ጥር 14 ቀን 2015 ዓ.ም. ሦስት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጳጳሳት “የኦሮሚያ እና የብሔር ብሔረሰቦች ቤተ ክህነት” ተብሎ የሚጠራ አዲስ ቤተ ክህነት ማቋቋማቸውን እና ለሃያ ስድስት የሃይማኖት አባቶች የጵጵስና ማዕረግ ሹመት መስጠታቸውን ይፋ ማድረጋቸው እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሲኖዶስ ጥር 18 ቀን 2015 ዓ.ም. ይህንኑ ውሳኔ ውድቅ በማድረግ ሦስቱን ጳጳሳት ጨምሮ እነሱ የሾሟቸውን የሃያ ስድስት አባቶችን ማዕረግ በማንሳት ከቤተክርስቲያኗ በውግዘት እንዲገለሉ መወሰኑ ይታወሳል።
ይህንን ተከትሎ በተለያዩ ቦታዎች እየተፈጠሩ ያሉ ክስተቶች እና የሰብአዊ መብቶች ሁኔታዎችን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ/ኮሚሽኑ) በቅርበት በመከታተል፣ እንዲሁም ሁሉንም ወገኖች እና የሚመለከታቸውን አካላት በማነጋገር ለችግሩ እልባት ለማግኘት ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡
ኮሚሽኑ ይህ መግለጫ እስከወጣበት ቀን ድረስ ሲያደርግ በነበረው ክትትልና ምርመራ የሚከተለውን ለመረዳት ተችሏል፡-
– አዲስ “ቤተ ክህነት” አቋቁመናል በማለት ያሳወቁት ጳጳሳት በአንዳንድ ቦታዎች በኃላፊዎች ድጋፍ ጭምር በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች የሚገኙ ሀገረ ስብከቶችን መያዛቸውን፣ ጥር 27 ቀን 2015 ዓ.ም. የሻሸመኔ ደብረ ስብሐት ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያንን ለመያዝ ያደረጉትን እንቅስቃሴ ተከትሎ እርምጃውን ለመቃወም የወጡ ሰዎችን ለመበተን በመንግሥት ጸጥታ አባላት በተወሰደ ተመጣጣኝ ያልሆነ የኃይል እርምጃ እና ከጸጥታ አባሎቹ ጋር ሲተባበሩ በነበሩ ሰዎች ቢያንስ ስምንት ሰዎች በጥይትና በድብደባ መገደላቻውን ኮሚሽኑ ያረጋገጠ ሲሆን፣ ቁጥራቸው ገና በትክክል ያልታወቀ ሰዎች ለተለያየ ዓይነትና መጠን የአካል ጉዳት መዳረጋቸውን እንዲሁም በርካታ ሰዎች ለተለያየ ጊዜ መጠን መታሰራቸውን፣ (የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ኃላፊዎች በሻሸመኔ የሞቱት ሰዎች ቁጥር 13 መሆኑን ለኮሚሽኑ የገለጹ በመሆኑ የማጣራት ሂደቱ እንደቀጠለ ነው)
– በተለያዩ ቦታዎች አዲስ “ቤተ ክህነት” አቋቁመናል በማለት ያሳወቁትን ጳጳሳት በተቃወሙ ሰዎችና የሃይማኖት መሪዎች ላይ ድብደባ፣ ማዋከብ፣ ከቤተ ክርስቲያናት ማባረር፣ የመንቀሳቀስ መብትን በኃይል መገደብ እና ከሕግ ውጭ እስራት እንደተፈጸመ፤ እንዲሁም ሲኖዶሱ ከጥር 29 እስከ የካቲት 1 ቀን 2015 ዓ.ም. የሚታሰበውን የጾም ወቅት አስመልክቶ ያቀረበውን የጥቁር መልበስ ጥሪ የተቀበሉ ሰዎች ላይ በተለያዩ ቦታዎች እስር፣ ወከባ፣ ከሥራ ቦታና አገልግሎት መስጫ ቦታዎች ማግለል እንደተፈጸመ፣ እንዲሁም
የችግሩ ግዝፈት ቢለያይም በተለይ በነቀምቴ፣ በግምቢ፣ በደምቢ ዶሎ፣ በሻምቡ፣ በአሰላ፣ በሻሸመኔ፣ በጭሮ፣ በያቤሎ፣ በጅማ፣ በቡሌ ሆራ፣ እና በነጌሌ ቦረና ከተሞች ከሕግ ውጭ እስራትና ተመሳሳይ የማዋከብ ድርጊቶች እንደተፈጸመ ታውቋል፡፡
– በመንግሥት የጸጥታ አባሎች ተመጣጣኝ ባልሆነ ኃይል አጠቃቀም በጥይት እና በድብደባ የተፈጸሙ ግድያዎች፣ ከሕግ ውጭ የተፈጸሙ እስሮችና የእንቅስቃሴ ገደቦች፣ እንዲሁም ሲኖዶሱ ያቀረበውን የጥቁር መልበስ ጥሪ የተቀበሉ ሰዎች ላይ የተፈጸሙ እስሮች፣ ከአገልግሎት እና ከሥራ ቦታ ማግለልና ማንገላታት ፍጹም ተገቢ ያልሆኑ እና የዜጎችን በሕይወት የመኖር፣ በነጻነት ሃይማኖታቸውን እና ሐሳባቸውን የመግለጽ ሕገ መንግሥታዊ መብቶችን የሚፃረሩ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ናቸው፡፡ ስለሆነም መንግሥት የተሟላና ተገቢውን ማጣራት አድርጎ ተገቢውን ሕጋዊ እርምጃ ሊወስድ እና የተጎዱትንም ሊክስ ይገባል። በተጨማሪም የመንግሥት ጸጥታ ኃይሎች ሰላማዊ ተቃውሞ በሚያደርጉ ሰዎች ላይ ኃይል ከመጠቀም፣ ከማንገላታት፣ ከሕገ ወጥ እስር እና የሰዎችን እንቅስቃሴ ያለበቂ ምክንያት ከመገደብ መቆጠብ ይኖርባቸዋል፡፡
– በተጨማሪ በማኅበራዊ ሚዲያና በሌሎችም መገናኛ ብዙኃን የሚሰራጩ ትክክለኛ ያልሆኑ መረጃዎች ለሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ሥጋቱን የሚጨምሩ በመሆናቸው በሁሉም አካላት ኃላፊነት የተሞላው የሚዲያ አጠቃቀም ያስፈልጋል። እየተከሰተ ያለው ችግር አስቸኳይ እልባት ካላገኘ ለከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ሥጋት ነው፡፡ ስለሆነም ኮሚሽኑ ከመደበኛው የክትትል እና የምርመራ ሥራው ጎን ለጎን ጉዳዩ የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት በሙሉ በማነጋገር እና በመመካከር፣ በቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ የተፈጠረው ችግር የሃይማኖት ነጻነት መሠረታዊ መብትና የሃይማኖት ጥበቃ ሕገ መንግሥታዊ መርህ መሠረት በቤተ ክርስቲያኗ የውስጥ ሥርዓት መሠረት እንዲፈታ፣ የመንግሥት ሰላምና ጸጥታ የማስከበር ተግባርና ኃላፊነት በሕጋዊ ሥርዓት እንዲመራ፣ ሰብአዊ መብቶች በሁሉም ወገኖች እንዲከበሩና እንዲረጋገጡ የሚያስችል የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን የመከላከል ጥረት በማድረግ ላይ የሚገኝ መሆኑን ይገልጻል። ይህንን አስመልክቶ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋማት ከዘርፈ ብዙ ሥልጣንና ኃላፊነታቸው ውስጥ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች እንዳይከሰቱ እና እንዳይባባሱ የተለያዩ የምክር፣ የሽምግልና እንዲሁም የውትወታ ተግባራት እንደሚያከናውኑ አስታውሰው፣ “የሀገርን ሰላም እና ደኅንነት መሠረት በማድረግ፣ የኃይማኖቶችና ሌሎችም ነጻ ተቋሞችን ነጻነት ማክበርና መጠበቅ አስፈላጊነት በማጤን፣ ሁሉም ሰው እና ማኅበረሰብ፣ ለችግሩ መፍትሄ ለመፈለግ የሚደረገውን ጥረት እንዲያግዙ” ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን