February 9, 2023
11 mins read

የት ሄደች ኢትዮጵያ (አንዱ ዓለም ተፈራ)

የቅድመ ታሪክ

የሰው ልጅ መስፈሪያ ሆና
አሻራውን አስቀምጦባት፣
የሰው ዘር መብቀያ
የሃይማኖቶች ሁሉ መሬት፣
የብዙዎች መሰብሰቢያ
የረጅም ታሪክ ባለቤት፤
ያብሮ መኖር የነፃነት
የግብረገብ አምድ ፅናት፣
የዘመናት እናት አዛውንት
ልጆቻቸውን ያሳደጉባት፤
ተምሳሌት የሆንሽ
የሁሉ እናት፤
አገራችን ኢትዮጵያ
እናታችን የምንላት፤
የት ገባች አሁን?
ኧረ የት!
ደካሞችን ደግፋ፣
ቤት ለንግዳ ብላ አቅፋ፤
እንሰሳትን በጎጆዋ አግታ፣
እንዳይበርዳቸው አስጠግታ፤
ያኖርሽን ያኖርሺበት
ጎጆ ቤቴ፣
ሕይወቴ፣
ኧረ ወዴት ሄድሽ እናቴ!
እስኪ ንገሪኝ በሞቴ!
* * * * * * * * * *
ላባቴ ለናቴ ሳልል፣
ለህቶቼ ወንድሞቼ ሳልሆን፤
ኢትዮጵያዬ በልጆችሽ አተኩሬ፣
አስበልጨሽና አፍቅሬ፣
የኔን ሕይወት ገብሬ፤
የተሸከምኩሽ የተሸከምሽኝ፣
ኢትዮጵያዬ ሕይወቴ፣
ኧረ ወዴት ሄድሽ እናቴ?
እስኪ ንገሪኝ በሞቴ!
* * * * * * * * * *
ገና በለጋነቴ፤
በአፍላነቴ፣
ኢትዮጵያ ብርሃንሽን ላይ፣
ከጨለማ ወጥተሽ ከስቃይ፤
የአረመኔውን
የደርጋማውን የመንግሥቱ
ኃይለማርያም መንግሥት፣
የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር
ዕብሪት፣
በአሲምባ፣ በጠለምት፣
ባርማጨሆ በጭልጋ በወልቃይት፣
ስፋለምና ስሟገት፤
ሰውነቴ ተበሳስቶ፣
አካሌም ጎድሎ ተመቶ፤
ኢትዮጵያን ያለ ኢትዮጵያዊያን
ማየት አቅቶኝ፤
ዛሬን ሳልይዝ ነገ መግባት
ተስኖኝ፤
እያባነነኝ በየሰዓቱ፣
እንቅልፍ ነሳኝ ጉድለቱ፤
አልችል አለና አቅሌ፣
ተንዘፈዘፈ ሥጋ አካሌ፤
የተሸከምኩሽ የተሸከምሽኝ፣
ኢትዮጵያዬ ሕይወቴ፣
ኧረ ወዴት ሄድሽ እናቴ?
እስኪ ንገሪኝ በሞቴ!
* * * * * * * * * *
አምቄው እንዳይኖር ተሳስቼ፣
ልዘረግፈው ነው አውጥቼ፤
ከፊታችን በተገተረው መስተዋት
ራሳችንን ትናንት
ዛሬና ነገ በሀቅ ማየት ብንችል፣
ምን ብለን እንነግረዋለን
ለኛነታችን በትክክል!
አንቺ ኢትዮጵያ!

አይ ወገኔ!
እንዳትናገር ልሳንህ
በፍርሃት ተወጥሮ፤
በራስህ ሳይሆን
በሌሎች ምኞትና ፍላጎት
እጅ እግርህ ታስሮ፤
አይ ኑሮ!
ቀኑን በሌት
ሌቱን በቀን አሳዶ፣
ፀሐይን በጨረቃ
ጨረቃን በፀሐይ
ሰማይን በምድር
በየተራ ቀዳዶ፤
የመኖርን ትርጉም
የሕይወትን እቶ ፈንቶ!
ቀኑን በሰዓት
ሰዓቱን በደቂቃ
መሥርቶ፣
ዓመቱን በወራት
ቀኑን በሰዓታት
ደርቶ ደራርቶ፤
የኑሮን ዕዳ ተሸክሞ፣
ሰውን የሚያኖር አክሞ፤
እስኪ ንገሩኝ ለኔ
የት ገባ ዛሬ ወገኔ!
አንቺ ኢትዮጵያ!
የተሸከምኩሽ የተሸከምሽኝ፣
አገሬ ውዷ ሕይወቴ፣
ኧረ ወዴት ሄድሽ እናቴ?
እስኪ ንገሪኝ በሞቴ!
* * * * * * * * * *
ሳያከብሩ መከበር የሚፈልጉ፣
የራሳቸውን ትተው
የሰውን ማግኘት የሚጓጉ፤
ሕዝቡን ግራ አጋቡት በየጥጉ።
ጥላቻ አስተምረው
ክፋት ቀልበውን
በጎ ጎኑን ሳናይ፣
ጭካኔ ጋግተው
በደም የሰከርን
አውሬ አደረጉን ወይ!
ቃላት አሉን ወይ
ድርጊት ሥራውን
ይሄን የሰው ግፍ ዘርግፎ፣
ከሰብዓዊነት ውጪ
ካራዊትነትም አልፎ፣
ያጨከነን፣
ያስጨከነን፤
አእምሮ ልባችንን አርጎ ቀፎ፤
ይሄን ዘግናኝ ድርጊታችን
ከልብ ፈንቅሎ ጎልጉሎ፣
መግለጫ ማውጫ ፈልፍሎ፤
አለ ወይ ደርዳሪ ትርክቱን፣
አውጪ ነጋሪ እውነቱን!
ታች አምና ሬሳ ሲጎተት ዘግንኖኝ
የዛሬውን! ያሁኑን! ማየት አቃተኝ።
የሰው አውሬዎች ስንት ናቸው!
ያማራ ሥጋ የጣማቸው!
ጃዋር ሞሐመድ ያሜሪካው፣
የአማራ ሥጋ የቋመጥከው፣
ተጋድሞልሃል ሂድ ብላው።
ያመረተውን ጣጥሮ፣
በሉ አቅርቡለት ዘንድሮ።
በቀለ ገርባ ያውልህ፣
የቋንጣ ክምር አለልህ፣
ሂድና አመንዥክ ይለፍልህ።
በል ሂድ እፈሰው የዘራኸውን፣
ሲታጨድ እየው ምርትህን።
* * * * * * *
ሰውን በገጀራ ስታርዱት፣
ጣፈጣችሁ ወይ ስትበሉት!
ነዘራችሁ ወይ ውስጣችሁ፣
ሬሳ ስታርዱ ውሏችሁ!
አንቺ ኢትዮጵያ!
የተሸከምኩሽ የተሸከምሽኝ፣
አገሬ ውዷ ሕይወቴ፣
ኧረ ወዴት ሄድሽ እናቴ?
እስኪ ንገሪኝ በሞቴ!
* * * * * * * * * *
ማነው ሚጠየቅ ለዚህ ሁሉ!
ቁንጮውን ወዴት ነው ጥቅሉ፣
ሰዎች ተነሱ አንድ በሉ።
ስቃይሽ በዝቶ ስታፈጪ፣
ዙሪያውን ከቦሽ ስታምጪ፤
ተሰባስቦ ጎጆ ሠሪው፣
የዋህ ወገኔ በየቦታው፤
ምን ነካኝ አለ በየወንዙ፣
ሲጣል ሬሳ ሲጠፋ ደብዙ!
ኧረ ወዴት ሄድሽ!
ኧረ የት ገባሽ!
አዝለው ወሰዱሽ ባንቀልባ፣
አልቆምም አለ የኔ እንባ፤
ልቤ ሳሳልሽ እናታለም፣
በይ ካንቺ በፊት እኔ ልቅደም!
እንዲህ ከጨከንሽ አገሬ፣
የት ትምራኝ ይሆን ይቺ እግሬ!
አንቺ ኢትዮጵያ!
የተሸከምኩሽ የተሸከምሽኝ፣
አገሬ ውዷ ሕይወቴ፣
ኧረ ወዴት ሄድሽ እናቴ”
እስኪ ንገሪኝ በሞቴ!
* * * * * * * * * *

እናንት ያማራ ሹማምንት፣
የባሕርዳሩ ባለቤት፤
ግፍና ሲቃ ሰቆቃው፣
የሚመዘን የሚለካው፣
ይሄ ሁሉ ዕዳ በጃችሁ ነው!
የአማራ ሹሞች ነን ብላችሁ፣
ኃላፊነቱን ይዛችሁ፣
ባሕርዳር በክብር በድሎት
ተቀናጣችሁ ያላችሁ፤
የጥፋቱን ልክ ታውቃላችሁ!
ሂሳብ ግምቱን ትረዳላችሁ!
ከዚህ ሁሉ ስቃይ ሰቆቃ
ስንት ነው የናንት ድርሻችሁ?
ድርሻችሁ ስንት ነው
እንስማው ንገሩን፣
ከጥፋቱ በላይ
መፎከራችሁን።
እጅ አግር አጣጥፎ
መቀመጡንማ!
ጆሮውን ቆልምሞ
መጠቅለሉንማ!
ዘንዶም ያውቅበታል
ሆዱ ከሞላማ!
እሰረው ግረፈው
ስቀለው ማለቱን፣
ከደርግ የወረስነው
አረመኔነቱን፣
መቼ ይሆን ጨክነን
የምንጥል አርቀን!
ከኛ ተወግዶ
ርቆ እንዲርቀን።
አንቺ ኢትዮጵያ!
የተሸከምኩሽ የተሸከምሽኝ፣
አገሬ ውዷ ሕይወቴ፣
ኧረ ወዴት ሄድሽ እናቴ?
እስኪ ንገሪኝ በሞቴ!
* * * * * * * * * *

ዓይኖቼ ወደ ኋላ እየዞሩ
ልቤ ተንጠልጥሎ
ሩቅ እየዘመተ፣
ዛሬን በትናንት ለውጦ
ከተጨባጩ ይልቅ የሚመኘውን ሽቶ
በትዝታ እየሞተ፤
ሐዘን ባንገት ላይ
ሊሰነቀር እንደተቃጣ
ስለት እያስጨነቀ፣
የማይጨበጥ ራዕይ
በተስፋ ሠጥቶ
እየጨመቀ፤
አገሬ ኢትዮጵያ
ደንብና ወገኔ፣
አጥቼሻለሁ ፈልጌ፣
ወዲህ ና በሉኝ ያያችሁ፣
ባለሁበት በሩቅ
እንዳልቀር ጠውልጌ፤
እውነት አለሽ ወይ ኢትዮጵያ!
የት ነው የሄደች ኢትዮጵያ!
የት ሄደች የኔ ኢትዮጵያ!
* * * * * * * * * *
ከዚያ ብኖር ኖሮ፣
ያ ባይሆን ኖሮ፤
በሚል የሕልምና
የቅዠት ምኞት፣
በጨለማው መሓል
ክንፌን እያራገብኩ
ስሄድ ፊት ለፊት፤
ትናንት ዛሬ ነገ
ባንድ ላይ ተጨምቀው
የጊዜ ትርጉሙን አጥቼ፣
የጨለማ ጉዞ
ጭፍንነት
በድንግርግሩ ተሞልቼ፤
መኖር ወይንም መሞት ምርጫው
ከፊታችን ሲደፋ፣
የትኛውን እንመርጣለን
የግድ መምረጥ ኖሮብን
ፅዋችን መሮ ሲከፋ!
በዱር እንደተበተነ አፈር
መኖር አለመኖሬ
የክምር ሰበዝ ሲሆን፣
ነበርኩ የምልበት
ቅሬት ዕሴት ሳላዘግን፤
ሲጨልም፣
ሲጭለመለም፤
ሕፃናትና አዛውንት፣
ጎልማሳና አሮጊት፤
ያለ ርሕራሄና ያለ ፍርድ፣
እንደ እንሰሳ ስንታረድ፤
አንቺ ኢትዮጵያ!
የተሸከምኩሽ የተሸከምሽኝ፣
አገሬ ውዷ ሕይወቴ፣
ኧረ ወዴት ሄድሽ እናቴ?
እስኪ ንገሪኝ በሞቴ!
* * * * * * * * * *
ሙስና ቤቱን ሠርቶ፣
መተዛዘኑ ጥሎን ጠፍቶ፣
የኔ እበልጥ እኔ እበልጥ
ፉክክር ደርቶ፣
ከሰብዓዊነት ይልቅ
ብር መቋጠር በርትቶ፤
መተሳሰብ በመረጋገጥ
የኛ በኔነት፣
አብሮ መኖር
በኔ ድሎት፤
ማስተዳደር
ራስን በመጥቀም
ተተክቶ፤
አይ! እቶ ፈንቶ!!!
* * * * * * * * * *
አንቺ ኢትዮጵያ!
የተሸከምኩሽ የተሸከምሽኝ፣
አገሬ ውዷ ሕይወቴ፣
ኧረ ወዴት ሄድሽ እናቴ
እስኪ ንገሪኝ በሞቴ!
አንዱ ዓለም ተፈራ
ሰኒቬል፣ ካሊፎርንያ
ጥር ፩ ቀን ፳ ፻ ፲ ፭ ዓ ም

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

ከነፃነት ዘገዬ የአራት ኪሎው ኦነግ ሸኔ ከቁጥር ጋር እንደተጣላ ዕድሜውን አገባደደ፡፡ ኦነግ/ኦህዲድ ዛሬም ሆነ ዱሮ፣ በቤተ መንግሥትም ይሁን በጫካ ቁጥር ላይ ያለው አቋም ምን ጊዜም ያስደንቀኛል፡፡ ደግሞም እየባሰባቸው እንጂ ሲቀንሱ አይታዩም፡፡ ጥቂት

80 ቢሊዮን ብር ስንት ብር ነው?

በላይነህ አባተ ([email protected]) መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ምዕራባውያን የኢትዮጵያን ልጆች እያታለሉና እየደለሉ ከእምነታቸው ለመንጠቅ ሲቃጡ በ1951 ዓ ም ባሳተሙት ‘መድሎተ አሚን ወይም የሃማኖት ሚዛን ጥልቅ መጽሐፍ ሽፋን ላይ ሕዝብ ልቡናውን፣ ዓይኑን፣ ጀሮውንና

ሰው ሆይ!

“በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ።”  መዝሙረ ዳዊት 39:1 ወንድሙ መኰንን፣ ኢንግላንድ 15 January 2025 መግቢያ የአገር መሪ፣ በስሜታዊነት እንዳመጣለት አይዘረግፍም። እያንዳንዷ ንግግሩ እየተሰነጠቀች ትታይበታለች። ንግግሩ ቁጥብ መሆን

ከተዘራ ያልታረመ አንደበት የጠቅላይ ሚኒስትር አነጋጋሪ ንግግሮች

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

Go toTop