የተቆለፈበት ቁልፍ ! ከዶ/ር ምህረት ደበበ፣ የአዕምሮ ህክምና ስፔሺያሊስት፣ 438 ገጽ ትችት! –  በዶ/ር ፈቃዱ በቀለ

ከዶ/ር ምህረት ደበበ፣ የአዕምሮ ህክምና ስፔሺያሊስት፣  438 ገጽ  ትችት!  በዶ/ር ፈቃዱ በቀለ፣ የስልጣኔ ተመራማሪና የኢኮኖሚ ዕድገት ባለሙያ !

የካቲት 17 2023

ይህን መጽሀፍ አግኝቴ ለማንበብ እድል ያጋጠመኝ ባለቤቴ ወደ ኢትዮጵያ ሄዳ ስትመለስ ይዛልኝ ከመጣች በኋላ ነው። በዶ/ር ምህረት ደበበ የተጻፉ ሁለት ወፈፍራም መጽሀፎች ሲሆኑ፣ አንደኛው መጽሀፍና በቅርብ የወጣውን የሽፋኑ ሰዕል ደስ ስላለኝ እንደ አጋጣሚ አንስቼ ካገላበጥኩኝ በኋላ፣ እስቲ ብዬ ደግሞ ሌላውን ሳገላብጥ አቀራረቡ ደስ ስላለኝ  ሃሳቡን ይበልጥ ለመረዳትና ለመገምገም ሆነ ወይም ለመተቸት እንዲያመቸኝ በሚል በመጀመሪያ ያገላበጥኩትን በመተው ቀደም ብሎ የታተመውን ማንበብ ጀመርኩኝ። እንደ ዕውነቱ ከሆነ አንዳንድ ጊዜ ከኢትዮጵያ የሚመጡ በአማርኛ ቁንቋ የተጻፉ መጽሀፎችን ትንሽ ካገላበጥኩኝ በኋላ ምንም ስለማይጥሙኝና አብዛኛዎችም ዝም ብሎ ትረካና የህብረተሰባችንን ህሊናዊ አወቃቀርና፣ በዚያም አማካይነት በመሬት ላይ የሚታየውን ህያው በሆነ መልክ ለመተንተንና እንድንረዳው የሚያደርጉ ስላይደሉ በንባቤ አልገፋባቸውም። የስነ-ጽሁፍም ዋና ዓላማ በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ ያሉትን አስቀያሚም ሆነ ቆንጆ ነገሮች ስዕላዊ በሆነ መልክ መግለጽ ሲችሉና አንባቢውን በልዩ ሃሳብ ውስጥ ተመስጦ እንዲዋኝ ማድረግ ሲችሉ ብቻ ነው። ከዚህ አኳያ የዶ/ር ምህረት ደበበ መጽሀፍ ልዩና አንባቢዉን በሃሳብ ባህር ውስጥ ገብቶ እንዲዋኝ የሚያደርግና፣ የአገራችንን ነባራዊም ሆነ የህዝባችንን ህሊናዊ አወቃቀር ግሩም በሆነ መልክ የሚያቀርብ በታሪካችን ውስጥ በመጀመሪያ ጊዜ በልዩ አቀራረብ የተዘጋጀና የተጻፈ ትምህርታዊ መጽሀፍ ነው ብል ማጋነን አይሆንብኝም። የመጽሀፉ አርዕስትም ካለምክንያት የተመረጠ ሳይሆን፣ ለአንድ የተቆለፈበት ነገር መፍትሄው በአዕምሮ ውስጥ ያለ ቁልፍና፣ ለአንድ ህብረተሰብ መዘበራረቅና ስነ-ምግባር መበላሸት ደግሞ የጭንቅላት መቆለፍ ወይንም የአዕምሮን የማሰብና የመፍጠር ኃይል ለመገንዘብ ካለመረዳት ጋር የተያያዘ መሆኑን በግልጽ የሚያሳይ ነው። ጸሀፊው የኖይሮ ባዮሎጂ ሊቅ እንደመሆኑ መጠን በዚህ ሙያ ባልሰለጠነ ከማንኛውም ምሁር የሚበልጥ ግንዛቤ ስላለው፣ የአዕምሮን ልዩ ልዩ ባህሪዎች የበለጠ የተገነዘበና፣ በመጽሀፉ ውስጥ ደረጃ በደረጃ ቲያትራዊ በሆነ መልክ ያቀረበ ነው። በመጽሀፉ ውስጥ የተዘረዘሩት ልበ-ወለድ ስሞች ባህርይና ድርጊት በእርግጥም የማንኛውም ኢትዮጵያዊ አስተሳሰብ ብቻ ሳይሆኑ፣ የጠቅላላው የዓለም ህዝብ ባህርይ ሲሆኑ፣ በሌላ ወገን ግን ባደገና በሰለጠነው የካፒታሊስት ህብረተሰብ ውስጥ የሚኖረው ግለሰብም ሆነ ህዝብ ከማቴሪያላዊ ዕድገት ጋር በተያያዘ አስተሳሰቡና ድርጊቱ ለየት ያለ መሆኑን መረዳት ይቻላል።  ደራሲው በሁለት በተለያዩ አገሮች የኖረና፣ በአሁኑ ወቅት ደግሞ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖር በመሆኑ በሙያው እዚያው በመሰማራት፣ በሁለት አገሮች ያለውን የዕድገት ልዩነት በንጽጽራዊ መልክ በማወዳደር ማቅረቡ አጠቃላይ የሆነ ማቴርያላዊ ዕድገትም ሆነ ዕድገት በቀጨጨበት ዓለም ውስጥ የሚኖር ህዝብ ስለሰው ልጅም ሆነ ስለተፈጥሮ  የተለያየ አስተሳሰብና ግንዛቤ እንዳላቸው ቁልጭ አድርጎ ያስቀምጣል።  ወደ መጽሀፉ መሰረታዊ ሃሳብና የአሰራር ስልት ላይ ደረጃ በደረጃ ልምጣበት።

የትዕይንቱ ዋና ተዋንያን መላኩና ሰሎሜ ሲሆኑ፣ ሁለቱም ለየት ያለ የማህበረሰብ መሰረት(Social Background)  ያላቸውና፣ በአስተሳሰብም የሚራራቁ አይደሉም። ከሁለቱ ተዋንያን ባሻጋር፣ በመጽሀፉ ውስጥ ልዩ ልዩ ባህርያት ያላቸው ስዎች ተካተውበታል። ጥሩ አመለካካት ያላትና መላኩን እንደታናሽ ወንድሟ አድርጋ ያሳደገችውና ለቁም ነገር እንዲደርስ የረዳችው፣ የህሊና ስፔሻሊስት የሆነችው ዶ/ር ሳራ፣ የስሜቱ ተገዥና የሚያደርገውን በትክክል የማያውቀው ምንተስኖት የሚባለው የዶ/ር ሳራ ባል፣ ቀና አመለካከት ያለው፣ ራሱን ከተንኮል ያፀዳውና በራሱ ጥረት ከታች በመነሳት ከፍተኛ ቦታ የደረሰው ማርቆስ የሚባለው የመላኩ የቅርብ ጓደኛ፣  የስሜቷ ተገዢ የሆነችና፣ የራሷን ጥቅም ለማግኘት ስትል ምንም ነገር ከማድረግ የማትመለሰውና በተንኮል የተካነችው ስንክሳር የምትባል ሴት፣ ሰፋና ጠለቅ ያለ ዕውቀት ያላቸውና ብዙ ነገሮችን ማገናዘብ የሚችሉት የሰሎሜን አባትና እናት፣ አቶ ኦላናና ባለቤታቸው፣ መንፈሱ ቆንጆ የሆነውና በልጅነቱ የበሰለ አስተሳሰብን ያዳበረው የሶሎሜ ወንድም፣ ሶለን የሚባለው፣ በልጅነቷ ብዙ ስቃይን ያሳለፈችውና በእናቷ ግሪክ፣ በአባቷ ደግሞ ጥቁር አሜሪካዊ የሆነችው መንፈሷ ቆንጆ የሆነና የሰዕል ስጦታ ያላት ሶፊያ፣ የኩላሊት በሽታ ስፔሺያሊስት የሆነውና፣ የኩላሊትን በሽታ ከማከም በስተቀር በጭንቅላቱ ውስጥ ሌላም ብዙ ዕውቀት የሌለውና፣ ለመኖር ብቻ የሚኖረው፣ ክብሮም የሚባለው፣ እነዚህ ሁሉ እንደየባህርያቸው በመጽሀፉ ውስጥ በመካተት ለመጽሀፉ የንባብ ጣዕም  የሰጡት ናቸው ማለት ይቻላል።  ደራሲው እንደዚህ ዐይነት የተለያየና የተዘበራረቀ አመለካከት ያላቸውን ስዎች በልበ-ወለዱ ውስጥ ማካተቱና መቃኘቱ የሚያመለክተው የቱን ያህል  የህብረተሰብአችንን የተበላሸ ማቴሪያላዊ መሰረትና የህዝባችን የተዘበራረቀ የህሊና አወቃቀር እንደገባው ነው። ወደ ዋናው ተዋንያን ወደ መላኩና ሰሎሜ ጋ፣ እንዲሁም የሰሎሜ ቤተሰቦች ጋ በመምጣት የደራሲውን አመለካከትና፣ ስለሰው ልጅ ያለውን ግንዛቤና፣ እንዲሁም ይህ ጉዳይ ስለ አንድ ህብረተሰብ ዕድገትም ሆነ ፀረ-ዕድገት ላይ የሚኖረውን ተጽዕኖና አስተዋጽዖ ጠጋ ብለን እንመልከት።

መላኩ በአባቱ የአፋር ሰው ሲሆን፣ አባቱን ፈጽሞ አያውቀውም። ስለሆነም መላኩ አባቱ በሌለበት መቂ ከተማ አክስቱ ቤት የተወለደ ሲሆን፣ በእናቱና በአክስቱ አለመግባባት የተነሳ እናቱ አዲስ አበባ መጥታ አስር ዐመት እስኪሞላው ድረስ አሳድጋው በድንገት በመኪና አደጋ ሞተች። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ኑሮው ስቃይና ትምህርቱን በስርዓት ይከታተል አይከታተል የሚቆጣጠረው ዘመድ አልነበረውም። አጠገቡ ያለውም አጎቱ ሊረዳው የሚችል አልነበረም። መላኩም በኑሮው የተጎሳቆለ ስለነበር የትምህርት ቤት ጓደኞቹ ይስቁበት፣ ይሳለቁበት ነበር።  እናቱ ተቀጥራ ትሰራ የነበረበት መስሪያቤት አለቃ የነበሩት ወይዘሮ የትናየት የሚባሉት እንዳጋጣሚ በመንገድ ላይ ሲሄዱ፣  መላኩ አንድ ቀን ውሃ በባልዲ ተሸክሞ ሲሄድ አሳዝኗቸው እያዩት ጠጋ ብለው በመጠየቅ የማን ልጅ እንደሆነ ለማረጋጋጥ ይችላሉ።  የሚኖርበትን ሁኔታም እስከቤቱ ድረስ ሄደው በማየት ወስደው እሳቸው ጋር እየኖረ ያስተምሩት ዘንድ አጎቱን ይጠይቁታል። በስነ-ስርዓት መላኩን መከታተልና ማሳደግ ያልቻሉት የመላኩ አጎትና ባለቤቱ፣ እንዲያውም ጎርምሶ እስቸግሮናል በማለት በመሄዱ መስማማታቸውን ለወይዘሮ የትናየት ይነግሯቸዋል።   መላኩም ወይዘሮ የትናየት ቤት በሳቸው የመጨረሻ ልጅ ሳራ በምትባለው  እየታገዘ ትምህርቱን በመከታተል ጎበዝ እየሆነ መጣ። ማትሪክንም አልፎ የህክምና ትምህርት በመከታተል ላይ ሳለ ደስ ስላላው ለሳራ ሌላ ዐይነት ትምህርት ለመማር እንደሚፈልግ ይነግራታል። እንደ ወንድም የረዳቸውና ያሳደግችው ሳራም እንግሊዝ አገር የመማር ዕድል አገኘችለት። እንግዝሊም የኢኮኖሚከስ ትምህርቱን በመከታተል ላይ እንዳለ ይበልጥ ያደላ የነበረው ፍልስፍና፣ ታሪክና የስነ-ልቦና  መጽሀፎችን በማንበብ ነበር። የኢኮኖሚክስ ትምህርቱን እንደዋና አይመለከተውም ነበር። ይህ በዚህ እንዳለ አንድ ካናዳዊ ዝንባሌውን በማየት ረድቶት፣ ካናዳ፣ ቶረንቶ ሄዶ እዚያ ትምህርቱን የመከታተል ዕድል አገኝለት። መላኩም የማስተር ትምህርቱን በጥሩ ውጤት ካጠናቀቀ በኋለ ዶክትሬቱን ለመስራት ዕድል ቢያገኝም አገሬ ውስጥ ብዙ ያልተሰራ ነገር አለ በማለት በመመለስ አገሩን ለመርዳት ቆርጦ ተነሳ። እንደተመለሰ ተቀጥሮ የመስራት ዕድል ያገኘው የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን መስሪያቤት ውስጥ ነው። እዚያም አንድ አራት ዐመት ያህል ከሰራ በኋላ መስሪያቤቱ የሰውና የገንዘብ ጠር ነው፣ ጥቂቶችን የሚያደልብና ድህነትን የሚያጠናክር ነው በማለት በግልጽ የሚታይ አነስ ያለ መስሪያቤት ውስጥ ተቀጥሬ ብሰራ ይሻላል በማለት ብዙ ገንዝብ የሚያገኝበትን መስሪያቤት ጥሎ በመውጣት ሌላ ቦታ ተቀጥሮ መስራት ይጀምራል።  እንዳጋጣሚ ወይዘሮ  የትናየት ቤት ማደጉና፣ እንደ እህትም እየተከታተለች ታስረዳውና ታስተምረው የነበረችው ሳራና፣ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ለፍልስፍና፡ ለታሪክና ለህሊና ሳይንስ የነበረው ዝንባሌና፣ የተፈጥሮን ምንነት ጠጋ ብሎ ለመገንዝብ የነበረው ጉጉት ባህርይውንና ስለሰው ልጅ ያለውን አስተሳሰብና፣ ስለ አጠቃላይም ህብረተስብአዊ ዕድገት ያለውን አመለካከት መቅረጻቸው የማይካድ ለመሆኑ የልበ-ወለዱን አቀራረብ ለተመለከተ ሊገነዘበው ይችላል።

ሁለተኛዋና እንደሱው ዋናው ተዋናይ የሆነችው ሰሎሜ ደግሞ የተሻለ የህብረተሰብ መሰረት ካላቸው ቤተሰብ ውስጥ የተወለደች ስትሆን፣ ከአስራአንድ ዐመቷ ጀምሮ ከቤተሰቦቿ ጋር አሜሪካን አገር በመሄድ ትምህርቷን እዚያ  የተከታተለችና፣ በጥሩ ቤተሰብአዊ  አስተዳደግ በፍቅር ያደገችና፣ ስለሰውም ልጅ ያላት ዝንባሌ ከመላኩ ጋር የሚመሳሰል ነው። ሰሎሜ ትምህርቷን ካጠናቀቀች በኋላ እንደዚሁ ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ አንድ የጎዳና ተዳዳሪ ህጻናትንና ሴተኛ አዳሪዎችን መልሶ የማቋቋም፣ በውጭ ሰዎች የሚደጎም የገብረ-ሰናይ ድርጅት ውስጥ ተቀጥራ  መስራት ጀመረች። እዚያ ተቀጥራ መስራት ከጀመረች ወዲህ፣ ይህ ዐይነቱ በህፃናት ላይ የሚደርሰው ግፍና፣ ካለ አሳዳጊ ጎዳና ላይ ተጥሎ ለማኝ መሆንና፣ በትንሹ በትልቁ እንደ ቆሻሻ ዕቃ መታየትና፣ በሴተኛ አዳሪዎችም ላይ የሚደርስባቸው ግፍ እየከነከናት በፍጹም ልትቀበለው የማትችለውና፣  እንደ ህብረተሰብአዊና እንደ ተፈጥሮ ህግ ሆኖ መታየት እንደሌለበት መገንዘብና፣ ይህንንም መዋጋት እንዳለባት ቆርጣ ተነሳች። ደራሲው ቁልጭ አድርጎ እንደሚተነትነው፣ ሶሎሜ እየደጋገመች የምታነሳው ጥያቄና መልስም ለማግኘት የሚያስጨንቃት፣ የሰው ልጅ ለምን ደሃ እንደሚሆን ነው። ለድህነት መንስዔ  የሚሆነው ምክንያት ምንድነው ? ድህነት ከህብረተሰቡ የአኗኗር አወቃቀርና አስተሳሰብ ጋር የተያያዘ ወይስ ዋናው ምክንያት ሌላ ነገር ነው? የሚለው ጥያቄ ያብሰለስላታል። እንደደራሲው አተናተን፣ “ …. አንድ የጎዳና ተዳዳሪ ህፃን ወይም ሴተኛ አዳሪ ችግራቸውም ሆነ ማንነታቸው ከህብረተሰቡ ሁኔታ ተነጥሎ የሚታይ ሳይሆን፣ የተሳሰረና የተጠላላፈ ነው፣“ የሚለው መደምደሚያ ላይ እንደደረሰች ደራሲው በግሩም ብዕሩ ያረጋግጣል።  ሰሎሜ ጥያቄን በመጠየቅና መልስም ለማግኘት የምትጨነቅ ብቻ አይደለቸም። ለሰው ልጅ ሁሉ ፍቅር አላት። ደሃ፣ ሀብታም፣ ቆሻሻ ልብስ የለበሰ፣ ወይም የዘነጠ፣ ለአንዳንዶች አስቀያሚ የሆነ ወይም የአካል ጉድለት የደረሰበት፣ ለሷ የሰው ልጅ ሁሉ አንድ ነው። አንዱ ከሌላው እንደማይበልጥ ነው የምትገምተው። አንዳንዶች፣  አንዱን ሰው ቆንጆ ነው፣ ሌላውን ሰው ደግሞ አስቀያሚ ነው ሲሉ ግራ ይገባታል። የሰውንም ልጅ የምትለካው በለበሰው ልብስ ወይም „መልኩ በማማሩ“ ሳይሆን፣ በመንፈሱ ቁንጅናነትና፣ ስለሰው ልጅ ባለው አመለካከት ብቻ ነው። ለሷ የሰው ልጅ ሁሉ ሰው ነው። አንዱ ከሌላው የሚበልጥበት ወይም የሚያንስበት ምንም ምክንያት እንደሌለ ዕምነቷ ነው። አንድ ቀን ከመላኩ ጋር ተቀጣጠረው እሱን ለመጠበቅ ስትል አንድ ቡና ቤት ውጭው ላይ ትቀመጣላች። አንድ በፍጥነት የሚበር ታክሲ በአካባቢው ቆመው የሚለምኑ ሽማግሌ ገጭቶ ከወደቁበት ሳያነሳቸው ዝም ብሎ እየነዳ በፍጥነት ያመልጣል። የሽማግሌውን መውደቅና የደረሰባቸውን መጠነኛ ጉዳት የተመለከተችው ሰሎሜ በፍጥነት በመሄድ ከወደቁበት አንስታና ደግፋ በመውሰድ ቡና ቤቱ በራፍ ላይ ያለው የቡና ቤት መቀመጫ ላይ እንዲቀመጡ ታደርጋለች። ይህንን የተመለከተችው የቡና ቤቱ አሳላፊ ወደ ሰሎሜ ጋ በመምጣት ቡና ቤቱ እንደዚህ ዐይነት ቆሻሻ ልብስ የለበሱና የተጨራመቱ ስዎችን ማስተናገድ እንደማይችልና፣ እንደነዚህ ዐይነት ሰዎችም ደንበኞቿን እንደሚያባርሩባት ቦታውን ለቀው እንዲሄዱ ታመናጭቃቸዋልች። ሶሎሜም በአሳላፊዋ አነጋገር በመገረምና በመናደድ፣ ለምን እንደዚህ እንደምታስብና፣ ይህም ሊሆን እንደማይችል፣ የቡና ቤቱ ባለቤት መጥቶ እንዲያነጋግራት ለአሳላፊዋ ትነግራታለች። ይህ ሊሆን እንደማይችልና፣ እሷ ራሷ እንደምትወስን በመጨቃጨቅ ላይ እንዳሉ የቡና ቤቱ ባለቤት ውስጥ ሆኖ ይመለከታቸው ስለነበር ውጭ ወጥቶ ጉዳዩን ለማጣራት ከሰሎሜ ጋር ይነጋገራል። ሰሎሜም ነገሩን ካስረዳችው በኋላ ሁለቱም ብዙም ሰው የሌለበት ቦታ  ቡና ቤቱ ውስጥ ገብተው እንዲቀመጡ ቦታ ይሰጣቸዋል። ሰሎሜም በመኪና አደጋ የተጎዱትንና በድህነት የተጎሳቆሉትን ሽማግሌ ምግብ አዛላቸው ከተመገቡ በኋላ በህይወት ዘመናቸው አግኝተው የማያውቁትን ብዙ ገንዘብ አሽክማ ትሸኛቸዋለች። ደራሲው እዚህ ላይ ለማመልከት የሞከረውና በትክክልም እንዳስቀመጠው አብዛኛው ህዝብና፣ በተለይም ደግሞ በትንሽ ዕውቀት ጭንቅላቱ ለብ ለብ ያለው  ስለደሃና ቆሻሻ ልብስ የለበሰ ሰው ላይ ያለውን  የተዛባ አመለካከት ነው። የደራሲው አገላለጽ በአገራችን ውስጥ በተለይም ኤሊት ነኝ የሚለው ጭንቅላቱ ውስጥ የተንሰራፋውን የተወላገደና፣ ለህብረተሰብ ዕድገት ጠንቅና፣ በአጠቃላይ ሲታይ ደግሞ  ስለሰው ልጅ ያለንን የተዛባ አመለካከት ለማሳየት ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ አንድ ቀን መላኩና ሰሎሜ በመኪና ወደ ቦሌ አቅጣጫ እየነዱ ሲሄዱ የትራፊክ መብዛት በፍጹም አላንቀሳቅስም ይላቸዋል። ሰሎሜም በመገረም መላኩን ትጠይቀው የነበረው፣ ለመሆኑ አዲስ አበባ ማለት ቦሌ ብቻ ናት ወይ ? ለመሆኑ ለምን እዚህ አካባቢ ብቻ መኪናና ሰው በአንድ ላይ እየተጋፉ ይሄዳሉ ? እያለች ትጠይቀው ነበር። በተለይም ትላልቅ የቤት መኪና ይዞ የሚነዳውን ጎልማሳ ስትመለክት ስለሰው ልጅ ደንታ የሌለው ብቻ ሳይሆን መንገዱ ሁሉ ለሱ ብቻ የተሰራ ይመስል መንገዱን ሲያስጨንቅና በሰው ላይ ለመጋለብ ስታይ በጣም ያበሳጫታል። በተለይም የመንገድ አሰራሩ በደንብ ታቅዶና ለሰው ልጅ ታስቦ ባለተሰራበትና፣ የእግረኛ መሄጃ፣ መኪና ነጂዎች ልጆች ላይ አደጋ እንዳያደርሱ ተብሎ ልዩ መሄጃ መንገድ ባልተሰረባትና፣ የቢስኪሌትና የአውቶብሶች መሄጃ ልዩ መስመርና መንገድ በሌለበት ከተማ ውስጥ በሰው ላይ የሚደርሰው አደጋ ከፍተኛ መሆኑን ደራሲው በደንብ በመገንዘብ በጥሩ ብዕሩ ቁልጭ አድርጎ ያስቀምጣል።

ሰሎሜ በስራዋ ላይ እያለችና ከመላኩ ጋር ያላቸውን ግን ደግሞ በግልጽ ወጥቶ ያልተመነዘረውን ፍቅርና ግኑኝነታቸውን  በማውጣትና በማውረድ ላይ እያሉ፣ አባቱና እናቷ፣ እንዲሁም የሰሎሜ ሁለት ወንድሞች የሚኖሩበት ከቺካጎ ከተማ ከሷ በሁለት ዐመት ከፍ የሚለው ታላቅ ወንድሟ ሶለን ላይ ሽጉጥ ተተኩሶበት ከፍተኛ ጉዳት ስለደረሰበትና ሆስፒታልም ገብቶ በመታከም ላይ እንደሚገኝ፣ በፍጥነት ወደ ቺካጎ መምጣት እንዳለባት በስልክ ይነገራታል። ጉዞዋን ወደ አሜሪካ ከማቀናቷ በፊት ግን ከመላኩ ጋር በመገናኘት፣ እሷ የምታሳድጋቸውን የሷ አክስት ቤት ውስጥ የሚኖሩ ሁለት፣ ገና ለአቅመ አዳም ያልደረሱ ልጆችን  መላኩ እንዲከታተላቸውና  በማንኛውም ነገር እንዲረዳቸው አደራ ብላ  ጉዞዋን ወደ አሜሪካ ታቃናለች። የሷ ወደ አሜሪካን መሄድና በመላኩና በሰሎሜ መሀከል ያለው መፈላለግና ውስጣዊ ፍቅር ሳይወጣ ሁለቱም እንደሚዋደዱና እንደሚፋቀሩ ስሜታቸውን ሳይገልጹ መሄዱ ልበ-ወለዱን በጉጉት እንድናነበው ይጋብዘናል። በሌላ ወገን ግን የልበ-ወለዱ ዋና መልዕክት፣ ይህ በሁለት ሰዎች ያለውን በጾታ ላይ የተመሰረተ ፍቅር ለማሳየት ሳይሆን፣ ዋና ዓላማው ሁለት በአስተሳሰብ የሚገጣጠሙ ፍቅረኞች ስለህበረተሰብአቸው ኋላ-መቅረትና አገራዊ መዝረክረክና የሰው ልጅም ኑሮ በዚህ መልክ መሄድና መታየት እንደሌለበት የግዴታ በአዲስ አስተሳሰብ ላይ የተመሰረተ ሁለገብና አጠቃላይ ለውጥ መምጣት እንዳለበት ለማመልከት ብቻ ነው።

ሶሎሜ ሁለት ታላላቅ ወንድሞች ሲኖራት፣ በተለይም  የሁለት ዐመት ዕድሜ ከሚበልጣት ሶለን ከሚባለው ታላቅ ወንድሟ ጋር በጣም ይዋደዳሉ።  ቤተሰቦቿ የዲቪ ዕድል አግኝተው አሜሪካን በመሄድ ኑሮአቸውን እዚያ የመሰረቱ ናቸው። የሰሎሜ አባትና እናት የሚከባበሩና ልጆቻቸውንም በስነስራዓት ያሳደጉ ሲሆኑ፣ የስሎሜ አባት የጊዜንና የገንዘብን አጠቃቀምን በደንብ የተገነዘቡና፣ ካለምክንያት የሚባክን ገንዘብና ጊዜን በስርዓት አለመጠቀም ያበሳጫቸዋል።   „ገንዘብ የጊዜ ምንዛሬ ነው፤ ጊዜም ያልተመነዘረ ገንዘብ ነው“ የሚል ፍልስፍና አላቸው በማለት ደራሲው የኑሮ ፍልስፍናቸውን ያስረዳናል። ፍልስፍናቸው ከዚህ ርቆ በመሄድ በአጠቃላይ ስለ አንድ ህበረተሰብ ዕድገት ያላቸውን አመለካከት፣ ልጃቸው ለአደጋ ከመጋለጡ በፊት፣ ከልጃቸው ከሶለን ጋር ክርክር ወይም ውይይት በሚያደርጉበት ጊዜ ጣል ጣል የሚያደርጉትን አስተሳሰብ ለተመለከተ የአገራቸው ኋላ-ቀርነት የሚያስጨንቃቸው እንደሆነ ከልበ-ወለዱ መገንዘብ ይቻላል።  እንደዚሁም ሶለን የአባቱን ፈለግ በመከተል ስለሰው ልጅ ያለው አመለካከት በወጣትነት ጊዜው የዶክትሬትና የፕሮፌሰርነት ማዕረግ ከያዙትና በዕድሜም ወደ ስድሳና ወደ ሰባ ዐመት ከሚጠጉት ጋር ሲወዳደር  ልቆ የሄደ መሆኑን ደራሲው በግሩም መልክ ያሰቀምጣል። በተጨማሪም የጥቁር አሜሪካንን የጭቆናና የስቃይ ትግል ታሪክ ያነበበና  የእነ ዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግን ስራና የትግል እንቅስቃሴ ጠንቅቆ ያወቀ ስለነበር፣  አብዛኛውን ጊዜውን የሚያሳልፈው ከጥቁሮች ጋር ነው። ጥሩና ትችታዊ አመለካከት ያዳበረው ሶለን በተለይም አሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያኖች ራሳቸው ጥቁር ሆነው ጥቁር እንዳይደሉ፣ ጥቁር አሜሪካውያንን እነዚያ ጥቁሮች እያሏቸው ሲጠሩቸው በጣም ይገርመው ነበር፤ ይበሳጭም ነበር።  ይህም የሚያረጋግጠው የሶለንን የስባዊነት ባህርይና በዕውቀት የዳበረ መሆኑን ብቻ ሳይሆን ተማርን፣ ረቀቅን ብለው ሌላውን ወንድማቸውን የሚንቁትን፣ የዶክትሬትና የፕሮፌሰርነት ማዕረግ የያዙትን ስንትና ስንት እርምጃ እንደሚበልጣቸው ነው። በተጨማሪም ህብረተሰብአዊ ባህርይንና ሰብአዊነትን ያላካተተ፣ እንዲሁም ደግሞ ትችታዊ አመለካከት የሌለውና ስልጣኔ አጋዥ ያልሆነ የዶክትሬትነትና የፕሮፌሰርነት ማዕረግ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ እንደሚበልጥ ከስነ-ጽሁፉ መረዳት እንችላለን።

ሰሎሜም ወንድሟን ለመጠየቅ ወደ ሆስፒታሉ ከሄደችና ወንድሟን ማጽናናት ስትጀምር፣ በመሀከሉ ብልጭ ያለባት ወንድሟ የተኛበትን ሆስፒታል እኛ አገር ካለው ጋር ስታወዳድር በጣም ነው የገረማትም፤ ያዘነችውም። ሁለም በሃሳብ ላይ እያሉ መጠየቅ የጀመረችው እንደዚህ በማለት ነበር:  „አንድ እንኳ እንደዚህ ዐይነት ሆስፒታል አገራችን ቢኖር ስንት ሰው ከሞት ይተርፍ ነበር ?“  እያለች ነው የህዝባችን መበደልና የአገራችንን ኋላ-ቀርነት የሚያብከነክናት። ሰለሆነም፣ ጥሩ ነገር ስታይ ይህም ነገር እኛም አገር ቢኖር ኑሮ በማለት ነው ምሬቷንና ብስጭቷን እንዲሁም ምኞቷን የምትገልጸው።  ስለ ዕድገት ያላትን የልጃቸውን አገላለጽና አስተያየት ጠጋ ብለው የሚያዳምጡት አባቷ አቶ ኦላና፣ ይህ ዐይነቱ በጥሩ መልክና ቆንጆ አካባቢ የተሰራ ሆስፒታል ከሌሎች ነገሮች ጋር ተነጥለው መታየት እንደሌለባቸው ለማስረዳት ይሞክራሉ።  በሳቸውም ዕምነት፣ ይህ ዐይነቱ ሆስፒታል በአጠቃላይ ሲታይ ህዝቡ ወይም መንግስት ስለሰው ልጅ ያላቸው አመለካከት ለየት ያለና፣ ባህሉም የላቀ ስለሆነ የሰው ልጅ እንደ ዕቃ የሚጣል ሳይሆን የሚከበርም መሆኑን የሚያመለክት ነው በማለት ለልጃቸው ቀስ ብለው ያስረዷታል። እሷም የሳቸውን ነገር ሙሉ በሙሉ ሳትቀበል ይህ የግዴታ ከባህል ጋር ብቻ የሚያያዝ አለመሆኑን፣ ዱባይና ሪያድ ያሉትን በንጽህናና በአያያዝም የማይተናነሱትን ሆስፒታሎች እየተጠቀሰች ከኛው ጋር በማወዳደር „ደሃ ሁልጊዜም ደሃ ነው፤ አያልፍለትም“ እያለች ትነግራቸዋለች። ድህነት ተፈጥሮአዊ አለመሆኑ ስትናገር የነበረችው ሰሎሜ እዚህ ላይ ደግሞ ብዙም ሳታስብ ድህነትን እንደ ተፈጥሮአዊ እንደሆነና፣ ከባህል ጋር ምንም የሚያገናኘው ነገር እንደሌለ ለማስረዳት ትሞክራለች።  አቶ ኦላና ንግግሯን በደንብ ካዳመጡ በኋላ፣ የአረቦቹ ዕደገት ከጭንቅላት ተሃድሶና ከዕውነተኛ ስልጣኔ ጋር የተያያዘ ሳይሆን ከዘይት ሽያጭ የተገኘና፣ አንድ ቀን ዘይቱም ሲያልቅ የዶላርም እጥረት እንደሚኖርና፣ በድሮ ሁኔታቸውና የአኗኗር ስልታቸው ሊገፉበት እንደማይችሉ በሰከነና በጠለቀ መንፈሳቸው ረጋ ባለ መልክ ልጃቸውን ያስረዷታል። በሌላ አነጋገር፣ ዋናው የስልጣኔ ምንጭ በገንዘብ መደለብና መትረፍፈፍ ሳይሆን በጭንቅላት መዳበርና፣ ዕውቀትና ስልጣኔም ከጭንቅላት የሚፈልቁ መሆናቸውን ደራሲው በሚገርም ነገር ፕላቶናዊና ሶክራትሲያዊ በሆነ መንገድ ያስተምረናል። አቶ ኦላናም በመቀጠል፣ የጃፓኑንና የኮሪያውን ስልጣኔ ከአረቦቹ ጋር በማወዳደር ንጹህ በንጽሁ በአስተሳሰብና በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ሲሆን፣  ብዙ የአፍሪካ አገሮች የተትረፈረፈ የጥሬ-ሀብትና፣ ጥሩ አካባቢና አየር እያላቸው ባለማወቃቸውና መሪዎችም ስግብግቦችና የደነቆሩ ስለሆኑ ህዝቡ ደህ እንዲሆን አድርገውታል በማለት ያስረዷታል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ምርጫ፦ ህወሃት ወይስ ግብጽ?

ሰሎሜም የአባቷን ግሩም አገላለጽ ከአዳመጠችና በመደነቅ፣ እንደኛ ያለው ህዝብ ታዲያ ድህነትን ለማስወገድ ከየት መጀመር አለበት ብላ? አባቷን በጥያቄ ታፋጥጣቸዋለች። በመቀጥልም፣ በልመና መኖር ስልችቶኛል፣ እስከመቼ ነው በልመና የምንኖረው?  እያለች የምሬቷን ትናግራለች።  በመሀከሉ ስልክ በመወደሉ የሰሎሜ እናት፣ እንደመሰላቸት በማለት እስቲ ወደ ስልኩ ጋ ልሂድ፣ የአንድ ሺህ ዐመት ችግር በአንድ ቀን ክርክር አይፈታም በማለት ለባለቤታቸውና ለልጃቸው ይነግሯቸዋል። አቶ አላናም ፣ „ የአንድ ሺህ ማይል ጉዞ በአንድ እርምጃ ይጀመራል  በማለት ቀልዳቸውን ጣል ያደርጋሉ። አቶ ኦላናም አፋቸውን ከጠራርጉ በኋላ ከየት እንጀምር ብለው ጥያቄ በማቅረብ፣ እዚያው  ካለንበት ነው መነሳት ያለብን በማለት ለልጃቸው ያስረዷታል። በመቀጠልም ችግራችንን ለመቅረፍና ስልጣኔንም ለማምጣት የግዴታ ያለንበትን ሁኔታ በሚገባ ማወቅ እንደሚያስፈልግና፣ ያለፈውን ትውልድም እንደተጠያቂ ማድረግ እንደማይቻል ደራሲው እንደ አቶ ኦላና በመመስል ልቆ በሄደው አስተሳሰቡ እጅግ በሚያሰደንቅ አገላለጹ ዕድገት ከየት መጀመር እንዳለበትና፣ ምንስ መመስልና ወዴትስ መጓዝ እንዳለበት ያስተምረናል። ስለዚህም ይላል ደራሲው፣ በአቶ ኦላና በመመሰልና ኋላ-ቀርነትና የጎታች ባህልን የዕድገት ጠንቅነት እያመለከተ፣ „ በየትኛውም ሥልጣኔ ውስጥ ፈር ቀዳጅና ፋና ወጊ ተብለው ለውጥ ያመጡ ሰዎች መጀመሪያ ወንጀለኛ፣ ከዚያም አሳሳች ተብለው መፈረጃቸው የተለመደ ነው። በእርግጥም እነዚህ ጥቂት ብርቅዬ ከዋክብት ከህብረተሰቡ በሰላሳና በአርባ ዐመት ቀድመው ወደፊት የሄዱ ስለሆነ ከሰው አይገጥሙም፤ ሰው አንድም ባለበት ስለሚረግጥ አንድም የኋልዮሽ እንጽርት ጨዋታ ላይ ስለሚባትል እነሱን ይፈራቸዋል፤ ስለዚህም ይጠላቸዋል። ምንም እንኳ እንደ ዕውነት ፀርና አሳች መሲህ ቢታዩም በሚቀጥለው ትውልድ ግን ሁሌም ብሩህ ከዋክብት ተብለው ይሞገሳሉ፤ የመታሰቢያ ሐውልትም ይሰራላቸዋል።“  በማለት አቶ ኦላና ከልጃቸው ጋር ያደረጉትን የሃሳብ መለዋወጥ ይነግረናል። ይህ አገላለጹ በሶፊስቶች በውሸት ተወንጅሎ  መርዝ እንዲጠጣና እንዲሞት የተፈረደበት ሶክራትስን፣ ወደ እስር ቤት የተወረወረውን ጋሊሌዮንና፣ እንዲቃጠል የተደረገውን ታላቁን የሬናሳንስ ምሁር ጊዮርዳኖ ብሮኖን ሁኔታ ያመለክተናል። ሁልጊዜም ለዕውነት የሚታገል በመጀመሪያ አሳሳቸ በመባል የውሸት ወሬ እንደሚነዛበትና እንዲጠላ የሚደረገውን ሁኔታ ቁልጭ አድርጎ ደራሲው ያስረዳናል። ስለዚህም ይላል ደራሲው፣ የስልጣኔ ፈር ወዳጆች ጥቂቶች ሲሆኑ የሚቀጥለው ትውልድ ተግባር ያንን በመመርኮዝ፣ በማስፋፋትና በማዳበር ዕምርታ በመሰጠት ህብረተሰብአዊ ለውጥ መምጣት እንደሚችል ነው። ለዕውነተኛ ስልጣኔ የሚታገል በምንም ዐይነት በስም አጥፊዎችና ሰውን በሀሰት በሚከሱ መደናገጥና የስልጣኔውን መንገድ ለቆ መውጣት እንደሌለበት ደራሲው ያመለክታል። ዕውነት ለጊዜው ብትዳፈንም አንድ ቀን ግን ባሸናፊነት በመውጣት ውሽት ነዢዎችን እርቃናቸውን እንዲቀሩ ማድረጓ በታሪክ የተረጋገረጠ ነው። ዛሬ በቴክኖሎጂ የተራቀቁና ዓለምን የሚቆጣጠሩ አብዛኛዎቹ የምዕራብ አውሮፓ የካፒታሊስት አገሮች እዚህ ዐይነቱ የተወሳሰበና የአደገ ሁኔታ ላይ ሊደርሱ የቻሉት የአሰተሳሰብ ለውጥ በማድረጋቸው ሲሆን፣ የጭንቅላት ተሃድሶ ለማግኘትና የተፈጥሮን ህግ ለመረዳትና የነበሩበትን የጨለማ ሁኔታ ለመለወጥ ሶስት መንፈስን የሚያድስ መንገድ እንደተጓዙ ደራሲው ቁልጭ ባለ መልክ ያስተምረናል። በእሱም አገላለጽ፣ ሬናሳንስ ወይም የግሪኮችን ዕውቀት መልሶ ማግኘትና በሱ ላይ በመመርኮዝ የስልጣኔውን ፈር መቅደድ፣ ሬፎርሜሽን ወይም በሃይማኖት አካባቢ የተደረገው የአስተሳሰብ ለውጥና ይህም ለካፒታሊዝም መነሳትና ማደግ አንደኛው መንገድ መሆኑና፣ ከዚህም ባሻገር ኢንላየትሜንንት በመባል የሚታወቀው ሰፋ ያለ ምሁራዊ እንቅስቃሴ፣ እነዚህ ሶስቱ ደረጃ በደረጃ ለአውሮፓ ህዝብ ዕድገት መንገዱን ያሳዩት እንደሆኑ ደራሲው በደንብ ያስቀምጣል። ከዚህ ስንነሳ በአንዳንድ ኢትዮጵያውያን ኢኮኖሚስቶች የገበያ ኢኮኖሚ አማራጭ የሌለው የዕድገት ትክክለኛው መሳሪያ ነው የሚለውን የተሳሳተ አመለካከት መሆኑን ዶ/ር ምሀረት በግሩም ብዕሩ ሳይንሳዊ  በሆነ አቀራረብ ያስተምረናል።

ሰሎሜ ወንድሟን ለማስታመምና የጤንነቱን ሁኔታ ለመከታተል ወደ አሜሪካ ተመልሳ ከሄደች በኋላ እዚያው ለረጅም ጊዜ ትቆያለች። በመጀመሪዎች ሳምንታትና ወር በየጊዜው ኢ-ሜይልም ሆነ ስልክ ከመላኩ ጋር ይጻጻፉና ይደዋወሉ ነበር። መላኩም ስንክሳር ልምትባለው የሰሎሜ ጓደኛ ወደ አሜሪካ ስትሄድ ለሰሎሜ ቆሎና ደብዳቤም ይልክላታል። ይሁንና ግን ስንክሳር የደብዳቤውን ምስጢር ለማወቅ ስትል ቺካጎ ከደረሰች በኋላ ለራሷ በማስቀረት እንደጠፋባት ለመላኩ ትነግረዋለች።  በአንድ በኩል  ሰሎሜ አንድም በወንድሟ በሞትና በሽረት ላይ መገኝትና በደረሰበትም ከፍተኛ አደጋ በሀዘን ላይ በመውደቋ፣ በሌላ ወገን ደግሞ እንደ ቤተሰብ እዚያው ቤታቸው ውስጥ ጉድ ጉድ ከሚለው ክብሮም የሚባለው የኩላሊት ሀኪሙ ጋር ግልጽ የሌለው ግኑኝነት ይጀምራሉ። አልፎ አልፎም ለብቻቸው እየተገናኙ ይገባበዛሉ። እንደገና ቺካጎ ከተማ ውስጥ ለረጅም ወራት እንድትኖር የተገደደችው ሰሎሜ በመላኩና በክብሮም መሀከል መዋለል ትጀምራለች። በአንድ በኩል መላኩን ከልቧ ትወደዋለች፤ በሌላ ወገን ደግሞ በጠባዩ ቀለስለስ የሚለውን ክብሮምንም ላለማስቀየም ትሞክራለች። መላኩ ሰሎሜ ወደ ቺካጎ ከሄደችና እዚያም ለረጅም ጊዜያት እንድትኖር ከተገደደች ወዲህ በአስተሳሰቡ ብዙም ተለውጧል። በሃሳብ ከመዳበሩና ከመደንደኑ የተነሳ የመጀመሪያ ፍቅረኛው ልባዊ ፍቅር ማሳየት ስላልቻለ ወደ ካናዳ ጥላው ከሄደች በኋላ ግራ የተጋባው መላኩ ራሱን መልሶ መላልሶ የሚጠይቀው የመጀመሪያው ጓደኛው ለምን ጥላው እንደሄደች ነው። እሷንም በክርክክርና በሙጉት ለማሳመን ያደረገው ሙከራ ሁሉ የባሰውን እንዳራቃትና፣ ሌላ ሰው እንድትወድ እንደተገደደች ደራሲው ይነግረናል። ይህ በእንደዚህ እያለና በመላኩና በሰሎሜ መሀከል የነበረው የጠበቀ ግኑኝነት ወደ መላላቱ በማምራቱ፣ የቤተሰቦቹና በተለይም የአባቱ ሁኔታ የሚከነክነው መላኩ ከስራ ፈቃድ በመውሰድ ለመፈለግ ሲል ወደ መቂ ከተማ ያመራል። ወደ መቂ ከሄደ በኋላ አንድ ሆቴል ቤት ውስጥ ካረፈ በኋላ  አንደ ሆቴል ቤቱ ውስጥ በሚሰሩ ሴት አማካይነት ሁኔታውን ካጣራ በኋላ አብረው ያፈላልጉታል። የመጨረሻ መጨረሻም አክስቱንና የእህቱን ልጆች ሁሉ ያገኛቸዋል። የሚኖሩበትንም ሁኔታ ሲያይ በጣም ያዝናል። እንደ አጋጣሚ ከቤተሰቦቹ ጋር የተገናኘው የበዓል ዕለት ስለነበር አንዱን ልጅ ወደ ገበያ ይዞ በመሄድ በግ ገዝቶ  አምጥቶና አሳርዶ ያሽመነምናቸዋል። በረሃብና በችግር ሲሰቃዩ የኖሩትን ቤተሰቦቹን ደስታ በደስታ ያደርጋቸዋል። መላኩም ቀኑ ከመሸ በኋላ እዚያው ቤት ሲያድር ቁንጫና ትኋን በሰውነቱ ላይ እየደነሱበትና ደሙን እየመጠጡበት እንቅልፍ ያሳጡታል። አስተዋዩና አርቆ አሳቢው መላኩ በዘመዶቹ ላይ የሚደረሰውን፣ ከሃሳብ ድህነት የመነጨ ድህነትና ጉስቁልና እንዲሁም እጅግ አስቀያሚ ኑሮ ከጠቅላላው የኢትዮጵያ ህዝብ የኑሮ ሁኔታ ጋር በማገናኘት ይከነክነዋል። ጥቂት ቀናት እዚያ ከቆየ በኋላ ወደ አዲስ አበባ ለመመለስ ይወስናል። በመጀመሪያ ግን መኪናውን ወዳቆመበት ወደ ሆቴል ቤቱ ጋ ከአክስቱ ትልቋ ልጃቸው ከመዐዛ ጋር ተያይዘው ይሄዳሉ። ከመሄዱ በፊት እዚያ ተቀምጠው አንዳንድ ነገር አዘው በመጠጣት ላይ እያሉ መዐዛ አንድም በደስታ በመዋጧ፣ በሌላ ወገን ደግሞ መላኩ እስኪመጣ ድረስ እሷና ልጆቿ እንዲሁም እናቷ በከፍተኛ ችግር ላይ ወድቀው እንደነበርና፣ ልጆቿንም መመገብ ባለመቻሉ የመጨረሻ መጨረሻ የአይጥ መርዝ ጠጥታ ለመሞት መርዙን ገዝታ በመወሰንና ባለመወሰን ላይ እንዳለች መላኩ እንደደረሰላቸው ስቅቅ ብላ ታለቅሳለች። ቀደም ብሎ ግን መላኩ ለአክስቱም ሆነ ለመዐዛ ልጆች ገንዘብ ይሰጣቸዋል። ታሪኳን ከመናገሯም በፊት አምስት ሺህ ብር ያህል ይሰጣታል። እሱን ከሸኘች በኋላ ወደ ቤት በመመለስ ከእንግዲህ ወዲያ መላኩን በማስጨነቅ መኖር እንደሌለባቸው በመረዳት ገንዘቡን ሁሉ በመሰብስብ ንግድ ለመጀመር ቆርጣ ትነሳለች፤ በዕቅዷም በመግፋት ስኬታማ ትሆናልች። በየጊዜው በዕርዳታ መኖር እንደሌለባትና በትንሽም ገንዘብ ራሷን መለወጥ እንዳለባት በመረዳት የማሰብ ኃይል እንዳላት ታረጋግጣለች። መላኩም በአንድ በኩል ዘመዶቹን ለመርዳት በመቻሉና ከድህነት የሚወጡበትንም ሁኔታ በማመቻቱ ደስ ሲለው፣ በሌላ ወገን ደግሞ  እናቱ እሱን  አክስቱ ጋ ጥላ ብትሄድ ኖሮ ሊደርስበት የሚችለውን ሁኔታ ማውጣትና ማውረድን ተያያዘው። ብዙ አሰበ። ምናልባትም የኤይድስ ሰለባ ሆኖ ዕድሜው በለጋ ወጣትነቱ ይቀጭ እንደነበር ቁልጭ ብሎ ታያው። ካሊያም ሹፌር በመሆንና ትልቅ መኪና በመንዳትና ቤተሰብ በመመስረት ብዙ ልጆች ወልዶ አስቸጋሪ ኑሮም እንደሚኖር ታየው። እንድ አጋጣሚ የዶ/ር ሳራ እናት ባያገኙትና ባያስተምሩት ኖሮ ይህንን ያህል ደረጃ ላይ መድረስ እንደማይችል መገንዘብ ቻለ። ይህም በመሆኑና ጥሩ መንፈስም ስላለውና ጭንቅላቱም በፍልስፍና የተገነባ ስለሆነ ቤተሰቦችን ሳይረሳና ሳይንቅ ለመፈለግ መሄዱና እነሱንም መርዳት መቻሉ እያንዳንዱ የተማረ እንደሱ ማሰብ ቢችል የቱን ያህል ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ታየው። ይህ ዐይነቱ አስተሳሰብ የደራሲውን የላቀ የጭንቅላት መዳበርና ለአገርና ለህዝብ ማሰብ የሚያመለክት ነው። በዚህ መልክ እያንዳንዱ ዕውቀቱን ቢያገናኝና የማሰብ ኃይሉንም ካዳበረና ለወገኑ የሚያስብ ከሆነ ለውጥ በውጭ ዕርዳታ ሳይሆን ከውስጥ በራስ የማሰብ ኃይል ብቻ ሊመጣ እንደሚችል የኖይሮ-ባዮሎጂው ምሁርና ሃኪም፣ እንዲሁም በታሪክና በፍልስፍና ጭንቅላቱ የዳበረው ታላቅ ምሁር ድ/ር ምሀረት ከበደ ስለድህነት ዋናው ምክንያትና እንዴትም መፈታትና በአራት እግር መቆም እንደሚቻል በሚገባ ያስተምረናል።

የመላኩና የሰሎሜ ግኑኝነት ያልተቋጨ ፍቅር በነበረበት ሁኔታ ውስጥና፣ በመሀከላቸው የነበረውን መፈላለግ ለማፍረስ ተንኮል የምትሸርበው ስንክሳር አመቺ ጊዜን በምትጠባበቅበት ወቅት የስሎሜን ወንድምም ሶለን ከአደጋው ለመትረፍ ባለመቻሉ ከዚህ ዓለም በሞት ይለያል። ይህ በእንደዚህ እንዳለ እንደ እናት ሆነው ያሳደጓት ልጅ ዶ/ር ሳራ ከባሏና ከሶስት ልጆቿ ጋር የባሏን ቤተሰቦች ለመጠየቅ ለእረፍት ወደ አዲስ አበባ ይመጣሉ። ዶ/ር ሳራም በጣም ስለደከማት ያንኑ ዕለት የባለቤቷ ቤተሰቦች ጋር መሄድና ማረፍ ባለመፈለጓ ለጊዜው ሆቴል ቤት ውስጥ አረፉ።  የዶ/ር ሳራ ባል በራሱ ስሜት የሚነዳ ስለነበር ለባለቤቱና ለልጆቹ ደንታ ሳይሰጥ አብዛኛውን ጊዜውን ከድሮ ጓደኞቹ ጋር ነው የሚያሳልፈው። በሁለቱም መሀከል የነበረው ፍቅር የሻከረ ስለነበር ደራሲው እንደሚለን የመባለጊያ የወረቀት ፈቃድ የሰጠቺው ይመስል የትም እያደረ ነው የሚመጣው። ስለሆነም የህሊና ሳይንስ ሃኪም የሆነችው ዶ/ር ሳራ አብዛኛውን ጊዜዋን ከልጆቿና ከመላኩ ጋር ነው የምታስልፈው። አንደኛው ልጃቸውም ኦቲዝም(Autism) በሚባል የአዕምሮ መሰናክል የሚሰቃይ ስለሆነና፣ ከፍተኛ ክትትልም ስለሚያስፈልገው ዶ/ር ሳራ ከልጇ በፍጹም አትለይም። ጊዜዋን በተለይም ከአንድ ልጇ ጋር የምታሳልፈው ዶ/ር ሳራ ከመላኩም ሆነ ከመላኩ ጓደኛ ማርቆስ ጋር እየተዘዋወሩ በከተማ ውስጥም የተሰሩትን አዳዲስ ህንፃዎችና የአማኑኤልንም ሆስፒታል መጎብኘት ደስ ይላታል። በተለይም የአማኑኤልን ሆስፒታል ስትጎበኝ የምታነፃፅረው አሜሪካን ካሉ ካማሩና በአንድ ሆስፒታል ውስጥ ከመቶዎች በላይ የሚገኙበት ሃኪሞችና ነርሶች እንዲሁም ድሬሰሮች ጋር ነው። በተለይም የአማኑኤል ሆስፒታል መርካቶ ውስጥ መሆኑ ነገሩ ይከነክናታል። እንደዚህ ዐይነት ሆስፒታል እንደዚህ ዐይነት ቦታ መሰራት ያለበት ሳይሆን ወጣ ያለና፣ አካባቢውም ሆነ ግቢው በአማሩ ዛፎችና አበባዎች፣ እንዲሁም የሰውን ጭንቅላት በሚያድሱ መናፈሻዎችና መቀመጫዎች ማማርና መሰራት የነበረበት እንደነበር ለማስረዳት ትሞክራለች። ስለሆነም ሃሳቧ ስለዚህ ሁኔታና ስለጭንቅላት ህመምና በተለይም ደግሞ ስለ ኦቲዝም ምንነት በዩኒቨርስቲው የነርብ ህክምናና የህፃናት ክፍልና ሆስፒታል ውስጥ ሰሚናር ለመስጠት አቀደች። በቴሌቪዝንም ተጠይቃ ስለኦቲዝም ሰፊ ማብራሪያ ሰጠች። ቃለ-መጠይቁንና ገለጻዋን በተሌቪዝን የተመለከተው ባላቤቷ ይዘዙኝ ልቀቁኝ ማለት ጀመረ። ባለቤቷ ወያኔን የሚጣላ በመሆኑና እሷም በአባቷ ትግሬ ስለሆነች የባሰውኑ ወያኔን ሆንሽ አይደለም ብሎ ጮኸባት። ምንተስኖት አሜሪካን አገር በኢንተርናሽናል ዴቬሎፕሜንት የሰለጠነ ቢሆንም ይህንን ያህልም የዳበረ ጭንቅላት የለውም። በራሱ ስሜት የሚመራና አርቆ የማሰብ ኃይሉ ውስን ነው። ስለሆነም የነገሮችን ሄደት ሳያጤን ቶሎ ብሎ ወደ ጠብ ያመራል። ከሱ ዕምነት ውጭ ያለውን እንደ ጴንጤ ቆንጤ የመሰለውን ሃይማኖት ፈረንጆች ሆን ብለው የሰውን ጭንቅላት ለማደንዘዝና የጥቁርንም ህዝብ ተገዢ ለማደረግ የፈጠሩት ሃይማኖት ነው ብሎ ስለሚያምን ከመላኩ ጋር፣ መላኩ የጴንጤ ቆንጤን መዝሙር ሲያዳምጥ ሲሰማ በመብገን ግጭት ውስጥ ሊገባ ቻለ። መላኩም ረጋ ባለ መልክ መዝሙሩ የጴንጤ ቆንጤ በመሆኑ ወይስ ጠቡ ከሃይማኖት ጋር  ነው? ብሎ በመጠየቅ፣ የኦርቶዶክስም ሃይማኖት እንደዚሁ የራሱ መዝሙር እንዳለውና በአጠቃላይ ሲታይ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት በታሪክ ሂደት ውስጥ ብቅ ያለና የጥንት አባቶቻችንም ተገደው የተቀበሉትና እንደ ዕምነትም የወሰዱት እንደሆነ በጥሞና ያስረዳዋል። የመላኩን የበሰለና ረጋ ያለ ክርክር ያዳመጠው ምንተስኖትም በመገረም  ወደ ጠብ ሳያመራ በውይይት ብቻ በመሀከላቸው ያለውን ልዩነት ለማብረድ እንደቻሉ ደራሲው ግሩም በሆነ መልክ ያስረዳዋል።

ይህ በእንደዚህ እንዳለ መላኩ ወደ ዱባይ ለስብሰባ ከመሄዱ በፊት ከሳራና ከቤተሰቦቿ ጋር በየጊዜው እየተገናኙ ከተማውን ያሳያታል።  በተለይም በአገራችን ውስጥ ያለውን ጭንቅላት ላይ የሚከሰት በሽታ ሁኔታ ለማከም አንድ ማዕከል ለማቋቋም እንዳሰበች ለመላኩ ታስረዳዋለች። እንደ ኦቲዝም የመሳሰሉት የጭንቅላት መዛባቶች ቢኖሩም ችግሩ በደንብ የታወቀና በዚህም መስክ ስፔሽያላይዝ ያደረገ እንደሌለና፣ ህክምናም እንደማይሰጥ ደርሳበታለች። በመሆኑም ዕቅዷን በዝርዝር ለመላኩ ትነግረዋለች። መላኩም የሷን ቀና አስተሳሰብ በደንብ ካዳመጠ በኋላ ስለ ኦቲዝም ማለት ምን ማለት እንደሆነ እንድታስረዳው ይጠይቃታል። ዶ/ር ሳራም የመላኩን ጥያቄ ካዳመጠች በኋላ በጥሞና ጥያቄውን በሚከተለው መልክ ታስረዳዋለች። „ ኦቲዝም አንድ በሽታ ነው ማለት አይቻልም። በአጠቃላይ ተመሳሳይ መግለጫ ያላቸው ከአዕምሮ ዕድገት መዛባት ጋር የተያያዙ ችግሮች የጋራ ስም ነው። ኦቲዝም የሚለው ስም `አውቶ´ ማለትም የአንድ ሰው እኔነት (ራስ ) ከሚለው ቃል የወጣ ሲሆን፣ ኦቲዝም የተባለበት ምክንያት ይህ ችግር ያጋጠማቸው ሕፃናት አብዛኛው ዓለማቸው በራሳቸው ውስጥ ስለሚሽከረከር ነው። አሁን አየህ አዕምሮው በትክክል የሚሠራ ሰው ውስጣዊውንና ውጫዊውን ዓለም አመጣጥኖ ነው የሚኖረው። ኦቲዝም ያለባቸው ሕፃናት ግን ልክ ሳጥን ውስጥ እንዳለ ሰው ብዙውን ጊዜ የሚያሳልፉት በራሳቸው ጭንቅላት ውስጥ ነው። ከዚህም የተነሳ ለሰው ግራ የሚያጋባና ለመረዳት አስቸጋሪ የባህርይ፣ የቋንቋና የማህበራዊ ግኑኝነት ጉድለቶች ይታዩባቸዋል። ደግሞም በአብዛኞቹ ላይ የአዕምሮ ዝግመት ይከሰታል። እንደባቢዬ(ልጇ) በጣም የከፋ የአዕምሮ ዝግመት ያለባቸው ከሆነ፣ ህመሙን የበለጠ የከፋ ያደርገዋል። ሁሉም  ልጆች በሁሉም አቅጣጫ በተመሳሳይ ደረጃ ጉድለት ስለማይኖራቸው፣ ኦቲዝም ያለበት እያንዳንዱ ልጅ አንድ ሊሆን አይችልም።“ በማለት በሚገባ ታስረዳዋላች። የሷን ልጅም አድራጎትና ከአንድ አሻንጉሊት ጋር ብቻ መጫወት የተመለከተው መላኩ ለምን ከአንድ ነገር ጋር ብቻ አንደሚጫወት፣ ለምን ሌላም ነገር እንደማያሳኘው አጥብቆ ይጠይቃታል። የሷም መልስ፣ በአጠቃላይ ሲታይ ኦቲዝም ያለባቸው ህፃናት በራሳቸው ዓለም ወስጥ ስለሚኖሩ ለውጥ እንደማይፈልጉና፣ ለየት ያለ ነገር ሁሉ እንደሚረብሻቸው በጥሞና ታስረዳዋለች። ለምሳሌ ብርሃንና ለየት ያለ ድምጽ ይረብሻቸዋል በማለት ኦቲዝም ያለባቸውን ህጻናት ችግር ነገረችው። በመቀጠልም ዶ/ር ሳራ ስለ ኦቲዝም ምንንነትና በሚያድጉና በያዛቸው ህፃናት ላይ ያለውን ዘለዓለማዊ ጠንቅነትና፣ ራስን ችሎ አለመኖር ያደረገለችነትን ገለጻ  ካዳመጠ በኋላ ወደ ቤቱ መኪናውን እየነዳ ሲሄድ የህብረተሰቡ ኋላ-ቀርነትና በምድር ላይ የሚታየው መዝረክረክ የሚቆጨውና ግራ የገባው መላኩ፣ በህፃናትም ላይ የሚታየው ኦቲዝም በህብረተሰቡ ላይ እንደሚታይ መላምት ነገር ታየው። የህብረተሰቡን በስነስራዓት አለመደራጀትና የከተማውን ዕቅድ-የለሽ አሰራርና ቆሻሻነት አጥብቆ የተመለከተውና ሁሌም የሚቆጨው መላኩ ዶ/ር ሳራ ያስረዳቸው ሁሉ ፊቱ ላይ በመደቀን፣ በኦቲዝም የሚሰቃዩና ዘለዓለማዊ ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው ህፃናት አንድን ወደ ኋላ የሚጎተት ህብረተሰብ መግላጫ ምላ ምት ሊሆኑ እንደሚችሉ ተገነዘበ። አንድ ጭንቅላቱ በደንብ ያልዳበረ፣ ሎጂካዊ አስተሳሰብ የሌለውና በተወሳሰበ መልክም ማሰብ የማይችል ሰውና ህብረተሰብ ልክ ኦቲዝም እንደያዘው ህፃን ነው ብሎ ገመተ።  ስለሆነም አንድ ህብረተሰብም ሆነ ግለሰብ በበቂው በሰለጠኑና ፍልስፋናዊ አመለካከት ባላቸው አዋቂዎች ካልተደገፈና ቴራፒም ካላገኘ ዘለዓለሙን ደሃና ተመጽዋች ሆኖ እንደሚኖር ተሰማው። መላኩም የአገራችንና የሌሎች የአፍሪካ አገሮችን ችግር ከኦቲዝም ጋር በማመሳሰል እንዲህ ብሎ ይገልጸዋል።  „በእርግጥ በአፍሪካውያን ድምር አስተሳሰብም ላይ ኦቲዝም ያልተለየ ዝብርቅርቅ ያለ ዕድገትና የአስተሳሰብ መዛባት ያለ መሆኑ አይካድም። አኗኗራችንም የኦቲዝም አዕምሮ ከሚፈጥረው አኗኗር ብዙም ርቆ አልታየም። በእርግጥ ኦቲዝም ያለበት ልጅ ችግሩን ማወቅም ማመንም እንደማይችል፣ የኛም ማህበረሰብ ለዚህ ከኦቲዝም እጅግ ለማይለየው የአስተሳሰባችን በሽታ የነቃ አይመስልም።የህዝብ አስተሳሰብና አመለካከት በትክክል ካልዳበረና ካልተቃኘ ማህበራዊ ኦቲዝም ሊከሰት እንደሚችል ገመተ„፤ በማለት የኖይሮ ባይሎጂ አዋቂና የፍልስፍና ተመራማሪው ምሁር ዶ/ር ምህረት ደበበ በመላኩ በመመሰል የህብረተሰባችንን ውስን የማሰብ ኃይልና፣ ችግሩንም ለመቅረፍና ውበትና መልክ ለመስጠት አለመቻል በሚገባ መልክ ከኦቲዝም ዐይነቱ የአዕምሮ መዛባት ጋር ሊመሳሰል እንደሚችል ያስተምረናል። ይህ የአዕምሮ መዛባትና ራስን ለማወቅ አለመቻል በተማረውም ሆነ ባልተማረው፣ እንዲሁም ስልጣንን በጨበጡና ባልጨበጡ መሀከል ያለ አጠቃላይ ህብረተሰብአዊ ክስተት መሆኑን ደራሲው በሚገባ ያብራራል። መላኩም ስለኦቲዝም  ምርምርና መፍትሄም ለማግኘት የሚደረገው ርብርቦሽ በብዙ ውስብስብ ችግሮች የሚሰቃየው ህብረተሰባችንም እንደዚሁ እንደ ኦቲዝም ሰፊ ጥናት ማካሄድ የሚችሉና የህብረተሰብም ዕድገት ምን መምሰል እንዳለበት ምርምር ባደረጉና በሚያደርጉ የሰለጠኑ ምሁራን መመርመርና መፍትሄ ማግኘት እንዳለበትና፣ ይህም እንደሞዴል እንደሚያገልገል አሰበ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  አማራ የተሰጠውን ዕድል እንደማያበላሽ ተስፋ አደርጋለሁ!! - አምባቸው ዓለሙ (ከደሴ)

መላኩም ለሰሚናር ወደ ተባበሩት ኤምሬትስ በመሄድ እዚያ በቆየበት ጥቂት ቀናት በአገሪቱ ውስጥ ያለውን ዕድገትና ንጽህና ይመለከታል። ይሁንና የነሱ ዕድገት ከዘይት ሀብት ጋር የተያያዘ ቢሆንም ገንዘባቸውን በስነ-ስራዓት ስለሚጠቀሙበት ከምዕራቡ ቴክኖሎጂን በመግዛት ዕድገትን ሊቀዳጁና ለአገሮቻቸውም ውብትን ለመስጠት እንደበቁ መላኩ በሚገባ ይመለከታል። መላኩ ይህንን ሁሉ ከተመለከተና፣ የማሰብ ኃይላቸውም ወደፊት ቀስ በቀስ በመለወጥ ከአውሮፓ አገሮች ጋር በጊዜ ሊደረሱ እንደሚችል በማውጠንጠን የሌሎችን የአፍሪካን አገሮችንና የኛን ህብረተሰብ ችግር ግራ መጋባት በዚህ መልክ ይገልጸዋል።  „ የሥልጣኔ ትልቁ መለኪያ ገንዘብ ሳይሆን ለሰው ልጅ ያለን ክብርና እውነተኛ ሰብአዊነት ነው። አፍሪካውያን ግን ገና የራሳችንንም ህዝብ ያላከበርን፣ ዓለማችን ኪሳችን፣ መለኪያችን ድሎታችን የሆንን ስለሆነ፣ ብዙ መንገድ መሄድ ሳይኖርብን አይቀርም። መሪዎቻችንም የኛው ውጤት ስለሆኑ ምርጫውን አሸንፈው እስከ ቤተ መንግስት ቢደርሱም ራሳቸውን ማሸነፍ ሳይችሉ በሌላ ይተካሉ። ከራሳቸው በላይ ህዝባቸውን፣ ከምቾታቸውም በላይ መጭውን ትውልድ ማስበለጥ እስኪችኩ ያለወታደር አደባባይ መውጣት የማይችሉ እንደባነኑ የተኙ፣ እንደ ተጆሩ የመስከኑ ነገሥታት ሆነው ይቀራሉ„። በማለት የአፍሪካውያን መሬዎችን አስተሳሰብ ቁልጭ አድርጎ ያሳየናል።

መላኩም ዱባይ ሆኖ ተንኮለኛዋ ስንክሳር ከደወለችለትና፣ ሰሎሜ ከክብሮም ጋር ያላትን ወደ ዕውነተኛ ፍቅርና ግኑኝነት ያልተመነዘረ የውሸት ወሬ ከነገረችው ጀምሮ ህልሙ ወደ ቅዠትነት ተለውጧል። ይህ በእንደዚህ እንዳለና አዲስ አበባ ከተመለሰ በኋላ እንደገና መቂ ያሉትን ቤተሰቦቹን ለማየት ወደዚያው ከቀርብ ጓደኛው ማርቆስና ወደ አዲስ አበባ በመምጣት አንድ ፈረንጆች ባቋቋሙት የፌስቱላ ሆስፒታል ውስጥ ገብታ መስራት የጀመረችው የሶለን ጓደኛ ከነበረችው ከሶፊያ ጋር ሆነው ወደዚያ ያመራሉ። መቂ ከደረሱና ጥቂት ቀናት በቆዩበት ጊዜያት ውስጥ በመላኩ ርዳታ የአክስቱ ልጅ መዐዛና ቤተሰቦቿ የቱን ያህል ለውጥ እንዳመጡ ይገነዘባል። መላኩም ሆነ ማርቆስ በመዐዛ አርቆ አሳቢነትና ታታሪነት፣ እንዲሁም በአጭር ጊዜ ውስጥ ንግድ ጀምራ መሳካቱንና ሌሎች ሰዎችንም ቀጥራ ማሰራት በመቻሏ በብልሀነቷ ይደነቃል።

መላኩ ወደ አዲስ አበባ ከተመለሰ በኋላ ወደ አሜሪካን አገር ስልጠና ከመሄዱ በፊት የአባቱ ነገር እረፍት አልሰጠው ስላለ ወደ አፋር ለመሄድና ለመፈለግ ጉዞውን ይጀምራል።፡ ከአንድ ሹፌር ጋር በመሆን ወደ አፋር ያመራል። ደብረዘይት ደርሰው ምሳ ከበላሉ በኋላ ጉዞአቸውን በመቀጠል ወደ አፋር ከመድረሳቸው በፊት አዋሽ ወርደው ፓርኩን ያያሉ፤ አዋሽም ለማደር ይወስናሉ። ከአዋሽ ስባት ይልቅ፣ አዋሽ አርባ ለማደርና ትንሽም ለመዝናናት ሰለመረጡ ወደዚያ ሲነዱ አንድ በጨአት የመረቀ ሊፍት ጠይቆአቸው ይወስዱታል። በመንዳት ላይ እያሉ ሰውየው ዐይኖችቹ በጨአት መቃም የተመረዙና የሚቆጣም ፊት ያለው ስለሚያስመስለው መላኩ ሊጠይቀው ፈልጎ ነገሩን ሳብ ያደርጋል። ይህንን ሲመለከትና በአካባቢው ዝም ብሎ የሚንገላወተውን ሰው ሲመለከት ካለመስራት ሊመጣ የሚችለውን የጭንቅላት መቦዝና አጠቃላይ ስንፍና ማውጣት ማወረድ ይጀምራል። ጨአትም በህሊና ላይ ያለውን ከፍተኛ አሉታዊ ነገር ማሰላሰል ይጀምራል። በተከታታይ ጫት የሚቅም ሰው በውስጡ ባሉ ካቲኖንና ካቲኖል በሚባሉ ኬሚካሎች ጭንቅላቱ ስለሚመረዙና ሱሰኛም ስለሚሆን ቃሚው ጨአት ካላገኘ በስተቀር በፍጹም የማሰብ ኃይሉ እንደሚዳክምና ለስራ ያለውም ፍላጎት በጣም እንደሚቀዘቅዝ ይረዳል። በአዋሽ ያየውንና የተገነዘበውን ከጠቅላላው ከአገሪቱ ሁኔታ ጋር ያገናዝባል። አንዳንድ ቡና ቤቶችም ወደ ጨአት መቃሚያነት የተለወጡበትንና፣ ሴቱም ሆነ ወንዱ የጨአት ሰለባ በመሆን ከፍተኛ የህሊና ቀውስ ውስጥ እንደሚገኙ ይረዳል። የደረሰበትም ድምደማ ይህ ጉዳይ ታስቦበት ህጋዊ እርምጃ መወሰድ እንዳለበትና መከልከልም እንዳለበት ማውጣት ማውረድ ይጀምራል። በዚህ መልክ የአገሪቱ ችግሮች የተወሳሰቡና ልዩ ልዩ ገጾች ሲኖራቸው፣ ይህም በነቃና ሀብረተሰብአዊ ኃላፊነት በሚሰማው መንግስት መፈታት እንደሚችልና፣ እንደዚህ ዐይነቱ ትንሹንም ሆነ ትልቁን፣ ሴቱንም ሆነ ወንዱን ሰለባና ቁራኛ ያደረገ ዕፅ በህግ ካልተከለከለና ህብረተሰብአዊ መፍትሄ ካልተገኘለት የአገሪቱና የመጪው ትውልድ ዕጣ ምን እንደሚሆን ታየው። ካረፈበት ሆቴል ወጣ ብሎ ትንሽ ለመዝናናት ሲል በአካባቢው የቆመውን የትላልቅ መኪና ጉድ ይመለከታል። እነዚህ የኤይድስ በሽታ ምንጮች መሆናቸውንና፣ በዚህ መልክ ስንት ወጣት ሴቶች ህይወታቸው እንደተበከለና እንደተበላሸ ያወጣል ያወርዳል። በነጋታውም ጉዞአቸውን ወደ አፋር በመቀጠል ሲሄዱ አንዱ የአፋር መንገደኛ ሊፍት ሲጠይቃቸው ሹፌሩ አለመስማማተቻውን ይገጻልሉ። ምክንያቱም በዚያ ያለ ሰው ዝም ብሎ መኪና ሴሄድ ሊፍት የሚጠይቅና የሚሄድበትን ስለማያወቅ ዝም ብሎ የሚሳፈር ነው ብለው ሹፌሩ አለመስማማታቸውን ይነግሩታል። አንዳንዱም ሊፍት ከተሰጠው በኋላ  የሚሄድብትን ስለማያውቅ ውረድ በሚባልበት ጊዜ ጠብ እንደሚፈጥር ሹፌሩ ያጋጠማቸውን ችግርና የቀሰሙትን ልምድ ለመላኩ ይነግሩታል። መላኩም በሹፌሩ ሃሳብ በመስማማት መንዳታቸውን ይገፉበታል።  ጎዞአቸውንም በመቀጠልም የመኪናውን ጋጋታና የመንገዱን መበላሸት ይመለከታል። መንገዶቹ በቅርብ ጊዜ የተሰሩም ቢሆንም፣ ከመኪናዎች ክብደት ጋር እየተመጣጠኑ ባለመሰራታቸው ወዲያውኑ በመበላሸት ለመንዳት የሚያሰችግሩና ለአደጋም የሚያጋልጡ ሆነው ያያቸዋል።

መላኩ ከሹፌሩ ጋር ሆኖ ጉዘውን በመቀጠል በህይወቱ ዘመን ያላየውን በዕቅድ ያልተሰሩና ዝም ብለው ብቻ መንገድ ላይ ቁጥጥ ያሉትን ቤቶች ይመለከታል። ሰውም ሆነ ከተማዎች የሰውነትና የከተማነት ዕድል ሳያገኙ በዚያው ይሞታሉም፤ ያረጃሉም። ይህ ሁኔታ የጠቅላላው የአገራችንን ሁኔታና፣ እንደ ባህል የተወሰደወን ኋላ የቀረ የቤት አሰራረና የአኗኗ ስልት የሚያረጋግጥ ሲሆን፣ ከትውልድ ወደ ትውልድ የተላለፈና መፍትሄ ሊያገኝ ያልቻለ ትልቁ የማሰብ ኃይላችን ድክመት ውጤት ነው። የሰው ልጅ ለእንደዚህ ዐይነቱ የተዝረከረከና የጨለመ አኗኗር ሁኔታ የተፈጠረ ይመስል። መላኩ ከሹፌሩ ጋር ጉዞውን በመቀጠልና አካባቢውን በመቃኘት የቤቶችን አሰራር ሲመለከት የሰው ልጅ እንዴት በእንደዚህ ዐይነት ጎጆዎች ውስጥ መኖር እንደሚችል ግራ ይገባዋል። ለልጆችና በዕድሜ ለገፉ ተብሎ ተከልሎ ያለተሰራ ቤትና፣ ሁሉም ነገር እዚያው በዚያው የሚካሄድበትን ቤት ሲመለክት የአገሩን ኋላ-ቀርነት ጥልቀትነቱንና ውስብስብነቱን ይገነዘባል። በመንገድ ላይ እያሉና በረሃውን እያቋረጡ ሲሄዱ ዛፍ የሚመስል ነገርና ፍሬ ያዘለውን፣ ከብቶች ተንጠልጥለው ፍሬውን ሲበሉ ይመለከታል። በአካባቢው ሌላም ዛፍ አይታይም። ይህ ዛፍ በጥቂት ውሃ ወይም በትንሽ ዝናብ ሊበቅልና በርሃንም የሚቋቋም ነው ተብሎ ስለታመነበት በደርግ ዘመን ከሌላ ቦታ መጥቶ የተተከለ ነው። ስሩ ወደ ታች ሃምሳ ሜትር ያህል ስለሚደርስ የመሬት ውስጥ ውሃን የመምጠጥ ኃይሉ ከፍተኛ ነው። ስለሆነም በአካባቢው ያሉትን ሌሎች ዛፎችና አትክልቶች ሁሉ እያወደመ ለብቻው በአሸናፊነት የወጣ የአትክልቶችና የዛፎች ጠንቅ ነው። ፍሬውም በየቦታው ስለሚበተን በራሱ ውስጣዊ ኃይል በመብቀልና በመራባት አካባቢውን አዳርሶታል ማለት ይቻላል። በአሸናፊነት የወጣውን ኢምፔሪያሊስታዊ ኃይል የሚመስልና የሚቀናቀኑትን ሁሉ የሚደመስስ ልዩ የአፅዋት ዘር ነው። ስሙም ፕሮስፒስ ይባላል። የመጨረሻም የሄደበትን የአባቱን የመፈለግ ዓላማ ሳያሳካ ወደ አዲስ አበባ ይመለሳል። መላኩ እግረ መንገዱን ወደ አፋር ሲሄድና ወደ አዲስ አበባ ሲመለስ የተመለከተው ነገር፣ ከጂቡቲ የሚመጡ ትላልቅ መኪናዎች ዕቃ ጥቅጥቅ አድርገው ወደ አዲስ አበባ ሲጓዙ፣ እንደገና ደግሞ ወደ ጅቡቲ ሲሄዱ ምንም ነገር ይዘው የሚሄዱት ነገር ስለሌለ ለመኪናዎች የሚፈሰው የነዳጅ ወጪና የሾፌሮችም የቀን አበል የቱን ያህል እንደሆነ ይገምታል። በዚያውም እኛ ኢኮኖሚክስ ተማርን የምንለውን ሁሉ በመቅደምና አርቆ በማሰብ፣ በጥሬ ሀብት ማውጣትና በመሸጥ ላይ የሰለጠነ እንደኛ ያለ አገር ከውጭ አገር ጋር በሚያደርገው የንግድ ልውውጥ የቱን ያህል ለኪሳራ የሚዳረግ መሆኑን ያመለክታል። በመቀጠልም ተጨማሪ ውጤትና(value-added- በቴክኖሎጂ ምጥቀት ላይ የተመሰረተ የምርት ክንዋኔ)ዕውነተኛ ህብረተሰብአዊ ሀብት(National Wealth) ከጭንቅላት እንደሚመነጭ በመገንዘብ በአገራችን የሰፈነውን ከማሰብ ጉድለት የሚደርሰውን መረን የለቀቀ ድህነት ዋናው ምክንያት ሌላ ሳይሆን የሃሳብ ድህነት መሆኑን ያመለክተናል።

መላኩ አዲስ አበባ ከመድረሱ በፊት ሰሎሜ የፕሮጀክት ስራ ለማካሄድ አዲስ አበባ ከመጣች በኋላ የመላኩን ዐይን ላለማየት ስትል በቀጥታ ወደ መቀሌ ትሄዳለች። በመሀከሉ ማርቆስ በሰሎሜና በመላኩ መሀከል የደረሰውን መቃቃርና ኩርፊያ ምክንያቱን በመፈላለግ ለዚህ ሁሉ ዋናው ምክንያት ስንክሳር  ልትሆን እንደምትችል ገመተ። ስንክሳርም ወደ አገር ቤት መጥታ በአንድ በኩል በሰሎሜና በመላኩ መሀከል ያለውን መሻከር የባሰውኑ ለማባባስ የሆነ ያልሆነ ነገር ትቆፍራልች። በሌላ ወገን ደግሞ ክብሮም ወደ መቀሌ መጥቶ ከሰሎሜ ጋር ያላቸውን ግኑኝነት አንድ መቋጠሪያ እንዲኖረው እንደዚሁ ዘዴ ትፈላልጋለች። ይሁንና ግን እሷ ባላሰበችው ወቀት ደግሞ መላኩ ወደ አሜሪካን እንደሚሄድ ትሰማለች። ሰሎሜም ሳተሰማ ክብሮም ወደ አዲስ አበባ ይመጣል። አመጣጡም ወደ መቀሌ ለመሄድና ከሰሎሜ ጋር ለመገናኘት ነበር። ይህም  ውጥን የስንክሳር ሲሆን፣ በመላኩና በሰሎሜ መሀከል ያለውን መቃቃር የባሰውኑ ለማፋፋምና ምዕራፉ እንዲዘጋ ለማድረግና፣ እሷም መላኩን ጠቅልላ የራሷ ለማድረግ ነው ይህ ሁሉ እቅዷ።  ክብሮምም አዲስ አበባ ከመጣ በኋላ ስንክሳርም ለሰሎሜ ስልክ በመደወል እንዴት አድርጋ እንደምትነግራት ማውጠንጠን ጀመረች። ስልክ ደውላላትም ስርፕራይዝ እንደምታደርጋት ነገረቻት። ሰሎሜም ጭንቀት ውስጥ ገብታ በነበረችበት ጊዜ ክብሮም ባደረገው ስህተት ይቅርታ ሊጠይቃት እንደመጣ ታስረዳታለች። ይህም አሰፈላጊ እንዳልሆነና ችክ ያለ ተግባር ነው ስትል የምሯን ገለጸችላት። ሰሎሜም ምንም ማድረግ እንደማትችልና የስንክሳርም ተንኮል እንዳለበት በመገመት ነገሩን ተቀበለችው። ክብሮምም ከስንክሳር ጋር አብረው መቀሌ ከሄዱና ከሰሎሜ ጋር ከተገናኙ በኋላ፣ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ዘመድ ልጠይቅ ብላ ብቻቸውን ጥላቸው ወጣች። ክብሮም በነገሩ የተፀፅተ በመምስል ሰሎሜንን ይቅርታ ጠየቃት። አብረውም አንዳንድ ቦታዎችን ከጎበኙ በኋላ ወደ አዲስ አበባ አብረው መጥተው የሰሎሜ አክስት ቤት አረፉ። ሰሎሜና አክስቷ ብቻቸውን ሲሆኑ በክብሮምና በሷ መሀከል የሆነውን ነገር ሁሉ ነገረቻቸው። እሳቸውም ፍቅር የያዘው ሰው እውር ነው በማለት ለክብሮም ማድላታቸውን በተዘዋዋሪ ይነግሯታል። እሷም መላኩን ትወደው እንደነበረና፣ አሁን ግን በሱ ላይ መጥፎ ነገር ሰለሰማች ከፍተኛ ቅሬታ እንዳደረባት ትነግራቸዋለች። መላኩንም የምትወደው በመልኩ ሳይሆን ልክ እንደ ወንድሟ ተመሳሳይ አስተሳሰብ ስላለው እንደሆነ ትነግራቸዋለች። ይሁንና ግን የሱ አሜሪካን መሄድና መቆየት፣ በሌላ ወገን ደግሞ የሶፊያ ወደ አዲስ አበባ መምጣትና ከመላኩ ጋር መገናኘትና፣ አንዳንዴ አንዳንድ ነገሮችን ለማየት አብሮ መውጣት በመሀከላቸው ፍቅር ያለ ይመሰል ስንካሳር በማስወራቷ ሰሎሜ ማረጋገጫ በሌለው ወሬ በመናደድና ተስፋ በመቁረጥ ከእንግዲህ ወዲያ ከመላኩ ጋር ምንም ግኑኝነት እንደማይኖራቸው ወሰነች።  ከጥቂት ቀናት በኋላ ክብሮም ወደ አሜሪካ ሲመለስ፣ ሰሎሜ ደግሞ እንደገና ወደ መቀሌ ተመለሰች።፡ ግራ የገባው ማርቆስም የዚህን ዐይነቱን የተንኮል ምንጭ አፍላቂውን ማን እንደሆነ በማውጣት በማውረድ ላይ እንዳለ፣ ከስንክሳር በስተቀር ሌላ ሰው ሊያደርግ እንደማይችል ለሰሎሜ አክስት ይነግራቸዋል። ማራቆስ ራሱ በቅርብ የሚያውቀው ነገርና ከሱም ምንም የተሰወረ ነገር የሌለ መሆኑን ሰለሚያውቀው፣ በመላኩና በሶፊያ መሀከል ምንም ዐይነት ግኑኝነት እንደሌለና፣ ሊኖርም እንደማይችል፣ ሶፊያም አዲስ አበባ ከመጣች ጀምሮ ልክ እንደ እህቱ በማየት ያስተናግዳትና፣ የምትሰራበትንም ሆስፒታል በመሄድ የሚጎበኝ እንደነበር ሁኔታውን በጥብቅ የተከታተለ ነው። መላኩም በዚህ አጋጣሚም በፈረንጆች የተሰራውንና የሚተዳደረውን የፊስቱላ ሆስፒታል ከሌሎች አገሪቱ ውስጥ ካሉ ሆስፒታሎች ጋር ሲያወዳድር የሰማይና የምድር ሆኖ ይታየዋል። ግቢውም ሆነ የሰራተኞቹ አያያዝና ለአደጋው የተጋለጡትን ወጣት ሴቶች እንክብካቤ ለየት ያለ መሆኑንም ይገነዘባል። በሌሎች ሆስፒታሎች ውስጥ ያለው መግማማትና የአሰራር ሁኔታ ከቫይረስ በሽታ እንደሚብስና፣ ከበሽታው ይልቅ ግቢው፣ የሆስፒታሎቹና የሰራተኞቹ ሁኔታ ታማሚውን በሽታውን የባሰውኑ እንደሚያብሱበት ይገነዘባል።

መላኩም ወደ አዲስ አበባ ከተመለሰ በኋላ ተቆልሎ የሚጠብቀውን ስራ መልክ ካሲያዘ በኋላ እሱም በበኩሉ የሰሎሜንን ዐይን ላለማየት ለስልጠና ወደ አሜሪካ ለመሄድ ይዘጋጃል። በዝግጅት ላይ እያለ ግን ከአሜሪካ የዶ/ር ሳራ እናት ስልክ ደውለው በጣም አስደንጋጭ ወሬ ይነግሩታል። ስልክ የተደወለው በእኩሌሊት ላይ ስለነበር ስልኩን ስያነሳ የሳራ እናት መሆናቸውን ይገነዘባል። እሳቸውም እየጮሁ ይናገሩ ስለነበር ምን አደገኛ ነገር ተፈጠረ ብሎ ይጠይቃቻዋል። በሳራና በባሏ ምንተስኖት መሀከል ጠብ ተፈጥሮ እንደነበርና፣ ባልየውም ሳራን ሲመታት ትልቁ ልጃቸው በ911 ስልክ ይደውልና ለፖሊሶች ሲነግራቸው፣ ፖሊሶች ምንተስኖትን  ወስደው አስራ ቀን ያህል ካሰሩት በኋላ በማስጠንቀቂያ ፈቱት ብለው ይነግሩታል። ይሁንና ግን ደም ፍላቱ ያልበረደለት ምንተስኖት በሰተነጋታው እንደገና ጭቅጭቅ በመፍጠር ትንሽ ከተጨቃጨቁ በኋላ ትልቁንና ትንሹን ልጅ ገድሎ ባለቤቱንም በብዙ ጥይት ካቆሰላት በኋላ ራሱን ገደለ ብለው የሆነውን ሁኔታ  ያስረዱታል። መላኩም በበኩሉ ራሱን ይዞ ከጮኸና ካለቀሰ በኋላ  የሳራን ሁኔታ ይጠይቃቸዋል። በጣም ተጎድታ ሆስፒታል እንደገባችና አንድ ትንሽ ልጃቸውም ተደብቆ እንደተረፈ ይነግሩታል። መላኩም ድርጊቱን የሰማው አርብ ሲሆን እንደምንም ብሎ ቪዛውን ሰኞ ካገኘ በኋላ ማታውኑ ወደ አሜሪካን ለመብረር ወሰነ። እዚህ ላይ የደራሲው ገለጻ አንድ አርቆ አሳቢ ሰው ባህርዩ ካልገራና የማሰብ ኃይሉም ደካማ ከሆነ ሰው ጋር የጋብቻም ሆነ ወይም አንዳች ግኑኝነት ቢፈጥሩ ምን ዐይነት ስቃይ ውስጥ እንደሚወድቅ ነው። በሌላው ወግን ደግሞ ፍቅር የአጋጣሚ ነገር ስለሆነ፣ የሚፈላለገውም አንዱ በሌላው ጭንቅላት ውስጥ ገብቶ ምን ዐይነት ሰው መሆኑን መመርመር የሚያስችል መሳሪያም ሆነ ችሎታ ስለሌለው፣ መጀመሪያ ላይ ቅልስልስ ብሎ የገባው የኋላ ኋላ ዕውነተኛ ጸባዩን በማውጣትና ማንነቱን በማሳየት ሌላውን ሰው ስቃይ ውስጥ እንደሚከተው ከደራሲው ግሩም አቀራረብ መረዳት እንችላለን።

መላኩ አሜሪካን በቆየበት ጊዜ ታስተናግደው የነበረችው ተንኮለኛዋና፣ መላኩን ለማጠመድ የምትፈልገው ስንክሳር ነች። ስንክሳር እንደምንም ብላ መላኩን ጓደኛውና ምናልባትም የወደፊት የትዳር ጓደኛዋ ማድረግ ነበር ዋና ዓላማዋ። ቀስ በቀስ እያለች እሱን ለመጠጋት ያደረገችው ሙከራ በከፊል ቢሳካም አሁንም ቢሆን መላኩና እሷ ልብ ለልብ ሊገናኙ አልቻሉም። መላኩም ስለሰሎሜ ያለው ፍቅር ተሟጦ ያለቀ አየደለም። ስለሆነም መላኩም በትክክል ወዴት እንደሚያደላ ግራ ገብቶታል።  ይህ በእንደዚህ እንዳለ መላኩ አሜሪካን በቆየበት ጊዜም በሰሎሜና በክብሮም መሀከል ያለውን ግኑኝነት ዕውነት አስመስላ በመንገር ሃሞቱን እንዲቆርጥና እንዲረሳት ለማድረግ ትጥራለች። ክብሮም ሰሎሜን ጋብዟት በመርከብ ላይ እንዳሉና ተነስተው በመደነስ ላይ እንዳሉ ሰሎሜ ሳታስበው ቀለበት ጣቷ ላይ እንዳደረገላት፣ እንደሳማትና አብረው የተነሱትንም ፎቶ ታሳየዋልች። መላኩም በዚህ ይናደዳል። ይሁንና ግን ሰሎሜ ፈልጋው ያደረገችው ሳትሆን ባላሰበችውና ባልጠበቀችው ሰዓት ክብሮም ጣቷ ላይ የሰካላት ነው። ማርቆስም ይህንን ሁሉ ከተከታተለና መረጃም ከሰበሰበ በኋላ፣ በአንድ በኩል በሶፊያናና በመላኩ፣ በሌላ ወገን ደግሞ በሰሎሜና በክብሮም መሀከል አለ የሚባለው ግኑኝነት መሰረት የሌለውና፣ መላኩንና ሰሎሜንን የግዴታ ማስታረቅ እንዳለበት ስትራጂ ይቀይሳል። ሰሎሜ ወደ መቀሌ ከሄደችና ጥቂት ሳምንታት እዚያ ከቆየች በኋላ እሷ ሳታስበው ማርቆስ መቀሌ በአውርቶፕላን ይሄድና አንድ ሆቴልቤት ውስጥ ከአረፈ በኋላ ስልክ ይደውልላታል። መቀሌም እንዳለና ሊያገኛትም እንደሚፈልጋት ይነግራታል። በተቀጣጠሩበት ሰዓት ወደ ሆቴል ቤቱ ከመጣች በኋላና አንዳንድ ነገሮች አዘው በመጫወት ላይ እያሉ ቀስ በቀስ በሶፊያና በመላኩ መሀከል ያለው ግኑኝነት ውሽት መሆኑና፣ ከእሱም ምንም ነገር የተደበቀ ነገር እንደሌለና፣ ይህንንም ያደረገቸው ተንኮለኛዋ ስንክሳር እንደሆነች ያረጋግጥላታል። በመቀጠልም ችካጎ ድረስ ክብሮም ጋ ስልክ በመደወል የሰራውን ቲያትር አንድ በአንድ በመዘርዘር የግዴታ ካሳ መክፈል እንዳለበት ያስረዳዋል። ሰሎሜም የማርቆስን ጥበብና ለዕውነት የቆመ ሰው መሆኑን በመገንዘብ በድርጊቱ በጣም ትደሰታልች። ከእንግዲህ ወዲያ ከመላኩ ጋር የነበራትን ግኑኝነቷን እንዴት እንደገና እንደምትጠግንና መልክም እንደምታስይዘው  ታስባለች። የሚገኛኙበትንም ጊዜ በናፍቆት ነበር የምትጠባበቀው። ማርቆስ ስሎሜንን ካሳመነና እሷም አምና ከተቀበለችው በኋላ፣ አሁን ደግሞ መላኩን ማሳመን ነው የቀረው ስራው። መላኩ እስኪመጣ ድረስ ግን ጥቂት ቀናቶች መጠበቅ ነበረበት።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የውሸት ሽምግልና አቀንቃኞች ሆይ! ሳይንስ እንደሚያስረዳው ውሾች እንኳ የከዷቸውንና ያጭበረበሯቸውን ሰዎች ዳግም አያምኑም!

መላኩም ከሁለት ወር ስልጠና በኋላ ከአሜሪካ ጉዞው ይመለሳል። ይሁንና ትንሽ ብልጭታን ያገኘው በመላኩና በስንክሳር መሀከል የተጀመረው ግኑኝነት ዕረፍት አልሰጠው ብሏል። ስንክሳርም ወደ አገርቤት እንደምትመለስ ስለነገረችው በምን መንገድ ግኑኝነታቸውን እንደሚያጠንክሩ ያሰላስል ገባ። መላኩ ከአሜሪካ በተመለሰ ዕለት ማርቆስ ቤት ነበር ያረፈው። መላኩም ጸሎቱን ካደረገ በኋላ ማርቆስ ያዘጋጀለትን ቁርስ መብላት ሲጀምሩ፣ መላኩ በማርቆስና በሶፊያ መሀከል ሊኖር ስለሚችለው የወደፊት ግኑኝነት ሲያወራለትና በነገሩም እንዲገፋበት ሲያበረታታው፣ ማርቆስ ደግሞ ስንክሳር የወጠነችውን ተንኮል ውሸት እንደሆነ እንዴት አድርጎ እንደሚነግረው ማውጣት ማውረድ ጀመረ። ቀስ ቀስ እያለ በጣም አስፈላጊ ዜና እንደሚያሰማው ይነግረዋል። መላኩም ደንገጥ በማለት ምን እንደሚያመጣ በመጠባበቅ ላይ እንዳለ፣ ሰሎሜም ሆነ መላኩ ያሰቡት ነገር ትክክል እንዳይደለና፣ ስንክሳርም ያቀነባበረችው ተንኮል እንደሆነና፣ በእሱና በሶፊያ መሀከል የጦፈ ፍቅር እንዳለ አድርጋ ለሰሎሜ እንደነገረቻት ማርቆስ ለመላኩ ረጋ ባለ መልክ ይነግረዋል። መላኩም በስንክሳር በኩል ለሰሎሜ የላከው ደብዳቤ ስንክሳር እንዳለቸው የጠፋ ሳይሆን በመሀከላቸው ያለውን ግኑኝነት ለመበጠስ ስትል ነው ደብዳቤውን የደበቀችው ብሎ ማርቆስ እቅጩን ይነግረዋል።  መላኩ ግን ይህንን ባለማመን  ይህ ሁሉ የፈጠራ ስራ ነው፤ ታዲያ ቀለበት ሲያደርግላት የተነሱት ፎቶ ከየት መጣ ብሎ ይነግረዋል። ማርቆስም ለመላኩ የሆነውን ድራማ ሁሉ እየዘረዘረ ሲነግረው የባሰውኑ ግራ ይጋባል። በመቀጠልም ማርቆስ ከክብሮም ጋር በስልክ ያደረገውን ንግግርና በቴፕ የቀዳውን አንድ በአንድ ያሰማዋል። መላኩ ይህ ሁሉ ቲያትር ግራ ቢያጋባውምና ለማመንም ቢሳነው፣ ሳንዲያጎ በቆየበት ጊዜ ስንክሳር ያደረገችውንና የተጫወተችበትን ሁኔታ ፊቱ ላይ ድንቅር አለ።  ጠረቤዛውንም በመምታትና በመጮህ ሳንዲያጎ በነበረበት ወቅት የተጫውተችበትን ነገር ሁሉ ዘርዘሮ ነገረው። በመጨረሻም የማርቆስ ድርጊት ሁሉ እየገረመውና ነገሩን ለማውጣጣት የወሰደውን እርምጃ ሲያስበው፣ ለማርቆስ አንተም ልክ እንደተንኮለኛዋ ስንክሳር ሆነሃል አይደለም አንዴ ብሎ ይነግረዋል። ማርቆሰም ሰሎሜ ከመላኩ ጋር ለመገናኝተ በጉጉት እንደምትጠባበቅና ምግብ ሁሉ እንደተዘጋጀና ሶፊያም እዚያ ላይ እንደምትገኝ ያበስርለታል። በማርቆስ ልባዊ ቀናነትና ዕውነትን ለማግኝት ሳይታግቱ መስራት በሁለት ፍቅረኞች መሀከል የነበረውን መሻከርና ወደ ዕልክነት መሸጋገር እንደገና ሊጠገንና ወደ ጤናማ ሁኔታ እንደሚመለስ ደራሲው ሰዕላዊ በሆነ መልክ ይገልጸዋል። ደራሲው እንደሚለው በተንኮሎኞት የውሸት ወሬ የተነሳ በሁለት ሰዎች መሀከል ያለው ግኑኝነት መሻከሩና ወደ ጠብ ማብራቱ ብቻ ሳይሆን፣ እንደዚህ ዐይነቱ የጥቂት ተንኮለኞች ስራዎችና የውሽት ወሬዎች ስንትና ስንት ስልጣኔዎችን እንዳፈራረሱና፣ በመቶ ሺሆች ለሚቆጠሩ ስዎች ህይወት መጥፋት ምክንያት እንደሆኑ ደራሲው በደንብ ያብራራል። ቢያንስ ባለፉት አስርና አስራ ዓምስት ዓመታት በኢራክ፣ በአፍጋኒስታን፣ በሊቢያ፣ና ዛሬ ደግሞ በሶሪያ የደረሰውንና የሚደረሰውን የህዝብ እልቂትና የስልጣኔ ውድመት ስንመለከት ጥቂት ሰዎች በተሳሳተ ኢንፎርሜሽን በሚነዙት ወሬና በሚጭሩት እሳት የስንት ሰው ህይወት እንደሚያልቅ የምንመለከተውና በዐይናችን በየቀኑ የሚተላለፍ ሀቅ ነው። ሲአይኤ የሚባል እጅግ አሳሳች የሆነ ወሬ አምራችና ጠብ ጫሪ፣ እንዲሁም ሞሳድና ሌሎች የምዕራቡ ዓለም የስለላ ድርጅቶች በሚነዙት የተሳሳተ ወሬ በቂ ዕውቀት የሌላቸው ሰዎች ጥቂት መሳሪያና የገንዘብ ዕርዳታ በማግኘት የራሳቸውን ስልጣኔ እንደሚያፈርሱ በገሃድ የሚንመለከተው ጉዳይ ነው። ሰለጠንኩኝ የሚለውም የምዕራቡ ዓለም የሚሊታሪ፣ የኢኮኖሚና የፖለቲካ የበላይነቱን ተገን በማድረግና የውሸት ፕሮፖጋንዳዎችን በማስፋፋትና ጥቂት የዋሆችን መሳሪያ በማድረግ፣ በሃይማኖትና በጎሳ በማሳበብ አንድን ህዝብ እርስ በርሱ በማበላላት ፍዳውን እንደሚያሳየውና፣ ከእንግዲህ ወዲያም እንደገና እንዳያንሰራራ ሁኔታውን ሁሉ እንደሚያጨልምበት የውሸት ወሬ የትኛውን ያህል አሳሳችና አገርና ስልጣኔ አውዳሚ እንደሆነ መረዳት እንችላለን። በአገራችንም ምድር በአለፉት አርባ ዓመታት የደረሰው እልቂትና አገር መበታተን ከተሳሳተ ኢንፎርሚሽንና ዕውቀት በመነሳት በጥቂት ግለሰቦች በተጫረ እሳትና በቀላሉ ሊበርድ ባልቻለ መቀጣጠል የተነሳ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል። ስለሆነም ጭንቅላት እስካልዳበረና ማመዛዘን እስካልቻለ ድረስ  ለስልጣን የሚስገበገቡ ጥቂት ኃይሎች በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብን ገደል ውስጥ መክተት እንደሚችሉ በታሪክ ውስጥ የተረጋገጠ ነው።

መላኩና ሰሎሚ እንደገና ከታረቁና ከተጋቡ በኋላ ጫጉላቸውን ለማሳለፍ ለሽርሽር ወደ ደቡብ አፍሪካ ይሄዳሉ። መጀመሪያ ያረፉት ጆሃንስበርግ ሲሆን፣ በተነጋታው በአውቶቡስ የተወሰነ ቦታዎችን ካዩ ባኋላ አውቶቡስ ቀይረው ስዌቶን ዞር ዞር ብለው ያያሉ። ጆሃንስበርግም እዚያው በዚያው ደሃና ሀብታም፣ የወዳደቁና ቪላቤቶችን ያቀፈች ከተማ ስለሆነች በቅራኔ የተሞላችና ብዙ ወንጀልም የሚፈጽምባት ከተማ ነች። በተለይም ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ ለጉብኝት ለመጣ ሰውና፣ መግቢያውንና መውጫውን ለማያውቀው እንደልብ ተዝናንቶ የሚንሸራሸሩባት ከተማ አይደለችም። መላኩና ሰሎሜም የተቀራቸውን አራት ቀናት በኬፕ ታውን አካባቢ ለማሳለፍ አቅደው ስለነበር ወደዚያ ያቀናሉ። አካባቢውን ዞር ዞር ብለው በሳፋሪ ካዩ በኋላ ኔልሰን ማንዴላ የታሰሩበትን የሮቢን ደሴትን ለማይት በተነጋታው ወደዚያ ያመራሉ። ደሴቱም ለእስር የተመረጠበት ምክንያት በቀላሉ እስረኛው ለማምለጥ የማይችል መሆኑን ይደርሱበታል።  እነመላኩም ፕሬዚደንት ማንዴላ የታሰሩበትን ክፍል ከጎበኙ በኋላ የገረማቸው ነገር ሰውየው ለአስራስምንት ዐመታት ከታሰሩ በኋላ ሲፈቱ ቂምበቀል በልባቸው ሳይቋጥሩ በደቡብ አፍሪቃ ውስጥ የቀይ ደመና ትብብር እንዲፈጠር መስመሩን መቅደዳቸውና ሁሉም የደቡብ አፍሪካዊ ህዝብ ለጊዜውም ቢሆን በስምምነት ሊኖር  የሚችልበትን ሁኔታ መፍጠራቸው ነው።  በሌላ ወገን የኔልሰን ማንዴላ ልብ በፍቅር የተሞላ ቢሆንም፣ ነፃነትን ተቀዳጀ የተባለው ጥቁሩ ደቡብ አፍሪካዊ ከቀድሞ ሁኔታ ጋር ሲነፃፀር ከድህነት ያመለጠ ሳይሆን እንዲያውም በባሰ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኝ እነመላኩን የሁኔታው አለመቀየር ግራ ያጋባቸዋል። ስለሆነም አፓርታይድ  „በመወገዱ“ የጥቁሩ ህዝብ ኑሮ ይህን ያህልም ያልተለወጠ መሆኑን የተገነዘበችው ሰሎሜ፣ መላኩን እንደዚህ በማለት ትጠይቀዋለች። „ግን ያልገባኝ እሺ በማንዴላ ጉዳይ ምንም ጥያቄ የለኝም እንዳወራነው ነው። እኔ የሚገርመኝ አፓርታይድ ከወደቀ፣ ኃይልም(ስልጣንም) ለጥቁሮች  ከተሰጠ ታዲያ በተለይ ስዌቶና ጆሃንስበርግ፣ እዚህም ኬፕታውን የሚታየው የጥቁርና ነጭ ልዩነት ምንድነው?  እኔ ግን አሁንም የማንዴላ ሥራ ፍሬ አልታየኝም። ማለቴ አስገራሚ ሰው ናቸው፤ ግን በቃ ለውጥ ማለት ይሄ ነው?„  ብላ ጥያቄ ታቀርብለታለች።  መላኩም የማንዴላ ትግል ፍሬያማ እንደሆነና ህግም እንደተለወጠ፣ ትግሉ የመጨረሻ መጨረሻ ፍሬያማ እንዲሆን ከተፈለገ የእያንዳንዱ ዜጋ አዕምሮው መከፈትና ነፃ መውጣት እንዳለበትና፣ የታሪክም አደራ በመጭው ትውልድ ላይ እንደተጫነና፣ የሱም ተግባር እንደሆነ ለማስረዳት ይሞክራል። እዚህ ላይ ግን ከደራሲው ጋር ሙሉ በሙሉ መስማማት አይቻልም ይሆናል። የህግ መለወጥ በራሱ የመንግስቱን ምንነት መቀይርና ተግባሩም ምን መሆን እንዳለበት አይገልጽልንም። በደቡብ አፍሪካም ሆነ በሌሎች የአፍሪካ አገሮች የተካሄዱትን የነፃነት ትግሎች ስንመለከት ስልጣን ላይ ቁጥጥ የሚሉት አዲሱ ኃይሎች ያለውንና የፈረጠመውን የመንግስት መኪና ለራሳቸው በማድረግና ከህዝብ በመራቅ ወደ መጨቆኛ መሳሪያነት ይለውጡታል። የመንግስት ምንነት ግልጽ እስካልሆነና፣ ዲሞክራሲያዊ የሆነ የህዝብ ተሳትፎና የአስተዳደር አወቃቀር እስካለተመሰረተ ድረስ አዳዲስ ኤሊቶች ኢንተርናሽናል ኮሙኒቲ ከሚባለው ጋር በመቆላለፍ አገዛዙን የባሰ ጨቋኝ በማድረግ ዕውነተኛ ነፃነትን ብቻ ሳይሆን፣ ዕውነተኛ ዕድገትም እንዳይመጣ ጠንቅ ይሆናሉ። ስለሆነም የመንግስትም ሆነ የዲሞክራሲና የነፃነት ጉዳይ እንደገና በአዲስ መልክ መጠናት ያለባቸው ጉዳዮች ናቸው። የዲሞክራሲ፣ የነፃነትና የስልጣኔ ጉዳይ በምንም ዐይነት ጥቂት ኢሊት ነን፣ ሁሉንም ነገር እናውቃለን ለሚሉ መተው ያለበት ጉዳይ አይመስለኝም። በተለይም ምሁራዊ እንቅስቃሴና ትችታዊ አመለካከት ባልዳበረባቸው እንደኛ በመሳሰሉ አገሮች አምባገነናዊ አገዛዝ እየተመላለሰ መከሰቱና የድህነቱን ዘመን እንደሚያራዝመው መታወቅ አለበት። ፕሬዚደንት ማንዴላና ፓርቲያቸው ስልጣን ሲይዙ፣ በአንድ በኩል የዓለም አቀፍ ኮሙኒቲ የሚባለው የግዴታ የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚክ ፖሊሲን ተግባራዊ እንዲያደርጉ ግፊት አደረገ፣ በሌላ ወገን ደግሞ የመሬት ጥያቄና ሊሎችም የሀብት ይዞታ ጥያቄዎች መነሳት እንደሌለባቸው ማስጠንቀቂያ ተሰጣቸው። በዚህም ምክንያት አብዛኛው የደቡብ አፍሪካ ህዝብ የኢኮኖሚ ዕድገት ተጠቃሚ እንዳይሆንና በውሳኔ ውስጥም እንዳይካተት ማዕቀብ ተጣለበት።

መላኩና ስሎሜ አሁንም ደቡብ ከኬፕ ታውን ሳይወጡ እዚያው ሰለመጭው ዕቅዳቻው ሃሳብ ለሃሳብ ሲለዋወጡ፣ አዲስ አበባ ደግሞ ማርቆስና ሶፊያ ቢፈላለጉም፣ መፈላለጋቸውን ግን በግልጽ አውጥተው መናገር አልቻሉም። ሶፊያ ሆስፒታል ውስጥ ስራዋን እየሰራች፣ በተጨማሪ ደግሞ የስዕል ኤግዢቪሽን ለማሳየት ቀን ከሌሊት ደፋ ቀና ትላለች። በመጨረሻም አባቷ በልጅነቷ ሲያጫውታት ፈገግ ይል የነበረውን ገጽታውን ለመሳል ያቅታታል። በጭንቅላቷ ውስጥ እየመላለሰ የሚታያት ግን አሁንም ተስፋ የቆረጠና የተጨማደደ ፊቱ ነው። በመጨረሻም  አባቷ ወደ ላይ እየወረወራት ሲቀበላትና ስትስቅ፣ እሱም ፍልቅልቅ ሲል የተነሱትን ስዕል በትልቁ ትሰራለች። ይህ በእንደዚህ እንዳለ ሳታስበው ማርቆስ ከቸች ይላል።  አንድ ቦታ ተቀምጠው የአባቷን ሰዕል እያየች ያለፈችበትን ውጣ ውረድ ትዝ ብሏት ቀስ ቀስ እያለች የህይወት ታሪኳን ታጫውታዋለች። በሷ ምክንያት አባቷና የምትወደው ጓደኛዋ ሶለን ህይወታቸው እንደጠፋ ትነግረዋለች። በተጨማሪም ያላጬሰችው አንዳችም ዕፅ እንደሌለና፣ ሙሉ በሙሉ ተስፋዋ ተሟጦ እንደነበረ ትዘረዝረታለች። እሱም በጥሞና ካዳመጠ በኋላ፣ በሷ የጨለመ ታሪክ ሳይሳቀቅና ተስፋ ሳይቆርጥ እሱም በበኩሉ ያለፈበትን አስቸጋሪ ጉዞና፣ ብዙ ሰዎችም በድለውት እንደነበርና፣ ይህንን ሁሉ ከመጤፍ ሳይቆጥር ይቅርታ በማድረግ፣ ስንክሳር ደግሞ በሰሎሜና በመላኩ ላይ በደል እንዳትፈጽም በማለት ምን ዐይነት የብልህነት ስራ እንደሰራ ታሪኩን ይነግራታል።  እሷም በሱ ስራ በመደነቅና ግሩም ሰው መሆኑን በመረዳት ሁለቱም ቀስ በቀስ በፍቅር እንደተጠመዱና፣ በሃሳብና በልብም እንደሚገናኙ ፍላጎታቸውን ይገልጻሉ።

መላኩና ሰሎሜ ወደ አዲስ አበባ ከመመለሳቸው በፊት ወተር ፍሮንት በሚባለው መዝናኛ ባለበት አካባቢ ተቀምጠው ሳለ ሁለቱም በሃሳብ ማዕበል ይዋጣሉ። ስሎሜም መላኩ ምን ያስብ እንደነበር ትጠይቀዋለች። እሱም የሚጽፈው መጽሀፍ እንዳለው ነገር ግን ሃሳቡ ቶሎ አልመጣ እንዳለውና ግራ እንደገባውና በጭንቀት ዓለም ውስጥ እንደሚገኝ ይነግራታል። ለመሆኑ የመጽሀፉ አርዕስት ምንድንነው ብላ ትጠይቀዋለች። እሱም ርዕሱን እንደሚያውቀውና፣ ያልተጻፈና አልጻፍ ያለ መሆኑን ይነግራታል።  ታዲያ ማወቅ ይቻላል ብላ እንደገና ትጠይቀዋለች።  ቀና ብሎ እያያት „የተቆለፈበት ቁልፍ“   ነው ብሎ ይነግራታል። እሷም በበኩሏ፣  የምትጽፈው ስለተቆለፈበት ቁልፍ ከሆነ ቁልፉን ካገኘህ ሃሳቡም ይመጣልሃል ስትለው፣ ምን ትቀልጂያለሽ በማለት፣ ምናልባት በመጀመሪያ አርዕስቱን በመምረጤ ሳይሆን አይቀርም ሃሳቤን የቆላለፈው ይላታል። እንደዚህ እያሉ ሃሳብ ለሃሳብ ሲለዋወጡ የድሮው ትዝታቸው ብልጭ አለባቸውና ወደ ሌላ ዓለም ውስጥ ገቡ። መላኩም አሷ አሜሪካ በነበረችበት ወራቶች እኛ መኪና ግጭቷቸው ሳለ አንስታ የጋበዘቻቸውና ገንዘብም የሰጠቻቸው አባባ አራጋው የሚባሉት ሽማግሌ እንደሞቱ ይነግራታል። እሷም በጣም በማዘን አገሯ ምን ዐይነት አገር እንደሆነና፣ ሽማግሌና ህፃናትን የሚንከባከብና የሚረዳቸው እንደሌለ፣ ህብረተሰቡም ርስበርሱ የሚተጋገዝ እንዳልሆነ ያበሳጫታል። እሱም ህብረተሰብ ማለት ምን ማለት ነው? ውል የሌለው ነገርና ዝም ብሎ የተሰበጣጠረ መሆኑና፣ እሱም በታሪክ አጋጣሚ ሰው የመሆን ዕድል እንዳጋጠመው ይነግራታል።  ይህ ዐይነቱ አገላለጽ ምንድነው የሚያመለክተው?  ከሞላ ጎደል አንድ ህብረተሰብ በዕውቅ ካልተደራጀና፣ በተለይም ደግሞ ታዳጊው ትውልድ በሚገባ ታንጾ የታሪክ ባለቤት እንዲሆና ታሪክን እንዲሰራ ከተፈለገ ህብረተሰብአዊና ሰብአዊ ባህርይ ያለው አገዛዝና ኢንስትቱሽኖች መኖር አለባቸው። አንድ አገር በየአካባቢው ህዝቡን የሚንከባከብና፣ እያንዳንዱም ግለሰብ እንደየችሎታው የበኩሉን አስተዋፅዖ በማድረግ የታሪክ ባላደራ እንዲሆን ከተፈለገ የግዴታ በዕውቅና በዕውቀት ላይ የተመሰረተ የሰለጠነ አገዛዝ ያስፈልገዋል። ይህ በሌለበት አገር የየግለሰቡ ጉዞና አኗኗር ዓላማ-ቢስ ይሆናል። አገርና ህብረተሰብም ትርጉም አይኖራቸውም።    

በአጠቃላይ ሲታይ የዶ/ር ምህረት ደበበ መጽሀፍ በዐይነትም ሆነ በአቀራረቡ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያው መጽሀፍ ነው ብል ማጋነን አይሆንብኝም። ደራሲው በኖይሮ ባይሎጂ ዕውቀት የዳበረ ሰው ብቻ ሳይሆን የስልጣኔንም ትርጉም የገባውና ሰብአዊ ባህርይ ያለው ብቸኛው ኢትዮጵያዊ ነው ልል እችላለሁ። ስለህብረተሰብ ትርጉምና ስለህዝብ አኗኗር የጻፈው፣ ከዚህም በመነሳት ስለህበረተሳበችን ኋላቀርነት ያቀረበው ትንተና የምናየው ቢሆንም፣ ልንረዳውና ሊከንክነን ያልቻለ ነው። የዶ/ር ምህረት ደበበ አቀራረብ ሶክራትሲያዊና ፕላቶናዊ ነው። ስለዚህም ፍልስፍናዊ፣ ሳይንሳዊ፣ ህሊናዊ የሆነ የአንድን ህብረተሰብ ዕድገትም ሆነ ውድቀት ከጭንቅላት መዳበርና አለመዳበር ጋራ ያያዘ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ አሉ ከሚባሉት ስነ-ጽሁፎች ውስጥ ሊካተት የሚችል መጽሀፍ ነው ብል እንደመድፈር አይቆጠርብኝም። የደራሲው አቀራረብ የዳንቴ የአምላኮች ኮሜዲንንም የሚያስታውሰን ሲሆን፣ የአንድን ህብረተሰብ በጨለማ ዓለም ውስጥ መኖርና፣ የሆነውን ያልሆነውን በማድረግ በብልግና ዓለም ውስጥ መዝፈቅና፣ ከእንደዚህ ዐይነቱ ኋላቀር አኗኗር እንዴት መውጣት እንደሚቻል ብርሃኑን የሚያንፀባርቅልን ነው። የደራሲው አቀራረብ ሺለሪያዊም ነው።  የሰላሳ ዓመት ጦርነትን ታሪክ ያጠናው ፍሪድርሽ ሽለር እንደሚለን፣ ከአሪስቶተለስ ጀምሮ ስለዴሞክራሲ ሰምተናል፤ አሁንም ቢሆን ከአረመኔነት ባህርያችን አልተላቀቅንም ይላል ሺለር። በሱ እምነትም፣ የዚህ ሁሉ ችግር አዕምሮና ልብ አንድ ላይ ለመገናኘት ባለመቻላቸውና፣ ስራቸውንም ለማቀነባበር ስላልቻሉ ነው ይለናል። የኖይሮ ባዮሎጂስቱ አዋቂና ፈላስፋው ዶ/ር ምህረት ደበበም ይህንን መሰረት በማድረግ ነው የሚያስተምረን። በእሱ ዕምነት ብቻ ሳይሆን፣ በእኔም ዕምነት፣ ዛሬ በዓለም አቀፍ ደረጃም ሆነ በአገራችን ምድር በሃይማኖትና በጎሳ ስም ተሳቦ የሚካሄደው ቅጥ ያጣ ግድያ፣ ህዝቦችን አፈናቅሎ አገርን ወደ አጠቃላይ ድህነትና ረሃብ እንድታመራ ማድረግ ዋናው ምክንያት የጭንቅላት በደንብ አለመዳበርና ዘመናዊነት በሚባል አጉል ፈሊጥ፣ ነገር ግን ደግሞ ከስልጣኔ ጋር ምንም  የሚያገናኘው ነገር የሌለ፣ ጥቂት ኤሊት ነን በሚሉና ከውጭው ኃይል ጋር በተቆላለፉ ኃይሎች የሚካሄድ ዘመናዊ አረመኔያዊ ተግባር ነው።

የዶ/ር ምህረት ደበበ መጽሀፍ በአገራችን ታሪክ ውስጥ በዐይነትም ሆነ በአቀራረብ የመጀመሪያው ስለሆነ ለወደፊት ምርምራችንና ዕድገታችን እንደመመሪያ ሊያገለግል የሚችል መጽሀፍ ነው። ማንኛውም ለአገሬ አስተዋጽዖ አደርጋለሁ ወይም እታገላለሁ የሚል ከዚህ መጽሀፍ ወጭ ትግል ሊያደርግ አይችልም። ደራሲው እንዳለው ሁላችንም በኦቲዝም ትይዘን የምንሰቃይ ስለሆነ፣ አገራችንን ከማጥፋታችን በፊት እስቲ ባለንበት ቦታ ሁሉ በመቀመጥም ሆነ በመቆም እናስብ። በዚህ አማካይነት ራሳችንን ማግኘት ስንችልና ማንነታችንን ስንረዳ በእርግጥም ታሪክን ለመስራት ዝግጁ ነን ማለት ነው። በተረፈ ለዶ/ር ምህረት ደበበ ክቡራዊ መልዕክቴ ይድረሰው። ጤንነትህን እንዲጠብቅልህ ለእግዚአብሄር እጸልይልሃለሁ። ታላቅ ደራሲና በጣም ግሩም ጽሀፍ !!

ፈቃዱ በቀለ !!

fekadubekele@gmx.de

                                               www.fekadubekele.com

ማሳሰቢያ፤ በአገራችን ማህበራዊ ወይም ህብረተሰብአዊ ትችት(Social Critics) የሚባል ነገር የሚታወቅ አይመስልም። ጥያቄ ሳይጠይቁ እንዳላየ ዝም ብሎ ማለፍ እንደባህል የተለመደ ጉዳይ ሆኗል። መተቸት እንደስድብ ይቆጠራል። በመሆኑም እንደዚያ ዐይነት ዝብርቅርቅነትና ብልሹነት እያለ ሁሉም ይህን እንደ ተራ ነገር እያየ ያልፈዋል። ሌላው ችግራችን ደግሞ ደሀ የሆነን ሰው መናቅና ማንቋሸሽ የተለመደ ጉዳይ ነው። መተባበር፣ መረዳዳትና መተጋገዝ የሚሉት ለአንድ ህብረተሰብ እጅግ አስፈላጊ የሆኑ መሰረተ ሃሳቦች የሚታወቁ አይመስሉም። በተለይም ባለፉት 50 ዓመታት የአገራችን እሴቶች እንዳለ ወድመዋል ማለት ይቻላል። ይህ ጉዳይ የግሎባላይዜሽንና የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚ ውጤት ለመሆኑ ስንቶቻችን ተገንዝበን እንደሆን ማወቅ በጣም ያስቸግራል።

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share