February 12, 2023
ጠገናው ጎሹ
አሁን ላይ የምንገኝበት እጅግ አስከፊና አደገኛ ሁኔታ የትናንትና የዛሬ ዱብ እዳ ሳይሆን ለዘመናት እያጠራቀምነው የዘለቅነው ልክ የሌለው የገዛ ራሳችን የውድቀት አዙሪት ውጤት መሆኑን ለማስተባበል የሚሞክር የአገሬ ሰው ካለ የህሊናውን ሚዛናዊነት ከምር መጠራጠር ይኖርበታል።
በእውነት ስለ እውነት ከተነጋገርን ደረጃው ይለያይ እንጅ የሃይማኖት ተቋሞቻችን ፣ መሪዎቻቸው እና እኛም አማኞቻቸው የዚህ አስከፊና አስፈሪ የሆነ አጠቃላይ ማለትም ፖለቲካዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ባህላዊ፣ ሞራላዊ፣ሥነ ልቦናዊ፣ ሥነ ምግባራዊ እና መንፈሳዊ ውድቀት አካላት መሆናችንን ለማስተባበል መሞከር ከሰማያዊውም ሆነ ከምድራዊው እውታ ጋር በቀጥታ መላተም ነው የሚሆነው።
በየሃይማኖታቸው እምነት የፈጣሪ /የክርስቶስና የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያዎች (መቅደሶች) ናቸው ብለን የምናምንላቸው እጅግ አያሌ ንፁሃን ወገኖች በአሰቃቂ ሁኔታና በጅምላ ተገድለው እንደማነኛውም የማይፈለግ ቆሻሻ በየጉድጓዱ ሲጣሉ፣ በብዙ ሽዎች የሚቆጠሩት የአካል ጉዳተኞች ሲሆኑ እና በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩት ደግሞ ተፈናቅለው መግለፅ ለሚያስቸግር የቁም ሞት ሲዳረጉ የሃይማኖት መሪዎች፣ ሰባኪዎች እና እኛም አማኞች የመከራውን ፈተና በሚመጥን የመርህ ፅዕናት፣ በማይናወጥ የዓላማ ጥራት፣ በማይናወጥ የሥነ ልቦና እና የሞራል ልዕልና፣ የመከራን ፈተና ደፍሮ በሚጋፈጥ የሰብአዊና የዜግናት መብቶች አርበኝነት፣ እና ይህንን ሁሉ አቀነባብሮ ለውጤት በሚያበቃ ድርጅታዊ (መዋቅራዊ) ብቃት ለመወጣት አለመቻላችን ይኸውና ዛሬም ራሳችንን በውድቀት አዙሪት ውስጥ እንድናገኘው አድርጎናል ።
ከሰሞኑ በተረኛ ኦህዴዳዊያን/ኦነጋዊያን/ብልፅግናዊያን ገዥ ቡድኖችና ፍርፋሪ ለቃሚ ፖለቲከኞች እየታገዘ በኢትዮጵያ ተዋህዶ አርቶዶክስ እምነት ላይ አደገኛ ሰይፍ ተመዟል።
ሃይማኖትንና ፖለቲካን በቀጥታ አቀላቅሎ ለመግዛት ለሚፈልጉ እና ፈጣሪን ለምድራዊና ማቴሪያላዊ ርካታ ለሚፈልጉት የብልፅግና ወንጌላዊያንና ነቢያት ተብየዎች ሸፍጥና ሴራ በሩን በሰፊው የበረገድንላቸው በዋናነት ሌላ ሳይሆን ቃልን ወደ ተገቢና ገንቢ ድርጊት ለመተርጎም ተስኖን የውድቀት አዙሪት ሰለባ ሆነን የቀጠልነው የሃይማኖት መሪዎቻችንና የእኛው የአማኞች ነን። ይህ ደግሞ ነገረ ሥራችን ሁሉ ከክስተቶች የትካሳት መጠን ጋር ከመሞቅና ከመቀዝቀዝ እጅግ አስቀያሚ ምንነትና ማንነት የሚመነጭ ነው።
የሃይማኖቱ መሪዎች የጀመሩትና በአንፃራዊነት ይበል ያሰኘን ሰሞነኛ እንቅስቃሴ ብዙም ሳይራመድ በቤተ መንግሥቱ የሴራ፣ የሸፍጥና የጭካኔ ፖለቲካ ተጠልፎ ይኸውና መከራውና ውርደቱ ቀጥሏል ።
የሃይማኖቱ መሪዎችም ለምንና እንዴት የሚል ፈታኝ ጥያቄ ሲቀርብላቸው “አትረብሹን ፤ እኛ ሃይማኖተኞች ወይም በመንፈስ ቅዱስ የምናምንና የምንመራ ስለሆን የጠቅላይ ሚኒስትሩንና የባልደረቦቹን ድንቅ (ውብ) ቃላት እንዳለ (ያለምንም ጥያቄ ነው የምንቀበለው) ፤ የሞቱት፣ የተጎዱት ፣ የተፈናቀሉት ንፁሃን አማኞች እና በደም የጨቀዩት ቤተ እምነቶቸ አልበቃ ያሉ ይመስል ለመንግሥት ጊዜ እንስጠው፣ ወዘ” የሚል እጅግ የሚያሸማቅቅ ምላሽ ሲሰጡ መስማት በእጅጉ ህሊናን ያስጨንቃል ።
በእውነት ስለ እውነት ከተነጋገርን እንዲህ አይነት ወለፈንዲ (paradoxical) የሆነን የመልስ አቀራረብና ይዘት በጥሞና ያደመጠ (የሚያደምጥ) ሰው በተለይም የሃይማኖቱ ተከታይ “እውን ይህን ቃል (አነጋገር) እየነገሩን ያሉት እነዚያ እሰየው ያልናቸው የሃይማኖት መሪዎች ናቸው ወይንስ …” ሳይል የሚቀር አይመስለኝም።
መቸም ነገረ ሥራችን ሁሉ ከገዛ ራሳችን ግዙፍ፣ መሪርና ዘመን ጠገብ የውድቀት አዙሪት በየፈርጁ በሚደረግ ተጋድሎ ሰብሮ ለመውጣት ሲያቅተን ሰንካላ ምክንያት (የሰበብ ድሪቶ) መደርደሩ ስለሚቀለን ይህንን ግልፅና ቀጥተኛ አስተያየቴን እንደ ድፍረትና እንደ ኩነኔ (ሃጢት) በመቁጠር የውግዘትና የእርግማን ናዳ ሊያወርዱ የሚችሉ ወገኖች እንደሚኖሩ በሚገባ እገነዘባለሁ ።
ለዚህ ያለኝ መልስ የምንሰጠው አስተያየት ኢላማ በግላዊ ባህሪና ተግባር ላይ ሳይሆን አገርንና ሃይማኖትን በሚመለከት እስከሆነ ድረስ እንኳንስ ፈጥጦና ገጥጦ በሚታየው የራስችን ጉድ በማነኛውም ጉዳይ ላይ ቢሆን ትክክል እንጅ ስህተት ወይም ድፍረት ወይም ጨለምተኝነት ወይም ኢሃይማኖታዊነት ከቶ ሊሆን አይችልም የሚል ነው።
አዎ! ስለ ሰማያዊው ክርስቶስ መከራ፣ ስቅለትና ትንሳኤ እና ስለ ሃይማኖት ፣ ስለ አገርና ስለ እውነት ሲሉ በፋሽት ጣሊያን አረመኔያዊ ጥይት ተደብድበው ስላለፉት ታላቅ የሃይማኖት መሪ አቡነ ጴጥሮስ የምትሰብኩትን ያህል እንኳን ባይሆን ቢያንስ ከሸፍጠኛ፣ ሴረኛና ጨካኝ የቤተ መንግሥት ፖለቲከኞች ጋር እየተሻሻችሁ የመከራውንና የውርደቱን ዘመን አታራዝሙብን ብሎ መጠየቅ በምንም አይነት ሃይማኖታዊና ሞራላዊ ህፀፅ (ድክመት) ሊሆን አይችልም።
ይህንን አይነት ግልፅና ቀጥተኛ ሂሳዊ አስተያየት እንደ ሃጤአት የሚቆጥርና የቅጣት በትር የሚያነሳ እውነተኛ አምላክ የለም። እውነተኛው አምላክ እውነትንና እውነትን ብቻ ነው የሚወደው ። እናም የገዛ ራሳችንን ልክ የሌለው ውድቀት በእውነት ስለ እውነት ተጋፍጠን የሚበጀንን ማድረግ ነው የሚሻለን።
ምንም እንኳ ቁጥራቸው የበዛ ባይሆንም በየትኛውም የሥራና የሙያ መስክ በፅዕኑ ተልእኮ ፣ መርህና ዓላማ ላይ ቆመው አስፈላጊውን ዋጋ የሚከፍሉ ወገኖች አሉና አስተያየቴ የጅምላ እንዳልሆነ ግልፅ ይሁንልኝ።
ለመሆኑ ስንት ነፍስ እስኪጠፋ፣ ስንቱ ለምድረ ሲኦል እስኪዳረግ፣ ስንቱ በየማጎሪያ ቤቱ እስኪታጎር ፣ ምን ያህል የደም እንባ እስኪጎርፍ፣ ምን ያህል ህፃናት የሁለንተናዊ ሰቆቃ ሰለባዎች እስኪሆኑ፣ ስንት ትውልድ ድምፅ በሌለው ጨካኝ መሣሪያ (የትምህርት ደረጃ ዝቅጠት) የቁም ሙት እስኪሆን ነው ይህ እጅግ አሳሳች “ጥሩ ሲሰሩ የማመስገንና ሲሳሳቱ የመተቸቱ” ትርክት የሚቀጥለው?
አዎ! እንደ አንድ ተራ የሃይማኖቱ ተከታይ እንኳንስ ከፍተኛውን የመሪነትና የአስተማሪነት መንበርና ሃላፊነት የተሸከሰመ እና እውነተኛና ቅን ህሊና (ልቦና) ያለው ሰው ቃሉን ከተግባር ጋር በማዋሃድ የሚችለውን በጎ ነገር ሁሉ ለማድረግ የሚጥር ማነኛውም ሰው በመንፈስ ቅዱስ እንደሚታገዝ እረዳለሁ። በቅን ህሊና (ልቦና) በጎ ነገርን ለማድረግ ይቻለው ዘንድ የፈጣሪውን እገዛ በመጠየቅ እልህ አስስጨራ ጥረት የሚያደርግ ሰብአዊ ፍጡር ባለበት ቦታና ሁኔታ ሁሉ መንፈስ ቅዱስ መኖሩን ለማመን የረቀቀ ዓለማዊም ሆነ ቲዎለጃዊ ፍልስፍናን አይጠይቅም።
በእውን የእውነትና የእውነት ሰዎች ከሆን ይህ አይነቱን እኔነት/እኛነት የውስጠ ነፍሳችን (internal soul) አካል አድርገነዋል ወይ? የሚለውን ፈታኝ ጥያቄ በግልፅነትና በቅንነት መጋፈጥ ይኖርብናል።
አሁንም የገዛ ራሳችንን ልክ የሌለው ደካማነት መቀበልና የተሻልን ሆነን ከመገኘት ይልቅ ራሳችንን በሃይማኖት ስም ጨርሶ አይደፈሬ አድርገን ስለምንቆጥር ለተገቢው ጥያቄና አስተያየት ተገቢውንና ገንቢውን ምላሽ ከመስጠት ይልቅ የሚቀናን “ለምን ተደፈርኩ” በሚል የእርግማን ናዳ ማውረዱወይም አካኪ ዘራፍ ማለቱ ነው። እንደ አንድ ተራ አማኝም ሆነ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ይህ አይነት ደምሳሳና ገንቢነት የሌለውን አስተሳሰብና አካሄድ ተጠየቅ ማለት ተገቢ ነውና እንዲህ ልጠይቅ፦ ለመሆኑ በሸፍጠኞች፣ በሴረኞችና በጨካኞች ቤተ መንግሥት ተገኝቶ የአብይንና የቡድኑን የለየለት የማጭበርበሪያ ዲስኩር በመስማት “እውነተኛ የሃይማኖት መሪ ወይም ሰው ማለት ባህሪንና ተግባርን ሳይሆን እፁብ ድንቅ አንደበትን ሰምቶ ማመን ነው” የሚል መንፈስ ቅዱስ አለ እንዴ?
ይህንን የምጠይቀው የሃይማኖት መሪዎች ደጋግመው የሚነግሩን በቤተ መንግሥት ተካሄደ የተባለው ውይይት ያስገኘው ውጤት እና ለሰዓታት እንኳ ሳያቋርጥ እየወረደ ያለው ፖለቲካ ወለድ መከራና ውርደት ፈፅሞ አልገናኝልህም ስላለኝ ነው ።
በሌላ በኩል ከስህተታቸው ተመልሰው ይቅርታ ከጠየቁት ሁለቱ መካከል ሁለተኛው በዛሬው እለት የይቅርታ ደብዳቤያቸውን አንብበው ይቅርታ ሲጠይቁ ተመልክተናል።
በመሠረቱ ምንም ይሁን ምን ስህተትን ተረድቶና ተፀፀቶ በይቅርታ መመለስ በሰማያዊውም ሆነ በምድራዊ ዓለም የትክክለኝነት ሰብእና ባህሪ ነውና እሰየው ብሎ መቀበል በእጅጉ ተገቢ ነው የሚል እምነት አለኝ። ከዚህ መሠረታዊ መርህና እምነት አንፃር ነው ወደ ኖሩበት የቤተ ክርስቲያኗ የበላይ አካል (ሲኖዶስ) የተመለሱትና ወደ ፊትም ለመመለስ የሚወስኑ ካሉ እንኳን በደህና መጣችሁ መባል ያለባቸውና የሚኖሩባቸው።
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ግን ስለ መሳሳት (ስህተት ስለመፈፀም) የሚሰጡ ምክንያቶችን በትክክል ልብ ካልናቸውና ከእውነተኛ ሃይማኖታዊ እምነት አንፃር ካየናቸው የማሳመን ሃይል ጨርሶ የላቸውም። ለምሳሌ “… ምዕመናንን ባሳዘነና ቅዱስ ሲኖዶስ ቃለ ውግዘት ባስተላለፈበት ህገ ወጥ ሢመት ውስጥ ባለማወቅና ነገሩን ሳላጣራ …” የሚለውን አምኖ ለመቀበል በእጅጉ ያስቸግራል።እውን ይህ አይነት ልፍስፍስ (ሳላውቅና ሳልመረምር) የሚል አቀራረብ ከግዙፉና ከመሪሩ እውነታ አንፃር ሲታይ ለዚህ ትውልድ ትርጉም ያለው አሳማኝነትና አርአያነት አለው እንዴ?
መቸም የሃይማኖትን ለምንነትና እንዴትነት ከሃይማኖት አገልጋዮች ጋር ፍፁም በሆነ እይታ ስለምናይ በሃይማኖት መሪዎችና በአገልጋዮች ላይ ገንቢ በሆነና አክብሮትን በተላበሰ አቀራረብም ቢሆን ማሄስን (ስህተት አለባችሁ ማለትን) እንደ አርዮሳዊ ወይም ክፉ ኋጢአትና ድፍረት ስለምንቆጥር ለመቀበል ስእየቸገረን ነው እንጅ እንዲህ አይነቱ ምክንያት ለራስም ቢሆን ምቾት አይሰጥም። እውን በቤተ ክህነት ትምህርት አረዳድ እና በሥራና በዕድሜ ብዙ ተሞክሮ ያለው ሰው ምንም ሳያውቅና ስለ ጉዳዩ ምንም ሳያስብ (ቆም ብሎ ሳይጠይቅ) በእንዲህ አይነቱ እጅግ ስሜትን በሚንጥና አደገኛ በሆነ ሴራ ዘልሎ ይገባል ብሎ ለማመንና ለማሳመን ይቻላል እንዴ? እያልኩ ያለሁት የሃይማኖት መሪና አገልጋይ አይሳሳትም አይደለም። እንዲያውም አንዳንዴ ከእኔ ቢጤው ተራ አማኝ በባሰ ግጥም አድርጎ ይሳሳታል። እያልኩ ያለሁት በዚህ ደረጃ እውን ያለማወቅና ያለማገናዘብ ስህተት ይሠራል ወይ? ያንን ያህል ከአልባሳት ጀምሮ ሰፊ ዝግጅት የተደረገበትን ጉዳይ ባለማወቅ ነው ማለት እንዴት ያሳምናል? የሹመት ግብዣ ሲቀርብላቸውስ ቢያንስ ቀኖና አስፈፃሚው የበላይ አካል (ሲኖዶሱ) ያውቃል ወይስ መፈንቅለ ሲኖዶስ ነው? ብለው እንዴት አይጠይቁም ? ከባለ ጉዳዩ (ከሲኖዶሱ ጽ/ቤት) ወይም ከቅርብ የሥራ ባልደረባ ወይም ጓደኛ ጠይቆ ለማወቅ ይቸግር ነበር እንዴ?
በእውነት ስለ እውነት የሃይማኖታዊ እምነት አርበኞች ነን ካልን ትክክለኛው የይቅርታ አጠያየቅ “ሥጋዬ ነፍሴን ተፈታትኖብኝ (አታሎብኝ) ወይም በተፈፀመና እየተፈፀመ ባለ አስተዳደራዊ ብልሹነት ምክንያት የተሰማኝን ስሜት መቆጣጠር ተስኖኝ ስህተት ውስጥ ገብቸ ነበር። እያደር በተረጋጋና ዛሬን ሳይሆን ነገንና ከነገ ወዲያን በጥልቅ በሚመረምር ህሊና (አእምሮ) ሳጤነው ግን የገባሁበት ስህተት ለእኔም ሆነ ለኖርኩባት ቤተ እምነት ወይም ለዚህ ትውልድ ወይም በአጠቃላይ ለአገር (ለህዝብ) ፈፅሞ ጎጅ መሆኑን አምኘ ተመልሻለሁ” ማለት ትክል ነበር ወይም ነው ብየ አምናለሁ።
ይህ ለገፅታ (face value) የማይመች ከሆነ ደግሞ “የፈፀምኩትን ከባድ ስህተት ከምር ተረድቼ ተፀፅቻለሁና ይቅርታ እጠይቃለሁ” ማለት ይሻላል እንጅ “ሳላውቅና ሳላጣራ” የሚለው ሃረግ በተለይ የሃይማኖቱን መሠረታዊ ቀኖና ዶግማ አሳምሬ አውቃለሁ ለሚል እና በትምህርቱም ሆነ በተሞክሮ ረገድ የጎለበተ ሰብእና አለኝ ለሚል የሃይማኖት አገልጋይ ጨርሶ አይመጥንም። ለዚህ ትውልድም ጠንካራ አርአያነት የለውም።
የ1997ቱ እና የ2010ሩ የፖለቲከኞች (የፖለቲካ ድርጅቶች) አስከፊ ውድቀት ዛሬም በሃይማኖት መሪዎች ብቻ ሳይሆን በተከታዩ (በምዕመኑ) ደካማነት ምክንያት እንዳይደገምና ታሪካዊትና ታላቅ የምንላትን ቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይሆን አገርንም ክፉኛ እንዳይጎዳ ስጋት የተቀላቀለበት በጎ ምኞቴን እየገለፅሁ አበቃሁ!