፈት ቤት የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ዘላቂ መፍትሔ ልዩ አማካሪ ሮበርት ፓይፐር፤ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ዘላቂ መፍትሔ በማፈላለግ ዙሪያ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን አንስተው በዚህም ሂደት ትምህርት ሰጪ የሚሆኑ ተመክሮዎችን ለመሰነድ ከተመረጡት 16 ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ መሆኗን ገልጸዋል፡፡
ከ4.5 ሚሊዮን የሚበልጡ ተፈናቃዮችን ለምታስተናግድ ሀገር ይህ እንደመልካም እና ሊያመልጥ የማይገባ አጋጣሚ ሆኖ ሊወሰድ ይገባል። ምንም እንኳን ለተፈናቃዮች ዘላቂ መፍትሔ ማፈላለግን በተመለከተ መንግሥት ተቀዳሚ ኃላፊነት ያለበት ቢሆንም ልዩ አማካሪው በአጽንዖት እንደገለጹት የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም የዘላቂ መፍትሔ ጥረቶች ስኬታማ እንዲሆኑ የማገዝ ኃላፊነት አለባቸው። ኢትዮጵያ ከ15 ሀገራት ጋር ለተፈናቃዮች ዘላቂ መፍትሔ በማፈላለግ ዙሪያ ትምህርት ሰጪ የሚሆኑ ተመክሮዎችን ለመሰነድ ስትመረጥ ይህንኑ ለማሳካት በዘላቂ መፍትሔ ዙሪያ ለሚሠሩ የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ የሙያ እና የግብአት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ ተደርጓል። ይህንኑ ጥሪ መሠረት በማድረግ ድጋፍ ለማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው የገለጹ የልማት ተቋማት እና ድርጅቶች ያሉ ሲሆን፤ ይህንን ለመተግበር ግን በዋናነት የመንግሥትን ቁርጠኝነት ማየት እንደሚፈልጉ ገልጸዋል።
ዘላቂ መፍትሔን ማመቻቸት መንግሥት በባለቤትነት እና በከፍተኛ ቁርጠኝነት መተግበር ያለበት ትልቅ ኃላፊነት መሆኑን ኢሰመኮ ከዚህ በፊትም በአጽንዖት ሲገልጽ የቆየው ጉዳይ ነው። የዚህ ቁርጠኝነት አንደኛውና ዋነኛው መገለጫ በአንድ በኩል ለመፈናቀል መንስዔ ለሆኑ እና ለዘላቂ መፍትሔ መሰናክል ሆነው ለቆዩ በተለያዩ አካባቢዎች ለተከሰቱ ግጭቶች እልባት መስጠት ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ በመፈናቀል ወቅት የጥበቃና ድጋፍ ሥራዎችን የማሳለጥ እና ዘላቂ መፍትሔን የማመቻቸት ሥራዎችን በበላይነት የሚመራ እና የሚያስተባብር በሕግ ግልጽ ኃላፊነት እና ሥልጣን የተሰጠው ተቋም መሾም አስፈላጊ ነው። እንዲሁም ምንም እንኳን በርካቶች መፈናቀልን እንደ የሰብአዊነት ጉዳይ ብቻ አድርገው ቢገነዘቡትም መፈናቀል የሰብአዊ መብቶች፣ የልማት፣ የጸጥታ እና የደኅንነት ጉዳይ እንደመሆኑ ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔ ለማመቻቸት የበርካታ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ እና ርብርብ ያስፈልጋል።
ለተፈናቃዮች ዘላቂ መፍትሔ ማመቻቸት በቅድሚያ የመንግሥት ኃላፊነት ነው ሲባል እንደማንኛውም ዜጋ ተፈናቃዮች የሰብአዊ መብቶች ባለቤቶች በመሆናቸው መንግሥት ሰብአዊ መብቶቻቸውን የማስከበር፣ የመጠበቅ እና የማሟላት ግዴታ አለበት ማለት ነው። ይህም ማለት ዘላቂ መፍትሔን በማመቻቸት ሂደት ተፈናቃዮች ለበርካታ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ተጋላጭ በመሆናቸው መንግሥትም ሆነ ይህንን ሂደት የሚደግፉ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ለተፈናቃዮች ሰብአዊ መብቶች ጥበቃና መከበር ልዩ ትኩረት ሰጥተው ሊሠሩ ይገባል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት ኢሰመኮ በበርካታ አካባቢዎች የተደረጉትን እና እየተደረጉ ያሉትን የዘላቂ መፍትሔ ሥራዎች በተመለከተ ክትትል ባደረገበት ወቅት ሊበረታቱ የሚገባቸው ጥሩ ጅምሮች የተመለከተ ሲሆን፤ በአንጻሩ ሊሻሻሉ እንዲሁም በጭራሽ ሊደገሙ የማይገባቸውን ሂደቶች እና ሥራዎችም ለይቷል። በቅርቡ የተሰማውን እና ከላይ የተጠቀሰውን በጎ ዜና በአግባቡ ልንጠቀምበት ከቻልን በሀገራችን በተራዘመ የመፈናቀል ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙ እንዲሁም በየዕለቱ ቁጥራቸው እየጨመረ ላሉ ተፈናቃዮች ዘላቂ መፍትሔ ለማፈላለግ የሚያስፈልገውን ከፍተኛ ግብአት በተሻለ ሁኔታ ለማሰባሰብ የሚቻልበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል። ይህ ዕድል የተሳካ እንዲሆን ለተፈናቃዮች ዘላቂ መፍትሔ በማፈላለግ ሂደት ውስጥ ተሳታፊ የሚሆኑ መንግሥታዊም ሆነ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ለሚከተሉት የሰብአዊ መብቶች መርሆዎች ትኩረት ሰጥተው እንዲተገብሩ ኢሰመኮ ጥሪ ያቀርባል፦
- ትርጉም ያለው ተሳትፎ
ተፈናቃዮች ዘላቂ መፍትሔ በማፈላለጉ ሂደት ዋና ተዋንያን መሆናቸውን መቀበልና ዘላቂ መፍትሔው ሲታቀድ፣ ሲተገበር እንዲሁም ሲገመገም በአግባቡ እንዲሳተፉ ሁኔታዎች ሊመቻቹ ይገባል። በዚህም ሂደት የተለያዩ የተፈናቃዮች ቡድኖችን፤ ማለትም ሴቶች፣ ወጣቶች፣ አካል ጉዳተኞች፣ አረጋውያን፣ ኅዳጣንን በበቂ ሁኔታ ማሳተፍ ይገባል። ይህ የተፈናቃዮችን የተሳትፎ መብትን ከማክበር አኳያም ሆነ ተፈናቃዮችን ሙሉ ተሳታፊ አድርጎ ማብቃት ለዘላቂ መፍትሔው ስኬታማነት ትልቅ አስተዋጽዖ ያደርጋል። እንዲሁም ተፈናቃዮች ዘላቂ መፍትሔ በሚመቻችላቸው አካባቢ በሚካሄዱ ምርጫ፣ ሕዝበ-ውሳኔ እንዲሁም አስተዳደራዊ ጉዳዮችን ጨምሮ ሕዝባዊ ጉዳዮች ውስጥ እንዲሳተፉ ማስቻል ይገባል። ተቀባይ ማኅበረሰብ በተመሳሳይ በዘላቂ መፍትሔ የማፈላለጉ ሂደት ተሳታፊ ሊሆን ይገባል። ኮሚሽኑ የሰብአዊ መብቶች ክትትል ባደረገባቸው አካባቢዎች ተፈናቃዮች ወደ ቀድሞ የመኖሪያ አካባቢዎቻቸው እንዲመለሱ ወይም በሌሎች አካባቢዎች እንዲሰፍሩ በሚደረግበት ወቅት ስለሚመለሱበትም ሆነ ስለሚሰፍሩበት ቦታ ወይም ሁኔታ ምንም ዓይነት መረጃም ሆነ ውይይት ውስጥ እንዲሳተፉ ሳይደረግ የመመለስ ወይም የማስፈር እርምጃዎች እንደሚወሰዱ፤ በዚህም ምክንያት ለባሰ ችግር እንደሚዳረጉ እና የተወሰኑትም ለዳግም መፈናቀል እንደተዳረጉ ተመልክቷል። እንዲሁም ከተቀባይ ማኅበረሰብ ጋር ውይይት ባለመደረጉ ውስን በሆኑ የመሠረተ ልማቶች እና ማኅበራዊ አገልግሎት ዙሪያ ሊኖር የሚችለውን ውጥረት መቅረፍ ባለመቻሉ ላልተፈለገ ግጭት መንስዔ ሆኗል። ስለሆነም የዘላቂ መፍትሔው ዕቅዱም ሆነ አተገባበሩ ተፈናቃዮችን እና ተቀባይ ማኅበረሰብን ያሳተፈ ሊሆን ይገባል።
2. ፈቃድን ማግኘት
ተፈናቃዮች የዘላቂ መፍትሔ አማራጮችን በተመለከተ ነጻ ሆነውና በመረጃ የተደገፈ ሐሳባቸውን እና ፈቃዳቸውን ሊጠየቁ ይገባል። ተፈናቃዮች በሌላ የሀገሪቱ ክፍል ውስጥ ደኅንነትን የመፈለግ እና ሕይወታቸውን፣ ደኅንነታቸውን፣ ነጻነታቸውን ወይም ጤናቸውን አደጋ ላይ ወደሚጥል ማንኛውም ቦታ በኃይል ያለመመለስ ወይም እንዲሰፍሩ ያለመገደድ መብት አላቸው። የዘላቂ መፍትሔ አማራጮችን ይህንኑ ባገናዘበ ሁኔታ እንዲሁም ተፈናቃዮች እንደማንኛውም ዜጋ ወይም ነዋሪ በየትኛውም የሀገሪቷ አካባቢ ሄደው የመኖር መብታቸውን በሚያረጋግጥ መልኩ መተግበር አስፈላጊ ነው። ተፈናቃዮችን በዘላቂ ሁኔታ ለማቋቋም ወደ ቀድሞ የመኖሪያ ቦታቸው መመለስ ብቸኛው አማራጭ ተደርጎ ሊወሰድ አይገባም። ስለሆነም የዘላቂ መፍትሔ አማራጮች የተፈናቃዮችን ፍላጎት እና ፈቃድ ባገናዘበ መልኩ ሊተገበር ይገባል።
3. ጸጥታ እና ደኅንነትን ማረጋገጥ
ኢትዮጵያ ውስጥ ካለው ከፍተኛ የተፈናቃዮች ቁጥር እንዲሁም በየዕለቱ አዳዲስ መፈናቀሎች ከመፈጠራቸው አንጻር፤ ብዙውን ጊዜ በመንግሥት የተሻለ አማራጭ ተደርጎ የሚወሰደው ተፈናቃዮችን በተቻለ መጠን ወደ ቀድሞ ቀያቸው መመለስ ነው። ነገር ግን በመጀመሪያ ለሰዎቹ መፈናቀል መንስዔ የሆነው ግጭት ወይም የጸጥታ መደፍረስ በዘላቂ ሁኔታ መፍትሔ ሳያገኝ ተፈናቃዮቹን መመለሱ ዘላቂ መፍትሔ ሊሆን አይችልም። ይልቁኑም ለዳግም መፈናቀል እና ለተጨማሪ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች የሚዳርግ ይሆናል። ስለሆነም አስተማማኝ እና አሳታፊ የዕርቀ-ሰላም ሥርዓት ሳይፈጸም፣ ጸጥታ እና ደኅንነታቸው ባልተረጋገጠባቸው አካባቢዎች እንዲሁም መፈናቀል ወዳላቆሙባቸው አካባቢዎች ተፈናቃዮችን እንዲመለሱ ማድረግ ለተደጋጋሚ መፈናቀል እንደሚዳርግ ተገንዝቦ ለዘላቂ መፍትሔ በሚመረጡ አካባቢዎች ግጭት ወይም የጸጥታ ስጋት አለመኖሩን ማረጋገጥ ያስፈልጋል። እንዲሁም ተፈናቃዮችን የጦርነት ቀጠና ወደነበሩ አካባቢዎች ከመመለስ ወይም ከማስፈር አስቀድሞ አካባቢዎቹን ከፈንጂዎች እና ከሚፈነዱ የጦር መሣሪያ ቅሪቶች በአግባቡ ማጽዳት ያስፈልጋል።
4. የመመዝገብ እና ሰነድ የማግኘት መብት
የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን በሙሉ የሚመለከት መዝገብ ማደራጀትና ወቅታዊ መረጃዎችን መያዝ ቁጥራቸውን ለማወቅ ካለው ፋይዳ ባሻገር ለተፈናቃዮች ዘላቂ መፍትሔ ለማመቻቸት ጉልህ ሚና አለው፡፡ ነገር ግን በሀገር ደረጃ በተሟላ መልኩ የተደራጀ፣ የተሰባጠረ፣ በየጊዜው ወቅታዊ የሚደረግ የተፈናቃዮች መረጃ የለም። ኢሰመኮ ባከናወናቸው የክትትል ሥራዎችም እንደተመለከተው በተለያዩ ተቋማት የሚያዘው መረጃ አንዱ ከሌላው የሚለያይ መሆኑ፣ አንዳንዱ በአባወራ ወይም በቤተሰብ ደረጃ እንጂ በግለሰብ ደረጃ መረጃ ባለመያዙ እና በየጊዜው ወቅታዊ ባለመደረጉ ለተፈናቃዮች ዘላቂ መፍትሔ በአግባቡ ለማመቻቸት ትልቅ ተግዳሮት ሆኗል። በተጨማሪ ተፈናቃዮች የማንነት መታወቂያ እና ሌሎች ሰነዶችን ከቀያቸው ሳይዙ ከመጡ ወይም በመፈናቀል ሂደት ከጠፋባቸው ወይም ጊዜው ካለፈበት አዲስ ለማውጣት ወይም ለማሳደስ ይቸገራሉ። እንዲሁም በተራዘመ መፈናቀል ሁኔታ ለሚፈጠሩ አዳዲስ ኩነቶች የማረጋገጫ ሰነድ ለማግኘት ይቸገራሉ። መታወቂያ ወይም የማንነት ሰነድ ባለማግኘታቸው በቀላሉ ራሳቸውን ችለው መኖር ወይም የተወሰኑ ፍላጎቶቻቸውን በራሳቸው ማሟላት የሚችሉ ተፈናቃዮችም ጭምር ሰብአዊ ድጋፍ ጠባቂዎች እና ተረጂዎች ይሆናሉ። ስለሆነም ተፈናቃዮች የማንነት እና ሌሎች ሰነዶችን እንዲያገኙ በማድረግ በዘላቂ መፍትሔ ሂደት እራሳቸውን ሙሉ ለሙሉ እስኪችሉ ድረስ ሊያገኙ የሚገባውን ሰብአዊ ድጋፎችን እንዲያገኙ፣ ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው ሥራ እንዲሠሩ፣ የባንክ አገልግሎት እና መሰል መሠረታዊ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ፣ በሕዝባዊ እና ሀገራዊ ጉዳዮች እንዲሳተፉ እንዲሁም ሌሎች ሰብአዊ መብቶቻቸውን እንዲጠቀሙ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ያስፈልጋል።
5. ልዩ ጥበቃና ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ተመላሾች ትኩረት መስጠት
ዘላቂ መፍትሔ የማፈላለጉ ሂደት የተሟላ እና አካታች ሊሆን ይገባል። ይህም ማለት የተለያዩ የተፈናቃዮችን ቡድኖች ልዩ ፍላጎቶች መለየትና ማካተት ያስፈልጋል። ነፍሰ ጡር እና አጥቢ እናቶች፣ ሕፃናት፣ አካል ጉዳተኞች፣ አረጋውያን፣ ተጓዳኝ የሆኑ የተለያዩ የጤና ችግሮች ያሉባቸውን ሰዎች ልዩ ፍላጎት በመለየት የድጋፍ አሰጣጥ አሠራሩን ምቹ ማድረግ ያስፈልጋል። በተለይ የሕፃናት የትምህርት መብት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት የዘላቂ መፍትሔ በሚመቻቹባቸው አካባቢዎች የትምህርት እና የጤና አገልግሎት ሊኖር ይገባል። የኑሮ ሁኔታን በዘላቂነት የሚያሻሽሉ ፕሮጀክቶችን በበቂ ሁኔታ በማመቻቸት ተመላሾች በተለይም ሴቶች እና ሕፃናት ለጾታዊ ጥቃት፣ ለሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር እና መደበኛ ላልሆነ ስደት እንዲሁም ለጉልበት ብዝበዛ ተጋላጭ እንዳይሆኑ መከላከል ያስፈልጋል።
6. በበቂ የኑሮ ደረጃ የመኖር መብት
ተፈናቃዮች ዘላቂ መፍትሔ አገኙ የሚባለው በመፈናቀል ምክንያት ያገጠሟቸው ፍላጎቶች ወይም ችግሮች እንዲሁም አድሎዎ ተቀርፎ፣ በዘላቂነት ወደ ቀድሞ የመኖሪያ ቦታቸው ተመልሰው ወይም ወደ ሌላ ቦታ ሰፍረው፤ ወይም በተቀባይ ማኅበረሰብ ውስጥ በአግባቡ ተቀላቅለው እና እራሳቸውን ችለው መኖር ሲጀምሩ ነው። መፈናቀል የሚያመጣውን መዘዝ እንዲሁም ለሰብአዊ መብት ጥሰት ተጋላጭነትን ለመቅረፍ ረጅም ጊዜ ሊወስድ የሚችል ሂደት ስለሆነ ተፈናቃዮች ወደመጡበት ስለተመለሱ ወይም ወደሌላ ቦታ ስለሰፈሩ ወይም ከተቀባይ ማኅበረሰብ ጋር ስለተቀላቀሉ ዘላቂ መፍትሔ አግኝተዋል ማለት አይደለም። ይልቁንም ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ለማቋቋም ምቹ የሆኑ ሁኔታዎችን በማበረታትና በመፍጠር ለመፈናቀል ችግር እልባት መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ተፈናቃዮች መልሰው እራሳቸውን እስኪችሉ ድረስ የሰብአዊ ድጋፍ፤ ማለትም ምግብ፣ ውሃ፣ መጠለያ፣ ትምህርት፣ ሕክምና፣ የንጽሕና አገልግሎት እንዲሁም ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች ሊቀርቡላቸው ይገባል። የሰብአዊ ድጋፉ ልዩ ፍላጎት ያላቸው ወይም ለመብት ጥሰት ተጋላጭ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ፍላጎት ባገናዘበ ሁኔታ ሊቀርብ ይገባል። ዘላቂ መፍትሔ በሚመቻችባቸው አካባቢዎች፤ በተለይም በጦርነት መሠረታዊ አገልግሎቶች በወደሙባቸው አካባቢዎች መሠረታዊ አገልግሎቶች በአፋጣኝ ተጠግነው አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ ይገባል።
በተቀባይ ማኅበረሰብ ቀድሞውንም የነበረ ውስን መሠረተ ልማት እና አገልግሎት ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተፈናቃይ ሲጨመርበት ችግሩ ሊባባስ እና ከተቀባይ ማኅበረስቡ ጋር ለመጋጨት ምክንያት ሊሆን ይችላል። ስለዚህም ዘላቂ መፍትሔ በሚመቻቹባቸው አካባቢዎች ያሉትን መሠረታዊ አገልግሎቶች መለየት፣ ተፈናቃዮችን እንዲሁም ተቀባይ ማኅበረሰብን በአግባቡ ማወያየት እና ማሳተፍ፣ ተፈናቃዮች ላይ ብቻ የሚያተኩር ድጋፍ ከማድረግ ይልቅ ተፈናቃዮችን እና ተቀባይ ማኅበረሰቡን በጋራ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፕሮጀክቶችን መተግበር ይገባል። እንዲሁም ዘላቂ መፍትሔ በሚመቻችበት ወቅት ተፈናቃዮች ከመፈናቀላቸው አስቀድሞ የነበራቸውን የአኗኗር ዘይቤ፣ የሥራ ልምድና ክህሎት በመለየት ተፈናቃዮች እራሳቸውን ችለው በዘላቂነት ለማቋቋም ለሚደረገው ጥረት የራሳቸውን አስተዋጽዖ እንዲያደርጉ ማብቃት ያስፈልጋል።
7. ፍትሕ የማግኘት መብት
ሰሜን ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች በማኅበረሰባዊ እና አስተዳደራዊ ጥያቄዎች ምክንያት በሚነሱ ኃይል የቀላቀሉ ግጭቶች በርካታ ሰዎች ተፈናቅለዋል፣ ሴቶችና ሕፃናት ተደፍረዋል፣ አካላዊ ጉዳት ደርሷል፣ የግል እና የሕዝብ ንብረት ወድሟል፣ ጠፍቷል፣ ተዘርፏል። ነገር ግን ሰዎችን አስገድደው ያፈናቀሉ እንዲሁም የተለያዩ አካላዊ እና ቁሳዊ ጉዳት ያደረሱ ግለሰቦችም ሆኑ ቡድኖች ወደ ሕግ ቀርበው ተጠያቂ በማድረጉ እና ተጎጂዎችን በመካሱ ረገድ ክፍተቶች ተስተውለዋል። በተጨማሪም በግጭቱ ወይም በመፈናቀሉ ምክንያት የንብረት ባለቤትነትን የሚያረጋግጡ ሰነዶች ለጠፋባቸው ተፈናቃዮችና ተመላሾች ምትክ ሰነድ ለማግኘት ይቸገራሉ፣ ለወደመባቸው ንብረትና ሀብትም የጉዳት መጠን ተገምቶ ካሳ አያገኙም። በዚህም ምክንያት ወደቀያቸው ተመልሰው መደበኛ ኑሯቸውን ለመቀጠል ይቸገራሉ። ስለሆነም ተፈናቃዮች በመፈናቀል ሂደት በአካላቸውም ሆነ በንብረታቸው ላይ ለደረሰባቸው የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ተገቢውን ፍትሕ የሚያገኙበትን እንዲሁም ተጠያቂነት የሚረጋገጥበት ሁኔታ ሊኖር ይገባል። በተለይ ከተፈናቃዮች ንብረት ጋር በተያያዘ የሚነሱ ክርክሮችን ለመፍታት አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ቀለል ያሉ ሥነ-ሥርዓቶችን እና ሂደቶችን በመዘርጋት ተፈናቃዮች ሀብት እና ንብረቶቻቸውን መልሶ የሚያገኙበትን ምቹ ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ በተጨማሪም ለተፈናቃዮች ነጻ የሕግ አገልግሎት ሊመቻች ይገባል።